31. ተስፋዬ ድረሴ ጻድቅ Tesfaye Diressie Tsadik
የልደት ቀን - ሚያዝያ 23.1950
የትውልድ ቦታ - ክብረመንግሥት/አዶላ
ቁመት - 1.69
ክብደት - 76.6
የፀጉር ቀለም - > 50.5% ነጭ
የፀጉር ሽፋን - < 50.6%
ባለቤት - ሮማን ቱፋ
ደበሌ
የትዳር ዘመን -
ከጥር 19.1983 ጀምሮ
ትምህርት/ሙያ -
አፕላይድ ሶሽዮሎጂስት
የኑሮ ሁኔታ - ከድህነት
ወለል በላይ
መተዳደሪያ/ገቢ
- የግል ሥራ (“ተስፋዬ ድረሴ የማስታወቂያ ሥራ”)፣ ግጥም፣ ዜማ፣ ማማከር፣ ማሰልጠን፣ ወዘተ
“ተሰጥዖዎች” –
(በልማድ ያዳበራቸው ክህሎቶች)፤ ግጥም፣ ዜማ፣ ሙዚቃ፣ መጣጥፍ፣ ተረት፣ ወዘተ
የአዋቂነት ዘመን
በጊዜ ውስጥ ማለፊያ፣ ራስን ማዝናኛዎቹ - መዝፈን፣ የድምጽ ልምምድ፣ ዜማ መድረስ፣ ግጥምና ሌሎች መጽሀፍትን ማዘጋጀት (ማጠራቀም)፣
ማሰላሰል፣ ስፖርት (ዱብ ዱብ፣ ፑሽ አፕ፣ የእግር ጉዞ፣ ዳንስና ጭፈራ)፣ የተለያዩ አሰላሳዮችን፣ የተፈጥሮና የማህበራዊ ሳይንቲስቶችን
መከታተል፤ ለምሳሌ፡- Neil Degrasse Tyson, Sadhguru, Pro PLO Lumumba, Daniel Goleman,
Yuvula Noah፣ ቋንቋ መማር (ኦሮምኛ)፣ ከባሌበቱ፣ ከጎረምሳ ልጆቹና ከጓደኞቻቸው ጋር ማውጋት፣ መማማር፣ የአካባቢ ጉዳዮች
ላይ መሳተፍ፣ ነጻ ስልጠናዎችን መስጠት፡፡
ልዩ ምስጋና - ለአንድ፣
አንድ ሰው ብቻ፡- ከመምህራን - ለቲቸር ክብረት መንገሻ - የክብረመንግሥቱ፤ ከጓደኛ - ለተሾመ አማረ ኃ/ማርያም (አሁን ካናዳ
የሚኖር አብሮ አደግ)፣ ከቤተሰብ - ለታላቅ እህቱ አኅታገኘሁ ድረሴ፤ እና ከቤት፣ ለባለቤቱ ሮማን ቱፋ፡፡
ባህሪ - ቀልደኛ፤
ነገሮችን ቀለል አድርጎ የሚወስድና የሚያስተናግድ፤ “በማበድ እና በማካበድ መካከል ያለው ልዩነት “ካ” ብቻ ናት ባይ፣ ቁምነገረኛ
(የህፃን፣ የደሀ፣ የሀብታም፣ የባዳ፣ የዘመድ ሳይል ለሰው የገባውን ቃል ለማክበር የሚጥር)፣ አዝናኝ
/Entertainer/fun-raiser
“ተስፋዬ”
እናትና አባቴ እጅግ
ቢራቀቁ
አንድ ስም ሰጥተውኝ
ተናግረው አበቁ
ልጅ ተስፋ ነውና ተስፋዬ
ብለውኝ
ጡሬ እንድቀብራቸው በግልጽ
አደራ አሉኝ፡፡
እናቴ ለራስዋ እያለች
ተስፋዬ
አባቴም ለራሱ እያለኝ
ተስፋዬ
ተስፋቸውን ጣሉ በነገው
ተስፋዬ
ለካስ ስም አውጥቶም
እንዲህ ይናገሯል?
ያንዱን ተስፋ ሌላው
በተስፋ ይጠብቋል?
ተፃፈ - 1975 (የዚህ
ግጥም መነሻ ታሪክ ከታች ቀርቧል)
--------------------
ተስፋዬ ድረሴ ተወልዶ
ያደገው ክብረ መንግሥት ነው - በደቡብ አቅጣጫ፣ ኦሮምያ ክልል ውስጥ - 475 ኪ.ሜ ርቀት ላይ፡፡ “ከተወለድኩበት ቀስ በቀስ
ያወጣኝ፤ አዲስ አዲስ አበባ ድረስ ያመጣኝ፤ ትምህርት ነው” - የሚለው ቀልደኛው ተስፋዬ አባቱ አቶ ድረሴ ጻድቅ እና እናቱ ወ/ሮ
ይመኙሻል ገ/ዮሀንስ ህይወታቸውን ከመደበኛ ትምህርት ውጭ በስኬት የመሩ፣ በአያሌው በግብርና ይተዳደሩ የነበሩ ናቸው፡፡ አባቱ በአንድ
ፊት በሰፈሩ የታወቀ ቀልደኛ፣ በሌላ ፊት ቁምነገረኛና የአገር ሽማግሌ፤ እናቱ ደግሞ የቀልድ አድናቂ እና ዘፈን ወዳድ ነገር ግን
የበቁ ባለሙያ፤ “የሴት ቁንጮ” እንዲሉ አይነት፤ እንደነበሩ ይመሰክርላቸዋል፤ ልጃቸው፡፡ ሁለቱም አሁን በህይወት የሉም፡፡ በከፊል
ዓለሙን አይተው ነው ያለፉት፡፡ ተስፋዬ እናትና አባቱ ጎን ለጎን መቀበራቸውን ለመግለጽ፣ ወዲህም የሚተሳሰቡ ባልና ሚስት እንደነበሩ
ለማስታወስ ከእንጨት፣ ከቆርቆሮና ከጭቃ የጋራ መቃብር ቤት ካሰራላቸው በኋላ በስተኋላ ለሞቱት አባቱ የተስካር የጥሪ ወረቀት ያሳተመላቸው
ለሁለቱ እነዚህን ስንኞች ቋጥሮላቸው ነው፡-
በአካል ተነጣጥለው
- በነፍስ ተጣምረው
እንዬና ጋሼ - ሞተው
ተኙ አብረው፡፡
ህይወት ይቀጥላል -
ተስፋዬ ባህሪያቸውን ወርሶ፣ የራሱን ለዛ ጨምሮበት ኑሮውን ቀጥሏል፡፡
ተስፋዬ መደበኛ ትምህርት
የተከታተለው ከ1-8ኛ ክብረመንግሥት ራስ ብሩ ወ/ገብርኤል ት/ቤት (ከ1956-1964)፣ ከ9-12 ይርጋዓለም አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት (ከ1965 – 1971)፣
እና ከ1972 - 1975 በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ በአፕላይድ ሶሽዮሎጂ Applied Sociology BA Degree አግኝቷል፡፡
ከ1967 - 1968 የእድገት በህብረት የእውቀትና የሥራ ዘመቻ ላይ ተሳታፊ በመሆን በቦሬ ዘመቻ ጣቢያ የቆየባቸውን ሁለት ዓመታት
የእውቀት አድማሱን በብዙ አቅጣጫ እንዳሰፉለት እውቅና ይሰጣል፡፡ “ለመሰልጠን” እና የሙያ ልምድ ለማካፈል ወደ ኖርዌይ፣ ስዊድን፣
እንግሊዝ፣ ባንግላዴሽ፣ እና ዚምባብዌ ያደረጋቸው ጉዞዎች የእውቀት አድማሱን እንዳሰፉለት ይናገራል፡፡ የጉዞ ማስታወሻውንም ለሥራ
ባልደረቦቹ፣ ለቤተሰቦቹና ለጓደኞቹ ለማጋራት መብቃቱን ይመሰክራል፡፡
የብዙ ሙያዎች ባለቤት
ተስፋዬ ድረሴ ከሁለት
እጆቹ ጣቶች ቁጥር የሚበልጡ ሙያዎችን ራሱን በራሱ አስተምሯል፡፡ ባህሪው ፈታ፣ ዘና ያለ፤ ፈገግታ የማይለየው ሰው ነው፡፡ ሲጣደፍ፣
ሲጨናነቅ አይታይም፡፡ ብዙ የሚቆጠሩ ስኬቶችን ግን በስሙ እያስመዘገበ ኖሯል፡፡
ተስፋዬ፤ በእውቀቶች
መካከል የቆመ የግንብ አጥር መፍረስ እንዳለበት፣ የእውቀት ሚስጥርነትም መገለጥ እንደሚኖርበት የሚያምን አሰላሳይ ነው፡፡ “ደግነቱ
ኪነጥበብ” አጥር የላትም፤ ሊዚህ ነው ያለ የትምህርት ማስረጃ የተቀበለችኝ” የሚለው ተስፋዬ “ራስህን አስተዋውቅ” ለሚሉት ጋዜጠኞችም
ሆኑ ሌሎች ሰዎች በቀልድ “ይኸው ራሴ፣ ይህን ይመስላል” በማለት በራ ራሱን ዝቅ አድርጎ ያሳያል (ይህን አባባል የወሰደው አሰፋ
በየነ ከሚባል አንጋፋ የትምህርት ባለሙያ ነው)፡፡ በትምህርት ሶሾሎጂስት በኑሮ “ሰው-ሰው-ሎጂስት” ነኝ በማለትን ይተዋወቃል፡፡ ለዚህ ንግግሩ የሰጠንን
ማብራሪያ ለኋላ እናስቀምጥና የተስፋዬን ዘርፈ ብዙ “ማንነት” ካኖራቸው ቱሩፋቶቹ አንፃር ቀጥለን እንመልከት፡፡
1) ገጣሚ ተስፋዬ ድረሴ
- ባለ ተራ ግጥም፣ ውስጠ ወይራ፣ ቅኔ
ተስፋዬ “ገጣሚ” ነው፡፡
ለህትመት የበቁ፤ በድጋሚም የታተሙ፤ 2 የግጥም መጽሀፍት አሉት - የዕድሜ አስቤዛ ቁ.1፤ 86 ምርጥ ግጥሞች (የገጽ ብዛት
74) – በ1999 እና ምርግማን (የዕድሜ አስቤዛ ቁ-2)፤ 87 ምርጥ ግጥሞች (የገጽ ብዛት 92) — በ2002፡፡ ተለይቶ ከሚታወቅባቸው፤
እሱም አብልጦ ከሚወዳቸው፤ ግጥሞቹ መካከል “መክተፊያ” አንዱ ነው፡-፡
መክተፊያ
የእንጨት መክተፊያ
ማስዘልዘያ ... ማስተፍተፊያ
ለቢላዋ ብርታት ከስር
መደገፊያ ...
ከስለት ጋር ህብረት
ጉዳቱን ሳያውቀው
ከስንቱ ጋር ይሆን ተበልቶ
ያለቀው?
ሥጋ፣ ቆጮ፣ ካሮት፣
ጎመን፣ ቃሪያ ሳይል
...ሳይለይ ጥሬ ብስል
ከእህል ጋር ሁሉ እየተከተፈ
እየተሸረፈ ... እየተቀረፈ
ማለቂያ አጥቶ ጣጣው
ሆዱ ጎደጎደ ... ኩሬ
ብጤ ወጣሁ
ሽንቁሩ አፈሰሰ
... ሳስቶም ጌታው ጣለው
“መክተፊያ በላሁ” ግን
... አንድም ሰው አላለው፡፡
2) የዘፈን ግጥምና
ዜማ ደራሲ - የህፃናት መዝሙሮች፣ የአዋቂ ዘፈኖች፣ የልማት መዝሙሮች፡፡
2.1. የህፃናት መዝሙሮች፡፡
በ1989 - በአገራችን፣ በዘርፉ ፋና ወጊ የሆነ፤ በአያሌው የህፃናት መብቶች ላይ የሚያተኩሩ 10 መዝሙሮችን የያዘ፤ “አንደበት”
የተሰኘ ወጥ የህፃናት መዝሙር ካሴት አሳትሟል፡፡ በሺህ የሚቆጠሩ የካሴቱ ቅጂዎች ለት/ቤቶች፣ ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች፣ ለመገናኛ
ብዙሃን፣ የህፃናትና ወጣቶች ክበባት ተሰራጭተዋል፡፡ ሥራዎቹ በ1987
— 1997 መካከል ተፋፍሞ ይካሄድ ለነበረው የህፃናት መብት ንቅናቄ ግብዓት በመሆን አገልግለዋል፡፡ መዝሙሮቹ፤ የተወካዮች ምክር
ቤትና የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ የህፃናት ጉዳይ የሚመለከታቸው አካላት በሚገበኙባቸው መድረኮች ላይ ተዘምረዋል፤ ለህጻናት አንደበት
ሆነዋል፡፡ ለአፍሪካ ህፃናት ቀን፣ የዓለም አቀፍ የኤድስ ቀን፣ የሴቶች ቀን፣ ወዘተ ሰልፎችን ማድመቂያም ነበሩ፡፡ ለድምጻዊያን
ህፃናትም የድምጽ መለማመጃና ማነቃቂያ ሆነው አገልግለዋል፣ ለሬዲዮና ቴሌቪዥን የህፃናት ፕሮግራም አዘጋጆች (ራሔል አሰፋ፣ ዓይናለም
ደፈረሱ ወዘተ)ም አስፈላጊ ቁሳቁስ ለመሆን በቅተዋል፡፡ የመዝሙሮቹ ርዕሶች - “ድምጽ አልባ ነን”፣ “አገሬ አስተምሪኝ፣” “ቅጣት”
(ዶላ)፣ “ጠለፋ፣፣ “ሰንፍና(ሰነፍ ተማሪ)፣”፣ “ሞግዚቴ፣” “የሰው መልኩ ኑሮው፣” “ሆዴ ነው ጠላቴ” (በጎዳና ኑሮ ላይ)፣
“አዋጅ” (በኤድስ ጉዳይ) እና “አፍሪካ” (ጋዜጠኛ ዳዊት ንጉሱ ረታ ባዘጋጀው ክሊፕ ተደግፎ በቴሌቪዥን ሲተላለፍ የቆየ)፡፡ መዝሙሮቹ
የተዘመሩት በህፃናትና ወጣቶች ቴያትር ቤት ድምጻውያን (ለምሳሌ፤ ፋሲል ሽመልስ፣ ዮዲት ዘለቀ) ሲሆን ካሴቶቹን ሠራተኛና ማህበራዊ
ጉዳይ ሚነስቴር/ዩኒሴፍ፣ ኤስ ኦ ኤስ፣ የህፃናት አድን ድርጅት ጥምረት፣ ፕሮፕራይድ፣ ፕላን ኢትዮጵያ ወዘተ በስፋት አሰራጭተዋቸዋል፡፡
ዛሬም በብዙ ወጣቶችና አዋቂዎች ይታወሳሉ፣ በአርዓያነት ይጠቀሳሉ፡፡
2.2) የተዋልዶ ጤናን
አስመልክቶ የተሰሩ 3 መዝሙሮችን የያዘ “ሀኪሜ ድረሽ” የተሰኘ ሲዲ፡፡ መዝሙሮቹ 1)“ሀኪሜ ድረሽ” (“እናቴ ድረሽ” እየቀረ ነው
የሚልና እናቶች የጤና ተቋማት ውስጥ እንዲወልዱ ጥሪ የሚያደርግ፤ 2) “እድለኛ ህፃን፣” (ጎጂ ልማዶች እየቀሩ ነው፣ በዚህ ወቅት
የሚወለዱ ህፃናት እድለኞ ናቸው” በማለት ቀና ዜና ለማብሰር ታስቦ የተሰራ)፣ 3) “የህይወት ሩጫ” - የእናቶችንና የጨቅላ ህፃናትን
ሞት ለመቀነስ ለሚደረጉ ንቅናቄዎች (ለምሳሌ ታላቅ ሩጫ) ማድመቂያ እንዲሆን የተሰራ የአድቮከሲ መዝሙር፡፡ ዘማሪያን እሱባለው ይታየውና
ሌሎች ወጣት ድምጻዊያን፤ አቀናባሪ ታምሩ አማረ፡፡ ሲዲው በህፃናት አድን ድርጅት ድጋፍ የተሰራ ሲሆን ለመገናኛ ብዙኃንና ለሌሎች
ለበርካታ ተቋማት ተሰራጭቷል፡፡
2.3) “ዛሬ ናት!”
”ዓለምአቀፍ የህፃናት ቀን” (ህዳር 11)ን አስመልክቶ በፌዴራል ጠ/ፍርድ ቤት የህፃናት ፍትህ ቢሮ የገንዘብ ድጋፍ ሲሆን በፖሊስ
ማርች ባንድ የተቀናበረ እና ለዕለቱ ፍጆታ እየዋለ የሚገኝ ነው፡፡ ድምፃውያን - በህፃናትና ወጣቶች ቴያትር ቤት የሰለጠኑ ህፃናት/ወጣቶች
(እየሩሳሌም አምዴ፣ ልዋም ዳዊት፣ ገረመው ገ/ፃድቅ፣ እና ሙሉጌታ ለማ ሲሆኑ አስተባባሪው ኤልያስ ኃ/ሚካኤል፣ አቀናባሪው መሀመድ
ኑርሁሴን ነው)፡፡
2.4) “ባናት ባናቱ”
- ለቤተሰብ መምሪያ 25ኛ ዓመት ፍጆታ የተዘጋጀ (1983) እና ድርጅቱ ለረዥም ጊዜ በማስተማሪያነት የተጠቀመበት መዝሙር ነው፡፡
በመዝሙሩ ላይ ተስፋዬ ድረሴ ራሱ እና ገነት ቱፋ እንዲሁም ሌሎች ድምጻውያን ተሳትፈዋል፡፡ አቀናባሪው ዮሀንስ (ቡቡ) ነው፡፡
2.6) በድምሩ 6 መዝሙሮች
- በትምህርት፣ በህፃናት ተሳትፎ እና በልማት ዙሪያ ለActionAid
አክሽን ኤድ እና አንፕካን-ኢትዮጵያ የተሰሩ - የአድቮከሲ (ማስተማሪያ፣ ማንቂያ መዝሙሮች)፡፡ ቅንብር ታምራት
2.7) በድምሩ 7 ዘፈኖች
ለመደበኛ ድምፃውያን (ለገነነ ኃይሌ 3፤ ለመስከረም ሙሉ 4)
“ሁል ጊዜ ሳቅ የለም!”
በገነነ ሀይሌ
በዕንባ ጣልቃ - ሳቅ
ይነግሳል
እየሳቁም ይለቀሳል
ጥሩ አፍቃሪ ይህን ያውቃል
ዘወትርማ መች ይሳቃል::
እየሳቁ እያነቡ
ፍቅርን እንዲያ ነው
የሚገነቡ
ህይወት ማፈራረቅ ልምዷ
ወጣ ገባ ነው መንገዷ!
በፍቅር ሲኖሩ በዚህ
ምድራ በዓለም
የጫጉላ ሽርሽር ሁል
ጊዜ ሳቅ የለም! (ይቀጥላል …)
3) ድምጻዊ ተስፋዬ
ድረሴ፡፡
3.1. ተስፋዬ፤ በ2010
ግጥምና ዜማ የራሱ የሆነውና በመሀመድ ኑርሁሴን የተቀናበረ የመጀመሪያው ነጠላ ዘፈኑ “አብረን እንጨርጭስ!”ን አየር ላይ አውሏል፡፡
የዘፈኑን የመጀመሪያው ረቂቅ ጥር 28፤ 2003 ሁለቱን የግጥም መጽሀፎቹን በብሔራዊ ቴያትር ሲያስመርቅ በዳዊት ጽጌ ባንድ ታጅቦ
በመዝፈን በእለቱ ዝግጅቱን ትመራ የነበረቸውን ባለቤቱን እንዲሁም በመቶዎች የሚቆጠሩ እንግዶቹን አስደምሟል፡፡ ቀጥሎም፣ የሩብ ምዕተ ዓመት የጋብቻ ቀናቸውን በማስመልከት ለባለቤቱ በሲዲ
አበርክቶላታል፡፡ ሙዚቃው በሬዲዮ በስፋት ተሰምቷል፡፡ ተስፋዬ ይህን ዘፈን ከጥቂት አመታት በፊት በዋሺንግተን ሆቴል የፍቅረኞች
ቀን (ቫላንታይን ዴይ)ን አስመለክቶ በተዘጋጀ ኩነት ላይ ባለቤቱን ከጎኑ አድርጎ መድረክ ላይ በመዝፈን ራሱን፣ ባለቤቱንና የእለቱን
ታዳሚዎች አዝናንቷል፡፡ ዘፈኑን ሰዎች እያስፈቀዱት ለዝግጅቶቻቸው እሴት ዋጋ ጨምረውበታል፡፡ “ከመኪናዬ ሲዲ ውስጥ ማውጣት አቃተኝ”
በማለት ዘፈኑን በሚመለከት አበረታች ግብረ-መልስ ከሰጡት በጥበብ መንገድ ተጓዦች መካከል አንዱ ተስፋዬ ማሞ ነው፡፡ የተከበረው
ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠም “ይህ ክስተት ነው” በማለት አወድሶታል፡፡
አብረን እንጨርጭስ!
ያሳላፍነው ጊዜ በጣም
ረዥም ነው
ፍረጅ የኔን ያህል ያፈቀረሽ
ማነው?
ሩብ ምዕተዓመት ሞላኝ
ስወድሽ የምሬን
ካልሞትኩ አልመልስም
የአፍቃሪ ደብተሬን፡፡
ለኔ እንዳንቺ የለም
ላንቺ እንደኔ ልክሽ
ታናሼ ብትሆኚም አብረን
እናርጅ ባክሽ፡፡ ...
ቆዳችን ለስልሶ ከሻሽ
እስኪሳሳ
ልውደድሽ ውደጂኝ እስክንረሳሳ፡፡
ፀጉራችንም በእድሜ ደመና
ይምሰል ጭስ
በፍቅር ተቃቅፈን አብረን
እንጨርጭስ፡፡ ...
ምናልባት ምናልባት እሱም
በምናልባት
እናትሽን ብቻ ነው የምጠረጥረው፤
ያፈቅሩሽ ይሆናል እንደኔ
አሳምረው፡፡
ምናልባት ምናልባት እሱም
በምናልባት
አባትሽን ብቻ ነው የምጠረጥረው፤
ይወዱሽ ይሆናል እንደኔ
አሳምረው፡፡
(እያለ ይቀጥላል)
3.2) በ1982 ራስ
ቴያትር ቤት ዝክረ ኪነጥበባት ላይ እንግዳ ሆኖ ለአራት ሳምንት ያህል ራሱን በክራር እያጀበ ዘፍኗል፡፡ የዘፈነው ለጓደኛው፣ ለዛሬው
ባለቤቱ፤ ለሮማን ቱፋ ከደረሰላት በርካታ ዘፈኖች መካከል አንዱ የሆነው “ተው አለች ተውኩላት” እና “የእግር እሳት” የተሰኙ ሁለት
ዘፈኖችን ነበር፡፡
ተውኩላት
ይህን ሲጋራህን ተው
አለች ተውኩላት
ይህን መጠጥህን ተው
አለች ተውኩላት
ደሞ ማምሸትህን ተው
አለች ተውኩላት
“አርብ፣ ሮብ ሁዳዴን
ጹም” አለች ጾምኩላት
የቡና አመሌን ግን
- እምቢ ብያታለሁ
ከሷ ሌላ አንድ ሱስ
ሲገለኝ አያለሁ፡፡
ያፈቀረ ልቡ የተነካ
በአያያዝ ይለወጣል ለካ
(እያለ ይቀጥላል)
----
3.3) ተስፋዬ በድምጻዊነትና
በአዝናኝነት - የመድረክ ቀልዶችን በማቅረብ ጭምር - ተወዳጅ በሆነው “እርሶም ይሞክሩት” በተሰኘው የመድረክ የመዝናኛ ፕሮግራም
ላይ ተሳታፊ ነበር፡፡ መስሪያ ቤቱ (ዕርዳታ ማስተባበሪያ ማቋቋሚያ ኮሚሽን/ዕ.ማ.ማ.ኮ)ን በመወከል ላሳየው ተሳትፎ የቁሳቁስና
የምስክር ወረቀት በሽልማትነት ተበርክቶለታል፡፡
3.4) በሰራባቸው መስሪያ
ቤቶች ሁሉ በድምጻዊነትና በአዝናኝነት ተወዳጅ የስራ ባልደረባ ነበር፡፡ የመስክ ጉዞ፣ የStaff retreat, እንዲሁም የስብሰባ/ስልጠና
ማብቂያዎች በተስፋዬ የክራር ጨዋታዎች ደምቀዋል፡፡ የኖርዌይ ህፃናት አድን ድርጅት ሥራ አስኪያጅ የነበረው ቢዮን ሀገን
Bjorn Hagen አብሮን የሚኖር አዝናኛችን ነው - He is our resident entertainer በማለት ነበር ለመስሪያ
ቤቱ እንግዶች የሚያስተዋውቀው፡፡ ተስፋዬ ቀልድና ቁምነገር አይጋጩበትም፡፡
4) የዘፈን ግጥም አርታዒው
(critic) ተስፋዬ ነው፡፡
ተስፋዬ ድረሴ - አንዳንድ
የአማርኛ ዘፈኖች ከህፃናትና ሴቶች መብትና ደህንነት አንጻር ያላቸውን “አሉታዊ” ሚና በመንቀስ፣ ማህበረሰቡን ለአዎንታዊ ለውጥ
ከማዘጋጀት አንጻር ዝግምተኛ መሆናቸውን በመተንተን ጽፏል፡፡ ማኅበራዊ
ጉዳዮች ላይ የተደረሱ በርካታ ዘፈኖች የተለመዱ አስተሳሰቦችን የሚደግሙ (recycle የሚያደርጉ)፣ የዜጎችን ስህተቶች የሚያደምቁ
እንጂ ከማህበረሰቡ አንድ እርምጃ የቀደሙ ያለመሆናቸውን (ጥበባዊነታቸው ውስን መሆኑን) አስመልክቶ ጽፋል፡፡ ለአብነት፤ በኢትዮጵያ
ደራሲያን ማህበር መጽሄት (ብሌን) ላይ “ዘፈን፣መዝሙር እና ዘፈመዝሙሮቻችን” በሚል ርዕስ ያቀረበው ጽሁፍ የተለየ አተያይን ያስተዋወቀ
በመሆኑ ከአንባቢያን አድናቆትን አስገኝቶለታል፡፡ ይኸው ጽሁፍ በሸገር 102.1 (ሸገር ሼልፍ) - በአንዱዓለም ተስፋዬ ሶስት ጊዜ
ተነቧል፡፡ የድምጽ ፋይሉ (Audio) በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያ አማካይነት
ተሰራጭቷል፡፡ በ2012ም “ዘፈኖቻችን ይፈተሹ” በሚል ርዕስ - በተለያዩ ቋንቋዎች የተዘፈኑ እና እየተዘፈኑ ያሉ እጅግ ብዙ ዘፈኖች
(ብዙ ትኩረት ሳይሰጣቸው) አሉታዊ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኙ ጠቁሟል፡፡
የቀደሙ ጥበባቂ ስራዎችንም አድንቋል፡፡ ይህ - ለፍልስፍና እና ለመጠየቅ ያለውን ዝንባሌ የተጠቀመበት አንድ አውድ ነው፡፡
5) መጣጥፈኛው ተስፋዬ
ተስፋዬ ድረሴ የተለያዩ
ጋዜጦች ላይ፤ ከላይ የተጠቀሰውን ጨምሮ፣ ከ50 በላይ መጣጥፎችን/ጽሁፎችን በማቅረብም ይታወቃል፡፡ ብዙዎቹ ጽሁፎች የወጡት በጋዜጦች
ላይ ነው - አዲስ አድማስ፣ አዲስ ዜና፣ አዲስ ዘመን፣ በቅርቡም “አስኳላ” (4 በእንግሊዝኛ፤ ሄራልድ ትሪቢዩን) ላይ፡፡ በጋዜጣ ላይ ካወጣቸው መጣጥፎች (ጽሁፎች) “የኮርማዎች ውጊያ፣” “ዘፈን፣
መዝሙርና ዘፈ-መዝሙር፣” “ባንዲራ ነክ ወጎች” በ102.1 ሸገር ሬዲዮ 102.1 ላይ ተነበዋል (በአንዱአለም ተስፋዬ እና በተስፋዬ
ማሞ እና ትዕግስት ማሞ፡፡) የተስፋዬ ጽሁፎች የተለመዱ አስተሳሰቦችን የሚሞግቱ ናቸው፡፡ ለአብነት - “ከሰደበኝ የነገረኝ” በሚል
ርዕስ ያቀረበው ጽሁፍ በየስብሰባው ላይ አሉታዊ ተረትና ምሳሌዎችን ከመሰብሰብ ይልቅ አዎንታዊ አንድምታ ያላቸውን አዳዲስ “ተረትና
ምሳሌ”ዎች ፈጥሮ በማህበረሰቡ ውስጥ መናኘት እንደሚሻል ጠቁሟል፡፡ እሱ ከፈጠራቸው “ተረቶች” ለአብነት፡- “ልጅን ያሳተፈ በከፊል
አረፈ፣” “ለእህቱ ያላዘነ ሚስቱም ላይ ጨከነ! “ለጀበና ማቶት፣ ለልጅ ምቾት!” “ልጅ አያውቅም ያለ ራሱን አታለለ!” “ኃይለኛ
ወላጅ ልጁን ሳያውቅ ያረጅ!” “ጠዋት ከልጁ ጋር አስተዋውቀኝ ሲመሽ ስለአባቱ ጠይቀኝ!” “ሰነፍ አባት ለልጆቹ ይሰንፋል፣ ጎበዝ
ለጎረቤት ይተርፋል!”
ይህን ተረት እየፈጠሩ
ወደ ማህበረሰቡ የመናኘት ዘዴ እሱ በአሰልጣኝነት በተሳተፈባቸው አውዶች ተጠቅሟል፡፡ ተፈላጊውን ውጤትም አይቶበታል፡፡ ለምሳሌ
“ልጅ ደረሰ፤ ቤት ፈረሰ”ን፣ “ልጅ ደረሰ ቤት ታደሰ” በማለት ቀይሮ በማለማመዱ አንፕካን - ኢትዮጵያ የሚባል አንጋፋ ድርጅት
ህፃናትን እያሳተፈ ያሳትም በነበረው “የህፃናት ድምጽ” መጽሄት ላይ ህፃናት አዎንታዊ አንድምታ ያላቸው ተረቶችን ሲሰበስቡ ይህን
እና ሌሎችንም ተረቶች አግኝተው አካተው አሳትመዋል፡፡
6) የህፃናት መጽሀፍት
ደራሲው ተስፋዬ ድረሴ፡፡
ተስፋዬ ተረቶችን
Comic Storiesን አፍላቂ ነው፡፡ በ2007 በሶስት የበጎ አድራጊ ድርጅቶች (Save the Children, Master
Card, PADet) በጋራ ባወጡት ጨረታ አሸናፊ በመሆን 50 ወጥ (Original) አስቂኝና አስተማሪ ታሪኮችን የያዙ 11 የህፃናትና
የወጣቶች የንባብ መጽሀፍትን በአማርኛ ቋንቋ አሳትሟል፡፡ ሙዚቃን በመጠቀም እንዳደረገው ሁሉ፣ በህፃናት መጽሀፍት ውስጥ ባካተታቸው
መጽሀፍት ለልጅም ሆነ ለአዋቂ የሚመጥኑ ታሪኮችን አካቷል፡፡
7) የሥልጠና ባለሙያው
ተስፋዬ
ተስፋዬ ድረሴ የተዋጣለት
አሰልጣኝ/አመቻች (Trainer/facilitator) መሆኑን ብዙዎች ይመሰክሩለታል፡፡ ከ1987 ጀምሮ “አሰልጣኝ”ነትን/አመቻችነትን
የመደበኛ ሥራው አካል አድርጎ (ከ2007 ወዲህ ደግሞ ከመተዳደሪያዎቹ እንደ አንዱ በማድረግ) ኖሮበታል፡፡ በአሰልጣኞች አሰልጣኝነት
Trainer of Trainers ይሰራ ለነበረበት ድርጅት ሠራተኞች፣ ድርጅቱ በአጋርነት ለሚደግፋቸው አገር በቀል በጎ አድራጎት
ድርጅቶች (ሜሪ ጆይ፣ የጎዳና ተዳዳሪ ህጻናት ማኅበር፣ አይሪሽ ኤድ፣ ወዘተ)፣ ት/ቤቶች፤ ከዚህም በማለፍ ለበርካታ ዓለምአቀፍና
አገር በቀል በጎ አድራጎት ድርጅቶች ሰራተኞች፣ የወጣቶች ክበባት፣ የቴያትር ቤት ሠራተኞች ሰጥቷል፡፡ ለአብነት፡ እ.ኤ.አ በ2012 ለብሔራዊ ቴያትር ቤት ሰራተኞች፣ አርቲስቶችን ጨምሮ፤
“የተግባቦት ጥበብ” ላይ የግማሽ ቀን ስልጠና፣ በቅርቡ (በ 2013) ለ6ኛው ዙር የምርጫ ታዛቢዎች የአሰልጣኞች ስልጠና ሰጥቷል፡፡
አቶ ተስፋዬ ቀደም ሲል
ጀምሮ ታዋቂነትን ያተረፈው በተግባቦት ክህሎት
(Communicatioin Skill) ቢሆንም፣ ያለውን የረዥም አመት የህይወት ተሞክሮ፣ ሙያዊ እውቀትና ኪነጥበባዊ እይታ በመጠቀም
በተለያዩ የማህበራዊ ዘርፎች ስልጠናዎችን ይሰጣል፡፡ በልጅ አስተዳደግ፣ ከህፃናትና ወጣቶች ጋር አብሮ የመስራት ጥበብ፣ የህፃናት፣
የማህበረሰብ ተሳትፎ፣ የሪፖርት አፃፃፍ ጥበብ፣ የፎቶግራፍ አነሳስና አሰናነድ፣ የመልካም ተሞክሮ ስነዳ፤ የደንበኞች አያያዝ (በቅርቡ
ለናሆም የጥርስ ህክምና ተቋም) ወዘተ፡፡ በአማካሪነትም ከጀማሪ አገር
በቀል በጎ አድራጊ ድርጅቶች እስከ በመቶ የሚቆጠሩ አገር በቀል ድርጅቶችን የሚረዱ ድርጅቶችን አገልግሏል፡፡ ለምሳሌ - CSSP (Civil Sosiety Support Programe) የሙያውን
ፍሬ አጋርቷል፡፡
የተስፋዬ የስልጠና መድረክ
በርካታ የኪነጥበብ ዘርፎችን ያካትታል - ግጥም፣ ዜማ (መዝሙር/ዘፈን)፣ ድራማ፣ ኮሜዲ፣ ተረት፣ ወዘተ፡፡ እሱ በሚያስተምርበት
ወይም በሚመራው ስብሰባ አዳራሽ ውስጥ ኪነጥበብ ባይተዋርነት አይሰማትም፡፡ ተሳታፊዎች ይዘፈናሉ፣ ይገጥማሉ፣ ይደንሳሉ፡፡ ይህን
በማድረጉም፣ ብዙ ስልጠናዎች ላይ የሚታየው ማዛጋት፣ መቁነጥነት፣ ማንቀላፋት በሱ መድረኮች ላይ አይታሰብም፡፡ ከዚህም ሌላ፣ ህፃናትና
ወጣቶች ከአንጋፋ ባለሙያዎች፣ ከወላጆች ጋር ወዘተ ቀላቅሎ በማስተማር (ለህፃናትና ወጣቶች ተገቢውን ክብር በመስጠት) ስልጠናዎች
ውጤታማ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡
😎
ተስፋዬ የስነዳ እና የሰነድ አያያዝ ባለሙያ ነው፡፡
ተስፋዬ፤ በኖርዌይ የህፃናት
አድን ድርጅት ውስጥ በዶክመንቴሽን አስተባባሪነትና በኮምንኬሽን ማኔጀርነት ሲሰራ ያካበተውን እውቀት በመጠቀም (በ2006 ድርጅቱን
በራሱ ፍላጎት ለቅቆ፣ በግሉ መስራት ከጀመረ ወዲህ) የብዙ ድርጅቶችን መልካም ተሞክሮ (good practices) እንዲሁም ታሪክ
በመጽሀፍ (Booklet) መልክ አሳትሟል፡፡ ሰነዶቹ ለግጥሞች፣ ተረቶች ተገቢውን ቦታ የሚሰጡ ናቸው፡፡ አቀር በቀል እና ዓለም
አቀፍ ድርጅቶችን በማማከርም ሙያዊ አገልግሎት ሰጥቷል፡፡
9) ተስፋዬ የድራማ
ደራሲም ነው/ነበር፡፡
10) አነቃቂ ንግግሮች
ተስፋዬ ለገጣሚያንና
ለሌሎችም ወጣቶች ቅርብ የሆነ እንደመሆኑ፣ ብዙ መድረኮች ላይ በመገኘት ልምዱን አካፍሏል፤ አነቃቅቷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ፣ እንደ
የፍቅረኞች ቀን፣ የእናቶች ቀን፣ የአባቶች ቀን በተሰኙ ዝግጅቶች ላይ በእንግድነት እየተጋበዘ እና ከባለቤቱ ጋር እየተገኘ ዘርፈ-ብዙ
ተሞክሮውን በሚያምር ሁኔታ ሲያካፍል ቆይቷል፡፡ በቅርቡም፣ ከ30 ደቂቃ ጀምሮ ረዘም ላሉ ሰዓታት የሚፈጁ የአነቃቂ ንግግሮች፣ እና
ትምህርቶችን ለተለያዩ ታዳሚዎች በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡ እንደተለመደው፣
የሚመራቸው መድረኮች በልዩ ልዩ የኪነጥበብ ሥራዎቹ የበለፀጉና ከበርካታ የህይወት ተሞክሮዎቹ በሚመነጩ አነቃቂ ንግግሮች የዳበሩ
ናቸው፡፡
11) ሶሽዮሎጂስቱ ተስፋዬ
ድረሴ፡፡
የሥራ ልምድ - ተስፋዬ
በተቀጣሪነት መጀመሪያ በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር (ከነሀሴ 1975 - እስከ ታህሳስ 1983 - በመሃከል ለ4 ዓመት በትውስት
ለእርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን) በመቀጠል፤ በኖርዌይ ህፃናት አድን ድርጅት Redd Barna/Save the
Children Norway-Ethiopia (ከጥር 1983 - መስከረም
2006) አገልግሏል፡፡ ከሙያው ጋር የተያያዙ በርካታ ስልጠናዎችን በአገር ውስጥ እና ከአገር ውጭ ተከታትሏል፡፡ ለተፈጥሮ ዝንባሌዎቹ
ሰፊ እድል ለመስጠት በማሰብ ከ2006 – ጀምሮ የራሱን የንግድ ተቋም (ተስፋዬ ድረሴ የማስታወቂያ ሥራ) በማስኬድ ላይ ይገኛል፡፡
በሙያው በሚከተሉት ዘርፎች
የላቀ ውጤት አስመዝግቧል፡፡
- በድርቅ ወቅት ከወላጆቻቸው
የተለያዩ ህፃናትን መልሶ በማገናኘትና፣ ወላጅ ለሌላቸው ህፃናት ዘላቂ መፍትሔዎችን በመጠቆም፣ አዳዲስ የመረጃ መሰብሰቢያ ስልቶችን
በማስተዋወቅ የራሱን አሻራ አኑሯል፡፡ ርዕሱን በሚመለከት አገር ውስጥና ከአገር ውጭ ተሞክሮውን አጋርቷል፡፡
- የህፃናት መብቶች
ኮንቬንሽንን በማስተዋወቅ፣ የህፃናት ተሳትፎን በሚመለከት የተለያዩ የማስተማሪያ ስልቶችን በመተግበርና ሰርቶ በማሳየት፣ አካላዊ
ቅጣትን ከቤትና ከት/ቤትና ለማስወገድ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን በመምራት፣ ሴቶችና ህፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች እንዲቆሙ ድምጹን
በማሰማት ወዘተ የጎላ ሚና ተጫውቷል፡፡
- የኖርዌይ ህፃናት
አድን ድርጅት የተከተላቸው የገቢ ማስገኛ ስልቶችን ከሌሎች ባለሙያዎች ጋር ሆኖ በማዳበር፣ እንዲሁም በሚያነሳቸው ፎቶግራፎች፣ ቪዲዮዎችና
በሚጽፋቸው አዎንታዊ ስሜትን የሚያዳብሩ ጽሁፎች ድርጅቱም ሆኑ ድርጅቱ የሚደግፋቸው አገር በቀል ድርጅቶች ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ
(ብዙ ሚሊየን ዶላሮችን) እንዲያገኙ አስችሏል፡፡ በዚህ ረገድ ስልጠናዎችንም ሰጥቷል፡፡ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በህፃናት መብት ዙሪያ
የሚተላለፉ ፕሮግራሞችን ይዘት በመገምገምም ያግዝ ነበር፡፡
- ልዩ የምስክር ወረቀት
- 13ኛው የዓለም አቀፍ የህፃናት ቀንን በማስመልከት - የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የህፃናት አድን ድርጅት ህብረት
- በኢትዮጵያ Save the Children Alliance - Ethioiopia በጋራ - “የህፃናት መብቶች ኮንቬንሽንን በማስተዋወቅ፣
ህፃናት ተኮር ኪነጥበባዊና ስነ-ጽሁፋዊ ሥራዎችን በማዘጋጀት ላበረከተው አስተዋጽዖ … የአድናቆት/ምስጋና የምስክር ወረቀት ሰጥተውታል፡፡
12) በርካታ የህፃናት
ጨዋታዎችን ከትምህርት ጋር በማያያዝ፣ አዳዲስ ጨዋታዎችንም በመፍጠር - ለትምህርት ቤቶች እና በስልጠና አጋጣሚ ላገኛቸው ሰዎች
አጋርቷል፡፡ ከነዚህ መካከል “ድንጋይ ቅነሳ” በሚል ርዕስ የፈጠረው ተማሪዎች ውጤታቸውን እንዲያሻሽሉ የሚያነቃ ስልት ይጠቀሳል፡፡
ተስፋዬ ድረሴ እና ከህይወቱ
ጋር ተያያዥነት ያላቸው ወጎች
ተስፋዬና ግጥም መቼ
ተገናኙ?
ግጥምና ተስፋዬ የተዋወቁት
ገና የሶስተኛ ክፍል ተማሪ ሳለ ነው፡፡ አንድ ቀን አስተማሪው፤ ቲቸር ክብረት መንገሻ፣ ለአንዲት “በላይነሽ አሥራት” ለምትባል
የክፍሉ ተማሪ (ልጅቱ የጀምጀም አውራጃ ዲሬክተር ልጅ ናት) እዚያው በዚያው እየገጠሙ ጥቁር ሰሌዳው ላይ በሚያምር የእጅ ጽሁፍ
ሲያሰፍሩ ይመለከታል፡፡ በአስተማሪው ችሎታ ይደነቃል፡፡ ግጥሙ እነሆ፡-
“በላይነሽ በላይነሽ
ከሁሉም በላይነሽ
በርቺና መርምሪው በአሁኑ
እድሜሽ
ልጅነት ካለፈ ኋላ እንዳይቆጭሽ፡፡”
ተስፋዬ፤ ወደ ኋላ ዞሮ
በማሰብ የአጭር ግጥምን እንጎቻዊ ሙሉነት የተረዳው ያኔ መሆኑን ይናገራል፡፡
ተስፋዬ ግጥሞቹን ለህትመት
ከማብቃቱ በፊት ሥራዎቹን በተጋበዘባቸው መድረኮች - ለምሳሌ፤ ቀንዲል ቤተ-ተውነት የግጥም ምሽት - ላይ እያቀረበ የተደራሲያንን
ጭብጨባ እና ፉጨት ጠግቧል፡፡
ተስፋዬና ዘፈን መቼ
ተገናኙ?
ህፃኑ ተስፋዬ፣ ለመጀመሪያ
ጊዜ በማያውቃው ሰዎች ፊት የዘፈነው ገና ሰባት አመት ሳይሞላው ነው፡፡ ያኔ ዘፈነ፤ የጭብጨባን ጣዕምም ቀመሰ፡፡ አውዱ ይህ ነበር፡-
መስከረም ለአዲስ አመት ትምህርት ቤት በተከፈተ ሰሞን፣ የሁለተኛ
ክፍል ተማሪዎች ስም ጠሪ የነበረች መምህርት ከተማሪዎቿ ጋር ለመተዋወቅ ወደ ሜዳ ትወስዳቸውና ክብ አሰርታ ስማቸውን ከጠየቀች በኋላ
“እስቲ ዘፈን የሚችል” ብላ ትጠይቃለች፡፡ በወቅቱ በጣም ፈሪና ዝምተኛ የነበረው ተስፋዬ እጁን አውጥቶ “እኔ” አለ፡፡ ቀጥሎም፤
በሚጢጢ መዳፎች ጭብጭባ ታጅቦ እንዲህ ብሎ ዘፈነ፡-
ተራራ ነው ቤቱ
(4)
- ያበራል ጥይቱ፡፡
አሊ ቦሩ መጣ፣ ቦረና
ደረሰ (2)
የፈረሱን ጭራ እየነሰነሰ!
ተስፋዬ “ጎበዝ” ተባለ፡፡
ደስ አለው፡፡ ማታ እናቱን ከማግኘቱ ዛሬ “ዘፈንኩ” ብሎ ይነግራቸዋል፡፡ ምን እንደዘፈነ፣ የት እንደ ዘፈነ ሳያጣሩ እቅፍ አድርገው
ይስሙትና “ጎበዝ የኔ ልጅ እስቲ ምን እንደ ዘፈንክ ልስማ” ይሉትና ያንኑ ግጥምና ዜማ ደግሞ ይዘፈንላቸዋል፡፡ በቀደመው አመት፣
ከልጆች ጋር አልቀላቀል አብሬ አልጫወት ብሎ አስቸግሮ የነበረው ልጃቸው ጭራሽ ለመዝፈን መብቃቱ ያስደሰታቸው እናቱ በድጋሚ ከሳሙትና
ካጨበጨቡለት በኋላ በህይወት ዘመኑ የማይረሳውን ትምህርት ሰጡት፡፡
“ተሳስተሃል” በማለት ፈንታ - "ለወደፊቱ እንዲህ ብለህ ዝፈን" ብለው አረሙት፡-
“ከላላ ነው ቤቱ(4)
- ያበራል ጥይቱ፡፡
ለካስ “ከላላ” ወሎ
ውስጥ የሚገኝ ቦታ ስም ኖሯል! መጀመሪያ አድንቆ፣ አጨብጭቦም ማረም አለ ለካ! “ተሳስተሃል” ማለት ሳያስፈልግ ስህተትን ማረም
ይቻላልና! ሙሉውን ስራ ሰህተት ነው ከማለት የተሳሳተውን ብቻ በትህትና ለማረም ይቻላልና! ይህን ከእናቱ የተማረውን ስልት ተስፋዬ
ዛሬም ይጠቀምበታል፤ ያስተምርበታልም፡፡
ተስፋዬ ድረሴና ሙዚቃ - የደበዘዘ የሙዚቃ ተሰጥዖ
ታሪክ
ተስፋዬ ሥደተኛ ሠፈር
ውስጥ በድምጻዊነት ይታወቁ ከነበሩት ከነ መላኩ ደጉ፣ ሙሉጌታ ሩፎ ጋር የሚወዳደር አልነበረም፡፡ ይሁንና ሆያሆዬ ላይ “አውጪ”
አቀንቃኝ የመሆን አጋጣሚዎች አያልፉትም ነበር፡፡ ለሆያሆዬ ማዳመቂያ ሀርሞኒካ መንፋትም እንዲሁ፡፡ ሁሌም የማንጎራጎር፣ የመዝፈን
ፍላጎት ግን ነበረው፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ 7ተኛ ክፍል ሲደርስ የዘፈን ግጥሞችን በስነ-ስርዓት ጽፎ በማጥናት በክፍል ጓደኞቹ
ዘንድ ተወዳጅ አዝናኝ ለመሆን በቅቶ ነበር፡፡ ስምንተኛ ክፍል ሲደርስ (1964)፣ በቀደሙ አመታት የነበረበት አይናፋርነት ጥሎት
እየሄደ ነበር፡፡ አንድ የትምህርት ክፍለ ጊዜ አልቆ ሌላ አስተማሪ እስኪለወጥ ድረስ ወደ መድረክ ወጣ ብሎ መቀለድ፣ ማሳቅ ልማዱ
ሆነ፡፡
መጥፎ አጋጣሚ - በዚህ
ሁኔታ ላይ እያለ አንድ አስደንጋጭ ነገር ገጠመው፡፡ ለክፍሉ ተማሪዎች ለመዝፈን ገና እንዴት አድርገው እንደሚያጨበጭቡ እያለማመዳቸው
ሳለ በውጭ መስኮት በኩል አንድ ረዥም፣ ሪዛም፣ ጥቁር በራ ሰው እየተመለከተው እንደሆነ ያስተውላል፡፡ ተስፋዬ ክው ብሎ ይደነግጣል፡፡
ሰውየው “እጅ ከፍንጅ ያዝኩህ” በሚል ፉከራ ተንደርድሮ ይገባና ተስፋዬን ማጅራቱን ጨምድዶ ወደ ቢሮው ይወስደዋል፡፡ ከዚያም ከጭንቅላቱ እስከ ጀርባው በሚጋደም የግራዋ ልምጭ ይገርፈዋል፡፡ ሁለተኛ እንዲህ ያለ ብልግና እንዳይደግመውም
አስጠንቅቆ ይለቀዋል፡፡ ዘፈን ያህን ያህል የሚያስገርፍ ጥፋት መስሎ ታይቶት አያውቅ የነበረው ታዳጊው ተስፋዬ ከዚያን ቀን ጀምሮ
በይፋ መዝፈን አቆመ፡፡
በእኩዮቹ ፊት በድጋሚ
መዝፈን የጀመረው ከሁለት አመት ጽሞና በኋላ “የእድገት በህብረት የእውቀትና የሥራ ዘመቻ ላይ ነው - ቦሬ! ያኔ በምሽት ሜዳ ላይ
እሳት ዙሪያ (camp fire) ተሰብስቦ መዝፈን የተለመደ ነበር፡፡ ተስፋዬም የተለያዩ ድምጻውያንን በተለይም የአያሌው መስፍንን
ዘፈኖች በመዝፈን ተወዳጅና አዝናኝ ለመሆን በቃ፤ ዘፈን ነክ ፍርሃቱም ለቀቀው፡፡ በ1969 ክራር መግረፍና መደርደር ተማረ፡፡ ለራሱና
ለቅርብ ጓደኞቹ ማንጎራጎሩን ቀጠለ፡፡ ከዚያ ደግሞ በ1970 ሻኪሶ የወጣቶች ኪነት ቡድን አቋቁሞ፣ ከድምጻውያን አንዱ ሆኖ ይዘፍን
ነበር፡፡ ለብዙ አመታት መድረክ ላይ የመዝፈን ፍላጎት ሳያሳይ፣ ከዘፈን ይልቅ ወደ ድራማ ድርሰት እያደለ ሲሄድ ቆይቶ ፍቅር ሲይዘው
የዘፈን ግጥም ለመድረስ መታገል ጀመረ፡፡ እሱና ክራር ጨርሶ የማይለያዩ ሆኑ፡፡ በ 1980 ከ30ኛ አመት ልደቱ ጋር አያይዞ ለጓደኛው፤
ለአሁን ባለቤቱ፤ የዘፈነላትን 10 ያለቀላቸው ዘፈኖቹን በካሴት ቀድቶ አበረከታላት፡፡ ዘፈን ድርሰትን መለማመድ ቀጠለ፡፡ በ1981/82
“እርሶም ይሞክሩት” በሚባል የመዝናኛ ፕሮግራም መድረኮች ላይ በመዝፈንና ቀልዶችን በማቅረብና በማዝናናት (ተሸላሚ ለመሆን በቃ)፡፡
በ1982 ራስ ቴያትር ተጋባዥ ድምጻዊ ለመሆን በቃ፡፡ ሙዚቃ ነክ እንቅስቃሴው አንዴ ደመቅ፣ አንዴ ብዥ እያለ ሳይቋረጥ ቀጠለ፡፡
ተስፋዬ ድረሴ እና ግጥም
ያላቸው ቁርኝት
የተስፋዬ ድረሴ የህይወት
ታሪክ ውስጥ ግጥም ቁልፍ ቦታዎችን ይዞ ይገኛል፡፡ ለአብነት የሚከተሉት ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ሀ) ግጥም መተከዣው፣
ራሱን ማረጋጊያው ነው፡፡
በ1975 - ተስፋዬ
ድረሴ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፕላይድ ሶሽዮሎጂ 4ኛ አመት ተማሪ ሆኖ “መች ተመርቄ፣ መች ከትምህርት ተገላግዬ” እያለ ባለበት ሰዓት በሁለት የትምህርት አይነቶች
ብዙ ተማሪዎች “F” ማግኘታቸው በግቢው ይወራል፡፡ ሁለቱም ትምህርቶች ጠጣር ሂሳብ ያለባቸው ነበሩ፡፡ ተስፋዬ ደግሞ የሂሳብ ቁስለኛ
ነውና ላልመረቅ እችላለሁ የሚል ስጋት ያድርበታል፡፡ ያኔ ነው ለራሱም “ተስፋዬ” ላሉት ወላጆቹም “ሊዘገይ” መሆኑ አስተክዞ ከላይ
የተቀመጠችውን “ተስፋዬ” የተሰኘች ግጥም የጻፈው፡፡
ሌላ ጊዜ ደግሞ - የእግር
ጉዞ ድካሙን ሊቀንስለት በቅንነት በመኪናው በነጻ ያሳፈረው ሰው ሲወርድ ከኋላ ወንበር ላይ አንድ እቃውን ይዞበት መሄዱን ባወቀ
ጊዜ በጎ ነገር ከማድረግ መቆጠብ እንደሌለበት እና ለምን መቀጠል
እንዳለበት ራሱን ለማሳመን (ለሌሎች ቅኖችም ማበረታቻ እንዲሆን፣ ደግነት ተጨማሪ ክፍያ እንደሚያስከፍል በምሳሌ) የሚከተለውን ግጥም
ምርግማን ላይ ጽፏል፡፡
ደም ልገሳ
እኔው ወድጄ
ደም ልሰጥ ሄጄ
መርፌ ተወጋ እጄ -
ተገድጄ
ደግነቱ፣ ደግነትን አውቀዋለሁ
“እሺ” ላለው ተጨማሪ
ክፍያ አለው፡፡
ለ) ግጥም አቤቱታ ማቅረቢያው
ነው፡፡ ለየት ያሉ ወጎች ይቀጥላሉ፡-
ወጣቱ ተስፋዬ በ1976
ዲላ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ተመድቦ ይሄዳል፡፡ ቢሮው ውስጥ መቀመጫ ወንበር ግን አልተዘጋጀለትም ነበር፡፡ ይህን
ሲያይ፤ “ቶሎ ካልመጣልን” እያሉ አዋሣ የነበረውን የክ/ሀገሩን ቢሮ ሃላፊ ሲያስጨንቁ የነበሩትን የዲላ አውራጃ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት፤
አቶ ግርማ ወ/ጻድቅ (በኋላ ከፍተኛ አድናቂው የነበሩ ሰው)ን ቁራጭ ወረቀት ላይ ጽፎ ይህን ይጠይቃቸዋል፡-
ካልተሰጠኝ ቦታ መቀመጫ
ወንበር
እኔ ዝንብ አይደለሁ
አልንሳፈፍ በአየር
ትርፍ ነህ ካላችሁ ምን
ነበር እዚያው ብቀር?
(ይላቸዋል፡፡ እዚያው ሀዋሳ ማለቱ ነው)
ወደ አዲስ አበባ ሊዛወሩ
የተተኪያቸውን፤ የተስፋዬን፤ መለማመድ ብቻ ይጠብቁ የነበሩት የጽ/ቤቱ ኃላፊ፤ የእንግዳቸው “ውስጠ ወይራ” ግጥም ያስደንቃቸውና “አባትህ ባለቅኔ ኖረዋል?” ብለው ይጠይቁታል፡፡ ተስፋዬ ድረሴም፤ ለአንድ
አምስት ደቂቃ ያህል ከፊታቸው ገለል ብሎ ካሰበ በኋላ ይህን በቁራጭ ወረቀት ላይ ጽፎ ይሰጣቸዋል፡-
“መዘውተሩ እንጂ በገዳሙ
መምህር (2)
ቅኔ ቅመራ እንኳ የአያሌ
ሊቅ ነበር
ሆሄያት ሽብሸባው ጥበብ
ቢጠይቅም
ችግር የባሰበት ከመስረቅ
አይርቅም!”
ይህን ሲሰሙ - በልጅነታቸው
ቅኔ የተማሩት አቶ ግርማ “ይበል! ይበል! … ና የኔ ወንበር ላይ ተቀመጥ” ብለውት ጓዳ ከሚገኝ አንድ የሂሳብ ሰራተኛ ወንበር
ላይ ይቀመጣሉ፡፡ ተስፋዬም አመስግኗቸው የአለቃው ወንበር ላይ ተቀምጦ ሲያበቃ፤ የሚከተለውን ሙገሳ አሁንም ቁራጭ ወረቀት ላይ ጽፎ
ይሰጣቸዋል፡-
“ጭቅጭቅ ጉዳቱን አባቴ
ቢረዳ
ሳሎኑን ለቆልኝ ገባ
ወደ ጓዳ!”
ጎረምሳ መሆኑን አይተው
ለቢሮ ሀላፊነት ብቁ አይሆን ይሆናል ብለው የጠረጠሩት ሰው፤ ጭራሽ በግጥም ያነጋግራቸው ገባ፡፡ ስለዚህም፤ በእሱ መደሰታቸውን ለመግለጽ፤ “አንተ ትክክለኛ ምትኬ ነህ” ይሉታል - አለቃው፡፡ ተስፋዬ ግን ብዙ መደነቅ
አልታየበትም፡፡ ምክንያቱም እሳቸው በረዥም አመት የስራ ልምድ የደረሱበትን ደሞዝ (ብር 450) ያለፈው በመጀመሪያ የዲግሪ ደሞዙ
(ብር 500) ነው፡፡ እሳቸው ይህን አላወቁም፡፡ በዚያ ላይ ወንበራቸው ምቾት ያለው አልነበረም፤ አጭር፣ ቅብር ያለ ነው፡፡ ለማንኛውም
“ሰሙ” ወንበራቸው ይሁን ብሎ ይህን ግጥም እንደለመደው በቁራጭ ወረቀት ላይ ጽፎ ይሰጣቸዋል፡-
“አግኝቼ ነበረ ስም
ያለው ወንበር
ትንሽ አዘቅዝቆ ባያሰኘኝ
ቅር፡፡”
ዝርዝሩን ተነጋግረው
ተሳሳቁ፡፡ ተስፋዬ ሌላ ከፍ ያለ ወንበር እንደሚያስፈልገው ተመኙለት፡፡
ከግጥም ወደ ዝርው
- ማመልከቻ (ተጨማሪ ወግ)
ከዚሁ ቢሮ ሳንወጣ
- ተስፋዬ በቢሮዋ ጥበት ተገርሞ አቶ ግርማን ይጠይቃቸዋል፤ “ቢሯችን ጠባብ ሆነችሳ!”
አቶ ግርማም ታዛቢ ስላገኙ
ይደሰታሉ፡፡ ቀደም ሲል የነበራቸው ሰፊ ግቢ ለወቅቱ የመንግሥት ፓርቲ (ኢሠፓአኮ) አንደኛ ጸሀፊ ተላልፎ ተሰጥቶባቸው እንደዚያ
ያለ ችግር ላይ መውደቃቸውን በቁጭት ያጫውቱታል፡፡ አከታትለውም፤ ቢሮው ከሚዋረድ ቢዘጋ ይሻላል በሚል በቀጥታ ለሠራተኛና ማህበራዊ
ጉዳይ ሚኒስትር፤ ለብርሃኑ ባይህ፤ የሚላክ ደብዳቤ እንዲጽፍ ይጠይቁታል፡፡
ተስፋዬም መ/ቤቱ ላይ
የደረሰውን በደል አሳምሮና አምርሮ ይጽፍና ደብዳቤው ይላካል፡፡ በምላሹም፤ ጽ/ቤቱ እንዲዘጋ ተወስኖ ባለሙያዎች ዲላ ይመጣሉ (ያኔም
ብዙ ግጥሞችን አዝንቧል - ተስፋዬ፡፡ አቶ ግርማም ቁርጥራጭ ወረቀቶቹን መሰብሰብ ቀጥለዋል)፡፡ እቃዎችም ለቆጠራ ደጅ ወጥተው ይኮለኮላሉ፡፡
ዋናዋ ክፍል እቃ አልባ ስትሆን ከቀድሞውም የበለጠ ጠብባ ታየች፡፡ በዚህን ጊዜ አቶ ተስፋዬ እንደ ልማዱ በቁራጭ ወረቀት ላይ ይህን
ጽፎ ያቀብላቸዋል፡-
“አንተ ጽ/ቤቴ ጨለማ
ውጦህ
ምነው ለአንድ አፍታ
ብርሃኑ ባይህ!”
ብርሃኑ ባይህ ሚኒስትሩ
ናቸው፡፡ የተስፋዬ አለቃ በደስታ ሰከሩ፡፡ አንግዶቹም ተደነቁ፡፡ ቢሮው ተዘጋ፡፡ እቃው ተጭኖ ወደ አዋሳ ተጓዘ፡፡ ለሚኒስትሩ በስማቸው
የተፃፈላቸው ግጥም በመጡት ባለሙያዎች አማካይነት ደረሳቸው፡፡ የተስፋዬ ዝና በመሥሪያ ቤቱ ናኘ፡፡ ገና አንድ አመት ሳያገለግል
በዋናው መሥሪያ ቤት ደረጃ ታዋቂ ሆነ፡፡ ከዚህ ጋር ተያያዥነት ያለው ታሪክ፤ ለ10ኛው የአብዮት በዓል 3000 (ሶስት ሺህ) ያህል
ስራ አጥ (የተባሉ፣ በየበረንዳው ተኝተው የተገኙ) ሰዎች ታፍሰው ፍቼ ከተማ ተወስደው ነበርና፤ ለእነሱ የስነልቦና ተሀድሶ ሊሰጡ
የሚችሉ ነቃ ነቃ ያሉ ሶሾሎጂስቶች፣ ሳይኮሎጂስቶች ከሁሉም የመ/ቤቱ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ይሰብሰቡና ወደ ፍቼ ካምፕ ይላኩ ተብሎ
ጥሪ ሲደረግ፣ ተስፋዬ ከተመረጡ ጥቂት ባለሙያዎች አንዱ ሆኖ ወደ
ፍቼ አመራ፡፡ ቀጣዩን ይመልከቱ :-
ሐ) ለተስፋዬ ግጥም
የትዳሩ መሰረት ነው፡፡ “ምርግማን” ላይ“ግጥሜ” የሚላት የዛሬ
ባለቤቱን ያገኛት ከላይ ለተጠቀሰው ፕሮጀክት በጸሀፊነት/ታይፒስትነት
ተቀጥራ ፍቼ መጥታ ነው፡፡ በተዋወቁ ማግስት፣ በቁራጭ ወረቀት ላይ ይህን ነበር ጽፎ የሰጣት፡፡
“ጣጣ፣ ጣጣ ጣጣ፣ ጣጣጣጣጣጣ!
አወይ ፍዳ ጣጣ
አንቺ ታይፑን ታይፑን
ታይፑ ጆሮ ግንዴን
የያዝሺው መሳሪያ አሸበረው
ሆዴን!”
ከ20 ዓመት የዘለለ
የፍቅር ቆይታ በኋላ ደግሞ ባለቤቱን እንዲህ በማለት አወድሶ ግጥሙን ምርግማን የመጨረሻው ገጽ ላይ አሳትሞታል (በ2000)፡-
ሰው-ሰው-ሎጂ ተማርኹ
አሰልጣኝ ሆኜ አማርኹ
በዕውቀት ረሰረስኹ
- ተቆረጠ ጥሜ
መጠሪያ ማዕረጌ ግን
እንቺ ነሽ ግጥሜ!
(ለሮም)
መ) ግጥም የስራ ባልደረቦቹን
ማድነቂያው፤ የሚያከብራቸውን ሰዎች ማወደሻው ነው፡፡ ለምሳሌ፤ ለቀድሞው የዕርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን ኮሚሽነር፣ ቀጥሎም
የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ለነበሩት ለአቶ ሽመልስ አዱኛ (አንድ አየር ጣቢያ አግኝቷቸው) ይህን ግጥም በቁራጭ ወረቀት
ላይ ጽፎ አበርክቶላቸዋል፡፡ ግጥሙን በቃላቸው ይዘውለታል፡፡
“ድሆች ናችሁ” ያሉን
“ድሆች” ነን ወይ እኛ
በእጃችን እያለ ሺ መልስ
አዱኛ?”
“አዱኛ” ሀብት የሚል
ፍቺ ስላለው ነው እንደዚያ ያላቸው፡፡
ለአትሌት ሻለቃ ኃይሌ
ገ/ሥላሴ በ”ምርግማን” ላይ፡-
የአበሻ ወጌሻ - ኃይሌ
ቆፍጣናው
ሰባራ አንገቴን - ስንተዜ
አቀናው?! በማለት አወድሶታል፡፡
በ22.8.2003 ሀዋሳ ከተማ የተካሄደ
”ሁሉም” የተሰኘ ታላቅ ሩጫ (የእናቶችና የህፃናትን ሞት የመቀነስ ዘመቻ አካል) ላይ አትሌት ኃይሌ በዘመቻው አስተባባሪዎች (አንደኛው ተስፋዬ ነው) በተጠየቀው
መሰረት ፊርማውን ለገቢ ማስገኛነት) (fund raising) ለገሰ፤ ለዝግጅቱ ላይም ለተሳታፊዎች በእንግሊዝኛ ንግግር አደረገ፡፡
በዚህ ድርጊቱ የተደነቀው ተስፋዬ ሁለቱንም ተግባሩን በማድነቅ የሚከተሉትን
የውዳሴ ግጥሞች በቁራጭ ወረቀት ላይ ጽፎ አበርክቶለታል፡፡
በዚህም ዘመን - ምትሃት
አለ - ግን ማን ያምናል?
አትሌት ኃይሌ፣ ፊርማህ
ብቻ ነፍስ ያድናል፡፡
----
ኃይሌ ይሉት አትሌት
ስንቱን አሳሰበን?
መች በሩጫ ብቻ በቋንቋም
ደረበን፡፡
-----
እጅግ ለሚያደንቀው ወጣት
ገጣሚ፤ ለ ”በእውቀቱ ሥዩም” ም በስጦታ ባበረከተለት መጽሀፉ (ምርግማን) ላይ ይህን ጽፎለታል፡-
“ከኛ የቀደሙ - ይህን
ወግ አላዩም
በቲፎዞ ሳይሆን - በእውቀቱ
ሥዩም”
የግጥሙ ሀሳብ፤ በእውቀቱ
በገጣሚነት ከፍ ያለ ሰገነት ላይ የወጣው፤ “ገጣሚ” ተብሎ የተሰየመው፤
ባሳየው የረቀቀ የግጥም ችሎታ እንጂ በዙሪያው ያሉ ሰዎች ስለመሰከሩለት አይደለም የሚል ነው፡፡
ሠ) ግጥም፤ በመደበኛ
ሙያው ከተሰማራባቸው አውዶች በቂ መልስ ያላገኘላቸውን ጥያቄዎችን ማንሻው ነው፡፡ ለምሳሌ፤ ፆታዊ ትንኮሳን፣ ሴቶች ላይ የሚደርስ
ጥቃትን ለማስቀረት “ህጉ መጥበቅ አለበት” ለማለት የሚፈጥኑ ባለሙያዎችን ለመምከር፤ “አበባ”ንም “አበበ”ንም አስቡ ለማለት “የዕድሜ
አስቤዛ” ላይ ይህን ጽፏል፡-
የአስተማሪ ያለህ
ህግ ወጣ የሚቆጣ
በእስር የሚቀጣ - መግደል
የሚቃጣ
ለሴቷስ ቀን ወጣ
ለወንድ ልጆቼስ መካሪ
ከየት ላምጣ?
ረ) ግጥም፤ የመኪና
አደጋን፣ የትምህርት ጥራትን የሚመለከቱ እንቅስቃሴዎችን መደገፊያውም ነው፡፡
ቀበቶ ማሰር ህግ ሆኖ
ከመውጣቱ አስቀድሞ “እግዜር ቀበቶ አያስር” በሚል ርዕስ ጽፏል፡፡ ዜጎችን ሀላፊነት ውሰዱ፣ በማንም ላይ አታሳብቡ ለማለት ሙግቱን
በብዙ ስንኞች አቅርቧል፡፡ እነሆ በከፊል፡-
እግዜር ቀበቶ አያስር
“የአበሾች እግዚአብሔር
የሥራ መዘርዝር
በምድር የሌለ ነው ላስተዋለው
ከምር
ህዝቡ ሰነፈና በዕንባ
እየለመነው - እየተማጸነው
የማይሰራው የለም “እሱ”
የማይከውነው፡፡
መኪና ስትነዳ ቀበቶህን
እሰር
ሲሉት በግድፈቱ ሲሆን
እንደማፈር
ምን ያደርጋል ይላል
መጨነቅ መቸገር
የተቆረጠች ቀን ላትቀጠል
ነገር፡፡
የእሱን ቀላል ስራ ለአምላኩ
ሰጥቶ
እዩት ሰነፍ ሾፌር አያስርም
ቀበቶ፡፡
(እያለ ይቀጥላል)
“ምርግማን” ላይ ደግሞ
“የራስ መንገድ” በሚል ግጥሙ - የመንገድ መስፋት ብቻውን ከአደጋ አያስጥልም በማለት ይሞግታል፡፡
የራስ መንገድ
ትራፊክ ፖሊሱ - ስንቱን
ፈር ያስጨብጥ፣ ስንቱን አንድ ይበለው?
ስንቱን አስቁሞ ይቅጣ፣
ስንቱን ያቻችለው?
ሰው መተላለፊያው -
ጎዳናው እንደሆን ራስ ውስጥ ነው ያለው፡፡
አሽከርካሪ በእውቀት
በስርዓት ይርቀቅ
በምክር በተግሳጽ በህግም
ይታረቅ
አሊያ ግን ይጠንቀቅ
መጋጨቱ አይቀርም መንገድ
ቢንቦራቀቅ፡፡
የትምህርት ጥራት መጓደልን፤
የትምህርት ስርዓታችን ላይ የሚያያቸውን እንከኖች በሚመለከትም፤ “ትምህርታችን” በጠቅላላ እውቀት እያኩራራ ወደ ጠቅላላ ውድቀት የሚገፋ፣ …. ነው - ለማለት
“ኤ-ፎር-አፕል”ን ጽፏል፡-
ኤ-ፎር-አፕል/A
for Apple
ፈረንጅ ላገሩ ህፃን
ጣፋጭ ፍሬ መርጦ
ያውም እያሳየው ከጓሮው
ዛፍ ቆርጦ
ደግሞም - እያስነካው
ማለት እያስለካው
... በእጁ አስጨብጦ
ጣዕሙን እያስለየ በጥርሱ
አስገምጦ፤
ፊደል ሲያስቆጥረው
... አስቦ እንዲቀለው
“በ - በሬ” እንደ
ማለት
”ኤ - ፎር - አፕል”
አለው፡፡
ታዲያ የነሱ ፈደል ሲመጣ
ወደኛ አገር
አፕሉ እዚያው ቀረ ወንዝ
ሳይሻገር፡፡
ሆኖም ከመጻፍ ላይ ስዕሉ
ስላለ
አፕል የ “ኤ” አስታዋሽ
ሆነና ቀጠለ
ቀጥሎ፣ ቀጥሎ እስከ
ዛሬም አለ፡፡
እንዲያ፣ እንዲያ ሆነና
እንደዚያ ሆነና
እኛ አገር ተፋቱ ፊደልና
ቃና፡፡
አፕል ሳይኖር ገና
ኤ - ፎር- አፕል!
ኤ - ፎር-አፕል! ብለው
ፊደል አንበልብለው፤
የተማሪን ላንቃ፣ ትናጋ
ያስከፈቱ
በግምት፣ በጭፍን
በልሙጥ ሽምደዳ የባዕድ-አፍ
ያስፈቱ፤
ሞልተዋል መምህራን ተማሪዎችም
አለን
ሳያዩ በማመን
ሳይነኩ በመማር በዓለም
አቻ የሌለን!
የግርጌ ማስታወሻ፡-
ዛሬማ አፕል አለ፤
ወይ የቦሌ ሃብታም
ይልቁንም ደሞ የጨንቻ
ልጅ ያውቃል፤
የአራዳ መምህርም ገዝቶ
እንኳ ባይቀምሰው
ኢት ፍሩት ቆም ብሎ
ዋጋ ይጠይቃል፡፡
ሰ) ለተስፋዬ ድረሴ
ግጥም ከሚያደንቃቸው አንጋፋ ባለሙያዎችና ጠቢባን ዜጎች ጎን መቀመጫው፣
“አንቱ” እያለ “ኖር!” መባያው ነው፡፡ ከልዩ ገጠመኞቹ አንዱ እነሆ፡-
የኢትዮጵያ ደራሲያን
ማህበርን 50ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ምክንያት በማድረግ፤ “የአፍሪካ ደራሲያን ዓለም አቀፍ ጉባኤ” (International
Confrence of African Writers) የሚል መድረክ አዘጋጅቷል - እ.ኤ.አ ሜይ 2 - 4፣ 2011፡፡ ቦታው የማዘጋጃ
ቤት አዳራሽ ነው፡፡ ታላላቅ እንግዶች እንዲሳተፉ የሚጠበቅበት ታላቅ
ኩነት ነው፡፡ ሥርዓቱ ይጀመራል የተባለው ከጠዋቱ 2፡30 ነው፡፡ ተስፋዬ ድረሴ ከጠዋቱ 2፡15 ላይ ከስፍራው ደርሶ ከአዳራሹ በር አካባቢ ይንጎራደዳል፡፡
አርፍጃለሁ ብሎ በጥድፊያ እየነዳ የመጣው ሰውዬ ከበር ላይ አንድ
ሰው እንኳን አጥቶ ተገርሟል፡፡ ከአንድ አምስት ደቂቃ በኃላ፣ አበባ
የያዙ ሰዎችን አዳራሽ ውስጥ ይመለከትና የስብሰባውን ቦታ ያለመሳሳቱን
እርግጠኛ ይሆናል፡፡ ነገር ግን የስብሰባው ተሳታፊዎች ተገኝተው ቦታ ቦታቸውን ያለመያዛቸው እንዳሳሰበው ይቆያል፡፡ “በዚህ አይነት፣
ስብሰባው በስንት ሰዓት ሊጀመር ነው? ወይ እኛ ና ሰዓት!”) እያለ
ራሱን ይጠይቃል።
በዚህ ሁኔታ ላይ እያለ፤
እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌና አንጋፋው ጸሀፊ ተውኔት አያልነህ ሙላት ወደ አዳራሹ በጥድፊያ ሲመጡ
ይመለከታል፡፡ እነሱም ያረፈዱ መስሏቸው እንደ ተጨናነቁ ከአረማመዳቸው
ተረድቷል፡፡ ጋሽ አያልነህ፤ ወደ ተስፋዬ እየተጠጋና እጁን ለሰላምታ እየዘረጋ “እንዴ ተስፍዬ፣ ሰው የለም እንዴ?” ብሎ ይጠይቃል::
ሰውየው፣ አንዴ ወደ ኦናው አዳራሽ አንዴ ወደ ተስፋዬ እየተመለከቱ ይጠጉታል፡፡ እሱም የማደግደግ ያህል አጎንብሶ ሰላምታ ይሰጣቸዋል፡፡
እኒያን ለምድር ለሰማይ የከበዱ ባለሙያ ባለሙያ እና ኩሩ ብቻ ሳይሆን ቀብራራ ዜጋ እንዴት ብሎ ማነጋገር እንዳለበት አላወቀም፡፡
እሳቸው ፊታቸውን ዞር ዞር እያደረጉ ግራና ቀኙን ማስተዋል ይጀምራሉ፡፡ ይኼን ጊዜ፣ ጋሽ አያልነህ በእጅ ምልክት ተስፋዬን ይጠራውና፤
“እባክህ ተስፍዬ ከጉድ አውጣኝ፡፡ ይሄ ሰውየ በሰዓት ቀልድ አያውቅም፡፡ የጥሪው ሰዓት ካለፈ ጥሎ ነው የሚሄደው?” ይለዋል፡፡
“ምን ላድርግ?” ይለዋል፤ ተስፋዬ፡፡
እነዚያን “አጫጭር፣
ቦምብ፣ ቦምብ ግጥሞችህን ልቀቅበት” ይለዋል፡፡ ወዲያውም እጁን እንደ ልጅ አንጠልጥሎ ወደ ሰውየው በማስጠጋት “ከተስፍዬ ጋር በደንብ
ላስተዋውቅህ” ይላቸዋል፡፡ ቀጥሎም ''እስቲ ከነዚያ ግጥሞችህ፤ ከአጫጭሮቹ
አንድ ሁለት አቅምሰልኝ” ይለዋል፡፡ ተስፋዬ አላመነታም፤ በቅድሚያ ስንጥርን፣ ቀጥሎ፣ ጌሾ ወቀጣን፣ ቀጥሎ ጥሩምና ነፊውን፣ ከዚያም
“ድንጋይ ፈንቃዩ”ን በቁሙ ይወርድላቸዋል፡፡
ጌሾ ወቀጣ
ዘነዘና እንጨት - ሙቀጫም
እንጨት
ጌሾ ቦነነ በመበሳጨት
ሲነረት ሀቁን ገና አሁን
ዋጠው
የራስ ወገን ነው የሚያስወቅጠው!
ድንጋይ ፈንቃዩ
ስሜት ሲያፈላልግ ፍቅር
ነው ሸምጋዩ
አውጥቶ ያገናኛል ኤሊን
ከድንጋዩ!
ሰውየው በእያንዳንዱ
ግጥም ሲስቁ፣ ይቆዩና “You are a poet! ትልቅ ገጣሚ/ባለቅኔ ነህ … ይገርምሃል፤ Painting ስዕልም እንደዚሁ ነው፡፡
ዋናውን ሀሳብ ካገኘህ፣ እሱ ላይ ነው ቀሪውን ቀለም የምትቀባው” አይነት ነገር እያሉት - ቁጭ ብለው የሚጨዋወቱበትን ቦታ በአይናቸው
መፈለግ ይጀምራሉ፡፡ ጋሽ አያልነህ፣ ቀደም ቀደም እያለ “ኑ፣ እዚህ” ብሎ ሁለቱን ወንበር ያስይዝና፣ እሱም በጨዋታቸው ላይ መሳተፍ
ይጀምራል፡፡ ትንሽ ቆይቶ፣ ኢንጂነር ታደሰ ብጡል ይዳበላሉ፡፡ ለእሳቸውም ከግጥሞቹ እንዲያቀርብ ይጠየቅና ተስፋዬ አንድ ሁለት ግጥሞችን
ይጋብዛቸዋል፡፡
እንዲያ እንዲያ እያሉ
አራቱ ሲጫወቱ፤ አዳራሹ ሞልቶ ስብሰባው መጀመሪያው ደረሰና “ግቡ” ይባላሉ፡፡ አሁን የወንበር ልዩነት የሚመጣ መሆኑ ተስፋዬ አልጠፋውም፡፡ ሰውየው፣ “ና እዚያች ጋ” ሲሉት “ግድ የለዎትም ይኼ
የእርስዎ ወንበር ነው፤ እኔ አንድ ሁለት ወንበር ወደ ኋላ ልዝለል ብሎ ይለያቸዋል፡፡ ሁለቱ ጠቢባን ከዚያን ቀን በፊትም፣ ከዚያን
በኋላም ተገናኝተው አያውቁም፡፡
ሰ) ለተስፋዬ፤ ግጥም አማራጭ መልዕክት/እውቀት ማስተማሪያና ማዝናኛ መሳሪያው
ነው፡፡ በርካታ ማህበራዊ አውዶች ላይ ቁም ነገር አዘል ግጥሞቹን በማቅረብ የተያዘው ርዕሰ ጉዳይ ከጥበብ አንጻር ሲታይ ምን እንደሚመስል
ያሳያል፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ባለሙያዎችም ከግጥም መጽሀፎቹ የተወሰኑ ግጥሞችን በማንበብና በማስነበብ ስልጠና ተካፋዮች ወይም
ሰልጣኞች እንዲነቃቁባቸው ያደርጋሉ፡፡ ከጤና ባለሙያውና ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በመተንተን ታዋቂ የሆነው ዶ/ር ኤርሲዶ ለንዴቦ
እንዲሁም ሌላው የማህበራዊ ጉዳዮች ምሁር ደረጀ ሽፈራው በአሰልጣኝነት ከሚይዟቸው ቁሳቆሶች መካከል አንዱ የእድሜ አስቤዛን መሆኑን
ይናገራሉ፡፡
ተስፋዬ ግጥሞቹን ለማሳየት
ዘግይቷል? - ሌላ ወግ!
ተስፋዬ ግጥሞቹን ሰብስቦ
ለማሳተም አልፈጠነም፡፡ ይህን በማስመልከት፤ የመጀመሪያ መጽሀፉ ጀርባ ላይ ይህን ግጥም አውጥቷል፡፡
ራስን ፍለጋ
“ራሴን ሳላገኝ ብዙ
አመት የሞላኝ
የት ይሆን የእድሜ ጅብ
አጋድሞ የበላኝ!?”
ሁለተኛው የግጥም መጽሀፉ፤
ምርግማን፤ ላይም “ራስን ፍለጋ” ላይ ግጥም አለው፡፡ በዚህኛው ግጥሙ፣ የእድሜ ጅብ ያልበላው መሆኑን፣ ራሱ ያልጠፋ መሆኑን ያውጃል፤
እንዲህ በማለት፡-
ላልጠፉ
ራሴን ፍለጋ ወጣሁ ወደ
ደጋ
ርቄ አልፌ ኬላ ተመለስኩኝ
ቆላ፤ ምሳ እንኳን ሳልበላ፡፡
ስዋከብ ሳላየው ስንት
አመት ስሸበር
'ጠፋ' ያልኩት ራሴ
- አንገቴ ላይ ነበር፡፡
መጽሀፎቹን ያሳተመው
በራሱ ጊዜ መሆኑን ለራሱ ለመመስከርና “ሰዎች ከኔ መፍጠን ምን ጉዳይ አላቸው?” የሚል የራሱን ጥያቄ ለመመለስ ደግሞ እንዲህ ብሏል:-
የመብራት ውስጥ ጋን
ከነፍሴ ጋን ውስጥ ተደብቆ
የኖረው ፋኖሴ ርቆ
ቀኑን ቆጥሮ ---
ተሰማምሮ ---
--- ቢወጣ አደባባይ
ዕልፍ አዕላፍ ሰው መጣ
“በጣም ዘገየህ” ባይ
በኔ ብርሃን ጨረር የየራሱን
ጋን ሊያይ!!
ተስፋዬ ከበርካታ የግጥም
ታዳሚዎች ጋር የተገናኘው መቼ ነው?
ተስፋዬ እስከ 20ኛ
አመቱ ድረስ በቃላት ሲጫወት፣ በግጥሞቹ ሲስቅና ሲያስቅ ቆይቶ፤ የ12ኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን (ያኔ እድሜው 21 ሆኗል) - ግጥሞቹን
በአደባባይ የሚያቀርብበትን አንድ ትልቅ አጋጣሚ አገኘ፡፡ የአመቱ ትምህርት ማጠናቀቂያ ላይ በተደረገ የግጥምና የድራማ ውድድር በሁለቱም
አሸናፊ ሆኖ ነበርና ግጥሙን በአማርኛ መምህሩ በይልማ ጥሩነህ የመድረክ አጋፋሪነት መድረክ ላይ አነበበ፡፡
በፑሽኪን የኪነጥበብ
ማዕከል በእንግድን ግጥሞችን ካነበባቸው ምሽቶች በአንዱ ላይ የክብር እንግዳው ክቡር ዶክተር ጥላሁን ገሠሠ ነበር፡፡ ተስፋዬ መድረክ ላይ በእሱ የመሸለምን ክብር አግኝቷል፡፡ ከዝግጅት በኋላም አብረው ቆይታ እንዲያደርጉ ጥላሁን ጋብዞት፣ ከሌሎች አርቲስቶች
(አያልነህ ሙላት፣ ችሮታው ከልካይ፣ ….) ጋር፤ ባለቤቱም በተገኘችበት ሀሳቦችን ተለዋውጠዋል፡፡ ተስፋዬ ያነበባቸውን ግጥሞች በሰማ
ቁጥር ጥላሁን ሞቅ አድርጎ ሲያጨበጭ ነበር፡፡ ጥላሁንን ከወንበሩ ከወዘወዙት ግጥሞች አንዱ “ባለሳምንት” የሚለው ነበር፡-
ባለሳምንት
በቀዳም ስዑር (“ቅዳሜ
ሹር”) ዕለት እልፍ አዕላፍ ዶሮ
አንገቱ በካራ ተቀንጥሶ
አድሮ
ለዘር አልተረፈም -
አውራ አለቀ ሲባል
ከቢላ ያመለጠው፣ ኩ
- ኩ - ሉ - ኩ! ይላል፣
ይጣራል፣ ያቅራራል
ወንድሙን ሊያስበላ ፋሲካን
ያበስራል፤
የሞተ ቀረ እንጂ ህይወት
ይቀጥላል፡፡
የተስፋዬ ግጥሞች ከፊል
ባህሪ
የተስፋዬ ድረሴ ግጥሞች
በአብዛኛው “ሰው-ሰው-ሎጂያዊ” ናቸው፡፡ ማህበራዊ እውነታን የሚያንፀባርቁ፤ አንድ ሶሾሎጂስት (ማህበራዊ ኑሮ ባለሙያ) በዝርው
ቢጽፍ የሚገልጻቸው ወይም አንድ የስነልቦና አማካሪ በምክር ደረጃ እንዲናገራቸው የሚጠበቁ፤ ቁምነገሮች ናቸው፡፡ ለአብነት የእድሜ
አስቤዛ - “ብድር በምድር”ን ይጠቅሳል፡፡ የግጥሙ ጭብጥ፣ ኃይለኛ ሆነው፤ የልጆቻቸውን ነጻነት አቆርቁዘው፣ በማብላትና በማጠጣታቸው
ወይም አስተምረው ከፍተኛ ደረጃ በማድረሳቸው ብቻ የሚኩራሩ ወላጆች በሚያረጁበት ወቅት ልጆቻቸው በተራቸው ልክ እነሱን ያደርጉዋቸው
እንደነበረው ሁሉ “ነጻነታቸውን” ከልክለው አሽቀርቅረው ለአደባባይ በማውጣት(ታቸው) ይኩራራሉ የሚል ነው፡፡ አንዳንድ ቱባ ግጥሞቹ በጠለቀ እውቀት የሚተረተሩ ናቸው፡፡ ለምሳሌ፤ “ጉራማይሌ” የሚለው መንቶ ግጥሙ እንዲህ ይነበባል፡፡
ጉራማይሌ
ባህል በየፈርጁ አለው
ጉራማይሌ
እንጀራ በሹካ ጠጅ በብርሌ፡፡
የግጥሙ ቋጠሮ ሲፈታ
ይህን ይመስላል፡- እንጀራ ኢትዮጵያዊ ባህል ነው (ቁሳዊ ባህሉ ሲታይ፤ ጤፉ፣ ምጣድና አከንባሎው፣ መስቲው፤ ጉልቻና መሰቅሰቂያው፣
ማሰሻው ሳይቀር፤ አገር በቀል ነው)፡፡ እንጀራው ከወጥ ጋር በቀረበ ጊዜ ግን፤ አንዳንዴ ፈረንጆች ወይም ዘመናይ አበሾች እንደሚያደርጉት፤
በሹካ የሚበላ ከሆነ ባህሉ ጉራማይሌ ይሆናል፤ ሹካው የኢትዮጵያ ቁሳዊ ባህል ውጤት አይደለምና፡፡ ልክ እንደዚሁ፤ ጠጅ ኢትዮጵያዊ
ነው፡፡ በጋንም ተጣለ በእንጨት በርሜል (ከተጠረበ ጣውላ የሚሰራ) የኛው ነው፡፡ ጠጁ የሚቀዳው ግን ብርሌ ውስጥ ከሆነ ባህሉ ጉራማይሌ
ይሆናል፡፡ ምክንያቱም፣ ብርሌ የኢትዮጵያ ቁሳዊ ባህል ውጤት ባለመሆኑ፡፡ ይህ ግጥም፤ ሰዎች “ባህላችን” “ማንነታችን” ብለው የሚኮሩባቸው
ነገሮች (ቁሳቁሶች) በከፊል፣ መሰረታቸው ከኢትዮጵያ ውጭ መሆኑን እንዲያስተውሉ ይረዳል፡፡
ግጥሞቹ የት ደረሱ
?
የተስፋዬ ድረሴ ግጥሞች
በአዲስ አበባ በሚገኙ ሬዲዮች ብቻ ሳይሆነ በደቡብ ኤፍ ኤም፣ በጎንደር የትምህርት በሬዲዮ በባህርዳር ሬድዮ በተከታታይ ተነበዋል፡፡
የፕሮግራም ማስኬጃ ሆነዋል፡፡ በአገር ውስጥና ውጭ አገር ተሰራጭተዋል፡፡ ፖለቲካ ነክ ጽሁፎችን የሚያቀርቡ መጣጥፈኞች ተጠቅመውባቸዋል፡፡
ከመጽሀፎቹ የተወሰዱ
ግጥሞች ደራሲ ጌታቸው በለጠ ባዘጋጀው የስነጽሁፍ ማስተማሪያ ትልቅ ጥራዝ መጽሀፍ ውስጥ ተጠቃቅሰዋል፡፡ የአማርኛ መምህራን ለፈተና ለሚመርጧቸው ግጥሞች (ምንባቦች) አማራጭ ሥራዎች
ሆነዋል፡፡ ዮሀንስ ተስፋ የተባለ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋ ተማሪ
መመረቂያ ጽሁፉን በ”ምርግማን” ላይ አድርጓል፡፡
የተስፋዬ ድረሴ የግጥም
አይነት ምርጫ
ተስፋዬ - ከረዥም ግጥም
ይልቅ አጭርና እምቅ ያለ ግጥም መጻፍ ነው ምርጫው፡፡ ግጥምን የሚያፈቅሩ ሰዎች፣ የአጥንት መቅኔን እንደሚወዱ ሰዎች ሁሉ አጥንቱን ሰብረው ውስጡን ያገኙታል የሚል እምነት አለው፡፡ ጥር
3/2003 ሁለቱ መጽሀፍቱ በተመረቁ ቀን የወቅቱ የደራሲያን ማኅበር ፕሬዚዳንት የነበሩት ደራሲ ጌታቸው በለጠ፤ “ተስፋዬ ስንጥርን
መዝዞ ስለ አገር ማውራት ይችላል፤ የእድር ጥሩንባ ነፊን በመጥቀስ ብዙ አነጋጋሪ ባህሪያችንን ለማጋለጥ ይችላል … እኔ የወታደር
ልጅ ነኝ፡፡ በውትድርና “አብሪ ጥይት” የሚባል አለ - ጨለማውን ወገግ የሚያደርግ - የተስፋዬ ግጥሞች እንደዚያ ናቸው” አይነት
ንግግር ያደረጉት የግጥሞቹን መቅኔ ስላገኙ ነው፡፡ ከግጥሞቹ ለአብነት እነሆ፡-
ስንጥር
ስንጥር “ማነሽ?” ቢሏት
“ግንድ ነበርኩ” አለች
በጥንት ታሪኳ ስትኮራ
ታምራለች
መውጣት ካቃታት ግን
ከነበር ጉራንጉር
መቅረቷ ነው ቆማ ጥርስም
ሳትጎረጉር!
ጥሩምባ ነፊው
የእድራችን ጥሩምባ ነፊ
ማስታወቂያና መርዶ ለፋፊ
ምነው ሰው መርጦ አፍህ
ያዳላል
የዳኛ ቤት ጋ ድምጽህ
ይጎላል፡፡
--------
(የዚህ ግጥም የግርጌ
ማስታወሻ እንዲህ ይላል፡-)
በሰፈሬ ዳኛ ሆኜ የእድሬ
ታዝቤያለሁ ይህን ነገር
አንድምታውን ይለይ አገር፤
ለሹም ታምነው የሚያለምጡ
የትም ቢሆን አይታጡ፡፡
በዚያው የመጽሀፍ ምረቃ
መድረክ ላይ የክብር እንግዳ የነበሩት ወ/ሮ ታደለች ዳለቾ “ … እኔ የማነበው ረዥሙን ግጥም ነው” ካሉ በኋላ፤ በፊደላት ቁጥር
ከሁሉም ትንሹንና በስንኞች መስመር ቁጥርም አጭር የሆነውን፤ ነገር ግን ሲፈታ ረዥም የሆነውን ግጥም አነበቡ፡፡ እነሆ፡-
ሥራ ለራስ
ለራስህ ሥራ - ለአገርህ
ገብር
እስቲ አንተ ከብረህ - እሷ ትጣ ብር፡፡
(አገሬን እወዳለሁ ያለ
ለራሱ ይስራ፤ ነገር ግን ግብሩን ለአገሩ ይክፈል፡፡ እሱ ከከበረ ግብሩ ስለማይቀርባት አገር አታጣም፤ አትደኸይም” ነው የግጥሙ
መልዕክት፡፡)
የተስፋዬ ድረሴ - የሂሳብ
ቁስለኛ - ዋናው ወግ!
“እዚህ የተገኘሁት ከሂሳብ
ስሸሽ ነው” ማለት የሚያዘወትረው ቀልደኛው ተስፋዬ የህይወት አቅጣጫው የተወሰነው ከሂሳብ (ከቁጥር) ለመሸሽ በሚያደርገው ጥረት
መሆኑን ይናገራል፡፡ ለምሳሌ፤ ትዳሩ ከሂሳብ ርቆ ሶሾሎጂ የመማሩ ውጤት ነው፡፡ ስነጽሁፍን፣ ቋንቋን፣ “ስራዬና ኑሮዬ” ብሎ የዘለቀውም
አንድም ከሂሳብ ጋር በቀጥታ ስለማያነካኩት ነው፡፡
ቁጥር ወይም ሂሳብን
የጠላው ትምህርት ቤት በገባበት በመጀመሪያዋ ቀን ነው፡፡ የቄስ ት/ቤት ሳይማር፣ ወይም በሌላ አጋጣሚ ከፊደላት ጋር ሳይተዋወቅና
ብዙ መቁጠር ሳይችል በቀጥታ ራስ ብሩ ወልደገብርዔል ት/ቤት አንደኛ ክፍል ይገባል፡፡ ከብዙ፣ ከማያውቃቸው ልጆች ጋር መቀመጡ እንግዳ
ነገር ሆኖበት ይጨናነቃል፡፡ አስተማሪው ጀርባቸውን ለጥቁር ሰሌዳው
ሰጥተው የክፍሉን ተማሪዎች በ ”ጎበዝ” እና “ሰነፍ” ለመለየት ተነሱ፡፡ ከዚያም “ጎበዞች” በዚህ ረድፍ “ሰነፎች” በዚህ ረድፍ
ትቀመጣላችሁ” ብለው መፈተን ጀመሩ፡፡
ፈተናው ቁጥር ነው
- ከ1-100 ፈጠን ብሎ መቁጠር፡፡ ተስፋዬና ጥቂት ልጆች እስከ 70 ድረስ እንኳ በቅጡ ሳይቆጥሩ ይቀራሉ፡፡ እናም “ሰነፍ” በሚባለው
ረድፍ እንዲቀመጡ ይደረጋል፡፡ ተስፋዬ ለራሱ እንዲህ ሲል ነገረ “ቁጥር ሰነፍ ነኝ!” ማታ ቤት ሲገባም “ሰነፍ” ምድብ ውስጥ መግባቱን
ለቤተሰቡ ነገረ፡፡ ደግነቱ ማንም ከቁብ የቆጠረው የለም፡፡ ምሽቱ አለፈ፡፡
ሁለተኛ ክፍል ሳለ ደግሞ
ጓደኞቹ ወደቁና ክፍል መድገም ነበረባቸው፡፡ ተስፋዬ፣ “አልፌያለሁ” ብሎ ለማመን አልደፈረም፡፡ እሱን ያሳሰበው አንድም ካለፈ የሚያውቃቸው ጓደኞቹን ትቶ እንግዳ ወደ ሆነ
ክፍል ሊዛወር መሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ፣ ድምጹን አጥፍቶ ከወዳቂዎች ጋር ቁጭ ብሎ ለሳምንት ያህል ሁለተኛ ክፍል በድጋሚ ተማረ፡፡
በሆነ ቀን፣ የሶስተኛ ክፍል መምህር (ያኔ ሁሉንም ትምህርት የሚያስተምረው አንድ መምህር ነበር Self-Contained) እሱ ወዳለበት መጥተው ስሙን ይጠራሉ፡፡
ትንሹ ተስፋዬም “አቤት”
ይላል - እየተርበተበተ፡፡
“እዚህ ምን ትሰራለህ?
አንተኮ አልወደክም፤ አልፈኻል!” ብለው ወደ ሶስተኛ ክፍል አጅበውት ይሄዳል፡፡
እንደምንም ከክፍሉ ተማሪዎች ጋር ተለማመደ፡፡ ዝምተኛ፣ ነገር ግን በእንግሊዝኛ
ትምህርት (Spelling) ጎበዝ ስለነበረና አስተማሪው ቲቸር ክብረት “ጀንትል ማን” የሚል ቅጽል ስም ሰጥተውት ስለነበረ ትምህርቱን
በጥሩ ስሜት መከታተል ቀጠለ፡፡
በዚህ ሁኔታው ግን አልቀዘለቀም፡፡
አራተኛ ክፍል ላይ ከአንድ ጥፋት ሲሰራ ከነበረ ልጅ ጋር ቆሞ ተገኘ፡፡ ምንም እንኳን ንጽህናው ቢረጋገጥለትና ነጻ ቢወጣም ለጊዜው
ተደናገጠ፡፡
ጓደኛው ከግርፍ ለማምለጥ
ሲል ብቻውን ከት/ቤት እንዳይቀር ብሎ በሰጠው መረጃ ተስፋዬ ፈርቶ ከት/ቤት መቅረት ጀመረ፡፡ ከዚያ ልጅ ጋር ከት/ቤት ውጬ መዋል
መጣ፡፡
ከአንድ ወር በኃላ በመምህሩ
ጥረት ወደ ትምህርቱ ተመለሰ፡፡ ነገር ግን የሂሳብ ትምህርትን ጨርሶ ለመጨበጥ ተቸገረ፡፡ ዴሲ ሜትር፣ ዴካ ሜትር የሚባሉ፤ በቀረው
የህይወት ዘመኑ አንድም ቀን፣ በምንም ወረቀት ላይ ያላያቸው ነገሮች አሰቃዩት፡፡ ግርፍ የየእለት ምሱ ሆነ፡፡
አንድ ቀን፤ አራተኛ
ክፍል እያለ፤ የሂሳብ አስተማሪው የብዜት የክፍል ፈተና ሰጥቶ አጠገቡ ቆሞ ሲከታተለው የሆነውን ነገር እያሰበ ይስቃል፣ በውስጡ
ግን ይንሰቀሰቃል (ዛሬም የብዙ ህፃናት አሳዛኝ እጣ ነውና)፡፡ ተስፋዬ ላቡን ጭኑ ላይ እየጠራረገ፤ “4 ጊዜ 5 ሀያ፣ 2 ትን
ጽፈን 0ን እንይዛለን” በማለቱ አስተማሪው በማስመሪያ ጭንቅላቱን ቀወረው፡፡ ተስፋዬ፤ አሁን ስለ ጥምህርት ጥራትና የተማሪና የአስተማሪ
ተግባቦት ምን መምሰል እንዳለበት ሲያስተምር ሳቅ ለማጫር ያህል “… ከዚያ፣ ጭንቅላቴ ሲመታ የያዝኳት ዜሮም ወደቀች፡፡ ለዚህ ነው
ሂሳብ እምቢ ብሎኝ የቀረው” እያለ ይቀልዳል፡፡
አምስተኛ ክፍል ደግሞ
በሂሳብ ለወደቁ ተማሪዎች 15 ነጥብ ተጨምሮላቸው እሱ ብቻ 49 አግኝቶ መውደቁንና በተማሪዎች ፊት መሰደቡን ያስታውሳል፡፡
ተስፋዬ “ማካፈል” ሳይችል
እስከ ስድስተኛ ክፍል የመጀመሪያ መንፈቅ ትምህርት ድረስ በቀሺም ተማሪነት ዘለቀ፡፡ ሁለተኛው መንፈቀ ትምህርት ላይ ግን ከክፍሉ
ተማሪዎች 10ኛ ደረጃን አገኘ፡፡ ነገር ግን አንድ ነገር አበሳጨው፡፡ ት/ቤቱ ጉድ ይላል ብሎ ሲጠብቅ ከኋላ ተስፈንጥሮ ስለመምጣቱ
አንድም አስተማሪ ሳያነሳ፤ ቤተሰቡም ምንም ሳይለው አመቱ አለፈ፡፡ ከዚህ ሂደት የወሰደው “መሻሻል፣ ወደ ፊት መምጣት በራሱ ሊያስደንቅ፣
ሊያስሸልም ይገባል” የሚል ትምህርትን ነው፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ ከሰነፍ
ተማሪዎች ተርታ ራሱን ቀና ሊያደርግ የነበረው ተስፋዬ ሚያዝያ አካባቢ የስድስተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና (ማትሪክ) ተፈተነ፡፡ የሰፈሩ
ልጆች እንዳለ ሲወድቁ እሱ ብቻ አለፈ፡፡ ውጤቱ 44.0 % አግኝቶ ሰባተኛ ክፍል ገባ፡፡ 7ኛና 8ኛ የሂሳብ ውጤቱ በመጠኑ የተሻለ
ቢሆንም ወይ ከሚወድቁ አሊያም ዝቅተኛ ውጤት ከሚያመጡ ተማሪዎች ተርታ አይወጣም ነበር፡፡ 11ኛ ክፍል ብቻ፤ ከእድገት በህብረት
ዘመቻ እንደተመለሰ፤ ከክፍሉ ተማሪዎች 2ኛ ወጥቷል፡፡ ውጤቱን ለሰው ለማሳየት ግን አልተማመነም ነበር፡፡ ይህ መሸማቀቅ፣ እስከ 12 ክፍል ድረስ ተከትሎታል፡፡ ቁጥር ሲያይ ይጨንቀዋል፡፡
የሂሳብ አስተማሪዎች ያስጠሉታል፡፡ እነሱም አይምሩት፤ ወይ ይሰድቡታል ወይ ይገርፉታል፡፡ ተስፋዬ ሞራሉን ከመሰበርና ከት/ቤት ግቢ
ከመራቅ ያተረፉት ሶስት ነገሮች ናቸው፡፡ አንደኛ በሚችላቸው የትምህርት አይነቶች ላይ ማትኩሩ (እና እጅ አልሰጥም ባይነቱ፣ እልሁ)
ሁለተኛው፤ ቤት ውስጥ፣ በእርሻ ቦታ ወላጆቹ የሚሰጡት ምርቃትና አድናቆት የአስተማሪዎቹን ስድብና ማዋረድ በብዙ እጥፍ የሚደመስስለት
መሆኑ እና ከ9ኛ ክፍል በኋላ ተሾመ አማረ የሚባል በትምህርት ጎበዝ የሆነና የሚያስጠናው ብቻ ሳይሆን ወደ ጨዋታ እንዳያደላ ጨምድዶ
የሚይዘው ጓደኛ ማግኘቱ ናቸው፡፡
“ሂሳብ ይሰራል እንጂ
አይጠናም”
ተስፋዬ ታህሳስ አካባቢ
ከዩኒቨርሰቲ ከመባረር ያተረፈውን ምክር ያገኘው አንድ ጀማል ከሚባል የመኝታ ክፍል ተጋሪው ነው፡፡ በ1972 የመጀመሪያ አመት፣
ለመጀመሪያ ሴሚስተር (freshman) ፈተና እንቅልፍ አጥቶ በሚያጠናበት ወቅት፣ ፈተናው ሊጀመር አንደ ነገ፣ ሌሊት በ8፡00 ገደማ
ጀማል ሌላ ክፍል ከጓደኞቹ ጋር ሲያጠና ቆይቶ ሊተኛ ወደ ክፍል ሲመጣ፣ ሌሎች ደባሎቹ ተኝተው ተስፋዬ ብቻውን በጀርባው ተኝቶ ሲያነብ
ያገኘውና “ምን እያጠናህ ነው?” ይለዋል፡፡ ተስፋዬም፣ ቀለል አድርጎ “ሂሳብ” ይለውና ንባቡን ይቀጥላል፡፡ ጀማል - “ሂሳብ ይሰራል
እንጂ አይጠናም!” ብሎት አልጋ ውስጥ ገብቶ ይተኛል፡፡ እስከዚያን ቀን ድረስ በሂሳብ ነገር ሲሰቃይ የኖረው ይህን ሚስጢር የሚነግረው
አጥቶ ነው፡፡ ቀደም ባሉ አመታት ሁሉ በደረቱም ተኝቶ ሆነ በጀርባው ተንጋሎ ያነባል እንጂ ስክሪፕቶ ወይም እርሳስ አውጥቶ አይለማመድም
ነበር፡፡
ተስፋዬ ባገኘው ምክር
መሰረት እስኪነጋ ድረስ ተለማመደ፡፡ ደጋግሞ ሠራ፡፡ ሲያጠና የቆየውን ሁሉ ፈተሸ፡፡ ሳያሸልብ ቁርስ በልቶ ወደ መፈተኛ ክፍል ገባ፡፡
የፈተና ወረቀት ቀረበለት፡፡ የሂሳብ ፈተና ሲያይ ለመጀመሪያ ጊዜ ሳይርበተበት ጥያቄዎቹን ተመለከታቸው፡፡ በከፍተኛ በራስ መተማመን
ስሜት ተፈትኖ ወጣ፡፡ በዚያው ሴሚስተር ከወሰዳቸው ፈተናዎች ውስጥ ሂሳብ፣ ጆኦግራፊና እና ፖለቲካል ኢኮኖሚ የሂሳብ ስሌት ነበረባቸው፡፡
ሁሉንም ተፈጥቶ ጨረሰ፡፡
ከጥቂት ቀናት በኋላ
ውጤቱን ለመቀበል ወደ አንድ መስኮት ተጠጋ፡፡ የውጤት ማሳወቂያ ወረቀቱን ከርቀት ሲያይ፤ ቀይ መቀነት ተጋድሞበታል፡፡ ተስፋዬ አልተደናገጠም፡፡ ክሪስመሰን በማስጠንቀቂያ ካለፈ በቀጣይ የትምህርት ጊዜዎች እንደማይቸገር
ያውቃል - ስለ ሂሳብ አሰራር ገብቶታላ፡፡ ውጤቱ ግን እሱ እንዳሰበው አልነበረም፡፡
ውጤት ከሚያከፋፍሉ ሴቶች
አንዷ ድምጽዋን ከፍ አድርጋ “ተስፋዬ ድረሴ” ብላ ተጣራች፡፡ “አቤት፤ አለሁ” ይላል ተስፋዬ፡፡ ሴትየዋ ወረቀቱን ከነቀይ መቀነቱ
እያሳየችው “ብራቮ፣ ብራቮ - ኦነር ሊስት (Honour list) ስምህ የዩኒቨርሲቲው የክብር መዝገብ ውስጥ ገብቷል!” አለችው
በደስታ እየተፍነከነከች፡፡ “ተስፋዬ የስም ስህተት ካለ ብሎ ወረቀቱን ደጋግሞ ተመለከተ፡፡ እውነትም የራሱ የፈተና ውጤት ነው፡፡
3:4 አምጥቷል (ሂሳብ
Bን ቀላቅሎ A እና Bዎች)፡፡
ተስፋዬ ለብዙ አመት
በሂሳብ የተነሳ ስሜቱ ተጎድቷል፡፡ ዛሬ ድረስ በህልሙ በሂሳብ ምክንያት ሲገረፍ ወይም ተለዋጭ አስጨናቂ ህልም ያያል፡፡ እንዲህም
ሆኖ የሂሳብ አስተማሪዎቹ ላይ ቂምና ጥላቻ የለመውም፡፡ ይህንንም በእድሜ አስቤዛ ላይ ባሰፈረው የሚከተለው ግጥም ገልጾአል፡-
የሂሳብ ቁስለኛ
በዚህ ብለው - በዚያ
ብለው
ባየው፣ ባየው - ባየው
ባየው
የደብተሬን ከመጽሀፌ
ባስተያየው - መላው ገዶኝ
ከምንጣሬ፣ ከቁፋሮ
- ከእርሻ በላይ ሂሳብ ከብዶኝ፤
የቤት ሥራዬ ላይ አፍጥጬ
አምሽቼ በዚያው እንቅልፍ ወስዶኝ
እልህ ሲቃ አንድዶኝ፤
ጧት የክፍል ሥራዬ
…
ጣሪያ እያስቆጠረ በፍርሃት
አርዶኝ
ላቤ ወርዶ አዋርዶኝ፤
ውጤቴ ባነሰ
ውስጤ በኮሰሰ - ክብሬ
በቀነሰ
ለምን ነበር መምህሮቼ
የገረፉኝ?
“ደደብ” ብለው የዘለፉኝ
ሌላ ቢቀር፣ ማንበርከኩን
ያላለፉኝ?
የግርጌ ማስታወሻ ፡-
“ከዱላ በስተቀር ሌላ የማትጊያ ስልት ስላልነበራቸው (ነው መቼም) በግርፍ ብዛት ላስመረሩኝ፣ በእኩዮቼ ፊት “ደደብ” ብለው ሰድበው
ላዋረዱኝ የሂሳብ መምህሮቼ ሁሉ የተላከ ልባዊ የይቅርታ ደብዳቤ ይሁንልኝ፡፡” ይላል፡፡
ትልቅ ወግ
- “ሰው-ሰው-ሎጂስት?” ተስፋዬ ድረሴ
ብዙ ሰዎች ልዩ ችሎታዎችን
በመታዘብ ለምን ቴያትር፣ ስነጽሁፍ፣ ሙዚቃ፣ እንዳልተማረ ይጠይቁታል፡፡ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ እይታውን ሲያጋራ
ለምን ይህን፣ ያን አልተማርክም
ይሉታል፡፡ እነሆ ማብራሪያው፡፡
ተስፋዬ፤“ሰው-ሰው-ሎጂስት”
የሚለውን “ቃል” ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማው በ1973 ከአንድ ተስፋዬ አመነ ከሚባል የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ነው፡፡ ከዚህ፤ እሱ “ተስፍሽ”
ከሚለው ሞክሼው ጋር የተዋወቀው እድገት በኅብረት የእውቀትና የሥራ ዘመቻ (1967 — 1968) ላይ ነው፡፡ ሁለቱም ቦሬ ምድብ
ጣቢያ ዘማቾች ነበሩ፡፡ ዘመቻው በ1968 ከተጠናቀቀና ከተለያዩ በኋላ በአይነስጋ የተገናኙት ተስፋዬ 6 ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ከገባ በኋላ
ነው - በ1972፡፡ ያኔ ተስፋዬ አመነ (ተስፋሽ) የአራተኛ አመት ተማሪ ነበር፡፡ ሁለቱ፤ ግቢው ውስጥ አንድ ሁለት ቀን ተገናኝተው
በቁም ተጨዋውተዋል፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት ተስፋዬ የህይወት አቅጣጫውን ለመወሰን ጭንቀት ውስጥ በነበረበት ሰዓት ነው፡፡ ነገሩ
እንዲህ ነው፡- ተስፋዬ የመጀመሪያውን አመት የዩኒቨርሲቲ ትምህርት (freshman) ሶስት ተርም እንዳጠናቀቀ በ6ኪሎ ዩኒቨርሲቲ
ይሰጡ ከነበሩ የትምህርት አይነቶች አንዱን መምረጥ ነበረበት፡፡ “መምረጥ” ያልመረጡትን መተው ነውና - ድርጊቱ ለእሱ ቀላል አልነበረም፡፡
መምረጥን ሲያስብ ከዚህ ቀደም አራት ኪሎ ከአንድ መጽሀፍት ቤት ጎራ ብሎ ከመደርደሪያ ላይ አንስቶ በቁሙ ካነበባቸው ውስን ገጾች
መካከል ቀልቡን የማረከው ጥቅስ ይታወሰዋል፡፡ ጥቅሱ የቤንጃሚን ፍራንክሊን (1976-1790፡ a statesman, author,
publisher, scientist, and diplomat) ነው፡፡ “How many selves have you, and which
of these selves would you like to perfect?” (ስንት እኔነቶች በውስጥ አሉ፤ ከነዚህ መካከል የትኛውን
ነው ብታልቅ የምትወደው?) ይላል፤ በጥያቄ መልክ የቀረበው ጥቅስ፡፡
ምርጫውን ለማሳወቅ የቀረው
ቢበዛ ሁለት ሰዓት ነው፡፡ ተስፋዬ - የትኛው ዝንባሌውን መርጦ የትኞቹን ይጣል? የሆነ ትምህርት (ዲፓርትመንት) ካልመረጠ ደግሞ
ግቢ ውስጥ ሊቆይ አይችልም፡፡ የሚመርጠው ሙያ የሚወደውና የሚችለው ቢሆንለት ይሻል፡፡ በሀሳቡ የተለያዩ አማራጮችን ማንሳትና መጣል ከጀመረ ቆይቷል፡፡ የ“ሂሳብ” ትምህርት እንደማይሆነው ስለሚያውቅ ቁጥር ይበዛባቸዋል የተባሉ
የትምህርት አይነቶችን አስቀድሞ ከምርጫ ውጪ አድርጓቸዋል፡፡ በዚህም መሰረት፣ ኢኮኖሚክስ፣ አካውንቲንግና ማኔጅመንትን አያስባቸውም፡፡ ከሚወዳቸውና ቢማር ጥሩ ውጤት ሊያመጣ ከሚችልባቸው ከቀሪዎቹ የትምህርት አይነቶች
“ፍልስፍናን”ም ቀንሷል፡፡ ይህን ያደረገው ደግሞ በዚያን ጊዜ የፍልስፍና ዲፓርትመንት ሀያ ተማሪ ወስዶ አንድ ተማሪ ነው የሚያስመርቀው
እየተባለ ይነገር ስለነበረ ነው፡፡ ሳይኮሎጂን ሲያንጓልል ቆይቶ እሱም ሂሳብ አለበት መባልን ስለሰማ ላያነሳው ጥሎታል፡፡ የቴያትር ጥበባት (theatre arts) ተማሪ ለመሆን የቆየ ፍላጎቱንም
አጥቷል፡፡ የዚህ ምክንያት ደግሞ ልክ እንደ የፖለቲካ ምርጫ ቅስቀሳ፤ የልደት አዳራሽ ውስጥ ተሰይመው፤ ተማሪዎችን ወደየሙያቸው ሊስቡ ተጋብዘው መጥተው የነበሩት አንጋፋ “አርቲስቶች”
- እነ ደበበ እሸቱ፣ ወጋየሁ ንጋቱ፣ ጌታቸው ደባልቄ - ተማሪውን “ወደኛ ኑ” ብለው በማማለል ፈንታ ኪነጥበብን አስመልክቶ የገለጡት
አስፈሪ እውነታ ስለገፋው ነበር፡፡ እነዚህ ባለሙያዎች በቅስቀሳቸው ቀን “የድራማ ደራሲያን ሀሳባቸውን በነጻነት ለመግለጽ እንደማይችሉ፣
ሳንሱር የሚባል መቀስ ጥሩ ጥሩ ሀሳቦች ቆርጦ እንደሚያስቀርባቸው … “ መናገራቸው (እና፤ ይባስ - ዶ.ር ፈቃደ አዘዘ 'ፍቅርን በሱ አየሁት' በሚል ርዕስ የተፃፈ/የፃፉትንና
ፊታቸውን ቅጥነቱ ራሱ ተጨማሪ ስንኝ ሀኖ ወደሚነበበው ወደ ወጋየሁ ንጋቱ አዙረው ያነበቡት ግጥም እነ ደበበ የተናገሩትን ስላጠናከረለት
ነው)፡፡ የ12ኛ ክፍል ትምህርቱን ሲያጠናቅቅ በድራማ “የት ይደርሳል?” የተባለው ተስፋዬ ደራሲ የመሆን ህልሙ እንደጉም በንኖበት
ግቢ ውስጥ ክልትው ክልትው እያለ ጭንቅላቱን ለማሳረፍ ወደ መኝታ ቤቱ በሚሄድበት ሰዓት ነው ከዘመቻ ጓዱ ከተስፍሽ ጋር የተገናኙት፡፡
ልጁ፤ ተስፋዬን ሲያይ አላመነታም፤ “ምን እንደመረጥሽ ገና ከማዶ ሳይሽ ነው ያወኩት” ይለዋል፡፡
ተስፋዬ፤ በጉጉት “ምን?”
ብሎ ይጠይቀዋል፡፡ በዚያን ዘመን የሀረር ልጆች ወንዱን አንቺ እያሉ ነበርና የሚጠሩት - “ሰው-ሰው-ሎጂ ነዋ! ሰው-ሰው- ሎጂ! ስለሰው ታጠኛለሽ፤ ስለሰው ትጽፊያለሽ!”
ይለዋል፡፡ ተስፍሽ ይህን ለማለት የቻለው፣ ተስፋዬ ድረሴ እድገት በህብረት ዘመቻ ላይ ለጽሁፍና ለንባብ እንዲሁም ለቀልድና ለሙዚቃ
የነበረውን ዝንባሌ (ተሰጥዖ) ያውቅ ስለነበረ ነው፡፡ ተስፍሽ ይህን ተናግሮ አላበቃም፡፡ እሱ ራሱ የሶሾዮሎጂ ተማሪ መሆኑንና ሙያውን
በፍቅር እንደሚወደው ጭምር ቀለል አድርጎ ያወራለታል፡፡
ተስፋዬ፣ መካሪውን አመስግኖ
የምርጫ ወረቀት ወደሚሰጥበት ክፍል (ሪጂስትራር) ይገሰግሳል፡፡ የሚሞላውን ቅጽ ይቀበላል፡፡ ቅጹ የተዘጋጀው ተማሪው ካሉት አስራ
ምናምን አማራጮች አንደኛ ምርጫው ላይ 1 ቁጥርን፣ ሁለተኛ ምርጫው ላይ 2 ቁጥርን እየፃፈ የመጨረሻው ምርጫው ላይ የመጨረሻውን
ቁጥር እንዲጽፍ ታስቦ ነው፡፡ እሱ ግን መወዛገብ አልፈለገም፡፡ “አፕላይድ ሶሽዮሎጂ” ከሚለው ጽሁፍ ፊትለፊት ያለው ሳጥን ውስጥ
የራይት ምልክት አድርጎ፤ ሌሎቹን ሳጥኖች ባዶ ትቶ፤ ወደ መኝታ ክፍሉ ይመለሳል፡፡ በዚያን ጊዜ ጥርቅም ውጤቱ GPA 3.00 ነጥብ
እና ከዚያ በላይ የነበረው ተማሪ ከሞላ ጎደል ምርጫው ይጠበቅለት ስለነበረም ይሆናል፤ አንድ ብቻ መርጦ ያቆመው፡፡
በዚያው ሰሞን ት/ቤቱ
ይዘጋ ነበርና ተስፋዬ ወደ አገር ቤት፤ ክብረመንግሥት፤ ይጓዛል፡፡ በመሃከል፤ ዩኒቨርሲቲው የተማሪዎችን የዲፓርትመንት ድልድል ጨርሶ
ነበርና፤ አንድ አዲስ አበባ የሚኖር፤ ታደለ አብተው የሚባል፤ የጓደኛው ወንድም፤ የማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ የተለጠፈውን የዲፓርትመንት
ምደባ ተመልክቶ ሶሾሎጂ ዲፓርትመንት መመደቡን በስልክ ያበስረዋል፤ ይደሰታል፡፡ ተስፍሽ እንዳለው፣ ስለሰው ሊያጠና፣ ስለሰው እየፃፈ
ሊኖር ነውና ግቢ ውስጥ በሀሴት ይቦርቃል፡፡
ተስፋዬ ድረሴ በሶስተኛው
ተርም ላይ የሶሾሎጂ ተማሪ ሆኖ ከመማሪያ አዳራሽ ውስጥ ተገኘ፡፡ የትምህርት ዝርዝሩን Course Outline ሲያይም ወደደው፡፡
ጥሩ ተማሪ ሆኖ ጀመረ፡፡ ግጥም መጫጫሩን፣ ክራር መከርከሩን፣ ኬኔዲ መጽሀፍት ቤት እየተመላለሰ ልብወለዶችንና የፍልስፍና መጽሀፍትን፣
መጽሔቶችን ማገላበጡንም ተያያዘው፡፡ ምንም እንኳን ቀደም መስሎት እንደነበረው ሶሽዮሎጂ ሂሳብ አልባ ትምሀርት ሳይሆን፣ እንደ አካውንቲንግና
ዲሞግራፊ ያሉ የለየላቸው ሂሳብ ነክ ኮርሶችን ይዞ የጠበቀው ቢሆንም
በቆይታው በጥሩ ሁኔታ ተምሮና በጥሩ ውጤት አጠናቅቆ ሶሽዮሎጂስት ሆኖ ተመረቀ፡፡ በኑሮውም“ሰው-ሰው-ሎጂስትነቱን” ቀጠለበት፡፡
ተስፋዬ፤ ቤንጃሚን ፍራንክሊን ባለው መልክ አንዱን የሙያ ዘርፍ ነጥሎ ማውጣት ሳያስፈልገው እርስበርሳቸው ተመጋጋቢ የሆኑ ሶስት
አራት፣ አንዳንዴም አምስት የሙያ ኳሶችን በአንዴ/ተራበተራ እየወረወረና እየቀለበ (juggle እያደረገ) እስከ 63 ዓመት እድሜው
ድረስ ዘልቋል፡፡ በኑሮው ስኬታማ ነው፡፡ አሁን የተቀመጠበት ወንበር
ላይ ቁጭ ብሎ በመጻፍ ላይ የሚገኘው አንድ ሰው በአንደበቱ ባወጣቸው ቃላት መሆኑን ያውቃል፡፡
በመሆኑም ለቃላት፣ ለሀረጎች እና ለአረፍተነገሮች ትልቅ አክብሮት አለው፡፡
ከአንደበቱም ሆነ ከብዕሩ የሚወጡ ቃላት ሌሎች ሰዎች ላይ አዎንታዊ ወይም አሉታዊ ውጤት ሊያመጡ እንደሚችሉ ያውቃልና ይጠነቀቃል፡፡
ንግግሩ ኃይለቃልን፣ ጽሁፎቹ ስድብና ዘለፋን፣ ቀልዶቹ ብሽሽቅን አይጨምሩም - ጨርሶ! ፌስቡክ ላይ ሳይቀር ጓደኞቹ ስድብና ዘርጣጭ
ቃላትን እንዲያስቀሩ ይመክራል!
ተስፋዬ ተወልዶ ያደገበት፣
ስብዕናው የተቀረፀበት ልዩ ማህበረሰብ
ተስፋዬ ተወልዶ ያደገበት
አካባቢ “ስደተኛ ሠፈር” ይባላል፡፡ አካባቢው ስያሜውን ያገኘው በኢትዮ-ጣሊያን ጦርነት ወቅት (1928 — 1933)፤ አባቴን ጨምሮ፤
ኬንያ ውስጥ በስደተኛነት ይኖሩ የነበሩ ሰዎች፤ ከነፃነት በኋላ (1933/34)፤ ቦታ ተፈልጎላቸውና ከስደት ተመልሰው መጥተው፤
የሰፈሩበት በመሆኑ ነው፡፡ ሌላው ተመሳሳይ ስም ያለው ኬንያ የነበሩ የስደት ተመላሾች ሠፈር የሚገኘው ይርጋዓለም ከተማ ውስጥ ነው
- “ሥደተኛ ሰፈር፡፡” ከስደት ተመላሾቹ ሁለት ቦታ የተከፈሉት ምርጫ ቀርቦላቸው ነው፤ ከፊሉ ክብረመንግሥትን መርጠው ቀሩ፣ ከፊሉ
ወደ ይርጋዓለም ተሻገሩ፡፡
በቁጥር ከ50 በታች
የነበሩት፣ “ማንነታቸው”በሠፋሪነት የተገለጸ ሰዎች እንግዳ በነበሩበት
ሥፍራ ኑሮን የጀመሩት ከሞላ ጎደል እንደ አንድ ቤተሰብ ሆነው ነው፡፡ የእርስበርስ ሰላምታቸው ሞቃት ነው፡፡ በየመንገዱ ተቃቅፎ
መሳሳምና ረዥም ሰላምታ መለዋወጥ የአሁን አሁን ትዕይንት ነው፡፡ ሠፈርተኞቹ ለአካባቢው ባይተዋር እንደመሆናቸው በአካልም ሆነ በስሜት
መቀራረብ የውዴታ ግዴታቸው ነበር፡፡ የዕለት ተዕለት ኑሯቸውን ለማሸነፍ፣
ያለፉበትን የጦርነትና የስደት ሰቆቃ ለመርሳት፣ እዲሁም የየዘመዶቻቸውን ናፍቆት ለመቋቋም ቶሎ ቶሎ እየተገናኙ መጨዋወት፣ አብሮ
መሳቅ፣ መቀላለድና በመግብና መጠጥ ዘና ማለት ነበረባቸው፡፡ የመቀራረቢያ ምክንያቶቻቸውና ብዙ ናቸው፡፡ ከኢኮኖሚ አንጻር በደቦና
በወንፈል አብረው ያርሳሉ፣ ይወቃሉ፣ አጥር ያጥራሉ፣ በረት ወይም ጎተራ ይሰራሉ፡፡ የተወሰኑ ጎረቤቶቹ በስራ እንዲያግዙት “ደቦ”
የጠራ ሰው ቤት ቀን ምሳ ይዘጋጃል፡፡ ምሽት ላይ ደግሞ ራት ከመጠጥ ጋር ይቀርባል፡፡ ሳቅ ጨዋታ ይደራል፡፡ እቁብ አብረው ይጠጣሉ፡፡
እቁብ የወጣለት ይጋዛል፡፡ በሬውን የሸጠ “የፍንጥር” ያጠጣል፡፡ የማዕረግ እድገት ያገኘ “የደስደስ!” ይጋብዛል፡፡
ሰፈርተኞችም “ደስታህ
ደስታችን ነው” ብለው መጠጥ ይዘው በመምጣት ምሽቱ በጭፈራ ይገባደዳል፡፡ ሀይማኖታዊ ምክንያቶችም ብዙ ናቸው፡፡ የገብርዔል፣ የሚካኤል፣
ወዘተ ማህበር (ጽዋ) አብሮ (በዙር) ይጠጣል፡፡ ምጥ የያዛትን ሴት ማጀብ አለ፡፡ እናቲት በሰላም እንድትገላገል ተሰባስቦ ፈጣሪን፣
ከራማን መለማመን አለ፡፡ ህፃን ሲወለድ ደስታን በእልልታ መግለጽ አለ፡፡ ቡና አብሮ መጠጣት፣ ለአራስ የተዘጋጀን እህል ተልባም
ሆነ ገንፎ ቀምሶ መመረቅ አለ፡፡ በተከታይ ቀናት ደግሞ የወልደችን ሴት መጠየቅ፤ “እንኳን ማሪያም ማረችሽ” በማለት ደስታን መግለጽ
አለ፡፡ ተጠራርቶ ገንፎ መብላት አለ፡፡ ህፃን ልጅ ሲገረዝም ዝግጅት
ይኖራል፡፡ ያኔም ይበላል፣ ይጠጣል፡፡ የታመመን ሰው አጅቦ ሀኪም
ቤት፣ ጠንቋይ ቤት፣ መድሃኒት አዋቂ ቤት መሄድ አለ፡፡
ህፃኑ ተስፋዬ ድረሴ
ስብዕናው የተቀረጸው “… በእኒህ የጋራ ታሪክ ባላቸው፣ በሚዋደዱና በብዙ ማህበራዊና ኤኮኖሚያዊ መስተጋብሮች የተነሳ እርስበርሳቸው
በተጋመዱ ማህበረሰቦች እቅፍ ውስጥ …” ነው፡፡ ሥደተኛ ሰፈር ውስጥ ህፃናት የሚያድጉት በሰፈርተኛው ሁሉ በፍቅር ተስመው፣ በፍቅር
ታቅፈው፣ “ጎሽ” ተብለው፣ ተመርቀው፣ ተደንቀው፤ እንዲሁም በፍቅር ተገስፀው ነው፡፡ በእያንዳንዱ ልጅ ህይወትና ስኬት ውስጥ የሰፈርተኛው
እጅ አለበት፡፡ እያንዳንዱ አባወራ ከራሱ አልፎ የጎረቤቱን ልጆች መከባከብ፣ ባህሪያችንም መከታተል ግዴታውም ነበር፡፡ ይህ ግዴታ
እንዲፀና ያስቻለው ደግሞ የተለያዩ ማህበራዊና ኃይማኖታዊ መስተሳስሮችና ስርዓቶች መኖር ነው፡፡ ለምሳሌ፣ አንድ ህጻን ክርስትና
ሲነሳ/ስትነሳ (ወንድ በ40 ቀን፣ ሴት በ80 ቀን) “የክርስትና አባት” ወይም “የክርስትና እናት” ይኖረዋል/ይኖታል፡፡ በተመሳሳይ
ሁኔታ፣ በግርዛት ጊዜ፤ የተገራዡ/ዧን ህፃን አይን ያዢው/ዋ “የአይን አባት/እናት” ይሆናሉ፡፡ በቤተሰቦች መካከል የበለጠ መቀራረብ
ሲያስፈልግ ደግሞ ለየት ያለ ሥርዓት ይዘጋጅና፤ “የጡት አባት” መሆን የፈለገ ሰው አውራ ጣቱ ላይ ወለላ ማር ቀብቶ “የጡት ልጅ”
እንዲሆን የመረጠውን ህፃን (ጣቱን) ያስጠባል፡፡ ከዚያ ስርዓት በኋላ ህፃኑ የአጥቢው የአደራ ልጅ የሆነ ያህል ተጨማሪ ፍቅርና
ክብካቤ እያገኘ ያድጋል (ታገኛለች)፡፡ የደም ትስስር ያላቸውም ሆነ
ሌሎች ህጻናት የሚያድጉት የሠፈርተኛው “ልጅ” እንደሆኑ እያሰቡ ነው፡፡ “ወንድማማችነት” እና እህትማማችነት” በተፈጥሮም በባህልም
የሚለመልምበት መንደር ነበር - ሥደተኛ ሰፈር፡፡ “ያደኩት የወላጆቼንም ሆነ የሰፈሬን ሰዎች ፍቅር ጠግቤ ነው፡፡ ለዚህ ይመስለኛል፤
ሰዎችን በቀላሉ አምናለሁ፡፡ እገሌ የማን ልጅ ነው? ሳልል፤ ዝርዝር ውስጥ ሳልገባ፤ ማንንም በእኩል አይን ለማየት እችላለሁ፡፡
የሌሎች ሰዎች ስኬት የኔ ስኬት የሆነ ያህል ያስደስተኛል፡፡ ስስቅ ከአንጀቴ ነው፡፡ ለቅሶዬም መራር ነው፡፡ ለባዳም ለዘመድም እኩል
ነው የማለቅሰው” ይላል ተስፋዬ ድረሴ - አሁን ስላለው ስብዕና ሲናገር፡፡”
ተስፋዬ ድረሴ በመገናኛ
ብዙሃን
ተስፋዬ ድረሴ ቀልደኛና
ትልልቅ ሀሳቦችን ቀለል አድሮ የማቅረብ ክህሎት ያለው ሰው በመሆኑ ለቴሌቪዥንም ለሬዲዮም (በቅርቡም ለዩቲዩብ) የሚመች እንግዳ
ነው፡፡ አንድም በሶሾሎጂስትነቱ አንድም በኪነጥበብ ሰውነቱ ሚዲያ ላይ ቀርቦ እውቀትና የህይወት ተሞክሮውን በማጋራት በርካታ እድሎችን
አግኝቷል፡፡ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የ ”ቤተሰብ” ፕሮግራም ላይ - ሙሉ
ቤተሰቡ ከአንዴም ሁለት ጊዜ ቀርቧል፡፡ በኤፍ ኤም
97.1 “ዝክረ-ፍቅር፣” ለ6 ሳምንታት የዘለቀ የቤተሰብ ተሞክሮ (የአመቱ ምርጥ)፣ በኤም ኤም 98.1 (ፋና) አርዓያ ቤተሰብ/ትዳር
መላውን ቤተሰብ ያካተተ - በተናጥል፤ የማለዳ ወግ ላይ በ102.1
የአባትነት ተሞክሮ፤ በ96.3 የገጣሚነት ተሞክሮ ለሶስት ሳምንትት የዘለቀ ቃለ-ምልልስ፣ በ97.1 ሁለት ጊዜ “እንደ ገጣሚ በመኪና
አደጋ ዙሪያ …” በ97.1 ላይ “ያልተዘመረላቸው”(በገጣሚ አበባው
መላኩ አቅራቢነት)፣ በጀርመን ድምጽ ሬዲዮ በግጥም መጽሀፍትና በህፃናት
መዝሙሮች ዙሪያ … ሀዋሳ ከተማ፣ ባህር ዳር ከተማ ኤፍ ኤም ሬዲዮዎች
… 107.8 የልጆቻችን ኢትዮጵያ፣ በቅርቡ በEBS ቴሌቪዥን
ላይ የእናቶች ቀንን አስመልክቶ “እናት መቼ ትሙት?” ግጥም አቅርቧል (ቪዲዮው የተነሳው በመኖሪያ ቤቱ ነው)፡፡ በ102.1 የጥበብ
መንገድ ላይ - በተስፋዬ ማሞ አንባቢነት “ሰማንያ እግሯ አገሬ” - ረዥም ግጥም ተነቦለታል (የተነበቡ መጣጥፎች ከላይ ተገልጸዋል)፡፡
የልጅነት/ወጣትነት
ሥራ ልምድ - ከብቶችን ማገድ፣ ከብቶችን ማከም፣ ከአልጌ ቃጫ ማውጣት፣ ወተት መናጥ፣ ቆቅ ማጥመድ፣ ማረስ፣ መነገድ (ዶሮ፣ ፍየል)፣
ሰሌን/ኬሻ ስራ፣ ከሰል ማክሰል፣ ጎጆ/ጎተራ መስራት፣ ጠምዶ ማረስ፣ በበሬ ከወንዝ ውሃ በበርሜል እያንከባለሉ ማምጣት፣ አውድማ
መለቅለቅ፣ መውቃት፣ አጥር ማጠር፣ ታናናሾችን መንከባከብ፣ ወላጆችን መንከባከብ፣ ወዘተ - ይህ ሁሉ፣ የስራ መፈለጊያ ወረቀት
CV – Curriculum Vitate ላይ “በሥራ ልምድነት አይይሰፍርም!” ዘመናዊ ትምህርት እንዲያ ነው፡፡ “ይሁንና - በጽሁፍም፣
በተረትም፣ በዘፈንም - ብቻ በምንም፣ በምንም ብለን እውቀታችንን እንጠቀምበታለን!” ይላል
ተስፋዬ ድረሴ፡፡
መዝጊያ፤ ይህ የመዝጊያ
ጽሁፍ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ወይም የዊኪፒዲያ መስራቾች አቋምን የሚገልጽ ስለሆነ ያመንበትን ሀሳብ ለአዲሱ ትውልድ እናሰፍራለን፡፡ተስፋዬ
ድረሴ ጻድቅ በእኛ አቋም ለዛ ባለው አቀራረብ ኪነ-ጥበብን እያኖረ እና እየከሸነ የሚያቀርብ ታላቅ ሰው ነው፡፡ ግን ምን ያህሎቻችን
እናውቀዋለን? ብናውቀው ጥሩ ነው፡፡ ጥልቀት ያላቸው አሳቢዎች ከፊት ወንበር ላይ እንዲቀመጡ እንሻለን፡፡ ለተስፋዬም ይህን የክብር
የፊት ወንበር ሰጥተነዋል፡፡ ኢትዮጵያ አንደኛ የወጡ ልጆቿን ረስታ መጨረሻ የወጣውን ተሰሚነት ያለውን ደካማ ልጆቿን እየሸለመች
የምትኖረው እስከመቼ ነው? እንደ ተስፋዬ ድረሴ ያሉ አንደኛ የሆኑ ሰዎች ለምንድነው በየቀኑ ሚድያው ላይ የማናያቸው? ታሪካቸው
በየጊዜው እንዲዘከር እንሻለን፡፡ እንደተስፋዬ ድረሴ ጻድቅ አይነት በተለይ ማህበረሰባዊ ንቃተ-ህሊና ያላቸው ሰዎች መታወቅ አለባቸው፡፡
አንዱ ማሳወቂያ መድረክ ደግሞ ይህ የዊኪፒዲያ ገጽ ነው፡፡ በእኛ እምነት ተስፋዬ ድረሴ ታሪኩ በዚህ መልኩ እንዲሰራ ስንሻ አንዳች
ቁምነገር እንደሚገኝበት እርግጠኞች ነበርን፡፡ እንዳነበቡትም ግለ-ታሪኩ ከግጥም ጋር ተዋዝቶ ሲቀርብ ደስ ያሰኛል፡፡ የእኛ አላማ
የሰው ታሪክ መሰነድ ነው፡፡ የእኛ ግብ ያልተጻፈላቸውን እና ያልጻፉትን ግለ-ታሪክ እንዲጽፉ አድርጎ የሀገርን ታሪክ በዚያ መልኩ
ማሳየት ነው፡፡ እናም እንዲህ ሲሆን ደስ ይለናል፡፡ / ይህ ጽሁፍ የተስፋዬ ድረሴ ጻድቅ ን ግለ-ታሪክ መሰረት አድርጎ የተጻፈ
ሲሆን የአርትኦትና እንዲሁም ባለታሪኩን የመምረጥ እንዲሁም ታሪኩን እንዲልክ የመገፋፋቱን ስራ ያከናወነው ጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ ነው፡፡
ይህ ጽሁፍ በ 8441 ቃላት የተሰናዳ ሲሆን በዊኪፒዲያ ላይ የተጫነውም እሁድ ነሀሴ 23 2013 ነው፡፡
በፌስ ቡክ የማውቀው እጅግ የማከብረው ሰው ነው ግለ ታሪኩን ተመስጬ አንብቤዋለሁ።
ምላሽ ይስጡሰርዝየተስፋዬ ድረሴን ግለታሪክ በዚህ መልኩ አደራጅተው ላቀረቡት አካላት ምስጋናዬ ከፍ ያለ ነው፡፡ ተስፉ ዛሬ ተዋውቀሄው የዘመናት ጓደኛ ያክል አቅርቦ ያማክርሃል ይመክርሃል ያጫውትሃል፡፡ በሚገርም ሁኔታ አብረን አንድ መ/ቤት ማለትም Save the children በምንሰራበት ወቅት እንኳን በዚህ ልክ ከልጅነቱ ጀምሮ በኪነጥበብ የተቃኙ ማህበራዊ አገልግሎቶች ላይ ከፍተኛ ተሰትፎ እያደረገ እንደሆነ አላውቅም ነበር፡፡ ተስፉ በርታልን ፡፡ አሁንም እያደረክ ያለሄው ማህበራዊ አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም ቀጥልበት፡፡ ከዚህ በተጨማሪ *ራሴን ፍለጋ* ብለህ በከተብካት ግጥም መሰረት ራሳቸውን ካንገታቸው ላይ እንኳን ያላገኙ ሰዎች የአገር አስተዳደር ቦታውን ተቆጣጥረው አገሪቱንም እንደነሱ ራስ አልባ እያደረጉ ስለሆነ ፍላጎትዎ ቢሆንና በዚህኛውም ዘርፍ ቢሳተፉ የሚል የግል አስተያየቴ ነው፡፡
ምላሽ ይስጡሰርዝ