የሚድያ መሪ ፍሰሀ ይታገሱ
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ለሚድያ እድገት አስተዋጽኦ ያደረጉ ባለውለታዎችን እያፈላለገ የህይወት ታሪካቸውን ሲሰንድ እንደነበር ይታወቃል፡፡ የአንድን የሚድያ ሰው ታሪክ መሰነድ የሀገር ታሪክ ጠብቆ እንደማቆየት ነውና ይህን ስራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡
ለአንድ ሚድያ በእግሩ መቆም ከላይ እስከ ታች ያለው አመራር እና ባለሙያ ሚና ይኖረዋል፡፡ ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን ባለፈው ሀምሌ 30 2014 የ180 በሚድያ ውስጥ አሻራ ያኖሩ ሰዎችን ታሪክ መዝገበ-አእምሮ በሚል ርእስ አሳትሞ ማስመረቁ ይታወቃል፡፡
አሁን በቅጽ 2 ‹‹የስነጽሁፍ እና የሚድያ አሻራ ያኖሩ›› በሚል የጎላ አሻራ ያስመዘገቡ ሰዎችን እናያለን፡፡ በሚድያው ዘርፍ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ አምጥተው በብዙዎች እየተመሰገኑ ያሉት የኢቢሲ ስራ አስፈጻሚ አቶ ፍሰሀ ይታገሱ ትጋትን በተግባር ያሳዩ ናቸው፡፡
ትንሽ የሰራ አይዞህ መባል አለበት ጅምሩን አይቶ በክፍተቱ መቆም ግድ ነው በሚለው የመዝገበ አእምሮ የቦርድ አባላት እምነት የአቶ ፍሰሀ ይታገሱን አበርክቶ ለትውልዱ ልናስቀምጠው ወደናል፡፡
ሊነገር የሚችል የጎላ አሻራ ያላቸው የሚድያ መሪዎችን እያመጣን ምስጋናችንን እንገልጽላቸዋለን፡፡ እስካሁን 16 የኢትዮጵያ የሚድያ መሪዎች ፈቃደኛ ሆነው ታሪካቸውን ለመስጠት እሺታቸውን የገለጹ ሲሆን ከእነዚህም አንዱ የኢቢሲ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ፍሰሀ ይታገሱ ነው፡፡ አቶ ፍሰሀ ይታገሱ በአሁኑ ሰአት የ36 አመት ወጣት ባለትዳር እንዲሁም የ2 ልጆች አባት ነው፡፡
አቶ ፍሰሀ ይታገሱ ፈቃደኛ ሆኖ የስራ ታሪኩን ስላካፈለን ምስጋናችን የላቀ ነው፡፡ እዝራ እጅጉ በርካታ ሰዎችን በማነጋገር የአቶ ፍሰሀን ታሪክ እነሆ ብሏል፡፡
ውልደት እና ትምህርት
የኢቢሲ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ፍሰሀ ይታገሱ ባለፈው ሀምሌ 3 2015 36ኛ አመቱን የደፈነ ወጣት የስራ መሪ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በቀለም ማሳየት የጀመረ ሰሞን በ1979 የተወለደው ወጣቱ የስራ መሪ አቶ ፍስሀ ይታገሱ ኢቲቪ 57ኛ አመቱን ባከበረበት በጥቅምት ወር 2014 የስራ መሪነቱን ተቀላቀለ፡፡
ትውልዱ አርሲ ነጌሌ ሲሆን የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በዚያው በአርሲ የተከታተለ ሲሆን 12ኛ ክፍልን ደግሞ በደብረብርሀን ሀይለማርያም ማሞ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት አጠናቅቋል፡፡ አቶ ፍስሀ በልጅነቱ ከፍተኛ ፍቅር የነበረው ሲሆን በውጤቱም ጥሩ ከሚያስመዘግቡት አንዱ ነበር፡፡
2 ድግሪ 2 ማስተርስ እና አንድ ፒኤችዲ
በ1998 ወደ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በመዝለቅ በሳይኮሎጂ የመጀመሪያ ዲግሪውን ያገኘ ሲሆን ለእውቀት ባለው ከፍተኛ ጥማትም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ ተጨማሪ ዲግሪውን ለማግኘት ችሏል፡፡ በመማር የሚያምነው በየጊዜው ራስን በእውቀት ማሻሻል መሰረታዊ እንደሆነ የሚያምነው አቶ ፍሰሀ ይታገሱ ሶሻል በሳይኮሎጂ ሳይኮሎጂ የማስተርስ ዲግሪውን፤ በልማት ኢኮኖሚክስ ደግሞ ሌላ የማስተርስ ዲግሪውን ለመያዝ የቻለ ነው፡፡በአሁን ሰአት ደግሞ የፒኤች ዲ በእንግሊዝ ከትምህርቱን በመከታተል ላይ ሲሆን መስከረም 2016 ላይ ፒኤችዲውን ይይዛል፡፡
አቶ ፍስሀ በኢንሳ
አቶ ፍስሀ ይታገሱ 22 አመቱን ባከበረ ማግስት የጎንደር ዪኒቨርሲቲ ትምህርቱን ሲያጠናቅቅ የመጀመሪያ መስሪያ ቤቱ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲን በ2002 መስከረም ተቀላቀለ፡፡ በኢንሳም የመረጃ አናሊስት ወይም የትንተና ባለሙያ ሆኖ ይሰራ ነበር፡፡በስራው ታታሪ እና ፈጣን ስለነበርም ብዙ ነገር ለመማር የቻለበት የስራ ቤቱ ነበር፡፡ አቶ ፍስሀ ዛሬ ስለ ስራ ስኬቱ ሲያስረዳ ኢንሳ ትልቅ መሰረት ያስቀመጠለት ቤት መሆኑን ያምናል፡፡ ባለሙያ ሆኖ የገባው ወጣቱ ፍስሀ ኢንሳ በነበረው ቆይታ ጥሩ የስራ አፈጻጸም ስለነበረው ቡድን መሪ ለመሆን ጊዜ አልፈጀበትም፡፡ በጊዜው በኢንሳ አለቃው የነበሩት የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ሲሆኑ በጊዜውም ለስራ ያሳይ የነበረውን ትጋት በቅርበት ይከታተሉ ነበር፡፡
በሳይንስና ቴክኖሎጂ መረጃ ማእከል
ከ2002 እስከ 2006 የካቲት ወር ድረስ በኢንሳ ያገለገለው አቶ ፍስሀ በ2006 አ.ም የሳይንስና ቴክኖሎጂ የመረጃ ማዕከል ተቀላቅሎ በዋና ዳይሬክተርነት ለመምራት ችሎ ነበር፡፡ በዚህ መስሪያ ቤት ባገለገለበት ጊዜ አብረውት የሰሩት እንደሚመሰክሩት አቶ ፍስሀ ተግቶ የሚያሰራ የስራ መሪ ነው፡፡ አቶ ፍስሀ በጊዜው ይመራ የነበረው የሳይንስና ቴክኖሎጂ የመረጃ ማእከል በሳይንስና ቴክኖሎጂ ጉዳይ ላይ ሰፊ ትንታኔ የሚሰጥ ማእከል ሲሆን ለፖሊሲ አውጪዎችና ለመንግስት የትንታኔውን ውጤት የሚያቀርብ ተቋም ነበር፡፡
አዳዲስ እውቀቶችን ለመገብየት ፈጣን የሆነው አቶ ፍስሀ የሳይኮሎጂና እና የኢኮኖሚክስ እውቀቱን መሰረት በማድረግ በዚህ ማእከል በብቃት ለማገልገል ሞክሯል፡፡ ቀደም ብሎ ስራ አንድ ብሎ ከጀመረበት የኢንሳ ተቋም የቴክኖሎጂ እውቀቶችን የቃረመ ሲሆን ይህም ማእከሉን እንዲመራ ያስቻለው ነበር፡፡ በዚህ ማእከል ውስጥ የኢኖቬሽን ፖሊሲዎች እንዲወጡ ፤ ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ጋር በተያያዘ የተሰሩ ጥናቶች የሚዳሰሱ ሲሆን የማእከሉ አባላትም በትጋት ሲያገለግሉ የነበሩ ናቸው፡፡ ከ2006 እስከ 2010 ድረስ በማእከሉ ውስጥ ያገለገለው አቶ ፍስሀ እንደ አንድ የስራ መሪ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ጉዳይ ትልቅ ምርምር እንዲሰራ የተቻለውን ጥረት አድርጓል፡፡
አቶ ፍስሀ ከ2002-2010 ለ 8 አመት በኢንሳ እና በመረጃ ማእከል ውስጥ ሲያገለግል ከቆየ በኋላ ከ 2010 ለውጥ በኋላ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በሚኒስትር ዴኤታ ማእረግ የፖለቲካ እና ወቅታዊ ጉዳዮች ሃላፊ በመሆን ማገልገል ጀመረ፡፡ በጽ/ቤቱም ውስጥ ለ 3 አመት ከ 6ወር ሀገራዊ ሃላፊነቱን የተወጣ ሰው ነው፡፡ አቶ ፍስሀ ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ ከትንሽ ተነስቶ እድገት ያሳየ የስራ መሪ ሲሆን ባልደረቦቹም ይህን ትጋቱን በሙሉ አንደበታቸው የሚመሰክሩ ናቸው፡፡
አቶ ወንድወሰን አንዱአለም ስለ አቶ ፍስሀ ይታገሱ
አቶ ወንድወሰን አንዱአለም በአሁኑ ሰአት የአርቲፊሻል ኢንተለጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሲሆን ስለ ኢቢሲ ዋና ስራ አስፈጻሚ የሰጠውን ምስክርነት እነሆ ብለናል፡፡
በስራ ላይ በቆየሁባቸው ለሀያ ጥቂት ፈሪ ለሆኑ አመታት ከበርካታ ሰዎች ጋር የመስራት ዕድል አግኝቻለው፤ ከፍሰሐ ይታገሱ ጋር በስራ የተገናኘሁበት አጋጣሚ ግን በህይወቴ ማርሽ ቀያሪዋ ወይም ለአዲስ ትግል ለአዲስ ሁነት ራሴን ያዘጋጀሁበት ቅጽበት ናት ብዬ ወስዳታለሁ፡፡
ከፍሰሐ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተዋወቀኝ ወዳጄና ጓደኛዬ መሐመድ ሐሰን ነው፤ የሳይንስና ቴክኖሎጂ መረጃ ማዕከል ውስጥ ከአሁኑ ጠቅላይ ሚንስተር ዶ/ር አብይ አህመድ ጋር በጋራ የመስራት ዕድል አግኝቶ ስለነበር ፍሰሃ ጋር ወሰደኝ፤ከፍሰሐ ጋር አብሬ የመስራት ዕድል ያገኘሁበት አጋጣሚ ከአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስተራችን ከቀድሞ የሳይንስና ቴክኖሎጂ የመረጃ ማዕክል ዳይሬክተር አቶ አብይ አህመድ ጋር የምሰራበትን እድል ፈጠረልኝ፡፡
ፍሰሐ ወንድም ፣ጓደኛ እና አለቃ መሆንን እኩል የሚችልበት ወንድምነቱ አለቃነቱን፤አለቃነቱ ጓደኝነቱን የማያዛናፍበትና የማይሸራርፍበት ብርቱ ሰው ነው፡፡ከፍሰሐ ጋር በቀድሞ ሳይንስና ቴክኖሎጂ የመረጃ ማዕከል በኋላም ‹‹ቴክኢን›› በተባለው ተቋም ውስጥ ቀጥሎም በጠቅላይ ሚንስትር ፅ/ቤት አብሮ የመስራት ዕድሉን እና አጋጣሚውን አግኝቻለሁ፤ነገሮችን ሳያወሳስቡ ግን ደሞ በጥንቃቄና በዲሲፒሊን እንዴት አድርጎ መምራት እንደሚቻል ለማየት ፍሰሐን ቀድሞ የሚጠራ አለ ብዬ አላስብም፤በጣም ቀላል ሰው ነው፡፡ ቀለል ማለት እንዴት ውበት እንደሆን ቀለል በማለት ውስጥ እንዴት መከበር፣መስራት፣ማሰራት እና ማክበርም ጭምር እንደሚቻል ፍሰሐ ይታገሱ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡
ያሰበውን ነገር ካላሳካ እንቅልፍ የማይወስደው፣ራሱ በትጋት ሰርቶ ሌሎች ሰራተኞችን በሙሉ በትጋት ከኋላው ማሰለፍ የሚችል፣ከሰራተኞቹ ጋር እፍኝ ሽምብራ እየቆረጠመ የእግር ጉዞ የሚያደርግ፣አብሮ ስፖርት የሚሰራ ፣አብሮ ምሳ የሚበላ ፣አብሮ ቡና ሚጠጣ በስራ ገበታው ላይ ሲገኝ ደግሞ ጎበዝ ብርቱ አለቃ ተናግሮ የሚደመጥ፣የሰጠውን አሳይመንት በሰጠው የግዜ ገደብ ውስጥ የሚሰራለት ብርቱ ሰው ነው ፍሰሐ ይታገሱ፡፡
እውቀት፣ደግነት፣ታማኝነት እና የመልካም ስብዕና ባለቤትነት አንድ ላይ የተቸሩት ዕድለኛ ሰው ነው፡፡አብሬያቸው በመስራቴ እጅግ በጣም ከምኮራባቸው እና ብዙ ትምህርት ከቀሰምኩባቸው በህይወቴ ውስጥ ወሳኝ የምላትን ነጥብ ካገኘሁባቸው ሰዎች ከጥቂቶቹ አንዱ ፍሰሐ ይታገሱ ነው፡፡
በሳይንስና ቴክኖሎጂ መረጃ ማዕክል ወስጥ አቶ ፍሰሐ ይታገሱ የመረጃ ማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ሆነው እኔ በዕውቀት አስተዳደር እና ስርጭት ዳይሬክቶሬት ስር እሰራ በነበረበት ግዜ ቴክ-ሳይንስ የሚል ሳይንስና ቴክኖሎጂ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ፕሮግራም ለበርካታ አመታት በእርሳቸው አስተዳደር ስር ስናዘጋጅ ቆይተናል፡፡ ቴክ-ሳይንስ የተሰኘው ይህ ፕሮግራም ሳይንስን ከሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር ለማህበረሰባችን ዕውቀት እና መረዳት ቅርብ በሆነ መልኩ በማቅረብ ትታወቅ እንደነበር ትዝ ይለኛል፤ሀገራዊ ዕውቀቶችን እና ሌሎች ሳይንሳዊ ዕውቀቶችን ለተደራሲያን ወይም ለአድማጭ ተመልካች ሊገባ በሚችል መልኩ ማቅረብ እንዳለብን እና በዛም ረገድ የተለያዩ ስልጠናዎችን እንድናገኝ በማድረግ የአቶ ፍሰሐ ይታገሱ የአስተዳደር ብቃት እና አዳዲስ ነገሮችን የማምጣት ትጋት ቴክ-ሳይንስን በጥሩ ቁመና ላይ ሆና ለበርካታ አመታት ተደማጭ እና ብዙ ተመልካች ያላት የቴሌቪዠን ፕሮግራም እንድትሆን ረድቶን ነበረ፡፡
ከዚህም ባሻገር እስካሁን ድረስ በበርካታ መንግስታዊ ተቋማት ባልተለመደ መልኩ ደረጃቸው ከፍ ያሉ ጆርናል መሰል ጆርናል አከል የሆኑ በጥናትና ላይ የተመሰረቱ ፅሁፎችን የያዙ መጽሔቶችን እናዘጋጅ እንደነበር ትዝ ይለኛል፤ቴክ-ሳይንስ የሚል በየሶስት ወሩ የሚታተም መጽሔት በአቶ ፍሰሐ ይታገሱ የቅርብ ክትትል፣ድጋፍ እና በአዳዲስ ሀሳቦች አመንጪነት ደረጃውን በጠበቀና ከፍ ባለ መልኩ እየታተመ እስከ ቅርብ ግዜ ድረስ ቆይተዋል፤በርካታ መንግስታዊ ተቋማትም የቴክ-ሳይንስ መጽሔትን ልምድ እና ተሞክሮ የይዘት የጥራት እና የተነባቢነት ልክ መሰረት በማድረግ ለመስራት ይጥሩ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡
በቅርብ የተመረቀውን የኢቢሲን የሚዲያ ኮምፕሌክስ ከምንም ጀምረው በአንድ አመት ከስድሰት ወር ጊዜ ውስጥ ለውጤት ሲያበቁት እጅግ የሚገርም የሚደንቅ ቢሆንም ነገር ግን እኔ እና አቶ ፍሰሐ ይታገሱን በቅርብ የምንውቃቸው ወዳጆቼ ብዙም የምንገረምበት ጉዳይ አልሆነብንም፡፡ ምክንያቱም የሳይንስና ቴክኖሎጂ ማዕከል፣የጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት እና ሌሎችም ተቋማት በአዲስ አሰራር በሚያምር የስራ ከባቢ ፈጠራ ወደሌላ ምዕራፍ ሲገለጡ የአቶ ፍሰሐ ይታገሱ አስተዋጽዎ እጅግ ከፍ ያለ እንደነበረ ስለምናውቅ ነው፡፡
አቶ ፍሰሐ ይታገሱ ከሄዱት መንገድ ይልቅ ገና የሚሄዱት መንገድ እንደሚልቅ እንደሚረቅ እረዳለው፤ በዚህች ሀገር ታሪክ ውስጥም ለወደፊቱ ደማቅ አሻራቸውን እንደሚያኖሩ ብዙ ስራዎችንም እንደሚሰሩ ተስፋ አደርጋለው፤እናም ጓዋደኛ፣ አለቃ፣ ባልደረባና ወንድም መሆን ለሚችሉት ብርቱ ሰው መልካም ምኞቴን እገልጻለሁ!!
ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ስለ አቶ ፍስሀ ይታገሱ
የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ የማህበራዊ ጉዳይ አማካሪ ዲያቆን ዳንኤል ክብረትም ስለ ኢቢሲው የስራ መሪ ይህን ብለዋል፡፡
ፍሥሐ ይታገሡ
በማወቄ ከምደሰትባቸው ሰዎች አንዱ። ነገር ማቅለልና የሥራ እልክ የታደለ። የኢቢሲ አራተኛው ምዕራፍ የአንተ ዐሻራ ነው። አዲሱ የኢቢሲ ሕንጻ ያለበት ግቢ መጀመሪያ ስንሄድ የነበረው መልክና ዛሬ ያለው መልክ፤ ፍሥሐን ያገኘ ቦታ እንዴት እንደሚለወጥ ማሳያ ነው።
መለመን፣ ማሠራት፣ ማግባባት፣ የረጋውን ውኃ መረበሽ፣ ፍሥሐ ዘንድ ያሉ ጸጋዎች ናቸው። ፍሥሐ ይታገሡ - ደስታና ትዕግሥት አብረው መኖር ነው ያለባቸው።
አቶ ፍስሀ በኢቢሲ
አቶ ፍስሀ ይታገሱ ከ 27 ዓመቱ ጀምሮ ባሉት 9 ዓመታት በስራ መሪነት አቅሙን ያሳየ ሲሆን ከላይ ምስክርነት የሰጡት አቶ ወንድወሰን እንደመሰከሩት በመሪነት ትልቅ ተጽእኖ መፍጠር የቻሉ ነበሩ፡፡ አጠቃላይ ከኢቢሲ በፊት በነበረው ቆይታው 200 ሰዎችን በስሩ የመራ ፤ በጀት ማስተዳደርንን ጨምሮ በርካታ የተቋማት ግንባታ ስራዎች ላይ የድርሻውን የተወጣ ነበር፡፡ በመሆኑም በጥቅምት 2014አ.ም ወደ ኢቢሲ በዋና ስራ አስፈጻሚነት ሲመጣ የተጣለበትን ትልቅ አደራ እንደሚወጣ ጥርጥር አልነበረውም፡፡
አቶ ፍሰሀ ይታገሱ ወደ ኢቢሲ ሲመጣ እንዴት መለወጥ ይቻላል ? በሚለው ላይ ቆም ብሎ አስቦበት ነበር፡፡ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ማእከል ሳለ 150 ሰዎችን መርቷል፡፡ ይህ ማእከል 50 ሚሊዮን ነበር በጀቱ፡፡ ኢቢሲ ደግሞ ወደ 2300 ሰራተኛ እና ወደ 1ቢሊዮን በጀት ያለው ነው፡፡ ታዲያ ይህን መስሪያ ቤት ለመምራት አቶ ፍሰሀ ሲሾም ብዙ ጉዳዮችን አገናዝቦ ነበር፡፡ ከዚህ ቀደም ከኢቢሲ አመራሮች ቤቱን ለመለወጥ በርካታ ጅምሮች እንደነበሩ አቶ ፍስሀ ያውቃል፡፡ ኢቢሲ በጣም ብዙ የሰው ሀይል ያለበትና ወጣ ገባ በሆነ ለውጥ ውስጥ ያለፈ እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ፡፡
አቶ ፍሰሀ ይታገሱም ወደ ኢቢሲ ሲመጣ ነገሮችን በጥንቃቄ መያዝ እንዳለበት ተገንዝቦ ነበር፡፡ ከዚህ ቀደም ስለ ኢቢሲ ሲባሉ የነበሩ አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ነገሮችን መስማቱም አልቀረም፡፡ አንድን ተቋም ለመምራት ቀደም ብሎ የተቋሙን ዳራ ወይም የቀደመ ታሪክ ማወቅ ግድ ስለሚል አቶ ፍስሀ በዚህ መንፈስ ሆኖ ኢቢሲን ለማጥናት ሞክሮ ነበር፡፡
በጊዜው አቶ ፍስሀ ኢቢሲ በመጣበት ጊዜ ጣቢያው ከውድድር ወጥቶ ነበር፡፡ በርካታ ጣቢያዎች ከመከፈታቸው ጋር ተያይዞ የእውነትም ሬድዮም ሆነ ቲቪ አንዳች ለውጥ ያስፈልጋቸው ነበር፡፡
ኢቢሲ ውስጥ ያለው ችግር ውስብስብ መሆኑን አቶ ፍስሀ ቢረዳም ለምንድነው ከዚህ ቀደም የነበሩት ለውጦች ያልተሳኩት ብሎ ጠይቆ ነበር፡፡ የስትራቴጂክ ነው? የመንግስት ድጋፍ ማነስ ነው? የባለሙያ ማጠር ነው? ለውጥን ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆን ነው? እነዚህን ሁሉ አቶ ፍሰሀ ጠይቋል፡፡ የተጠቀሱትን ጥያቄዎች ሁሉ በሚመልስ መልኩ አንድ ፍኖተ-ካርታ መዘጋጀቱን አቶ ፍስሀ ያስረዳል፡፡ ይህን ፍኖተ-ካርታ በመያዝ አመራሩ አንድ ላይ ሆኖ ህብረት በመፍጠር ኢቢሲ አሁን ያመጣውን ለውጥ ማምጣት መቻሉን አቶ ፍሰሀ ይናገራል፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩም የኢቲቪን ፕሮጀክት
በቅርበት እንደሚከታተሉ አቶ ፍስሀ ያስረዳል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቋም እንዲገነባ ትልቅ ፍላጎት ያላቸው መሆኑን እና ይህም ለአሁኑ ስኬት እንደረዳም ያምንበታል፡፡
ኢቢሲ በ1አመት ከ6 ወር ይህን ትልቅ የሚድያ ኮምፕሌክስ ገንብቶ ማስመረቁ ብዙዎችን ያስገረመ ነበር፡፡ ይህ አስደናቂ ስኬት ሊመጣ የቻለው በተከተልነው የአመራር ፍልስፍና ነው ሲል አቶ ፍስሀ ይናገራል፡፡ ከሰራተኛ ጋር መተማመን መፈጠሩ አንዱ ለስኬት መምጣት አስተዋጽኦ ያደረገ ጉዳይ እንደነበር አቶ ፍስሀን ጨምሮ ሌሎች ባለሙያዎችም የሚመሰክሩት ሀቅ ነው፡፡
አቶ ፍስሀ ከጥር 2014 እስከ ሰኔ 28 2015 ባለት 18 ወራት ውስጥ የሚድያ ኮምፕሌክሱን ግንባታ በልህቀት ለመጨረስ ብዙ ጥረት ማድረጉን ይገልጻል፡፡ ‹‹ …. 10 ሰአት ኢዲቶሪያል መርቼ ከዚያ ደግሞ ስበር መጣና ሸጎሌ ደርሳለሁ፡፡ ሸጎሌ ደግሞ ከ10 ሰአት እስከ 2 ሰአት እቆያለሁ፡፡ ግንባታውን አያለሁ፡፡ እከታተላለሁ፡፡ ቤት 4 ሰአት ስገባ ደክሞኝ ነው የምተኛው፡፡1 አመት ከ 6 ወር ለቤተሰብ አንዳችም ጊዜ አልነበረኝም›› በማለት የሚድያ ኮምፕሌክሱን ግንባታ ከዳር ለማድረስ የተሄደበትን ርቀት ይነግረናል፡፡
በተለይ ይህ ስራ እንዲሁ የህንጻ ግንባታ ብቻ ሳይሆን የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ድጋፍና እውቀት ይጠይቅ ስለነበር የኢቢሲ የቴክኖሎጂ ሰዎችም ያደረጉትን ርብርብ አቶ ፍሰሀ በበጎ ጎኑ ያነሱታል፡፡ ባለሙያዎቹ እስከ 3 እያመሹ እሁድ ቅዳሜ እየገቡ መስራታቸው ለስኬት አብቅቷቸዋል፡፡ እነዚህ የኢቢሲ ባለሙዎች ያለምንም ተጨማሪ ክፍያ ይህን ታሪካዊ አደራ ተወጥተዋል፡፡
አቶ ፍስሀ በዚህ አጋጣሚም ለባለሙያዎቹ ምስጋናቸውን ማቅረብ ይወዳሉ፡፡
አቶ ፍሰሀ እንደሚናገረው እርሱ ኢቢሲን መምራት ከጀመረ በኋላ በርካታ የአሰራር መንገዶች ተቀይረዋል፡፡ የመዋቅር ለውጥ ፡ የአሰራር ማሻሻያዎች ተደርገዋል፡፡ ወደ 250 አመራሮችን ደግሞ እንደ አዲስ መመደባቸውንም አቶ ፍስሀ ነግሮናል፡፡ ሌላው ኢቢሲ ካደረጋቸው ለውጦች አንዱ የደሞዝ ማሻሻያ ሲሆን ይህም የኢቢሲን ሰራተኛ ሊያነቃቃ እንደሚችል የታመነበት ነበር፡፡ ሌላው የቴሌቪዥን ባለንብረት ክፍያም ከኤሌክትሪክ ክፍያ ጋር አብሮ እንዲከፈል መደረጉን አቶ ፍስሀ ይናገራል፡፡
የሸጎሌ ፕሮጀክት የኢቢሲ የለውጥ ማእከል ነው፡፡ ኢቢሲ በአንድ በኩል ምቹ የስራ ቦታን ለመፍጠር ያደረገውን ጥረት አጠናክሮ ደግሞ በስልጠና ባለሙያዎችን ብቁ ለማድረግ የስልጠና አካዳሚ በመጀመር ስራን በእውቀት እንዲታገዝ ለማድረግ የተቻለውን ያህል አድርጓል፡፡ሁሉም ሰራተኛ በተደጋጋሚ ሰልጥኗል፡፡ አቶ ፍሰሀ እንደሚናገረው ሰራተኛው በሁሉም የመስሪያ ቤቱ የለውጥ ሂደት ላይ ተሳታፊ ሲሆን ለውጡን የሚፈታተን መሆኑ ቀርቶ ተባባሪ እንዲሆን አስችሎታል፡፡ ይህም የእኔነት ስሜትን መፍጠር የቻለ ነበር፡፡
ከምረቃ በኋላ ……
አቶ ፍሰሀ ይታገሱ እንደሚናገረው ኢቢሲ ለውጥን ማጽናት ላይ ሁሌም ይተቻል፡፡ በ2010 በኢቢሲ የመጣው የይዘት ለውጥ እንደነበረ አልቀጠለም፡፡ ወደ ኋላ ይመለሳል፡፡ ይህ አንዱ ፈተና ነው፡፡ ኢቢሲ አዲሱን የሚድያ ኮምፕሌክስ በይፋ ካስመረቀ በኋላ ትልቁ ሀላፊነት ለውጡን የማጽናት ስራ ነው፡፡ አቶ ፍስሀ ይህን ለውጥ ለማስቀጠል የሚያቆመን ያህል አይኖርም ሲል በሰራተኛው ላይ ያለውን መተማመን ይገልጻል፡፡ በቀዳሚነት አቶ ፍሰሀ ሰራተኛውን ለማነጋገር ይሞክር ነበር፡፡ ታዲያ ሰራተኛውን ሲያነጋግር የተባለውን ሁሉ አይወስድም-በተቻለ መጠን ለማብላላት ይሞክራል፡፡ ብዙዎች እንደሚናገሩት አቶ ፍሰሀ ምክር ለመስማት የፈጠነ ነው፡፡ ከሁሉም መማር እንደሚቻል ያስባል፡፡ ከዚህ አንጻር ኢቢሲ ውስጥ ብዙ አቅም ያላቸው ቀና ሰዎች መኖራቸውን ዋና ስራ አስፈጻሚው አቶ ፍሰሀ ይናገራል፡፡ ነገር ግን እነዚህ ቀና እና ችሎታ ያላቸውን ልጆች ስናሳትፋቸው ስላልነበርን አቅማቸውን ሳንጠቀም እንቀራለን፡፡
አቶ ፍስሀ ነገሮችን በፍጥነት መከወን ይቀናዋል፡፡ ስብሰባ ሲመራም ሆነ ሀሳብ ሲያፈልቅ ነገሮችን በአጭሩና ወደ ጉዳዩ በቶሎ በመግባት ያምናል፡፡ ይህ አይነቱ የአመራር ፍልስፍና የሸጎሌው የሚድያ ኮምፕሌክስ በ18 ወራት እንዲጠናቀቅ አስችሎታል፡፡
ሀቢባ ፋሪስ ስለ አቶፍሰሀ
በእርግጥም እንደ ብሔራዊ ሚዲያ ሀገር ሊኖራት የሚገባውን ተቋም በመገንባት አሻራውን ያኖረ ወጣት ቅን መሪ ነዉ "።ከሱ ጋር በመስራቴ ብዙ ያተረፍኩ እያንዳንዱ ቀኔ ትምህርት ቤት ነገሮችን በይቻላል መንፈስ እንድስራ ዕድል ስጥቶኛል ።
ለሃሳቦች ሁሉ ዋጋ መስጠት መተግበር እንዲተገብሩ ዕድል መስጠት የሱ ናቸው።የnegative energy ንግግሮች ጠል ነው።ለወጣት ቅን መሪ ምን ይባላል ?አላህ ያሰብከውን ያሳካልህ ትልቅ ደረጃ ደርሰህ ማየት ህልሜ ነው።
ሀቢባ ፋሪስ የአቢሲ ምክትል ስራ አስፈፃሚ
አቶ ፍስሀ በመሰለ ገብረህይወት አንደበት
የሚድያ ሰው መሰለ ገብረህይወት በጋዜጠኝነት ስራ ከ 20 በላይ የዘለቀ እና በአሁኑ ሰአት ደግሞ በኢቲቪ በዋና የዜና አንከርነት እና አማካሪ በመሆንም እያገለገለ ይገኛል፡፡
ሰርቶ አይደክመውም :-
ፍስሐ የተሠጠውን ኃላፊነት ለመወጣት ቀን ከሌት የሚጥር ነው። ሰርቶ ቢውልና ቢያድር አይደክመውም። የእረፍት ቀን የሚባል በሱ ስሌት አይታወቅም ። ለዚህ ነው በአንድ አመት ከ6 ወር ትልቅ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ማስመረቅ የቻለው።
ሐሣብ ያከብራል :-
ሚዲያ በሀሣብ እንደሚመራ የዘርፉ ሰው ሳይሆን ጠንቅቆ የተረዳ ነው። የሚመጡ ሐሣቦችን አይንቅም ። እንደቅደምተከተላቸው ይጠቀምባቸዋል ። አብሮ ለመሥራት ሃሣብ ይዘው ወደሚዲያችን የሚመጡ ባለሙያዎች በሚገባ አስተናግዶ እንዲሠሩ እያደረገ ነው። ለምሣሌ የመዝናኛው ቻናል እያስነሳ ያለው የለውጥ አብዮት ማሣያ ነው። በዜናው ዘርፍ አዳዲስ የአቀራረብ ለውጦች የመጡት በሱ ሃሣብን የመቀበል ችሎታ ነው።
ቅን ነው:-
ነገሮችን ሁሉ የሚያያቸው በቅንነትና በበጎነት ነው። አዎንታዊ አመለካከት በውስጡ ሰርጿል። ስራዎች የሚሳኩት በአዎንታዊ ሃይል (postive energy)ነው ብሎያምናል።
ኃላፊነት ከነሙሉ ክብሩ ይሰጣል:-
ለሠራተኛው የሚሠጠውን የቤት ስራ ከነኃላፊነቱ ነው። የቤት ስራው የተሠጠው ሃላፊ ወይም ባለሙያ ስራውን በሃላፊነትና በራስ መተማመን ሰርቶ ጨርሶ እንዲያመጣለት ነው የሚፈልገው። ይኸ ደግሞ ስራውን ደስ እያለህ እንድትሠራ ያደርግሃል ።
ውጤት ይፈልጋል :-
በወሬ አያምንም። አሉባልታ ጠል ነው። እንዲህ ይሠራ ብሎ ሳይሰራ ዞሮ የሚልም አይወድም ። ሰርቶ ውጤት የሚያሣየው ሰው ለሱ የልብ ወዳጁ ነው።
ፍስሐ ይታገሱ በዘካርያስ ብርሃኑ አንደበት
ዘካርያስ ብርሀኑ በኢቢሲ የስፖርትና መዝናኛ ቻናል ማኔጂንግ ኤዲተር ሲሆን ስለ አቶ ፍሰሀ የሰጠው ምስክርነት እነሆ፦
ፍስሐ የኢትዮጵያ የሚዲያ ወርቃማ ታሪክን በደማቁ የጻፈ ሰው ነው።መወጠን፣መወሰን እና መተግበር ይችላል። ከኮንትራክተርም ከኮንቴንትም ጋር ሰርቶና አሰርቶ ተቋሙን ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገረ፣ለትውልድ የሚተርፍና በትውልድ የሚዘከር መሥሪያ ቦታና አሰራርን የቀረጸ ታላቅ የሚዲያ መሪ ነው።ተቋምን ከውስጥም ከላይም የሚቀይር መሪ በኢትዮጵያ ብዙም የተለመደ አይደለም።በዚህ ጉዳይ ከልቡ የሰራና በተግባር ያስመሰከረ መሪ ፍስሐ ይመስለኛል።ኢቢሲ ትልቅና ሰፊ ተቋም ነው።የሱ የሥራና የመሪነት መንፈስ ከዳር እስከዳር፣ከሥራ ክፍል እስከ ግለሰብ ሰራተኛ
ተጋብቷል።አድማጭ ተመልካችን ነቅንቋል። ይህ ትልቅ ጸጋ ነው።ከዕውቀትና ከትጋትም በላይ መሰጠትና መባረክንም ይጠይቃል።
ታማኝ እና አማኝ መሪ ነው።ያለውን ይፈጽማል፣ ለምትሰራው ሥራ ሙሉ ኃላፊነትና እምነት ይሰጣል። በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የተቋማት መሪዎች ሊቀስሙት የሚገባ፣እንዲሆኑት የሚያስመኝ የመሪነት ክህሎትን የተጎናጸፈ መሪ ነው ፍሰሐ።
አቶ ሃብቴ ገመዳ ስለ አቶ ፍሰሀ
አቶ ሀብቴ ገመዳ በኢቢሲ ለ 40 አመት በላይ ያገለገሉ የሚድያ ሰው ሲሆኑ ስለ አቶ ፍሰሀ ይታገሱ የሚከተለውን ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡
‹‹አቶ ፍሰሃ ይታገሱ ወደ ኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን ወደ ስልጣን ከመጡበት ጊዜያት ጀምሮ እኛን እና የተለያዩ በጡረታ ላይ የሚገኙትን ቀደምት የቀድሞ የመስሪያ ቤቱ ሰራተኞች እና ባለሙያዎችን አግኝተው ሰበሰቡ፡፡›› ሲሉ አቶ ሀብቴ ገመዳ ሀሳባቸውን መግለጽ ይጀምራሉ፡፡
አቶ ፍስሀ ብዙውን ነገር ለመማር እና ያቀዱትን ነገር በጋራ ለመስራት ሃሳብ እንዳላቸው ተናግረው ነበር፡፡
እንዲሁም ባለሙያዎቹ አቡነ ጴጥሮስ አካባቢ በተለምዶ ስቱዲዮ ሲ በሚባለው ቦታ ላይም የራሳቸውን መቋቋሚያ መገናኛ ቢሮ እንዲኖራቸው አስችለዋል፡፡
አቶ ሀብቴ ገመዳ እንደሚናገሩት በአዲሱ አመራር ላይ የሚታየው ለውጥ ለማምጣት የሚሄዱት እንቅስቃሴ እና ጅማሮ መልካም እና የሚደገፍ ነው።
‹‹አቶ ፍሰሃ ይታገሱ ወጣት ከመሆኑም ባሻገር የመንግስትን ፍላጎት እና የገበያውን ፍላጎት አስታርቆ የሄደ የሚድያ መሪ እና ታታሪ ጥሩ አመራር እንዲሁም ታላላቆችን የሚያከብር የተቆጣን ማስታገስ የሚችል መልካም እና ጠንካራ ሰው ነው። ›› ሲሉ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
አቶ ፍሰሀ በመቅደስ ጥላሁን አንደበት
አቶ ፍሰሀ ይታገሱ በአብዛኞቹ የኢቢሲ ሰራተኞች እንደሚጠሩት ፊሽ ወደ ተቋሙ ተመድቦ ሲመጣ ካደረጋቸው ነገሮች አንዱ በየዘርፉ እና በየክፍሉ ያሉ ባለሙያዎችን ስለ ተቋማቸው እና ስለክፍላቸው ያላቸውን አስተያየት መጠየቅ ነበር።
በእነዚህ የውይይት መድረኮች የሚነሱ ሀሳቦችን በአንድም በሌላም መንገድ እርሱ ቀድሞ ያውቃቸዋል። ተቋሙን ለመምራት ሀላፊነት ሲሰጠው የሚመራውን ተቋም በራሱ መንገድ በሚገባ አጥንቶ ነው የመጣው። እንደ ወጣት አመራር ከየትኛውም ሀላፊነት ላይ ካለ ሰው ከየትኛውም ባለሙያ ጋር በቀላሉ ይግባባል፡፡ ቀላል በሚመስሉ ጥያቄዎቹ ችግሮችን ይለያል ፡፡መፍትሄዎችን ከችግሮች ተነስቶ ያመጣል።
ይዘት ያውቃል። በሚዲያ ነፃነት ያምናል። ነገር ግን ሁሌም ነፃነትን በሀላፊነት እንዲሰራ አጥብቆ ይፈልጋል።
አነጋጋሪ ጉዳዮች ፤ ለሰዎች ህይወት የቀረቡ ሰዋዊ ይዘቶች እንዲሰሩ ይፈልጋል ።
ትልቅ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ገንብቷል ሚዲያ ኢንዱስትሪው ላይ ቢቆይ በእርግጠኝነት ትልቅ የይዘት ለውጥ ማምጣት ይችላል። ሁለተኛውን ትልቁን የቤት ስራ ይዘትን በበላይነት መርቶ ትልቅ ለውጥ ማምጣት እንደሚችል እተማመናለሁ።
መዝጊያ ፤ ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ የመዝገበ-አእምሮ ቦርድ አባላት አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡
የዛሬ ዜና የነገ ታሪክ ነው ይላሉ የታሪክ ሰናጆች፡፡ እውነት ነው፡፡ ዛሬም የምናፈልቃት ሀሳብም ነገ ታሪክ ላይ የምትከተብ የትውልድ አሻራ ትሆናለች፡፡ በኢትዮጵያ የሚድያ መሪነት ታሪክ ውስጥ ሁሉም በተቻለው መጠን ይመራል፡፡ ግን እንዴት መራ የሚለው የተቀመጠ ሰነድ የለም፡፡ በየት ዘመን የቱ ሚድያ ጥሩ አመራር ነበረው ተብሎ ቢጠና በመረጃ የታጨቀ ጥናት አይገኝም፡፡ የ100 አመት የሚድያ ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ ስንት ዋና አዘጋጅ ፤ ስንት መምሪያ ሃላፊ ፤ ስንት ስራ አስፈጻሚ ነበራት ተብሎ ቢጠየቅ መልሱ አዳጋች ብቻ ሳይሆን አይታወቅም፡፡ እነማን ነበሩ ተብሎ ስራዬ ተብሎ ካልተጠና ከቶ የማይቻል ነው፡፡ እና በዚህ ጽሁፍ የህይወት ታሪኩን ያየንለት ወጣቱ የኢቢሲ መሪ አቶ ፍሰሀ በሀገሪቱ የሚድያ መሪነት ታሪክ ውስጥ ገብቶ እናገኘዋለን፡፡ ይህ ወጣት የሚድያ መሪ ሰርቻለሁ ብሎ የሚኩራራ ሳይሆን ብዙ መስራት የሚችል ገና ልሩጥ ብሎ ራሱን ያሰናዳ እንደሆነ ያስታውቃል፡፡ በ18 ወር የሚድያ ኮምፕሌክስ አስገንብቶ ማስመረቅ ግን እድለኝነት ብቻ ሳይሆን ከታሪክ መዝገብ ላይ የሚያሰፍር ነው፡፡
ከኢቢሲ ሁላችንም ይዘት እንጠብቃለን፡፡
ይዘቱን የሚያመጣው ከባቢያዊ ሁኔታ ደግሞ ተፈጥሯል፡፡ አንድ ልጅ አንደኛ ደረጃ አጠናቅቆ ሁለተኛ ደረጃ ጨርሶም ይመረቃል፡፡ ሁሉን አወቀ ማለት አይደለም፡፡ ግን ለቀጣዩ እደግ ተመንደግ ተብሎ ይመረቃል፡፡ አሜን ይላል፡፡ ምርቃት ያዳብር ብሎ ያመሰግናል፡፡ ይመረቃል እንጂ ልጁ መቼ ድግሪ ያዘ አይባለም፡፡ ድግሪ ደግሞ ይቀራል አይባልም፡፡ አንዳንድ ጉዳዮች ጊዜ ይፈልጋሉ፡፡ አቶ ፍሰሀ ይታገሱ ከእነ ባልደረቦቻቸው ያመጡት አሁናዊ ለውጥ መደነቅ ፤ መወደስ መሰነድ አለበት ፡፡ ከዚያ ቀጣዩ ለውጥ ይመጣል፡፡ ያኔ ለይዘት ይታሰብበታል፡፡ እስከዚያ ግን በቃ እንመርቅ ፡፡ ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ለየትኛውም ሚድያ ሳይወግን የተሰሩና የሰሩ ባለሙያዎችን ወደፊት ያመጣል፡፡ ሰው ከታሪካቸው እንዲማርም ያደርጋል፡፡ የአቶ ፍሰሀ የስኬት ታሪክም ለአዲሱ ትውልድ የሚያስተምር ነው ብለን በማሰባችን ታሪኩን ከክብር መዝገባችን ላይ አስፍረነዋል፡፡ የሰራ ይሰነዳል፡፡
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ