ታምራት ገብረጊዮርጊስ





ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የሚድያ ባለሙያዎችን የህይወት እና የስራ ታሪክ እያሰባሰበ ይገኛል፡፡ በሚያዝያ 12 2013 አ.ም በተጀመረው በዚህ መርሀ-ግብር እስካሁን ከ250 በላይ የሚድያ ሰዎች ታሪካቸው ሊሰነድ ችሏል፡፡ መዝገበ-አእምሮ የሚለው የ180 የሚድያ ሰዎች ታሪክን ያካተተ መጽሀፍ ተጠቃሽ ነው፡፡ ተወዳጅ ሚድያ ራሱን የቻለ የመማክርት ቦርድ ያለው ሲሆን በቦርዱ የተመረጡ ፤የተቀመጠውን መስፈርት የሚያሟሉ ባለሙያዎች የህይወት ታሪካቸው ለአዲሱ ትውልድ እንዲቀመጥ ይደረጋል፡፡ አሁን በዚህ ጽሁፍ ታሪኩን የምናይለት ሰው ወደ ጋዜጠኝነት የገባው ገና በ21 አመቱ ሲሆን በህብር መጽሄት እና በጦማር ጋዜጣ ላይ ብእሩን አሳይቷል፡፡ ከዚያም ከ1985-1992 በተለያዩ የህትመት ውጤቶች ላይ ከሰራ በኋላ ዘንድሮ ግንቦት 2015 ላይ 23ኛ አመት እድሜዋን ያከበረችውን ፎርቹን ጋዜጣን መሰረተ፡፡ ፎርቹን ጋዜጣ በቢዝነስ ጋዜጠኝነት ታላቅ አሻራ ያኖረች መሆኑን ብዙዎች ያምኑበታል፡፡ በኢትዮጵያ የነጻ ፕሬስ ታሪክ ላይ በሀገሪቱ የቢዝነስ ጋዜጠኝነት በባለሙያነት ወይም በፕሮፌሽናሊዝም መንገድ እንዲሰራ ታምራት የተቻለውን ሁሉ አድርጓል፡፡ በ1990ዎቹ ላይ ደግሞ ከአለም ባንክ ጋር በመነጋገር የሚድያ ሰዎች ደረጃውን የጠበቀ ስልጠና እንዲወስዱ አድርጓል፡፡ ከ20 አመት በፊት በአሜሪካን ሀገር የጋዜጠኝነት ስልጠና የወሰደው ታምራት በባህር ማዶ በሚገኙ ጋዜጦችም ላይ በመጻፍ ብእሩን ያሳየ ነው፡፡
በተለይ እርሱ በመሰረተው ፎርቹን ጋዜጣ ላይ ያገለገሉ የዘመናት የእውቀት ስንቅ ከእርሱ መቅሰማቸውን ይናገራሉ፡፡ ብዙም የታይታ ሰው ያልሆነው ታምራት ስለ ራሱ መናገር ብዙም ደስታን አይሰጠውም፡፡ ይልቁንም በኢትዮጵያ ሚድያ ውስጥ ገና ብዙ መስራት ሲገባን ምን ሰርተን ነው የሕይወት ታሪካችን ለንባብ የሚበቃው የሚል የጸና አቋም አለው፡፡ ይሁንና የተወዳጅ ሚድያ የህይወት ታሪክ ቡድን አባላት ለ 2 አመት ባደረጉት የማሳመን ስራ ታምራት ታሪኩ እንዲሰራ ፈቃዱን ሰጥቷል፡፡ ታምራት እንዳለው የሀገራችን ሚድያ ገና ድክ ድክ ላይ ቢሆንም ይህንኑ ሚድያ አሁን ላለበት መልካም ለሚባል ደረጃ ካበቁት ውስጥ ታምራት ቀዳሚው ነው፡፡ በአሁኑ ሰአት የ50 አመት ሰው የሆነውና በሚድያ ሙያ ከ30 አመት በላይ የቆየው ታምራት ገብረጊዮርጊስ የህይወት ታሪኩ ምን ይመስላል? አብረወት የሰሩትን ስለ እርሱ ምን ይላሉ? 11 ሰዎችን አነጋግረናል፡፡ እዝራ እጅጉ የህይወት ታሪኩን እንደሚከተው አጠናክሮታል፡፡
ታምራት እና ኮከበ ጽባህ
የካዛንቺሱ ታምራት ገና በልጅነት ብእር ከወረቀት ማዋሀድ ይቀናዋል፡፡ አንደኛ ደረጃም ሁለተኛ ደረጃ ሳለ ከማንበብ እና ከመጻፍ ቦዝኖ አያውቅም፡፡ ለዚህ ደግሞ የኮከበ-ጽባህ ተሳትፎው አይዘነጋም፡፡ ከመጻፍ ይልቅ ግን ያኔ ማንበቡ ላይ ትኩረት ይሰጥ ነበር፡፡ የወደፊት ምኞቱንም ሲጠየቅ ጋዜጠኛ ይል ነበር፡፡ ታምራት ከውጭ ሀገር ሰዎች ጋር ገና በታዳጊነቱ መዋሉ የእንሊዝኛ ችሎታውን አዳብሮለታል፡፡ በየጊዜው የሚያነባቸው መጽሀፍትም የእውቀት አድማሱን አሰፉለት፡፡ በኋላ ግን ቁጥር አንድ ኢዲተር ሆነ፡፡ በ1985 አ.ም በህብር መጽሄት እና ጦማር ላይ የሚጽፋቸውን መጣጥፎች እንዳየነው ገና በጠዋቱ ለሚድያ ስራ እንደተፈጠረ መገመት አያዳግትም፡፡ ብእሩ የሰላ ነው፡፡ እይታው እና ምልከታውም ብስለት ያለው ነው፡፡ይህ እንዴት ሆነ? ታምራት ስለ ራሱ መናገር ስለማይወድ እንጂ ብሉ ሊለን ይችላል፡፡ ወደፊት ግን ሀሳብ መስጠቱ ስለማይቀር በጥናት የተደገፈ የራሱም ሀሳብ የተካተተበት መጣጥፍ ማቅረባችን አይቀርም፡፡
ስለ ራሱ ብዙም መናገር የማይወደው ታምራት ስራው ግን ይናገራል፡፡ እና ስለ ስራ ማንነቱ የቅርቦቹ ሲገልጹት የህይወት ታሪኩ ሆነ ማለት አይደል?
ታምረኛው ብዕረኛ
ከሀይሉ ወንድሙ (የፎርቹን የቀድሞ ምክትል ማኔጂንግ ኤዲተር)
ታምራት ይመራው ከነበረው የጋዜጠኛ ቡድን ጋር የተቀላቀልኩት የዛሬ 24 ዓመት ገደማ በ1999 ነበር። በዛን ወቅት ያስተዳድረው የነበረው ድርጅት Crown Publisher ሲሆን ቢሮውም መገናኛ መስመር ፕላዛ ሆቴል ጀርባ ነበር።
ከድርጅቱ ጋር ሥራ ስጀምር ኋላፊነቴ ለጋዜጣው አንባቢን የማፈላለግ ሥራ (Subscription Department) ስለነበር ቀጥተኛ የሆነ የሥራ ግንኙነት ባይኖረንም ቢሮው አንስተኛ ቪላ ስለነበር እርስ በእርስ ለመተዋወቅ አዳጋች አልነበረም። ጋዜጠኞቹ ከሙያ አጋርነት ባሻገር ብዙዎቹ ጓደኛማቾች ነበሩ። በዛ ጊዜም ቢሆን ታዲያ ታምራት ኮስታራ እና ለስራው ቅድሚያ የሚሰጥ ሰው እንደነበር አስታውሳለሁ።
ጥቂት ወራቶችን በነበረበት ቢሮ ከሠራ በኋላ አከራዮቹ ቤቱን ስለፈለጉት እና ቶሎ ተቀያሪ ቢሮ ማግኘት ስላልተቻለ Crown Publisher የተባለውን ድርጅቱን አብረውት በሽርክና ይሰሩት ወደ ነበሩት ግለሰብ ቢሮ ሣር ቤት አካባቢ ወደሚገኘው እምወድሽ ህንፃ ላይ ተዛወረ።
በዚህ ጊዜ ነበር የታምራት የሙያ ነጻነት ይፈተሽ የጀመረው። የድርጅቱን አብላጫ ድርሻ ባለቤት የነበሩት እና ለጊዜውም ቢሆን የቢሮአቸውን በር ከፍተው ቢሮ ካጋሩት የሥራ ሸሪኩ ጋር {ጉዳዩን መጥቀስ ባያስፈልግም} በአንድ የዜና ጉዳይ ላይ «ይታተም ወይም አይታተምም» በሚል ፍጥጫ ገቡ። የዛኔው ወጣቱ ጋዜጠኛ ታምራት ለሙያው በማድላት በባለሃብት እና በኤዲቶሪያል መካከል ያለውን ድንበር በደማቅ ቀይ መስመር አሰመረው።
ያኔ የወሰነው ውሳኔ ዘላለም የሚወደስበትን እና እኔም ሆንኩ በወቅቱ የነበሩ የሥራ ባልደረቦቹ እስከዛሬ እንደምሳሌ የምናነሳውን ታሪክ ሠራ። ለሥራ ሸሪኩም «የእኔ ኤዲቶሪያል ቡድን ከአንተ ውሳኔ እና ተፅዕኖ ነፃ ነው» ብሎ የተቃጣውን ጣልቃ ገብነት በሙያ ነፃነት አጠፈው። እንዳይታተም ጥያቄ የቀረበበትም ዜና በኤዲቶሪያል ውሳኔ ታተመ። ይህ ጉዳይ ከተከሰተ ብዙ ሳይቆይ ሌላ ቢሮ በመከራየቱ ሣር ቤት የነበረው ቢሮው ለቆ አትላስ ሆቴል አካባቢ አንድ ቪላ ቤት ተከራይቶ ያንኑ የካፒታል ጋዜጣን ሥራ ቀጠለ።
ወደ አዲሱ ቢሮው ከተዛወረ ጊዜ ጀምሮ ጋዜጣው በይዘትም ሆነ በስፋት ከፍ እያለ የሄደበት ዘመንም ነበር። ይህ ሲሆን ታምራት በሁለት ሀላፊነት የተወጠረበትም ወቅት ነበር። ምክንያቱም ድርጅቱ በሰው ሃይልም እየሠፋ ስለመጣ ከበፊቱ ጠንከር ያለ የስራ ማስኬጂያ ካፒታል በደንብ ያስፈልገው ጀመር። የጋዜጣው የማስታወቂያ ሥራ ይከናወን የነበረው ሸሪኩ ባገናኘው የማስታወቂያ ድርጅት ስለነበር ከዚህ ድርጅት የሚያገኘው ገቢ ለስራ ማስኬጃ ከሚያስፈልገው ካፒታል ጋር ስላልተመጣጠነ ታምራት በራሱ ዲፓርትመንት ማስታወቂያውን እንዲሰራ ወሰነ። ከመረጃ ፍለጋ በተጨማሪ በፋይናንስ በኩል ያለውን ክፍተት የመድፈኑ ሀላፊነት ወጣቱ ጋዜጠኛ ትከሻ ላይ አረፈ።
ካፒታል ጋዜጣ እንዲህ እንዲህ እያለ ዓመት ከመንፈቅ ሞላው። ሆኖም በ71ኛ ዕትሞ ገደማ አሁንም የታምራትን ቆራጥ ሙያዊ ውሳኔ የሚያስፈልግበት ጉዳይ ተከሰተ። የታምራት የሥራ ሸሪክ ይመሩት በነበረው መንግስታዊ ያልሆነ ማህበር ዙሪያ ጋዜጣው ይሰራው በነበረው ዘገባ ሸሪኩ ኤዲቶሪያል ጣልቃ ገብነት ለማድረግ ዳግም ሞከሩ። አሁንም ታምራት የሙያውን ነፃነት ለማስከበር ዘብ ቆመ። ምናልባት ይህ ውሳኔው የድርጅቱ ህልውና ላይ የሚያመጣውን ነገር ሳይገነዘብ ቀርቶ አልነበረም። ሆኖም ግን የመርህ ሰው በመሆኑ ቅድሚያ ለሚሰጠው ቅድሚያ በመስጠት ለሙያው ልዕልና ዳግም ቆመ።
ይህ ሁኔታ እንደመጀመሪያው ውሳኔ ቀላል ስላልነበር ከሸሪኩ ጋር ፍጥጫ ገቡ። ይህንንም ፍጥጫ ታምራት ወደኋላ ሳይል ዓመት ከመንፈቅ የደከመበትን ጋዜጣውን እስከሚያሳጣው ድረስ በአቋሙ ፀና። ይህንን ጉዳይ በገዛ ጋዜጣው ፊለፊት ገፅ ላይ በሁለቱ ሸሪኮች ፎቶ የተደገፈ ዘገባ በመፃፍ ለሚያከብረው አንባቢው ለንባብ አብቅቶት ነበር። ይህም ጋዜጣ በታምራት ሀላፊነት የታተመ የመጨረሻ ካፒታል ጋዜጣ ሆኖ ቀረ። በዚህም ምክንያት ክስ ተመስርቶበት ለረጅም ጊዜ ፍርድቤት ተመላልሶ በስተመጨረሻም ነጻ ወጥቷል። ይህንን ፍጥጫ የዘገበበት ጋዜጣ የፊት ገጽ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ቢሮው በፍሬም አድርጎ እንዳስቀመጠው አስታውሳለው።
የታምራት የሙያ ነፃነቱን ያልተረዱለት ወይንም ለማክበር ያልፈለጉት ሸሪኩ በወቅቱ ሲታተም በነበረው ADDIS TRIBUNE ጋዜጣ ላይ «አቶ ታምራት ከካፒታል ማኔጂንግ ኤዲተርነት እንደተባረሩ እና ሁሉም የጋዜጣው አባል ሜጋ ህንጻ ላይ በሚገኘው የሸሪኩ ቢሮ ሪፖርት እንዲያደርጉ» የሚል ማሳሰቢያ መሳይ ማስታወቂያ ታተመበት።
ታምራት በቅርብ የሚያውቁት ሰዎች ሊመሰክሩ እንደሚችሉት ብዙ ለድርድር የሚከፍታቸው በሮች ቢኖሩትም በስራ እና በሙያው ልዕልና ላይ የሚመጡትን የትኛውንም ዓይነት ተፅዕኖዎች ለድርድር የሚከፈተው በር የለውም፡፡ ይህንንም በማድረጉ ድርጅት አይደለም ሌላም ነገር ቢፈርስ ከውሳኔው ንቅንቅ የሚያደርገው ነገር አልነበረም።
ለታምራት ጋዜጣ ሀ ብሎ መመስረት ካፒታል ጋዜጣ የመጀመሪያው አይደለም፡፡ ጦማር እና በእንግሊዘኛ የሚታተም Entrepreneur የሚጠቀሱ ናቸው። እኔ እስከማውቀው ድረስ ጋዜጣዎቹን ሲለቅ ዴስኩ ላይ ያሉትን መጽሐፍቶቹን ከመያዝ በስተቀር ስለሌላው ነገር ግድ ሳይሰጠው ነው የሚለቀው። ይህ ሁኔታው የሚያሳየው ትልቅ በእራስ የመተማመን አቅም እንዳለው እና ውስጡ ያለው ችሎታ የትም ሄዶ ከነበረው በላይ አሳምሮ እንደሚሰራው ስለሚተማመን ነው። ለዚህም ነው «ጋዜጠኝነት ቁስ ላይ ሳይሆን ሰው ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንት ነው» ብሎ የሚያምነው።
በካፒታል ጋዜጣም የሆነው ይህ ነበር። «ኤዲቶሪያል ነጻነት ይከበር» በማለቱ እጁ ላይ የነበረው ድርጅት በአንዲት ቀጭን ትእዛዝ በአንድ ሳምንት ውስጥ ከእጁ ወጣች። ይህ ሲሆን እንደ ሰው ምን ሊሰማው እንደሚችል መገመት ቀላል ነው። ታምራት ግን ከስሜቱ በላይ በማሰብ ችግሩን ለሥራ ባልደረቦቹ አቀረበው። «ሪፖርት አድርጉ» የተባሉትም ባልደረቦቹ «ጥቃትህ ሙያህን በማስከበርህ የደረሰብህ ጥቃት ነው ስለዚህ ይሄ የእኛም ጥቃት ነው» በማለት የምናውቀው አንተን እና ሙያህን እንጂ ከድርጅቱ ጀርባ ያለውን ባለድርሻ አይደለም በማለት ሁሉም ከታምራት ጎን ቆሙ።
ይህ ሁሌ ሳስበው ሙያውን ስላከበረ ሙያው የከፈለው ክፍያ ይመስለኛል፡፡ ። በዚህ ጊዜ ነበር እንደገና ታምራት ሌላ ጋዜጣ ለመጀመር የወሰነው። ታምራት ካለው ፀጋ አንዱ የራሱን ነገር አሳልፎ ሰጥቶ ሰዎች የራሳቸው እንዲመስላቸው እና የእኔነት ስሜት እንዲያድርባቸው የማድረግ ፀጋ አለው። በወቅቱ ሁሉም ሰው በአንድ ቆሞ እንዲቀጥል ያደረገው ይህ ጸጋው ነው። ውጣ ውረዱ እንዲህ እንደሚፃፈው ቀላል ባይሆንም ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ባሉት ቀናቶች ውስጥ የሚመሰረተው ድርጅት ስምና እና ማን የሚባል ጋዜጣ ይታተም የሚለውን እንደአንድ ቤተሰብ ለሁሉም የሥራ ባልደረቦቹ ለውይይት እድል በመስጠት «ፎርቹን» የሚባል ስያሜ ጋር በመድረስ ተቻለ። ይህ ድርጊቱ የታምራት ሁሉንም አካታች እንደሆነ እና በችግር ጊዜ ነገሮችን እንዴት በብልሃት ማለፍ እንደሚችል ያሳያል።
የታምራት ጠንካራ የዲፕሎማሲ ጎኑ ይበልጥ ጎልቶ መታየት የጀመረው ከፎርቹን መመስረት በኋላ ነበር። የፎርቹንን ስም በጥሩ መሰረት ላይ ለመጣል እና ገበያ ላይ ካሉት ጋዜጦች ከሁሉም በልጦ እንዲወጣ ለማድረግ ሁሉም በየፊናው ይጥር ጀመር። ታምራት ከበፊቱ ልምድ በመውሰድ ይመስላል ፎርቹን የሦስተኛ አካል የገንዘብ ጥገኛ እንዳይኖረው ይለፋ ጀመር። የፋይናንስ ክፍሉን እና የማስታወቂያ ክፍሉን ከኤዲቶሪያል ጋር ለመለየት በማሰብ የሌላ ሰው ተፅዕኖ የሌለበት እህት ኩባንያ በማቋቋም ጋዜጣው ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ የኤዲቶሪያል ነፃነቱን አረጋገጠለት። ይህ ውሳኔው ይመስለኛል እስከዛሬ ድረስ ጋዜጣው የኤዲቶሪያል ነፃነቱን ጠብቆ እንዲኖር ያደረገው።
ይህንን አጢኖ ለተመለከተው ሰው ታምራት ለኢትዮጵያ ሚዲያ ኢንዱስትሪ ቀድሞ የተፈጠረ ሰው ነው ለማለት የሚያስደፍረው። የሚዲያው ኢንደስትሪ ውስጥ ቀድመውትም ሆነ ከሱ በኋላ ተሳታፊ ከሆኑት አካሎች በበለጠ ሚዲያው ላይ ተስፋ ይጥል ነበር። በዚህም ምክንያት አዳዲስ ነገርን ለመሞከር ለሚወጣ ገንዘብ ወደኋላ አይልም ነበር።
ለምሳሌ Research Department በማቋቋም ታምራት ፋና ወጊ ነበር… በወቅቱ ኢንዱስትሪው ላይ ዜና ማለት አዲስ የተፈጠረው ነገር እና የሚስብ ዓርዕስት ነው ብሎ ከማመን የዘለለ ልምድ በሌለበት ዘመን የታምራት ግን የዜና ትልቁ ሥራ ከዜናው ባሻገር በዙሪያው የሚሰበሰቡ Background information እና የምርመራ ሥራ እንደሆነ ቀድሞ የተረዳ ስለነበር መረጃዎችን ያለመታከት ይሰንድ ነበር። ለምሳሌ አገሪቷ ውስጠ ያሉ የአክሲዩን ድርጅቶች ሲቋቋሙ ከመነሻ ካፒታላቸው ጀምሮ እስከ አክሲዮን ድርሻቸው ድረስ ከተለያዩ ግብዓቶች እየተቃረመ ይሰንድ ነበር። ይህም መረጃ ከንግድ ሚኒስቴር መዝገብ ቤት ፣ ከንግድ ምክር ቤት ቢሮ እና ከኢንቨስትመንት ቢሮ ተጨማሪ መረጃዎች ይካተቱበት ነበር። ይህ ግብዓት ፎርቹን ለሚሰራቸው ዜናዎች ታማኝነት እና ለመረጃ ሰጪነቱ ትልቅ አስተዋፅኦ ነበረው።
በዚህ የተጀመረ ዲፓርትመንት በማስፋት የ data analysis መስራት ድረስ በማሳደግ በተለያዩ አገር አቀፍ ምርጫ በተካሄዱበት ወቅት public opinion polls በመስራት አሁንም ታምራት የሚያሳትመው ጋዜጣ ፋና ወጊ ነበር። በዚህም ዲፓርትመንት እገዛ ፎርቹን ከተለመደው ፎቶ ግራፍ ሽፋን የፊት ገፅ ወጥቶ ወደ Illustrations በማሳደግ የአንባቢን ቀልብ በመሳብ ቀዳሚነትን አግኝቷል ። ይህ ታዲያ አብረውት የሚሰሩ የሥራ አጋሮቹ ይድከሙበት እንጂ ህልሙ እና አመራሩ የታምራት ነበር።
በጋዜጠኝነት ስነ-ምግባር ጋዜጣው ሁሌም ተወዳሽ እና ፋና ወጊም ነበር። ለምሳሌ የውሎ አበል ባለው ሥራ ላይ የተላከ ከፎርቹን ጋዜጠኛ ውሎ አበሉን ጠሪ ድርጅት ሳይሆን የሚከፍለው እራሱ ጋዜጣው ነበር። ይህ ድርጊት እስከዛሬ ድረስ ሌላ ጋዜጣ አደረገ ሲባል ሰምቼ አላቅም። ይህንን የሚያደርገው ታምራት ገንዘብ ተርፎት ሳይሆን የኢዲቶሪያል ነፃነት ምን ያህል መስዋእትነት እንደሚጠይቅ ከሌላው በተለየ መልኩ ገብቶት ስለነበር ነው። ስለ ፋና ወጊነቱ ሆነ ስለ ኤዲቶሪያል ነፃነት ሲል ስለሚጋፈጠው ግድግዳ ለመናገር አንድ መፀሐፍ እንጂ እንዲህ አጭር ፅሁፍ የሚበቃው አይመስለኝም።
ያለምንም ግነት የታምራት ጋዜጠኝነት ከሙያ ባለፈ በደሙ ውስጥ ሰርፆ የገባ ነው። ነገሮችን የሚያይበት መንገድ ጉዳዮችን የሚያስረዳበት መንገድ ሁሉም ነገሩ ከስራው ጋር የተያያዘ ነበር። እሱን ያለጋዜጠኝነት ማሰብ አይንን ጨፍኖ እንደመራመድ ይሆንብኝና ማሰቡን እተወዋለሁ። ታምራት ሁሉ ነገሩ ሥራው ነው። በአንድ ወቅት ጋዜጠኛ ለመቅጠር ባወጣነው ማስታወቂያ የመጡትን አመልካቾች ከእሱ ጋር በመሆን የመመልመል ሥራ ላይ እሳተፍ ነበር። ታዲያ በምልመላው ወቅት በጣም ቀላል የሚመስሉ ግን እሱ ሚስጥሩን የሚያውቃቸውን ጥያቄዎችን ይጠይቃል። ከሚጠይቀው ጥያቄዎች ግን ዘላለሜን የማረሳውን ልጥቀስ…
አንድ ወጣት አመልካችን ጥያቄ እየጠየቀው ነበር፡፡ በመሐል ድንገት "እናትህ ትወድሃለች?" ብሎ ጠየቀው። ልጁም በኩራት «አዎ» አለ… ታምራት ከተል ብሎ… «እንዴት አወቅክ?» አለው… ወጣቱም «እንዴ እናቴ አይደለች እንዴ?» አለ… «አሃ ሁሉም እናት ልጁን ይወዳል እያልከኝ ነው?» ብሎ ታምራት አከለበት… ወጣቱ ዝም አለ… ያኔ ታምራት ቀጠለ… እናትህ እንደምትወድህ አባትህን ጠይቀኸው ታውቃለህ? ወይስ ከቤታችሁ ውስጥ እህቶችን ወይስ ወንድሞችህን እናትህ ስለአንተ ምን እንደሚያስቡ ጠይቀህ ታውቃለህ? አለዚያም ጎረቤቶችህን እናት ስለአንተ ምን እንደሚያወሩላቸው ጠይቀህ ታውቃለህ? ብሎ የጥያቄ መዓት አዥጎደጎደበት… በዚህ ግዜ የወጣቱ ዓይን ፈጠጠ… በቃ ጋዜጠኛ መሆን ከፈለክ ለእነዚህ ሁሉ ቦታ መስጠት አለብህ አለው። የልጁን ስሜት መገመት ቀላል ነበር። በእኛ ሐገር ባህል እና የቤተሰብ ሁኔታ እንዲህ ያለው አስተሳሰብ ማሰብ ከዕብደት ተለይቶ አይታይም። ታምራት በዚህ ደረጃ ነበር የጋዜጠኝነትን አስኳል ለሌላው ሰብሮ ለማሳየት ሲታገል የኖረው። if you do not like the heat get out of the kichen የሚላትም አባባል ጋዜጠኞች በአካባቢው ውጥረት ተጨናንቀው የማይሆን ሰንጣቃ ውስጥ ሲገቡ የሚያነቃቸው አባባል ነበር።
ዕድል ሰጪ ነው
ታምራት ከዲግሪ እና ከዲፕሎም ይልቅ ይልቅ የማደግ ህልም ያለው ስራ አመልካች ይማርከዋል። እንደአሰሪ ብዙ ዲግሪ ያለው እና የተሰጠውን ሥራ ጥንቅቅ አድርጎ የሚሰራ ከራሱ አልፎ ለሌላው አጋዥ የሆነ ሠራተኛ ቢኖረው አይጠላም… ግን በሂደት እንዳየው ከሆነ እንዲህ ዓይነቱን አመልካች እሱ ሁሌም እንደሚለው "an actor with a samsonite" ብሎ እንደሚጠራው የሚያውቀውን ለመስራት እንጂ የሌላውን ሰምቶ እና አገናዝቦ ለችግሮች መፍትሄ ለመፍጠር ፍላጎት የላቸውም ይላል። በዚህም ምክንያት የትምህርት ደረጃው ምንም ይሁን ምንም ፍላጎት እና የማደግ ተስፋ ያለው ሰው ካገኘ ብዙ ትኩረት በመስጠት በስራ ብቁ ለማድረግ ይለፋ ነበር።
ለዚህም ነበር ፍላጎት ያላቸው እና እነሱ ያላዩት ችሎታቸውን እሱ ቀድሞ በመረዳት ብዙ ወጣቶች ላይ ጊዜውም ገንዘቡንም ሲያወጣ ቅር የማይለው። ለምሳሌ ከብዙ ጥቂቶቹን ለመግለፅ ዲዛይነር ለመሆን ያመለከተን አንድ ሰራተኛ ለማመልከቻ የፃፈው ፕሮፖዛል በመመልከት የልጁን የመፃፍ ችሎታ ተገንዝቦ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጥሩ Opinion ፀሀፊ አድርጎታል። በተመሳሳይ ሁኔታም ለጋዜጣው የፊልም ግምገማ ዓምድ ላይ ይጽፍ የነበረን የዩኒቨርሲቲ ተማሪ አቶ ታምራት ችሎታውን ቀድሞ በመረዳት ከጊዜ ሂደት በኋላ ጎበዝ የኤዲቶሪያል ፀሐፊ እንዲሆን አብቅቶታል። ይህ ችሎታው አብረውት የሚሰሩትን ሰዎች ቀድሞ ነገአቸውን የማየት ድንቅ ተሰጥኦ እንዳለው ያስታውቃል። እኔም ብሆን የዚህ ድንቅ የማስተዋል ችሎታው ተጠቃሚ በመሆኔ ነው ከ Subscriptions Department የጀመርኩት የስራ ድርሻ ወደ ፎቶግራፈርነት አድጎ ከዛም አልፎ ፎቶግራፍ ኤዲተር እና ሲኒየር ኤዲትር በመቀጠልም ድርጅቱን እስከምለቅበት ድረስ በምክትል ማኔጂንግ ኢዲተርነት የሠራሁት። ምንአልባት በእኔ ታሪክ እንደ ታምራት አይነት ሜንቶር/ ባልንጀር መጋቢ/ ባላገኝ ኖሮ በሙያው ይህንን ያህል ዘመን (ለ16 ዓመት) እቆያለሁ ብዬ አላምንም። ምክንያቱም ለሙያው ያለው ፍቅር ከራሱ አልፎ ለሌላ ሰው ላይ የማጋባት ሀይል ነበረው።
አንጋፋ ጋዜጠኞችን አክባሪ እና አስታዋሽ ነው
ታምራት አዲስ የጋዜጠኛ ትውልድ ለመፍጠር እንደሚደክመው ሁሉ አንጋፋዎችንም የረሳ ሰው አይደለም…ለአንጋፋ ጋዜጠኞች በጣም የሚገርም አክብሮት ነበረው። ከማስታውሳቸው ለአቶ ተፈሪ ወሰን ያለው አክብሮት የአባት እና የልጅ ያህል ነበር … አቶ ግርማ ፈይሳ (ዳንዴው ሰርቤሎ ከስድስት ኪሎ በሚል የብዕር ስም የሚታወቁት) … ፎርቹን ሲመሰረት ጀምሮ በሞት እስኪለዩ ድረስ በፎርቹን አምድ እንዲኖራቸው አድርጎ ዘመናቸውን ሙሉ ከጋዜጣ ሳይለዩ እንዲኖሩ ምክንያት ሆኗል። አቶ ሙሴ አንጋፋ የሬዲዮ ሰው ነበሩ ፡፡ ከአሜሪካ ለተወሰነ ጊዜ አዲስ አበባ ሲኖሩ በፎርቹን ጋዜጣ በኮፒ ኤዲተርነት ያሳትፋቸው ነበር። እነ አቶ መለስካቸው አምሃ (በአሜሪካ ድምጽ ዘጋቢነት የሚታወቁት) በኤዲተርነት አብረውት ይሰሩ ነበር። እነዚህን ጨምሮ ሌሎችም የተለያዩ ዘመን ላይ ጎበዝ ስመጥር ጋዜጠኞች የነበሩ አብረውት እንዲሰሩ ዕድሉን ያመቻች ነበር። ይህ የሚያሳየው ከሙያ ታላላቆቹ ትምህርት ለመውሰድ ምንያህል ራሱን ያዘጋጀ እንደሆነ ነው፡፡
ታምራት Game Changer ነው
ይብዛም ይነስም የሚዲያ ኢንደስትሪው የተለያዩ ውድድሮች እና ውጥረቶች ነበሩት። በሰራተኛ ቅጥር ፣ በዜና ምንጭ ፣ በስፖንሰር አድራጊ ድርጅቶች እና የመሳሰሉ ፉክክሮች ነበሩት… በዚህን ጊዜ ታምራት በነበረው ሂደት ላይ ብዙ ጊዜ አያጠፋም፡፡ ይልቁኑ አዲስ ነገር ፈጥሮ ጨዋታውን ይቀይረዋል። ይህም ለምሳሌ ለማስረዳት አንድ ወቅት የጋዜጣ ላይ ማስታወቂያ የሚያወጡ ድርጅቶችን ለመያዝ ውድድሩ ጠንክሮ ነበር። የፎርቹን ዋጋ ከሌላው ጋዜጣ ዋጋ ከፍ ይል ስለነበር አስተዋዋቂዎቹን ስቦ የመምጣት ስራው ቀላል አልነበረም። በዚህን ጊዜ ነበር ታምራት ለኢንደስትሪው አዲስ አሰራርን በማስተዋወቅ የባለቀለም ማስታወቂያን የጀመረው። ያኔ ለምርጫ ሲግደረደሩ የነበሩት ድርጅቶች የጥራት ልዩነቱ የሰማይ እና የምድር ሆኖባቸው ፊታቸውን ወደ ፎርቹን መልሰዋል። ሌሎች ተፎካካሪ ሚዲያዎች ወደ ቀለም ገፅ ማስታወቂያ እስከሚመጡ ድረስ ጨዋታውን ቀያሪው ታምራት ጊዜውን ተጠቅሞበታል።
በሰራተኛ ቅጥርም እንዲሁ ነበር። የፎርቹን የሥራ አካባቢ ከባድ የሚባል ስለነበር ብዙ ኤዲተር ሪፖርተር ወደ ቀለለው አካባቢ ይሄዱ ነበር። ይህ ሲሆን ታምራት የኤዲተር ደሞዝን ኢንደስትሪው ከሚያስበው በላይ በማድረግ ኢንደስትሪው ላይ ያለውን የባለሙያ ዝውውርን ገታ አድርጎት ነበር። ከዛን ጊዜ ጀምሮ ፎርቹን ጋዜጣ ጥሩ ክፍያ በመክፈል የመጀመሪያ ረድፍ እንደያዘ ነው።
ከሙያው ባለፈ የግል ባህሪውን በተመለከተ አብሮት እረጅም ጊዜ እንደኖረ ሰው ታምራት በጣም ደግ እና ያለውን ሲሰጥ ያልቅብኛል ብሎ የማይሰስት መልካም ሰው ነው። የታምራት ደግነት ሳስብ በህይወቱ ውስጥ ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠውን አሜሪካዊ ወዳጁን ፕሮፌሰር ዶናልድ ሊቪስን (Donald N. Levine) ያስታውሰኛል። ታምራት ገና የኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ ድክ ድክ በሚልበት በሰማኒያዎቹ መጀመሪያ ላይ በወቅቱ በጋዜጣ በዘገበው ዜና ምክንያት ለእስር ተዳርጎ ነበር። በሀገሪቱ ታሪክ ገና የግል ሚዲያ መጀመሩ ስለነበር ለሚታሰሩ ጋዜጠኞች ሆነ ስለመብታቸው የሚሞግትላቸው የረባ ማህበር አልነበራቸውም። በዚህ ጊዜ ነበር ታምራት በፍርድ ቤት ጥፋተኛ ተብሎ የ10ሺ ብር ቅጣት የተበየነበት። ያኔ ያን ያክል ብር እንኳን ከጋዜጠኛ ኪስ አይደለም ከነጋዴም ኪስ ለማግኘት የማይታሰብ ህልም ነበር። በዚህ ጊዜ ነበር ፕሮፌሰር ዶናልድ ሊቪስ እንደመላዕክት የታምራት ህይወት ውስጥ ደግነትን ይዞ የተከሰተው። የጋዜጠኛው መታሰር እና መክፈል የማይችለውን ቅጣት መጣሉን በሰፊው ይወራ ስለነበር ፕሮፈሰሩ የታሰረበት ድረስ በመሄድ «እኔ ከፍዬ ከእስር አስፈታሀለው» በለው የደግነት ጥግን ለዛ ጊዜው ልጅ እግር ጋዜጠኛ አሳዩት። እንዲህ አይነቱ የደግነት አሻራ ስላረፈበት ይመስለኛል ታምራት ሰው ሲቸገር ካየ ባልጠበቁት መንገድ ከፊት ሆኖ ለችግር መድረስ የሚሳካለት። ታምራት በህግ ከለላ ስር የነበሩ ጋዜጠኛ ጓደኞቹን ተመላልሶ ለመጠየቅ የሚያክለው የለም። ለዚህም ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ትልቅ ምስክሩ ነው። ታምራት አብረውት ሲኖሩ የግሌ የሚለው ነገር የለውም፡፡ የታምራትን መኪና ለመዋስ የቢሮውን በር ማንኳኳት ብቻ በቂ ነው፡፡ ከቢሮ የሚወጣበት ጉዳይ ከሌለው «ለምን?» ብሎ እንኳን አይጠይቅም፡፡ አይኑን ኮምፒውተሩ ላይ ሳይነቅል የመኪናውን ቁልፉን አሳልፎ ይሰጥ ነበር። ሌላው ቢቀር ለሥራ ወደ ውጪ ሀገር እንኳን ሲጓዝ እንደስራ ባልደረባ ሳይሆን እንደ አንድ የቤተሰብ አካል ነበር አብሮት ለሚሰሩ ሰዎች ስጦታ ይዞ የሚመጣው። ምናልባት ይህ የምፅፈው ፅሁፍ ለንባብ በቅቶ ካነበበው ሊናደድብኝ እንደሚችል እርግጠኛ ነኝ። ምክንያቱም ሰለራሱ ማውራት ወይም እንዲወራ እንደማይፈልግ አውቃለሁ። ሆኖም ግን ታምራት በሙያው ያበረከተው አስተዋፅኦ ወደደም ጠላም ከግለሰብነት አሻግሮት የሕዝብ ሀብት እንዲሆን አድርጎታል።
ቁጥር አንድ ኤዲተር
ሀሙስ ሰኔ 1997 ዓ.ም ለውድነህ ዘነበ ልዩ ቀን ነበር ። ጠዋት ላይ ሃያ ሁለት አካባቢ ከሚገኘው የFortune ጋዜጣ ቢሮ ደረሰ፡፡
ታምራት ገ/ጊዮርጊስን አገኘው፡፡ ፎርቹን ጋዜጣ ላይ መስራት እንደሚፈልግ ነገረው ። ታምራትም ውድነህን በአግራሞት ከተመለከተው በኋላ አንዳንድ ጥያቄዎች ጠይቆት ሲያበቃ - ዛሬ ጀምር አለው ። ውድነህ በዚህ ሰአት ልቡ በደስታ መምታት እየጀመረች እጁ ላይ ያሉትን ዜናዎች ለታምራት አቀረበ - ታምራትም ውድነህን ለዋና አዘጋጁ አየነው ሀይለስላሴ አሳልፎ ሰጠ፡፡ ከዚህ በኋላ የፎርቹን እና የውድነህ ውህደት ተጀመረ፡፡
‹‹….በዚያው ሳምንት ነበር አንዱ ዜና ፊት ለፊት ገፅ አንዱ ዜና ደግሞ ገፅ አስር ላይ የታተመልኝ ። ይህን እድል ማግኘት ለእኔ ተአምር ነበር ።››ይላል ውድነህ 18 አመት ወደ ኋላ እየነጎደ፡፡
የታምራት ቢሮ መስራት ለሚፈልግ ማንኛውም ሰው ክፍት ነበር ። የፎርቹን ጋዜጣ ቢሮ የስራ ከባቢ ትጋት ፣ ንቃት ፣ ትኩረት የሚፈልግ በመሆኑ ‹‹ሰው አይበረክትም - ቢሮው በውጥረት የተሞላ ነው።›› ሲሉ ብዙዎች ሀሳብ ይሰነዝራሉ፡፡
ውድነህ በአምስት አመት ቆይታው ብዙ የፎርቹን ባልደረቦቹን ያስታውሳል፡፡ አንዳንዱ ውጥረት ሲበዛበት ተሰላችቶ ስራውን ይተዋል፡፡ ሌላው ደግሞ አቅም አዳብሮ ማለፊያ መስሪያ ቤት ይገባል፡፡ ፎርቹን ገብተው የወጡ ሁሉ የማይክዱት ሃቅ ቢኖር ስራ አውቀው ወደ አንድ ትልቅ ምእራፍ መሻገራቸውን ነው፡፡ ይህም አንዱ የታምራት ትልቅ አሻራው ሲሆን ሰዎችን ማብቃት ትውልድን የመቅረጽ አደራንም እንደተወጣ መመስከር ያሻል፡፡
‹‹ታምራት በእኔ እይታ በኢትዮጵያ ቁጥር 1 ኤዲተር ነው ።›› ሲል ውድነህ አፉን ሞልቶ ስለ ታምራት ይመሰክራል፡፡ ውድነህ እና ባልደረቦቹ ዜና ፅፈው ታምራት ቢሮ ገብተው ሲወጡ ዜናቸው ተገለባብጦ ፣ ተደበላልቆ ፣ ተቆርጦ ፣ ረዝሞ በአስገራሚ ጥራት ኤዲት ተደርጎ ተከሽኖ ይቀርባል፡፡ ። ‹‹…የመጨረሻውን ኮፒ ስናየው የራሳችን መሆኑን እንጠራጠር ሁሉ ነበር ።›› ሲል ውድነህ የኤዲተር ብቃት በጋዜጠኛ መመዘን እንደሚችል ያስረዳል፡፡
ውድነህ እና ባልደረቦቹ ዜና ይዘው ታምራት ቢሮ በገቡ ቁጥር ረመጥ ላይ ቆመው ፣ ተለብልበው፣ ነደው፣ ግለው ፎርቹን የገቡበትን ቀን ረግመው ይወጣሉ፡፡- አንዳንድ ልጆች ሸልለው ገብተው አመድ መስለው ይወጡ ነበር ።
አንድ የፎርቹን ጋዜጠኛ ከግለቱ በረድ ሲል ብዙ እየተማረ መሆኑን ያስባል - ለአዲስ ስራም ይነሳሳል ። ውድነህ እሁድ ጠዋት አራት ኪሎ ኢንተር ሜዞ ቁጭ ብሎ ቡናውን እየላፈ ጋዜጣውን ሲያነብ ልዩ ስሜት ይሰማዋል - የሚደወሉለት ስልኮች አንዳች ሀይል ያጎናጽፉታል፡፡
ውድነህ ፎርቹን የገባው በታሪከኛው ምርጫ 1997 ዓም ማግስት በመሆኑ ወቅቱ ውጥረት የተሞላበት ነበር ። አንድ ረቡዕ ጠዋት ሁሌም እንደሚደረገው ኤዲቶሪያል ተቀምጠው የተደረሰበት የስራ ደረጃ እየታየ ሳለ በአዲስ አበባ ከተማ ከባድ ደም አፋሳሽ ግጭት ተነሳ ።
ውድነህ ያንን ቀን ሲያስታውስም ‹‹..በወቅቱ ታምራት ያቀረበልን ሀሳብ ዛሬም አይረሳኝም ። እስካሁን የሰራነውን እሁድ አናትመውም - አዲስ ስራ እንስራ ወይስ ትተን ቤታችን እንግባ ? በማለት ጠየቀ ። የተወሰንን ጋዜጠኞች እንስራ አልን። መስራት የማይፈልግ አይገደድም ። የተፈጠረው ከባቢ ለህይወት አስጊ ስለሆነ አስቡበት በማለት ጊዜ ሰጠን ። እኛም እንሰራለን የሚል ታሪካዊ ውሳኔ አሳለፍን ። ለሚያልፍ ዝናብ አንበሰብስም ያሉ ጋዜጠኞች ወደ ቤታቸው ሲከቱ ታምራት እና የተወሰንን ጋዜጠኞች ስራ ላይ እንደነበርን በታሪክ ተፅፏል - በማለት ውድነህ ያስታውሳል ። ለአራት ይመስለኛል አዲስ አበባን አስምረን ተከፋፍለን ከሕይወት ጋር ግብግብ ፈጥረን - አዲስ አበባ ስታነባ - የኢህአዴግና የቅንጅት ፖለቲካ ሰው ሲበላ ተመለከትን - ለአንባቢዎቻችን ታማኝ በመሆን ጉደኛ ጋዜጣ አትመን አስነበብን።›› በማለት ታምራት ደፋር እና ለአንባቢ የታመኑ ጋዜጠኞች እንዲኖሩት ይፈልግ እንደነበር ውድነህ ያስረዳል፡፡
የታምራት ፎርቹን ጋዜጣ ለኤዲቶሪያል ስራዎች ከፍተኛ ገንዘብ ያፈሳል። ከከተማ ወጣ ባሉ ቦታዎች ዜና ሲፈጠር በድርጅቱ ተሽከርካሪ እና በጀት ከማንም ቀድመው የፎርቹን ጋዜጠኞች ቦታው ይደርሱ ነበር ። የፎርቹን ኤዲቶርያል ክፍያን በተመለከተ - ውድነህ ከአንድ ሺህ ብር በታች በሆነ ደሞዝ ጀምሮ በኢትዮጵያ ፕሬስ ዘርፍ ትልቁ ተከፋይ እስከመሆን ደርሶ ነበር። የተወሰኑ ጋዜጠኞች ከድርጅቱ ጠቅላላ ወርሃዊ ገቢ የሆነ ፐርሰንት ከደሞዛቸው በተጨማሪ ይከፍል ነበር።
አብረውት የሰሩት እንደሚሉት ታምራት እንደ አሰሪ ዳር ሆኖ ወይም እንደ ባለሃብት ከፍታ ላይ ሆኖ አይደለም ተቋሙን የሚመራው ። የእያንዳንዱን ጋዜጠኛ እንቅስቃሴ ይከታተላል - በአገሪቱ እየተካሄደ የሚገኘው ክስተት እንዲያመልጠው አይፈልግም ። ‹‹ከታምራት ጋር ዜና መስራት አስደሳች ነው ። ›› ሲል ውድነህ ይህን አባባሉን ብዙዎች ባልደረቦቹ እንደሚጋሩትም አይዘነጋውም፡፡
ውድነህ እና ባልደረቦቹ በፎርቹን ጋዜጣ ላይ ብዙ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ፅፈዋል ። የአገሪቱን ማክሮ ኢኮኖሚ ፣ መሠረተ ልማት ፣ የግብርና ዘርፍ ፣ የአካባቢ ጥበቃ ፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ ፣ የአገሪቱ ገቢ እና ወጭ ንግድ ፣ የፌደራል መንግስት በጀት ፣ የኢንዶመንት ድርጅቶች ግዝፈት ፣ የውጭና የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ትኩረት ፣ የአዲስ አበባ አስተዳደር እንቅስቃሴ … በትኩስ ትኩሱ እንካችሁ ብለዋል፡፡ ቀንም ማታም እየተሰራ ለአንባቢ ታማኝ መሆን ማለት ምንድነው የሚለው በተግባር ይታያል፡፡ ለዚህ ውጤት ደግሞ ታምራት የአንበሳውን ድረሻ ይወስዳል በሚለው ብዙዎቹ ይስማማሉ፡፡
ታምራት ራሱም እንደጋዜጠኛ እየጻፈ ፤ አርትኦቱን እየሰራ ብዙ ውጣውረዶችን አሳልፏል፡፡ በዚህ ሂደት ከግዙፍ ኩባንያዎች ዛቻ ፣ ማስፈራሪያ አልፎ ተርፎም ክስ ቀርቦበት በፍርድ ቤት መድረክ በዝረራ ማሸነፍ ችሏል ።
ውድነህ እንደሚለው ታምራት ለጋዜጣ አንባቢው ማህበረሰብ ሃብት ነው ፣ ታማኝ ነው ፣ ለጋዜጠኞቹም ጥላ ነው ። እሱ ከማንም ጋር ጠብ የለውም ፣ ከማንም ጋር በፍቅር አይወድቅም ። የመርህ ሰው ነው። በኢትዮጵያ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚታተመውን ትልቁን ፎርቹን ጋዜጣ በብዙ ችግር ውስጥ ይዞ መቆየቱ ያስመሰግነዋል ።
የታምራት የሊደር ሽፕ ፍልስፍና አነጋጋሪ መሆኑ እንዳለ ሆኖ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ከሁለት አስርት አመታት በላይ ጋዜጣውን ይዞ የመጣበት መንገድ ተጠንቶ መማሪያ ቢሆን ሲል ውድነህ የቀድሞ አለቃውን የከፍታ ልክ ተናግሯል፡፡ ውድነህ የቀድሞ አለቃውን ታምራትን ሲያመሰግን ከልቡ ነው፡፡ እዚህ ደርሻለሁ እና ይህም በአንተ ምክንያት ነው ሲል ለታምራት ያለውን ስፍራ ይነግረናል፡፡
ውድነህ በአሁኑ ሰአት ግሪን ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የተሰኘ የማማከር ድርጅት ከፍቶ እየሰራ ይገኛል፡፡ ውድነህ ታምራት ጋር ሲሰራ የቀሰማቸውን በጎ ልምዶች በራሱ ድርጅት ላይ ተግባራዊ ያደርጋል፡፡ ውድነህ ሀገራዊ ሪፎርም ዳግም የተወለደው የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የተሰኘ ባለ 200 ገጽ መጽሀፍ ጽፎ ያሳተመ ሲሆን ጽናትን ከፎርቹን በማግኘቱ ታምራትን ደግሞ ማመስገን ይወዳል፡፡
ታምራት ወደ ሚድያ እንዴት መጣ?
ይበቃል ጌታሁን እና ታምራት ገብረጊዮርጊስ ካዛንቺስ መናኸሪያ አካባቢ አደጉ፡፡ ይበቃል ስለ አብሮ አደጉ ታምራት ሲገልጽ ‹‹…. ታምራት በህብር መፅሄት የስራ ጅማሮውን አደረገ፡ ቀጥሎም በ1985 ዓ.ም ወደ ጦማር ጋዜጣ አቀና፡፡ ገና በታዳጊነቱ ነገሮችን የሚያይበት እይታ የተለየ ነበር ። ለጓደኞቹ ሰላነበባቸው መፃሃፍት እና ስላጋጠሙት ጉዳዮች ሲያስረዳ ልዩ ክህሎት ነበረው፡፡›› በማለት የታምራት የታዳጊነት ህይወት በአንባቢነት የተሞላ እንደነበርም ትዝ ይለዋል፡፡
ታምራት ህብር መጽሄት እና ጦማር ጋዜጣ ላይ ከሰራ በኋላ በ1988 ዓ.ም ሶስት ሆነው የከፈቱትን ኢንተርፕረነር ጋዜጣን እውን አደረጉ፡፡ ጋዜጣው ባለ ስምንት ገፅ እንደነበር እና በውስጡ ዜናዎች፣ አርቲክሎች ፣ የተለያዩ ሁነቶችን የሚያሳይ ጋዜጣ ነበር። ‘’ታምራት ለዚህ ስራ ተሰፍቶ የተሰጠ ነው ለስራው ፍላጎት ያለው ነው እራሱን ፕሮፌሽናል ያደረገ እና ለሚድያ መሪ ነው አስተማሪም ነው ‘’ ይለናል። ይበቃል፡፡ ኢንተርፕረነር ለ 2 አመት እንደቆየ በነገሮች አለመመቸት እንደተቋረጠ እና በወቅቱም ለትንሽ ግዜ የኢትዮጵያ ንግድ ቻምበር ጋዜጣ ላይ ታምራት ሰርቷል፡፡
ታምራት አሜሪካን ሀገር የአጭር ጊዜ ስልጠና መውሰዱ በሙያው ላይ ትልቅ ስራ እንዲሰራ መሰረት አስቀምጦለታል፡፡ ታምራት በ1991 ካፒታል ጋዜጣን ከአቶ ክቡር ገና ጋር በጋራ የጀመረ ሲሆን ከአንድ ዓመት ከስድስት ወር በኃላ ግን ካፒታልን ትቶ ፎርቹንን አንድ ብሎ ጀመረ፡፡
የፎርቹን ጋዜጣ ውልደት ታምራትን ደስ ያሰኘ ነገር ነበር፡፡ ታምራት ቀድሞ አብረውት ይሰሩ የነበሩ ጋዜጠኞች በመያዝ ፎርቹን ጋዜጣን መመስረት ችሏል፡፡ በዚያን ወቅት ፎርቹን ሲመሰረት የነበሩ ባለሙያዎች ይበቃል ጌታሁን፤ ሚኪያስ ወርቁ ፤ መላኩ ደምሴ ፤ ሜሪ ደጀኔ ፣አበበ ታደሰ ይጠቀሱ ነበር፡፡ ይበቃል በፎርቹን ውስጥ በግራፊክስ ዲዛይነርነት የስራ መደብ ያገለግል ነበር፡፡ ይበቃል እንደሚለው የስራ ባልደረቦቹ ወደ ፎርቹን መምጣታቸው እና የራሳቸውን ስራ መጀመራቸው ትልቅ ነገር እንደነበር ይገልጣል። የመጀመሪያዎቹ እትሞች በሚወጡ ሰዓት አልጋ በአልጋ እንዳልነበር የሚናገረው ይበቃል በጥረት እና በብዙ ድካም ወደመልካም መንገድ መምጣታቸውን ይገልጻል ። የመጀመሪያ የሰራተኞች ደሞዝ ከ700 እስከ 1500 ነበር። ታምራት በሙያው ላይ በፊት ከነበረበት የህትመት ስራዎቹ በተለየ ፎርቹን ላይ ጨምሮ መስራቱን ይነግረናል።
የመረጃ ጥልቀት እና ታምራት
ኢሳያስ መኩሪያ በአሁኑ ሰአት መልህቅ በሚል ርእስ በኣራዳ ኤፍ ኤም ላይ በቢዝነስ ላይ ያተኮረ የራሱን ፕሮግራም በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
‘’ታምራት ለእኔ የህይወት መሰረቴ እና በጋዜጠኝነት ህይወቴ ላይ ያሳደረው ተፅእኖ ቀላል አይደለም’’ የሚለው ኢሳያስ መኩሪያ ከታምራት ገብረ ጊዮርጊስ ጋር በአንድ ሰፈር አብረው ያደጉ እና በተለይም በሁለቱም ዘንድ የስነ-ጽሁፍ ፍቅር የነበራቸው ሰዎች ስለነበሩ ለመቀራረቡ እንዳገዛቸው ኢሳያስ ይናገራል። በጊዜው ታምራት የተለያዩ ፅሁፎችን እና የትርጉም ጽሁፎችን ለህትመቶች በመስጠት ሙያዊ ፍቅሩን ይወጣ ነበር፡፡ ኢሳያስም ደግሞ በኢትዮጵያ ሬድዮ ይሳተፍ ነበር ። ታምራት ጥሩ የስነጽሁፍ ሰው፣ ጥሩ አንባቢ፣ ብዙዎች የማይደፍሩትን መፅሃፍ አንብቦ የሚተረጉም ሰው እንደሆነ ኢሳያስ ያስታውሳል፡፡ ታምራትና ኢሳያስ ወደሙያው በሚገቡበት ግዜም አንድ አይነት ዝንባሌ ስለነበራቸው ይበልጡኑ መቀራረባቸውን ያነሳልናል። በጋራ የተሳተፉብት ‹‹ህብር›› መፅሄትም ላይ በአዲስ አበባ ስቴዲየም ውስጥ አንድ ብር ለአንድ ወገን የተሰኘ ፕሮግራም መሳተፋቸው ወዳጅነታቸውን አጠንክሮታል፡፡
በ1993 ዓ.ም ወደ ፎርቹን እንደገባ የሚያስታውሰው ኢሳያስ ነገሮች ቀላል እንዳልነበሩለት አይዘነጋውም፡፡ ታምራት ለእኔ በእድሜም በሙያም ቀድሜው ልጀምር እንጂ አስተማሪዬ ነው፡፡ ጋዜጠኝነት ምን እንደሆነ ያስተማረኝ ያሰለጠነኝ ታምራት ነው፡፡አሁንም ድረስ እንደምናገረው እኔ ጋዜጠኛ የሆንኩት ፎርቹን ስገባ ነው፡፡ ጋዜጠኛ እንድሆን ቀርፆ ያወጣኝ ታምራት ነው ‘’ ይላል ኢሳያስ።
ታምራት ጋዜጠኞቹን ለማሰልጠን ብዙ ርቀት እንደሚሄድ ይነገርለታል፡፡ አንድ ሰው ጋዜጠኝነት የእንጀራ ስራ እንዳልሆነ የሚያውቀው ከታምራት ጋር ሲሰራ ነው፡፡
ኢሳያስ 20 አመት ወደ ኋላ መለስ ብሎ ሲነግረን እንደሚለው…..
‘’ ታምራት በጣም አጭር ሰዓት እየተኛ ነው የሚሰራው፡፡ ይህም ጠንካራ ሰውነቱን የሚናገር ነው፡፡ እርሱ ጋር ያሉት መረጃዎቹም ጥልቀት ያላቸው በመሆኑ ማንም መማር ይችላል፡፡ መረጃን እንዴት በተን በተን አድርገን ነገሮችንም በየትኛው ጎን መመልከት እንዳለብን በየሳምንቱ ያስተምራል’’ እያለ ኢሳያስ ትውስታውን ይነግረናል።
የታምራት የኤዲቲንግ መንገዱ ሃሳቦችን ዜናዎችን በጥልቀት የማየት ችሎታው በብዙዎች ይደነቃል፡፡ ኢሳያስ ታምራትን ባለውለታዬ ይለዋል፡፡ በጋዜጠኝነት ት/ቤት ሲያስተምር ማየትን እናፍቃለሁ ሲልም ለታምራት መልካሙን ሁሉ ተመኝቶ ኢሳያስ ሀሳቡን ይቋጫል፡፡
ጦማር- ታምራት
በፈቃዱ ሞረዳ በአሁኑ ሰአት በአሜሪካ የሚኖር የታምራት የቅርብ ወዳጅ ነው፡፡ ታምራት እና በፈቃዱ ትውውቃቸው 1985 ላይ አንድ ይላል፡፡
በጊዜው በ1985 ዓ.ም በፈቃዱ የህብር መጽሔት ዋና አዘጋጅ ነበር፡፡ ታምራት ደግሞ ለመጽሔቱ ጽሑፍ ያቀርብ ነበር፡፡. በፈቃዱ እንደሚያስታውሰው በዚያን ጊዜ ታምራት የግርሀም ሀንኮክ ታቦተ ፅዮንን ፍለጋ የተሰኘውን ጽሑፍ ወደ አማርኛ እየተረጎመ ያቀርብ ነበር፡፡ በጊዜው ታምራት አስራ ሁለተኛ ክፍልን የጨረሰ ተማሪ ቢሆንም የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታው ድንቅ እንደ ነበር በፈቃዱ ያስታውሳል፡፡
ትውስታውን ሲቀጥልም ‘’ ህብር ላይ አብረን ስንሰራ ቆይተናል፡፡ እንደ ህብር ያሉ በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ መጽሔቶች ገበያቸው እየቀነሰ ሲሄድ ጋዜጣ መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን ከተወያየን በኋላ እኔ እና እሱ ተቀምጠን የጋዜጣ ስም መረጣ ውስጥ ገባን፡፡ ጥቂት ስሞችንም አቀረብኩኝ፡፡ ከእነዛ ስሞች መካከል ጦማር ይሻላል ያለው ታምራት ነበር፡፡
በአንድ ወቅት አራት የጦማር ጋዜጣ ባልደረቦች ከርቸሌ ወርደው እንደነበር እና ታምራትም ታስሮ እንደነበር በፈቃዱ አይዘጋውም፡፡ ከአራቱ ውስጥ አሁን ላይ በህይወት የሌለው ሀብታሙ ውበቱ ፣ ዛሬም ሪፖርተር ጋዜጣ ውስጥ ሁነኛ ሰው የሆነው መላኩ ደምሴ አብረው ነበሩ። ታምራት እና በፈቃዱ ከማእከላዊ ምርመራ እስከ ከርቸሌ መራራ ትዝታ አሳልፈዋል፡፡
በፈቃዱ ስለ ታምራት ትዝታውን ሲያወጋ ‘’የያኔው ታምራት ወጣት ሆኖ ፍቅርን ሀገርን ቤተሰብን በተመለከተ የነበረውን አንዳንድ ሐሳቦችን አልቀበለውም ነበር.፡፡ አሁን ላይ ወደ ኋላ ተመልሼ ሳስባቸው ልክ እንደነበር ተረድቻለሁ፡፡ ቀድሞኝ የበሰለ ሰው እንደሆነ ተገንዝቤያለሁ.’’ ይላል። የጦማር ሰዎች ለሁለት ከተከፈሉ በኋላ ወዳጅነታቸው እንዳልተቋረጠ የሚናገረው በፈቃዱ ‘’በዚህ ዘመን አሉኝ ከምላቸው ወንድም ጓደኞቼ መካከል አንዱ ታምራት ገብረጊዮርጊስ ነው፡፡ ታምራት በኢትዮጵያ የግል ወይም የነፃ ፕሬስ ታሪክ ውስጥ ፋና ወጊ ከሆኑት ጋዜጠኞች እና ኢንተርፕረነሮች መካከል አንዱ ሆኖ ሥራው ለዘላለም አሻራውን ጥሎ የሚኖር ሰው ነው።’’ በማለት በፈቃዱ ሀሳቡን ሰንዝሮ ነበር፡፡
አየነው ሃይለስላሴ የፎርቹን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆኖ አገልግሏል፡፡
ታምራትን ከ1995 ጀምሮ ያውቀዋል፡፡ ታምራት ለጋዜጠኝነቱ ያበረከተውን አየነው ሲናገር ‘’በመጀመሪያ ደረጃ ፎርቹንን ማበርከቱን ያሰምርበታል፡፡ በመቀጠል ታማኝ የሆኑ በደንብ ምርመራ የተደረገባቸውን ትክክለኛ መረጃ ያላቸውን ሃሳብ ያላቸውን ዘገባዎችን በመስጠት የሚታወቅ ጋዜጣን ፈጥሯል፡፡ ሲል ይህም ለኢትዮጵያ ሚድያ ትልቅ ውለታ ነው ይላል፡፡
ፎርቹን ላይ ጥልቅ ሀሳብ ያላቸው ፅሁፎች እንዲሁም የፊቸር አርቲክሎች በከፍተኛ ጥረት ታትመው ይወጣሉ፡፡ አንባቢዎች ፎርቹንን በጉጉት ይጠብቃሉ፡፡ በተለይ ደግሞ የንግዱ ህብረተሰብም ለፎርቹን ልዩ ግምት ነበረው፡፡
ለጋዜጠኝነት ጉጉት ያላቸው ሰዎች እራሳቸውን ለማስተማር ከፎርቹን ትልቅ እድል አግኝተዋል፡፡ አንዴ ፎርቹን ገብተው ከወጡም በኋላም ጥሩ ትምህርት ስለሚቀስሙ በሄዱበት መስሪያ ቤት ሁሉ ፈርጣማ አቅም ይዘው ብቅ ይላሉ፡፡
ታምራት የጋዜጣ ዋና አዘጋጅ በሚኮንበት ወቅት ሁል ጊዜ ሰው ላይ ጥገኛ መሆን አያስፈልግም ባይ ነው፡፡ ያልታሰበ ችግርም በሚያጋጥም ሰዓትም ሁሉንም ሰው ሸፍኖ የመስራት ችሎታ ያስፈልጋል ሲልም በተደጋጋሚ ያነሳ ነበር፡፡
አየነው እንደሚለው የታምራት ትልቁ ችሎታው እና የሚደነቅለት ለጥራት ቅድሚያ መስጠቱ ነው፡፡ ታምራት ሀሳብ እና ጉዳይ ላይ ቅድሚያ ይሰጣል፡፡
የእንግሊዝኛ ቋንቋ አፍ መፍቻቸው ወይም ቋንቋውን አቀላጥፈው የሚናገሩትን ሰዎች እንደ ኮፒ ኤዲተር አድርጎ ታምራት በብዛት ይቀጥር ነበር፡፡ ይህም የጋዜጣውን ደረጃ ከፍ እንዳደረገው ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ታምራት ጋር ሲሰሩ ቢሮ እያደሩ መስራት የተለመደ ነበር፡፡ ይህም ጋዜጠኞቹ የስራ ጫናን ተቋቁመው እንዲሰሩ ለወደፊት ህይወታቸውም እንዲጠነክሩ በር ከፍቶላቸዋል፡፡
አቶ አየነው ቢሮ የማደሩን ጉዳይ ሲያነሳ እንዲህ ይላል‹‹….አብዛኛው ሪፖርተር ቢያንስ ሁለት ቀን ወይም ሶስት ቀን ቢሮ የሚያድርበት እና ስራውን በወቅቱ ጨርሶ የሚያስረክብበት ሁኔታ ነበር››
ፎርቹን ቢሮ ውስጥ የብዙ ሃገር ጋዜጦች ነበሩ፡፡ የጋዜጣው ዲዛይነሮች በከፍተኛ ጥራት ዲዛይኑን ማምጣት ቢያቅታቸው ካሉት ጋዜጦች አገላብጠው ጥሩ የሆነ ዲዛይን ማውጣት እንዲችሉ ይደረግ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ በታምራት ድንቅ አመራር አማካይነት የተገኘ የስራ ብሂል ነው፡፡
አየነው ስለ ታምራት እና ስለ ፎርቹን ሲናገርም ‘’ታምራት ፎርቹን ጋዜጣን ሲጀምር ሁል ጊዜ ቀዳሚ የነበረው ፎርቹን እንደ ነበር አልጠራጠርም፡፡ በማንኛውም ሰዓት ለፎርቹን የሚሆን መረጃ ለማግኘት ባለቤት ነኝ ሳይል ከሪፖርተሮች እኩል እንቅስቃሴ ሲያደርግ ነበር፡፡ ፎርቹን ውስጥ ቀዳሚው ነገር ሁሌም ስራ ነው። እውነተኛ ፤ ሚዛናዊና አስተማማኝ መረጃዎችን ለአንባቢ ለማቅረብ ሁል ጊዜም ይለፋል፡፡እንዲህም ሆኖ በብዙ ጥረት በብዙ ድካም የተሰሩ ታሪኮች ጥራታቸው ሳይሟላ ይቀርና ሳይታተሙ ይቀራሉ፡፡ ይህም ጋዜጣው ለአንባቢ ያለውን ጥልቅ ታማኝነት የሚገልጽ ነው፡፡›› በማለት ሀሳቡን ገልጾ ነበር፡፡
አየነው ፎርቹንን ሲገልጸው እንደ ፀሃፊም እንደ ኤዲተርም ያደገበት ይህም ዛሬ መለስ ብሎ ሲያስበው ትልቅ የመንፈስ ርካታ እንደፈጠረለት ያስባል፡፡በፎርቹን አማካይነትም የተለያዩ የስራ እድሎችን ማግኘት ችሏል፡፡ በፎርቹን አማካይነት የስራን ዋጋ ተምሮበታል፡፡
የፎርችኑ ታምራት በቃለየሱስ በቀለ
"እሱ ጋር መስራት የጀመርኩት ጁላይ 2001 ላይ ነው። በእርሱ መሪነት የሚገርም ቲም ተፈጥሮ ነበር፡፡ በወቅቱ ጋዜጠኝነት የገባቸው መልካም ልጆች ነበሩ ሚኪያስ ወርቁ፣ መላኩ ደምሴ፣ ይበቃል ጌታሁን ፣ዳዊት ታዬ፣ ሜሪ ደጀኔ ፣ኢሳያስ መኩሪያ ናቸው። ታምራት ጋዜጠኝነትን በፍቅር የሚሰራ ነው፡፡ እራሱንም ብዙ ያስተማረ ነው። በጋዜጠኝነቱ ሙያ እራሱን ለማዳበር የተለያዩ ስልጠናዎችን ያገኘ ነው፡፡ አሜሪካ ሃገር በመሄድ ለወራት የወሰዳቸው ሁለት ኮርሶች የጠቀሙት ነገር ቢኖርም ታምራት ግን እራሱን በጣም አስተምሯል፡፡ ስለ አንባቢነት ካነሳን በጣም አንባቢ ነው ።በቅርበት የሚያውቁት ሰዎች ይሄን ባህሪውን ሊያውቁት ይችላሉ፡፡ ብዙ ሰው ደግሞ ላያውቅ ይችላል፡፡
ታምራት ቤቱን ያጣበበው መፅሀፍት ነው፡፡ መኪናው ውስጥ መፅሃፍ አይጠፋም፡፡ ብዙ ጊዜ በሹፌር ይንቀሳቀስ ነበር፡፡ ይሄን የሚያደርገው አንድም ስልክ ለማውራት ነው፡፡ አንድም ደግሞ መፅሃፍ ለማንበብ ነበር።
ታምራት ጋዜጠኝነትን የጀመረው ከሪፖርተርነት ነው ። ዜና መፃፍ ፣ ፊቸር፣ አርቲክሎች መስራት፣ ኤዲት ማድረግ ታምራት ሁለገብ ነው ። እነዚህን ብቻ ሳይሆን የጋዜጣን የንድፍ ስራ ይሰራል ጋዜጣን ዲዛይን ሲያደርግ በጣም ጎበዝ ነው። እንደገና ጋዜጣን ሰራው ፅፌ ጨረስኩ ብሎ ቢሮ አይቀመጥም፡፡ ማተሚያ ቤት ሄዶ የህትመት ሁኔታውን ሁሉንም ይቆጣጠራል ። የጋዜጠኝነትን ሙሉ ስራ በህትመት ጋዜጠኝነት ላይ ከሃ እስከ ፐ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ይህ የሱ የተለየ ብቃቱ ነው፡፡
ታምራት በጋዜጠኝነት ላይ ጠለቅ ያለ እውቀት የጨበጠ ነው፡፡ ሰፊ ተሞክሮም አለው ። በርካታ አለም አቀፍ ስብሰባዎች ላይ በመሳተፉ ጋዜጣዋን አለም አቀፍ ቅርጽ እንድትይዝ አድርጓታል፡፡ በጉብዝናውና ታታሪነቱ የታወቀ ነው፡፡ ኮምፒተር ላይ እስኪወድቅ ከእንቅልፉ ጋር ታግሎ ነው የሚሰራው። በግሌ ከሱ ጋር መስራት ስልጠና ነው፡፡ ዜና እንዴት እንደሚገኝ ፣የዜና ምንጮች በምን አይነት መልኩ ከእጅ ማስገባት እንደሚቻል የአፃፃፍ መንገዱን ሁሉንም ያስተምራል ። ከዚህ ባለፈ ስልጠና ሲኖር እንድንሰለጥን እድል ይሰጠን ነበር። በሙያው ምንም የሚወጣለት ነገር የለም፡፡ ጎበዝ ጋዜጠኛ ነው ። አንድን ነገር የማያምን በጣም ተጠራጣሪ ሁሌም ግራ ቀኙን ታይቶ ዘገባ እንዲሰራ የሚያደርግ ነው። በዛው ልክ ደግሞ ሃይለኛም ነው፡፡ ስህተቶችን የማያልፍም ነው። በቢዝነስ ጆርናሊዝም በብዛት እንደመስራቱ መጠን የቢዝነስ ጋዜጠኝነት አባት ነው። አሁን ላይ ይሄን ስራ የሚሰሩት አብዛኞቹ ፎርቹን የሰሩ የታምራት ግርፍ ናችው። ታምራት እና ጓደኞቹ በዛን ወቅት የቢዝነስ ጆርናሊዝም ጀማሪ ናቸው ። በወቅቱ የጋዜጠኝነት ዘርፍ እንደሆነም አይታወቅም ነበር፡፡ ፅንሰ ሃሳቡም አልነበረም ነበር። በታምራት አስተባባሪነት ካፒታል ጋዜጣን ፣ኢንተርፕረነርን ፣ፎርቹንን የጀመሩት እነሱ ናቸው። ቢዝነስ ጆርናሊዝም በሚል በስፋት ከጓደኞቹ ጋር ሆኖ የሰራው ለዛ ነው።
በግሌ ለኔም ሆነ አጠቃላይ ለሙያ አጋሮቼ እንዲሁም ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ቢዝነስ ጆርናሊዝም እንዲሰርፅ እንዲስፋፋ ላደረገው ከፍተኛ አስተዋፅኦ አመሰግነዋለሁ።"
ዘሪሁን አሰፋ የራሱን የግራፊክስ ተቋም የከፈተ ባለሙያ ሲሆን የተወዳጅ ሚድያ ሁሉንም የህትመት ስራዎች በጥራት በማከናወን ይታወቃል ።ስለ ታምራት የሰጠውን አስተያየት እነሆ ።
ታምራት ቁጡ የሆነው ስለእኛ ነው
ታምራት ስለ ቲፖግራፊ፣ ማስታወቂያ እና ሌሎች ዕይታዊ ጥበብ ግብአቶች በሚገባ ያውቃል። እኔና ታምራትን ያገናኘን ወዳጄ ኤፍሬም ክረምቱ ሲበረታ ነሀሴ ወር 1996 ዓ.ም. ነበር፡፡ አንድ ዕለት ወደ ቢሮው አቀናን፡፡ “ምን ልርዳችሁ ብሎ” በታላቅ ትህትና ተቀበለን፡፡ እኔም ሌይአውት ዲዛይነር መሆን ፈልጌ ነው የመጣሁት አልኩት፡፡ በእኔ ለሥራው አዲስ መሆን፣ የምርቃት መጽሔት ዋና አዘጋጅ ሆኖ መስራትም ሳይሆን በሌሎች የራሱ መመዘኛ ተመለከተኝና ነገ መጥተህ ጀምር አለኝ፡፡ በወሩ የመጀመሪያ ደመወዝ 600 ብር አገኘሁ፡፡ ታምራት ስለ ቲፖግራፊ፣ ስለህትመት ሥራ፣ ማስታወቂያ እና ሌሎች ዕይታዊ ጥበብ ግብአቶች በሚገባ ያውቃል (Cover design, Title and body text balance, Left out quotes, Teaser, illustrations, photojournalism, press photo, mug shot, Business and Finance tables and graphs, New site plan, perspective view, etc.) ታዲያ ታምራት ስቲቭ በተባለ አሜሪካዊ የእንግሊዝኛ ሌክቸረር አማካሪነት የዲዛይን ፍልስምና መጽሔት በመስራት የጀመረን ወጣት ዘሪሁን አሰፋን ተቀብሎ በወንድምነት በሀገሪቱ አንደኛ የሆነ ጋዜጣ ላይ የመስራት እቅዱን አሳካለት፡፡ እኔም ከሥር ከሥሩ እያልኩ ብዙ አተረፍኩ፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ለመጣ የሌይአውት ዲዛይን፣ አጻጻፍና ፕሬስ ፎቶግራፊ ሥልጠና ግብዣ ደብዳቤውን አስይዞ ላከኝ፡፡ ቀን ቀን በሥልጠናው ላይ ውዬ ቀለል ያሉ ገጾችን ደግሞ ማምሻውን እየሰራሁ የአውሮፓውንም የዲዛይን ፍልስምና ጠግቤ አጠናቀኩ፡፡ የራሴንም መንገድ እንድይዝ በህይወቴ ትልቁን ዕድል የሠጠኝ ሰው ነው ታምራት፡፡ የህትመት ሥራን ሱስ አጋባብኝ፡፡ እንደማውቀውም ለሌሎችም ተመሳሳይ ትልቅ አስተዋጽዖዎችን እንዳደረገ አውቃለሁ፡፡ በእርጋታ መፍጠን እንደሚቻልም የተረዳሁት ከእርሱ ነው፡፡
ታምራት ቁጡ የሆነው ስለእኛ ነው።ታምራትን ቁጡ ያደረገው የብዙዎቻችን የሥራ ትጋትና ለሙያው ብቁ አለመሆናችን ነው፡፡ እኛ ያደግነው በቀስቃሽ አንደበት እንዲህ አድርግ፣ ይህን ተመልከት፣ በዚህ ግባ በዚህ ውጣ እየተባልን ስለሆነ በራሳችን ጊዜ በተገቢው ሰዓትና ሁናቴ ሥራችንን አናደርስም፡፡ በወቅቱ የነበሩት አንጋፋ ጋዜጠኞች ዜናቸውን የሚጽፉት በአማርኛ ነው፤ አሳይመንት ኤዲተሮቹ ከእነርሱ ይቀበሉና ወደ እንግሊዝኛ ይተረጉሟቸዋል፡፡ ማኔጂንግ ኤዲተሩ ታምራት ጋ ለመድረስ ስንት መንገዶችን አልፈው ነው፡፡ ታምራትም ከኤዲተሮቹ ጋር ብቻ ሳይሆን ከምንጩ ባለቤት ጋዜጠኛ ጋር የግድ መገናኘት አለበት፡፡ በመሀል ለሁለትና ለሦስት ቀናቶች ጋዜጠኞቹ ከአሁን አሁን ተጠራሁ እያሉ አምሽተው ያነጉ ነበር፡፡ ብዙ ጊዜም ታምራት ጠረጴዛ ላይ ድፍት ብሎ ያድራል፡፡ ይህ ሂደት ታዲያ ብዙ ጊዜ ሥራውን ወደ ኋላ ይመልሰዋል፤ መረጃውን ለማጣራት፤ ተጨማሪ ባክግራውንድ ለመጨመር ብዙ ይደክማል፣ የራሱንም የሙያ ልህቀት ዘወትር ስለሚጠብቅ፣ የጋዜጣውንም ደረጃ ስለሚመለከት በቀላሉ ነገሮችን አያልፍም፡፡ ከእሱ እጅም እስኪወጣ በሚወስደው ጊዜ ምክንያትም ሥራው ይጓተታል፡፡ ታዲያ ታምራት በእነዚህና በሌሎችም የግሉ ንጻሬ አኳያ ይቆጣል፤ በአንድ ወቅት የአንዱን ትልቅ ጋዜጠኛ የግል ተንቀሳቃሽ ስልክ ወርውሮ ከግድግዳ ጋር ሲያላትምና ሲሰባበር ተመልክቻለሁ፡፡ ያገኘውን የቢሮ መገልገያ አንስቶ እመሬት ሲፈጠፍጥ አይቻለሁ፡፡
ከጂብ ጋር መፋጠጥ፣ የማምሸት ዳፋ
አንድ ዕለት የሆነውን በአስረጂ ላምጣ፡፡ ቀኑ አርብ ዕለት ነበር፡፡ ሁሉም በየፊናው ያለውን አከናውኖ አምሽቶ ወጥቷል፤ ሰዓቱ 6፡30 ለሊት ነው፡፡ መኖሪያዬ ጉርድ ሾላ አካባቢ ነበር፡፡ ከሚያደርሰኝ ባለ ላዳ ታክሲ ጋ ወርጄ ወደ ቤቴ ሳቀና የሆነ ጥላ ውልብ አለብኝ፤ በጨለማው መካከልም ግዙፍ አካል በዓይኑ አበራብኝ፤ ደነገጥኩ፡፡ ትልቅ ጅብ፡፡ መንገዱ ግራ ቀኝ የለውም፡፡ ወይ ወደ ፊት አሊያም ወደ ኋላ፡፡ ፈራሁ! በጥቂት ሜትሮች ልዩነት እሱም እኔም ቀጥ ብለን ተፋጠጥን፡፡ ድንገት፣ ከኋላዬ የሰዎች ኮቴ ተሰማኝ፡፡ ዳናው እየቀረበኝ ሲመጣ የልቤ ምት ተረጋጋ፡፡ ከቡና መፈልፈያ ኢንዱስተሪዎች የሚወጡ ሠራተኞች ናቸው፡፡ ሴቶች በርከት ብለው ወደ እኔ ቀረቡ፡፡ አጅሬም የሴቶቹን ድምጽ ሰምቶ ወደ ኋላ እያነከሰ ተፈተለከ፡፡ እኔም ወደ ቤቴ በውጥረት ገባሁ፡፡ በነጋታው ተሾመች ክትፎ ቤት ጋ ወደነበረው ቢሮ ስንደርስ የቢሮ ኮምፒዩተሮች የሉም፡፡ ማን ወሰዳቸው… ትርምስ ሆነ፡፡ ሥራ አስኪያጁ ተረበሸ፣ ዘበኞቹም ተደናገጡ፤ ሌሎች ዕቃዎችም ጠፉ ተባለ፡፡ ቆየት ብሎ ታምራት ሆዬ በወቅቱ በነበረው መኪና ይዞት ተመለሰ፡፡ በኋላም በሥራው ሂደት ደስተኛ ስላልነበረ ያደረገው እንደነበረ አወቅን፡፡ ታምራት ቁጡ የሆነው ስለእኛ ነው፡፡ ይህ እውነት ቢሆንም እንኳን እሱ ሥራዎቹን ለሌሎች በመሥጠት ለማሰራት የሞከራቸው ፕሮፌሽናል መንገዶች አላስኬዱት እንደሆነ እርግጠኛ ባልሆንም ከጽሑፍ፤ ፎቶ፣ ማስታወቂያ እስከ ህትመትና ስርጭት ድረስ የሚገባበት ሁናቴ ይገርመኝ ነበር፡፡ በእኔ ዕሳቤ የምቀይረው ከሌለ፤ የዚህ ሂደት መፋለስ አካል መሆንን ስላልፈለግሁ እና ለሦስት ቀን ውሎ ማደርን ውስጤ ስላላመነበት በጤናዬ ሁናቴ የሚያማክረኝ ሐኪምም ስላልተቀበለው “በአስቸኳይ ወስን” አለኝ፡፡ እኔም ከአምስት ወራት በላይ ቆይቼ በወደረኛ ምክንያቶች ከፎርቹን ወጣሁ፡፡ እስከ አሁንም ይህን ጀግና በክብር ተሰናብቼው ባለመውጣቴ አዝናለሁ፡፡ ታምራት ራሱንና ጋዜጣውን ከፍ አድርጎ ያበራል።በታምራት ፎርቹን ሥራዎች በጊዜ እንዲጠናቀቁና ማንም ከቢሮ እንዳይርቅ ቅዳሜ በምግብ ሰርግና ምላሽ ነው፡፡ ምሳ ላይ ሜኑ ይመጣና ማንም የፈለገውን አዝዞ ሲሰራ ውሎ ሲሰራ ያድራል፡፡ ታምራትም አብሮ ሲመገብና የጋራ ነገርን በመፍጠር ድንቅ ነው፡፡ በእነዚህንና በሌሎች መልካም ሥራዎቹ፣ በታታሪነቱና በሥራው ልዕልና የፎርቹንን ታግ ላይን በሁሉም ልብ ላይ ያትምና የጋዜጣው ጠበቃ አድርጎ ከውስጥ በምቾት ያስቀምጣል፡፡ እሱ ጋር የሰራ ሁሉ ለዚያ ነው “ፎርቹን! ፎርቹን!” የሚለው፡፡ እኔ፣ አሁን በእርሱ ዕድል ምክንያት ተርታ ሰው አይደለሁም፡፡ በህትመቱም ሆነ በሌሎች ዕይታዊ ጥበቦች እየደመቅሁ አለሁ፡፡ ዛሬ ወደ 20 ዓመት ሊጠጋን ሆነ ታምራትን ካየሁት፡፡ እሱ! አሁንም ራሱንና ጋዜጣውን ከፍ አድርጎ ያበራል፡፡ የልጆች አስተዳደግ ላይ የሚሠሩ የሥነ-ልቡና ባለሙያዎች “ሄሊኮፕተር የሆነ ቤተሰብ መልካም አይደለም” ይላሉ፡፡ ይህንን እውነታ ታዲያ ከሥራ አንጻር ሳጣቅሰው ታምራት ለዚህ አገር ጋዜጠኝነት በሆነው ልክ ተወድሶ፣ ተመስግኖና አርፎ እየኖረ ባየው ደስ ይለኛል፡፡ አቻ አጣሁለት በእውነት፡፡ ራዕይ አይሞትምና ፎርቹን መቶና ከዚያ ዓመት በላይ ቢኖር ብዬ እመኛለሁ፡፡
ታምራት በሉሊት መነጽር
ሉሊት አምደማርያም በፎርቹን ጋዜጣ ላይ በአምደኝነትና በዋና አዘጋጅነት የሰራች ሲሆን ታምራትን ስትገልጸው በኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት ከታዩት ያልተነገረለትና የሚገባውን ያክል እውቅና ያላገኘ ጋዜጠኛ ሳይሆን አይቀርም ትለዋለች፡፡
ጋዜጠኛ ታምራት ለበርካቶች መነሻ፣ መማሪያ እና የእድገት ምንጭ ሆኗል።
የእርሱ አበርክቶ ማንም ልብ ያላለውና እውቅና ያልሰጠው ግን ደግሞ በበርካቶች ዘንድ የሚወሳ እንደግለሰብ ደግሞ ለኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች አባት ነው ጋዜጠኛ ታምራት።
ሉሊት ታምራት ለማወቅ ያለውን ጉጉት፣ የማይናወጥ ፍላጎቱን እና ለመማር ያለውን ፍቅር ስትገልጽ እነዚህም ምርጥ የእርሱ ባሕርያት መገለጫዎቹ ናቸው ትላለች።
ሉሊት ሀሳቧን በወጉ ስታብራራም ‹‹…..ሁልጊዜም ቢሆን የተደበቁ፣ የሰዎችን ፍላጎት የሚስቡና ስሜታቸውን ሰቅዘው የሚይዙ ብቻ የሚሰራውን ነገር የሚያሻሽሉና ውጤታማ የሚያደርጉትን እና ዕውቀቱን የሚያሰፉለትን ብሎም የእሱን ፍላጎት በአግባቡ እንዲተገበር የሚያደርጉለትን አዳዲስ ነገሮችን ለማወቅ ይተጋል። ይህ የእርሱ ሃብቱ ሲሆን የእሱን ተደራሽነትም ያሰፋለታል። ጋዜጠኛ ታምራት ካስፈለገ ኤዲተር፣ ዲዛይነር፣ ወይም በመደበኛ ጋዜጠኝነት ሲሰራ ሊታይ ይችላል፤ ምክንያቱም ይህ የእርሱ ልዩ መገለጫው ነውና። ከሀላፊነት ይልቅ እርሱ በቦታው ተገኝቶ የሚዘግበውን ዜና በመረዳት የሚደሰት አይነት ሰው ነው። በተፈጥሮው እሱን ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ ሌሎች የእሱን አስተዋይ አዕምሮና አስተሳሰብ ተጠቅመው የበለጠ እንዲማሩና እንዲያውቁ የሚያስችል ጥልቅ እውቀት ይፈልጋል፤ለዚህ ደግሞ ከእኔ በላይ ምስክር ያለ አይመስለኝም። እኔ ዛሬ ላይ ያለሁበት ቦታ ትናንት ከእርሱ ጋር በመስራት ያገኘሁት ትምህርትና የቀሰምኩት ዕውቀት ውጤት ነው፤ በአጭር ቋንቋ እኔ የእርሱ የትናንት የእጅ ስራ ነኝ ብል ማጋነን አይሆንም፡፡
የዛሬ
እኔነቴ ትናንት በእርሱ ተቀርጿልና። በርካቶች ከእርሱ ባገኙት ዕድል ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ለበርካቶችም የዕድገት ምንጭ ሆኗል፤ ለዚህ እኔም ምስክር ነኝ። ከእርሱ ጋር ያሳለፍኩት ጊዜ አንዳንድ ጊዜ ፈታኝ ቢሆንም እጅግ ጠቃሚው የህይወቴ ክፍል ነበር፡፡ ያን ጊዜ ሳስብ የሚሰማኝ ከረጅም አድካሚ ጉዞ በኋላ የማገኘውን እፎይታና የጉዞየ መልካም ትዝታዎች ናቸው ምክንያቱም በብዙ አትርፌበታለሁና።›› ብላለች፡፡
ፈቃዱ በሻህ ታምራትን ላለፉት 25 አመታት ያውቀዋል፡፡ ፈቃዱ በአሁኑ ሰአት በሄኒከን ኢትዮጵያ በሚድያ ይዘት ዝግጅት በኃላፊነት ላይ ያለ ሰው ነው፡፡ በፈቃዱ እይታ ታምራት በስራው ላይ ቀልድ አያውቅም፡፡ አንድን የዜና ጽሁፍ 5 ሰአት አደርሳለሁ ካለ 5 ሰአት ግድ ነው፡፡ ይህንኑ ከጋዜጠኛው ይጠብቃል፡፡ በፈቃዱ አባባል ይህ የታምራት ትልቁ ጠንካራ ጎኑ ነው፡፡
ታምራት በፈቃዱ በሻህ አንደበት
‹‹ ታምራት ለአንባቢው ግድ የሚለው ሰው ነው፡፡አንባቢው መረጃ እንዲቀርበት አይፈልግም፡፡ የተናገሩት ሰዎች ተአማኒ እና ለጉዳዩ ትክክለኛ ሰው መሆናቸውን ማረጋገጥ ይፈልጋል፡፡ ታምራት ብዙ ያነበበ ነው፡፡ እና ጋዜጠኛው በሚጽፈው ዜና ላይ አንዳች ቁምነገር ጠብ የማድረግ ልዩ አቅም አለው፡፡ እኔ በሙያዮ እስከ ማስተርስ ተምሬአለሁ፡፡ በሙያውም ላይ ለ30 አመት በላይ ቆይቻለሁ ከዜና ጀምሮ እስከ ዘገባ አጻጻፍ ድረስ ታምራት ብዙ የማስተማር ችሎታ ያለው ሰው ነው፡፡›› በማለት ፈቃዱ በሻህ ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡
ታምራት የሪፖርተሮችን ጽሁፍ ከማየቱ በፊት ለጋዜጠኛ በቂ የሆነ ምሪት ይሰጣል፡፡ እንዴት ዜናው ሊሰራ እንደሚችልም መንገዶችን ያመላክታል፡፡ ፈቃዱ እንደሚለው ታምራት በቂ ሀሳብ ከሰጠ በኋላ ከጋዜጠኛው የተሟላ ታሪክ ይጠብቃል፡፡ ካልተሟላ ንቅንቅ አይልም በማለት የታምራትን ቁጥር አንድ ኤዲተርነት በይፋ ይመሰክራል፡፡
ፈቃዱ በሻህ ፎርቹን ሚዛናዊ ጋዜጣ መሆኑን ያምናል፡፡ እንደ ሄኒከን የስራ ሃላፊ አንድ መረጃ ስለ ሄኒከን ከወጣ ፎርቹን ሚዛኑን አስጠብቆ እንደሚያወጣው ፈቃዱ ያምናል፡፡ በመሆኑም ፎርቹንን እንደ አንባቢ እና ቀድሞ ፎርቹን ላይ እንደሰራ ሰው ሙሉ በሙሉ የምተማመንበት የህትመት ውጤት ነው ሲል ሀሳቡን ሰንዝሯል፡፡
በእንተ ታምራት ገ/ጊዮርጊስ ከአጥናፉ አለማየሁ
በእኔ አጠራር ከ[ልጅ] ታምራት ገ/ጊዮርጊስ ጋር የተዋወቅኹ ጦማር ጋዜጣ ላይ በሪፖርተርነት ከተቀጠርኩበት ሐምሌ 1985 ጀምሮ ነው፡፡
እንደማስውታሰው ጋዜጣው ላይ ከሚተታሙ አሥር፣ አሥራ አምስት ዜናዎች እኩሉ የታምራት ሲሆኑ ቆየት ብዬ ማወቅ እንደቻልኩት “ባህረ ነጋሽ” በሚል የብዕር ስም ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ጉዳዮችን ይጣጥፍ ነበር፡፡
በጊዜው ከመካከላችን ማለፊያ እንግሊዚኛ የሚናገረውና የሚጽፈው ታምራት፣ ዓለማቀፉ ሚዲያ ስለኢትዮጵያ የዘገበውን በመተርጎም ከሌሎች ጋዜጦች ይልቅ ጦማር የተሻለ ዕይታን እንዲያገኝ ያደረገው በእርሱ አስተዋጽዖ እንደሆነ አስባለሁ፡፡
በነገራችን ላይ በኢትዮጵያ የግሉ ፕሬስ ታሪክ፣ ፍርድ ቤት አሥራ አምስት ሺህ ብር የቀጣው የመጀመሪያው ጋዜጠኛ ታምራት መኾኑ ነው፡፡
ታምራት ከጦማር በኋላ በእጅጉ የሚታወቀው በፎርቹን ጋዜጣ መሥራችነትና አሳታሚነቱ ሲኾን በቢዝነስና ኢኮኖሚ ተአማኒ መረጃ እየሰጠ ከመገኘቱ ጋር ከርሱ ጋር የሠሩ ጋዜጠኞች ጠቃሚ ግንዛቤ እንዳገኙ የነገሩኝ አሉ፡፡
የኢትዮጵያ የፕሬስ ዐዋጅ እንዲሻሻልና ለዚሁ በተዘጋጁ የተለያዩ የውይይት መድረኮች ላይ ረቂቅ ዐዋጁ ማካተት ያለባቸው ጉዳዮች በተመለከተ፣ አበክረው ከተሟገቱና ከጻፉ ጋዜጠኞች አንዱ ታምራት እንደሆነ ይታወሳል፡፡
በኢትዮጵያ የሙያዊ ጋዜጠኝነት ክፍተት እንዳለ የሚያምነው ታምራት፣ በዚህ ረገድ በሀገራችን የሚስተዋለውን ሙያዊ ጉድለት አምርሮ ሲተች ይታወቃል፤ አሁንም እንደዚያው ነው፡፡
ተድባባ ጥላሁን ስለ ታምራት
'' ከታምራት ጋር እንደ ጓደኛ እና እንደሙያ ባልደረባ የጠነከረ ጓደኝነት መፍጠር ከጀመርን ከ 30 ዓመት በላይ ይሆናል። ታምራት ከጓደኛም በላይ የሚታይ ነው፡፡ ታምራት ነገሮችን ከተለያዩ አቅጣጫ እንዳይ የተሻለ አድማጭ፣ መራጭ አንባቢ እንድሆን ራሴን አካባቢዬን ሀሳቤን የሌላ ሰው እውነታን ነገሮችን በተሻለ መንገድ ማጤን እንድችል ያደረገኝ ነው። ለዚህም እወደዋለሁ፡፡.ለዘመናት አጥብቄ የያዝኩዋቸውን እውነቶችን እውነቶችህ እውነት አይደሉም ሳይለኝ እውነቶች እውነተኛ ያለመሆናቸውን የማይበትን ብርሃን ያሳየኝ አሁንም የሚረዳኝ ታምራት ነው ።በጣም ብዙ ነገር እናወራለን፡፡ ግን አንድ ቀንም ተሳስተሀል አይለኝም፡፡ ወይም ልክ አይደለህም አይለኝም፡፡ ልክ ያልሆንኩበትን መንገድ በማመልከት እራሴን እንዳይ ነው የሚያደርገው.።
ለእኔ ታምራት ዛሬ ላይ የደረሰው ተራማጅ ባህሪይ ስላለው ይመስለኛል፡፡አክራሪ እንዳልሆነ አውቃለሁ፡፡ አክራሪም አይደለም፡፡ በዚያው መጠን ስለ ምንም ነገር ባገኘው አጋጣሚ ማወቅ ይፈልጋል። ያ የማወቅ ጉጉት ደግሞ ጥሩ አንባቢ አድርጎታል፡፡ ከታሪክ እስከ ፖለቲካ፣ ከሥነ ልቦና እስከ እምነት ፣ተራ ነገር ቁም ነገር ከታምራት ጋር ማውራት ይቻላል። ስለ ዓለም ስለ አካባቢው በተረዳ ቁጥር እና ብስለትን እያገኘ በአቋሙ እየጠነከረ የአሁኑን ታምራት ፈጥሯል ብዬ አስባለሁ። ታምራት ለሚያምንበት ነገር ዋጋ ይሰጣል። በሕይወት ውስጥ ዋጋ አላቸው ብሎ ለሚያምንባቸው ነገሮች ደግሞ አይደራደርም ። በስራ አጋጣሚ ብዙ ፈተና ላይ ጥሎታል፡፡ ባለፈው አስራ አምስት ሃያ አመታት ውስጥ ከትላልቅ ማስታወቂያ ሰጪዎች እስከ ትልልቅ ፖለቲከኞች ጋር ተላትሞበታል። ይህም ዋጋውን ስለነኩበት ነው። ይህንን ፈተና ደግሞ በጥበብ ነው የሚያልፈው፡፡ ሁል ጊዜ ቢያንስ በሶስት በአራት ዓመት የከፋ አደጋ ያጋጥመዋል፡፡ ዋጋውን የሚነካ ያንን ደግሞ ጊዜ ይፈጅበት እንጂ እንዳይደገም አድርጎ ነው የሚወጣው።
ታምራት ሁሌ የተሻለ ነገር ይመጣል ብሎ ያምናል፡፡ እነዚህ ባህሪዎቹ ሁሉን ነገር የሚቀበል አዕምሮ ስላለው ብቻ ሳይሆን ራሱን መቆጣጠር የሚችል ሰው አድርገውታል። የራስ መተማመኑ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ታምራት. በምንም መንገድ የኔ ሃሳብ ትክክል ነው ብሎ አያውቅም፡፡ ከ 30 ዓመት በላይ ሳውቀው የሌላውን ሐሳብ ያዳምጣል፡፡ እሱን ለማድመጥ ከፈለገው ሰው ጋር ብቻ ነው ለመወያየት ዕድል የሚሰጠው፡፡ አለበለዚያ ሃሳብ ያዳምጣል ያውቀዋል መስማማት እንደማይችል።
ባለፉት 20 ዓመታት ብዙ መጽሐፍ በሱ መራጭነት አንብቤ ብዙ ተወያይተናል።
ታምራት ቤቱ ላይብረሪ ነው፡፡ እነዚህ የጠቀስኳቸው ባህሪዎቹ ናቸው ጠንካራ የሚዲያ ሰው ያደረጉት ብዬ አምናለሁ። የግሉ ሚዲያ ከጀመሩት ወጣቶች አንዱ ታምራት ነው፡፡እሱና በፍቃዱ ሞረዳ አንድ አርብ ጠዋት ጦማር የተባለ ጋዜጣ ይዘው ሲወጡ የአጻጻፍ ዘዴዎቹ አምዶቹ ከሌሎቻችን የተለዩ ነበሩ፡፡ የመጀመሪያው ጦማር ሲወጣ የሚጮሁ እና በተቃዋሚነት አስተያየት አይደለም፡፡ እነሱ የሚፅፉት ታምራት ከብዙዎቻችን በተሻለ የፕሬስ ነጻነት አላማ እና ተግባር ጠንቅቆ የተረዳ ስለነበር ይመስለኛል፡፡
.ብዙዎቻችን አውቀን ሆነ ሳናውቅ የግል ፕሬሱም 1983 እና 1984 የጀመርነው መንግሥትን እና ህወሀትን ከመቃወም አኳያ እንጂ ለህብረተሰቡ መረጃ ከመስጠት አኳያ አልነበረም፡፡ ይህን እምነቴን አሁን ድረስ የማምንበት ነው። ከዚህም በላይ ብዙዎቻችን የመጻፍ ድፍረት ኖሮን እንጂ ሐሳብን በነፃነት ለመግለጽ በቂ ግንዛቤ እንኳን አልነበረንም፡፡ የፕሬስ እና የሐሳብ ነጻነት ከጋዜጠኝነት እና ሥነ ምግባር አኳያ ምን እንደሆነ በሚገባ ቋንቋ ያስረዳኝ እና የሚረዱ መጽሃፎችን እንዳነብ የሰጠኝ ታምራት ነበር፡፡ ነገር ግን ያ ሁሉ እውቀት ኖሮትም የዛሬ 28 ወይ 29 ዓመት ከመጀመሪያዎቹ የግል ፕሬስ ጋዜጠኞች የ 10 ሺህ ብር ተቀጪ የነበረው የመጀመሪያው የግል ፕሬስ ጋዜጠኛ ታምራት ነበር።
የዛሬ 30 ዓመት በፊት ጥሩ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታ ስለነበረው ስለ ጂኦ ፖለቲካ እና የኢትዮጵያ ፖለቲካ በቂ ግንዛቤ ይዞ ነበር፡፡. የቋንቋ ችሎታው ራሱን በራሱ የማስተማር ክህሎቱ ከሌሎቻችን የተሻለ የፕሬስ ግንዛቤ ስላለው በቀላሉ አሜሪካ ሄደ፡፡. የጋዜጠኝነት ሞያ ማጥናቱ ተመልሶ ደግሞ የተሻለ ስራ ለመስራት መምጣቱ ዛሬ ታምራት የደረሰበት ደረጃ አድርሶታል ብዬ አምናለሁ፡፡
ዛሬ ተመልሶ ከመጣ በኋላ በተለይ ያለፉትን አስራ አምስት አመታት በታላላቅ ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ የራሱን ሚዲያ እና ኢትዮጵያን እየወከለ እንዲሳተፍ ጥናታዊ ጽሑፎችን እንዲያቀርብና ከሌሎች እንዲማር እድል ሰጥቶታል፡፡ይህ አጋጣሚ የአፍሪካና የኢትዮጵያን መሰረታዊ ችግሮች እንዲያይ ሌሎችም ይህን ልብ ብለው እንዲያጤኑ አድርጓል፡፡ እንዲወያዩበት ዕድል ሰጥቶ ሠርቷል ብሎ ያምናል አምናለሁ፡፡.
በሌላ በኩል ታምራትን የማደንቅለት የሚዲያ የመሪነት ብቃት አለው፡፡ ይሄ ብቃቱ ጋዜጠኛ ሆኖ ሆኖ ሲሰራ ሲታተም ኤዲተሮቹ ጋ ሲነጋገር ብዙ አጋጣሚዎች ላይ አብሬው ተገኝቻለው በሌላ በኩል ታምራት የግሉ ፕሬስ እንዲያድግ በግልና በቡድን በጥናት በአለም አቀፍ ኮሚቴ ላይ ተጽዕኖ በመፍጠር ያሉትን ግብአቶች በመጠቀም ቅን የሆነ እርዳታ ለኢትዮጵያ ሚድያ እንዳበረከተ ይሰማኛል።
በርካታ ጥናታዊ ጥሁፎችን አቅርቧል፡፡ በተለያየ መድረኮች ከአሜሪካ እስከ አፍሪካ ከአውሮፓ እስከ እስያ ተመላልሷል። በብዛት ይጋብዙታል፡፡ ብዙ ጥናታዊ ጥሁፎቹ ታትመዋል፡፡ በተለያየ አለም አቀፍ የሚድያ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ጋር ተገናኝቷል፡፡ የኢትዮጵያንም እውነታ አሳይቷል፡፡
የጋዜጠኝነት ት/ቤት መምህሩ ስለ ታምራት
ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ መካሻ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ና ኮሚኒኬሽን ት/ቤት መምህር ሲሆን ስለ ጋዜጠኛ ታምራትና ስለ ፎርቹን የሚከተለውን ሙያዊ ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡
ፎርቹን ጋዜጣ የሚያተኩረው በይበልጥ የቢዝነስና ኢኮኖሚክ ዘገባዎች ላይ ነው። ይህ ዓይነት አቀራረብ የተለመደ አይደለም፡፡ ምክንያቱም አንደኛ በጣም ጥሩ የሆነ አሠራር የሚጠይቅ እንደሆነ እና በተለይ የሃገሪቷን ኢኮኖሚ የሕዝቡን ኑሮ እና መሰል ጉዳዮችን የሚዳስስ ኢንቨስትመንትን የሚያይ የሚያበረታታ ስለሆነ እጅግ በጣም ጠቃሚ የሆነ ጋዜጣ ነው፡፡ከቋንቋውም ከአቀራረቡም ከጥልቀት አንፃር በከፍተኛ ጥራት የሚሰራ ነው፡፡ ስለዚህ ይህን ስራ መስራት የሚችለው ሁነኛ ሰው ደግሞ እውነትም ታምራት ብቻ ነው፡፡
የህትመት ሚዲያ ሥራ ጥልቀት ይፈልጋል፡፡ ታምራት በተለይ ልዩ የሚያደርገው ጋዜጣውን የሚያስተዳድርበት መንገድ ነው፡፡
እንደዚህ ዓይነት ጥልቀት የሚፈልጉ ሥራዎችን ሲያሰራ በሚገባ ጊዜያቸውን ጋዜጠኞች ሰጥተው እንዲሰሩ በማድረግ ስለሆነ ከጋዜጠኞች ብዙ ነገር ይጠብቃል ፣ ብዙ ነገር ይፈልጋል ምክንያቱም ብዙ መስማት ስለሚፈልግ ነው። ታምራት በዚህ በኩል ምንጊዜም ተጠቃሽ የሆነ ብስለት ያለው ነው። ትልልቅ የመሪዎች የፕሬስ ኮንፈረንስ ሲያደርጉ ወሳኝ የሆኑ ጥያቄዎችንየሚያቀርብ ጥልቀት ያለው ጋዜጠኛ ነው።
ብዙ ነገር መስራቱን እንዲሁም የኢትዮጵያ ሚዲያ ካውንስል እንዲቋቋም በኢትዮጵያ ውስጥ የፕሬስ ነፃነት እንዲኖር በማድረግ ጥራት ያለው ጋዜጠኝነት በተለይም የፕሪንት ጋዜጠኝነት እንዲኖር የጣረ ሰው ነው። ታምራት ለኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት ያውም ደግሞ በፕሪንት ሚዲያው እጅግ በጣም አስቸጋሪ በሆነው እና የሕዝቡ የማንበብ ባህል ዝቅተኛ በሆነው ፣የፕሪንት ዋጋ እጅግ በጣም እየናረ በሚሄድበትን ሁኔታ በዚህ ውስጥ አልፎ ሃያ አምስት እና ሃያ አራት ዓመታት መሥራት ማለት ትልቅ ጥረት የሚጠይቅ ከሚዲያ ማናጀር የሚጠበቅ ሌሎችም ወደፊትም ከእርሱ ብዙ ልምድ የሚያገኙበት ነው፡፡
ዋና አዘጋጇ ስለ ታምራት
በአሁኑ ሰአት የፎርቹን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የሆነችው ትዝታ ሸዋፈራው ስለ አለቃዋ ታምራት ገብረጊዮርጊስ ይህን ሀሳብ ሰንዝራለች፡፡
እኔ ደከመኝ ሰለቸኝ አለማለቱን አደንቃለሁ፡፡ በአንድ በኩል ደግሞ የተመሰከረለት ብእረኛ ነው፡፡ አንባቢን እንዴት አድርጎ መማረክ እንደሚችል ያውቅበታል፡፡ለዚህ ደግሞ የተዋቡ ቃላት አሉት-ጥቅም ላይ ያውላቸዋል፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ ጥራት ላይ ድርድር የሚባል ነገር አይነካካውም፡፡ ሰዎች ውስጣቸው ያለውን ድንቅ ተሰጥኦ ሳያውቁ ነገር ግን አቅማቸውን እንዲያወጡ ያገዘ ሰው ነው፡፡ ለመማር ዝግጁ ለሆነ ሰው እንደ ባልንጀር መጋቢ ወይም ሜንተር ሆኖ እውቀቱን ሳይሰስት ይሰጣል፡፡
በቅርበት ከታምራት ጋር በመስራቴ ራሴን ልክ እንደ እድለኛ አድርጌ ቆጥረዋለሁ፡፡ ከታምራት ብዙ ነገሮችን ተምሬአለሁ፡፡ በጎ አስተሳሰቦችን ተምሬአለሁ፡፡ እኔ ምን ያህል ውድ እንደሆንኩ በደንብ ተምሬበታለሁ፡፡ ታምራትን በ ሚድያ ኢንዱስትሪው ላይ ካሉት የሚለየው በዚህ ድንቅ ሰብእናው ይመስለኛል፡፡ ፎርቹንን ደረጃውን ጠብቆ እንዲቆይ ያደረገው ይህ የተለየ የታምራት የህይወት ምልከታ ነው፡፡ ደግሞ ታምራት ለማወቅ ወደ ኋላ አይልም፡፡ ሰርክ እንደሚለው የማወቅ ቢዝነስ ላይነን ይላል፡፡ ሁሌ የምንማር ዜጎች ለማለት ፈልጎ ነው፡፡ ታምራት ላሳየኸን መንገድ ሁሉ እናመሰግናለን፡፡
ታምራት እንደ ሰው
ሠው ሁሉ በሁሉም ነገር እንከን አልባ፣ የተዋጣላት ፍጡር አይደለም እና ታምራም አብረውት በሰሩ፣ በሚያደንቁትና ባለውለታችን በሚሉት ባለደረቦቹ የሚነቀስ እንከን አይጠፋውም፡፡ ብዙዎቹ የታምራት ባልደረቦች የታምራትን የሙያ ብቃት ግዝፈት አውርተው የማይጠግቡትን ያህል እንከን ብለው ያለ ልዩነት የሚያነሱት ቁጡነቱን ነው፡፡ ምንም እንኳን የታምራት ቁጣ መንስኤ ለሥራው ጥራት ካለው ቀናኢነት የሚመነጭ ቢሆን ግን ደግሞ የባለደረቦቹን ስህተት የሚገልጽበት መንገድ ጣራ በነካ ጩኸት ብዙዎችን አስከፍቷል፡፡
ኢሳያስ እንደሚያስታውሰው ይህ ባህሪው ድክመቱ መሆኑን እራሱ ታማራትም በተደጋጋሚ ሲቆጭበት ይደመጣል፡፡ ‹‹ይሄ ነገር ጤናዬን እየጎዳው መሆኑንና አንገር ማኔጅመንት እንደሚያስፈልገኝ ሙያተኞች ነግረውኛል ብሎ አጫውቶኝ ያውቃል›› ሲል ኢሳያስ ያስታውሳል፡፡
መዝጊያ ይህ የመዝጊያ ጽሁፍ የተወዳጅ ሚድያ የኢንሳይክሎፒዲያ ቦርድ አባላትን አቋም የሚያንጸባርቅ ነው፡፡
ስለ ታምራት ለመሰነድ ያሰብነው ከ 2 አመት በፊት ነበር፡፡ አልሆነም፡፡ አሁን ደግሞ ተቻለ፡፡ በተወዳጅ ሚድያ ኢዲቶሪያል መሰረት ባለ ታሪኩን በክብር ማስፈቀድና ማሳወቅ ግድ ይል ስለነበር 24 ወራት መጠበቅ ግድ ነው፡፡ በመሆኑም የባለ ታሪኩን ፈቃደኝነት ወይም ተቃውሞ አለመኖር ካወቅን በኋላ ይህን በምስክርነት የታጀበ የስራ እና የህይወት ታሪክ ለመስራት ወገባችንን ታጥቀን ተነሳን፡፡ ሰው ስለ ራሱ ከሚናገር ሌሎች ቢያወሩ የተሻለ ስለሚሆን፡፡
ለካ ስንት ሊወራለት የሚገባ ሊጻፍለት የሚገባ ሰው አለ ነው ያስባለን፡፡ ታምራት በሚድያ ሰዎች ዘንድ በእርግጥ ቢታወቅም ከህትመት ሚድያ ውጭ ያለው አዲሱ ትውልድ አያውቀውም፡፡ ለማወቅ ብሎ ሰነድ ቢያገላብጥም አያገኝም፡፡ ከድረ-ገጽ ላይ ቢፋጠጥም ከቶ የለም፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ብዙ ስለሆነ ለጊዜው እናልፈዋለን፡፡ ዋናው የእኛ አላማ ለሰዎች እውቅና መስጠት ብቻ አይደለም፡፡ ከእውቅናው በዘለለ የአንድ ጋዜጠኛ ታሪክ የኢትዮጵያ ሚድያ ታሪክ መሆኑን ማወቅ ያሻል፡፡ ስለሆነም የታምራት ታሪክ ተደበቀ ማለት በ25 አመት ውስጥ የነበረው ከፊሉ የሀገሪቱ ሚድያ ታሪክ ተጋረደ እንደማለት ነው፡፡


ዛሬ ስለ ጋዜጠኝነት በተለይ ባለፉት 25 አመታት ስለ ነበረው የህትመት ሚድያ እናጥና ቢባል ሁነኛ ሰነድ ማግኘት አዳጋች ነው ፡፡ ሁሉም የራሱን ታሪክ እየሰነደ ቢያስቀምጥ ግን ነጮች ከሚጽፉልን የራሳችን ታሪክ እንድን ነበር፡፡ የራስ ታሪክ ደግሞ መድሀኒት ነው፡፡
ስለ ታምራት በዚህ ጽሁፍ የምንለው አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡ መድመቅ ያለበት ማስተማር ያለበት የእውቀት አባት፡፡ ይህን እኛ ብቻ ተናግረን የምናበቃው አይደለም፡፡ ከላይ አብረውት የሰሩት በሙሉ አንደበት የመሰከሩት ጉዳይ ነው፡፡ ወደ ኋላ መለስ ብለን ከ19 አመቱ ጀምሮ የጻፋቸውን ስናይ ታምራት ገና በልጅነቱ ለሚድያ የተፈጠረ ነበር፡፡ ሰው ደግሞ በሚችለው ሙያ ላይ ከተሰማራ ካልሰነፈ በቀር ስኬታማ መሆኑ አይቀርም፡፡ በመሆኑም ታምራት ለሩብ ክፍለ ዘመን እና ከዚያም በላይ ሌሎችን ሲያደምቅ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ እርሱ ሊደምቅ ተራው ነው፡፡ ይህ ጽሁፍ በተወዳጅ ሚድያ የፌስ ቡክ ገጽ እና ብሎግ ላይ ተጭኖ ብዙዎች ይማሩበታል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡














አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች