እማማ ፂዮን አንዶም በ100 አመታቸው አረፉ
ተወዳጅ
ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በየትኛውም ሙያ ፤ በየትኛውም ሀገር የሚኖሩ
ኢትዮጵያውን የህይወት ታሪክ እያወጣ ፤ እያስተዋወቀ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡
የሀገር ታሪክ ከሰው ታሪክ ይቀዳል እንዲሉ በ10 አመት ውስጥ የ5000000/ 5ሚሊዮን ኢትዮጵያንን አጭር ግለ-ታሪክ ጽፈን በፌስ
ቡክ እና በብሎጋችን ላይ የሚቀመጥ ሲሆን ለዚህም ተመጣጣኝ ክፍያ እያስከፈልን ፕሮጀክቱን ለማዝለቅ ጉዞውን አንድ ብለናል፡፡ ዛሬ
ህዳር 29 2015 ህይወታቸው ያለፈው እማማ ጺዮን ሚካኤል አንዶም ለኢትዮጵያ የሰሩ እና ኢትዮጰያን ወደው የኖሩ እስከ 100 አመታቸው
ብዙ ያዩ እናት ናቸው፡፡ የሁለት ልጆች እናት የሆኑት እማማ በተለይ ለኢትዮጵያ የባህር ልብስ መተዋወቅ የቀዳሚ አምባሳደርነቱን
ስፍራ ይወስዳሉ፡፡ እኒህ እናትማናቸው ለሚለው እዝራ እጅጉ አጭር ግለ-ታሪካቸውን እንደሚከተለው አሰናድቶታል፡፡
አባታቸው አቶ ሚካኤል አንዶም
ይኖሩበት ከነበረው አስመራ በመነሳት የተሻለ ትምህርት ለማግኘት በሚል ወደ ሱዳን አቀኑ፡፡ እዚያም በአሜሪካን ሚሲዮን ተማሪ ቤት ትምህርታቸውን
መከታተል ጀመሩ፡፡ ያን ጊዜ ሱዳን በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር ነበረች፡፡
አቶ ሚካኤል አንዶም ባሳዩት መልካም ሥነ-ምግባር በአስተርጓሚነት
ሥራ አገኙ፡፡ ትግርኛ፣ እንግሊዝኛ ጣሊያንኛ አረቢኛ ሌሎችንም ቋንቋዎች አቀላጥፈው ይናገሩ ስለነበር ከእንግሊዞቹ ጋር በቀላሉ
ለመግባባት ጊዜ አልፈጀባቸው ነበር፡፡ በዚህ ሰአት የዚያን ጊዜዋ ፂዮን ሚካኤል ተወለዱ፡፡የተወለዱትም በህዳር 18 1915 ነበር፡፡
አቶ ሚካኤል እና ባለቤታቸው ወ/ሮ ግደይ ኪዳነማርያም አስመራ ውስጥ ተማሪ
ሆነው ይተዋወቁ ነበር፡፡ ከዚያም ተጋብተው ልጆችን አፈሩ፡፡ እማማ
ፂዮን የ12 አመት ልጅ ሳሉ አባታቸው አንድ የስፌት መኪና በስጦታ መልክ
አበረከቱላቸው፡፡ በጊዜው በሀሴት የተሞሉት እማማ ጺዮን
ለአሻንጉሊቶታቸው እና ለራሳቸውም ልብስ እየሰፉ እጅግ ወደታወቁበት ሙያ ገና በጠዋት ሰተት ብለው ገቡ፡፡እማማ በዚህ ዓይነት አንድ ብለው የጀመሩትን የስፌት ሙያ በየጊዜው እያሳደጉት ሄዱ፡፡ ልዩ ልዩ ዲዛይኖችንም እየፈጠሩ በሙያዊ ፍቅር ተነድፈው መስራት ጀመሩ፡፡
እማማ
ጺዮን ወደ ልብስ ዲዛይነርነት ሙያ ሲገቡ በጊዜው እንደነውር የሚቆጠር ሙያ ነበር፡፡ በተለይ ደግሞ አንዲት ከደህና ቤተሰብ የተገኘች
ልጅ ገንዘብ እያስከፈለች ልብስ መስፋት መነጋገሪያ የሚያደርግ ተግባር
ነበር፡፡
እማማ
ፂዮን ግን የጊዜው ኋላ ቀር ባህል ለአንድም ጊዜ ሳይበግራቸው ልብሱን
እየሰፉ ለራሳቸው ማድረግ ጀመሩ፡፡ በዚህ ሰአት የንጉሳውያን ቤተሰብ ልጆች በልብሶቹ ማማር ተሳቡ፡፡‹‹ለእኛም ስፊልን ›› መባል ጀመሩ፡፡ ነገር ግን ማስከፈል
ከቶ አይታሰብም፡፡ ለተወሰኑ ጊዜያት ያለክፍያ እየሰሩ ማስረከብ ጀመሩና
ኋላ ላይ የግድ ሥራውን ለማሳደግ ማስከፈል ጀመሩ፡፡ቤታቸው ሆነው ልብስ መስፋት የጀመሩት እማማ ሳይታሰብ ደንበኛ ጎረፈላቸው፡፡ ሥራውን መቆጣጠር አቃታቸው፡፡ ከዚያም ሱቅ ተከራይተው መሥራት
ጀመሩ፡፡
‹‹ ልብስ ሰፍቶ መሸጥ ነውር አይደለም ›› አሉ ልእልቶቹ በልብሶቹ በጣም ተማርከው
‹‹ ወይኔ ልብሴ ተወደደልኝ ›› ይሉ ነበር እማማ ጺዮን የደንበኛ አስተያየት
ልባቸውን እያሞቀው፡፡
ልእልቶቹ ጭራሽ ከእማማ ጺዮን የልብስ ስፌት ሱቅ መዋል ጀመሩ፡፡ ይህም እንደማበረታቻ
ብቻ ሳይሆን የወጣት ጺዮንን ገበያ ለማድራት የተጠቀሙበት ስልት ነበር፡፡
እማማ ጺዮን ከ 6 አመት በፊት በሰጡት ቃለ-ምልልስ የንጉሳውያን
ቤተሰቦችን አመስግነዋል፡፡
ያን
ጊዜ ፈረንጆቹም ቢሆኑ የኢትዮጵያን ልብስ ለማስተዋወቅ ታላቅ ጥረት ያደርጉ ነበር፡፡ በዓል ሲሆን የኢትዮጵያን ልብስ እየለበሱ ነጮቹ በእማማ ፂዮንን ልብስ ይደምቁ ነበር፡፡
50 አመት በዚህ ሙያ የዘለቁት እማማ ጺዮን ራሳቸው በአንድ ወቅት እንደተናገሩት
የበጎ አድራጎት ሥራን በኢትዮጵያ ውስጥ የጀመሩት እርሳቸው ናቸው፡፡ ከሰው እየለመኑ የበጎ አድራጎት ስራን በወጉ ማከናወን ጀመሩ፡፡ በዚህ አይነት
ለቀይ መስቀል ፤ ለሴቶች ማህበር ለቼሻየር ሆም ትልቅ እገዛ አደረጉ፡፡
እማማ
ጺዮን በምእራባውያን ሀገራትም የነበራቸው ቆይታ ብዙ እውቀት የቀሰሙበት ነበር፡፡ እማማ ጺዮን ሴቶች ከወንዶች እኩል ናቸው ብለው የሚያምኑ ናቸው፡፡ በተለይ
ግን ሴት ልጅ ብዙ ኃላፊነትን ተሸክማ የምትጓዝ መሆኑንም አይዘነጉትም፡፡ ሴት ልጅ በቤት ውስጥ ልጅ ከመውለድ እና ከማጥባት አንስቶ
ሮ ያላት የስራ ድርሻ ተደራራቢ በመሆኑ ልናስብላት ይገባል ብለው ያምናሉ፡፡
እማማ
ጺዮን አንዶም የ52 አመት እድሜያቸውን በያዙ ማግስት የመንግስት ለውጥ ተደረገ፡፡ የ1966ቱ አብዮት ፈነዳ፡፡ የልብስ ዲዛይነሯም ወደ ወህኒ ገቡ፡፡ ለምን ታሰር?ኩ የሚል ምሬት ማሰማታቸውን ተወት በማድረግ
በእስር ቤት የበጎ አድራጎት ተግባራትን በማከናወን የነፍሳቸውን ጥሪ ማድመጥ ጀመሩ፡፡ ልጆችን በማስተማር ፣ ልብስ በመስፋት ፣
ሰው ስለ ተስፋ እንዲያስብ በማድረግ በእስር ቤት ውስጥ ትልቅ ከበሬታን አገኙ፡፡ በዚያው በእስር ቤት የምግብ አሰራር ፤ የልብስ
ስፌትን ሲያስተምሩ ከልብ ደስ እያላቸውና ፍሬም እያፈሩ ነበር፡፡ ከተባበሩት መንግስታት ምን ስቃይ ደረሰብሽ? ተብለው
ሲጠየቁ እንዲያውም በመታሰራቸው ደስ የተሰኙ መሆኑን በሙሉ አንደበት ነበር የተናገሩት፡፡ እማማ በአንድ ወቅት እንዳሉት እስር ቤቱን ገነት በማድረጋችን ደስታዬ ወደር የለውም ብለዋል፡፡ እርሳቸው ወደ 20 ህጻናትን በእስር ቤት ያስተማሩ ሲሆን ይህም ታላቅ በጎ
አድራጊ መሆናቸውን የሚያመለክት ነበር፡፡
እማማ
ጺዮን የታሰሩት በታናሽ ወንድማቸው በጀነራል አማን ሚካኤል አንዶም ምክንያት ነበር፡፡ እማማ ለታናሽ ወንድማቸው የተለየ ፍቅር አላቸው፡፡
ወንድማቸው በደርግ በተገደለ ጊዜ ሀዘኑን እንዲህ በቀላሉ መቋቋም የሚችሉት አልነበረም፡፡
እማማ
ጺዮን በ100 ዓመታቸው ህይወታቸው ከማለፉ አስቀድሞ የኑሮ ዘዮአቸው ደስታን የሚፈጥርላቸው ነበር፡፡ ቁርስና ምሳቸውን ራሳቸው የሚሰሩ
በመሆኑ የሚወዱት እና ለጤናቸው ተስማሚ የሆነ ምግብን ይመገባሉ፡፡ እማማ ፂዮን ከምንም በላይ የቤት ንጽህና ይወዳሉ፡፡ አብራቸው
ታገለግል የነበረችውም ለ 8 አመት አብራ የኖረች በመሆኑ በዚህ በኩል እርሳቸውን ደስ ለማሰኘት የተቻላትን ታደርግ ነበር፡፡ እማማ
ጺዮን በህይወት ሳሉ እንደተናገሩት ውጭ ሀገር ከመኖር ኢትዮጵያ ውስጥ መኖር ይበልጥ ርካታ ይሰጣቸው ነበር፡፡ እንዳሉትም ህይወታቸው
እስካለፈበት ሰአት ድረስ በእናት ሀገራቸው ነበር የኖሩት፡፡ ልጃቸው በእንግሊዝ ሀገር መኖርያዋን ያደረገች ሲሆን አልፎ አልፎ ለ3 ወር እርሷን ለመጎብኘት
ወደዚያው ያቀናሉ፡፡
በ1974 ከእስር ቤት ሲወጡ ብዙ ሰው ለምን ባህር ማዶ አትሄጂም? የሚል ምክር ለግሷቸው ነበር፡፡ እማማ ግን ለኢትዮጵያ ያላቸውን ፍቅር በየጊዜው ይገልጹ ነበር፡፡ ፍቅር መግለጽ ብቻ ሳይሆን ሀገራቸውን በነጻ አገልግለዋል፡፡ ይህም እንደ በጎ ታላቅ ሴት የሚያስቆጥራቸው ነው፡፡ እማማ ጺዮን ፤ ‹‹ፂዮን ጥበብ፡፡ የተሰኘ ሱቅ በመክፈት መጽሄትም በማሳተም የኢትዮጵያ ልብስ እንዲተዋወቅ የአንበሳውን ድርሻ የተወጡ ናቸው፡፡እማማ ፂዮን የንጉስ ሀይለስላሴንም ካባ የሰሩ ናቸው፡፡ በጣም በብዙዎች ዘንድም እንዲደነቁ ያደረጋቸው ሁሌም የኢትዮጵያን ልብስ አዘውትረው ይለብሱ ነበር፡፡
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ