ሀቢባ ፋሪስ ጀማል
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የሚድያ ሰዎችን የህይወት እና የስራ ታሪክ እያሰባሰበ ይገኛል፡፡ ከዚህ ቀደም የ180 የሚድያ ሰዎችን ታሪክ በጠንካራ ሽፋን መጽሀፍ አሳትመን ማስመረቃችን ይታወሳል፡፡
አሁን ደግሞ ቅጽ 2 እያዘጋጀን ስለሆነ የሚድያ ሰዎች የሚድያ መሪዎች የስነ-ጽሁፍ ሰዎች የህይወት ታሪካችሁን በመስጠት ወይም ፈቃደኛ በመሆን ትብብር እንድታሳዩ በታላቅ ትህትና እንጠይቃለን፡፡ በዚህ ጽሁፍ የህይወት ታሪኳን የምናይላት የሚድያ ሰው ወይዘሮ ሀቢባ ፋሪስ ትባላለች፡፡ በሚድያ ስራ 24 አመት የቆየች ሲሆን በአሁኑ ሰአት የኢቢሲ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ በመሆን እያገለገለች ትገኛለች፡፡
ሀቢባ ለረጅም ጊዜ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሰራች ሲሆን በዋልታ ቲቪ እና በኤልቲቪ ላይ በስራ ሃላፊነት ሙያዊ አደራዋን ተወጥታለች፡፡ እዝራ እጅጉ ታሪኳን እንደሚከተለው ያቀርበዋል፡፡
ትውልድ እና ልጅነት
ወቅቱ የደርግ መንግስት ወደ ስልጣን የመጣበት አብዮት በአል በደማቅ የሚከበርበት፤ ክረምቱም ተጠናቆ አዲሱ አመት በአዲሰ ተስፋ በአል የሚደምቅበት እለት ነው፡፡ መስከረም 1 ቀን 1968 ዓ.ም ድንገት የመጀመሪያ የሆነ አንድ እንግዳ በአቶ ፋሪስ ጀማልና ወይዘሮ ፋጡማ ጀማል ቤት መወለዱ ይበሰራል ፡፡ በጋንዲ ሆስፒታል የነበረው የውልደት የምስራች ዜና ለበአላት በተንቆጠቆጠው አበባ ታጅቦ ፣ ይህችስ ልጅ አበባ ናት የሚል የቤት ሰም እንዲወጣላት ምክንያት ሆኗል፡፡የጋዜጠኛ ሃቢባ ፋሪስ፡፡
ትውልዷና እድገቷ አዲስ አበባ በተለምዶ ቄራ ‹‹መብራት ሀይል›› ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው፡፡
ሀቢባ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን በአካባቢው በሚገኘው ሀዋሪያ ጴጥሮሰ ከ1 እሰከ 3 አጋዚያን ቁጥር 1 ከ4 እስከ 5 አፄ ዘርአያያእቆብ ደግሞ ከ6 እስከ 8 ተምራለች፡፡ የመጀመሪ ደረጃ ትምህርት ቤት የመቀየሯ ምክንያትም እናቷ የተሻለ ትምህርት ውጤት እንድታመጣ ከነበራት ፍላጎት እንደነበርም ትናገራለች፡፡ የእናቷ ውጤት ሰምሮ ከስድሰተኛ ከፍል ጀምሮ የደረጃ ተማሪ መሆን እንደቻለች ትናገራለች፡፡
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ደግሞ ግንቦት 20 ተምራለች፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ሰፔሻል ክፍል ተማሪ ነበረች፡፡ በትምህርት ቤቱ በነበሩ ክበባት ንቁ ተሳተፎ የነበራት ሲሆን በኪነጥበባት ክበባት በሙዚቃ ምርጫና የአጫጭር ልቦለዶችን በማቅረብ የነበራት ተሳትፎ ጥሩ የእናቷ አለማቀፍ ድርጅት ውስጥ መስራት መጽሀፍ አንባቢ እንድትሆን ትልቅ እድል ፈጥሮላታል፡፡
ተወልዳ ያደገችበት አካባቢ በአረንጓዴ ዛፎች የተከበበ በመሆኑ ለተፈጥሮ ልዩ ፍቅር ሊኖራት ችሏል፡፡
ሀቢባ ለቤተሰቡ የመጀመሪያ ልጅ ስትሆን ሶስት ወንድሞችም አሏት፡፡
የሚድያ እና የጥበብ ዝንባሌ
ማትሪክ በወሰደችበት 1988 አ.ም ወጤት እስኪወጣ ባሉት የክረምት ጊዜያት የልጅነት ህልሟ የሆነውን የስነጽሁፍ ት/ቤት በማፈላለግ በርካታ አርቲስቶችን ባፈራው በጋሸ ተስፋዬ አበበ ማሰልጠኛ ማእከል በመግባት የጋዜጠኝነት ሀሁ ትምህርት ጀመረች፡፡
በ1989 ዓ.ም መጀመሪያ አመት ማስ ሚዲያ ኢኒስቲትዩት ለመጀመሪያ ጊዜ በሰራ ላይ ላሉ ጋዜጠኞች ሰልጠና ሊሰጥ በተጨማሪም አዳዲስ ተማሪዎችንም ሊቀበል ማሰቡ ተሰማ፡፡ እናም በወቅቱ እንዲገቡ ከተፈቀደላቸው 20 አዳዲሰ ተማሪዎች አንደኛዋ በመሆን በውድድር በማሸነፍ የትምህርት ተቋሙን ተቀላቀለች፡፡ ከሁለት አመት የዲፕሎማ ትምህርት በኋላ ኢዜአ ባወጣው ማስታወቂያ ተወዳድራ ሚያዚያ 18 1991 አ.ም በጀማሪ ሪፖርተርነት ስራ ጀመረች፡፡
የኢ.ዜ.አ ቆይታ
በወቅቱ አንጋፋ ጋዜጠኞች የነበሩበት ስለሺ ተሰማ፣ ዳሪዮሰ ሞዲ አሰፋ በቀለ ሀሳቡ ቀፀላና ሌሎች አንጋፋ ጋዜጠኞች የነበሩበት ኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት የተጀመረበት የኢህአዴግ ግምገማ የበዛበት በመሆኑ አብዛኛው ጋዜጠኛ በወቅታዊ ዜና ተጠምዶ ነበር፡፡
ጀማሪ ተብለው የተቀጠሩት ሀቢባ ፋሪስ እና ሃይማኖት ዘለቀ በራስ ታቅዶ የሚሰራ ዜና እንዲያመጡ ታዘዙ፡፡
እናም በጋራ ሁለቱ ሀቢባ እና ሀይማኖት ደረጃዎች ባለስልጣን በማቅናት የመጀመሪያ የሆነውን ዜና በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ የገባ ተቀጣጣይ ክብሪት በቁጥጥር ሰር ዋለ የሚል ዜና ሰርተው ለሚዲያዎች ተላከ ፡፡ሁሉም ሚዲያዎቸ ተቀባበሉት፡፡ መነጋገሪያ ሆነ፡፡ ይህ የመጀመሪያ ዜና ለመጀመሪያዎቹ መነቃቃትን በመፍጠሩ ከዚያን እለት ጀምሮ የህዝብ ቅሬታ የመልካም አስተዳደር ችግር፤ የውሃ የመብራት እያሉ መስራት ጀመሩ፡፡ ወቅቱ የጦርነት በመሆኑ ህዝቡን የመታሰለቀሱበት ጊዜ አይደለም ተሰፋ የሚሰጡ ዜናዎችን ሰሩ ተብለን ትእዛዝ ተሰጠን
እናም የዜና ስራዎቻቸው ገቢ ተገኘ፡ ማእደን ተገኘ በሚሉ ዜናዎቸ ተቀየሩ፡፡
በወቅቱ ከተሰሩና በተለያየ መንገድ ተጽእኖ ፈጥረው ከነበሩ ስራዎች መካከል ኢትዮጵያን ለመቶ አመት የሚያኖር የጨው ክምችት መገኘቱ፤ የከሰል ድንጋይ ፋብሪካ በእያዩ ሊገነባ መሆኑና ምንም እንኳን ስራው ባይጀመርም በተከታታይ ዜና ችግሩንም የሚያሳይ ስራ ሊሰራ ችሏል፡፡
ሀቢባ በጋምቤላ ክልል የነዳጅ ክምችት እንደተገኘ የሰራችው ዜና በአለም አቀፍ ደረጃ መነጋገሪያ ለመሆን የቻለና በጋዜጠኝነት ህይወቷ ዜና ከተለያየ አንግል ማየት እንዳለባት የተማረችበት ነው፡፡
በተመሳሳይ፤ ኢትዮጰያ ለጅቡቲ ውሃ ልትሸጥ ነው የሚለው ዜና በማህበረሰቡ ዘንድ ፈጥሮ የነበረው ስሜት ዜናና የሚያመጣውን ተጽእኖ በሚዛኑ ማየት እንዳለባት የተረዳችባቸው ጊዜያቶች ናቸው፡፡
ሀቢባ በጋዜጠኝነት ሕይወቷ ደስ ብሏት ከሰራቻቸው ዜናዎች የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሊገነባ የመሆኑ ዜና ነው፡፡ ያኔ የመንግስት ኮሚኒኬሸን የሰጠው የመጀመሪያ መግለጫ ጉዳዩ በግልጽ ስለምን እንደሆነ ያልተነገረበት ሁሉም በዜናው የተደናገጠበት ነበር፡፡ ሀቢባም በጊዜው መረጃውን በሚገባ በማጠናከር ተገቢውን ኢንፎርሜሽን ሰጥታለች፡፡
ሀቢባ ፋሪስ እንዲህ ትላለች ‹‹ በጣም ካዘንኩባቸው ሌላው ዜና በ1999 ዓ.ም ኢዜአ እንዲፈርስና ወደ መንግሰት ኮሚኒኬሸን እንዲቀላቀል የተደረገበትን የፓርላማ ውሎ ዜናዬ እንባዬን እያፈሰስኩ የሰራሁት ዜና ነበር›› በማለት ከ16 አመት በፊት የነበረውን ትዝታዋን ታወጋለች፡፡
በኢዜአ ለ15 አመታት ከሪፖርተር ጀምሮ እስከ ምክትል አዘጋጅነት ድረስ የሰራች ሲሆን በኢኮኖሚና ዲፕሎማሲ ዘርፍ በርካታ ዜናዎችን ሰርታለች፡፡ በፓርላማ ዘገባዎች፤ቤተመንግስትና ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ከተቋማት ደግሞ ማዕከላዊ ስታትስቲክሰ ገቢዎች እና ማእድን ላይ በብዘት ዜናዎችን ሰርታለች፡፡
ለአጫጭር ሰልጠናዎች ለስራ የተለያዩ አገራት ተጉዛለች፡፡ ጅቡቲ ፤ኬኒያ፤ ታንዛኒያ፤ የመን፤ እንግሊዝ÷ ቻይና ሪያድ ስፔን ቃታር ታይላንድ ቱርክ ህንድ ሌሎች በርካታ አገራትን የማየት እድል አግኝታለች፡፡
ሌሎች ተቋማት
ከሚያዚያ 4 ቀን 2007አ.ም ጀምሮ ዋልታ አዲስ ቴሌቪዥን ለመክፈት በዝግጅት ላይ ስለነበር ዜና ክፍሉን በዳይሬክተርነት በመምራት ስራ ተጀመረ ፡፡በዚህ ጊዜ ውስጥ የዜና ፎርማት ስራዎችን በመሰራት የሰው ሃይል በማደራጀትና ቴሌቪዥኑ ተወዳዳሪ እንዲሆን ጥናቶችን አሰራሮችን በመዘረጋት አሻራ አኑራለች፡፡ በአምስት አመት ቆይታም የዋልታ የይዘት ዘርፍ ስራ አስፈጻሚ በመሆን በርካታ የለውጥ ስራዎች ተግባራዊ እንዲሆኑ አድርጋለች፡፡ በተለይ የህብረተሰቡ ጥያቄ ምላሸ እንዲያገኝ የአመራርነት ሚናዋን በሚገባ ተወጥታለች፡፡ ለ11 ወራት በኢል ቲቪ የዜና ዳይሬክተር ሆኖ በመስራትም ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆኑ የውይይት ፕሮግራሞችን ተግባራዊ በማድረግ የቡድን ስራ በማጠናከር አሻራዋን ማኖር ችላለች፡፡
በአዲስ ሚዲያ ኔት ወርክ በምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚና ቴሌቪዥን ዘርፍ ሀላፊ በመሆን አገልግላለች፡፡ አስር ወራት አጭር ጊዜ ቢሆንም ተቋሙ የራሱ የሚዲያ ኮምፕሌክስ እንዲኖረው ፕሮፖዛል እስከማዘጋጀት ሳተላይት የራሱ ቦታ እንዲኖረው እንጦጦ ቦታ ወስዶ ስራ የማስጀመር ሰራ መሰራቱን ሀቢባ ትናገራለች፡፡
ይዘቱ ከተማዋን እንዲመጥን የሚያስችል የፎርማትና የሚዲያ ሚናን የመለየት ሰራም በጊዜው በወጉ መሰራቱን ሀቢባ ትናገራለች፡፡
በአሁኑ ሰአት በኢትዮጰያ ብሮድካሰት ኮርፖሬሸን ምክትል ዋና ሰራ አሰፈጻሚና የቴሌቪዥን ዘርፈ ሀላፊ ሆና እየሰራች ነው፡፡ በአሁኑ ሰአት ኢቢሲ የራሱ የሚድያ ኮምፕሌክስ ያለው ከስራ ሃላፊዎቿ ጋር በመሆን ለዚህ ሚድያ ኮምፕሌክስ የበኩሏን ጥረት አድርጋለች፡፡ ሀቢባ ሁሉንም የስራ ባልደረቦቿን በተለይም የኢቢሲ ዋና ስራ አስፈጻሚን በዚህ አጋጣሚ ማመስገን ትፈልጋለች፡፡
በጋዜጠኝነት መያዋ በስራ ምክንያት የሚነሱ መታየት ያለባቸውን ችግሮች ምላሽ እንዲያገኙ ከሞያ ባሻገር ፖለቲካል ተሳትፎዋን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ በማመኗ ለውጡን በመቀላቀል የምክር ቤት አባል በመሆን ከህብረተሰብ ጋር በቅርበት እየሰራች ትገኛለች፡፡
የ21 አመት ወንድ ልጅና የ20 የ17 የ10 አመት ሴት ልጆች እናትም ነች፡፡
የትምህርት ደረጃዋም ከዲፕሎማ እስከ ማስተርስ መድረስ ችላለች፡፡ ሀቢባ በባልደረቦቿ እና በአለቆቿ ስሟ በመልካም የሚነሳ የሚድያ ሰው ስትሆን ኢዜአ ሳለች አለቃዋ የነበረው ዶክተር ተሻገር ሺፈራውም ሀቢባ ለስራዋ የተሰጠች ብርቱ ከሚባሉ ጋዜጠኞች መካከል አንደኛዋ መሆኗን መስክሯል፡፡
ስለ ሀቢባ የተሰጡ ምስክርነቶች
ሀቢባ በሞላልኝ ከሳቴብርሀን አንደበት
ከሃቢባ ጋር የተዋወቅነው ዋልታ ነው፡፡ በወቅቱ ዋልታ የቴሌቪዥን ስርጭት ለመጀመር ከየሚዲያው ልምድ ያላቸውን ባለሙያዎች ሲያሰባስብ እኔ ከፋና ሀቢባ ከኢዜአ ተጠርተን ዋልታ ተገናኘን፡፡ሃቢባ የዋልታ ቴሌቪዥን የመጀመሪያዋ የዜናና ወቅታዊ ክፍል ዳይሬክተር ስትሆን እኔ ዋና አዘጋጅ ሆኜ ተመደብን፡፡ስለዚህ የቅርብ አለቃዬ ነበረች፡፡
ሃቢባ በባህሪዋ በጣም ቀላል እና ተግባቢ ባትሆን ኖሮ ክፍላችን እነዚያን አስቸጋሪ የቴሌቪዥን ጅምሮ ስራዎቹን ለማሳካት ይቸገር ነበር፡፡ ነገሮችን ቀለል ባለ መልኩ የመገንዘብና የማስረዳት ባህሪይም አላት፡፡ ያው እያወራን ያለነው ስለ ዜና ነው፡፡እንደ ጀማሪ ሚዲያ ዜና ላይ ጥቃቅን ስህተቶች ያጋጥማሉ፡፡ያኔ ከላይ ወዲያው ትኩስ ድንች የሚወረወረው ወደ ሃቢባ ነው፡፡ ሃቢባ ትኩሱን ድንች አብርዳ፣ አቅልላ፣ለሌላ ጊዜ አስተማሪ በሆነ መንገድ ወደ ዜና ክፍሉ ታወርዳለች፡፡እርሷ በደነገጠችበት ልክ እኛን አታስደነግጥም፡፡ ይሄ ባህሪዋ የቲም ስፕሪት ለመፍጠርና የዋልታ ዜና እንዲጸና አድርጎታል፡፡
ሃቢባ የክፍሉን ባለሙያዎች የምትይዘበት መንገድ ውስጡ የጓደኝነት መንፈስን የተላበሰ ነው፡፡ጀማሪ ባለሙያዎች ለዛውም በቁጥራቸው ከአስራዎቹ ያልዘለለ ባለሙያዎች ያለመታከት እንዲሰሩ በማድረግ ውጤት አስመዝግባለች፡፡በዚህ የሰው ሃይል እየተሰራ የዋልታን ዜና ብዙ ቁጥር ካላቸው ሚዲያዎች ጋር ተፎካካሪ እንዲሆን አድርጎታል፡፡
በእርግጥ ሃቢባ ትንሽ ትልቅ፣ሪፖርተር ዋና ስራ አስፈጻሚ የማትል፣ከጥበቃ ጀምሮ ከሁሉም ጋር የምትግባባ ቀለል ያለ ስብእና ስላላት ብዙ ሰው ለሷ ቀና ስሜት አለው፡፡
ሃቢባ ጠንካራ ናት፣አይደክማትም፣ከቤተሰቧ ሰአቷን ቀንሳ ዋልታ ግቢ ውላ ታድራለች ብል ያጋነንኩ አይመስለኝም፡፡ምክንያቱም ዜና መገኘትን እንደሚጠይቅ በውሉ የተረዳች ናት፡፡ከዋልታን ግቢ ትንሽ ዞር ማለት ዋጋን ያስከፍል ነበር፡፡በወቅቱ ዋልታ አልተደራጀም፣በቂ የሰው ሃይልና ዲፓርትመንት የለውም፣የመረጃ ቅብብሎሽ ስርአቱ በኔትወርክ አልዘመነም፡፡ይህንን ጫና ተቋቁማ ተቋሙን አሻግራለች፡፡
ወደ ስራዋ ስንመጣ የህብረተሰቡን ችግሮች የሚቀርፉ፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለማስወገድ የሚያስችሉ ዜናዎች እንዲሰሩ አቅጣጫ ትሰጣለች፡፡አቅጣጫ ብቻም ሳይሆን ከ150 በላይ እቅዶችን ከባልደረቦቿ ጋር በማዘጋጀት የቴሌቪዥን ዜና ባክ ሎግ እንዲሰሩ በማድረግ ያላሰለሰ ጥረት አድርጋለች፡፡በአቀራረብ አሰልቺ የሆኑ በናሬቲቭ የሚቀርቡ ዜናዎች በአንድ አየር ሰአት ላይ እንዳይታጨቁ የተለያዩ ፎርማቶችን በመቅረጽና በማውረድ እንዲተገበሩ አድርጋለች፡፡በወቅታዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች የመንግስት የስራ ሃላፊዎችን ስቱዲዮ በማስመጣት እንዲቀርቡ ታደርጋለች፡፡የቀጥታ ስርጭት ስራዎች እንዲሳኩ ክትትል ታደርጋለች፡፡ከሚዲያዎች ጋር፣ከባለድርሻ አካላት ጋር ዋልታ መልካም ግንኙነት እንዲኖረውም አድርጋለች፡፡
ሃቢባ የቴሌቪዥን ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚም ሆና በመስራት ዜናና ወቅታዊ፣ዶክመንተሪን፣ትምህርታዊና መዝናኛ ፕሮግራሞችን በአንድነት በመምራት በክፍሎቹ መካከል መልካም ግንኙነት እንዲኖር በመስራት ውጤት አስመዝግባለች፡፡በዚህ ቦታ ለዋልታ ሰራተኞች የትራንስፖርት ሰርቪስ ከአንበሳ አውቶብስ ጋር በማመቻቸት ሰራተኞች ስራቸው ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ አድርጋለች፡፡ይህ የተቋሙ የረጅም ጊዜ ችግር በመሆኑ ሳያነሱት ማለፍ አይቻልም፡፡የጋዜጠኞች ጥያቄዎች የነበሩ የአልባሳት፣ የመዋቢያ ክፍሎች ችግሮች እንዲቀረፉ እና ጣቢያው እንዲዘምን ብዙ ሃላፊነትን ተወጥታለች፡፡ባጠቃላይ ጎበዝ ጋዜጠኛና መሪ ነበረች ለማለት እችላለሁ፡፡
ሞላልኝ ከሳቴብርሃን
የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ሀላፊ
ሀብታሙ አሻግሬ ስለ ሀቢባ
ከሀቢባ ፋሪስ ጋር የምንተዋወቀዉ ኢዜአ ዉስጥ ሲሆን ጊዜዉ ደግሞ ከ2005 እስከ 2008 ዓ.ም ነዉ።
ሀቢባ ጠንካራ ነች። የሷ ጥንካሬ መነሻዉ የራሷ ግላዊ ህይወት እንደሆነ ይሰማኛል። በህይወቷ የተፈጠሩ ፈተናዎች ማለፏ የበለጠ እንዳጠነከራት ይሰማኛል።
በመጨረሻዎቹ የኢዜአ ቆይታዋም በፈተናና በጥሩ አጋጣሚዎች የተሞላ ነበር። ከጥቂት የተቋሙ የበላይ ሀላፊዎች ና ኤዲተሮች ፈተናዎች ቢመጡም በድል ተወጥታዋለች።
ለማሳያነት በ2007 ከአርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስትር ጋር ሄደን የሰራችዉ ዘገባ በወቅቱ ከነበረዉ የተቋሙ ዋና ስራ አስኪሀጅ ሳይቀር ዜናዉ ተገልብጦ እንዲሰራ ትእዛዝ ቢሰጣትም ሀቢባን ስላላሳመናት ጥያቄዉን ሳትቀበል በመቅረቷ የተፈጠረዉን ችግር የያዘችበት መንገድ በሳልነቷን ብቻ ሳይሆን ለሙያዉ የተሰጠች መሆኗን ያረጋገጠ ነበር።
በወቅቱ ስሙን መጥቀስ የማልፈልገዉ የተቋሙ አመራር ያለ ሀቢባ ፈቃድ ዜናዉን ገልብጦ ሰርቶት ለህዝብ ተላልፏል።
በነገራችን ላይ ይህ በሷ የተሰራዉ ዜና በ2007ዓ.ም በአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ተቃዉሞ የተቀጣጠለዉን ህዝባዊ እምቢተኝነት የዳሰሰና የተነበየ ስራዋ ነበር። በወቅቱ አልሰማ ያሉ ሀሳብ የለሽ ፖለቲከኞች ለዉጡ ከነ ግሳንግሳቸዉ ደርሶ ጠራርጓቸዋል!
ከዚህ ቀደምም በነበሩ የኤዲቶሪያል ስብሰባዎች በምትሰጣቸዉ የላቁ ሀሳቦች ጥርስ የነከሱባት ሰራተኞች አድመዉባት እንደነበር አስታውሳለሁ። ሀሳቧ አዲስና ያልተሰራበት ስለነበር ለነባር የተቋሙ ኤዲተሮች ከተለመደዉ አሰራር የሚያወጣ ስለሚመስላቸዉ ይረበሻሉ። ሁሉም ባይሆኑ አብዛኞቹ ኤዲተሮች አዲስ ነገር መሞከር ያስፈራቸዉ ነበር።
በየ15 ቀኑ በሚደረግ ግምገማ በሀቢባ የሚመራዉ ዘርፍ ብዙ ጊዜ የላቀ ፈፃሚ ስለነበር የሚረበሹ ሌሎች የዘርፍ አስተባባሪ ኤዲተሮች እንደነበሩ አስታዉሳለሁ።
ከዚህ በኋላ ያደገችበትንና ብዙ በሆነችለት ተቋም መቆየት አልፈለገችም። መገፋቷን ሳትረዳዉ ቀርታ ሳይሆን በምትወደዉ ፍሬያማ ስራ ትፅናና ስለነበር እስከ ጣልቃ ገብነቱ ቆይታ እንደ እስትንፋሷ በምትወደዉ ሙያዋ ሲመጡ ከነክብሯ ኢዜአን ለቃ ወጣች። አገልግሎቷን ይፈልጉ የነበሩና ቀድሞም ይጠይቋት የነበሩ በርካታ የሚዲያ ተቋማት የነበሩ ቢሆንም ዋልታን መረጠች።
ስለ ሀቢባ ሳስብ በሚዲያዉ ዘርፍ ለሚቀላቀሉ አዲስና ወጣት ጋዜጠኞች ሌላ ተቋም እንደሆነች ይሰማኛል።
በርካታ ጥሩ ሰብእናዎች አሏት። ንግግሯ ቀላል ነዉ። የእቅድ ስራዎቿ ጊዜያቸዉን የጠበቁና መፍትሔ አመላካች ናቸዉ። ከእቅድ እስከ ትግበራ ያሉ ስራዎች ላይ ሚናዋ ከፍ ያለ ነዉ። ምልከታዋ ጥልቅ ነዉ። የትኛዉ ጋዜጠኛ ምን አይነት አቅም እንዳለዉ የምትረዳበት አቅም አስገራሚ ነዉ። የቸሰተዉንና ድብርት ያጠቃውን ጋዜጠኛ በአይነ ዉሀዉ ትለየዋለች። የት ወጣህ የት ገባህ ሳይሆን እጅህ ላይና አእምሮህ ዉስጥ ምን አለ ትልሀለች። ፈግታዋ እውነት ነዉ። ከሁሉም በላይ በስሯ ላሉ ጋዜጠኞቿ ለሚፈጠሩ ማንኛዉም ችግሮች መቶ በመቶ ሀላፊነት ትወስዳለች።
አሁን ደግሞ የበለጠ በምትፈተንበትና ራሷን በምታሳይበት ተቋም ዉስጥ እየተመለከትኳት ስለሆነ ደስ ይለኛል።
ሀብታሙ አሻግሬ ከኢቢሲ እንግሊዘኛ ክፍል
ሀቢባ በሊያ ተስፋዬ አንደበት
በቅድሚያ እዝራ ሁሌም ለብርታትህ አድናቆት አለኝ። በመቀጠል የሀቢባን ፕሮፋይል ስለሰራህ በጣም ደስ ብሎኛል ።እኔም ዋልታ እያለች በስራ ሀላፊነት /የበላይ አለቃ/ሆና አውቃታለው። በነገራችን ላይ ሀቢባን አብዛኛው አለያም ሁሉም የዋልታ ባልደረባ ሀቢቢ አሊያም ሀቢቲ በማለት የሚጠራት ሲሆን ሁሌም ፈገግታ ከፊቷ ማሽ አላህ የሚል ቃል ደግሞ ከአንደበቷ አይጠፋም፤ እውነት ለመናገር በስራ ህይወቴ ካጋጠሙኝ ቅን ልብ ከተቸሩ አለቆች መካከል ናት።
በጣም ቀላል የጓደኝነት መንፈስ የምትፈጥር በመሆኗ የኃላፊነት ደረጃዋ የቱ ይሁን እንኳን በቅጡ አላውቀውም። በተለይ የሙስሊም ወገኖቻችን በአል ሲደርስ በተደጋጋሚ አረቢያን መጅሊስ ከሀቢባ ቤት አስመጥተን ስቲዲዩ ቀኑን ሙሉ የበአል ቀረፃ ሰርተናል። እኔ በግሌ ዘናጭ ዘመናዊ ቀሚሷን ከነሂጃቡ ለብሼ የበአል ፕሮግራም ሰርቼ አውቃለው።
ዋልታን ለቃ ለአጭር ግዜ ኤልቲቪ በነበረችበት ግዜም ቅንነቷን ስለማውቅ አንድ በአል መኖሪያ ቤቷ ድረስ ሄጄ ፕሮግራም ሰርቻለው። እውነት ለመናገር እንዲህ አይነት ሰርተው የሚያሰሩ ሰዎች ከራሳቸው አልፈው አንተም ስራህን እንድትወደውና የበለጠ እንድትሰራ ጉልበት ይሆኑሀል። ፤በተቃራኒው አለቅነት አሊያም የስራ ኃላፊነት አንድን ሰራተኛ እ ስንት ሰአት ወጣህ? ገባህ? ብለው ወንበር ብቻ ለሚያሞቁ ጥቂቶች ትልቅ ማሳያ ናት።
እንደሴት የአራት ልጆች እናት ሳይከብዳት ሁሉን አቻችላ ሁሌም አዲስ ነገር የምታሳይ ለሴቶች ምሳሌ መሆን የምትችል ሴት ናት ሀቢባ ፋሪስ ፤ዛሬ ለደረሰችበት ጥንስሱ ያለፈችበት መንገድ ሲሆን ለነገዋ ደግሞ የዛሬ ስራዋ ስንቅ ነው በርቺ ሀቢቲ …
ሀቢባ በሀይማኖት ዘለቀ አንደበት
ሀቢባን ስራን አንድ ብላ ከጀመረችበት ከኢዜአ ጀምሮ አውቃታለሁ፡፡ በኢዜአ ለ8 አመት አብረን ሰርተናል፡፡ ሀቢባ ለሙያዋ ትልቅ ፍቅርና መሰጠት አላት፡፡ በስራዋ አዲስ ነገር ለመፍጠር የተቻላትን ሁሉ ታደርጋለች፡፡ እርግጥ ነው የአለቆቃችን የእነ ስለሺ ተሰማ የእነ ዶክተር ተሻገር ሺፈራው እገዛ ትልቅ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ሀቢባ የፕሮጀክት ዜናዎችን በራሷ አቅዳ የመስራት ተነሳሽነት እንደነበራት አስታውሳለሁ፡፡ አንዳንድ ደግሞ ሂዩማን የሆኑ ለሰው ቅርብ የሆኑ ለየት ያሉ ዜናዎችንም በማምጣት ሙያዊ ሀላፊነቷን ለመወጣት የቻለች ናት፡፡ ሀቢባ እንደ መሪ ቤተሰባዊ ስሜት የመፍጠር ልዩ ችሎታ አላት፡፡ በጣም ስለምትግባባ ስራ ከእርሱዋ ጋር ለመስራት አዳጋች አይሆንም፡፡ ራሷን ሳትኮፍስ ተግባብታ ስራ የማሰራት አቅም ያላት የሚድያ ሰው ናት፡፡ተናባ በቡድን እንዴት መስራት እንደሚቻል ጠንቅቃ የምታውቅም ናት፡፡ በእኔ እምነት ይህ አይነቱ ቀረብ ብሎ የማስተዳደር የማኔጅመንት ስታይል ያስፈልጋል፡፡ እርሷም በዚህ አይነት መንገድ እየሰራች በመሆኑ የተሳካላት መሆኑን እገነዘባለሁ፡፡
ሀቢባ በሁናቸው ታዮ አንደበት
ሁናቸው ታዬ ይግዛው በአሁኑ ሰአት በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በቲቪ ዘርፍ የዜና ቻናል ማኔጂንግ ኤዲተር ሲሆን ስለ ሀቢባ ፋሪስ የሚከተለውን ምስክርነት ሰጥቶናል፡፡
ሀቢባን ጋር አብረን መስራት ከጀመርን 1 አመት ከ 5 ወር ገደማ ይሆነናል፡፡ ሀቢባ በእኔ እይታ በቀላሉ የምትግባባ የስራ መሪ ናት፡፡ እንዲህ አይነት የስራ መሪዎች በቀላሉ አይገኙም፡፡ ሀቢባ ይህንን ስራ ብላ ከማዘዝ ይልቅ እንደ ቅርብ ወንድም በፍቅር ማሰራቱ ይቀናታል፡፡ በውይይት ታምናለች፡፡ ሳማክራት እንደ እህት ታደምጣለች፡፡ አንድን ሰው ተጭኖ ማሰራት አትወድም፡፡ወጣት ስለሆነችና በጋዜጠኝነት የካበተ ልምድ ስላላት ምን ማሰራት እንዳለባት ታውቃለች፡፡ በተጨማሪም ጋዜጠኛው ለራሱ ብሎ እንዲሰራ ጥሩ እገዛ ትሰጣለች፡፡ ከዚህ በፊት የነበሩ አመራሮች በማዘዝ የሚያምኑ አሉ፡፡ ይህ ግን በፍጹም አይሰራም፡፡ ሀቢባ ከበፊተኞቹ የተሻለ በቡድን ስራ የማመን ልዩ ክህሎት ነበራት፡፡ ይህ ደግሞ ስራው በተሳካ መልኩ እንዲከናወን የሚያደርግ ነው፡፡
ሀቢባ በተለይ መዝናኛው ተወዳዳሪ እንዲሆን አዳዲስ ፎርማቶች እውን እንዲሆኑ ትልቅ እገዛ አድርጋለች፡፡ አዳዲስ የተጀመሩ ፎርማቶች በቶሎ እንዲጀመሩ ሙያዊ እና የመሪነት ክትትሏን አጠናክራ በመቀጠል እየሰራች ነው የምትገኘው፡፡ ቢሻሻሉ የምትላቸውን ሀሳቦች ሁሉ ስትሰጥ ነው የቆየችው፡፡ በእርሷ ዘርፍ ውስጥ ወደ 200 ሰዎች አሉ፡፡ እነዚህን ሰዎች ነው የምትመራው፡፡ በመሆኑም በእኔ እምነት ከጋዜጠኝነት ጀምራ እስከ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ በሁሉም ደረጃዎች አልፋ የመጣች በመሆኑ ሚድያውን በብቃት ለመምራት አቅም ያገኘች ይመስለኛል፡፡ ወደፊት ደግሞ ከዚህ በላይ አቅሟን ጨምራ ትልቅ ስራ ልትሰራ እንደምትችል አምናለሁ፡፡ ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የጀመረው የሚድያ ሰዎች ታሪክ ስነዳም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡ ፈጽሞ የማናውቃቸውን የቀድሞ እና የአሁን የሚድያ ሰዎችን ስላሳወቃችሁን ምስጋናችን ወደር የለውም፡፡
መዝጊያ ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ የመዝገበ-አእምሮ ቦርድ አባላት አቋምን የሚያንጸባርቅ ነው።
በሀገራችን የመጀመሪያዋ ሴት ጋዜጠኛ በ1930ዎቹ የሚድያ እና የስነ-ጽሁፍ ፍቅር ስለነበራቸው በጠዋቱ የሚድያውን አለም ተቀላቀሉ፡፡ የመጀመሪያዋ ሴት ጋዜጠኛ ለመሆን ቻሉ፡፡ እርሳቸው መጽሀፍ በመጻፍም እውቅና የተቸራቸው ነበሩ፡፡ እርሳቸው በዘመናቸው የሚጻፍ ታሪክ ስለሰሩ ከ50 አመት በኋላም ታሪካቸው ታሪክን በሚጽፍ ብእረኛ ይከተባል፡፡ የወይዘሮ ሮማን ወርቅ ካሳሁን ያኔ ዜና ነበር አሁን ግን ታሪክ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ታሪክ ወይዘሮ ሮማን ወርቅን ሳያነሳ የማያልፍ የለም፡፡ ምክንያቱም ታሪክ ሰርተዋል፡፡
ዛሬ የህይወት ታሪኳን የከተብንላት ሀቢባ ፋሪስም ለነገው ትውልድ ሊያስተምር የሚችል ደማቅ ታሪክ አስቀምጣለች፡፡ ሰዎች በየዘመኑ ያኖሩት አሻራ በወጉ ስለማይቀመጥ እንጂ በ1990ዎቹ የዜና ጋዜጠኝነት የራሷን ጡብ አኑራለች፡፡ የምናወራውም ስለዚህ ጡብ ነው፡፡ የምንጽፈው ስለ ግለሰብ ሳይሆን ስለ ዘመንን እና ስለ ሀገር ነው፡፡ ያስቀመጥነው ታሪክ የሚድያ ታሪክ ነው፡፡ የሚድያ ታሪክ በሰዎች ውስጥ ሲያልፍ እንደምን ይመስላል ስንል ነው መሰል ታሪኮችን እየሰነድን ያለነው፡፡
ወይዘሮ ሀቢባም 24 አመት በዘለቀ የሚድያ ቆይታዋ ብዙ ዘግባለች፡፡ ብዙ ሀገራት አይታለች፡፡ ሀገሪቱ በ24 አመታት እንዴት እንዳለፈች አይታለች፡፡ ይህን ደግሞ በብእሯ ስታሳየን ፣ መሪ ሆናም መረጃዎች ወደ እኛ እንዲደርሱ ስታደርግ ኖራለች፡፡ ይህ ደግሞ ተጽፎ መቀመጥ ስላለበት ሙያዊ የስነዳ ሃላፊነታችንን እየተወጣን እንገኛለን፡፡ ሀገር ማለት ሰው ነውና፡፡ ሌሎች የሚድያ መሪዎችም አሻራ ማኖራችሁ ከተረጋገጠና ታሪካችሁን ስጡን ካልናችሁ ያለ አንዳች ማመንታት ተባበሩን፡፡ ታሪካችሁን አቆያችሁ ማለት መድሀኒት ደበቃችሁ እንደማለት ስለሆነ በራችሁን ስልካችሁን ክፍት በማድረግ ምን ችግር አለ ታሪኬን ብሰጣችሁ በማለት ቀና ምላሽ ትሰጡን ዘንድ በታላቅ ትህትና እንጠይቃለን፡፡ ወይዘሮ ሀቢባም ቀና ትብብር አሳይተው ላደረጉት ትብብር ምስጋናችን ወደር የለውም፡፡ ይህ ጽሁፍ ዛሬ ሀምሌ 1 2015 በተወዳጅ ሚድያ ዲጂታል ሚድያዎች የቀረበ እና የተጫነ ሲሆን የታሪኩም አዘጋጅ ጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ ነው፤፡
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ