ሌ/ኮሎኔል
ፋንታሁን ተምትሜ
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በውትድርና ሙያ ትልቅ አስተዋጽኦ የነበራቸውን ባለሙያዎች የህይወት ታሪክ እያወጣ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በተለይ ደግሞ ወታደራዊ
ሳይንስን መሰረት በማድረግ ሀገራቸውን በእውቀት ያገለገሉ ሰዎች ታሪክ
ተሞክሯቸው ለአዲሱ ትውልድ አንድ ነገር ያስተምራል ብለን እናስባለን፡፡ ዋናው ግባችን አዲሱ ትውልድ የቀደሙ የታሪክ ባለውለታዎች
በወጉ እንዲያውቅ ማድረግ ስለሆነ እርስዎም ታሪኩ መሰነድ አለበት የሚሉትን ሰው ይጠቁሙን፡፡ ተገቢውን መስፈርት የሚያሟሉትን በዚህ
ገጽ ላይ እናቀርባለን፡፡ አሁን በዚህ ጽሁፍ ታሪካቸው የሚታየው ሌተናል ኮሎኔል ፋንታሁን ተምትሜ ሲሆኑ ከ31 አመት በፊት ነበር
ህይወታቸው ባልታወቀ ሁኔታ ያለፈው፡፡
እኒህ በወታደራዊ እውቀት የካበተ ልምድ ባለቤት የሆኑ ሰው ብዙ የሰሩ ቢሆኑም ብዙ አልተዘመረላቸውም
ብለን ስላሰብን ይህን የህይወት ታሪካቸውን አውጥተነዋል፡፡ ወደፊት ከቤተሰቡ ጋር በመነጋገር እና አንድ ላይ በመሆን በህይወታቸው ዙርያ ተጨማሪ የስነዳ ተግባራትን እናከናውናለን፡፡ ይህን የህይወት ታሪክ ስናሰናዳ ልጃቸው ህይወት ፋንታሁን እና አብሮ አደግ
ጓደኛቸው ኮሎኔል አደፍርስ ታፈሰ ላደረጉልን ትብብር ምስጋናችን የላቀ
ነው፡፡ ይህ ጽሁፍ በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ ተሰናድቶ በተወዳጅ ሚድያ ብሎግና የፌስ ቡክ ገጽ ላይ የወጣ ሲሆን አስፈላጊው ማሻሻያ
እየተደረገበት በየጊዜው እንዲወጣ ይደረጋል፡፡
እንደ መግቢያ
ሌ/ኮሎኔል (ሌ/ኮ) ፋንታሁን ተምትሜ: ጠይም፣
መልከ- መልካም፤ ቀጭን መለሎ ቁመና ያለው፤ በወታደር ቤት በሥነ ሥርዓት ታንጾ ያደገ፤ የመርህ ሰው፤በአነጋገሩ የተቆጠበ፤ በአለባበሱ
የተሽቀረቀረ፤ ቀጠሮ አክባሪ፤ ከፍተኛ የማስታወስ ችሎታ በተፈጥሮ የታደለ፤ በሥራው ታታሪ፤ ለወሬና ለአሉባልታ ጊዜውንና ልቡን የማይሰጥ፤
ቻይና ትዕግስተኛ ግን ገደብ ካለፈ ቆራጥ አቋም የሚይዝ፤ ለዘመድና ጓደኛ ችግር ደራሽና ሰው አክባሪ፤ በብዙዎች ዘንድ ያልተለመደ
የየቀን ውሎውን ማታ የሚመዘግብና አንደበተ- ርቱዕ ሰው ነበር።
ትውልድና ልጅነት
የሌ/ኮ ፋንታሁን አባት የአስር አለቃ ተምትሜ
ሳሴ ማይጨው በነበረው የጦር ክፍል በማገልገል ላይ ሳሉ ሌ/ኮ ፋንታሁን በ1945 ዓ/ም ተወለደ፤ ብዙም ሳይቆዩ አስር አለቃ ተምትሜ
ወደ አዲስ አበባ ተቀይረው በጨርቆስ ሠፈር መኖር ጀመሩ። የሌ/ኮሎኔል መንግሥቱ ኃ/ማሪያም አባት አምሳ አለቃ ኃይለማሪያም ወልዴ
ጂማ ከነበረው መድፈኛ ሻለቃ ወደ አዲስ አበባ ተቀይረው በዚሁ ሠፈር ኗሪ ነበሩ፤ ሁለቱ ወታደሮች በሠፍር ተገናኝተው ከጓደኝነትም
በላይ ቤተሰብም ለመሆን በቅተዋል። የእነሱን ፈለግ በመከተል ልጆቻቸውም በጣም ይቀራረቡ ነበር።
ወደ ትምህርት አለም
ሌ/ኮ ፋንታሁንም በዚሁ ሠፈር አድጎ ዕድሜው ለትምህርት ሲደርስ የአንደኛ ደረጃ
ትምህርቱን በሽመልስ ሃብቴ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት አጠናቅቆ የ2ኛ ደረጃ ትምህርቱን በሽመልስ ሃብቴ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት እስከ 11ኛ
ክፍል ድረስ ተምሮ እንደ አባቱ አገሩን በውትድርና ለማገልገል የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሐረር ጦር አካዳሚ መሰናዶ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት
12ኛ ክፍል መግባት የሚያስችለውን የአካዳሚክና የአካል ብቃት ፈተና በማለፉ በነሐሴ 1961 መሰናዶ 2ኛ ት/ቤት ከ10ኛ ክፍል
ለ14ኛ ኮርስ ተመልምለው 11ኛ ክፍል አጠናቀው ወደ 12ኛ ክፍል ካለፉት ተማሪዎች ጋር ተቀላቀለ። ፋንታሁን በአንድ ዓመት የመሰናዶ ት/ቤት ቆይታው
በአንድ በኩል ለ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከፍተኛ ዝግጅት ሲያደርግ በሌላ በኩል ደግሞ ከክፍል ጓደኞቹና ከከተማው አካባቢ ጋር
ራሱን ሲያስተዋውቅ ቆየ።
ጠቅላይ ፋንታሁን
የክፍል ጓደኞቹ ከእርሱ በፊት የገቡት በአንድ
ዓመት የመሰናዶ ቆይታቸው ያልተገነዘቡትን ጠቅላላ የወታደራዊ ሁኔታ ፋንታሁን በወታደር ቤት በማደጉ ወታደራዊ ቃሎችን፤ አሠራሮችን
ወዘተ ጠቅላላ ዕውቀት ስለነበረው በክፍል ጓደኞቹ “ጠቅላይ“ የሚል ቅጽል ስም ተሰጠው፤ አካላዊ ቁመናውም ትንሽ ስለነበረ በቅጽል
ስሙ ላይ አንቱታ ተጨምሮለት ጠቅላይ ይህን አሉ፤ ጠቅላይ ይህን ሠሩ ይባል ነበር።
የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሐረር ጦር አካዳሚ መሰናዶ
2ኛ ደረጃ ት/ቤት በ1962 ዓ/ም ለ2ኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና (ማትሪክ) ካቀረባቸው ውስጥ 58 ተማሪዎች አልፈው በዕጩ መኮንነት
ወደ አካዳሚው ሲገቡ ከእነርሱ ውስጥ አንዱ ፋንታሁን ነበር።
ሻምላ ተሸላሚው
ዕጩ መኮንን ፋንታሁን ተምትሜ በ3 ዓመት የአካዳሚ
ቆይታው ከኮርስ ጓደኞቹ ተግባቢ፤ የሚሰጠውን የወታደራዊና የአካዳሚክ ትምህርት በጥሞና የሚከታተል፤ በስፖርታዊ እንቅስቃሴ ሁለገብ
የሆነ፤ ሥነ ሥርዓት አክባሪ፤ በአስተማሪ መኮንኖች ዘንድ የተወደደና የተከበረ ነበር። በአካዳሚው የሚሰጠውን የ3 ዓመት ሥልጠናውና ጨርሰው የተመረቁት 49 ሲሆኑ ከእነሱ ውስጥ አንዱ
ፋንታሁን ነበር። በአካዳሚው የ3 ዓመት በአካዳሚክና በወታደራዊና ሥልጠና ከፍተኛ ወጤት ላመጣ ዕጩ መኮንን የሚሰጠው ከፍተኛ ሽልማት
ሻምላ ነበር፤ ዕጩ መኮንን ፋንታሁን ተምትሜ ሁለ-ገብ ተብሎ ከንጉሠ ነገሥቱ እጅ ሻምላ የተሸለመው እሱ ነበር።
የ14ኛ ኮርስ መኮንኖች ምደባ ለየት ያለ ነበር፤
ከኮርሱ 1ኛ የወጣው ብቻ አየር ወለድ ሲመደብ የቀሩት ሁለት ተከፍለው ግማሹ 2ኛ ክ/ጦር አሥመራ ሲሆን ሌላው ግማሽ ደግሞ 3ኛ
ክ/ጦር ሐረር ነበር። ሁለቱም ክ/ጦሮች የተላኩላቸውን መኮንኖች በክፍሎቻቸው ደልድለዋል። በዚሁ መሠረት መ/አለቃ ፋንታሁን የተመደበው
አዲግራት በሚገኘው 1ኛ መድፈኛ ሻለቃ ነበር። በዚህ ክፍል ብዙም ሳይቆይ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሐረር ጦር አካዳሚ በአስተማሪነት
እንዲመደብለት ለምድር ጦር መምሪያ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት ተፈቅዶ ወደ አካዳሚው ተዛውሮ መጣ።
አስተማሪው ፋንታሁን
መ/አለቃ ፋንታሁን በአካዳሚው ውስጥ በዕጩ መኮንንነት
ቆይታው የቀሰመውን የወታደራዊ ሳይንስ ዕውቀት አሁን ደግሞ ለማስተማር የሚያደርገው ዝግጅት ወታደራዊ ዕውቀቱን ከፍተኛ ደረጃ ላይ
ለማድረስ ረድቶታል። ፋንታሁን በአካዳሚው በአስተማሪነት ቆይታ ጊዜ፤ ሁለገብ፤ ሁሉንም ትምህርት ማስተማር የሚችል፤ ተወዳጅና ጎበዝ
አሰልጣኝ እንደነበረ ያስተማራቸው ኮርሶች ይመሰክሩለታል። የአካዳሚው
የትምህርት መኮንን የነበሩት ሌ/ኮሎኔል ደምሴ ቡልቶ (በኋላ ሜ/ጀኔራል) በዝግጅቱና በአቀራረቡ ያደንቁት ነበር።
መንግስቱና ፋንታሁን
የሌ/ኮሎኔል መንግሥቱ ኃ/ማሪያም አባትና የሌ/ኮሎኔል ፋንታሁን አባት የቅርብ
ጓደኝነትና ቤተሰብነት ልጆቻቸውን ያቀራረበ ነበር። ሌ/ኮሎኔል ፋንታሁን ተምትሜ ከልጅነቱ ጀምሮ ሌ/ኮሎኔል መንግሥቱን በደንብ ያውቃቸዋል
ይቀርባቸዋል። በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሐረር ጦር አካዳሚ ዕጩ መኮንን ሆኖ ሥልጠና ላይ በነበረበት ጊዜ ሌ/ኮሎኔል መንግሥቱ 3ኛ
ክ/ጦር መሣሪያ ግምጃቤት ይሠሩ ስለነበር ፋንታሁን በእረፍት ጊዜው ቤታቸው ይሄድ ነበር፤ ባለቤታቸውም ወ/ሮ ውባንቺም ያቀርቡታል።
በዚሁ ቀረቤታቸው የተነሳ ሌ/ኮሎኔል መንግሥቱ ኃ/ማሪያም ሥልጣን ላይ እንደወጡ ሌ/ኮ ፋንታሁንን አዲስ አበባ ቤተመንግሥት አስጠርተው
ሲቪል ሆኖ ከእርሳቸው ጋር እንዲሰራ ጠይቀውት ነበር፤ ሆኖም አገሩን ማገልገል የሚፈልገው በሠለጠነበት ወታደራዊ መስክ መሆኑን ሲገልጽላቸው
ደስተኛ ባይሆኑም አሰናበቱት።
የዚያድ ባሬን
ጦር ያባረረ
በሰኔ ወር 1969 ዓ/ም ሶማሊያ ያሰማራችው
ሠርጎ ገብ ወንበዴ የሐረር ጂጂጋን መንገድ በፋፈም ሸለቆ አካባቢ ላይ ለመዝጋት እንቅስቃሴው እያየለ በመሄዱ ይህን ሥጋት ለመቀነስ
ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሐረር ጦር አካዳሚ የገላጭ ሻምበል ጦር እንዲሄድ ታዘዘ። የሻምበል አዛዥ ሆነው የተመደቡት ከ7ኛ ኮርስ ሁለት
ዕጩ መኮንኖች ተመርጠው ወደ እንግሊዙ ሳንዲረስት ጦር አካዳሚ ተልከው ተመርቀው ተመልሰው በአካዳሚው ውስጥ አስተማሪ ከነበሩት አንዱ
ሻምበል ኢያሱ ዜጎ ነበሩ። መ/አለቃ ፋንታሁን የመቶ መሪ ሆኖ ዘመተ። ይህ ሻምበል ጦር ጠቅላይ ሠፈሩን ቆሬ ላይ አድርጎ ጥበቃውን
ጀመረ። የዚህ ሻምበል ጦር ቆሬ ላይ መሆን ከጂጂጋ ያፈገፈገው ጦር ቆሬ ላይ አስቁሞ መከላከያ ቦታ እንዲይዝ ለማድረግ ረድቷል።
ገላጭ ሻምበሉ በመንገድ ጥበቃ ላይ እያለ ግንቦት
19 ቀን 1969 ዓ/ም ከፍተኛ ኃይል ያለው የወንበዴ ጦር ማጥቃት ሰንዝሮ ነበር፤ ሆኖም የወገን ጦር በመልሶ ማጥቃት ወንበዴውን
ከቦ የደመሰሰ ሲሆን በወገንም በኩል የተከፈለው መስዋዕትነት ቀላል አልነበረም። የሻምበሉ አዛዥ ሻምበል ኢያሱ ዜጎና በርካታ ወታደሮች
ተሰውተዋል። የመቶ መሪ የነበረው መ/አለቃ ፋንታሁንም በከባድ ሁኔታ ቆስለው ወደ ምሥራቅ ዕዝ ሆስፒታል ከተላኩት ውስጥ አንዱ ነበረ።
መቶ አለቃ ፋንታሁን በምስራቅ እዝ
መ/አለቃ ፋንታሁን ሕክምናውንና የሐኪም ዕረፍቱን
ጨርሶ ወደ ሥራ ሲመለስ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሐረር ጦር አካዳሚ ተዘግቶ ስለነበር አዲስ በተቋቋመው የምሥራቅ ዕዝ በዘመቻ መምሪያ
ውስጥ ተመደበ። በዚህን ጊዜ የምሥራቅ ዕዝ አዛዥ ኮሎኔል ሙላቱ ነጋሽ (በኋላ ሜ/ጀኔራል)፤ የፖለቲካ ኃላፊው ሻምበል ገዛኸኝ ወርቄ፤
የዘመቻ መምሪያው ኃላፊና የመ/አለቃ ፋንታሁን አለቃ ኮሎኔል መስፍን ገብረቃል (በኋላ ሜ/ጀኔራል) ነበሩ። ፋንታሁን በዘመቻ መምሪያ
ሆኖ ቅልጥፍናው፤ እውቀቱ ለሥራ ያለው ፍቅር የሚደንቅ ነበር።
መ/አለቃ ፋንታሁን በዘመቻ መምሪያው ሥራ ላይ
እያለ የሶማሊያ መንግሥት በሃገራችን ላይ ወረራ በመሰንዘሩ፤ ወረራውን ገቶ በመልሶ ማጥቃት ከአገራችን ለማስወጣት ከወዳጅ አገሮች
ከፍተኛ አመራር የሚሰጡ ከሶቪየት ሕብረት ጀኔራል ፔትሮቭና ከኪዩባ ጀኔራል ኦቻዎ ውጊያውን አቅዶ ለመምራት ቢሮ የተሰጣቸው በድሬዳዋ
ቤተ- መንግሥት ነበር፤ መ/አለቃ ፋንታሁንም ከዕዙ ዘመቻ መምሪያ ተመርጦ ከሁለቱ ጀኔራሎች ጋር ሆኖ እንዲሰራ ወደ ቤተ- መንግሥት
ተልኮ ሥራ ጀመረ። ሁለቱ ጀኔራሎች ስለወራሪው የሶማሊያ በነበራቸው የሳታላይት መረጃ መሠረት የመልሶ ማጥቃቱ ሲታቀድ፤ የዕቅዱ ተሳታፊ
ነበር።
በመልሶ ማጥቃቱ ወቅት በየግንባሩ የሚደረገውን
የወገን ጦር የየቀኑን እንቅስቃሴ መረጃ እያጠናቀረ የዘመቻ ሪፖርት እያዘጋጀ ለብሔራዊ አብዮታዊ ዘመቻ መምሪያና ለሌሎችም ለሚመለከታቸው
ሁሉ ይልካል። ሪፖርቱ ለሁለቱ ጀኔራሎች በአማርኛ አስተርጓሚዎቻቸው ይገለጽላቸው ነበር። በሪፖርቱ ዝግጅትና ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች የሚሰጠው ምላሽና በአቀራረቡ ዘይቤ
በጣም ያደንቁት ነበር።
ሁለቱ ጀኔራሎች በተለይም የሶቪየቱ ጀኔራል ፔትሮቭ
የኢትዮጵያን መኮንኖች ችሎታ ዝቅ አድርጎ የማየት ዝንባሌ ነበራቸው፡፡
በተለይም የዕዙ አዛዥ ኮሎኔል ሙላቱ ነጋሽ በሚያደርጉት ገለጻና በሚሰጡት አስተያየት ላይ የሚሰጡት ትችት ለቦታው ብቁ
አለመሆናቸውን የሚጠቁም ነበር። ለዕዙ አዛዥነት ከእርሰዎ ይልቅ መ/አ ፋንታሁን ይመጥናል እያሉ በተደጋጋሚ ስለሚናገሩ ኮሎኔል ሙላቱ
በሌ/ኮ ፋንታሁን ላይ የጥላቻ መንፈስ እንዲፈጠርባቸው አድርጓል።
በ1970 ዓ/ም የሶማሊያ ጦር በመልሶ ማጥቃት ከተባረረ በኋላ ድሬዳዋ ቤተ
መንግሥት ውስጥ ተቋቁሞ የነበረው የሁለቱ ጀኔራሎች ቢሮ ሲዘጋ መ/አለቃ ፋንታሁን ፊት ወደ ነበረበት ምስራቅ ዕዝ ዘመቻ መምሪያ
ተመልሶ ሥራ ጀመረ። በዕዙ መምሪያ ውስጥ ፋታ ተገኝቶ ቅዳሜና እሁድ ከተረኛ በስተቀር ሌላው በየቤቱ ማደር ተጀምሯል። ግንቦት 12
ቀን 1970 ዓ/ም ቅዳሜ ቀን የዘመቻ መምሪያ ተረኛ መ/አለቃ ፋንታሁን ተምትሜ ነበር። ከምሽቱ 2 ሰዓት ሲሆን ኮ/ል ሙላቱ ነጋሽ
ደውለው ነገ ሄሊኮፕተሩ ፈልጎ አንሽ ጦር (Rescue Team) ይዞ መሄዱ ቀርቶ ደጋሃቡር ላይ 3 ቁስለኞች ስላሉ ሄዶ እነሱን
ያምጣ ብለው ለመ/አለቃ ፋንታሁን ትዕዛዝ ይሰጣሉ።
ለጦሩ ቁሳቁስ የሚያመላልስ DC-3 (ዳኮታ)
አውሮፕላን ብልሽት ገጥሞት ቀብሪደሃር ላይ ነበር። ከምሽቱ 3 ሰዓት ሲሆን የተበላሸው አውሮፕላን ተጠግኗል፤ ነገ ጣት ወደ ድሬዳዋ
ይሄዳል የሚል መልዕክት ቀብሪደሃር ካለው ጦር ደረሰው። ሲመጣ ደጋሃቡር በመንገዱ ላይ ስለሆነ አርፎ 3ቱን ቁስለኞች ይዞ እንዲመጣና
ሄሊኮፕተሩ ለተዋጊዎቹ ፈልጎ አንሺ ጦር ይዞ እንዲሄድ አቅዶ ይህንኑ ለአዛዡ ለማሳወቅ ቤታቸው ቢደውል ኮ/ል ሙላቱ ስልካቸውን አላነሱም።
ያቀደው ምንም ችግር አያስከትልም በሚል ማታውኑ ቀብሪደሃር ያለው አውሮፕላን ደጋሃቡር አርፎ ቁስለኞቹን ይዞ እንዲመጣ፤ ሄሊኮፕተሩ
ፈልጎ አንሺ ጦር ይዞ እንዲሄድ ለሚመለከታቸው ትዕዛዝ አስተላለፈ።ድሬዳዋ ላይ ከነበረው የአየር ኃይል ምድብ ተዋጊ አውሮፕላኖች
ዒላማ ተሰጥቷቸው ሄደው ሲመቱ ድንገት አንድ አውሮፕላን ተመቶ አብራሪው በዣንጥላ ሲወርድ እሱን ፈልጎ የሚያነሳ ጦር
(Rescue Team) በሄሊኮፕተር በቅድሚያ በዒላማው አካባቢ መድረሱን ሲያሳውቅ ተዋጊዎቹ ይነሳሉ። ፈልጎ አንሺውን ጦር የሚወስድ
ሄሊኮፕተር ከሌለ ተዋጊ አውሮፕላኖች እንዳይበሩ የሚያዝ ደንብ ነበር።
እሁድ ጧት መ/አለቃ ፋንታሁን የሚቀይረውን ተረኛ
በመጠባበቅ ላይ እንዳለ ተዋጊ አውሮፕላኖች ከድሬዳዋ ወደ ኦጋዴን አቅጣጫ በሐረር ላይ ሲያልፉ ድምጻቸው ተሰማ። ወዲያው ኮ/ል ሙላቱ
ደውለው ወዴት ነው የሚበሩት? ብለው ይጠይቁታል። መ/አለቃ ፋንታሁን ለዕቅዱ የእርሳቸውን ይሁንታ ለማግኘት ማታ ስልክ ደውሎ እንዳጣቸው
ገልጾ ቁስለኞቹም ድሬዳዋ መድረሳቸውን፤ ሄሊኮፕተሩም ፈልጎ አንሺ ጦር ይዞ በመሄዱ ተዋጊ አውሮፕላኖች የተሰጣቸውን ዒላማ ለመምታት
መሄዳቸውን ያስረዳቸዋል። ኮ/ል ሙላቱም በአደረባቸው ጥላቻ ይመስላል ትእዛዜን አልፈጸምክምና ወታደር ፖሊስ ሄደህ አመልክት ብለው
አዘዙት። ወታደር ፖሊስ ጥፋተኛ የሆኑ የሠራዊቱ አባላት የሚታሰሩበት
ነው። መ/አለቃ ፋንታሁንም በትዕዛዙ መሠረት ቁርሱን እንኳን ሳይበላ ሄዶ እስር ቤት ገባ። መ/አለቃ ፋንታሁን የሰራው የሚያስመሰግን
እንጂ የሚያሳስር አልነበረም። ልብ በሉ ቁስለኞቹም ተነስተዋል፤ ሄሊኮፕተሩም ለአየር ኃይል ግዳጅ ውሏል፤ እንደኮሎኔል ሙላቱ ትዕዛዝ
ቢሆን ኖሮ ቁስለኞቹ ይነሳሉ፤ ተዋጊ አውሮፕላኖች ለግዳጅ አይነሱም ነበር።
የመ/አለቃ ፋንታሁን ያለ ጥፋቱ መታሰሩ በዕዙ
መምሪያ ባሉ መኮንኖችና የበታች ሹሞች መነጋገሪያ ሆኖ ስለነበር በዕዙ ፖለቲካ መምሪያ የታሰረበትን ምክንያት አቅጣጫ የሚያስለውጥ
ዘዴ ተቀየሰ። መ/አ ፋንታሁን ፖለቲካ አይወድም፤ ለካድሬዎች አጎብዳጅና አሽቃባጭ ባለመሆኑ የዕዙ ፖለቲካ መምሪያ ኃላፊ በሻምበል
ገዛኸኝ ወርቄና በሥራቸው ባሉ ካድሬዎች ፋንታሁን የታሰረው የኢህአፓ አባል መሆኑ መረጃ ስለተገኘ ነው የሚል ዘመቻ ተጀመረ፤ ለሌ/ኮሎኔል
መንግሥቱ ኃይለማሪያምም ደረሰ። ኢህአፓ ይሁን አይሁን ማወቂያ ዘዴ ስለሌለ የፋንታሁንን ጉዳይ የሚያነሳ ጠፋ፤ እሱም የዕሥር ቤት
ኑሮውን ተያያዘው።
መ/አለቃ ፋንታሁን የኢህአፓ አባል ሆኖ ሳይሆን
በተቀነባበረ ቂም በቀል የታሰረ በመሆኑ ሞራሉ ዝቅ እንዳይል የየዕለት የተለምዶ ድርጊቱን ያከናውን ነበር፤ በየቀኑ በጠዋት ተነስቶ
ተጸዳድቶ፤ ጥርሱን ፍቆ፤ ፀጉሩን አበጥሮ፤ ልብሱን ቀይሮ ለሥራ እንደሚሄድ ሆኖ ይዘጋጃል። በዚህ ተግባሩ አብረውት የታሰሩ “የደቦቃው
ጆሊ“ የሚል ቅጽል ስም አውጥተውለት ነበር። ትርጉሙን ግን አላውቀውም።
ከላይ እንደተጠቀሰው መ/አለቃ ፋንታሁን ሌ/ኮሎኔል
መንግሥቱ ኃይለማሪያምን በደንብ የሚያውቃቸው በመሆኑ ያለ ጥፋቱ ታስሮ ኢህአፓ የሚል ታፔላ የተለጠፈለት ትክክል አለመሆኑን በቤተሰብና
ሌ/ኮሎኔል መንግሥቱ አካባቢ ባሉ የሚያውቃቸው ባለሥልጣኖች በኩል ለሌ/ኮሎኔል መንግሥቱ እንዲደርስ አድርጓል፤ ሆኖም አብሯቸው እንዲሰራ
ያቀረቡለትን ጥያቄ ባለመቀበሉ የተነሳ እርሳቸውም ለማስፈታት ፈቃደኛ አልሆኑም።
መ/አለቃ ፋንታሁን ለ9 ወራት በእስር ቤት እንደቆየ
የምስራቅ ዕዝ አዛዥ የሆኑት ብ/ጀኔራል ሙላቱ ነጋሽ በብ/ጀኔራል ደምሴ ቡልቶ ተተኩ። እንዲሁም የፖለቲካው መምሪያ ኃላፊ ሻምበል
ገዛኸኝ ወርቄ በኮሎኔል ወርቁ ቸርነት ተተኩ። ብ/ጀኔራል ደምሴ ቡልቶ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሐረር ጦር አካዳሚ የትምህርት መኮንን
በነበሩበት ጊዜ መ/አለቃ ፋንታሁንን በዕጩ መኮንንነት ቆይታውና ከተመረቀም በኋላ በአካዳሚው በአስተማሪነቱ ጊዜ ጠንቅቀው የሚያውቁት
በመሆኑ የታሰረበትን ምክንያት አጥንተው መታሰር የማይገባው መሆኑን በማመናቸው እንዲፈታ አድርገዋል። መ/አ ፋንታሁን መጋቢት
28 ቀን 1971 ዓ/ም ተፈቶ ቀብሪደሃር ላይ በነበረው በብ/ጀኔራል ይርጋለም ተ/ኃይማኖት በሚታዘዘው የ8ኛ ክ/ጦር የዘመቻ መኮንን
ሆኖ ተመድቦ ወደዚያው አመራ።
መቶ አለቃው በሩሲያ
የክ/ጦሩ ዘመቻ መምሪያ በደንብ የተደራጀ ስለነበር የመ/አለቃ ፋንታሁንን ሥራ
የተቃና አድርጎለታል። ከክ/ጦሩ ክፍሎች ጋር በአጭር ጊዜ ተዋውቆ የዘመቻ ሥራውን በተቀላጠፈ ሁኔታ መምራት ጀመረ። በአብዛኛው የክ/ጦሩ
ብርጌዶችና ልዩ ልዩ ክፍሎች በቂ ሥልጠና ያላገኙ ስለነበር በክ/ጦሩ ውስጥ የተቀናጀ ሥልጠና እንዲሰጥ አቅዶ በተግባር እንዲውል
አድርጓል። በአጭር ጊዜ በክ/ጦሩ ውስጥ ታዋቂ ለመሆን በቅቷል። በዚሁ ሥራ ላይ እንዳለ በ1979 ዓ/ም ለከፍተኛ ወታደራዊ ትምህርት
ተመርጦ ወደ ሶቪየት ሕብረት የመሄድ ዕድል ገጠመው።
መ/አለቃ ፋንታሁን የተላከው ሞስኮ ከተማ ውስጥ
በነበረው በታዋቂው ፍሩንዜ የጦር አካዳሚ ሲሆን የሚያጠናውም ከፍተኛ የአዛዥነትና የመምሪያ መኮንንነት (COMMAND AND
STAFF) ነበር። በትምህርቱ በጣም ጎበዝ ስለነበር በትምህርት ቤቱ በወርቅ ደረጃ የሚመረቅ ተብሎ የሚታሰብ ታዋቂና ተወዳጅም ነበር።
በሞስኮ ከተማ አካባቢ በነበሩ ኢትዮጵያውያን ሲቪል ተማሪዎችም ዘንድ ታዋቂና ተግባቢም ነበር።
በአንድ የፖለቲካ ስብሰባ ላይ በዕውነትና በቅንነት በሰጠው አስተያየት ከፖለቲካ
ተቃዋሚዎች ጋር ተፈርጆ ሊመረቅ አንድ ዓመት ሲቀረው ለዕረፍት አዲስ አበባ መጥቶ ወደ ሞስኮ እንዳይመለስ ተደረገ። መ/አ ፋንታሁን
ሕይወቱ ውጣውረድ የመላበት ቢሆንም አንድም ቀን ተስፋ ቆርጦ አያውቅም። አሁንም ይህ ትክክል ያልሆነ ፍረጃ ማን እንደለጠፈበት ለማወቅ
አንድ ዓመት ሙሉ ጥረት አደረገ፤ ብዙ ባለሥልጣኖችን አነጋገረ፤ በስተመጨረሻም ሌ/ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማሪያም ጋር ቀርቦ ሁኔታውን
አስረድቶ ተመልሶ ሄዶ ያቋረጠውን ትምህርቱ እንዲጨርስ ተፈቀደለት። ሞስኮ ተመልሶ ከታዋቂው የፍሩንዜ ጦር አካዳሚ ያቋረጠውን ትምህርት
በማዕረግ ጨርሶ ተመለሰ።
ከሶቪዬት ሕብረት እንደተመለሰ ቤላ በተከፈተው
የጦር ኃይሎች የአዛዥነትና የመምሪያ መኮንኖች አካዳሚ በረዳት የትምህርት መኮንነትና በአስተማሪነት ተመደበ። በዚህ አካዳሚ ከምድር
ጦር ከአየር ኃይልና ከባህር ኃይል ከሙሉ ኮሎኔል እስከ ሜ/ጀኔራል ድረስ ማዕረግ ያላቸው መኮንኖች የአዛዥነትና የመምሪያ መኮንንነት
በማስተማር ሦስቱም ኃይሎች የሕብረት ውጊያ ማድረግ የሚያስችላቸውን ዕውቀት ለማስጨበጥ ነበር። ከአገር ውስጥና ከውጪ በቀሰመው ወታደራዊ
ሳይንስ ዕውቀቱን በማካፈል ታዋቂና ተወዳጅ አስተማሪ ለመሆን በቅቷል። ኢህአዲግ አዲስ አበባ እስከገባ ድረስ በጦር ኃይሎች አካዳሚ
በአስተማሪነት ቆይቷል።
ፍጻሜው
ኢህአዲግ አዲስ አበባን በ1983 ዓ/ም እንደተቆጣጠረ የቀድሞ ሠራዊትን ለተሃዲሶ
ሥልጠና ጦላይ፤ ኡርሦና ሌሎችም ወታደራዊ ማሠልጠኛ ጣቢያዎች አስገብቶ የተሃዲሶ ሥልጠና በመስጠት ላይ እያለ በተለያየ የወታደራዊ
ሞያ መስክ ዕውቀት አላቸው ያላቸውን እየመረጠ ወደ መከላከያ መልሷል፤ ተመርጠው ከተመለሱት ውስጥ አንዱ ሌ/ኮሎኔል ፋንታሁን ተምትሜ
ነበር። ማንኛውም የተመረጠ መኮንን ከእናንተ ጋር አልሰራም ብሎ እምቢ ለማለት የሚቻልበት ሁኔታ አልነበረም። ሌ/ኮሎኔል ፋንታሁንም
አእምሮው በሙሉ ፈቃደኝነት ተቀብሎት ነው የተመለሰው ብሎ ለማመን የሚከብድ ቢሆንም ከመሞት መሰንበት በሚል ሥራ ጀምሯል።በአስፈላጊነት
የተመለሱ መኮንኖች በነበራቸው ማዕረግ የሚጠሩ ቢሆንም ቅሉ ዩኒፎርም አይለብሱም፤ የኪስ ገንዘብ እንጂ ደሞዝ አይከፈላቸውም፤ ምንም
ዓይነት ወታደራዊ ጥቅማጥቅሞች አያገኙም ነበር። ቆይቶ መከላከያው ከተደራጀ በኋላ ይህ ሁኔታ አልቀጠለም።
ሌ/ኮሎኔል ፋንታሁን ከነበረው ወታደራዊ ዕውቀት
አኳያ የተመደበው በወቅቱ ለመከላከያ ከፍተኛ አመራር ሰጪ ለነበሩት
አቶ ስዬ አብርሃ፤ ጀኔራል ፃዲቃን ለመሳሰሉት አማካሪነት ነበር።
እነዚህ ባለሥልጣኖች ከጫካ መጥተው ሥልጣን ያዙ እንጂ ስለመከላከያ አሠራርና አደረጃጀትን ዕውቀት ስላልነበራቸው ሌ/ኮሎኔል ፋንታሁን
በአገር ወዳድነት የሚያቀርበውን ቀና ሃሳብ የሚቀበሉና የሚያቀርቡትም ነበር።
የካቲት 17 ቀን 1984 ዓ/ም ሌ/ኮሎኔል ፋንታሁን
ተምትሜ እንደማንኛውም ቀን ጧት ተነሥቶ ወደ ሥራው ይሔዳል። ባለቤቱ ወይዘሮ ዘውዲቱ ይርጉ ወደ ሥራዋ ጧት ስትሄድ ልጃቸውን ሕይወት
ፋንታሁንን ማጂክ ካርፔት አድርሳ ትሄዳለች። ከሰዓት በኋላ ሌ/ኮሎኔል ፋንታሁን ወደ ቤት ይዞ ይመለሳል። ከላይ በተጠቀሰው ቀን
ሌ/ኮ ፋንታሁን በምሳ ሰዓት አካባቢ ለባለቤቱ ስልክ ደውሎ ልጃችንን አንቺ ከትምህርት ቤት ውሰጃት እኔ አይመቸኝም ብሎ ሌላ ምንም
ሳይናገር ስልኩን ዘጋ። ስልክ የደወለውም በአፋኞቹ እጅ ሆኖ እንደነበረ ይታሰባል።
ሌ/ኮሎኔል ማታ ቤት አልመጣም፤ ቢሮውም እንዳልገባ
ተረጋገጠ። ማግሥቱን በቤተሰቡና በጓደኞቹ እንዲሁም በመሥሪያ ቤቱ የተደረገው ፍለጋ ሁሉ ፍሬ አላፈራም። ሌ/ኮ ፋንታሁን የደረሰበትን
ማወቅ አልተቻለም፤ ቀኑ በዚሁ አልፎ በሦስተኛው ቀን ጧት ከመከላከያ ለቤተሰቡ ስልክ ተደውሎ ሕንድ ኤምባሲ ፊት ለፊት መንገድ ላይ
በጆንያ ተጠቅሎ የተጣለ አስከሬን ምኒልክ ሆስፒታል ስለተወሰደ ሄዳችሁ አጣሩ የሚል መልዕክት መጣ፤ ጓደኞቹ ሄደው እሱ መሆንና በገመድ
ታንቆ እንደተገደለ አንገቱ ላይ ካለው ምልክት አረጋገጡ። የሌ/ኮ ፋንታሁን መጥፋት በመከላከያና በደህንነቱ ባለሥልጣናት ትኩረት
ተሰጥቶት ስለነበር ድርጊቱን ማን እንደፈጸመው ለቤተሰብ እንቆቅልሽ ነበር፡፡
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ