134. አቶ ሀይሉ ገብረማሪያም - ATO HAILU GEBREMARIM



ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ለሀገራቸው ሳይሰስቱ የሰጡ፤ ለእኔ ሳይሉ ለእናት ሀገሬ  ብለው አስደናቂ አሻራ ያኖሩ ሰዎችን ግለ-ታሪክ በዚህ የኢትዮጵያዊያን ታሪክ በሚዘከርበት ድረ-ገጽ ላይ ያኖራል፡፡ አሁን የምንዘክራቸው ሰው በአሁኑ ሰአት የ87 አመት ሰው የሆኑት አቶ ሀይሉ ገብረማሪያም ናቸው፡፡ እርሳቸውም በምህንድስና ዘርፍ ሃላፊነታቸውን የተወጡ ታላቅ ባለውለታ በሚለው ዘርፋችን ውስጥ አስተዋጽኦዋቸው በዝርዝር ይቀርባል፡፡ 

ይህ ታሪክ በሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ታሪክ ትልቁን ድርሻ የሚይዙትን የሀይሉ ገ/ማርያም ህይወት እና ስራ ያካተተ  ፅሁፍ ነው፡፡የአቶ ሀይሉ ገብረማርያምን የሰማንያ ስድስት ዓመት ጉዞን እና በዚሁ ድርጅት  ደግሞ ለሀምሳ አምስት አመታት በመታተር መስራቸውን ያሳያል፡፡

 አቶ ሀይሉ ፣ሲቪል ኢቪዬሽንን ድሮ እና ዘንድሮን የምናይባቸውም ታላቅ ሰውም ናቸው፡፡

ሕይወታቸው መማሪያ፣ማወቂያ እና ነገን መመልከቻም ይሆናል፡፡በዚህ የግለ-ታሪክ ጽሁፍ  የልጅነታቸውን፣የትምህርታቸውን፣የስራ እና ሕይወታቸውን ጊዜያቸውን በጥቂቱ ለመዳሰስ ተሞክሯል፡፡

አንብቦ ለማሰብ አስቦ ለመመራመር ዕውቀትን ከትላንት ጨልፎ ለነገ ለማሻገርም የሕይወት መርሀቸውን በማወቅ ወደ ነገ እንሻገር፡፡

 

 

            




                            

           ልጅነት፣ትምህርት እና የስራ ጅማሮ

አቶ ሀይሉ ገ/ማርያም ትውልዳቸው በትግራይ ክፍለ ሐገር አድዋ አውራጃ በቀድሞ አጠራር ማይምሻም ተብላ በምትጠራ ቦታ ነው፡፡ ወደ እዚህች ምድር በወርሃ ሚያዝያ አስራ ዘጠኝ መቶ ሀያ አምስት ተቀላቅለዋል፡፡

ገና በሦስተኛ ወር ጨቅላነት ጊዜያቸው ከተለዩዋቸውን እናታቸው ወይዘሮ ለምለም እንግዳ እና ከአባታቸው መምህር ገ/ማርየም ንጉሴ ነበር የተወለዱት፡፡

አባታቸው የቤተክርስቲያን አገልጋይ የነበሩ ሲሆን  አይተ ጎይታይም ተብለው በማህረሰቡ ዘንድ የሚጠሩ  እና የሚከበሩ የነበሩ ቢሆንም አቶ ሀይሉ ግን ያደጉት ከታላቅ እህታቸው ጋር ነበር፡፡

ባደጉበት አካባቢ አለቃ ተወልደ መድህን ሀይሉ የተባሉ (የታዋቂው ደራሲ የስብሃት ገ/እግዚአብሄር አያት የነበሩ) ታዋቂ ምሁር ነበሩ፤ታዲያ ልጅ  ሀይሉም በወቅቱ ሀሁ የተማሩትም  የማይረሳ ትዝታን ያሳለፉት የመጀመሪያው የዕውቀት ገበታቸው በዚህም የማስተማር ብቃታቸው የታወቁ ሰው ዘንዳ ነበር፡፡በተጨማሪ ግን አባታቸው ያገለግሉበት ከነበረው ከጉስቋም ማርያም የቤተ ክርስቲያንንም ትምህርት በሌሊቱ መርሃ ግብር ቀስመዋል፡፡

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በንግስተ ሳባ ትምህርት ቤት ተምረዋል፡፡የዚህ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር የነበሩት የእህታቸው ባለቤት የነበሩት ብላታ ገብሩ ተ/ሃይማኖት ነበሩ፡፡ለአቶ ሀይሉም  እንደ አባትም የቅርብም ነበሩ፡፡ እሳቸውም እንደ ልጅ ብሎም እንደ ተማሪም ከስራቸው ብዙ ዕውቀትን ገብይተዋል፡፡

በርካታ ተማሪዎች ጥቂት መምህራን የነበሩበት ትምህርት ቤት የሚማሩት ታዳጊው ሀይሉ ሁኔታ እንደ እናት ላሳደጉት ታላቅ እህት ወይዘሮ አወጣሽ ገ/ማርያም አልዋጥ አላቸው፤ነገን በማሳብ የተሻለ ትምህርት ይገኝታል ወደ ሚባለው አዲስ አበባ ለመላክ ቢያስቡም ወዳጅ ዘመድ ሁሉ እንዴት ካንቺ ተለይቶ ቢላቸውም የወንድማቸው ታላቅ የመሆን የወደፊት ህይወትን በማሳብ በር ከፋች ሆኑ፡፡

ጉዞ ወደ አዲስ አበባ ሆነ፤ታላቅ ሀላፊነት ከተጣለባቸው ብላታ ገብሩ ተ/ሃይማኖት ጋር ከረዥም ጉዞ በሁዋላ ደርሰው ትምህርታቸውንም ጥሩ ከሚባለው የተፈሪ መኮንን አዳሪ ትምህርት ቤት ሊያስገቡ ቢያስቡም ጉዞውን በመዘግየታቸው ሳይሳካ ቀረ፡፡

ዕውቀት ውሀ ለሆነላቸው አቶ ሀይሉ የአድዋ የትምህርት ቆይታን የልጅነት ጓደኛቸው አቶ ግርማይ ተ/ሃይማኖት ሰባ ዓመታት ተጉዘው የህፃንነት ጉዞን ሲያስታውሱ ‹‹አቶ ሀይሉ በልጅነት አማርኛን ግዕዝን የሚያቀላጥፉ ጎበዝ ነበሩ፤ታዛዥ እና ተግባቢ የታዘዙትን ፈፃሚ፣የታላላቆች ፣ምርቃት ተቀባይ ነበሩ፡፡›› ሲሉ ይመሰክሩላቸዋል፡፡

ከአድዋ  ተጉዘው ዕውቀትን ፍለጋ አዲስ አበባን የረገጡት አቶ ሀይሉ የስውዲሽ የሚሽን ትምህርት ቤትን በአስራ ዘጠኝ መቶ አርባ በአራተኛ ክፍል ቢቀላቀሉም ያላቸውን የትምህርት መቀበል ፍጥነት የተመለከቱት መምህራን ወደ አምስተኛ ክፍል አሸጋገሯቸው፡፡

በወቅቱ የስድስተኛ ክፍል ጓደኞቻቸው ደግሞ ፈተና በሚፈተኑበት ጊዜ ይዘዋቸው በመሄቸው ተቀላቅለው  አብረው ፈተኛውን ይወስዳሉ፤ቀድሞውኑ የዕውቀት ቀንድ ነበሩ እና ከሌሎቹ በመብለጥ ካልደረሱበት ክፍል ፈተኛውን በቀዳሚነት አለፉ፡፡

ይህንን ፈተና ላለፉ የሁለተኛ ደረጃ መግቢያ ፈተና መዘጋጃ ጊዜ ሆነ፤ፈተናውንም የተሰጠው የአሁኑ ኮተቤ ሜትሮፖሊታን  የቀድሞ ቀዳማዊ ኃ/ስላሴ ትምህርት ቤት ነበር ፤ፈተናው ከወሰዱ በሁዋላ ግን በክረምቱ መሄጃ ስላልነበራቸው ኮተቤ ሰባተኛ ክፍልን ዘለው ስምተኛ ክፍልን መማር ጀመሩ፡፡በዚህ የቀጠሉት አቶ ኃይሉ የትምህርት ደረጃቸውን አሳድገዋል፡፡

በቀዳማዊ ኃ/ስላሴ ትምህርት ቤትም ፈተናው ቢከብድም አልፈው የዕውቀት ፈለጋቸውን ቀጥለዋል፡፡አስራ አንደኛ ክፍልን እንዳለፉ የቴክኒካል አቪዬሽን ኮሌጅ በዩናይትድ ኔሽን ተቋቁሟል ተብሎ በፊዝክስ ፣በሂሳብ ጥሩ የሆኑ አስራ ሁለት ተማሪዎች ተመርጠው ተወሰዱ፤ከተመረጡት ውስጥ እሳቸው አንዱ ነበሩ፡፡

የአቶ ሀይሉ ገብረማርያም የአቪየሽን ጉዞ በ1945 ተጀመረ፡፡

ለአቶ ኃይሉ ቴክኖሎጂ ትልቅ ፍላጎት ብርቱ ዝንባሌያቸው የሚታይበት መሆን የጀመረው  ከዘጠነኛ ክፍል ጀምሮ ነበር፡፡ በጊዜው በመማሪያ ክፍላቸው ውስጥ በነበረው ትልቅ ሳጥን ላይ በመመራመር የተጀመረ ነው፡፡የዘመኑ ራዲዮ ነበር በዚህ ላይ የዕውቀት መስመራቸውን ለመክፈት በመመሞከር ምርምራቸው ባገኙት ኤሌክትሮ ማግኔቲክ የሚል አዲስ ቃል ላይ በማብሰልሰል ለቴክኖሎጂ ፍላጎት አድሮባቸው ኖሮ የሲቪል አቪዬሽን መቀላቀል የእርሳቸው ወርቃማው ጊዜ ሆነ፡፡በወቅቱ ሰላሳ የኪስ ብርም ይሰጣቸውም ነበር፡፡

አስራ ሁለተኛ ክፍልን እንደጨረሱም ረዳት መምህር በመሆን በአንድ መቶ ሀምሳ ብር በርካታ ዕውቀትን መቅሰም ጀመሩ፡፡ጊዜው ለአቪዬሽን ትልቁን መንገዳቸው በሰፊው ያመላከተም ነበር፡፡በዚህ ወቅት የሲቪል አቪዬሽን ትምህርትንም ተከታትለው ጨረሱ፡፡ጉዞው ግን በዚህ አላበቃም ወደ እንግሊዝ ለተሻለ ትምህርት አመሩ፡፡

በ1946 በእንግሊዝ በተመቻላቸው የነፃ የትምህርት ዕድል ለመከታተል በዛው ቢደርሱም የመጣሀው ለአንድ ዓመት ነው የሚል ሀሳብ ተነሳ ፤ይሄ ግራ ቢሆንም በሁዋላ ግን የተሰጣቸውን ፈተና በማለፍ ከኤምባሲውም ጋር ግንኙነት በማድረግ ከኢትዮጵያ መንግስትም ጨምሮ በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ፈቃድም ጨምሮ ሁለት ነፃ የትምህርት እድልን አገኙ፡፡

በእንግሊዝ ቆይታቸው ታላቅ የኢትዮጵያውነት ፍቅር፣ኩራት እና ክብርም ይሰማቸው ነበር፡፡የሚያገኙዋቸውም በኢትዮጵያዊነታቸው ያከብሯቸውም ጭምር ነበር፡፡በአንድ የታወቀ የቲአትር መድረክ ላይም ከታላቁ ባለቅኔ ፀጋዬ ገ/መድሕን ጋር የመገናኘት እድሉም እንደነበራቸውም ያስታውሳሉ፡፡

በ1950ም በዛው የተማሪዎች ህብረት ተመሰረተ፡፡በዚህም ወቅት የእንግሊዙን ህብረት መስራቾች ውስጥ አንዱ ነበሩ፡፡የኮሚቴውም ፀሀፊ ሆነው አገልግለዋል፡፡ጥሩ ግንኙነት ፣የታቀዱ ስርዓታዊ ውይይቶች የተካሄዱበት እና ትምህርትም የቀሰሙበት ነበር፡፡በወቅቱም ሐገርን ማበልፀግ በኢኮኖሚ፣በፖለቲካው እና በማህበራዊ አስተተሳብ ላይም ሰርተውበታል፡፡

የምህንድስና ትምህርታቸውን ለአራት ዓመታት ተከታትለው ተመልሰዋል፡፡

 በ1954 በሀገራችን የሲቪል የአቪዬሽን ልማታዊ ስራ ውጤታማ ለማድረግ እንቅስቃሴ የተጀመረበት ወቅት ነበር፡፡

እሳቸው የተመለሱበት  ይህ ወቅት የበረራ አየር ማረፊያ የግንባታ ስራ ተጠናቆ የርክክብ ሂደት ላይ ነበር፡፡የድሬዳዋ፣አስመራ እና የጅማ አየር ማረፊያዎች የግንባታ ስራቸውም እየተጠናቀቀ ነበር፡፡

አቶ ሀይሉ በሲቪል አቪዬሽን አስተዳደር በቴክኒካል ክፍል የራዳር እና ናቪጌሽን ግንኙነት ኢንጂነር ሆነው ባገለገሉበት ዘመን በእንግሊዝ የቀሰሙትን ዕውቀት ወደ ተግባር ለመለወጥ ቀን ከሌት እንቅልፍ አልነበራቸውም፡፡እንቅልፌን ምቾቴን ያላሉ ሀገራቸውን ያገለገሉ በስራ ዘርፋቸው ታላቅ ባለውለታም ናቸው፡፡

በመስሪያ ቤቱ የመገናኛ እና ኮሚኒኬሽን ስራው ቀድሞ የተሰራ ቢሆንም ጥቅም ላይ ብዙም ሳይውል የቆየ ነበር፡፡ይህም በአቶ ሀይሉ እና ጓደኞቻቸው አማካይነት ጥቅም ላይ በአግባቡ እንዲውል ተድርጓል፡፡

ለአየር መንገድ ስራ ዋናው የሜዳው ሁኔታ ነው ይላሉ አቶ ኃይሉ፡፡የቦሌ አየር ማረፊያ ደግሞ በወቅቱ የነበረው ሁለት አውሮፕላን ብቻ ነበር ቢሆንም በአሜሪካኖች የተሰራው ሜዳው ችግር መፈጠር ጀመረ እና ማሻሻያ ያስፈልገዋል ተባለ፡፡ይህን እንዲቆጣጠሩ ኃላፊነት የተጣለባቸው ዕውቀትን ከብልሃት የታደሉት አቶ ሀይሉ ነበሩ፡፡

በ1960 አውሮፕላን ለማብረር አሁን ላይ በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ፈቃድ የሚሰጠው በወቅቱ ደግሞ ፈቃዱ የሚገኘው የግድ ኤደን ወይም የመን ከነበረው የእንግሊዝ ቀኝ ገዢ ፈቃድ በማግኘት ነበር፡፡

አቶ ኃይሉም በዚሁ ጉዳይ ኢትዮጵያ በራሷ የአየር ክልል ለምንድነው እሯሳን የማታስተዳረው የሚለውን ለማጥናት ወደ እስራኤል ተላኩ፡፡ ጉዳዩን ሲያጠኑት የመኖች ከአንግሊዝ ነፃ ሊወጡ መሆኑን ይህም ከሆነ ደግሞ ኢትዮጵያ ፈቃዱን ለማግኘት ቁጥጥሩ በግብፅ ስር ሊሆን ነው ተባሉ፡፡እንዴት ያሉት አቶ ሀይሉ እንዴት ይሻላል ሲሉም ባገኙት ምላሽ ፈቃዱን በራሳችሁ ቁጥጥር ስር ለምን አታደርጉትም የሚል ነበር፡፡ለአንድ ሳምንት ባደረጉት ኢትዮጵያ በሯሳ የአየር ክልል እራሷን ማስተዳር እንድትችል በሚያደርገው ስራ ላይ ተምረው ሪፖርት አድርገውም የድርሻቸውን ተወጥተዋ፡፡ይህ ስራቸው የእሳቸው ታታሪነት እንዲሁ አርቆ አሳቢነት ማሳያ አንዱ ነው፡፡

በ1966ም የባህርዳር እና አክሱየም ኤርፖርትን ጨምሮ በርካቶችን ዲዛይን ሲደረጉ ቦታውን የመረጡትም እሳቸው ናቸው፡፡

አቶ ሀይሉ የሲቪል አቪዬሽን መስሪያ ቤት የፕላኒንግ ኮሚሽን በነበሩበት ወቅት አንድ አንድ አዋጅ ይወጣል፡፡አዋጁ አስደንጋጭ ነበር፤በሱዳን የአየርክልል በኩል የኢትዮጵያ አይሮፕላኖች እናዳይልፉ ሆነ አየር መንገዱን እንዳይጠቀሙ የሚል ከፕሬዝዳንቱ የተሰማ አዋጅ ነበር፡፡በርካታ በረራዎች በሱዳን በኩል ይደረጉ የነበሩ ናቸውን እና ሁሉም ተደናገጡ፤በጊዜው የፕላኒንግ ሀላፊ የነበሩት አቶ ሀይሉ ከችግሩ ይልቅ መፍትሄን መሻት ላይ ትኩረታቸውን አደረጉ፡፡በወቅቱ ያለው አማራጭ የኢትዮጵያ አንድ አካል በነበረችው አስመራ አድርጎ ወደ ሳዊዲ አረቢያ በኤር ስፔስ ተጠቅሞ  ሰሜን አፍሪካዊት ወደሆነችው ግብፅ መዳረሻ ማድረግ ነበር፤ይህንን ለማድረግ ደግሞ የሳዊዲ አረቢያ ፈቃደኝነት በእጅጉ ያስፈልጋል፡፡

ሰዎችን መተዋወቅ እና መባባት የሚቻላቸው አቶ ሀይሉ በአንድ ስብሰባ ላይ በሳውዲ አረቢያ የሲቪል አቪዬሽን ከሚሰራ አቻው ጋር ተዋውቀው ነበር እና በዚህ ወቅት ከእርሱ ጋር ያለውን ነገር ሲያስረዱ ወዲያው ጊዜያዊ ፈቃድን አገኙ፡፡አቶ ሀይሉ ለማሳመን ማን ብሏቸው የሚባልላቸው አይነት ሰው ነበሩ እና ተሳካ ፡፡

ጥያቄው ግን ለምን ሱዳን ይህንን አዋጅ ማወጅ ፈለገች ወደ ሚለው ጥያቄው ተቀየረ፡፡

ከመንግስት የመጣው ሃሳብ እናንተም በተመሳሳይ የሱዳንን የአየር ክልል በኢትዮጵያ ዝጉ የሚል ነበር  ይህ የሚሆነው አንዳች የሚያተርፈው ጥቅም ሲኖር ነው ታዲያ ሱዳኖች ምን ለማትረፍ ነው እኛስ ብንዘጋ ምን እንጠቀማለን ብለው ቀድመው ማሰላሰልን ያዙ፡፡በተጨማሪም ይህ በዓለም ዓቀፍ ሕግ ላይ የፈረሟቸውን ሁሉ ስምምነቶችም ገደል የሚከት ነበርና ዕውቀታቸውን ከህጉ ጋር ማጠመርን ያዙ፡፡በባለስልጣኖቹ ሃሳብ ልክ አለመሆን የተገነዘቡት አቶኃይሉ መረጋትን ሲመርጡ በተመሳሳይ ሚኒስቴር የነበሩትም አቶ ይሱፍ አህመድም የዚህ ተጋሪ ነበሩ፡፡

ይህ የሚያሣየው መደራደር መስማማት ሰላማዊ ውይይት ያስፈልጋል የሚለው ሀሳብ ገዢ ነው ባይ ነበሩ እና ሱዳን  የአየር ክልሏን እንድትፈቅድ የሚያስማማ ፅሁፍን ማሰነናዳት ጀመሩ፡፡ይህም በተጀመረበት ወቅት የደርግ ፅ/ቤት እነርሱ ፈለገ፡፡የአየር መንገድ ሀላፊዎችን ጨምሮ አምስት ሰዎችን ጓድ መንግስቱ ሀ/ማርያም በተገኙበት በደርግ ፅ/ቤት ታደሙ ሀገራዊ ታላቅ ጉዳይም ነበር፡፡

በስብሰባውም ላይ  ለሰላማዊ ድርደሩ የተዘጋጀው ፅሁፍ ተነበበ፡፡ይህንን ተከትሎ በርካታ ጥያቄዎች መነሳት ጀመሩ፡፡ሱዳን የአየር ክልሏን መዝጋት ሉዓላዊ መብቷ ነው የሚሉ እና የመሳሰሉ አይነት ሃሳቦች፤ሆኖም በጊዜው ከአቪዬሽን ተወክለው የሄዱት የህግ አማካሪ አቶ  አበራ መኮንን የአቪየሽንን ህግ ጠንቅቀው ያውቁ ስለነበር ተገቢውን ምላሽ ሰጡበት፡፡

አቶ ኃይሉም ቢሆን በደርግ ፅ/ቤት በተሰበሰቡበት ወቅት በዕውቀት የታገዘ ምላሻቸውን ያጋሩ ነበር፡፡ሃሳባቸውን ተናግው ሲጨርሱ ያደረጉኝ ያድርጉኝ ብለው ዕውነታውን ከተጨባጭ ዕውቀት ጋር እያስተሳሰሩ ይናገሩም ነበር፡፡

 አቶ ኃይሉ በመንግስቱ ኃይለመርያም የነበረውን ምላሽ ሲናገሩ ግን በዕውቀት የታገዘ ትክክለኛ ውሳኔ  ነው የያዛችሁት ቀጥሉበት ተብለው እንደተደነቁባቸው ነበር፡፡መታገስ መልካም ነውና ሱዳኖችም ከ አንድ ወር ድርድር በሁዋላ ታላቅ ይቅርታን አቅርበው ስጦታም ሰጥተው ግንኙነቱ እንደገና ማደስ ተችሏል፡፡

ባለታሪካችን አቶ ኃይሉ ገ/ማርያም የአቭዬሽንን ሙያ ዘልቀው እንደማጥናት እና መመራመራቸው በሁለት ሐገራት መካከል የአየር በረራ ግንኙነት መኖርን ከበፊት ጀምሮ ያምኑበት ነበር፡፡ ስራን በጀመሩበት በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘመን በአንዳንድ ሀገራት በረራ ይደረግ ነበር፤ ሆኖም በ1966 መንግስት ሲቀየር በረራ የሚደረግባቸውን ሐገራትም የግድ ማስተካከል ያስፈልግ ነበር፡፡

ለሐገር ያላቸው ፍቅር ከፍተኛ የሆነው አቶ ኃይሉ ስራ ላይም በታታሪነታቸው ይታወቃሉ፡፡ከ1966 በሁዋላም ለሀገራችን የተለያዩ ሐገራት የአየር ክልላቸውን ክፍት እንዲያደርጉ ጥረት አድርገዋል፡፡በተለያዩ ሀገራትም የአየር በረራ እንዲጀመርም አድርገዋል፤ከነዚህም መካከል ጋና፣ኬንያ፣የመን ፣አቡዳቢ፣ባህሬን እና ጣሊያን ይነሳሉ፡፡የአቶ ኃይሉ ህልማቸውን የዕውን ያሳኩ በመሆናቸው ጥረታቸውም ከግብ በመድረሱ ስማቸው በጉልህ ሰፈረ፡፡

በሲቪል አቪዬሽን የፕላኒንግ  እና የፖሊሲ ኃላፊ በነበሩበት ወቅት ደግሞ አንድ ያሳኩት ሌላ ቁምነገር ነበር፡፡የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አቢጃን ለመብረር ብዙ ጊዜ ሞክሮ አልተሳካለትም ነበር፤በተጨማሪም አየር መንገዱ ትርፋማ ባለመሆኑ የመዘጋት እጣ ፋንታ ከፊቱ ተደቅኖበትም ነበር፤የነበሩት አውሮፕላኖችም ከማርጀታቸው የተነሳ መላ ዘይዱላቸው የተባለበትም ጊዜ ነበር፡፡አየር መንገዱ በዚህ ውስጥ ቢሆንም ወደ አቢጃን መብረር አለበት የሚል ቁርጥ አቋም ነበረው ነገሩ ደግሞ እንዲህ በቀላሉ የማይቻል ነበር፡፡ይህን የማይቻለውን ወደ የሚቻል እንዲቀይሩ ታላቅ ሀገራዊ ኃላፊነት ደግሞ ታምኖባቸው የተሰጣቸው ለአቶ ኃይሉ ነው፡፡ስራውን ጀምረው ጉዞን ወደ እዛው ያደረጉት አቶ ኃይሉ በድርድር መድረኩ ላይ ከዚህ ቀደም የሚያውቁትን አንድ ሠው ያገኛሉ፡፡በዚህ ድርድር ሀገራችንን ወክለው ተጨማሪ ሠዎች ለድርድሩ መምጠት ቢኖርባቸውም በአውሮፕላን እጦት ሳይገኙ ቀሩ፤ስለዚህ ሙሉ ኃላፊነቱ በእርሷቸው ላይ ወደቀ፡፡

በወቅቱ በምዕራብ አፍሪካ ኃላፊ ሆነው አክራ የነበሩት አቶ ግርማ ዋቄ የተወሰኑ ሰነዶችን እያመጡላቸው እና መረጃዎችን እየሰጧቸው ድርድሩ ቀጠሉ፡፡በወቅቱ የኢትየጵያ አምባሳደር የነበሩት ስዩም መሐመድም ከእርሳቸው ጋር በመሆን ተራራን የመግፋት ያህል ከባድ ነው ሲሉ የሚገልፁን ክርክር ሲያደርጉ ቆዩ፡፡

ብዙ ልምድ በቀሰሙበት በዚህ ድርድር የአቢጃው ዋና ሀላፊ ወደ ሌላ ሀገር ለስራ ተፈልጎ ሲሄድ በምትኩ ቀደመ ሲል በአንድ ስብሰባ ያገኙት፣ ብዙ የተጨዋወቱት እና በደንብ የሚዋወቁት የሕግ ሰው ቦታውን ይረከባል፡፡በዚህ ድርድር ነጮችም ነበሩ፤ እንደ አቶ ኃይሉ አባባል እነሱ በነገሮች ሁሉ የሚከራከሩ እና አለመደማመጥን የሚዘሩም ነበሩ፡፡በሁዋላ ግን ነጮቹን አስወጥተው እርስ በርሳቸው አቶ ኃይሉ እና ሀላፊው ኩሊ ባሊ ብቻ ማውራት ጀመሩ፡፡አፍሪካዊያን ለአፍሪካዊያን ብቻ መወያየታቸው መፍትሄን እንደሚያመጣ ማሳያ የሆነወ ድርድር ቀናት ቢወስድም ተሳካ፡፡ታይቶም በማይታወቅ መልኩ የአየር በረራ ፈቃድን አሰጡ ይህ በሁሉም ውስጥ መደነቅን ስራቸው የጫረ ነበር፡፡

አቶ ግርማ ዋቄ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በዋና ስራ አስፈፃሚነት የመሩ ሲሆን አቶ ኃይሉ ከአዲስ አበባ አቢጃ የአየር በረራ እንዲጀመሩ ያደረጉት አስተዋፅኦ አይዘነጉትም፡፡ዛሬ ላይ ሆነውም ያንን ጊዜም በትውስታ እንዲህ መለስ ብለው ያነሱታል፡፡

አቶ ግርማ ዋቄ የኮትዲቯሩን አቢጃ ትዝታ ሲያነሱ  የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ያቋቋሙት ኤር አፍሪክ የሚባል አየር መንገድ አቋቁመው እንደነበር በማንሳት ነው፡፡ኤር አፍሪክ የአስራ አንድም የፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪ የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ብሄራዊ አየር መንገድ ተብሎ የሚቆጠር ነበር፡፡ታዲያ ከምን የመነጨ ሃሳብ እንደሆነ ባይታወቅም ኤር አፍረክ የኢትየጵያ አየር መንገድ እንዲበር በጭራሽ አይፈቅዱም ነበር፡፡በተደረገው እልህ አስጨራሽ የድርድር ስብሰባ ላይም ከአቶ ኃይሉ ጋር በጋራ መስራቸውን ያነሳሉ፡፡ያልታሰበውን ይህን ገበያ ሰብሮ ለመግባት ደግሞ የአቶ ኃይሉ ብስለት እና ወንድማማቻዊ ቅርበት ዛሬም ጥቅም ላይ ያለውን በረራ አሳክተው ደብዳቤውን ይዘው መመለሳቸውን ያስደንቃቸዋል፡፡

የአቶ ኃይሉ ገ/ማርያም ስራ በዚህ ብቻ የሚያበቃ አይደለም፡፡አቶ ግርማ ዋቄ ከአቢጃውም ስራቸው በተጨማሪም ስላላቸው የሀገር ፍቅር ያነሳሉ፡፡እሳቸው ሩዋንዳ በነበሩበት ወቅት አማካሪ ሆነው ይሰሩ በነበረበት ወቅት ማለት ነው ከአቶ ኃይሉ ጋር ተገናኝተው እንደነበር እና እሳቸው ያሰቡትን ነገር ከግብ ለማድረስ ያለመታከት እና ያለመሰልቸት የሚሰሩ መሆናቸውን ይመሰክሩላቸዋል፡፡በተጨማሪም ምንም አይነት ንዴት እና ብስጭትን ሳያሣዩ ሁለንም እንደ አመሉ ይዘው ወደ አንድ ዓላማ እና ግብ እንዲመጣ የማድረግ ከፍተኛ የሆነ የማግባባት እና የመግባባትም ችሎታ አላቸው ሲሉነው አቶ ኃይሉን የሚገልፁዋቸው፡፡ስራቸው፣ታታሪነታቸው እና ታሪካቸውም ለአዲሱ ትውልድ መማሪያም ይሆናል ሲሉም ያክላሉ፡፡

 

ይህ የአቶ ኃይሉ ጥረት ከሀገራች አልፎ በዓለም ዓቀፍ ሰዎች በጉልህ እንዲጠራም አድጎታል፡፡ሁ ኢዝ ሁ ኢን አቪዬሽን የተሰኘ የመረጃ መፅሀፍ እ.ኤ.አ በ1973 ባወጣው እትሙ የእሳቸውን ስም በደማቅ ብዕሩ አስፍሮታል፡፡

       









         የትዳር  እና የቤተሰብ ህይወት

አቶ ኃይሉ ከእንግሊዝ ከተመለሱ ከሰባት ዓመት በሁዋላ ትዳር የመያዝ ፍላጎት አደረባቸው፡፡ሃሳቡን እንዲያሰላስሉት ያደረጓቸው ታላቅ እህታቸው ናቸው፡፡ወደ አድዋ በሚሄዱበት ወቅት ሁሌ የወ/ሮ አወጣሽ ስም ሲጠራ ይሰማሉ፤አንድ ቀን ግን ለትዳር የምትሆን የባላምባራስ ፍስሐም ልጅ አለች ይላሉ፡፡ይሄኔ ማናቸው ብለው አቶ ኃይሉ ሲጠይቁ እንዴ ወንማቸውንም ታውቀዋለህ ይሏቸዋል በዚህ መነሻነት አዕምሯቸው  ስለ ትዳር ማሰቡን ይጀምራል፡፡

በተጨማሪ  አሁን በህይወት የሌሉት ፕሮፌሰር መርዕድ ወ/አረጋይ የአቶ ኃይሉ ጓደኛ ሲሆኑ እህቴ ባትሆን ኖሮ አንድ ጥሩ ልጅ አለች እያሉ ስሟን በተደጋጋሚ የሚያነሱላቸው ሴት አለች፡፡ይህ ሁሉ ተደማማሮ ነው አዕምሮዋቸውን ትዳር እዲያስቡ ያደረጋቸው፡

በሌላኛ በአንዱ ቀን ደግሞ ፕሮፌሰር መርዕድ ለትምህርት ወደ ውጪ በሚሄዱበት ወቅት ለሽኝት አየር መንገድ በተገኙበት የአሁኗን ባለቤታቸውን ወ/ሮ አሰፋሽን ከአጎታቸው ጋር በመሆን ከደረጃ ሲወርደ ያዩዋቸዋል፡፡እንዴ እህቴ እያልክ እስከዛሬ ስታወራልኝ የቆየኸው ወ/ሮ አሰፋሽ ባላምባራስ ፍስሀ እሷን ነው እንዴ በማለት ይጠይቃሉ፡፡ይህ አጋጣሚ ካፖርት ለብሰው ከሩቁ ሲመጡ የጠመለቷቸውን እና  ብዙ ሲወራላቸው የሰሙትን ወ/ሮ አሰፋሽን በፍቅር አይን እንዲያዩ አደረጋቸው፡፡

 በዚህም መነሻነት አቶ ኃይሉ ሰናገሩ ቦሌ ለስራቸው ብቻ ሳይሆን ለህይወታቸውም ትልቅ ቦታ ያለው ስፍራ በመሆኑ ከህይወቴ ጋር የተጣመረም ቦታ ነው ይላሉ፡፡ስራቸውን ለረዥም ዓመት የሰሩበት ብቻ ሳይሆን የትዳር አጋራቸውን ያገኙበትም ቦታ መሆኑን ለመግለፅ፡፡

በወቅቱ በፍቅር የከነፉት አቶ ኃይሉ እና ወ/ሮ አሰፋሽ በ1962 ፍቅራቸውን ወደ ትዳር ለማሻገር አስበው ቀለል ያለ ሰርግን ለማድረግ ይወስናሉ፡፡ሆኖም በጓደኞቻቸው እና በቤተሰብ ሃሳብ አድዋ ላይ ሁሉም ከገጠር እስከ ከተማ የተሰባሰበበት ሰርግ ይደገሳል፡፡ከአዲስ አበባ ተነስተው ለአቶ ኃይሉ ሚዜ የነበሩት አቶ ግርማይ ተ/ሀይማኖት አዲስ ዳክሰን መኪና በመግዛት ከታናሽ ወንድማቸው አቶ አማረ ተ/ሀይማኖት ፣አቶ ካህሳይ መንግስት አብ ፣አቶ አባተ መንክር ጋር በመሆን መኪናቸውን እየነዱ አድዋ ገብተዋል፡፡ጓደኞቻቸው ፣ቤተሰቦቻቸው እና ሁሉም ከአዲስ አበባ፣ከአድዋ እና ከአስመራም ጨምሮ የተሰባሰቡበት ለታሪክም ድጋሚ በዓመቱ ለምን ክርስትና አድዋ ላይ አልደገሱም መሰባሰቢያችን ነበር የተባለለት ትልቅ ሰርግ ሰርገው ተጋቡ፡፡

ወይዘሮ አሰፋሽም ቢሆኑ ይህ የሰርግ ስነ ስርዓት ሀምሳ ዓመታትን ወደ ሁዋላ ቢመልሳቸውም ዛሬም ትዝታው አይጠፋቸውም፡፡የቴሌኮሚኒኬሽን ጀማሪ ሰራተኛ በነበሩበት ጊዜ የተደረገው ሁለት ሺህ የሚደሩሱ የመጥሪያ ካርድ የታተሙበት እና ብዙዎችም የታደሙበት እሳቸው ደግሞ በቤተሰቡ የመጀመሪያ በመሆናቸው ትልቅ ቦታ እንደተሰጠውም ያነሳሉ፡፡

በዚያው ወቅት ለሰርጉ ወደ አድዋ እየሄዱ ሳለ ቡልጋሪያ አካባቢባለ ሶስት መኝታ ቤት ትልቅ ግቢን በሁለት መቶ ሀምሳ ብር ተከራይተው የሰርጉን ጉዞ ወደ አድዋ ቀጠሉ፡፡

አድዋ ኒያላ ሆቴል ከተደረገው ትልቅ የእራት ግብዣ በሁዋላ የወ/ሮ አሰፋሽ አባት አ.ንድ ሺህ ብር በኪሳቸው ከተቱላቸው፡፡ ለጫጉላ ሽርሽርም ወ/ሮ አሰፋሽ እና አቶ ኃይሉም ወደ ምፅዋ ተጓዙ፡፡ምፅዋ ለአንድ ሳምንት ከተቀመጡ በሁዋላም ወደ አስመራ ፣አክሱም በመቀጠልም ወደ ጎንደር ተጉዘው ከሁለት ሶስት ቀን ቆይታ በሁዋላ ወደ ባህርዳር በመጓዝ ብቻ የቱሪስት ቆይታን በማድረግ ወደ አዲስ አበባ  ወደ ቤታቸው ተመለሱ፡፡

በዚህ በፍቅር በደመቀው በትዳር በሞቀው ቤት በ1963 የመጀመሪያው የሆነው ሌላኛው የቤቱ ድምቀት አሉላ ተወለደ፡፡አሁን ላይ የኮምፒዩተር ኢንጂነሩ አሉላ በአሜረካ በሚገኘው ፕራት ኤንድ ዊትኒ ዪናየትድ ካምፓኒ የዲዛይን ክፍል ኃላፊ ነው፡፡

አሉላ ኃይሉ ስለአስተዳደጉ እና ስለቤተሰቡ ሲናገርም ደስታን በተሞላ አኳሃን ሲሆን አባቱ ወደ ትምህርት ቤት ሲያደርሱት እና ወደ እቤት ሲመልም ደግሞ ያለው ሁኔታ  ትልቁ ትውስታው ነው፡፡

ወ/ሮ አሰፋሽም ያን ጊዜ ሲያስታውሱት ልዩ የሆነ ምንም ችግር የሌለበት ቤቱ በቤተሰብ እና በዘመድ የተሞላ ሁሉ የሞላበት ጊዜ ነው በማለት ነው፡፡አቶ ኃይሉንም ቢሆን ወንድሜ፣ጓደኛዬ እና ባለቤቴም ነው ሲሉ ነው የሚገልፁዋቸው፡፡

አቶ ኃይሉ ከነበረባቸው የስራ ኃላፊነት በተጨማሪም ቤተሰብ እና አዳዲሶቹን ሶስት ልጆቻውን መንከባከብ ሌላው ትልቅ አደራቸው ነበር፡፡ይህንንም በአግባቡ እየከወኑ የመጀመሪያዎቹን የ1960ዎቹን ዓመታት ተሸገሩ፡፡

ባሳለፍነው ሚያዝያ 2012 ሀምሳኛ ዓመት የአብሮነት እና የትዳር ቆይታ ጊዜያቸቸውን ያከበሩት የትዳር አጋሮች ለዛሬ ለመድረሳቸው ዋናው ምክንያት ሦስተኛ ሰው ሳያስገቡ እርስ በርስ መተሳሰባቸው እና መዋደዳቸው መሆኑን ያነሳሉ፡፡

ዛሬ ላይ ቆመው ትላንትን ሲመለከቱ የሶስቱ ልጆቻቸውን ሁኔታ ሲያስቡት እና ዛሬ ላይ ሲመለሱ የደስታ ስሜት ይወራቸዋል፡፡

አቶ ኃይሉ ስለ ባለቤታቸው ሲናገሩ ሩህሩህ ይሏቸዋል፤ለራሳቸው ሳይሆን ለሌላ የሚያስቡ ልበ ቀና ናቸው የእኔ ቤተሰቦች ከእኔ ይልቅ ለእሷ ነው ቅርበታቸው ይላሉ፡፡ቤታቸው በሰው ሲሞላ የሚደሰቱ በሰው መከበብ ለሰው መኖር የሚወዱ ናቸው ሲሉም ይመሰክርላቸዋል፡፡

አባትነታቸው በልጆቻቸው አፍ ሲመሰከር ደግሞ ልዩ ስሜት አለው፡፡ሁሉም ልጆቻቸው የአባታቸውን ፍቅር ሲገልጹም ያሳለፉት ፍቅር ምስክር ነው፡፡

ሁለተኛ ልጃቸው የሆነው አቶ ሚካኤል ኃይሉም አባቴን እንደ ጓደኛም በሌላ በኩል እንደ ወንድሜም የማየው ቅርቤ ነው ይላቸዋል፡፡በሁሉም ዘርፍ ዕውቀትአላቸው ይህም የሆነው ሲል ሚካኤል ሰለ አባቱ ይናገራል ‹‹በጣም አንባቢ ነው፤ቤት ውስጥ፣መኪና ውስጥ ሆነ ቢሮ ውስጥ መፅሀፍ አለ፤ሁሌም እኛም እንድናነብ ታሪክን እንድናውቅ ረድቶናል፡፡ሌላው በእረፍት ቀን በሆነው እሁድ ረዣዥም የእግር መንገድ እንሄድ ነበር፡፡››ሲል ያስታውሳል፡፡

ሌላው እና የአቶ ኃይሉ ሦስተኛ ልጅ የሆነው አቶ ብሩክ ኃይሉ የአባቱን በሲቪል አቪዬሽን መስሪያ ቤት ያሳረፉትን አሻራ ያነሳል፡፡ልጆች ሆነው የአባታቸውን እዚህ ቦታ መደረስ ያላቸውን ተቀባይነት ሆነ የስራቸውን ደረጃ እንደማይረዱት ያነሳል፡፡ቀስ በቀስ ግን እቤታቸው ከሚመጡ ሰዎች ጓደኖቻቸው ጋር ሲያወሩ ሲሰሙ የሳቸውን ቦታ አክብሮት እያወቁ መጡ፡፡ሌላው የአቶ ኃይሉን ለታሪክ ያላቸውን ትልቅ ቦታ እና ዕውቀት ሲያነሳ እና ያላቸውን ትውስታ ሲያስብ ይደነቃል፡፡እያንዳንዷን ሁነት አብጠርጥረው የሚያስታውሱ መሆናቸውን ለቴክኖሎጂ ያላቸውን ዕውቀትም ጭምር ከፍተኛ ነው ሲል ያነሳል፡፡

ልጃቸው ሚካኤል ስለ አባቱ ባህሪ ሲያወራ ‹‹አቋሙ ወጥ ነው፤ይሄ ትልቅ ነው ይሄ ትንሽ ነው የሚል ባህሪ የለውም ለእሱ ሁሉም እኩል ነው፡፡ከሁሉም ጋር እኩል ያወራል፡፡ተንኮል ከድሮም አይወድም፡፡ያለው የማስታወስ ችሎታ ግን የሚደነቅ ነው፡፡አሁን ላይ ከጓደኞቹ ጋር ቁጭ ብሎ የተገኘኑበትን ጊዜ እና ቦታ ጭምር ማስታወሱ እና እያንደንዷን ቅንታት ማስታወሱ ይደንቀኛል፡፡››ሲል ስለ አባቱ ባህርይ ይመሰክራል፡፡

የመጀመሪያ ልጃቸው አሉላው የማስታወስ ችሎታቸውን ሲያነሳ ‹‹ትንንሽ የሆኑ ነገሮችን በጣም ነው የሚያስታውሰው፣መንገዶችን በጣም ነው የሚያውቀው ለማያውቀውም መንገድም ቢሆን አቅጣጫ የማወቅ የተለየ ክህሎት አለው፡፡በጣም የአዕምሮ ሠው ነው፡፡በጣም ነው ምኮራበት፡፡››ሲል የእርሳቸው ልጅ መሆኑ ኩራት ባላበሰው መልኩ ይመሰክርላቸዋል፡

ባለቤታቸውም‹‹ኃይሉ ስራ ይወዳል፤ቤት የሚያጠፋው ጊዜ በጣም ትንሽ ጊዜ ነው፡፡ሌሊትም ቢሆን እንቅልፍ እንቢ ካለው ስራውን ይሰራል፡፡››ሲሉ ስለ ባለቤታቸው ትጋት ያነሳሉ፡፡በተጨማሪም ስለ አቶ ኃይሉ ሲነገሩ‹‹እንጀራ ይወደል፤ከፈረንጅ ምግብም ፓስታ ይወዳል፡፡ከጤና ጋር በተያያዘ ግን የፈረንጅ ምግብ ምርጫው ነው፡፡በባህሪውም ቶሎ ቱግ ይላል፡፡ይህ የሚሆነው ግን ሁሉም ሰው እንዴት ይሄን ሁሉንም አያውቀውም ሲል ነው እኔም ገና እንዳልገባኝ እረዳለሁ፡፡››ይላሉ፡፡

ቤታቸውን በፍቅር እንዲቆይ ጎጇቸውም እንዳይዘም ያደረገው የባለቤታቸቸው ሁሉም የማቻቻል ባህሪ እንደሆነም ይናገራል፡፡በዘመኑ አንድ ሺህ ሁለት መቶ ብር ደሞዝተኛ የነበሩት አቶ ኃይሉ በሀገራችን ከፍተኛ ተከፋይ ከነበሩትም ውስጥ የነበሩ ሲሆን ለአስራ አምስት ዓመታትም በዚሁ ደሞዝ ሰርተው ነው ጡረታ የወጡት፡፡

 

       

 














 

         ጉዞ ከኃይለስላሴ ስርዓት በኋላ ውልደተ ደርግ

የ1966ቱ ለውጥ የመጣ ሰሞን አቶ ኃይሉ በሀገሪቱ የነበረውን እንቅስቃሴ በወጉ ማስተዋል ችለዋል፡፡ንጉሱ ገና ሳይወርዱ ደርግ ቀስ በቀስ እየመራ እንደ የሲቪል አቪዬሽን ያሉ መስሪያ ቤቶችን በለውጡ ነክቷቸዋል፡፡

አቶ ኃይሉ በአንዱ ቀን ወደ መስሪያ ቤታቸው ጊዜው የካቲት 1966 ጠቅላይ ሚኒስቴር ልጅ እንዳልካቸው የአቪዬሽኑ ሚኒስቴር ደግሞ አቶ ኃይሉ አለማየሁ ነበሩ፡፡ታዲያ በዚህ ቀን አንድ አመፅ ተነስቶ ነው ቢሮ የደረሱት፡፡አመፁም ከእነሱ መስሪያ ቤት አጠገብ ያለው እነሱ የውሃ ልማት ባለስልጣን ከእነሱ አለቃ ጋር ጓደኛ ናቸውአብረውም ተምረዋል ፡፡ታዲጣ ሰራተኛው እነሱን አንዱ በአንዱ ሊተካ ነው ይሄኛው በዛኛው ያኛው በዚህኛው ሊያስመታን ነው እኛ ደግሞ አንፈልግም በሚል ሃሳብ ታላቅ አመፅ መነሳቱን ያስታሰውሳሉ፡፡

እንደምንም ቢሮ ገብተው ሲመለከቱ የእርሳቸው ቢሮ ብቻ ክፍት ሆኖ ሌላው ታሽጎ ነበር ስራ ለመስራትም አመቺ ባለሆነበት ሰዓት ልጅ ሚካኤል ዕምሩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴር እንደሆኑ ተነገረ፡፡አቶ ኃይሉም ገ/ማርያም ሲቪል አቪዬሽንን እንዲመሩ ስልጣን ተሰጣው፡፡ሆኖም በመስሪያ ቤቱ አላግባብ በሆኑ ትዕዛዞች ከሰራተኞቹ ጋር መጣላት ጀመሩ፡፡

ከ1923 እስከ 1966ም በንጉሳዊ ስርዓት በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ስትመራ የበረችው ሀገራችንም አዲስ ለውጥ ውስጥ የገባችበት ወቅት ነበር፡፡

ለአቶ ኃይሉ ይህ ጊዜ በርካታ ትዕዛዞች በስልክም ሳይቀር እቤት ድረስ እየደወሉ የሚታዘዙበት ኤር ስፔስ አንዲዘጋ እንዲያደርጉ የሚጠየቁበትም ሰዓት መሆኑን ባለቤታቸውም ያወሳሉ፡፡

‹‹በጣም እፈራ ነበር፤ያዘዙትን ካላደረገ አንድ ነበር ያደርጉታል ብዬ እሰጋ ነበር፡፡ወጥቶ እስኪመለስ ድረስ ያስጨንቀኛል፤ምን አድርጎ ይሆን እሱ ደግሞ ደፋር ነው ካላመነበት ያሉትን በስህተት ማድረግ አይፈልግም እና ያስጨንቀኝ ነበር፡፡››ሲሉ ወቅቱ የጭንቅት መሆኑን ያነሳሉ፡፡

ለአቶ ኃይሉ ከየቦታው ሚስጥራዊ መረጃን በስልክ እየደሉ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ የተለየዩ ስልኮች እየተደወሉ ማስፈራሪያዎችም ጭምር ከደርግ ካድሬዎችም ይደርሷቸው ነበር፡፡ይህ ወቅት እሳቸውንም ሆነ ቤተሰቦቻቸውን እንቅልፍ የነሳ ነበር፡፡ይሄ ባለበት ሁኔታ አንድ ዓመት እንደሰሩ አይኪውኦ ሲቪል አቪዬሽን በየሶስት ዓመቱ ለሚደረገው ስብሰባ አንተ መሪ ሆነህ ሂድ ተብለው በሚኒስቴሩ ታዘዙ፡፡

በዚህ የካናዳው ዓመታዊ ጉባኤ እንዱሳተፉ የተደረጉት አቶ ኃይሉ በነበረው ስርዓት በእጅጉ ተሰላችው ነበር፡፡በዚህም መነሻነትም ከካናዳ ስመነስ እኔን አንሱኝ እና በቦታው ሌላ ሠው ሹሙበት ብለው ነበር፡፡ይህ በራሱ የአቶ ኃይሉን ቆራጥነት የሚያሳይ ነበር፡፡

እዛው ስብሰባ ላይ እንዳሉ ጀነራል ታፈሰ የተሰኙ ሰው ተሹመዋል ተባሉ፤ለእሳቸው ይሄ ደስታ ነበር፡፡

አቶ ኃይሉ በልጆቻቸው እና በባለቤታቸው ብቻ ሳይሆን በአብሮ አደጎቻቸው ሲገለፁም ትልቅ ክብርን የተገጎናፀፉ ናቸው፡፡

አቶ ጥላሁን ውብ ነህ ከአቶ ኃይሉ ጋር ከመጀመሪያ ደረጃ ንግስተ ሳባ ትምህርት ቤት ጀምሮ ትውውቅ አላቸው፡፡አቶ ጥላሁን ስለ አቶ ኃይሉ ምስክርነት ከመስጠታቸው በፊት ለአቶ ኃይሉ ትምህርት ቤት መግባት ትልቅ አስተዋፅኦ ያደረጉትን የታላቅ እህታቸውን ወ/ሮ አወጣሽ ባለቤት ብላታ ገብሩን ያመሰግናሉ፡፡በንግስተ ሳባ ትምህርት ቤት ለሁለቱ መገናኘትም ትልቅ አስተዋፅኦ አላቸው፡፡ስለ ንግስተ ሳባ ትምህርት ቤት ትዝታቸውም ሲያወጉ‹‹ኃይሉ ጎበዝ ፣ረጋ ያለ እና ቁምነገረኛ ነበር፤በንግስተ ሳባትምህርት ቤት በነበርንበት ወቅት በሁሉ ዘንድ በአማርኛ የቁም አጻጻፉ የታወቀ እና የተደነቀ ነበር፡፡ፅህፈቱም የተለየ ስለነበር በፅሁፍ እንዲያግዝ ይደረግ ነበር፡፡አፃፃፉ የገነነ ስለነበር ከትምህርት ቤት ውጪም አንዳንድ ባለስልጣናት እንዲፅፍላቸው ይጠይቁት ነበር፡፡››ሲሉ ያን ጊዜ አቶ ኃይሉ የነበራቸውን ዝና ያነሳሉ፡፡

አቶ ገብርኤሉ ቢታሌ ከአቶ ኃይሉ ጋር ለኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን በረዳት የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪነት ተቀጥረው በነበረበት ወቅት ስልጠና ላይ እያሉ ነው የተዋወቁት፡፡አቶ ኃይሉ ደግሞ በዚህ ወቅት የመስሪያ ቤቱን የቴክኒክ ክፍል በዳይሬክተርነት ይመሩ ነበር፡፡በእሳቸው ስርም የነበሩት ክፍሎች የአየር ትራፊክ አገልግሎት እና የኦፕሬሽን መምሪያ፣ሜትሮለጂ አገልግሎት መምሪያ እና የሬዲዮ ኢንጂነሪንግ እና ናቪጌት መምሪያ እና የምህንድስና መምሪያ ነበሩ ሲሉ ያነሳሉ፡፡

አቶ ኃይሉ በሌሎች ሀገራት ላይ በሚደረጉ ማንኛውም ውይይቶች እና ትልልቅ ውሳኔ በሚያስፈልጋቸው ዓለም ዓቀፍ መድረኮች ላይ ሀገራቸውን እና መስሪያ ቤታቸውን በመወከል ይቀርቡ እንደነበር ይናገራሉ፡፡በሀገራችንም ከተለያዩ የውጭ ሀገራት መሀንዲሶች ጋር በመዘዋወር የአውሮፕላን ደህንንት የሚያስጠብቁ የናቪጌት መሳሪያዎች የሚተከሉበትን ቦታ በመምረጥ ጭምር እንዲተከሉም አድርገዋል ሲሉ በመስሪያ ቤቱ የቴክኒክ ኃላፊ በነበሩበት ወቅት ከሰሯቸው  ውስጥ የሚያነሱላቸው ተግባራቸው ነው፡፡

አቶ ግርማቸው ስለ አቶ ኃይሉ ባህርይ ሲናገሩ‹‹ቁምነገር ካልሆነ የማይረባ ትርኪ ሚርኪ ወሬ አይፈልግም፡፡ቁምነገር አልያም ቀልድ እና ጨዋታ ብቻ ነው የሚፈልገው፡፡ቻይ ነው፤በጣም ትዕግስተኛ ነው፡፡የማይሆን ነገር ከሰማ ደግሞ ይለወጣል››ሲሉ የጓደኛቸውን ባህሪ በሳቅ ይገልፃሉ፡፡

አቶ ጥላሁን እሳቸው ኢሲኤን ወክለው አቶ ኃይሉ ደግሞ የኢትዮጰያ መንግስትን ወክለው የምስራቅ እና የመካከለኛው አፍሪካ ስብሰባ ላይ አብረው ስለመሳተፋቸው ያነሳሉ፡፡የትግራይ ልማት ማህበር የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ በተቋቋመበት ጊዜ የጎላ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን እና ቅርንጫፉን በሊቀመንበርነት መምራታቸውን ጭምር ያነሳሉ፡፡

አቶ ወርቅነህ ደገፉ በሜትሮሎጂ ሙያቸው የሚታወቁ ባለሙያ ናቸው፡፡ከአቶ ኃይሉ ጋር የመተዋወቅ እድሉን ያገኙት በ1960ቹ መጀመሪያ ነበር፡፡ታዲያ ወደ ሁዋላ ለስራ ብለው ሲያስቡ እኚህ ሠው ብዙ ቢባልላቸው የሚገባቸው ሠው ናቸው ይላሉ፡፡‹‹በስራ እንገናን ነበር፤የሜትሮሎጂ ስራ ሬዲዮን እና በርካታ ኤሌክትሮኒክስን የሚጠቀመ ስለሆነ እነዚህ መሳሪያዎች ሲገዙም ሆነ ሲጠገኑ በእሳቸው በኩል የሚያለፉ ናቸው፡፡በዚህም በየቀኑ በስራ እንገናኝ ነበር፡፡በሁዋላም በሲቪል አቪዬሽን የቴክኒካል ክፍል ዳይሬክተር ሆነው ሲሰሩም አለቃዬ ሆነው አብረን ሰርተናል››በማለት የሁለቱን የግንኙነት ጊዜ ያስታውሳሉ፡፡

አቶ ግርማቸው ስለ ጠንቃቃነታቸውም ያነሳሉ፡፡ በተለይ ስለ ሀገር ወዳድነታቸው ይመሰክሩላቸዋል፡፡

አቶ ጥላሁን በሲቪል አቪየሽን ትምህርት ቤት አብረዋቸው አንድ ክፍል ባይማሩም የመማሪያ ግቢያቸው አንድ በመሆኑ በትምህርት ጎበዝ እንደነበሩ ያውቁ እንደነበር ያነሳሉ፡፡

የአቶ ኃይሉ የመጀመሪያ ልጃቸው አሉላ አባታቸው ሽርሽር ይወስዷቸው እንደነበር ያስታውሳል፡፡በተለያየ ምክንያት አየር መንገድ መሄዳቸውንም ያነሳል፡፡የመቆጣጠሪያ ክፍል ድረስ መግባታቸው ትውስ ይለዋል፡፡ከእሁድ ትዝታዎቹ መካከል ደግሞ አስደሳቹ አየር መንገድ በሚገኘው ካፌ ኬክ በልቶ መመለስ ነበር፡፡ከዚህ በተጨማሪ የአባቱን ዕውቀት ሲመሰክርም‹‹አባ በጣም የተማረ ነው፤የውጪ ነገር በጣም ያውቃል ስላወቀቅ ነገር ስለሚያብራራ ከልጅነቴ ስለውጪ አስብ ነበር፡፡አስተሳሰቤም የሰፋ ነበር፡፡አባቴን እየተከታተልኩ ጋዜጣን አነብ ነበር፡፡ሁሌም እሱን ስለምከተል እሱን እየሆንኩ ነው፡፡ጠዋት ተነስቶ አትክልት ያጠጣል፡፡ስራ ወዳድ ነው ጠዋት ተነስቶ ስራ መስራት ይወዳል››ሲል አባቱን ይገልጻቸዋል፡፡

ሌላኛው ልጃቸው የሆነው አቶ ሚካኤል ኃይሉ ደግሞ አባቴን አሁን ድረስ አላወኩትም ሲል ነው የሚናገረው የእሳቸውን ታሪክ ሁል ጊዜም በሰማ ቁጥር ሌላ የሳቸው ታሪክ ተያይዞ መምጣቱ አባቱ ከሰሩት ስራ ስፋት እና ጥልቀት  አንጻር መፅሀፍ ናቸው ሲል ሁሌም ይደነቅባቸዋል፡፡ ሌላው ደግሞ ስለ አባቱ ሲያነሳ‹‹አንድም የተቀየመው ሠው አጋጥሞኝ አያውቅም ፡፡ጥፋትም ካለ እዛው ቁጭ አድርጎ አንተ እኮ ጥፋትህ ይሄ ነው ይለዋል በሕይወቴ አንድም ሠው ተቀይሞትም አያውቅም እንደውም በተቃራኒው ጋሽ ኃይሉ እኮ የተናገረኝ ልክ ነው ሲሉ ነው የምሰማው፡፡››በማለት ከሰውም ጋር ስላላቸው ግንኙነት ይመሰክርላቸዋል፡፡

አቶ ኃይሉ ገ/ማርያም እንዲህ እና መሰል አስታየቶች ቢሰጧቸውም ገና ምኑን ሰራሁ እና የሚሉ ሰው ናቸው፡፡ ገና በንጉሱ ዘመን ለአስራ ሶስት ዓመታት በልዩ ልዩ ሙያ በኃላፊነት አገልግለዋል፡፡ከኢንጂነርነት እስከ የሲቪል ቪዬሽን ተጠባባቂ ዳይሬክተርነት ድረስ፡፡በደርግ ዘመነ መንግስትም በ1970ዎቹ ደግሞ የሀገራችንን የአቪዬሽን ልማት ለማሳደግ በእጅጉ ሰርተዋል፡፡

በ1972 የማዕከላዊ ፕላን ኮሚሽን በሀገሩቱ ባለው በኢኮኖሚ ዘርፍ ጥናት ለማድረግ ሲቋቋም አቶ ኃይሉ ተሳታፊ ነበሩ፡፡በወቅቱ ባለው የአየር እና የባህር ዘርፍም የበኩላቸውን እንዲወጡ እና እንዲሰሩ ተደረጉ፡፡

በወቅቱ ታዲያ እሳቸው እንደሚገልፁትም እስርቤት የመግባት ያህል ነው ፓለቲካዊ ሽኩቻ ቢኖረውም ብዙ ነገር የተማሩበትም ነው፡፡

ሲቪል አቪዬሽን መስሪያ ቤት አቶ ኃይሉ እንደሚሉት የመንግስት ተዋካይ ነው፡፡በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስር አለም አቀፍ የሲቪል አቪየሽን ድርጅት የሚል ተቋም አለ፡፡ይህ ተቋም መገኛው ካናዳ ነው፤ኢትዮጵያም የዚህ አንዷ ፈራሚ አባል ነበረች፡፡

ሁለት ኃፊነት ባለው የሲቪል አቪየሽን ህግ ላይ አየር መንገዶችን መስራት እና ማስተዳደር እንዲሁም ፈቃድን መስጠት ፣መቆጠጠርን የሚሉ ህጎች ያሉት ሲሆኑ ኢትዮጵያም የዚህ ህግ ተገዢ ነበረች፡፡

ሁሌም ማረፍን ሳይሆን አዲስ ነገር ማቀድን መስራትን ተግባራቸው ያደረጉት አቶ ኃይሉ በማዕከላዊ ፕላን ኮሚሽን እያሉም የቦሌ አየር መንገድ ማስፋፊያ እንደታቀደ ይናገሉ፡፡በወቅቱ ከፕሬዝዳንት መንግስቱ ኃ/ማርያም የመጣው ደብዳቤ እንድ ትልቅ አየር መንገድ ዱከም ላይ እንዲሰራ እና በጠቅላይ ሚኒስቴሩ የሚመራ እንዲሆን የማዕከላዊ ፕላን ኮሚሽን ደግሞ እንዲከታተለው እና እንዲያስፈፅም የሚል ነበር፡፡አለቆቻውም እየጠሯቸው የዱከሙ መቼ ነው የተጠናው የሚል ጭቅጭቅ ይነሳሉ፡፡ስብሰባዎች ይበዛሉ፡፡መጨረሻ ላይ ግን ዱከም ላይ ከሚሰራ ከሰሩት ጥናት ቦሌን ማስፋፋት እንጂ ዱከም ላይ መስራት እንደማይቻል ድምዳሜ ላይ ይደርሳሉ፡፡


 

 

        ድህረ ደርግ ዘመነ ኢህአዴግ እና ጡረታ

በ1983 ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ከመጣም በሁዋላ የቦሌ የማስፋፈፊያ ስራው ለጊዜው ቢቋረጥም ከአፍሪካ ልማት ባንክ በተገኘ ብድር የአየር ማረፊያው ላይ የሜዳ ጥናት የሚል ምክረ ሃሳብ ቀረበ፡፡ለዚህም ታምስ የተሰኘ የአሜሪካ አማካሪ ኩባንያ ተቀጥሮ ነበረ፡፡ታምስ ዲዛይኑን ለሁለት ዓመት ወስዶ ካጠና በሁዋላ የሰራውን አቀረበ፡፡በጥናቱም በተመሳሳይ አዲስ የሆነ የተርሚናል ማስፋፊያ እንጂ አዲስ አየር መንገድ መስራት ከአቅም አንፃር እንደማይቻል ለዚሁም 247 ሚሊየን ዶላር እንደሚያስፈልግ በጥናቱ ነገሯቸዋል፡፡

አቶ ኃይሉ ገ/ማርያም ጡረታ በወጡበት በዚህ ዓመት ኤቢሀም የተሰኘ የግ አማካሪ ድርጅትን መሰረቱ፡፡በጊዜው የአየር ትራንስፖርት ፖሊሲ እና ስትራቴጂን አጥንተው ለሲቪል አቪየሽን መስሪያ ቤት አቅርበዋል፡፡በዚህ ጥናት ላይ ከአቶ በቀለ ሰርቤሳ  እና ኮረኔል ውብሸት ተፈራ የራሳቸውን አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡በምላሹም ጥናቱ ተቀባነትን አግኝቶ ለካ ኢትዮጵያ እንዲህም አይነት ሰዎች አሏት ተብሎ ለእነ አቶ ኃይሉንም ትልቅ ግምትም ተሰጣቸው፡፡

የሀገር ውስጥ በረራ መጀመር አለበት በሚልም ጥናት ይጠና ተብሎ የእሳቸው ቡድን ጥናትን አጥንቶ አቅርበዋል፡፡በወቅቱ የነበረው ሚኒስቴርም ‹‹ሲቪህን አምጣ አለኝ እኔም ሰጠሁት›› የሚሉት አቶ ኃይሉ የአለም ባንክ እና የአፍረካ ልማት ባንክ ተቀባይነትን አግኝተው ነበር፡፡

የቦሌ አየር መንገድ የግንባታ እና የማስፋፊያ ስራ በ1987 አሀዱ ብሎ ሲጀመር ከአፍሪካ ትልቁ እንደሚሆን ታምኖበት ነበር፡፡የዚህ ስራ ዋና መሪ የነበሩት አቶ ኃይሉ ደከመኝ ሰለቸኝ ሆነ እረፍት አማረኝ ሳይሉ ስራቸውን ቀጠሉ፡፡ትልቅ ኃላፊነት በርካታ ትዕዛዞችም ነበሩበት፡፡በተያዘለትም በጀት ላይ በመንግስት ከስምንት መቶ ስልሳ ሚሊየን ብር እንዳታልፉ ሲባሉ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ደግሞ ገንዘንብን በማሰብ ከጥራቱ የወረደ ስራ እንዳይሰሩ አንድም ዲዛይን የተደረውን እንዳትቀንሱ የሚል መመሪያ ተሰጣቸው፡፡

የቦሌ አየር ማረፊያን የማስፋያ ፕሮጀክትን የማረፊያ ሜዳውን ስራ በመማከር ዳር አል ሀዳንሳ የተባለ የሊባኖስ ኩባንያ ሲሆን ኮንትራክተሮቹ ደግሞ  ካጂማ እና ቺንጋም የተባሉ የጃፓን እና የኮርያ ኩባንያዎች ነበሩ፡፡በሜዳው ስራ ላይ በገንዘብ ደግሞ የአፍሪካ ልማት ባንክ እና የኢትየጵያ መንግስት ተሳትፎ አድርገዋል፡፡

በሁለተኛው ምዕራፍ የህንፃውን እና ተያያዥ ስራዎች በአማካሪነት የሰራው አሌክሳንደር ጊብ የተባለ የእግሊግሊዝ ኩባንያ የሰራው ሲሆን ኮንትራክተሩ ደግሞ አል ካራፊ የተባለ የኩዌት ኩባንያ ሲሆን ስራውን የሰሩት ሲሆን በገንዘብ ድጋፍ ደግሞ የኩዌት የፈንድ ፣ኦፔክ ፈንድ እና የአረብ ባንክ ነበሩበት፡፡

በሦስተኛው የኤሌክትሪክ እና የኤር ናቪጄሽን ስራ በማማከር ደግሞ የጀርመኑ ፊሽነር ተሳትፎ የበረው ሲሆን ኮንትራክተሩም ከዛው ከጀርመን ሲመንስ ነበር፡፡ይህንን ደግሞ በገንዘብ የደገፈው የአውሮፓ ኢንቨስትመን ባንክ ነበረ፡፡

የአራተኛውን ፓኬጅ ኮንትራክተር የፊላንድ ኩባንያ ነው፡፡አማካሪው ደግሞ የእንግሊዙ ጊብ ሲሆን በገንዘብ ደግሞ ኖርዲክ ደቨሎፕመንት ባንክ ስሙ ይጠቀሳል፡፡ይህንን ሁሉ አብራርተው እንደ መፅሀፍ ታሪኩን እየተገለጡ የሚነበቡ ታሪኩን ጠንቅቀው የሚያውቁ ሰው ናቸው፡፡

ስራው በአጠቃላይ የተጀመረው በ1988 ሲሆን ሜዳው ስራው ሲጀመር ከባድ የሆነ ዝናብ መዝነብ በመጀመሪ እና ጥር የጀመረ እስከ ቀጣዩ ዓመት ጥቅምት ድረስ በመቀጠሉ ስራው በዚህ ዓመት ይጀመር እንጂ ሊቀጥል አልቻለም፡፡

በተነደፈው ዕቅድ መሰረት ሜዳው ይሰራል፣ህንፃው ይሰራል፤የኤሌክትሪክ ስራውም ይቀጥላል፡፡

ኮንትራክተሮቹም አንዱ ሲጨርስ ሌላው የሚቀጥል ሲሆን እነዚህን ሁሉ ማስተባሩም እራሱን የቻለ ስራ ነው፡፡ሁሉም በተያዘላቸው ጊዜ፣የሚያነሷቸው ችግሮች ሁሉ ማስተካከል ትልቅ ስራ ነበር፡፡ይህን ሁሉ ኃይሉ በመስራት ትልቅ ኃላፊነትን ተወጥተዋል፡፡

በዚህ ስራ ላይ በሰብ ኮንትራክተርነት ገብተው ስራውን ያንጓተቱ ኢትዮጵያውያን ኮንትራክተሮች እንደመኖራቸው ጥሩ ስራ ሰርተውም ስማቸው የሚነሳም እንደ አሶሼት ኢንጂነርስ፣ ስለሺ ኮንሰልት፣ኤም ኤች ኢጂነሪንግ መኖራቸውንአቶ ኃይሉ ይናገራሉ፡፡ከዚህም ባሻገር የህግ ጉዳዮችን በመከተታል እና የማማከር ስራዎችን በመስራት አቶ እስራኤል ተክሌ ታላቅ ስራን እንደሰሩ ዛሬም አይዘነጉትም፡፡

አቶ ኃይሉ የአዲስ አበባ ምሁራን ትልቅ አስተዋፅአ አበርክተዋል፡፡በስራው ላይም ጥሩ አበርክቶ ለነበራቸው ኢትዮጵያዊያን ኮንትራክተሮች ዛሬም ምስጋናቸውን ያቀርባሉ፡፡

አቶ ገብርኤሉ ቪታሊ ዮሀንስ ስለ ቦሌ ዓለም ዓቀፍ አየር ማረፊያ ማስፋፊ ሲነሳ የአቶ ኃይሉ ስም በቀዳሚነነት ሊነሳ ይገባል ይላሉ፡፡

አቶ ኃይሉ በጥንካሬ ከሰራን ማንም የሚሰራውን ሰርተን በማሳየት ጥሩ ውጤት ማምጣን እንችላን የሚሉ ሲሆን አብረዋቸው የሚሰሩት ሰዎች የስራ ታታሪነትን ያነሳሉ፡፡

የቦሌ ዓለም ዓቀፍ አየር ማረፊያ ማስፋፊያ በወቅቱ በሀገራችን ከነበሩ ትላልቅ ስራዎች አንዱ ነበር፡፡በመንግስትም ትልቅ ትኩረት ተሰጥት ነበር፡፡አቶ ኃይሉም በጥራት እና በፍጥነት ብዙዎች እንደሚመሰክሩላቸው የማስተባበር ስራን በስኬት ሰርተው ተወጥተዋል፡፡

ይህ ምስክርነት አብረዋቸወ ከሰሩ ባልደረቦችቸው ብቻ የመጣ ሳይሆን እንደ አፍሪካ ልማት ባንክም ያሉ ተቋማት ተዟዙረው ገንዘብ ካወጡበትም ባሻገር ከተመለከቱ በሁዋላ በፕሬዝዳንቶቻው አማካይነት ትልቅ ምስጋናንም ተችረዋል፡፡በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስቴር የነበሩት መለስ ዜናዊም ለ2 ሰዓት ከ30 ደቂቃም እያንዳንዱን ስራ ከተመለከቱ በሁዋላም ሀገሪቷም ምን ያህል እዳ ውስጥ ገብታለች ብለው ይጠይቋቸዋል  እንዴ ሁሉስ ቢሆን በብድር አይደል እንዴ የተሰራው ብለው ሲመልሱ አብረዋቸው የነበሩት አቶ ሀይሌ አሰግዴም ከዋጋው በላይ ስንት ብር አውጠተናል ማለታቸው ነው ሲሏቸውም አቶ ኃይሉም በመጨረሻም ገና ብዙ የሚሰሩ ነገሮች ቢኖሩም በፈረምነው ገንዘብ አልያም ጥቂት ገንዘብን አትርፈን እንጨርሳለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስተሩ ከተቀመጡበት ተነስተው በልጆቾ ይካሱ እንዳሏቸው ይናገራሉ፡፡እነዚህ ሁለቱ ለእሳቸው ትልቅ ቦታ የሚሰጧቸው የሕይወት ዘመን ብርታቶቻቸው ናቸው፡፡

በምድራዊ ህይወት ሁሌም ወጣትነት፣ብርታት እና ጤናማነት ይገኛል ማለት አይቻልም፡፡በኢትዮጵያ የሲቪል አቪየሽን ታሪክ ጉልህ አሻራ ያኖሩት አቶ ኃይሉ በዛን ሰሞን ህመም አጋጥሟቸው ነበር፡፡ለስራ ጉዳይ ወደ ጀርመን አምርተው በዛውም የህክምና ምርመራ ሲያደርጉ ከባድ ደረጃ ላይ የደረሰ የፕሮስቴት ካንሰር እንዳለባቸው እና ቀዶ ጥገና እንዲያደርጉ ይነገራቸዋ፡፡ከዛ ሁሉ ድንጋጤ እና ፍርሃት በሁዋላ በባለቤታቸውም ጥረት እና በስራ በሚያውቋቸው ጓደኞቻው አማካይነት ለሁለት ወራት ህክምናውን ተከታትለው ተመለሱ፡፡

እረፍት ለምኔ የሆኑት አቶ ኃይሉ ከህክምናው መልስ ወደ ስራ እንደገቡ ሌላ ህመም አጋጥሟቸው ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ገቡ፡፡አሁንም በስራ የሚያውቋቸው ደቡብ  አፍሪካ ያሉ ጓደኞቻው አማካይነት ወደ እዛው እንዲያመሩ ተደርገው አሁንም የአንጀት ካንሰር ተብለው ትልቅ የሆነ ቀዶ ጥገናን አደረጉ፡፡ይህም ሁሉም ስላለፈ ዛሬም ሁሉንም አመስጋኝ ናቸው፡፡

የቦሌ አየር ማረፊያ ማፋፊያ ስራ መጠናቀቂያው ላይ ነው እና ይሄ ሁሉ የተከሰተው ሳላየው አንድ ነገር ልሆን ይሆን እንዴ ብለው የፈሩት አቶ ኃይሉ ሁሉን አልቆ ሲያዩት ትልቅ ተስፋን ያገኘሁበት ዳግም የመወለድ ያህል የተሰማኝ ጊዜ ነው ይላሉ፡፡

በውጪ ያለው ክብራቸው እንዳለ ሆኖ በቤት ውስጥ ደግሞ ለእኔም ሆነ ለልጆቼ ትልቅ መምህራችን እና መሪያችን ነው ይሏቸዋል ባለቤታቸው፡፡

ልጃቸው አሉላም ‹‹የአባቴ ትልቅ ተፅእኖ ያለብኝ ሲሆን ዛሬም ቢሆን ለገንዘብ እና ለትርፍ ብቻ እናዳልሰራ አዲስ ነገርንለማወቅ እና ለሰው ለማሳወቅ እንድሰራ አድርጎኛል፡፡ምን ያህል አዋቂ እንደሆነ አሁን ነው የሚገባኝከእርሱ ጋር ጊዜን አለማሳለፌ ይቆጨኛል››ባይ ነው፡፡

 

ባለታሪኩ አቶ ኃይሉ መስራት ብቻ ሳይሆን መዝናትን የሚያውቅም ሰው ናቸው፡፡ዛሬ ሰማንያዎቹ አጋማሽ ላይ ሆነውም ለሲንፈኒ ሙዚቃ የተለየ ፍቅር አላቸው፡፡ስለ ሲንፈኒ ሙዚቃም ሲናገሩ በዕውቀት እና በተመስጦ በተሞላ መልኩ ነው፡፡ በእንግሊዝ ተማሪ እያሉ ነው ስለ ትላልቆቹ ሲንፈኒ እና ሙዚቃዎች ማወቅ የጀመሩት፡፡ከሁለተኛ ደረጃ ጀምሮ የሚያውቁት ጓደኛቸው አቶ አረፋይኔ አብርሃም ከእሳቸው ቀድሞ ለትምህርት ወደ እንግሊዝ ሄዶ ነበር እና እዛ ያለውን ነገር ያውቅ ነበር ከዛ በበላይ ገንዘብን ሲያገኙ ክላሲካል፣ግሬት ጃዝ እና የሲንፈኒ ሙዚቃን እንዲያውቁ አግዟቸዋል፡፡ለአቶ ኃይሉ የሩሲያ ሙዚቀኛው ቻኮስኪ ደግሞ የሙዚቀኛ  ምርጫቸው ነው፡፡

ይህንን የሙዚቃ ፍቅራቸውን ልጃቸው አቶ ኃይሉም ሲገልፀው በጣም ብዙ የሸክላ ሙዚቃዎች እንደነበሩዋቸው ነው፡፡ከነዚህም ውስጥም የክላሲካል ሲንፈኒ አንድናቂ በተለይ ደግሞ የቻኮስኪን ሙዚቃ ከምሳ ሰዓት በሁዋላ በጣም በማጣጣም መፅሀፍ እያነበቡ ያዳምጡ እንደነበር ውስጣዊ የሆነ ደስታም እንደሚሰማቸው ነው፡፡

ከሀገር ውስጥ ሙዚቀኞች ደግሞ ድምፃዊት ፀሀይቱ ባራኺ ምርጫቸው ናት፡፡

እድሜያቸውን ለስራ የሰጡ ብቻ ሳይሆኑ አንድ መስሪያ ቤት ላይ ረዥም ዓመታትንም ያሳለፉ ሠው ናቸው፡፡ ጓደኞቻቸው እንደሚመሰክሩላቸውም ሌላ ሰው በሳቸው ያህል አንድ ሰው አንድ ስራ ላይ መቆየታቸው ያስገርማቸዋል፡፡እንደውም እኔ ስራሴ አላደርገውም ሲሉ ነው የሚናገሩላቸው፡፡

አቶ ሚካኤል ስለ አባታቸው ሌሎች ሲናገሩ በደስታ እንደሚነዘራቸው ሁሉ ያስታውሳሉ፡፡ኢትዮጵያ እንዲህም ዓይነት ሰው አላት ተብሎ ሲነገር መስማት ታላቅ ሐሴትን ያጎናፅፋቸዋል፡፡የእሳቸው ልጅ በመሆናቸውም ኩራታቸው ከፍ ያለ ነው፡፡እስከ ዛሬ ላበረከቱት ሁሉ የሚገባቸውን አልተደረገላቸውም ስማቸውም አልተወሳም ቢሉም ታሪካቸውን እና ለሐገር ያበረከቱትን አስተዋፅኦ ተወዳጅ ሚዲያ አናነ ኮሚኒኬሽን ሰንዶ በማስቀመጡ ምስጋናቸው ከፍ ያለ ነው፡፡ረዥም እድሜ እና ጤናን ሰቷቸውም ለሀገር ሆነ ለተተኪው ትውልድ መነሳሻ እና ትልቅ መማሪያ እንዲሆኑ ምኞቱ ነው፡፡
አቶ ኃይሉ ገ/ማርያም በልጆቻው እና በጓደኞቻቸው ብቻ ሳይሆን በልጅ ልጆቻቸው የሚመሰከርላቸው በትውልድ ሽግግሮሽም ታላቅ አሻራን ያሳረፉ ታላቅ ሰው ናቸው፡፡

የልጅ ልጃቸው የሆነው ካሊ ብሩክ ‹‹በልጅነቴ አያቴ ደስ የሚሉ ታሪከችን ይነግረኝ ነበር፤እኔም ተመስጬ አዳምጠው ነበር፡፡ካደኩኝ በሁዋላም ለእኔ አና ለእህቴ በልጅነቱ ስላሳለፍ ታሪክ ሁሉ ነግሮናል፡፡በሚሰራበት ሲቪል አቪየሽን እና ቦሌ አየር መንገድ ወስዶ አስጎብኞቶኛል፡፡አያቴ ሀገራችንን በመወከል ብዙ ስብሰባዎችን ተካፍሏል፡፡እኔም እንደ አያቴ በደንብ ተምሬ ሀገሬን ማስጠራት ፈልጋለሁ፡፡አያቴ መልካም ፣አዋቂ እና ሀገሩን የሚወድ ሰው ነው፡፡››ሲል ምን ያህል አያቱ ተፅዕኖ በልጅ ልጆቻቸው ላይም እንዳላቸው ማሳያ የሆነ ምስክርነነትን ገና በታዳጊነቱ ይሰጣል፡፡

ሌላኛው የአቶ ኃይሉ የልጅ ልጃቸው የሆነችው የአስር ዓመቷ ሊና ብሩክ ስለ አያቷ‹‹አያቴን በጣም ነው የምወደው፤ያልገባኝን ነገሮች ሁሉ ስጠይቀው ይመልስልኛል፡፡ደስ የሚል ጨዋታም ያጫውተኛል፡፡አያቴ ድሮ ስለ ነበሩ ታሪኮች እና ስላሳለፋቸው ደስ የሚሉ ታሪኮች ይነግረኛል፡፡ከአያቴ ጋር ማውራት፣ጥያቄን መጠየቅ እና መጫወት ያስደስተኛል፡፡እሱ ደግ እና ታታሪ እንደሆነ ማወቄ እኔም ጎበዝ ልጅ እንድሆን አስችሎኛል፡፡››ስትል እድሜዋ ትንሽ ቢሆንም በልጅነት አንደበቷ አያቷን ማወደስ አላገዳትም፡፡የእሳቸውን አበርክቶ በእርሷ ላይ ያሰደሩትን ሁሉ ትናገራለች፡፡

የልጃቸው የአቶ ብሩክ ባለቤት የሆኑት ወ/ሮ አንቀጽ አቶ ኃይሉን ከአስራ ስድስት ዓመት በፊት ማወቃቸውን አንስተው  ‹‹ምንም የባለቤቴ አባት በቢሆንም እንደ አባቴ ይሰማኛል፡፡ጋሽ ኃይሉ አስደናቂ እና ደስ የሚል ህይወት ያሳለፈ የቤተሰባችን መሪ እና በህብረተሰባችንም ውስጥ ትልቅ ቦታ ያለው ሰው ነው፡፡ጋሽ ኃይሉ ሃሳቡን ፊት ለፊት ለመግለፅ የማይፈራ ፣ተጫዋች፣ለሠው አዛኝ፣ ማንበብ የሚወድ ፣ባለቤቱን እና ልጆቹን በአጠቃላይ ቤተሰቡን የሚያከብር እና የሚወድ ሰው ነው፡፡ሁል ጊዜም ዕውቀቱን ፣ጊዜውን እና ፍቅሩን ያለ ስስት የሚሰጠን እና ለእኛም ለልጆቻችንም አርዓያ የሚሆነን የምንወደው አባታችን ነው፡፡እድሜ እና ጤናን ሰጥቶት ከእኛ እና ከልጆቻችን ጋር ላሳለፍነው ጊዜ እግዚአብሄርን አመሰግነዋለሁ፡፡›› ስትል አባታዊ ፍቅር እና ሰስት ስለ እሳቸው ስትመሰክር አቶ ኃይሉ በስራ ብቻ ሳይሆን በቤተሰብም ምን ያህል ስኬታማ እንደሆኑ የሚያሳይ ነው፡፡

በአቶ ኃይሉ ገ/ማርያም የህይወት ፍልስፍና መስራት የማሸነፍ አንዱ መንገድ ነው፡፡ለሀምሳ አምስት አመት በአቪየሽን ሙያ ያለ አንዳች መሰልቸት መቆየት ታላቅ የሆነ ትዕግስትን ይጠይቃል፡፡አሁንም ቢሆን አንድ የአቪየሽን ባለሙያም ቢሆን ከእኚህ ተነበው ከማያልቁ ታላቅ ምሁር በርካታ ዕውቀትን መቅሰም ይቻላል፡፡

አቶ ብርሀኑ አቶ ኃይሉ ለሜትሮሎጂ ሳይንስ ያላቸው ፍቅር የሚታየው በሀገራችን የሚከሰተውን የአየር ሁኔታ በመከታተላቸው ነው፡፡አንድ የተለየ የአየር ሁኔታን ሲያዩ በመደወል እንደሚያረጋግጡ ያነሳሉ፡፡የኢትዮጵያ የሜትሮሎጂ ኤጀንሲም ከኢትዮጵያ የሲቪል አቪየሽን ባለሙያ ተለይቶ ራሱን ችሎ እንዲቋቋም በተደረገው ሂደት እና አሁን ላይ ኤጀንሲው ላለበት እድገት የአቶ ኃይሉ አሻራ ከፍተኛ መሆኑን ቋሚ ምስክር ናቸው፡፡ካላቸውም ቅርበት አንጻር ስለ አቶ ኃይሉም ባህርይ ሲያነሱ‹‹ረጋ ያለ፣ልታይ ልታይ የማይል ፣ትሁት ፣ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ተሳታፊ ፣ሰው አክባሪ እና ሀገር ወዳድ መሆናቸውን መሰክራለሁ፤ለአቶ ኃይሉ ስራውን በስኬት እንዲወጣ የጀርባ አጥንት ሆና አስተዋፅኦ ያደረገችውን ክብርት ባለቤቱን ወ/ሮ አሰፋሽን አመሰግናለሁ፡፡››ሲሉ ነው፡፡

በጣም አንባቢ መሆናቸውን ሌሊት እንኳ እንቅልፍ እንቢ ቢላቸው መፅሀፍ ማንበብ ልማድ እንዳላቸው እና የበርካታ ሀገራት መፅሀፍ እንዳላቸው ባለቤታቸው ይናገራሉ፡፡በስራቸው ውጤትም እንደሚኮሩ ይናገራሉ፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለምን የጀት በረራ እንደማይጀምር ቢጠይቁም የሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን ፈቃደኛ ከሆነ ይቻላል እንዲሁ እንዲሁ የሲቪል አቪየሽን ባለስልጣንም የኢትዮጵያ አየር መንገድም ፈቃደኛ ከሆነ መጀመር ይቻላ በሚል በሁለቱ ፊት ለፊት አለመገናኘት ያልተሰራ ቢሆንም አቶ ኃይሉ ግን ሁለቱን እርስ በርስ በማገናኘት እንዲነጋገሩ አድርገዋል፡፡በአጭር ጊዜ ውስጥም የጀት  አውሮፕላን በረራ አክሱም ማረፍ ጀመረ፡፡ይህ ስራ መሳካት ትልቁ ድካም የአቶ ኃይሉ መሆኑን ጓደኞቻቸው ይመሰክራሉ፡፡

 አቶ ኃይሉ ቢበሳጩም ቶሎ ሚረሱ በተለይ በስራቸው የሚቀይሩ ሰው ናቸው፡፡ጡረታም ከወጡ በሁዋላ ወደ ስራ እንዲመለሱ ተለምነው የነበረ ቢሆንም ባለቤታቸው ይቅርብህ ብለዋቸው ብረዳቸው ይሻላል በማለት ለሀገራቸው ያላቸውን ፍቅር ያሳዩ ናቸው፡፡

ተወዳጅ ሚዲያ እና ኮሚኒኬሽን ባደረገው ጥናት በአቪየሽን ዘርፍ በአማርኛ የተፃፉ መፅሃፍት እምብዛም ናቸው፡፡እንደ አቶ ኃይሉ ያሉ ሰዎች በዚህ ዘርፍ የራሳቸውን አስተዋፅኦ ቢያበረክቱ ይላል፡፡

ቀደም ሲል ካነሳነው የልጅ ልጆቻቸው ምስክርነት በተጨማሪም የስምንት ዓመቱ የልጅ ልጃቸው ናትና  ሚካኤል ኃይሉ‹‹አንድ ቀን እኔ እና አባቴ ትምህርት ቤት ስንሄድ በትምህርት ቤት በተሠጠኝ ፕሮጀክት ላይ አየር መንገድ ሰራሁ፡፡አስተማሪያችን ደግሞ በስራው ዙሪያ አንድ ሠው ቃለ መጠይቅ አድርጉ ብላን ነበር፤ስለዚህ ማንን ባደርግ ይሻላል ብዬ አባቴንም ከነገርኩት በሁዋላ በደንብ ስለ ጉዳዩ የሚያውቀውን አያቴን ቃለ መጠይቅ አደረኩለት፡፡እንደዚህ ያለ አያት ስላለኝም ኮራሁ፤አያቶቼ እወዳችሁዋለሁ፡፡››ሲል በጣፋጭ አንደበቱ አያቱን ያመሰግናል፡፡

የናትና ታናናሽ እህት የሆነችው የሰባት ዓመቷ ሄለን ሚካኤል ኃይሉ ደግሞ ‹‹አያቶቼ ለሀምሳ ዓመት በዓላችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ፤የሚወዱኘ እና የምወዳቸው አያቶች ስላሉኝ ደስ ይለኛል፡፡እወዳችኋለሁ፤ኑሩልኝ፣እግዚአብሄር ጤናችሁን ይጠብቅ፡፡››ስትል አያቶቿን በኮልታፋ አፏ በልጅነት ልባዊ እና ውስጣዊ ዕውነታ ትመርቃለች፡፡

የአምስት ዓመቷ ማያ ሚካኤል ኃይሉም የአያቷን አስተዋፅኦ ለመናገር ልጅነቷ አላገዳትም፡፡እንደ እህቷ ለአያቶቿ መልካም የሀምሳ አመት መልካ ምኞትን ተመኝታ የአያቶቿ ምን ያህል እንደሚያጫውቷት በመናገር ፍቅሯን ትገልፃለች፡፡

ወ/ሮ አምሳለ ዮሴፍ የአቶ ኃይሉ ልጅ የአቶ ሚካኤል ባለቤት ናቸው፡፡የእነሱ የትዳር አብሮነት ቆይታ ለእነሱም ምሳሌ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡በተወዳጅ ሚዲያ እና ኮሚኒኬሽን የአቶ ኃይሉ ታሪክ መሰራቱ ደገፊ በመሆናቸው ደስተኛ ናቸው፡፡

እንደ አቶ ኃይሉ ያሉ ታላላቅ ሰዎች ታሪክ እየተረሳ እንዳይመጣ ልጆቻቸው ይህንን  ታሪክ በማስቀረት ስራ ትልቅ አስተዋፅኦ አላቸው፡፡አባታቸው በተለያዩ ጊዜያት የህይወት ታሪካቸውን ለማስቀረት ቢሞክሩም ጊዜው እየረዘመ በመምጣቱ ታሪክ እንዳይረሳ ነገም ምን እንደሚመጣ ስለማይታወቅ በዚህ መልኩ ታሪካቸውን በማስቀመጥ ረገድ ትልቅ ስራን ሰርተዋል፡፡

 

  መዝጊያ ፤ ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡  

ባለ ታሪካችን አቶ ኃይሉ በኢትዮጵያ የአቪየሽን ታሪክ ውስጥ የመጡትን የእድገት  ደረጃዎች ጥንቅቅ አድርገው ከማወቃቸውም በላይ በውስጡ ያለፉ የማይረሳ  ኗሪ የሆነ የሚታይ አሻራን እያሳለፉ የመጡም ናቸው፡፡ዘመናቸውን ከኃ/ስላሴ ጀምሮ በደረጃ በስራ ዘርፋቸው የሰሯቸው ስራዎቻቸው ምስክሮቻው ናቸው፡፡

በቅርቡም ቢሆን አቶ ኃይሉ በተለያዩ  በአፍሪካ የአቪየሽን መስሪያ ቤቶች ውስጥ እንዲሰሩ እና አቅማቸውን እንዲያወጡ ቢጠየቁም በሀገራቸው መሆንን መርጠዋል፡፡

የዛሬ ሁለት ዓመትም ሦስተኛው የአየር ማረፊያ ለአዲስ አበባ መጠናት አለበት ተብሎ አማካሪ መርጠው የፈረንሳይ ቡድን አጥንቶ ነበር፡፡ በዚህም ውስጥ ተሳታፊ ነበሩ፡፡፡፡በዚህም የተመረጠው ሜዳም ከአዲስ አበባ አርባ እና ሀምሳ ኪ.ሜ ወደ ደቡብ አቅጣጫ ርቀት ያለው ያለ ቦታ ነው፡፡ በዚህ እድገት ከተሄደም ሀያ ሁለት ሚሊየን መንገደኛን በአስራ አምስት ዓመት ተደራሽ ለማድረግ መሰራት አለበት፡፡እድገቱንም የሚፈልጉ አካላትም ይሄንን ስራ ቢቀጥሉበት የሚል ምክረ ሃሳባቸውን ያቀርባሉ፡፡

በህይወት መስመራቸው ላሳለፉት ሁሉ አቶ ኃይሉ አመስጋኝ ናቸው፡፡ኋላቸውን የሚያዩ ነጋቸወን  አሻግረው የሚመለከቱም ሰው ናቸው፡፡መሰናክሎቻቸው ያጋጠሟቸው ህመሞች አልፈው በየጊዜው እየፃፉ ያስቀመጣቸው ፅሁፎች እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡በመሀል ዓይናቸውን ስላመማቸው እንዲሁ በአቪየሽን ድጋሜ በመፈለጋቸው መዘግየቱን ይናገራሉ፡፡

መለመንን ፍፁም የሚጠሉት አቶ ኃይሉ ሁሉም ጠንክሮ ነገሮችን በማመቻቸት ሀያ አራት ሰዓትን በመስራት ሀገራችንን ለማሳደግ ይቻለናል፡፡ለዚህም ሁሉም ሰው መረባረብ አለበት ባይ ናቸው፡፡

የባለቤታቸውን ምክር የእርሳቸው ከጎናቸው መኖር ለእያንዳንዱ እርጃቸው ጠቃሚ እና አሻጋሪነቱን ይመሰክራሉ፡፡አመስግነዋቸው አይጠግቡም ምስጋና ያንሳታል ግን ከምስጋና በላይ ምን ይሰጣል ይላሉ፡፡በአጠቃላይ በህይወት ውጣ ውረድ ሁሉ አብረዋቸው ለነበሩት ዛሬም አመስጋኝ ናቸው፡፡

ሀገራችን ዛሬም ሰው እንዳሏት ማሳያ የሆኑ ታሪክን፣ዕውቀትን፣ማንነትን አሻጋሪ ሰዎች መካከል አንዱ አቶ ኃ/ገብረማርያም ናቸው፡፡ ድርጅታችን ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒሽን በአቶ ሀይሉ ገብረማሪያም ላይ ትኩረቱን ያደረገ የ100 ደቂቃ የድምጽ ዶክመንተሪ ግንቦት 30 2012 አዘጋጅቷል፡፡ ይህ የድምጽ ስራ ብዙዎች ምስክርነት የሰጡበትና በጥልቀት የተሰናዳ ስለነበር በተለይ በሲቪል አቬሽን ላይ ምርምር ለሚያደርጉ ሰዎች ጥሩ ግብአት የሚሆን ነው፡፡ በመሆኑም የአቶ ሀይሉ ቤተሰቦች በተለይም ልጆቻቸው የአባታቸው ታሪክ እንዲሰነድ ያደረጉትን ጥረት በእጅጉ ማድነቅ እንሻለን፡፡

እሳቸውን ማወቅ ሀገርን፣የአቪየሽን ሙያን ፣የህይወት ጉዞን ፣መፅሀፍን፣ሙዚቃን ፣ዕውነትን ማወቅ ነውና እወቋቸው፡፡እኛ ይሄንን ብለናል፡፡ነገውን የሚያልም ሁሉ ዕውን ለማድረግ ታሪክን ያሻግር፣ባለውለታዎቹን ይወቅም ያክብርም እንላለን፡፡አበቃን፡፡

 


 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 


አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች