አቶ ወርቁ ተገኝ  

 

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በድርሰትና በጋዜጠኝነት ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ የነበራቸውን  ባለሙያዎች የህይወት ታሪክ እያወጣ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ዋናው ግባችን አዲሱ ትውልድ የቀደሙ የታሪክ ባለውለታዎች በወጉ እንዲያውቅ ማድረግ ስለሆነ እርስዎም ታሪኩ መሰነድ አለበት የሚሉትን ሰው ይጠቁሙን፡፡ ተገቢውን መስፈርት የሚያሟሉትን በዚህ ገጽ ላይ እናቀርባለን፡፡ አሁን በዚህ ጽሁፍ ታሪካቸው የሚታየው  ጋዜጠኛ ወርቁ ተገኝ ናቸው ፡፡ እኒህ ሰው ከአንድ አመት በፊት ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን እዝራ እጅ እና ቤርሳቤህ ጌቴ እንደሚከተለው የህይወት ታሪካቸውን ሰንደውታል፡፡ ልጃቸው ብሌን ወርቁ ይህ ጽሁፍ በዚህ መልኩ እንዲወጣ ላደረገችው አስተዋጽኦ ማመስገን እንወዳለን፡፡

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ቦንጋ ከተማ በ1941 ዓ.ም የተወለዱት አቶ ወርቁ ተገኝ እናታቸው ወ/ሮ አስካለ  አሸብር እና አባታቸው አለቃ ተገኝ ስመኝ ከወለዷቸው ልጆች መካከል 13ኛው ልጃቸው ሲሆኑ እናታቸው ወ/ሮ አስካለ ብዙ ልጆች ስለሞቱባቸው ''እርሱ እንኳን በህይወት ቢተርፍ'' በሚል አዲስ አበባ አጎታቸው ዘንድ  መጥተው እንዲማሩ ተደርገዋል።

 

 የ2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውንም  በአዲስ አበባ ነበር ያጠናቀቁት። አቶ ወርቁ የስራ አለምን የተቀላቀሉት በማስታወቂያ ሚኒስቴር ሬድዮ ክፍል ተለማማጅ ሆነው በመግባት ነበር፡፡ ቀጥለውም በጋዜጠኝነት ለረዥም አመታት ሰርተዋል።በስራቸው በጣም ትጉህ የነበሩት አቶ ወርቁ የጋዜጠኝነት ሙያቸውን ይበልጡን ለማሻሻል ወደ ጀርመን እና አሜሪካ ሲራኩስ ዩኒቨርስቲ ተልከው ጋዜጠኝነትን ተምረዋል።ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላም ወደ እናት ሀገራቸው በመመለስ ያካበቱትን የጋዜጠኝነት እውቀት ተግባር ላይ ለማዋል ተችሏቸዋል።

 አቶ ወርቁ በየአጋጣሚው በኢትዮጵያ በጋዜጠኝነት ከሰለጠኑ ሰዎች  አቶ ሰለሞን ደሬሳን በተደጋጋሚ ያነሳሉ።ሀገራችንን የሶማሊያ ጦር በወረረበት ጊዜ በቅስቀሳና ፕሮፖጋንዳ ክፍል እንዲሰሩ ተመድበው ወደ ጦር ግንባር በመሄድ የሚጠበቅባቸውን የሙያ ግዴታ የተወጡት አቶ ወርቁ ጦርነቱ እንዳበቃም የለውጡን ሂደት ይበልጥ ለመርዳት እና የርዕዮት ዓለም ጥራቱን ለማዳበር በሚል ወደ ኩባ ተልከው የተሰጣቸውን ስልጠና አጠናቅቀዋል። አቶ ወርቁ ከዚህ በኋላ በኢሰፓ ጽ/ቤት ለጥቂት ጊዜ በስነፅሁፍ እና ዶክመንቴሽን ክፍል ተመድበው ከሰሩ በኋላ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዲፕሎማቲክ ደረጃ ሮም በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ውስጥ በፀሀፊነት ተመድበው ለብዙ አመታት ሰርተዋል።ከዚያም በካናዳ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በመቀየር በፀሀፊነት ማገልገላቸውን ቀጥለዋል። በኋላ ኢህአዴግ ወደ ስልጣን መምጣቱን ተከትሎ አቶ ወርቁ በካናዳ ጥገኝነት በመጠየቅ በኦታዋ ከተማ ኑሯቸውን ሊመሰርቱ ግድ ሆነ። አቶ ወርቁ በተለያዩ የንግድ ዘርፎች እና በትራንስፖርት ኢንዱስትሪ ላይ ለረዥም ግዜ ሲሰሩ የቆዩ ሲሆን ከዚያ ሁሉ አገልግሎታቸው በኋላ በገጠማቸው የጤና ችግር ለ4 ወራት በህክምና ሲረዱ ቆይተው በህዳር 13/2014 ነበር ከዚህ አለም በሞት የተለዩት።

 

አቶ ወርቁ ከልጅነት ባለቤታቸው ከወ/ሮ ውድነሽ ተድላ ገ/መድህን ሁለት ሴቶች ልጆችን እና አንድ ወንድ እንዲሁም ሁለት የልጅ ልጆችን ያፈሩ ሲሆኑ ለሀገራቸው ካበረከቷቸው በጎ አበርክቶዎች መካከል በተለምዶ መስቀል አደባባይ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ያለውን የኢትዮጵያ ኤክስፓ እና ኤግዚብሽን የማቋቋም ሚናቸው የሚዘነጋ አይደለም። አምባሳደር ተስፋዬ አብዲ  የአቶ ወርቁ ኤግዝቢሽንን በማቋቋም  ለኢትዮጵያውያን ቋሚ ንብረትን አቆይተዋል ይሏቸዋል። በ1969 እና 1970 ዓ.ም በነበረው የሶማሊያ ወረራ ሰራዊቱን በፕሮፓጋንዳና  በቅስቀሳ ግንባር ከሰማይ የሚበተኑ ቀስቃሽ ጽሁፎችን በማዘጋጀት ሰራዊቱ ለድል እንዲበቃ የታገሉ ሀገር ወዳድ መሆናቸውን አምባሳደር ተስፋዬ ይመሰክራሉ፡፡ አያይዘውም ህዝብ ለህዝብ በመባል የሚታወቀው ዝግጅት የኢትዮጵያን ባህልና ኪነ-ጥበብ ለዓለም እንዲያስተዋውቅ ሀሳብን በማመንጨትና በማስተባበር ከተስፋዬ ለማ ጋር ግንባር ቀደም ሆነው መስራታቸውን ያስታውሳሉ። ሌላው በአምባሳደር ተስፋዬ የሚታወሰው የአቶ ወርቁ አበርክቶ ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ በጣልያኖች ኤግዚቢሽን እንዲያቀርቡና በቫቲካንም የክብር ሜዳሊያ እንዲያገኙ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጋቸውን ነው።

ስለ አቶ ወርቁ ብዙዎች ቀና አመለካከት እና ለስራቸውም እውቅና ሲሰጡ ይሰማል፡፡ ከኦታዋ ቅዱስ ተክለሀይማኖት ቤተክርስቲያን የሚገኙት አቶ አበበ እንግዳሰውም አንዱ አክባሪያቸው ናቸው። አቶ አበበ እንደሚሉት ''ተወዳጅ ወንድማችን አቶ ወርቁ ተገኝ ለኦታዋ ቅዱስ ተክለሀይማኖት ቤተክርስቲያን ካደረጉት በርካታና ዘርፈ ብዙ አስተዋፅኦዎች መካከል የቤተክርስቲያናችን መስራች፣የሰበካ ጉባኤያት አባል፣አገልጋይና ለብዙ የቤተክርስቲያን አዳዲስ ክንውኖች ፋና ወጊ'' ብለው ያደናንቋቸዋል። አቶ ወርቁ፣ በኦታዋ የቅዱስ ተክለሀይማኖት ቤተክርስቲያን ምዕመናን እና ወዳጆቹ ምንጊዜም የማይረሷቸው በቤተክርስቲያንዋ ታሪክ በቅርስነት መዝግበው የሚያኖሩት ትልቅ ሰው ነበሩ ብለው ይገልጿቸዋል። በቤተክርስቲያኑ የተቋቋመው ቤተመፅሀፍትን የመሰረቱት አቶ ወርቁ ሲሆኑ በግላቸው ለረዥም ዘመናት ያከማቿቸውን ልዩ ልዩ ፅሁፎች፣ ምስሎች፣የታሪክ ማስታወሻዎች አዲሱ ትውልድ እንዲማርበት በማሰብ ለቤተክርስቲያንዋ ያበረከቱ ታላቅ ሰው መሆናቸውን መስክረውላቸዋል። አቶ ወርቁ በቤተክርስቲያንዋ ውስጥ የሚታተሙ በራሪ የትምህርትና የመልዕክት ጽሁፎችን፣ምስሎችን፣የታሪክ ማስታወሻዎችን ብሎም መፅሄቶችን አዘጋጅና አቀናባሪ የነበሩ ሲሆኑ ማህደረ ቅዱሳንና ቀንዲል ዘተክለ ሀይማኖት ብለው የሰየሟቸውን ሁለት መፅሀፎች በቤተክርስቲያኒቷ ማስታወሻ ሆነውላቸዋል።

 

አቶ አበበ እንዳሉት'' ቀንዲል ዘተክለሀይማኖት በሰበካ ጉባኤው እና በምዕመናን መካከል የመገናኛ ድልድይ፣በማስተማርና በማሳወቅ ደግሞ ምዕመኑን ለማቀራረብ የበኩሏን አስተዋፅኦ የምታደርግ ሀይማኖታዊ መልዕክቶችን የምታካትት ቀንዲል ዘተክለሀይማኖት የሁላችን መድረክ ናት በማለት ነበር የመሰረታት'' ብለው ይገልፃሉ።  አቶ ወርቁ ስለአለፈው ታሪክችን በኩራት የሚናገር የወደፊቱን እንዴት ማስቀጠል እንችላለን እያለ የሚጨነቅ የጊዜ ተሻጋሪ ህልም ያለው የእውቀት ባለፀጋ ነበር ብለውም ያደናንቋቸዋል።

 በ2014 (2006) በወጣው ማህደረ ቅዱሳን መፅሄት በርዕሰ መልክት ላይ በውጭ ያሉ ወጣቶች የወደፊት የታሪክና የባህል ኃላፊነትን በተመለከት አቶ ወርቁ እንደፃፉት ''ወጣቶች ከሀገራቸው ርቀው ሲኖሩ በባህልና በታሪክ የሚፈጠረውን ክፍተት ቤተክርስቲያናችን በትምህርት ለመሙላት በትጋት ትሰራለች የበለጠ መስራትም ይጠበቅባታል፤ ለእኛ ኢትዮጵያውያን ቤተክርስቲያናችን የክርስትና እምነት ማዕከል ብቻ አይደለችም የባህላችን የታሪክችን መዘከር ጭምር ናት።ወጣቱ ትውልድ አኩሪ ታሪኩንና ቤተክርስቲያኑን ተረክቦ መልካም ጅምሮችን ዳር ለማድረስ ብዙ ይጠበቅበታል'' ብለው አስፍረዋል ሲሉ አቶ አበበ ያስታውሳሉ።

የኢትዮጵያ ሬድዮ፣የአሜሪካ ድምፅ ሬድዮ እና አሁን ደግሞ በግል ጋዜጠኝነት የሚሰራው ጋዜጠኛ አዲሱ አበበ ስለ አቶ ወርቁ እንዲህ ፅፏል። '' በጣም የምወዳት ያሳደገችኝ እና ለቁም ነገር ያበቃችኝ ትልቅ እህቴ አለች። ቤተሰባችን ውስጥ ትልቅ ስፍራ አላት ይህች እህቴ የህይወት ታሪኳን ለመፃፍ አሰበችና ሁላችንንም ስለርሷ ያለንን አስተያየት እንድንሰጥ ጠየቀችን። ከብዙ ግዜ በኋላ የአንዷ እህቷ ልጅ እትዬ እኔኮ ምንም አልፃፍኩም ትላታለች ምነው ብትላት ከምኑ ተነስቼ ምኑን ፅፌ ላዘጋጀው ግራ ገባኝ እንዳለቻት ባለታሪኳ እህቴ አጫውታኛለች። እኔም ስለ ጋሽ ወርቁ ለመጻፍ ሳስብ የገጠመኝ ይሄው ነው። በጣም የምታውቁት የምትቀርቡት እና የምትወዱት ሰው እንደምን ሊገለፅ እንደሚችል ግራ ይገባኛል። በህይወታችሁ እጅግ በርካታ ሚና የተጫወተ ለዛሬ ማንነታችሁ ወሳኝ አስተዋፅኦ ያደረገ ሰው እንደምን እንደሚገለፅ ይቸግራል። እርግጠኛ ነኝ ይሄ በብዙዎቻችሁ የጋሽ ወርቁ ወዳጆች ዘንድ ያለ ነገር ነው።









 

 

 

አስተያየቶች

አስተያየት ይለጥፉ

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች