መዝገቡ አባተ ገብሩ
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን
በድርሰትና በጋዜጠኝነት ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ የነበራቸውን ባለሙያዎች
የህይወት ታሪክ እያወጣ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ዋናው ግባችን አዲሱ ትውልድ የቀደሙ የታሪክ ባለውለታዎች በወጉ እንዲያውቅ ማድረግ
ስለሆነ እርስዎም ታሪኩ መሰነድ አለበት የሚሉትን ሰው ይጠቁሙን፡፡ ተገቢውን መስፈርት የሚያሟሉትን በዚህ ገጽ ላይ እናቀርባለን፡፡
አሁን በዚህ ጽሁፍ ታሪካቸው የሚታየው የደራሲና የጋዜጠኛ መዝገቡ አባተ ነው፡፡ እኒህ ሰው ከ12 አመት በፊት ህይወታቸው ያለፈ
ሲሆን እዝራ እጅጉ እንደሚከተለው የህይወት ታሪካቸውን ሰንዶታል፡፡ ልጃቸው ጸሀይ መዝገቡ አባተ ይህ ጽሁፍ በዚህ መልኩ እንዲወጣ
ላደረገችው አስተዋጽኦ ማመስገን እንወዳለን፡፡
ትውልድ ልጅነት እና ትምህርት
ደራሲና ጋዜጠኛ መዝገቡ አባተ ከአባቱ ከአቶ አባተ ገብሩና ከእናቱ ከወ/ሮ ቦጋለች ወልደፃድቅ በሀረርጌ ክፍለ-ሀገር በጋራሙለታ አውራጃ ግረዋ ከተማ ህዳር 23,1923 አ.ም ተወለደ፡፡ አባቱ አቶ አባተ ገብሩ የጣልያንን ወረራ በመቃወም በሀረር በኩል የዘመተውን ጦር ተቀላቅለው ሲፋለሙ በጠላት እጅ ተገደሉ፡፡
መዝገቡ አባተ ገና በ5 አመት እድሜው አባቱን በጦርነቱ ቢያጣም እናትም አባትም ሆነው ያሳደጉት እናቱ
እርሱ እንደሚጠራቸው እናዬ ነበሩ፡፡
እድሜው ለትምህርት ሲደርስም
በአካባቢው በሚገኝ የቄስ ትምህርት ቤት ገብቶ ግእዝና አማርኛ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ ሀረር በሚገኘው ራስ መኮንን ት/ ቤት ዘመናዊ ትምህርቱን መከታተል
ጀመረ፡፡ አንድ ጠዋት
ወጣቱ የሀረሩ መስፍን ልኡል መኮንን ሃይለስላሴ በአያታቸው ስም የተሰየመውን ራስ መኮንን ትምህርት ቤት ሊጎበኙ ሲሄዱ እንዳጋጣሚ ሆኖ መዝገቡ አባተ ክፍል ይገባሉ፡፡ መዝገቡ አባተ ከክፍሉ ተማሪዎች ተለይቶ ጥቁር ሰሌዳውን በቅርብ ተጠግቶ ሲፅፍ ስላዩት አስተማሪውን ለምንድነው ይሄ ልጅ እንደዚህ ተጠግቶ የሚፅፈው ብለው ሲጠይቁ
ከሩቅ የማየት ችግር እንዳለበት ይነገራቸዋል፡፡ ልኡሉም
መዝገቡ አባተ አዲስ አበባ ምኒልክ ሆስፒታል ሄዶ አይኑን እንዲታከም ተከትለዋቸው ከመጡት ሰዎች
አንደኛው ጉዳዩን እንዲከታተል ይነግሩለታል፡፡ መዝገቡ አባተም አዲስ አበባ ዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ሄዶ አይኑን ታክሞ በሩቅ የማየት ችግሩ በመነፅር እንዲስተካከል ተደረገለት፡፡
ከዛን እድሜው ጀምሮ መነፅር ማድረጉን ቀጠለ፡፡ ለባለውለታው ለሀረሩ መስፍን ለልኡል መኮንን ከፍተኛ ፍቅር ነበረው፡፡
የአይን ህክምናውን እንደጨረሰ አዲስ አበባ ዳግማዊ ምኒልክ ት/ ቤት ገብቶ ትምህርቱን ቀጠለ፡፡
ወደ ስራ አለም
በ1942 አም ትምህርቱን አቋርጦ የመጀመርያ ስራውን ገንዘብ ሚኒስቴር ተቀጥሮ መስራት ጀመረ፡፡ መዝገቡ አባተ በተመደበበት የተለያዩ የስራ ክፍሎች በታማኝነት አገልግሏል፡፡
በ1949 አ.ም ከገንዘብ ሚኒስቴር ወደ ጡረታ ሚኒስቴር ተዛውሮ የእቃ ድርጅት ዋና ፀሀፊ ሆኖ በማገልገል ላይ እንዳለ የእቃ ግዥና ማከፋፈያ ዲሬክሲዬን ሀላፊ ሆኖ እንዲሰራ የተሰጠውን ሹመት ተግቶ በመስራት ላይ እንዳለ
የስነፅሁፍና የግጥም ፍላጎቱ
እየጨመረ ስለመጣ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ተቀጥሮ ለመስራት ወሰነ፡፡ በጊዜው የሚሰጠውን የመግቢያ ፈተና ወስዶ ፈተናውን
በጥሩ ውጤት ስላለፈ በ1957 ዓ.ም ማስታወቂያ ሚኒስቴር ተቀጠሮ የሰንደቅ አላማችን ጋዜጣ ምክትል አዘጋጅ ሆኖ መስራት ጀመረ፡፡
ጋዜጠኛ መዝገቡ አባተ የጋዜጠኝነት ሙያውን ከመጀመሩ በፊት በተለያዪ መፅሄቶችና ጋዜጦች በብእር
ስሙ የሚፅፋቸው ፅሁፎችና
ልብወልድ ድርሰቶቹ በአንባብያን ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነትን እንዲያተረፍ አስችለውታል፡፡
የቀዳማዊ ሀይለስላሴን ልደት እና በየዓመቱ የሚከበረውን የነፃነት በአል ምክንያት በማድረግ
ለንጉሱ በሚያቀርባቸው መፅሄቶችና መፅሀፎች እውቅና ከማግኘቱም በላይ የስነፅሁፍ ችሎታው እምን ድረስ እንደሆነ አሳይቷል፡፡
በተለያዩ
ግዜያት የህዝብ
መነጋገሪያ የነበሩ
ርእሶችን ከመንግስት ጋር በማያነካካው መንገድ እየተጠነቀቀ የሚፈልገውን ሃሳብ ለህዝብ ማስነበብ ችሏል፡፡ ከሰንደቅ አላማችን ጋዜጣ ምክትል አዘጋጅነት ዋና
አዘጋጅ ሆኖም ሙያዊ አደራውን ሊወጣ ችሏል፡፡
ጋዜጠኛ መዝገቡ አባተ ከሰንደቅአላማችን ወደ አዲስዘመን ጋዜጣ ተዘዋውሮ የጋዜጣው ረዳት አዘጋጅ ሆኖ ሰርቷል፡፡ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ በተለያዩ ርእሶች ሲፅፍ
"ከመዝገቡ አባተ" እያለ ነበር፡፡
የሚያቀርባቸው ጽሁፎች ችግር የሚያመጡበት መስሎ ከታየው "ከታገል " እያለ በብእር ስሙ ይጽፍ ነበር፡፡
መዝገቡ አባተ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ
ወደ ፕሬስ ድርጅት ተዘዋዉሮ የዋናው ስራአስኪያጅ ልዩ ረዳት ሆኖም ሰርቶ ነበር፡፡
ርእሰ-አንቀጽ ጸሀፊው
ጋዜጠኛ መዝገቡ አባተ በአዲስ ዘመን ላይ በሳምንት አንድ ቀን በሚታተመው ላይ ርእሰ- አንቀፅ ከሚፅፉ ጥቂት ጋዜጠኞች
አንዱ ነበር፡፡ ርእሰ- አንቀፁ የመንግስት ልሳን ሆኖ የሚቀርብ ፅሁፍ ስለነበር የፀሀፊው ማንነት አይገለፅም፡፡ በአዲስ ዘመን የሚታተመው ርእሰ-አንቀፅ ሁልጊዜም በኢትዮጵያ ሬዲዮ በምሳ ስአት ከእለቱ ዜና ቀጥሎ
ይነበባል፡፡
‹‹….ትዝ
የሚለኝ አባቴ የፃፈው ርእሰ- አንቀፅ በሬዲዮ በተነበበ ቁጥር የቤታችን ፀጥ ማለትና ወደድንም ጠላንም
ሁላችንም ቤት
ውስጥ ያለን ሰዎች
ያንን ርእሰ-አንቀፅ ማዳመጥ ነበረብን፡፡ አንድ አንድ ግዜ ፅሁፉን በሬዲዮ ሲያነቡ ሲያሳጥሩበት በጣም ሲናደድ አስታውሳለሁ›› ትላለች ልጁ ጸሀይ፡፡
መዝገቡ አባተ ጋዜጣ ማንበብ መፅሃፍ ማንበብ ምግብ የመብላትና ውሀ የመጠጣት ያህል ያዘወትራል ፡፡ መፅሀፍ ካላነበበ ወረቀት ላይ የመጣለትን ሀሳብ ይፅፋል፡፡ ያንን የፃፈውን ወረቀት አንዳንዱን ያስቀምጣል፡፡ ሌላውን ብጭቅጭቅ አድርጎ ይጥላል፡፡ ይሄ ቤት የምናየው የዘወትር ልምዱ ነበር፡፡
አንድአንድ ግዜ በብእር ስሙ "ከታገል" ብሎ ጋዜጣው ላይ በሚያሰፍራቸው መልእክቶች ከአለቃዎቹ ወቀሳና ማስጠንቀቂያ ይደርሰው ነበር፡፡ የቀዳማዊ ሀይለስላሴ ዩኒቨርሲቲ ተራማጅ ወጣቶች
ከመዝገቡ አባተ የብእር ስም በኋላ የተማሪዎች ማህበሩ "ትግላችን" የሚል መፅሄት በድብቅ እያሳተመ ማሰራጨት ጀመረ፡፡ "ታገል" የሚለውን የብእር ስም ለመጀመርያ ግዜ የተጠቀመ መዝገቡ አባተ ነበር፡፡ ከብዙ ጊዜ በኋላ የመጨረሻ ወንድ ልጁንም በብእር ስሙ ታገል መዝገቡ ብሎ ሰይሞታል፡፡
በሽጉጥ አስፈራሩት
ጋዜጠኛ መዝገቡ አባተ እንደተለመደው
አንድ ጠዋት ብርሀንና ሰላም ማተሚያ ቤት 6ኛ ፎቅ ላይ በሚገኘው ቢሮው ተቀምጦ ስራውን እየሰራ ነበር፡፡ ሶስት የቀዳማዊ ሀይለስላሴ ዩንቨርሲቲ ተማሪዎች ቢሮው ገብተው አንዱ
ሽጉጥ ይዟል ሁለተኛው
ከወንበሩ እንዳይነሳ ያስጠነቅቀዋል፡፡ ሶስተኛው በሩን ይቆልፋል፡፡ ጊዜው ለውጥ የተጀመረበት ወቅት ነበር፡፡
ተራ በተራ የስድብ ናዳ ያወርዱበታል፡፡ እናንተ ጋዜጠኞች "የዘውድ መንግስት ደጋፊ ናችሁ ንጉሱን ከማሞካሸት በስተቀር የህዝብ ድምፅ ሆናችሁ አታውቁም" እያሉ
ተሳድበው አስፈራርተው ሲጨርሱ ቢሮውን ጥለው
ይወጣሉ፡፡ መዝገቡ አባተ ጥቂት ቆይቶ ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ፣ ጋዜጠኛ ብርሀኑ ዘሪሁን ጋር ስልክ ሲደዋወሉ እነሱም እንደሱ ሶስት ሶስት ተማሪዎች ቢሯቸው ገብተው እንዳስፈራሯቸው ይነግሩታል፡፡
በሶስቱ ጋዜጠኞች ላይ የደረሰውን ማስፈራሪያና ዛቻ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ሚኒስትሩ ስምተው ጋዜጠኞቹ ቃላቸውን ለፖሊስ እንዲሰጡ ይደረጋል፡፡
በጋዜጠኞቹ ላይ የደረሰውን ማስፈራራት ንጉሱ ይሰማሉ፡፡ ለሶስቱም ጋዜጠኞች የራስ መጠበቂያ ሽጉጥ እንዲሰጣቸው ታዘዘ፡፡ መዝገቡም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ
ጠዋት ከቤት ሲወጣ ከሸሚዙ ላይ ከቆዳ የተሰራ (leather shoulder holster) ብራቴል
በሁለት ትከሻዎቾ አጥልቆ ሽጉጡን ካነገበ በኋላ በዛ ላይ ኮቱን ደርቦ መውጣት ጀመረ ፡፡ብዙም ሳይቆይ ደርግ ንጉሱን ገልብጦ ስልጣን ያዘ፡፡
ከ1967 በኋላ …ጡረታ
መዝገቡ አባተ በ1967 ዓም የማስታወቂያና ማከፋፈያ ድርጅት ዋና ስራአስኪያጅ
ሆኖ ሰርቷል፡፡
የኢትዮጵያ የማስታወቂያና የማከፋፈያ ድርጅት ከማስታወቂያ ሚኒስቴር ተገንጥሎ ራሱን ችሎ እንዲሰራ የወሰኑት ክቡር አቶ አሀዱ ሳቡሬ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ሚኒስትር ነበሩ፡፡
ድርጅቱ ራሱን ችሎ በብቸኝነት ሲንቀሳቀስ የመጀመርያው ስራ አስኪያጅ ሆኖ እንዲያገለግል የተሾመው ጋዜጠኛና ደራሲ መዝገቡ አባተ ነበር፡፡
ስራውን በተረከበ በሁለት አመት ውስጥ የጋዜጣ መሸጫ ኪዎስኮች ቁጥር እጥፍ እንዲያድጉ የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ የጋዜጣ
አዝዋሪዎችም ቁጥር በከፍተኛ ቁጥር ጨምሯል፡፡ ከጋዜጣ ሽያጭ የሚገባው ገቢም አጥፍ ከፍ ብሎ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ተጨማሪ ጋዜጣ የሚያድሉ የሞተር ሳይክሎች ተገዝተዋል፡፡ ለድርጅቱ የስራ መገልገያ የሚሆኑ አዳዲስ መኪናዎች ተገዝተውም አገልግሎት እንዲሰጡ አድርጓል፡፡
በ1967 ዓም የደርግ አስተዳደር መንግስት መዝገቡ አባተና ሌሎች ጋዜጠኞችን የንጉሱ ስርአት ደጋፊዎች ናቸው ብሎ ስላመነ ከጋዜጠኝነት ሙያቸው እንዲወጡ አድርጎ የተለያየ የስራ መደብ ስጥቷቸዋል፡፡ ጋዜጠኛ መዝገቡ አባተ ወደ ሀገር አስተዳደር ሚኒስቴር ተዛውሮ ሀረርጌ
ክፍለሀገር የህዝብ
ግንኙነትና ማስታወቂያ ስራ አስኪያጅ
ሆኖ በማገልገል ላይ እንዳለ በደርግ መንግስት ውሳኔ በ1968 ዓ.ም በተወለደ በ45 ዓመቱ በጡረታ እንዲገለል ተደረገ፡፡
ደራሲው መዝገቡ
ጋዜጠኛና ደራሲ መዝገቡ አባተ በተለያዩ የመንግስት ድርጅቶች ከማገልገሉ ባሻገር በርካታ መፃህፍትን ለንባብ አብቅቷል፡፡
የመጀመርያ መፅሀፉን የፃፈው በ22 አመቱ ሲሆን የመፅሀፉም ርእስ "የፍቅር ትዝታ" የሚል ሲሆን
በእውነተኛ ታሪክ
ላይ የተመሰረተ ድርሰት ነበር ፡፡ በአንባቢዎች ዘንድ ተወዳጅ ከመሆኑ የተነሳ 3 ጊዜ ለህትመት የበቃ ነው፡፡ ቀጥሎ "ፍቅር ምንእዳነው" የሚል ሌላ ልብ ወለድ መፅሀፍ አሳተመ፡፡ በ23 አመቱ ‹‹የመንፈስ ብልጭታ›› የተሰኘ መፅሀፉን ፅፎ ለአፄ ሀይለስላሴ 63ኛው የልደት በአላቸው ላይ ሲያበረክትላቸው የሚያሳይ ፎቶ
ጥበበስላሴ በሚል ርእስ የፃፈው መፅሀፍ ላይ ይታያል፡፡
አድናቆትን
ካተረፉለት መፃህፍት መሀል "የፍቅር ትዝታ" "ጥበበ ስላሴ" ልብወለድ ታሪክ
"ጠቅል አብነቴ" "የመንፈስ ማእበል" የመንፈስ ብልጭታ" የተሰኙት
ጥቂቶቹ ናቸው በመጨረሻም
ዋ!
መጨረሻቸው የተሰኘ መፅሃፍ ፅፎ ለመንግስት ሳንሱር ቀርቦ መታተም እንደማይችል ከከባድ ማስጠንቀቂያ
ጋር ተነግሮት
መፅሀፉ እንዳይታተም ተደረገ፡፡ ፅሁፉንም ከሳንሱር ቢሮ ማስመለስ አልቻለም፡፡የመፅሀፉ አቢይ ትኩረት ስለ ቀድሞ ባለስልጣኖች ስልጣንን ያለ አግባብ መጠቀምና መጨረሻቸውም እንደማያምር የተነበየ መፅሀፍ
ነበር፡፡
መዝገቡ
አባተ በሚፅፋቸው መፅሀፍት ሽፋኖች ሁሉ "ከመዝገቡ አባተ ከሀረር ወጣቶች አንዱ" የሚል ቃላት ያሰፍር ነበር ሀረር በመወለዱ ከፍተኛ ኩራት ይሰማውም ነበር፡፡
ጋዜጠኛና
ደራሲ መዝገቡ አባተ ስለ ኢትዮጵያ ከተፃፉ መፅሀፍት ካላነበበው ያነበበው ይበልጣል
ማለት ማጋነን አይሆንም ፡፡ የኢትዮጵያን ታሪክ አብጠርጥሮ ነበር የሚያውቀው፡፡ ይሄ
የኢትዮጵን ታሪክ መፅሀፎች የማንበብ ልምዱ በግሉ እንደአንድ ጋዜጠኛ የራሱን ጥናትና ፅሁፍ የማቅረብ ፍላጎት አሳደረበት፡፡ የኢትዮጵያን ጠቅላይ ግዛቶች ዋና ከተሞችና አካባቢያቸውን ለመጎብኘትና በጥናት የተደገፈ ፅሁፍ ለማዘጋጀት ወሰነ፡፡
ከማስታወቂያ ሚኒስቴር የስራ ፈቃድ ጠይቆ በ Chevrolet pickup መኪናው ለጉዞ የሚያስፈልገውን እቃ
ጭኖ መኪናው ቢበላሽ የሚሰሩለት መካኒክናና
ምግብ የሚያበስል ሰው ይዞ
የገጠር ጉዟቸውን ለመጀመር ከአዲስ አበባ ተነሱ፡፡ ለሚሄድባቸው ጠቅላይ ግዛት አስተዳዳሪዎች አስቀድሞ ስለጉዞው
አላማ በስልክ አነጋግሯቸው ስለነበር በየሄደበት ጠቅላይ ግዛቶች በተለያየ ሀላፊነት ላይ የነበሩ ባለስልጣኖች ከፍተኛ ትብብር አድርገውለታል፡፡
ጉዞው ረጅም አድካሚና አሰልቺ ነበር ፡፡
ከብዙ ወራቶች በኋላ የገጠር ጉዞውን ጨርሶ በሰላም አዲስ አበባ ገባ፡፡ ጥናት ያካሄደባቸውን ሰነዶች በጁ
ፅፎ አርትኦት የሚያደርገው እሱ ራሱ ነበር፡፡
የተለያዩ ከፍተኛና ዝቅተኛ ባለስልጣኖች
ቃለመጠይቅ አድርጓል፡፡ ቁጥራቸው ብዙ የሆኑ ፎቶግራፎች ሰብስቦ ርእሱ "ኢትዮጵያ" የሚል መፅሀፍ በማዘጋጀት ላይ እንዳለ የደርግ መንግስት የዘውድን መንግስት ገልብጦ ስልጣን ሲይዝ የቤቶች አሰሳ በሚደረግበት ጊዜ
መፀሀፉን ከቤት
አሸሸ፡፡
መፅሀፉን
ቢሮው ወስዶ ካዝና ውስጥ ቆልፎ በማስቀመጥ የደከመበትን መፅሀፍ ከመዘረፍ አድኗል፡፡ ከዚያን ጊዜ በኋላ በአገሪትዋ የሚታየው የአስተዳደርና የአስተሳሰብ ውጥንቅጥ መፅሀፋን ማሳተም አልቻልም፡፡ ከብዙ ዓመታት በኋላ
ልጆቹ በቅርቡ መፅሀፉን አርትኦት ማስደረግ ጀምረዋል፡፡
በዚህ አመት በ2015 መፅሀፉ ለህትመት ይበቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
መዝገቡ አባተ
"ጥበበስላሴ" በሚል ርእስ ከፃፈው ልብ-ወለድ መፅሀፍ ውስጥ ምርጥ ቃላት ብሎ ካሰፈራቸው ሀሳቦች የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡
ምርጥ ቃላት
"በአምላክ አምሳያ የተፈጠረውን ብልሁንና አዋቂውን የሰው ልጅ የሚንቅና ራሱን ብቻ ከፍ አድርጎ
የሚገምት ከቶ ማን መሆኑን ጠንቀቆ የማያውቅ ስለሆነ ከሱ መቆም የሞተ ይሻላል -ሙት አይሰማም አይለማም እና"
"ሁልግዜ ፈጣሪህን አትርሳ የማይወሰነው የእግዚአብሔር ፀጋ ካንተ ጋር እንዲሆን"
"ሰው
ነህና ውለታ ይክበድህ"
"ሁኔታህን ለማሻሻል ብትሻ ተስፋህን አታምክን"
"ስታገኝ የማይወድህ የለም ስታጣ ግን ለአይንም አትሞላ"
"መማር የህሊና
ብርሀን ነው አለመማር ግን በጨለማ መጟዝ ነው"
"ትእግስት ለተለሙት አላማ መዳረሻ ድልድይ ነው"
"ግዜ ከጣለው ጀግና ግዜ ያነሳው ፈሪ ይበልጣል"
"የምመኘውን ሁሉ እንዳገኝ እንደመቸኮሌ መጠን ትእግስት ባይኖረኝ ኖሮ የሚሆን ነገር ባልነበረ"
"በአለም ላይ ካለው ማንኛውም ፍጡር ሁሉ አንተ ውድ ስለሆንክ ስው ሆይ በመጥፎ ስራ አትርከስ"
"በሌላው ወገንህ ላይ የሆነውን አይተህ ሳትገነዘብ አይንህን ጨፍነህ እዚቅ ውስጥ አትግባ"
"ጋዜጣ የአለምን ሁኔታ የሚያሳይ መስተዋት ነው"
"ሰነፍ ሰው በስቃይ ወህኒ ቤት ያለ እስረኛ ነው"
"ድካምህ ፍሬ እስኪሰጥ ስራህን ከመስራት ቸል አትበል"
"ውጥንክን ሰበዝ ቀረሽ አታድርገው"
ልጆቹን የሚወድ አባት
የመዝገቡ አባተን የግል ታሪክ ስንመለከት ልጆቹን ከማንም በላይ አብልጦ የሚወድ አባት ነበር፡፡ ‹‹….ከስራ ቤት ሲመጣ ካላየን አንድ የተለመደ አጠራር ነበረው ድምፁን ከፍ አድርጎ "ልጆቼስ" ብሎ ሲጠራን
ከያለንበት ተሽቀዳድመን ሄደን እንስመዋለን እናቅፈዋለን፡፡ እንደአባትም እንደጓደኛም ሆኖ ነው ያሳደገን፡፡ በዛውም ልክ ከመጠን ያለፈ ቁጥጥር አድርጎብን ነው ያደግነው፡፡
ከከተማ
መውጣት ይወዳል፡፡ ብዙ ጊዜሽርሽር ይዞን ይሄዳል፡፡ አልፎ
አልፎም ሶደሬ ላንጋኖ ይወስደናል ፡፡ አባቴ ለአደን ልዩ ፍቅር ነበረው፡፡ እናቴ መሬት እየሄድን ከርከሮ ድኩላ ሚዳቋ ቆቅ ጅግራ ያድንም ነበር፡፡ hornet እና Fillover በአሁን ግዜ 22 Caliber air rifle የሚባል ጠመንጃ ነበረው፡፡ ሌላው መዝናኛ ቦታው ገፈርሳ ነበር፡፡ አባቴ እናቴ እኛ ልጆቻቸውና
ሌላ ቤተሰቦች ወይም የአባቴ ጓደኞች ተከታትለን
በመኪና እንሄድና የኢላማ ተኩስ ያደርጉ ነበር ፡፡ጠርሙሶች
ከፍ ያለ ቦታ ላይ ይደረድሩና የጠርሙሶቹን አንገት በጥይት መቀንጠስ ነው ኢላማው፡፡ ሌላው ሲጋራዎች ልክ እንደ ጠርሙሶቹ ይደረደሩና ለይቶ filterን የመታ ጎበዝ ተኳሽ ተብሎ ይጨበጨብለታል፡፡ በሰማይ የሚበሩ ወፎች ላይ እየተኮሱ
መሬት ላይ ጠብ ሲሉ ሮጦ ሄዶ ማየት ሌላው አደን ነበር ፡፡መዝገቡ አባተ ጥሩ ተኳሽ ነበር፡፡ በልጅነት ከአባታችን ጋር ያሳለፍነው የማይረሳ ህይወት እንድንወደውና ሁልጊዜም
እንድናስታውስው አድርጎናል፡፡
›› ትላለች ልጁ ጸሀይ ፡፡
አለባበስ እና መኪና መንዳት
መዝገቡ አባተ አለባበሱን በጣም ይጠብቃል፡፡ በጊዜው ከነበሩ ጋዜጠኞች ሁሉ
ቶክሲዶ ወይም ሞርኒንግ ኮት የሚለብስ ጋዜጠኛ መዝገቡ አበተ ብቻ ነበር ፡፡ ይህንንም የገለፁት በቅርቡ ያረፉት ጋዜጠኛና ደራሲ አቶ አጥናፍሰገድ ይልማ የመዝገቡ አባተን የ80ኛው የልደት በአሉን በሳንዲያጎ ከተማ በሚያከብርበት ጊዜ ተገኝተው ንግግር ባደረጉበት ወቅት ነው፡፡ በመቀጠልም ቤተመንግስት ለስራ ከሚላኩት ጥቂት ጋዜጠኞች አንዱ መዝገቡ አባተ እንደነበርም ገልፀዋልለለ
የጋዜጠኛ መዝገቡ አባተ ልጅ ጆኒ ወይም ታገል መዝገቡ የአባቱን ቶክሲዶ ለብሶ ነው የሰርጉን ምሽት ያሳለፈው፡፡
መዝገቡ አባተ
ጥሩ የፋሽን ተከታይ ነበር፡፡ ብዙ
ጫማዎችም ነበሩት፡፡ exotic የalligator leather shoes ሁሉ ነበርው
three piece suit/two piece suit ነበር
የሚለብሰው በየሳምንቱ ሽሚዞቹን ሽሪፍ ሎንድሪ እየወሰደ ነበር የሚያሳጥበው፡፡ ፀጉሩን የሚቆረጠው ፒያሳ በሚገኘው የአቶ አሰፋ የወንዶች ፀጉር ቆራጭ
ቤት ነበር፡፡ ጆኒ መዝገቡ ካደገ በኋላም
ፀጉራቸውን የሚቆረጡት አብረው እየሄዱ ነበር፡፡
መዝገቡ አእባተ በሀያ አራት አመቱ ነበር መኪና መንዳት የጀመረው፡፡ የመጀመርያ መኪና Topolino የምትባል ትንሽ የጣልያን መኪና ስትሆን የገዛትም ከአንድ ጣልያን ላይ ነበር፡፡
ቀጥሎ Ford "Prefect" የምትባል
የእንግሊዝ መኪና ይነዳ ነበር፡፡ ከዚያም Vauxhall የሚባል የእንግሊዝ መኪና
Chevrolet pickup,Volkswagen, Cadillac በመጨረሻም Mercedes መኪናዎች ይነዳ ነበር፡፡
በ80 አመቱ አረፈ
መዝገቡ አባተ ራሱን በራሱ ነው የደረስበት ደረጃ መድረስ የቻለው ጎበዝ ታታሪ ደግ ሩህሩህ ሰው ነበር፡፡ በዛው ልክ ጨዋታ ሳቅ ቀልድ የሚወድ ሰው ነበር ጋዜጠኛ አጥናፍስገድ የመዝገቡ አባተን ደግነት
ሲናገሩ " መዝገቡ ደግሰው ነበር አንድ ሰው ተቸገርኩ ካለው ከራሱ የሚሰጠው ገንዝብ ከሌለው ከሌላ ሰው ተበድሮ ለዛ ለተቸገረ
ሰው የጠየቀውን ገንዘብ የሚሰጥ ሰው ነው"ብለው
ነበር፡፡
መዝገቡ አባተ መንፈሳዊ ሰው አልነበረም፡፡
ነገር ግን የተዋህዶ እምነቱን ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ የመንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎች ቤታችን እየመጡ ስለ ወንጌል
ውይይትና አስተምሮ ያደርጉ ነበር፡፡ አንድአንድ እሁድ ጠዋት ከባለቤቱና ከልጆቹ ጋር
ቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን በመሄድ ያስቀድስ ነበር፡፡ በየአመቱ ቁልቢ ገብርኤልን ለማክበር 500 ኪሎሜትር እየነዳ ከአዲስ አበባ ሀረር ይሄድ ነበር፡፡
ጋዜጠኛ
መዝገቡ አባተ በጡረታ ከተገለለበት ግዜ ጀምሮ የግል ስራውን እየሰራ አዲስ አበባ ቀበና በሚገኘው መኖርያ ቤቱ ከአራት ልጆቹና ከባለቤቱ ጋር በሰላም መኖር ጀመረ፡፡
እንደ አውሮፓውያን
አቆጣጠር ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ ከባለቤቱ ከወይዘሮ ቀለምወርቅ ወልደአማኑኤል ጋር ልጆቻቸውን ለመጠየቅ ከአዲስ አበባ ካልፎርኒያ ይመላለሱ ነበር፡፡
ባለቤቱ ወ/ሮ
ቀለምወርቅ November 6,1992 ሴንዲዪጎ ከተማ አረፈች፡፡ ከዚያን ግዜ ጀምሮ አሜርካ እንደ ሁለተኛ አገሩ ሆነች፡፡
ጋዜጠኛና ደራሲ መዝገቡ አባተ ካሊፎርንያ ሴንዲየጎ ከልጆቹና ከልጅ ልጆቹ ጋር በሰላም ሲኖር በደረሰበት የጤና መታወክ 3 ዓመት ህክምና ሲደረግለት ቆይቶ በተወለደ በ80 አመቱ ከዚህ አለም ተሰናበተ፡፡ የቀብሩም ሥ-ስርአት አዲስ አበባ በሚገኘው ቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን ሀምሌ 30 ቀን 2003 ዓ.ም ተፈፀመ፡፡ ጋዜጠኛና ደራሲ መዝገቡ አባተ የፀሃይ መዝገቡ፣ የወሰኔ መዝገቡ የገነት መዝገቡና የታገል መዝገቡ አባት ሲሆን የስድስት የልጅ ልጆች አያትም ነበር
ጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ የአባቴን የጋዜጠኛና ደራሲ መዝገቡ አባተን ታሪክ ለመፃፍ እንዳስብክ ደውለህ ስትነግረኝ ካለኝ የግዜ መጣበብ የተነሳ የጠየከኝን information በፈለከው ስአት አላኩልህም አንተግን ሳትሰለች በጥሞናና በትእግስት ጠብቀኽኝ እንደዚህ የተሳካ ታሪክ ስላስነበብከን በእህቶቼና በወንድሜ ስም ከልብ አመሰግናለሁ እግዚአብሔር ያክብርልን
ምላሽ ይስጡሰርዝYou are welcome tsehaye
ሰርዝ