136 .ሳሙኤል በቀለ ዜና-samuel bekele zena


 

ሳሙኤል በቀለ ዜና፣ በታህሳስ 2014 ወደ ሀገር ቤት ከገቡ ትውልደ ኢትዮጵያውያን አንዱ ነው፡፡ 1983 .  ጀምሮ  መኖሪያውን በሲያትል ዋሽንግተን ያደረገ ሲሆን፣ በአሁኑ ሰአት በአውቶሞቲቭ በተለይም፣ የውድድር መኪኖች አካሚ ወይም መሀንዲስ ሆኖ እየሰራ ይገኛል፡፡  አቶ ሳሙኤል ለእናት ሀገሩ ትልቅ ፍቅር ያለውና አንድ ነገር ሰርቼ ሀገሬን ማስጠራት አለብኝ ብሎ የሚያምን ሀገር ወዳድ ነው፡፡  ጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አህመድ አህመድ ይፋ ያደረጓቸው ከአጼ ሀይለስላሴ  ዘመን ጀምሮ ስራ ላይ ይውሉ የነበሩ ጥንታዊ የቤተ መንግስት መኪናዎችን በነጻ ለመጠገን ፕሮፖዛል ያስገባው ሳሙኤል በቅርቡ ይህ ሀሳቡ ተሳክቶ እውን እንደሚሆን ተስፋ ያደርጋል፡፡    ወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በባህር ማዶ እየኖሩ ነገር ግን ሀገራቸውን ያልረሱ በልዩ ልዩ ሙያ ላይ ያሉ ሰዎችን ግለ-ታሪክ ለትውልድ እያስቀመጠ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከእነዚህ ታሪካቸው በዚህ ድረገጽ ላይ እንዲሰራ ከመረጥናቸው ባለሙያዎች መካከል አቶ ሳሙኤል ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ አቶ ሳሙኤል ማነው ለሚለው እነሆ ታነቡ ዘንድ ጋበዝናችሁ፡፡https://tewedajehistory.blogspot.com/2022/01/samuel-bekele-zena-2014-1983.html

 

 

 




        ትውልድና ትምህርት


አቶ ሳሙኤል በአዲስ አበባ ልዩ ስሙ መሹለኪያ በሚባለው ስፍራ ተወለደ፡፡የመጀመሪያ ደረጃ  ትምህርቱን በፈለገ ዮርዳኖስ ተማሪ ቤት የተከታተለ ሲሆን በመቀጠልም  የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱንም በሽመልስ ሀብቴ ትምህርት ቤት ሊከታተል ችሏል፡፡  በሽመልስ ሀብቴ  የቴክኒክና ሙያ ተማሪ  ነበር፡፡ እዛም ኤሌክትሪል እንዲሁም የእንጨት ስራ / ውድ ወርክ/ ይማር ነበር፡፡ አቶ ሳሙኤል እንዲህ አይነት ሙያ ከበፊትም አንስቶ ይስበው ስለነበር በፍላጎት ትምህርቱን ይከታተል ነበር፡፡ 2 ደረጃ ትምህርቱን እንደተቀላቀለ የኢትዮጵያ አየር ሀይል  የግራውንድ ስኩል ትምህርቱን ተከታተለ፡፡ከዚያም 2 አመት የግራውንድ ስኩል ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ ለስራ ድሬደዋ ተመደበ፡ ፡እዛም የኤሮስፔስ  እቃዎች  ልዩ ስፔሻሊስት በመሆን መስራቱን ቀጠለ፡፡


 

 

      የፈለገ ዮርዳኖስ ትዝታ 

 ሳሙኤል፣ ፈለገ ዮርዳኖስ በሚማርበት ጊዜ በርካታ መልካም ትዝታዎች አሉት፡፡ በተለይ ደግሞ ይህ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን ብቁ በማድረግ በኩል የራሱን ጉልህ ድርሻ የተወጣ መሆኑን ይናገራል፡፡ፈለገ ዮርዳኖስ በየጊዜው የተማሪዎች ውድድር በማድረግ የሚታወቅ  በዚህም ተማሪዎች በእጅ ጽሁፍ እንዲሁም በቋንቋ ብቁ እንዲሆኑ የሚያደርግ ተማሪ ቤት ነው፡፡ሳሙኤል በየዞኑ ይህ አይነቱ ውድድር መደረግ መቻሉ ተማሪውን ጎበዝ እንዲሆን አስችሎታል ብሎ ያምናል፡፡  በወቅቱ ማለትም በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ የፈለገ ዮርዳኖስ ተማሪዎች በሚኒስትሪ ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ እውቅና የተቸራቸው ነበሩ፡፡

 

     ሳሙኤል በአየር ሀይል 



በአየር ሀይል ቆይታ ባደረገበት ጊዜ   በተለይ በአሁኑ ጊዜ ዘመናዊ  በኤሌክትሪክ የሚሰሩ መኪናዎች የሚጠቀሙበትን ቴክኖሎጂ  ይጠቀም የነበረ የአውሮፕላን ማስነሻ ላይ አንድ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ ይህንንም ቴክኖሎጂ ከእንግሊዝ ሀገር እንዲመጣ በማድረግ በተለይ ኤሌክትሪክ በመጠቀም መስራት የሚቻልበትን ስልት ከነደፉ ኢትዮጵያውያን አንዱ ሳሙኤል በቀለ ነበር፡፡ ሳሙኤል ስለዚህ አስተዋጽኦው ሲያስብ ትልቅ ኩራት ይሰማዋል፡፡ ይህ ቴክኒሎጂ ከፍተኛ የሆነውን የጋዝ ወጪ የሚቀንስ ሲሆን በተለይ ደግሞ ይህ ለአየር ሀይሉ ትልቅ ጥቅም የሰጠ ነበር፡፡

 

አየር ሀይል ሳለ ብዙ ትምህርት እንደቀሰመ  ሳሙኤል ይናገራል፡፡ ሳሙኤል፣ አሁን ላለበት ሙያ በተለይም በኤሌክትሪክ ስለሚሰሩ መኪኖች  የመጀመሪያውን  እውቀት የቀሰመው ከአየር ሀይል  በመሆኑ አየር ሀይልን ትልቁ የእውቀት ቤቴ ሲል ይገልጸዋል፡፡

 

ሳሙኤል ወደ ባህር ማዶ የማቅናት ሀሳቡ የመጣለት በ1983 ግድም ነበር፡፡ በጊዜው በነበረው የፖለቲካ አለመረጋጋት ሳቢያ በኬንያ በኩል አድርጎ ወደ አሜሪካ ገባ፡፡ ኑሮውንም በዋሽንግተን ሲያትል በማድረግ ከወይዘሮ እመቤት ማሞ ጋር ትዳር በመመስረት 2ልጆችን ናቲና ሜላትን በማፍራት ለከፍተኛ ትምህርት አብቅቷል፡፡








 

            አሜሪካ የመግባቱ ነገር

 

ሳሙኤል ወደ ባህር ማዶ ለማቅናት ሀሳብ ሲያደርግ በዋናነት ውጭ ሀገር ጥሩ የትምህርት እድል እንደሚያገኝ ስላወቀ ነበር፡፡  አባቱ አቶ በቀለ ዜና ግን ሀገር ቤት እንዲኖር ይፈልጋሉ፡፡ ሳሙኤል አንዴ ልቡ ቆርጦ ስለነበር  ወደ ባህር ማዶ ለማቅናት ልቡ ተነሳሳ፡፡በአንድ በኩል ደግሞ ፍቅረኛው ቀደም ብላ አሜሪካ ያቀናች በመሆኑ ሳሙኤል ቶሎ መብረሩን ፈልጎታል፡፡


ጊዜው 1981 ግድም ነበር፡፡ ሳሙኤል ከሀገር ቤት ለመውጣት የተነሳሳበት አመት፡፡ አባቱ አቶ በቀለ ዜና የልጃቸውን ወደ አሜሪካ መሄድ የሰሙት ሊበር አንድ ሰአት በቀረው ጊዜ ነበር፡፡ መጀመሪያ የተጓዘው  በኬንያ ነበር፡፡


‹‹…. አባ በቃ ልሄድ ነው ባህር ማዶ ›› አለ ሳሙኤል

 አባት አቶ በቀለ ዜና ተደናገጡ፡፡ማመንም ተሳናቸው፡፡ቆም ብለው ሳሙኤልን አዩት፡፡ ደህና ሁን ካሉት በኋላም ዳግም ተመልሰው መጡ፡፡ ይቅናህ ብለው ሸኙት፡፡

 ሳሙኤል 200 ብር ከሚያገኝበት የአየር ሀይል ስራ ወደ ባህር ማዶ ሲያቀና ነገሮች በጎ ሊሆኑለት እንደሚችል ያስብ ነበር፡፡ኬንያ እንደደደረሰ ቤት ተከራይቶ መኖር ጀመረ፡፡ የተለያዩ መኪኖችን በመጠገን  ዲቪዲ ማጫወቻዎች ፈትቶ የመስራት ተግባራትን ያከናውን ነበር፡፡ የኬንያ ቆይታው ከ6 ወር የዘለለ አልነበረም፡፡

 





          ትዳር መያዝ -ቤተሰብ መመስረት



 ሳሙኤል ወዲያው በ1982 ግድም በፈረንጆች በ1991 ግድም ዋሽንግተን ሲያትል ገባ፡፡ ከዚያም ትምህርት ቤት ገባ፡፡ ዲግሪውንም ያዘ፡፡ የባለቤቱ የወይዘሮ እመቤት ማሞ  ቀድሞ ወደ አሜሪካ መሄድ እንደጠቀመው ሳሙኤል ይናገራል፡፡ በ1994 የመጀመሪያው ልጃቸው ናቲ ተወለደ፡፡ ከዚያም ሜላት ተወለደች፡፡

 ናቲ የምህንድስና 2ኛ አመት ተማሪ ሲሆን የ18አመቷ  ሜላት ደግሞ የአለም አቀፍ ግንኙነት ተማሪ ነች፡፡ ሁለቱም ልጆች ወደፊት ሀገራቸውን በብዙ መልኩ ለመርዳት የተነሳሱ ናቸው፡፡ እናታቸውም ብትሆን በጠንካራነቷ የተመሰከረላት ናት፡፡ የሳሙኤል ሁለቱንም ልጆች ነጻ የትምህርት እድል አግኝተው የሚማሩት በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ዋሽንግተን ሲሆን ይህም ሳሙኤልን ትልቅ ርካታ ይሰጠዋል፡፡ ልጆቹ ለዚህ ከፍተኛ ውጤት ሊበቁ የቻሉት በአንድ በኩል በወላጆች የቀን ተሌት ጥረት ሲሆን በሌላ ደግሞ በስነ-ምግባር የታነጸው የካቶሊክ ተማሪ ቤት የተማሩ በመሆናቸው ለትምህርታቸው ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጡ ችለዋል፡፡ ሳሙኤል እንደሚያምነው ልጆች ፈሪሀ እግዚአብሄር አድሮባቸው ሲማሩ ጥሩ ነው ሲል በልጆቹ ላይ ለውጥ ሊከሰት የቻለው ከተማሪ  ቤቱ መሆኑን ያምናል፡፡



        ስፔሻሊስቱ ሳሙኤል 


ሳሙኤል ከመጀመሪያው ጀምሮ ለመኪና ጥገና ፍቅር ያሳደረ በመሆኑ በዚህ ሙያ ላይ የመሰማራት  ፍላጎት ነበረው፡፡ እናም የጥገና ማእከል ከፍቶ መስራት ጀመረ፡፡ ለ10 አመታትም የራሱን ስራ በመስራት የሙያ ፍቅሩን ተወጣ፡፡ከዚያ ደግሞ ሌላ ኩባንያ ተቀጠረ፡፡ ዳግም ደግሞ ለ6 አመት የራሱን የጥገና ማእከል ከፈተ፡፡ሳሙኤል የኪያ መኪና ከሚሰራው ኪያ ኩባንያ ጋር በጣም የጠበቀ ግንኙነት አለው፡፡ በኪያ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ከመከታተሉ ባሻገር  እውቅና ያገኘባቸው ወይም በሙያው ሰርቲፋይ የሆነባቸው መረጃዎች አሉት፡፡ ይህም የበለጠ አቅሙን አጎልብቶ እንዲያወጣ ያስቻለው ጉዳይ ነበር፡፡


    ሳሙኤል የአልፋሮሚዮ ስፔሻሊስት 


 ሳሙኤል፣ በአንድ ወቅት የአልፋ ሮሚዮ መኪና ስፔሻሊስትም ነበር፡፡ አልፋ ሮሚዮ  የጣሊያን መኪና ሲሆን ሳሙኤል አልፋ ሮሚዮ ስፔሻሊስት የሚል የጥገና ማእከል በአትላንታ  ነበረው፡፡ ሳሙኤል በአሁኑ ሰአትም በሲያትል ከሚገኙ የአልፋሮሚዮ ስፔሻሊስቶች  ምናልባት በጣት ከሚቆጠሩት አንዱ ነው፡፡ የአልፋ ሮሚዮ ስፔሻሊስቶች ቢኖሩ እንኳን ጡረታ የወጡ ወይም በ80ዎቹ የእድሜ ክልል ያሉ ናቸው፡፡ ታዲያ እዚያ ጋር ኢትዮጵያዊው ሳሙኤል ተፈላጊ ሆኖ መገኘቱ ለሁላችንም ኩራት ነው፡፡ ሳሙኤል ስለ አልፋ ሮሚዮ መኪና ሲያነሳ ጣሊያኖችን ያደንቃል፡፡ ‹‹የእውነት ጣሊያኖች መኪናን ደህና አድርገው ያውቃሉ›› ሲልም ይገልጻቸዋል፡፡
















      ሳሙኤልና ባለእውቀት ደንበኞቹ 


የውድድር መኪኖችንም በመጠገን ሳሙኤል ትልቅ ሚና አለው፡፡ ብዙ አይነት የውድድር መኪኖች እንዳሉ ሳሙኤል ይናገራል፡፡ሳሙኤል ከመኪና ጋር በተገናኘ የሜካኒካልና የኤሌክትሪካል ስራዎችን ያከናውናል፡፡  ይህም ትልቅ ርካታ የሚሰጠው ስራ ነው፡፡ ሳሙኤል ይህ የመኪና አካሚነት ሙያ በአሜሪካ ትልቅ ከበሬታን እንዳስገኘለት ይናገራል፡፡ ከኒዮርክ ድረስ መኪና ለማስጠገን የሚመጡ ደንበኞች ነበሩት፡፡ ሳሙኤል እንደሚናገረው ብዙዎቹ ደንበኞቹ ስለ መኪና በቂ እውቀት የቃረሙ ሲሆኑ በዚህም ከደንበኞቹ ብዙ መማሩን ይናገራል፡፡ ብዙዎቹ ደንበኞቹ ፈረንጆች ናቸው፡፡


 ሳሙኤል አሁን የሚሰራበት የመኪና ስፔሻሊቲ ማእከል የበርካታ እውቀት ያላቸው ሰዎች ስብስብ ነው፡፡ ዋናው መስራቹ ቦይንግ ላይ በከፍተኛ ሃላፊነት የሚሰራ ነው፡፡  ሁለተኛው ባለሙያ ደግሞ አቬኒክስ አውሮፕላን  ላይ በጥገና የሚሰራ ሰው ነው፡፡ ታዲያ ሳሙኤል ከእነዚህ ጥልቅ እውቀት ካካበቱ ኢንጂነሮች ጋር እየዋለ በርካታ እውቀት መቅሰም መቻሉን ይናገራል፡፡

ሳሙኤል የአሜሪካን ሀገር ቆይታው ወደ 16 አመት ሲሞላ ማለትም በእኛ አቆጣጠር በ1999 በፈንጆች ደግሞ  በ2007 ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ የራሱን የአውቶሞቲቭ ማሰልጠኛ ለመክፈት በርካታ መሰናዶ አድርጎ ነበር፡፡ ነገር ግን በጊዜው ይህንን ስራ ለመስራት አመቺ ሁኔታ ባለመኖሩ ለስራው የገዛቸውን እቃዎች ይዞ ወደ አሜሪካ መመለሱን ይናገራል፡፡

 

 


ሳሙኤል በአሁኑ ሰአት ፕሮቫ ሞተርስ ስፖርት በሚባል ድርጅት በተለይ በዋጋቸው እጅግ ውድ የሆኑ የውድድር መኪኖችን በመጠገን ፤ በመገንባት እና አዲስ ቴክኖሎጂን በማላበስ ስራ ላይ ተሰማርቼ እገኛለሁ ይላል፡፡ እንደዚሁም እነዚህ ውድ የሆኑና እንደ ቅርስ የሚቆጠሩ የውድድር መኪኖች  የቀድሞ ይዞታቸው ሳይቀየር ጥገና እንዲደረግላቸው አቶ ሳሙኤል ትልቁን ድርሻ ይወጣል፡፡

 

ከዚህ ጋር በተያያዘ ሳሙኤል አንድ ጉዳይን አብሮ መግለጽ ይፈልጋል፡፡ በአዲስ አበባ ቤተ-መንግስት የሚገኙትን ብዙ ዋጋ ያላቸውን የቅርስ መኪናዎች በነጻ ለመጠገን ወስኗል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ይህ ጥያቄ ቀርቦለት በቅርቡ ይህን አገልግሎት ለመስጠት ራሱን አዘጋጅቷል፡፡  ሁኔታዎች ተመቻችተው መኪናዎቹ የሚጠገኑ ከሆነ ለሀገሪቱ ትልቅ የቱሪዝም ዘርፍ ትልቅ ገቢ መገኘቱ አይቀርም ሲል ሳሙኤል ተስፋው ትልቅ መሆኑን ይናገራል፡፡

 

 ሳሙኤል  በአውቶሞቲቭ ሙያ አንድ ሌላ ትልቅ አስተዋጽኦ ለማድረግ እንደቻለ ይናገራል፡፡ ይህም ስለ አውቶሞቲቭ ሙያ በቂ እውቀት ሊያስቀስም የሚችል ድረ-ገጽ በማዘጋጀት የእውቀት ሽግግር የሚደረግበትን ሁኔታ አመቻችቷል፡፡ ዘመኑ የሚጠይቀውን የትምህርት አሰጣጥ በመጠቀምም ሳሙኤል በዚህ ድረገጽ እውቀት ለማስጨበጥ ራሱን በማዘጋጀት ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ድረ-ገጽ አልቆ አገልግሎት መስጠት በሚችልበት ጊዜ በአውቶሞቲቭ ሙያ ላይ ፍላጎቱ ላላቸው አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ሳሙኤል ይናገራል፡፡

 

ሳሙኤል ኢትዮጵያ ባለፉት 13 ወራት የገጠማት የህልውና ፈተና ቀላል እንዳልሆነ በመገመት ከቀድሞ አየር  ሀይል አባላት ጋር በመሆን የተጎዱ ሰዎችን በመርዳት የበኩሉን አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ በተለይ በአዳማ የተጎዱ የአየር ሀይል አባላትን በመርዳት ወገናዊ አደራውን በአግባቡ የተወጣ ነው፡፡  እነ አቶ ሳሙኤል በመቀጠል የጀግኖች አምባን ለመጎብኘት እቅድ የያዙ ሲሆን ከወገን ጋር አብሮነታቸው እንደሚቀጥልም ተስፋ አድርገዋል፡፡

 

 


 

መዝጊያ፤ ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽንን አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡

 

አቶ ሳሙኤል በባህር ማዶ የሚኖሩ ወይም እዚያው የተወለዱ ልጆች ሀገራቸውን እንዳይረሱ መርሳትም እንደሌለባቸው ይመክራል፡፡ ይህም ትልቁ ሃላፊነት የቤተሰብ መሆኑን ያስረዳል፡፡ ይህች መተኪያ  የሌላት ሀገር በባህር ማዶ የሚኖሩ ዜጎቿን እገዛ እንደምትሻ ሳሙኤል ያምናል፡፡ በቻልነው ሁሉ ከኢትዮጵያ ጎን መሆን አለብን ሲልም ጥሪ ያቀርባል፡፡ በሙያው ሀገሩን ለማገዝ የተነሳው ሳሙኤል ገና ብዙ እንደሚጠበቅበት ይሰማዋል፡፡ ግን ሮም በአንድ ቀን እንዳልተገነባች ሁሉ በሂደት ነገሮች ቀስ እያሉ ሲሰክኑ የኢትዮጵያ ተስፋ ይለመልማል ብሎ ተስፋ አድርጓል፡፡ ይህ ተስፋው የእውነትም እንዲሆን ይመኛል፡፡ እንደ ሳሙኤል አይነት ኖሮአቸውን በባህር ማዶ አድርገው ለሀገር አንድ ሚና ለማበርከት የሚታትሩ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ እንዲህ አይነት ሰዎች ለእኛ የዘመኑ ጀግና ናቸው፡፡ ዛሬ የሚያኖሩት አሻራ ነገ ከታሪክ መዝገብ ላይ መስፈሩ ስለማይቀር  አሁን ግለ-ታሪካቸው ቢጻፍ ለነገ መነሻ ይሆናል፡፡ ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የኢትዮጵያውንን ታሪክ ሲሰንድ የሰሩት ነገር ጎልቶ እንዲወጣ ይፈልጋል፡፡ አቶ ሳሙኤልም ከዚህ አንጻር ምን እያበረከተ ነው ለምትሉ ይህን አጭር ግለ-ታሪክ በማንበብ ማንነቱንመረዳት ትችላላችሁ፡፡ አቶ ሳሙኤል ካለው የተጣበበ ጊዜ አንጻር ይህን ግለ-ታሪክ ለመስጠት ፈቃደኛ ስለሆነ ልናመሰግነው እንወዳለን፡፡/ ይህ ግለ-ታሪክ በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ ተጽፎ በተወዳጅ ሚድያ የፌስቡክና በዚህ ድረ-ገጽ ላይ ሊወጣ ቻለ፡፡ ይህ ግለ-ታሪክ ዛሬ እሁድ ጥር 15 2014 ከሌሊቱ 6 ሰአት ከ 41 የተጫነ ሲሆን አስፈላጊው ማሻሻያ እየተደረገበትም በየጊዜው እንዲወጣ ይደረጋል፡፡

 

    https://tewedajehistory.blogspot.com/2022/01/blog-post_22.html

 

   https://www.automechtraining.com/

    https://youtu.be/TPDa3OFGLXA  ጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አህመድ አህመድ ይፋ ያደረጓቸው ከአጼ ሀይለስላሴ  ዘመን ጀምሮ ስራ ላይ ይውሉ የነበሩ ጥንታዊ የቤተ መንግስት መኪናዎች




 

 

 


አስተያየቶች

  1. ሳሚ ያሰብከው እንዲሳካ ከልብ እመኛለሁ ። ኢትዮጵያ እንዳንተ በመሳሰሉ ልጆችዋ ዳግም ትነሳለች !

    ምላሽ ይስጡሰርዝ
  2. ሳሚ ያሰብከው ተሳክቶ ኢትዮጵያንም አንተም የጀርባ አጥንቴ የሖነው ያልከውን የኢትዮጵያ አየር ኃይል ኮሌጅንም አንተንም በመልካም ታስነሳ ዘንድ ጥረትህ በእግዚአብሔር ይባረክ ላግዝህ የምትፈልገው ነገር ካለ ግን አብሬህ እንዳለሁ እንድታውቀው በታላቅ ከበሬታ

    ምላሽ ይስጡሰርዝ

አስተያየት ይለጥፉ

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች