በላይ እለፋቸው
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያው ዘርፍ ላይ ከጋዜጠኛው ባልተናነሰ መልኩ ልዩ አሻራ ያኖሩ ባለሙያዎችን እያስተዋወቀ
፣ የህይወት ታሪካቸውንም እየሰነደ ይገኛል፡፡ በተለይ ስለ ሚድያ ስናነሳ የካሜራ ሰዎች ፣ የኤዲቲንግ ባለሙያዎች ለስራው ከግብ
መድረስ የማይተካ ሚና አላቸው፡፡ አንድ ዘጋቢ ፊልም ሲሰራ ስራው በቡድን የሚሰራ ስለሆነ ከቡድን አባላቱ ውስጥ በካሜራ እና በኤዲቲንግ
የጎላ ሚና ያላቸው ባለሙያዎች ሞቅ ባለ ሁኔታ ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ አሁን በዚህ ጽሁፍ አማካይነት የህይወት ታሪካቸውን ከምንሰንድላቸው
መካከል በላይ እለፋቸው ይጠቀሳል፡፡ በላይ ገና ወጣት ቢሆንም ባለፉት 10 አመታት በዘርፉ ላይ ታላቅ ትጋት ያሳየ በመሆኑ ለሌሎቸም
አርአያ በመሆኑ የህይወት ታሪኩን እንደሚከተለው አሰናድተነዋል፡፡ ባንቺአየሁ አሰፋ እና እዝራ እጅጉ እንዲህ ያቀርቡታል፡፡
ትውልድ ልጅነት እና ትምህርት
በላይ እናቱ ወ/ሮ ወርቅአለም ጸጋዬ ይባላሉ፡፡ አባቱ
እለፋቸው ተፈራ ናቸው፡፡ መጋቢት 16 ቀን 1984 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ 24 ቀበሌ ነበር ተወልዶ ያደገዉ፡፡ አባቱ እለፋቸዉ ተፈራ ከጃንሆይ ጀምሮ በቤተመንግሥት ውስጥ ያገለገሉ ሰው ሲሆኑ እናቱ ወ/ሮ ወርቅአለም ጸጋዬ ደግሞ በጤና ተቋም ውስጥ የሂሳብ ባለሙያ ሆነው ከ30 ዓመታት በላይ አገልግለዋል፡፡
በላይ እለፋቸው የመጀመሪያ ደረጃ
ትምህርቱን
ምስራቅ ድል 2ኛ ደረጃ የመሰናዶ ትምህርቱን
ደግሞ በዶ/ር ሀዲስዓለማየሁ ከዚያም የኮሌጅ ትምህርቱን ደግሞ በአድማስ ዩኒቨርሲቲ በአይሲቲ ኢንፎርሜሽን ተመርቋል፡፡
የፎቶ ፍቅር
በላይ እለፋቸው ገና በልጅነቱ የፎቶ ፍቅር አደረበት፡፡ ባደገበት መንደር ውስጥ ከነበረ አንድ ፎቶ ቤት ከትምህርት ቤት መልስ ፎቶዎችን እየተቀበለ በማሳጠብ በቀን
2 ብር እየተከፈለው
ይሰራ ነበር፡፡ እዚያው ቀስ በቀስ ሙያውን እየወደደው ፎቶ ማንሳት እና ኤዲቲንግን እየለመደ ለሙያውም ልዩ
ትኩረት
መስጠት ጀመረ፡፡ እንዲያውም ሲያድግ የሚያሳካው የልጅነት ህልሙ ፎቶግራፈር መሆን ሆነ፡፡
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀም ማስተር ወደተባለ የቪዲዮግራፊ ትምህርት ቤት አቅንቶ ፎቶ፣ቪዲዮ፣
ኤዲቲንግና ቀረፃን ተማረ፡፡ ትምህርት ቤቱ ሁሉንም ሙያዎች ካስተማረ በኋላ አንድን ነገር አጥርተው ይዘው እንዲወጡ የሚያስችል
ስለነበር በላይ
ወደ ቪዲዮግራፈር አዘነበለ፡፡
በሙያው ጥሩ ውጤት በማስገንዘብ ከአንድ እስከ 3 ለወጡ ልጆች ስራ የማስቀጠር እድል ይስጥ ስለነበር በላይም የእድሉ ተጠቃሚ ለመሆን በቃ፡፡ 2002 መጨረሻ በሰሜን ማዘጋጃ ሲነርጂ ሀበሻ ፕሮዳክሽን ተቀጠረ፡፡ የኤዲቲንግ ሥራዎችን በወር 500 ብር እየተከፈለው
መስራት ጀመረ፡፡
ሙያውን በእውቀት በመደገፍ በብዙ ሰርጎች ላይ የቪዲዮ ቀረጻም ላይ ተሳተፈ፡፡
ማንኛውም ሥራ ያለ ኤዲቲንግ መሰረቱ ብቻ እንደቆመ ቤት ነው ይላል በላይ እለፋቸዉ፡፡ ኤዲቲንግ ውበት
እና ህይወት መስጠት ነው፡፡ ለሰው አይን እና ጆሮ ተጨንቆ ጥሩ ነገርን ለተመልካች ማድረስ ነው፡፡
ጉዞ ወደ ሚድያ
በ2004 ዓ.ም በዋልታ ሚዲያ እና ኮሚኒኬሽን በ3 ወራት ኮንትራት ተቀጥሮ ከሰራ በኋላ ወደሰርግ ሥራው ተመለሰ፡፡
በድጋሚ በ 2006 መጨረሻ አካባቢ በላይ በዋልታ ተፈለገ፡፡ በኤዲተርነት ሙያ በ3700 ብር የወር
ደመወዝ ተቀጠረ፡፡ በዚያ ከፍ ያለ ሥራን በመስራት የተሻለ ሙያ ክህሎት በማዳበር
የእውቀት አድማሱን በማስፋት ስለዶክመንተሪ ምንነት በደንብ አወቀ፡፡ ዋልታ እንደትልቅ የትምህርት ማእከል ሆኖም አገልግሎታል፡፡ የተሰወረ አቅሙን አጉልቶ በማውጣት በሥራው የሚታይበትን መልካም አጋጣሚም ፈጥሮለታል፡፡ በላይም በዋዛ ፈዛዛ አጋጣሚውን አላሳለፈም፡፡ ጥሩ ባለሙያ ወጥቶታል፡፡
በላይ የተለያዩ አጫጭር ስልጠናዎችን ከተለያዩ ተቋማት ጋር ተሳትፏል፡፡ ዩኔስኮ ባዘጋጀው ዶክመንተሪ ፊልም ሜኪንግ ላይ በኤችአይቪ ኤድስ ዙሪያ በእንግሊዝኛ
ቋንቋ አጭር ዶክመንተሪም ሰርቷል፡፡
በኤዲቲንግ የተሳተፈበት
ገዳ የተሰኘው በኦሮሞ ባህላዊ ሥልጣን ላይ የሚያጠነጥነው የ30 ደቂቃ የዋልታ ዶክመንተሪ ሥራ
በላይ ሲነሳ አብሮ የሚታወስ ሥራው ነው፡፡በዚህ ታላቅ የዶክመንተሪ ስራ ጌትነት ታደሰ በአዘጋጅነት ሙሉቀን ታደሰ በካሜራ
በላይ እለፋቸው ደግሞ በኤዲቲንግ ተሳትፈው የማህበረሰብን ባህል ለትውልድ አስቀምጠዋል፡፡ ከእያንዳንዱ ውብ
ሥራ ጀርባ ያሉ ድንቅ ባለሙያዎች መኖራቸውን የሚመሰክር ነው፡፡ ይህ ስራ ሳይዛነፍ እንዲሰራ ለ1 ወር ያህል የፈጀ የሥራ ጊዜን ወስዷል፡፡
የኣካባቢ ገጽታን የሚቃኙ መሰረተ-ልማት ላይ ያተኮሩ ስራዎችን ሰርቷል፡፡ ‹‹ሀገሬ›› በሚል ርእስ
በርካታ የዶክመንተሪ ስራዎችን ሰርቶ ለህዝብ አይን እና ጆሮ አድርሷል፡፡
በሙያ
ወደ ማደግ
በተጨማሪም በ2009 ዋልታ ሲመሰረት በቀዳሚነት የስርጭቱን የኤዲቲግ ሥራ ሰርቷል፡፡ በዚህም በዋልታ ቴሌቪዥን ምስረታ ላይ ያለው ሙያዊ አስተዋጽኦ ቀላል የማይባል ነው፡፡ በላይ መስራቱን እንጂ ሰንት እንደሰራ አያውቅም፡፡ ብቻ በላይ በየቀኑ ኤዲቲንግ ላይ ነው፡፡ በጋዜጠኞች ዘንዳ በሥራው ፍጥነት እና ጥራት ተመራጭም ነበር፡፡ ከጀማሪ ኤዲተርነት እስከ ከፍተኛ ዶክመንተሪ ቪዲዮ ኤዲተርነት ሰርቷል;: በላይ እለፋቸዉ ከ2006 እስከ 2010 ወርሃ ጥር ድረስ በዶክመንተሪ ሥራ የጀርባ አጥንት በመሆን ዋልታን አገልግሏል፡፡ በላይ ሲያስረዳ ኤዲቲንግ የማይሰለች የፈጠራ ሥራ ነው ይላል፡፡ ከስራው በተጨማሪ በርካታ ቤተሰቦችንም ማፍራት ችሏል፡፡ ከነከብካብ አስፋው፣ ጌትነት ታደሰ፣ አልማዝ በየነ፣ ሺበሺ አለማየሁ፣ አሁን በህይወት ከሌለው መልካሙ ብርሃኑ ጋር በመሆን ለ4 ዓመታት የማይሞቱ ሥራዎችን ሰርቷል፡፡
በላይ እለፋቸው ፋና ቴሌቪዥን ሥራ ከጀመረ ከ5 ወራት በኋላ ተቀላቅሏል፡፡ በዶክመንተሪ
ቪዲዮ ኤዲተርነት ተቀጥሮ ይሰራም ነበር፡፡ በፋናም ዜና፣ ዶክመንተሪ፣ ፕሮግራም ከትንሽ እስከ ትልቅ ሥራ በልዩ ተነሳሽነት ሲሰራ ቆይቷል፡፡ በፋና ቀለማት ላይ በላይ ትልቅ አሻራም አሳርፏል፡፡ የመስክ ዶክመንተሪዎቸን፣
በየቀኑ ያለ እረፍት ሰርቶ ለህዝብ እይታ አቅርቧል፡፡ በላይ ፋናን
እና የፋና ተመልካቾችን ለ3 ዓመታት በሙያው አገልግሏል፡፡
ወደ ፕሬስ ድርጅት
በኋላም በላይ እለፋቸዉ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትን ተቀላቅሎ በርካታ የመስክ ስራዎችም ላይ የበኩሉን ማድረግ ጀመረ፡፡ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስቴር በተገኙበት እየተገኘ ሁነቱን በካሜራዎቹ አይን አስገብቷል፡፡ በጦርነቱ ወቅትም የግንባር ቀረጻዎችን አድርጓል፡፡ የአረንጓዴ ፕሮጀክት ምረቃዎችን፣ የታላቁ ንግድ ባንክ ምረቃ፣ የታላቁ አብርሆት
ቤተ-መጽሐፍት ምረቃ፣ የመከላከያ
ሚኒስቴር ህንፃ ምረቃ ፎቶና ቪዲዮዎች በበላይ እለፋቸዉ ተሰርቷል፡፡ ለታሪክም ጭምር ተቀምጠዋል፡፡ በ2013 ዓ.ም ሀገራዊ ምርጫ ላይ ሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ በመገኘት ምርጫውን
በመዘገብ ታሪኩን ሰንዶታል፡፡ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት የሆነው ኮይሻ እሰከ ጎንደር፣ አርባ
ምንጭ፣ሐረር፣ደሴ፣ ጅማ የተለያዩ ክልሎች ላይ ሙያዊ አስተዋጽኦውን አበርክቷል፡፡ በሱማሌ ክልል ድርቅ በተከሰተ ጊዜም በላይ ካሜራውን ሸክፎ ምስሎችን
ለታሪክ አስቀርቷል፡፡ ታዲያ በላይ ለስራ ከሄደባቸው የጦር ግንባሮች በርካታ ትዝታዎች ቢኖሩትም
በሸዋሮቢት ከተማ የገጠመውን አይዘነጋውም፡፡
ሀዘንና ደስታን አትርፎበታልም፡፡
የ14 ዓመቷ ኢክራም በታጣቂዎች ተደፍራ
በእልህና ቁጣ አልሰበርም፣ ነገ የምፈልገዉ ቦታ እደርሳለሁ ስትል ያደምጣታል፡፡
ምስሏን በካሜራ ከማስቀረት ባለፈ ንግግሯን መቅረጽ እንዳለበት አሰበ፡፡ ከዚያም ለስራ ባልደረባዉ ጋዜጠኛ ቪዲዮ እንቅረጻት በማለት ኢትዮጵያዊቷ ማላላ የተሰኘ ቪድዮ ሰራ፡፡
በዚህ ዶክመንተሪ ምክንያት የታዳጊዋ ጉዳይ ከሰው አይን እና ጆሮ መግባት ቻለ፡፡ ልጅቷም ህይወቷ በፍጥነት እንዲቀየር ከባለሀብቶች እና ሚዲያዎች እና ባለስልጣናት ጋር እንድትገናኝ እድልን ፈጠረላት፡፡ ይህ የቀረጻ ሥራው ታዲያ የሚኮራበት እና የሚረካበት ሆነ፡፡ ከዚህች ልጅ ጀርባ በላይ እለፋቸዉ ስለመኖሩ ግን ማን ያዉቀል?
በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ሌይአውትና ዲዛይን ባለሙያ በመሆን ለ6 ወራት የኮንትራት ሰራተኛ በመሆን መስቀል አደባባይ የሚገኙ እስክሪኖች ላይ የሚተላለፉ ስራዎቹን በምስልና ድምፅ
ቅንብር ተሳትፏል፡፡ በላይ ሁሌም አዲስ
ሙያ ለመማር እራሱን ለማሳደግ ይታትራል፡፡
በአፍሪኸልዝ ቲቪ (ትምህርት
በቤቴ) በሚል በኮሮና ጊዜ ተማሪዎች በቤታቸው ሆነው በቴሌቪዥን እንዲማሩ በኤዲቲንግ ስራ ላይ ተሳትፏል ፡፡ በኤንቢሲ ኢትዮጵያ ቲቪ ላይም አሻራውን አሳርፏል፡፡
አሁንም ወደ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን (ኢቲቪ) በማቅናት
ሙያዊ አስተዋጽኦውን እያበረከተ ነው፡፡
በላይ እና ዘጋቢ ፊልም
በላይ
እለፋቸው ከተወዳጅ ሚዲያ እና ኮሚኒኬሽን ጋር በመሆንም የተለያዩ ዘጋቢ ፊልሞች ሰርቷል፡፡ በላይ በኤዲቲንግ ተሳትፎ ካደረገባቸው
ስራዎች ውስጥ የዶክተር ስሜ ደበላ ፣ የዶክተር ጌታቸው ተድላ፣ከኤድንብራ ዩኒቨርሲቲ ጋር የተሰራው የላሞች ጡት በሽታ፣ ከሴቶች
ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በትብብር የተሰራው ዶክመንተሪ ይነሳል፡፡ እንዲሁም ተወዳጅ ሚድያ ያከናወናቸው ብዙዎቹ የምረቃ ስነ-ስርአቶች
በበላይ የተቀረጹ ነበሩ፡፡ በላይ ተዘዋውሮ አዲስ ነገርን ማየትከፍ ያለ ደስታ ይሰጠዋል፡፡ አዲስ እውቀትን መሸመት ራስን በሁሉም መንገድ ማስተማር መልካም ነውም ይላል፡፡ በላይ ከሚዲያዉ የመጋረጃ ጀርባ ሆኖ 11 ዓመታት ገደማ አገልግሏል፡፡ በሰራው ስራ ከፍተኛ ርካታ ቢሰማውም
ከዚህ በላይ በሙያው ትልቅ አስተዋጽኦ የማበርከት ግብ ሰንቋል፡፡
ከዋልታ ቴሌቪዥን ምስረታ ጀርባ፣ ከፋና ቴሌቪዥን እድገት ጀርባ፣ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የመስክ ሥራዎች፣ ከስለ ኢትዮጵያ
የፓናል ውይይትጀርባ የበላይ
እጆች አሉ፡፡ ከተወዳጅ ሚዲያ ጀርባም እውቀትና ልምዱን ቀናነቱንም ሳይሰስት
በላይ ብዙ ሚና አበርክቷል፡፡ ብዙውን ጊዜ ዕዉቅና እና ክብር የሚቸረዉ ከፊት ላለዉ ቢሆንም ዳሩግን የኋላዉ ከሌለ የለም የፊቱ ነዉና፡ እንደ በላይ አይነቶች ድንቅ ብቃት ያላቸው
ሰዎች ሊመሰገኑ ይገባል፡፡
በላይ እለፋቸዉ
ፎቶግራፍ በማንሳት ፣በፎቶ ኤዲቲንግ፣ ቪዲዮ ቀረጻ፣ ቪዲዮ ኤዲቲንግ፣ ግራፊክስ ከትንሽ ሰርግ እስከ ታላላቅ ሀገራዊ ሁነቶች አሻራዉን አሳርፏል፡፡
በላይ እለፋቸው ድንቅ
አቅም ያለው ባለሙያ እንደሆነ በአሁኑ ሰአት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ጌትነት ታደሰ ይመሰክራሉ፡፡
አቶ ጌትነት በላይን ከዋልታ ጀምሮ የሚያውቁት እንደመሆኑ መጠን ከዚያን
ጊዜ አንስቶ አቅሙን እያጎለበተ የመጣ ነው ሲሉ ይገልጹታል፡፡ የፋና ቲቪ የዶክመንተሪ ክፍል ሃላፊ የሆኑት አቶ ሺበሺ አለማየሁም
ከበላይ ጋር በዋልታ እና በፋና እንደመስራታቸው ድንቅ ብቃቱን መስክረዋል፡፡ አቶ ሺበሺ በላይ ታዛዥ ባለሙያ በስራው ላይ አንዳች ድካም የማይታይበት ታታሪ ሰው ነው ሲሉ ይገልጹታል፡፡
አቶ ሺበሺ እንደሚናገሩት
በላይ በባህል እና ላይ ትኩረታቸውን ያደረጉ መሰናዶዎች ይመስጡታል፡፡ እነዚህን ፕሮግራሞች ከፍ አድርጎ ለመስራት የተቻለውን ጥረት
ያደርጋል ሲሉ ምስክርነታቸውን ገልጸዋል፡፡
‹‹…..በላይ አንድ
ስራን ሲሰራ በሙሉ ሃላፊነት ነው፡፡ ከጋዜጠኛው ጋር አንድ ስራ ኤዲት
ማድረግ ከጀመረ የጋዜጠኛውን ሀሳብ ይረዳል፡፡ ስለሚረዳም ጋዜጠኛው ከሰጠው ሀሳብ ተጨማሪ ውበትና ሀሳብ አክሎበት ይገኛል፡፡ ይህም የበላይን ልዩ ክህሎት የሚያሳይ ነው
›› ሲሉ ሀሳባቸውን አቶ ሺበሺ ሰጥተዋል፡፡
የ31 ዓመቱ ወጣት በላይ እለፋቸዉ ባህርማዶ ተጉዞ ሲኒማቶግራፊን በመማር ኢትዮጵያ ያሏትን ታላላቅ ገድላት በፊልም ሰርቶ ለተመልካች ማቅረብ እና ታሪክን በፊልም ሰንዶ ለታሪክ ለማስቀመጥ ይፈልጋል፡፡ እስከዛሬ 650 የሚደርሱ የቲቪና
የዶክመንተሪ መሰናዶዎችን ኤዲት ያደረገው በላይ በ1000 የሚቆጠሩ ፎቶዎችንም አንስቷል፡፡ ገና ብዙ
መሰራት፣ ሀገርና ህዝቡን ማገልገል የሚችል አቅም ያለዉ ተስፈኛ ልጅ በመሆኑ ይህ ምኞቱ እንዲሳካ ተወዳጅ ሚዲያ መልካሙን ይመኛል፡፡
በላይ እለፋቸዉ በ 2006 ዓ.ም
መስከረም 21 ቀን ከተዋወቃት ፍቅር አህመድ ጋር ጋብቻ መስርቶ ሎዛ በላይ የተባለች ልጅን ወልዷል፡፡
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ