103. ደረጀ ሀይሌ ሺበሺ-   Dereje haile shibeshi

 ኮሜዲያ ደረጀ ሀይሌ የራሱን አሻራ ያኖረ ባለውለታ            

የዚህ ታሪክ አሰባሳቢ ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በስነ-ስእል ፤  በስነ-ጽሁፍ፣ በፊልም ፣ በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፤ በማስታወቂያ ዘርፍ ፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1990ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ ፤ በዊኪፒዲያ እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እያስተዋወቀ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ውድ ይህን ሀሳብ የምትደግፉ    መስፈርቱን ያሟላሉ  የምትሏቸው ሰዎች ጠቁሙን  ፤ እርስዎም ታሪኬ መሰነድ አለበት ካሉ ይላኩልን፡፡ ከተቀመጠው መስፈርት አንጻር አይተን ታሪክዎን እናወጣለን፡፡ በ tewedajemedia@gmail.com ግለ-ታሪክዎን ይላኩ፡፡ ጥቅምት 14 2014 የ1000 ሰዎች ታሪክ ሲሞላ ድንቅ ታሪካዊ ምረቃ ይኖራል፡፡ ታሪካቸው አሁን የሚሰራላቸው፤ ብዙዎቹ በወጣትነት አንዳንዶቹም በጉልምስና እድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የዛሬ ጎልማሳ የነገ የሀገር ባለውለታ ነውና ታሪካቸውን እየሰነድን ለትውልድ እናስቀምጣለን፡፡ ለወደፊቱም ምርምር ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡ በ6 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ ከኮሜዲ ዘርፍ ታሪኩን የምናቀርብለት ሰው ፊልም ላይ ይተውናል፡፡ መጽሀፍ ይጽፋል፡፡ ሁለገብ ነው፡፡ ደረጀ ሀይሌ ፡፡








  

        ትውልድ እና ልጅነት

ኮሜዲያን ደረጀ ሀይሌ ሺበሺ ሰኔ 25 1959 ነበር የተወለደው፡፡እናቱ ወይዘሮ እልፍነሽ ማስረሻ ሲባሉ አባቱ ደግሞ አቶ ሀይሌ ሺበሺ ይባላሉ፡፡ ካዛንቺስ የደረጀ የትውልድ ስፍራ ሲሆን የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱንም በበየነ መርእድ /እድገት በህብረት/ አጠናቅቋል፡፡ የ2ኛ ደረጃ ትምህርቱንም በዳግማዊ ምኒሊክ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ1976-1979 ተምሯል ፡፡ ደረጀ በዳግማዊ ምኒሊክ ትምህርት ቤት ቆይታው በሚኒ-ሚድያዎች ተሳትፎ ያደርግ ነበር፡፡ በተጨማሪም፤ለመምህራን ቀልዶችን በማውራት የኮሜዲ ስራውን ማዳበር ጀመረ፡፡

ደረጀ ካዛንቺስ ይወለድ እንጂ አብዛኛው እድገቱ ሜክሲኮ ዲአፍሪክ ፊትለፊት ነው፡፡ለዛ አካባቢ ደረጀ ልዩ ትዝታ አለው፡፡  

        የሙያ ጅማሮ 

የደረጀ የሙያ ጅማሮ ሰፈር ውስጥ ለሚገኙ ልጆች ቀልዶችን በማውራት ፤ የህንድ ፊልሞችን በመተርጎም እየዳበረ ሄደ፡፡ በዚህ ሰአት ነበር ደረጀ እና ጥበብ ትውውቅ የፈጠሩት፡፡ በኋላም በአኢወማ ውስጥ ሆኖ ይህን ክህሎቱን እያወጣ ሲሄድ የበለጠ በሙያው መዝለቅ እንዳለበት ተገነዘበ፡፡ በቀበሌ 51ከፍተኛ 3 እና ቀጠና 2 ውስጥም ከፍተኛ ተሳትፎ ያደርግ ነበር፡፡

          ለገዳዲ 

ደረጀ ስለ ኪነ-ጥበብ ጉዳይ ሲያነሳ ለገዳዲ ሬድዮ መልካም እድል የከፈተለት መሆኑን ያስረዳል፡፡ ያኔ በ1970ዎቹ መጨረሻ ትምህርት በሬድዮና የቅዳሜ ከእኛ ጋር እና እሁድን ላንዳፍታ የተሰኙት መሰናዶዎች ለወጣት የጥበብ አፍቃሪዎች በሬድዮ ላይ እንዲሰሩ እድል ይፈጥሩ ነበር፡፡ ደረጀ ብቻ ሳይሆን ሀብቴ ምትኩ፤ ታገል ሰይፉ ፤ዳዊት ከበደና ሰይፉ ፋንታሁን ፤ ኢሳያስ ልሳኑ ፤ ቴዎድሮስ ሙላቱ፤ጀሚል ከፍልውሃ ፤ ዳንዴው ሰርቤሎና ቤዛዬ ግርማ  ለገዳዲ ላይ ትልቅ ተሳትፎ ያሳዩ ነበር፡፡ ደረጀም ዛሬ መለስ ብሎ ሲያስበው በለገዳዲ የነበረው ጥረት የበለጠ በሙያው ላይ እንዲገፋ አስችሎታል፡፡

    የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን 

ኮሜዲያን ደረጀ አሁንም ለሙያው የተሰጠ መሆኑን በማወቅ በኢትዮጵያ ሬድዮ ፤በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ፤በአዲስ ዘመን ላይ በመጻፍ እጁን አፍታታ፡፡ በእነዚያ ጊዜያቶች ፤ ደረጀ  ስነ-ጽሁፍ፤ ግጥም ፤ ወጎችና ቀልዶችን  በተለያዩ መድረኮች በማቅረብ ከተመልካች ጋር ትውውቅ ፈጠረ፡፡ በቀጠና 2 የኪነ-ጥበብ ቡድን ውስጥም በመቀላቀል ሙያዊ ክህሎቱን የበለጠ ማሳደግ ጀመረ፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር በ1979 መሆኑ ነው በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ስራ የጀመረው፡፡ ያኔ በህብረ-ትርኢት ፤ በወጣቶች ፕሮግራም የደረጀ እና የሀብቴን ቀልዶች በተመልካች ዘንድ መውደድ ጀመሩ፡፡ በዚህ ሰአት ነበር ደረጀ በኮሜዲ ሙያ ዘመን ተሻጋሪ ስራ ሰራሁ ብሎ የሚያምነው፡፡ ከ1979-1987 ባሉት 8 አመታት ደረጀ በኢትዮጵ ያ ቴሌቪዥን ከጓደኛው ሀብቴ ምትኩ ጋር በርካታ የኮሜዲ ስራዎችን አቅርቧል፡፡

120 የተሰኘው የመዝናኛ ፕሮግራም በ1984 በተጀመረበት ጊዜ የደረጀ ሚና ቀላል አልነበረም፡፡ ያኔ ይቀርቡ የነበሩ የኮሜዲ ስራዎች ዛሬ ድረስ ሲታዩና ሲደመጡ ዘመን ተሻጋሪዎች ነበሩ፡፡

               ደረጀ በባህር ማዶ 

ደረጀ ከቲቪ ባሻገር ከ1979 አንስቶ የመድረክ ስራዎችን በሀገሪቱ በሁሉም ክልሎች ፤ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማእከል እና በሁሉም ቴአትር ቤቶች ሲያቀርብ ነበር፡፡የደረጀ የኮሜዲ ስራዎች በሀገር ውስጥ ብቻ የተወሰኑ አልነበሩም፡፡ በባህር ማዶ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም የኮሜዲ ስራዎችን የመመልከት ፍላጎታቸው እየናረ በመምጣቱ  ደረጀም ከጓደኛው  ሀብቴ ምትኩ ጋር በመሆን በኬንያ፤ በሳኡዲ አረቢያ ፤በዱባይ ፤በባህሬን ፤ በእስራኤል፤ በኳታር ፤በኩዌት በአሜሪካ በመገኘት የኮሜዲ ስራዎችን አቅርቧል፡፡

            ሁለ-ገቡ ደረጀ 

ደረጀ  ከሚያቀርባቸው የግጥምና የኮሜዲ  ስራዎች ባሻገርም  በቁምነገር መጽሄት ፤ በሮዝ ፤በታዛ ፤ በሪፖርተርና ፤ በኢንተር-ስፖርት ጋዜጣ ላይ ጽሁፎችን በመጻፍ ሙያዊ ክህሎቱን ለመወጣት ችሏል፡፡

ደረጀ ሀይሌ ከሚያከብረው አብሮ አደጉ ሀብቴ ምትኩ ጋር አንድ ላይ በመሆን የኮሜዲ ስራዎችን በቪኤች ኤስ አውጥቷል፡፡  በቀዳሚነት ያወጣው በኤሌክትራ ሙዚቃ ቤት አማካይነት ሲሆን ብዛታቸውም 3 ነበር፡፡ ሙያሽ የተሰኘውን ስራንም በቪሲዲ ያወጣው በአምባሰል ሙዚቃ ቤት አማካይነት ነበር፡፡

ገና በልጅነት በሁሉም የኪነ-ጥበብ ስራዎች ላይ የመሳተፍ ፍላጎት እና ችሎታም የነበረው ደረጀ ከ 20 በላይ ፊልሞችም ላይ በመተወን ሰርቷል፡፡ በትወና ከተሳተፈባቸው ፊልሞች መካከልም ፤ አያስቅም ፤ ይፈለጋል፤የኔታ ፤ ሰርግ ከአሜሪካ ፤ወደገደለው ፤የባል ጋብቻ ፤ ሰኚኮ ፤ባለቀሚስ ፤ ባለጉዳይ ፤ኤፍቢአይ 3 ፤ ሌባ እና ሌባ የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡

በኮሜዲ ስራ ፤ በፊልሞች ፤ በመጽሄት ላይ ጽሁፎች በማውጣት  ያልተወሰነው ደረጀ ሀይሌ መጽሀፎችን በመጻፍ ከአንባቢያን ጋር መገናኘት ችሏል፡፡ ‹‹ ትዝታ ሲጨለፍ ›› ፤አንዳንድ ነገሮች እና ሌሎች ፤ የሚሊየነሩ ፍዳ  የተሰኙት አንባቢ ጋር መድረስ የቻሉ ሲሆኑ  ወደ ፊት ሊያሳትመው ያዘጋጀው አንድ ስራም አለው፡፡ አንድ ገና ያልወጣ  የኮሜዲ ስራም አለው፡፡

            Derdare tube 

ደረጀ በፋና ቲቪ ላይ ጥበብ በፋና በተሰኘው መሰናዶ ላይ አቅራቢ በመሆን የሰራ ሲሆን

Derdare tube  በተሰኘ  የዩቲዩብ  መሰናዶው ም ላይ በርካታ የመዝናኛ ዝግጅቶችን እያቀረበ ይገኛል፡፡ ይህ በደረጀ ሀይሌ የተከፈተው ዩቲዩብ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ተቀባይነትን ያገኘ ሲሆን ደረጀም ይህን ዩቲዩም በሚገባ ለማሳደግ እየሰራ ይገናል፡፡

ደረጀ ለራሱ ብቻ ከማሰብ ይልቅ ሌሎችን በማብቃት እና በመርዳት ያምናል፡፡ ሙያ ይዘው ነገር ግን መድረክ ላጡ ወጣት ተዋንያንም ልምዱን በማካፈል ሃላፊነቱን ተወጥቷል፡፡  እንደ አርአያ የሚቆጥረውን ኮሜዲያን ልመንህ ታደሰን በመደገፍና በመንከባከብ  ትልቅ ወንድማዊ አደራውን በሚገባ ተወጥቷል፡፡  

ደረጀ ባለትዳርና የአንድ ወንድ ልጅ አባት ነው፡፡   ደረጀ ሀይሌ ለሀገሩ ታላቅ ፍቅር ያለው በሀገራዊ ንቅናቄዎች ላይ ከሙያ አጋሮች ጋር የሚሳተፍ በኢትዮጵያ ኮሜዲ ላይ አሻራ ያኖረ  ሰው ነው፡፡























አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች