ስመኝ ቴሶ
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያ ዘርፍ የተሻለ አሻራ ያኖሩ ባለሙያዎችን በተወዳጅ ዲጂታል ሚድያዎች በመጽሀፍ እና በልዩ ልዩ መገናኛ ዘዴዎች እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይህ ግለሰብን እውቅና ከመስጠት ባለፈ ሀገር ያለፈችበት እና እያለፈችበት ያለው ታሪክ ስለሆነ ባለ ታሪክ የሆኑ እና በእኛ ቦርድ ታሪካችሁን ትሰጡ ዘንድ የተጠየቃችሁ ትብብር ታሳዩ ዘንድ እንጠይቃለን፡፡ ዛሬ የሚጻፈው ታሪክ ነገ ለሚጀመረው ስራ መነሻ ይሆናልና እባካዎ ታሪክዎ አንድ ዋጋ አለውና ይተባበሩን፡፡ አሁን በዚህ ጽሁፍ የህይወት እና የስራ ታሪኳን የምታሳየን የሚድያ ሰው በአፋን ኦሮሞ የሚድያ ስራ ላይ ላለፉት 31 አመታት ተግታ የሰራች ነች፡፡ በተለይ በኢቢሲ ለ13 አመታት ‹‹ዳንጋ በተሰኘው የመዝናኛ መሰናዶ የራሷን ትልቅ አሻራ አኑራለች፡፡ ይህች ድንቅ ለኢትዮጵያ ፍቅር ያላት የሚድያ ሰው ስመኝ ቴሶ ትባላለች፡፡ እዝራ እጅጉ እና ቦጋለ ተስፋዬ ታሪኳን እንደሚከተለው አጠናክረውታል፡፡
ልጅነት
ውልደቷ ሚያዝያ 27 1959አ.ም በያኔው በወለጋ ክፍለ ሀገር በቤጊ ከተማ ነበር።ከሁለት የቤተሰቦቿ ሴት ልጆች መካከል የመጀመርያዋ ልጅ ህፃኗ ስመኝ ቴሶ፤ አባቷ አቶ ቴሶ_ዲሳሳ____ ቤጊ ከተማ የሚገኘውን ትምህርት ቤት ከመመስረታቸው ባሻገር፤በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ በጎበዝ መምህርነታቸው የታወቁ እንደ ነበር ይወሳላቸዋል። ስመኝ፣ በልጅነት ከአሁኗ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክብርት ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ ጋር አብሮ አደግ እና የልጅነት ወዳጆች እንደነበሩም ታሪኳ ያስረዳል።
ልጅነትና ሙዚቃ
በልጅነቷ ለሙዚቃ የጠለቀ ፍቅር የነበራት ስመኝ ከትምህርቷ ጎን ለጎን ሙዚቃንም ከማንጎራጎር አልፋ ያለችበትንም ክፍለ ሀገር ወክላ አዲስ አበባ እስከ መምጣት አድርሷታል።ቤት ውስጥ የነበሩት የአባቷ የሸክላ ካሴቶች በሙዚቃ ፍቅር ለመውደቋ ዋነኛ ምክንያቶችም ነበሩ።ሱቅ ስትላክ ፤ዘይት ስትገዛ የክቡር ዶ/ር አሊ ቢራን፤የአስቴር አወቀ፤የሙሉቀን መለሰ፤ቴዎድሮስ ታደሰና የመሀሙድ አህመድን ሙዚቃዎች አዘውትራ ትሰማቸው እንደ ነበር የህይወት ታሪኳ ያስረዳል፤በተለይ የአሊቢራ “አዋሽ ነማ ሾክሳ”፤”ሲንበርባዳ ኦጉ”፤የማህሙድ “የዘገየሽበት” ትዝታዎቿ ነበሩ።
ጉዞ ወደ ኪነት ቡድን
ቀስ በቀስ በእንጉርጉሮ የተጀመረው ሙዚቃ በሂደት አድማሱን እያሰፋ፤ከራስ አልፎ ጓደኞች፤ከጓደኞችም አልፎ በሰፈሩ ሰዎች ዘንድ ጭምር ተወዳጅ እየሆነ መጣ፤በቀበሌ ቡድን ውስጥ የአሊቢራን ዘፈኖች ስትዘፍን ተቀባይነትን ከማግኘት አልፋ በተለያዩ መድረኮች ዝግጅት ስታቀርብ በከተማው ባለሀብቶች ገንዘብና የተለያዩ ሽልማቶች በመድረክ ላይና በመድረክ ውጪ መሸለምን አሃዱ ብላ ጀመረች።
ጉዳዩ ያላማረው መምህሯ አባቷ ነገሩ አልጥም አለው፤ የሰፈር ጓደኞቹ ጭምር “ልጅህ ጎበዝ አዝማሪ ሆነችልህ አሉ” በማለት ያባሽቁት ጀመሩ፤አባት ልጅን “ይህ ሙዚቃ ይቅርብሽ አርፈሽ ፊደል ቁጠሪ “ቢላትም አሻፈረኝ አለች።ልጄ አይን ውስጥ ገባችብኝ ያለው አባት ወደ አዲስ አበባ ልኮ ትምህርቷን እንድትቀጥል ጥረት ቢያደርግም፤ጉለሌ መድሀኒያለም ት/ቤት ገብታ ጥቂት ብትሞክርም ከተማ አዲስ ቢሆንባት፤የሙዚቃ ፍቅሩ አልወጣልሽ ቢላት፤ቤተሰብና የወለጋ አየር ቢናፍቃት ትምህርቷን አቋርጣ ወደ ነቀምት ለመመለስ ተገደደች፡፡
ዳግም የወለጋ ዞን አስተዳደር የኪነት ቡድን ስር ታቅፋ ቋሚ ስራዋን ጀመረች ። በሙዚቃው ከወቅቱ ዝነኞች ከነ ሰለሞን ደነቀና ከነ ዳንኤል ታደሰ ጋር በመሆን በተወዛዋዥነት ዞኗን ወክላ ለሀገር አቀፍ የኪነት በድኖች ውድድር ወደ አዲስ አበባ የመጣችው ህፃኗ ስመኝ፤በወቅቱ ከመላው ኢትዮጵያ ለውድድር የመጡትን የኪነት ቡድኖች ስታስታውስ፤እነ ግሸን አባይና ላሊበላ የልጅነት ትዝታዎቿ እንደነበሩ ታስታውሳለች። ከትርኢቱ መልስ ወደ ወለጋ ስትመለስ እሳት ለብሶ እሳት ጎርሶ የጠበቃት አባቷ ለገብርኤል ስለት ተሳለ፡፡ “ቅዱስ ገብርኤል ሆይ ልጄን ዘፈን ካስቆምክልኝ በየአመቱ ዘክርሃለው” ብሎ እንዳለውም ያቺ በእነ አሊቢራና በእነ አስቴር አወቀ ሙዚቃ ቀልቧን የተሰረቀችው ስመኝ ሙዚቃን እስከወዲያኛው እርግፍ አድርጋ በመተዋ፤የአባቷ ስለት ሰምሮ እስከዛሬም ድረስ በየአመቱ ቤታችን ድግስ ሆኖ ቀርቷል ትላለች፡፡
የሬዲዮ ፍቅር (የማይታየው ምናባዊው ሳሙኤል ዳባ)
ከሙዚቃው በዘለለ ከፍተኛ የሬዲዮ ፍቅር የነበራት ስመኝ ፤ሬዲዮዋን ይዛ ሙዚቃዋን ከመኮምኮም ዉጪ በወቅቱ አንድ ለእናቱ በነበረው ብሄራዊ ሬዲዮ የሚተላለፉ ተከታታይ ድራማዎች ቀልቧን ይስቡት ነበር፡፡ በተለይ በኦሮምኛ ክፍለ ጊዜ ይተላለፍ የነበረውና ሁለገቡ ከያኒ ሳሙኤላ ዳባና ሰሚራ አወል የሚተውኑበት “ቴዲ ኮ” የተሰኘው ተከታታይ የሬዲዮ ድራማ ስመኝ አሁን ለደረሰችበት የሙያ ጣሪያ መድረስ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳደረገላት ከሀገሬ ቲቪ የጠያቂው ሲጠየቅ ፕሮግራም ላይ በደረገችው ቆይታ አስታውሳለች፡፡በወቅቱም የቴዲን ገፀ ባህሪ ተላብሶ ይጫወት የነበረውን ሳሙኤል ዳባን በድምፁ ተማርካ ታደንቀውና እንደሱ መሆንን ትሻና የልጅነት ህልሟም እንደ ነበር ገልፃ ኋላም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አብራ በስራ ባልደረባነት ዳንጋን ምርጥ ካደረጉ ጋዜጠኞች መካካል እንዷ ለመሆን በቅታለች ።
ትዳር በልጅነት
ከጥበቡ ፍቅር እንድትላቀቅ ብዙ ጥረት ቢደረግም፤ወደ አዲስ አበባ ቢሰዷትም ከጥበብ አልላቀቅም ያለችውን ስመኝ በሌላ አንድ ዘዴ ከጥበብ ሊለዩዋት ፈለጉ፤እሱም ትዳር፤ ገና በ 17 አመቷ መሆኑ ነው፡፡
ምርጫ ያልነበራት ስመኝ ከልጅነት አብሮ አደጓና ከውጭ መጣ የተባለውን ሰው ልታገባ ሆነና ወግ ወጉ ተደረገ፡፡ ጥበብን ፈታ ባሏን አግብታ ለኑሮ ጉዞ ወደ አርባ ምንጭ ሆነ፤ መጀመርያም ግዳጅ የሆነባት ስመኝ ብዙም ሳትቀጥል አንድ ልጅ አፍርታ ለሌላ አዲስ ህይወት ጉዞ ጀመረች፡፡
ከሸገር እስከ ድሬ፤ከድሬ እስከ ሸገር
ከትዳር በኋላ አዲስ ምእራፍ የጀመረችው ስመኝ ቴሶ ወደ ሸገር መጥታ ለገሀር አካባቢ በሚገኝ አንድ ካምፓኒ ወስጥ ጥቂት እንደ ሰራች ዳግም ወደ ድሬደዋ አቅንታ በንግዱ አለም ዘልቃለች፡፡ በዚህች ሀገር ሆና ነበር የኢቲቪን ማስታወቂያ የተመለከተችው፡፡ ወዲያው በነጋታው የአውሮፕላን ቲኬት ቆርጣ ለምዝገባ ወደ ሸገር ብትበርም ሸገር ደርሳ ማዘጋጃ ወደ ሚገኘው ኢቲቪ ብታቀናም ሰዓት አልፏል ተብላ በዘበኛ ትከለከላለች፤የልጅነት ህልሟን ልታገኝ ጫፍ ላይ ደርሳ የነበረችው ስመኝ አንዳች ውሃ የተከለሰባት መሰላት፤ይቅርታ ጠይቃ እሺ ካሉሽ ድረሺባቸው ተብላም እንደምንም 800ኛ ደረጃ ላይ ተመዝግባ ለፈተና ጉዞ ወደ ኢቲቪ ሆነ፡፡
የኢቲቪ ፈተናና ፈተናው
በ1984 ዓ/ም በመንግስታ ለውጥ ማግስት ከልጅነት ህልሟ ጋር ለመገናኘት ከ 800 ተፈታኞች ከ 6ቶቹ አንዷ ለመሆን የኢቲቪ በር ላይ የቆምችው ተስፈኛዋ ስመኝ ቴሶ ከወቅቱ ቆነጃጅት ጋር ተጋፍጣ ከ 800 ዎቹ ወደ 400፤ከ 400 ወደ 200፤ከ 200 ወደ 100 ከ 100 ወደ 80 ከ 80፤40፤20፤ እያለ መጨረሻ ከቀሩት 12 ተፈታኞች መካከል ስመኝ ቴሶ አንዷ ሆነች፡፡
በወቅቱ ከነበሩት የኢቲቪ ዳይሬክተሮች መካከል አንዱ አቶ ወርቁ ጋዲሳ ያኔ ከነበሩት ተወዳዳሪዎች መካካል ዘናጯና ዘመናይዋን ስመኝ ፕሮቶኮሉን ጠብቀው ከመጡት ውስጥ የሚደርስባት አልነበረም ይላል፤ለዚህም ማሳያው በወቅቱ የተነሳቻቸው ፎቶዎች ምስክሮች ናቸው።ምንም እንኳን ከመጨረሻዎቹ ውስጥ አንዷ ብትሆንም ገና ካልረገበው የወቅቱ ፖለቲካ አንፃር “ኦነግ ነች” የሚል ስም ተለጥፎባት አንቺ ጥቂት መቆየት አለብሽ የሚል የመጨረሻ መሰናክል መጣባት፤ባልዋለችውም ተወነጀለች፡፡
የትወና ህይወትና አማረ አረጋዊ
“አሪፍ ነበርሽ ግን ምን ያደርጋል ኦነግ ነሽ” የተባላችው ወጣቷ ስመኝ ቴሶ አሁንም ተስፋ አልቆረጠችም ፤ፈተናን ከልጅነቷ መጋፈጧ የጠቀማት ይመስላል፡፡ የባሰውኑ በእልህ ሰራች ለገሀር አከባቢ እየሰራች በመሀል ልጅ ሆና ትሰማው የነበረው ቴዲኮ ድራማ በቲቪ ሊቀርብ መሆኑን ሰማች፤እኔ ሙሉውን ዛሬም ድረስ አስታውሰዋለሁ፤ምክንያቱም በልጅነቴ እሰማው ነበረና የሚል አመክንዮ አቀረበች፤ እስቲ ትታይ ተባለች፤ስመኝ ስትታይ ማን ይቻላት፤ አሁንም ድረስ በቃሏ ቃለ-ተውኔቶቹን ከእነ ለዛቸው ታስታውሳቸዋለች፡፡
ድራማው ተቀርፆ አልቆ በኢቲቪ ሊተላለፍ ፕሪቪው ሲደረግ ያየው የወቅቱ የኢቲቪ አለቃ የአሁኑ የሪፖርተር ጋዜጣ ባለቤት ይህቺ ልጅ የትነው ያለችው? በማለት ይጠይቃል፡፡ በወቅቱ ፕሪቪው ላይ የነበሩት ሰዎችም እዚህ ተወዳድራ ነበር፡፡ በምን ምክንያት እንደወደቀች አናውቅም እንጂ ቢሉት አድራሻዋን ማፈላለግ ይጀምራል። በወቅቱ ጥሩ ስራ ላይ የነበረችው ተገፊዋ ስመኝ ትፈለጊያለሽ ብትባልም አሻፈረኝ አለች”አትፈለጊም ብላችሁኝ አልነበር ዛሬ ምን ተገኘ?” አለች። ቢሆንም የተፃፈላት ፍርቱናዋ ነበርና በወቅቱ ስራ አስኪያጅ በ አምባሳደር ደግፌ ቡላ ጉትጎታ ጥሪውን ተቀብላ ወደ ምትወደው ሙያ በ 1984 ዓ/ም ኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን ተቀላቀለች፡፡
ስልጠና በኢቲቪ ቤት
ኢቲቪ ማንም ከየትኛውም ሙያ ላይ ተነስቶ በህዝብ ላይ የሚለማመድበት ጣቢያ ያለመሆኑ ዛሬም ድረስ የምታመሰግነው ስመኝ ቴሶ፤ ወደ ኢቲቪ እንደ ገባች አየር ላይ ከመውጣቷ በፊት እንደ ሌሎች የወቅቱ ጋዜጠኞች ወደ ስልጠና ነበር ያቀናችው፡፡ አሁንም ድረስ በኢቲቪ ቤት የሚታወቁት አንጋፋ ዳሬክተሮች አለሙ ቶሎሳና ወርቁ ጋዲሳ ብዙ ነገር በወቅቱ አስተምረውናል ባይ ነች፡፡
አንድ ጋዜጠኛ ህዝብ ፊት ሲቀርብ ከስነ-ምግባሩ እስከ አለባበሱ ድረስ ከፀጉር ስታይሉ እስከ ጫማ አደራረጉ ድረስ ምን መምሰል እንዳለብን፤ህዝቡን እንዴት ማክበር እንደሚገባን ያስተማረን ቤት ኢቲቪ ነው ትላለች ምንም እንኳን አሁን ላይ ያለውን ብትቃወምም፡፡ በጆሮ ላይ የሚደረጉ ጌጣጌጦች እስከ ምን ድረስ ናቸው? የምንቀባቸው የገፅ ቅብስ? የእኛ ዳይሬክተሮቻችን ከኛ እኩል ይጨነቁልን ነበር፡፡በተለይ ሙያዊ ክህሎታችንን ለማሳደግ በፕሮግራም ማስተዋወቅ (ኮንቲኒቲ) ላይ ይዘን ስለምንጋባቸው መረጃዎቸ ትልቅ እውቀት እንዲኖረን፤ከምናወራው ርእሰ -ጉዳይ ጋር ስላለ ተያያዥነት፤ቁጥብና በተመረጡ ቃላት እንዴት የተሰጠንን ደቂቃ መጠቀም እንደምንችል የተሰጡን ስልጠናዎች ዛሬም ድረስ ላለንበት ደረጃ፤ ቀደምትና አንጋፋ የኢቲቪ ዳይሬክተሮችና ፕሮግራም አስተዋዋቂዎች (ሆስቶች) ድርሻው የጎላ ነው ባይ ነች፡፡
ዳንጋ (DHANGAA)
ኢቲቪ በፊሪላንስ የተቀጠረችው ስመኝ ፤አንድ አመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ቋሚ ሰራተኛ ሆና በ 285 ብር ስትቀጠር በወቅቱ የኦሮምኛ ክፍል በኢትዮጲያ ቴሌቪዥን ውስጥ ያልነበረ በመሆኑ ከነ ሳሙኤላ ዳባ፤ወርቁ ጋዲሳ ፤ኢሳያስ ሆርዶፋ፤አለሙ ቶሎሳ፤ደጀኔ ጉተማ ጋር በመሆን ከፈር ቀዳጅና ባለታሪክ ጋዜጠኞች ተርታ ታሪክ እንዲህ ሰንዷቸዋል፡፡
የአማርኛው መዝናኛ ፕሮግራም 120 በእነ ሰለሞን አስመላሽ ሲቋቋም፤ ዳንጋና ሰንበት ምሳና በመዝናኛው ዘርፍ ዛሬም ድረስ በአትዮጵያ ሚዲያ የመዝናኛው ኢንዱስትሪ ዘርፍ የማይረሳ አሻራቸውን ጥለው ዘወትር ይወሳሉ፤የፉክክር መንፈስ ያለበትና 120ን፤ቀደም ምሳናን፤ዳንጋን በተለያዩ ቋንቋዎች በቅዳሜና እሁዱ ፕሮግራም ይዞ ብቅ ያለው ኢቲቪ...ዘወትር ቅዳሜ ቀትር ላይ ይተላለፍ የነበረው የኦሮምኛው ዳንጋ በተደጋጋሚ በማሸነፍ ተሸላሚ እንደነበር በወቅቱ ኢቲቪ የነበሩት ጭምር ይናገሩታል፡፡ታዲያ የዚህ የቅዳሜ ዳንጋ መዝናኛ ፊታውራሪዋ ስመኝ ቴሶ መሆኗ ባለታሪክ ያደርጋታል። በተለይ በኮንቲኒቲ፤ወይም ሆስት (ፕሮግራም ማስተዋወቅ) ዘርፍ በስቱዲዮና ከስቱድዮ ውጪ ዘርፈ- ብዙ ስራዎችን ሰርታለች፡፡
የመስክ የበዓል ስራዎች
ኢቲቪ በ90 ዎቹ ከሚታዋቅባቸው ስራዎች ውስጥ አንዱ የበዓል ስራዎችን ቀደም ተብሎ ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በማቅናት፤ የቀጥታ ስርጭት አስመስሎ መቅረፅ ሲሆን በዚህ ረገድ የዳንጋ ቡድን ዛሬም ታሪክ የማይረሳው ዶክመንቴሽን በኢቲቭ አርካይቭ ውስጥ አስቅምጧል፡፡
ይህ አርካይቭ ሲወጣ ታዲያ በየትኛውም ታሪካዊ ካሴት መግቢያ ላይ ቀድማ ወደ ቴሌቪዥን መስኮት ብቅ የምትለዋ ደርባባዋ ስመኝ ቴሶ ነች ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ከሁለገቡ ከያኒ ሳሙኤል ዳባ ጋር በመሆን መድረኩን ሲጫወቱበት ተመልካቹን ያፈዙት ነበር፡፡በፀጉር ስታይሏና በአለባበሷ ዘመናይ የነበረችው ስመኝ፤ በቀላሉ የሰዎችን ትኩረት ለመሳብ ከመቻሏም በላይ፤የዳይሬክተሮቿን አስተያየት ዘወትር በመቀበል ራሷን እያሳደገች የመጣች ጋዜጠኛ እንደነበረች የወቅቱ ዳይሬክተር ወርቁ ጋዲሳ ይናገራል፡፡በተለይ በዞን ከተሞች በሚዘጋጁ የበአል ስራዎች ላይ ህዝቡን ለማነቃቃት የምትጠቀማቸው ቃላት መለያዎቿ ሲሆኑ ፤ራሷ ተነስታ ጨፍራ ታዳሚውን በማነቃቃት ረገድም መስላ ሳይሆን ሆና የምትጫወት ስለመሆኗ ሌላው ማሳያ ነው፡፡
የ3000 መድረኮች አጋፋሪ
በ13 አመት የኢቲቪ ቆይታዋ በርካታ የዞንና የክልል ከተሞችን በመጓዝ ፕሮግራም ስትመራ የነበረችው አንጋፋዋ ጋዜጠኛ በህይወት ዘመኗ የመራቻቸው መድረኮች ቁጥር ከ 3000 እንደሚልቁ ትናገራለች፡፡ ይህም ሲባል የበአልና የአዘቦት የመድረክ ስራዎችን በማካተት ጭምር ነው፡፡
አይረሴ እንግዶቼ
በርካታ እንግዶችን በየመድረኩ ቃለ-ምልልስ ያደረገችው ስመኝ ቴሶ፤በተለይ ከወቅቱ ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ፤ከወቅቱ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚዳንት ጁነይዲን ሳዶና ከአትሌት ደራርቱ ቱሉ ጋር ያደረገቻቸው ቃለ-ምልልሶች ዛሬም ድረስ በጋዜጠኝነት የህይወቷ መዝገብ የውስጥ ገፆች ላይ በደማቁ የወርቅ ቀለም የተፃፉ እንደሆኑ ዛሬም ድረስ ታወሳቸዋለች፡፡
የደራርቱ ካባ
ከላይ እንደተገለፀው ምንም እንኳን ደራርቱ የስመኝ የጋዜጠኝነት ህይወት አንዷ አይረሴ እንግዳ መሆኗን ብንገልፅም፤የደራርቱና የስመኝ ግንኙነት ከዚህም የዘለለ ነው፡፡ የመጀመሪያዋ የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያን ያጠለቀችውን ጥቁር ሴት፤ ከባርሴሎና ስትመለስ ከማንም ጋዜጠኛ ቀድማ ቃለ-መጠይቅ ያደረገቻት ስመኝ ቴሶ ስትሆን ዛሬም ድረስ ስለ ደራርቱና ስለዚያች ቀን ስታወራ እምባዋ ይቀድማታል፡፡
ደራርቱ በወቅቱ ቤተ-መንግስት ተሸልማ የነበረውን ካባ አሁን የት አደረገችው? ቢባል መልሱ አንጋፋዋ ጋዜጠኛ ስመኝ ቴሶ ዘንድ ነው፡፡ አጋጣሚውም ደራርቱ ይህን ካባ ለምወደው ሰው ነው የምሰጠው በማለት፤ የስመኝ የሰርጓ ቀን በዚሁ ካባ እንድትሞሸር ለማድረግ ችላለች፡፡ አሁንም አልፎ አልፎ የሚገናኙት ጠያቂዋ ስመኝና ተጠያቂዋ ደሬ ፍቅራቸው ዛሬም ድረስ ዘመን ተሻጋሪ ሆኗል፡፡
የኪነት በድን ምሥረታ
ስመኝ፣ ጋዜጠኛ ብቻ አልነበረችም፤በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የሚተላላፉ የመዝናኛ ይዘቶችን ለማሳደግ የበኩሏን ጥራለች፡፡በተለይ በወቅቱ ብዙም የሙዚቃ አርካይቭ ላልነበረው ኢቲቪ፤ የኦሮሚያ ዞኖችን ከእነ ወርቁ ጋዲሳ ጋር በመዘዋወር፤የዞን የኪነት ቡድኖች እንዲቋቋሙ ሚናዋን ተወጥታለች፡፡እነ ሃጫሉ ሁንዴሳን ያሳደገውን የሆራ አምቦ የኪነት ቡድን አቋቁማ የአካባቢው ባህል፤ወግ፤እሴትና ማንነት ጎልቶ እንዲወጣ ስመኝ ከጋዜጠኝነቱ ሌላ ዳንጋን በማሳመር ረገድ ያበረከተችው አስተዋፆ ነበር። ከኪነት ቡድኑ በተጨማሪ አሁን ላይ በኦሮሞ አርት ውስጥ ያሉትን ሙዚቀኞች አቅማቸውን እንዲያወጡ ወደ ህዝቡ መጥተው እንዲተዋወቁ መድረክ በመስጠት፤ የወጣቶች ክህሎት አደባባይ እንዲወጣ ያደረገችም ጭምር ነበረች፡፡
ለወጣት ጋዜጠኞች እድል መስጠት
ብቸኛ በነበረው ኢቲቪ በርካታ ወጣቶች ወደ ሙያው እንዲመጡና ከህሎታቸውን እንዲያዳብሩ በማድረግ ረገድም ስመኝ ሚናዋ ከፍተኛ ነበር፡፡ አሁን ላይ በኢቲቪና በተለያዩ ሚዲያዎች ውስጥ የሚገኙ ጋዜጠኞችንና ዜና አንባቢዎችን ከስር ጀምራ ኮትኩታ አሳድጋቸዋለች፡፡ የታደለ ገመቹ ባለቤት ጋዜጠኛ አይዳ ከበደ፤ዝናሽ ኦላኒ፤ቢሊሴ ኢረናና ሌሎችም ጋዜጠኞች የስመኝን ዱካ ተከትለው ያደጉ ጋዜጠኞች ናቸው፡፡ ከሙያዊ እናትነቷ በተጨማሪ የሁሉም አዲስ ገቢ ጋዜጠኞች አበረታችና፤በተለይ ሴት ጋዜጠኞች እንድንበረታታ እናታዊ ምክሯን የምትለግሰን ስናጣፋም የምትመክረን እናታችን ነበረች ይላሉ የቀድሞ ባልደረቦቿም።
አማተር ተዋንያንን ማብቃት
በወቅቱ የዳንጋ ቡድን በበአል ቀንም ሆነ ለዘወትር የቅዳሜ ፕሮግራም ድራማ አንድ የተለመደ ክስተት ሆኖ ተወዳጅነቱን ካሳደጉት የዳንጋ ክፍሎች ውስጥ አንዱ ነበር፡፡ ታዲያ የኢቲቪ ቅጥር ያልሆኑት እነኚህ አማተር ድራማ ሰሪዎች በየጊዜው ፊልድ ይዞ ለመሄድ የአበል ሁኔታቸው እያስቸገረ አንዳንዴ አላሰራ ይላቸዋል፡፡ይህን ያስተዋለችው ስመኝ ከጋዜጠኝነቱ ጎን ለጎን በየድርጅቱ በመዘዋወር ስፖንሰር በማፈላለግ የዳንጋ ድራማ እንዳይቋረጥ በግል ተነሳሽነቷ ጊዜዋንና ጉልበቷን ያለምንም ክፍያ ለኢቲቪ ስለ መክፈሏ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ምንም እንኳን ስመኝ ኢቲቪን ስትለቅ ስፖንሰር አፈላላጊ በመጥፋቱ ድራማ በዳንጋ ላይ መታየቱ ቢያቆምም፤ ያኔ ላይ ማንም አባከና ያላላቸው እነኝያ አማተር አርቲስቶች ዛሬ ላይ ትልቅ ቦታ ደርሰው የኦሮሞን አርት በማሳደግ ላይ ያሉ ሲሆን ለነሱ እዚህ መደረስ የያኔው የስመኝና የወዳጆቿ ውለታ በቀላል የሚታይ አይደለም፡፡
የጋዜጠኝነት ገጠመኞቿ
በተለያዩ ጊዜያት ወደ ክልልና ዞን ከተሞች በስራ የመጓዝ እድሉ የነበራት ጋዜጠኛ ስመኝ ቴሶ በህይወቷ አዝናኝም አስደሳችም የሆኑ ገጠመኞች ነበሯት፡፡
በአንድ ወቅት ኩዩ ሰላሌ ከጋዜጠኛ መሃመድ አህመድ ጋር በተጓዙበት ወቅት ቤተክርስትያን መስሏት መስኪድ የተሳለመችውን ዛሬማ በቅድሚያ ታነሳዋለች፡፤የባሌው ገንፎና ቅቤ ከአይኑዋ አይጠፉም፤ በኢትዮ፟_ ኤርትራ ጦርነት ወቅትም በዛላምበሳ መድፍ ተተኩሶ መኪና ስር ስለገባችበት አስጨናቂ እለት፤ከሳሙኤል ዳባ ጋር በአውሮፕላን ሲሄዱ የጮኸችው ጩኸት፤በጋዜጠኝነት ህይወቷ ውስጥ ዛሬም ድረስ የመትረሳው ገጠመኟ ነው፡፡
አበርክቶዎች
ጋዜጠኛ ስመኝ ቴሶ በኢቲቪ ቆይታዋ በበርካታ ነገሮች ፈር ቀዳጅም ጭምር ነች፡፡ በተለይ ኢሬቻ እንደ ባእድ አምልኮ በሚታይበትና በሚዲያ ጭምር ሽፋን በማይሰጥበት ወቅት ስመኝ ወደ ሰበታ አካባቢ በመሄድ በኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ታሪክ የመጀመርያዋ የበአሉ ዘጋቢ ጋዜጠኛ ነች፡፡
ብሄር ብሄረሰቦች ባህልና ማንነታቸውን መግለፅ በማይችሉበት ወቅት፤ ኢቲቪ በዝዋይ ከተማ ባዘጋጀው የበአል ዝግጀት ላይ፤ ፕሮግራም ስታስተዋውቅ የአርሲ የባህል ልብስ ለብሳ |”ከእንግዲህ በኋላ የኦሮሞ ሴቶች በራሳችሁ የባህል ልብስ አጊጡ፤ ወደ ማንነታቸሁ ተመለሱ” በማለት መልእክቷን አስተላልፋለች፤ከዚያ በፊት በኢቲቪ ታሪክ በኦሮሞ የባህል ልብስ ተለብሶ ፕሮግራም ተሰርቶ ዜና ተነቦ አይታወቅም ነበር፡፡ ከዚህም ባለፈ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ የኦሮሚያ ዞኖችን አለባበስ በቲቪ በማሳየት የወጣችበትን ማህበረሰብ ማንነትና ባህል ለመላው አለም አሳውቃለች፡፡
97 እና የኢቲቪ ስንብት
በኢቲቪ ቆይታዬ ካተረፍኳቸው ትላልቅ ስኬቶቼ መካከል፤ትልቁ የህዝቤ ፍቅር ነው የምትለው ስመኝ በተለይ ወደ ክፍለ-ሀገር ሲወጡ አልጋቸውን ለቀውላቸው እነሱ መሬት የሚያድሩ አርሶ አደሮች ዛሬም ውል ይሉባታል፡፡ የህዝቡ እንክብካቤና ፍቅር ሳትፈልግ በሙያው ውስጥ እንድትቆይ ያደርግሃል፤በተለይ ባሌ ሄደን ገንፎው በጋሪ፤ቅቤው በባልዲ መቶ የዳንጋ ልጆች የተደመሙበት ወቅት ትዝ ይለኛል ባይ ነች። ይሁን እንጂ ምንም እንኳ የህዝቡ ፍቅር ስመኝን ሳይመቻትም በኢቲቪ ጥቂት እንድትቆይ ቢያደርጋትም እስከወዲያኛው ግን አላዛለቃትም፤ ከዳይሬክተሩ ወርቁ ጋዲሳ ጋር ፊልድ ወጥታ ስትመለስ ነበር “እኔ የበቃኝ ይመስለኛል” ያለችው፡፡ ስለ ሙያው ምንም እውቀት ሳይኖረው ከየትም የሚመደብብህ ካድሬ ከሚከፈልህ እና ከምትደክመው ጋር ተደማምሮ ለ 13 አመታት የቆየሁበትን ኢቲቪን ለመልቀቅ ምክንያት እንደሆኗትም በትዝታ ታዋሳላች፡፡
የስደት ህይወት
ከኢቲቪ ወጥታ ብዙም ሳትቆይ ወደ ስዊድን ያቀናችው ተሰዳጇ ጋዜጠኛ ስመኝ ቴሶ ፤በ 13 አመት የስደት ቆይታዋ ጥቂት ከሙያው ርቃ በንግዱ ዘርፍ ህይወቷን ስትገፋ የነበረች ቢሆንም ፤በ2009 በሀገር አቀፍ ደረጃ የተነሱትን የተቃውሞ እንቅስቃሴ በመደገፍ ከታገሉት አንጋፋ ጋዜጠኞች መካከል አንዷ ነበረች፡፡በቆይታዋም ትዳር መስርታለች።
ስመኝ ከስደት መልስ
ከለውጡ በኋላ በርካታ ዜጎች ወደ ሀገር ሲመለሱ ይህ እድል ያጋጠማት ስመኝ ፤ወደ ቀድሞ ሙያዋ ተመልሳ ከናፈቃት የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ለመገናኘት የራሷን መልቲ ሚዲያ ከፍታ እንቅስቃሴ የጀመረች ቢሆንም ከኮቪድ መምጣት ፤ያልጠበቀችው የአባቷና የአንድ እህቷ ሞት፤በእጇ ላይ በንብ ተነድፋ እጅሽ መቆረጥ አለበት እስከተባለችበት ጊዜ ድረስ ነገሮች ተደማምሮ በፈለገችው ደረጃ ነገሮች ያልተስተካከሉላት አስቸጋሪ ወቅቶችን አሳልፋለች፡፡ ምንም እንኳን ስሙን ለጊዜው መጥቀስ ከማትፈልገው የሚዲያ ተቋም ጋር ለመስራት እንቅስቃሴ ብትጀመርም አንዳንድ ምቹ ባልሆኑ ምክንያቶች በሚዲያው ዘርፍ ከናፋቃት ህዝብ ጋር ለመገናኘት ሳትችል ቀርታላች፡፡
የስመኝ እቅዶች
በነቀምት ከተማ በኢቲቪ ባገለገለችበት ዳንጋ ስም የራሷን ምግብ ቤት ብትከፍትም ፤ በሚዲያው ዘርፍም ፍቃዷን ዳግም አውጥታ ዳንጋ የተሰኘ የኦሮሞን ባህል፤ቋንቋ፤አርትና ጋዜጠኝነቱን ከፍ ያደረጉ ባለሙያዎችን እውቅና የሚሰጥ የሽልማት ድርጅት አቋቁማ ወደ ስራ እየገባች ሲሆን ከአድናቂዎቹና ናፋቂዎቿ ጋር ለመገናኘትም በራሷ ቶክሾው ለመምጣት ቅድመ ዝግጅቷን መጨረሷን ለመረዳት ችለናል፡፡ ስመኝ ቴሶ በግንቦት 19 2015 ከኦሮሚያ ሴቶችና ህጻናት ቢሮ በሙያዋ ላደረገችው አስተዋጽኦ ሽልማት ያገኘች ሲሆን ይህም በሙያዋ እንድትኮራ ያደረጋት ነው፡፡
አቶ ይፍቱ ጎበሳ የሰጡት ምስክርነት
ዳንጋ የሚባል መሰናዶ ነበር፡፡ በጣም ጥሩ አድርጋ ትሰራ ነበረ፡፡ መሰረት ከጣሉት የኦሮሚኛ ጋዜጠኞች አንዱዋ ናት ፡፡ ዳንጋን የፈጠረች ናት፡፡ በጣም ተግባቢ ናት፡፡ የስመኝ ፕሮግራም በር ከፋች ነው፡፡ መዝናኛ ላይ ትልቅ አሻራ አኑራለች፡፡
ሁለገብም ነች፡፡ በማህበራዊ በባህል ላይ ትሰራለች፡፡ ከቀበሌ ኪነት ጀምራ ያደገች በመሆኑ ይህም በጥበብ ስራዋን እንድትሰራ አስችሏታል፡፡
ያንን ሁሉ ጥሳ ወጥታ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ትኩስ ጉልበት ያላት ናት፡፡
መዝጊያ፦ ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን አቋም የሚንፀባረቅበት ነው፡፡
ስመኝ ቴሶ በአፋን ኦሮሞ የመዝናኛ ጋዜጠኝነት ላይ የራሷን ትልቅ አሻራ ያኖረች ታታሪ ሰው ነች፡፡ የኦሮሞን ባህል እና ታሪክ በሚገባ ለማሳየት የቻለች ድንቅ ጋዜጠኛ ነች፡፡ በየዱር ገደሉ እየዞረች ሙያዋን አክብራ ስትሰራ የኖረች ብርቱ ሰው ነች፡፡ 13 ዓመት በቆየችበት ጊዜ በተለይ የኢቲቪ ትዝታዋ ፈጽሞ የማይረሳ ነው፡፡ ስመኝ ከሀገር ውስጥ ባሻገር ውጭ ባሉ አድናቂዎቿ የምትመሰገን ነች፡፡ ለሙያዋ ክብር መስጠቷ አስከብሯታል፡፡ ከወር በፊት ያገኘችውም እውቅና ይህንኑ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡ ስመኝ ቴሶ ለአመታት በባህር ማዶ ነበረች፡፡ አሁን ደግሞ በእናት ሀገሯ ላይ በሚድያ እና ፕሮሞሽን ዘርፍ አቅሟን ለመጠቀም ዝግጁ ነች፡፡
ስመኝ በኢትዮጵያ ቲቪ ታሪክ ውስጥ ትልቅ አሻራ ያኖረች ነች፡፡ ጣቢያውም ቢሆን ተገቢውን ክብር እና እውቅና ሊሰጣት ይገባል፡፡ በኢቢሲ ያለውን የመዝናኛ መሰናዶ በህዝብ ዘንድ ተወዳጅ ያደረገች በመሆኗ ልትመሰገን ይገባል፡፡ ስመኝ በኢትዮጵያዊነቷ የምትኮራ፤ ከሁሉ ጋር የምትግባባ ምርጥ የሚድያ ሰው ስትሆን የስራ ታሪኳም ብዙ ያስተምራል ብለን እናስባለን፡፡
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ