ዘካርያስ ኃይለማርያም በ62 አመቱ አረፈ




ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በቴአትር፣ በሚድያ እንዲሁም በልዩ ልዩ ሙያ አሻራ ያኖሩ በህይወት ያሉም ህይወታቸው ያለፈም ባለሙያዎችን ታሪክ በዚህ ገጽ እያወጣ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ባለፉት 37 አመታት በሚድያው ዘርፍ የደከመው ዘካርያስ ኃይለማርያም በዛሬው እለት ማረፉ ይታወቃል፡፡ይህ ታላቅ ሰው ለ17 አመታት መኖርያውን በአሜሪካን ሀገር አድርጎ የነበረ ሲሆን የፈጣሪ ፈቃድ ሆኖ ወደ ዘላለማዊ ቤቱ ሄዷል፡፡ ስራዎቹ እና ታሪኩ ግን ለቤተሰቡ እና ለሀገር የሚጠቅም ስለሆነ አዘጋጅተነዋል፡፡ ለዚህ ጽሁፍ መሰራት ወዳጃችን ኡመር መሀመድ ላደረገልን ትብብር ምስጋናችንን ማቅረብ እንወዳለን፡፡ የህይወት ታሪኩን እዝራ እጅጉ እንደሚከተለው አሰናዳው፡፡

ከእስር ቤት ወጥቶ ማትሪክ ወሰደ
በሳሉ የኪነጥበብ ሰው ዘካሪያስ ኃይለማርያም በጎሬ ከተማ በ1953 ዓ.ም ተወለደ፡፡ የመጀመርያ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱንም በጎሬ በቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለስላሴ በአሁኑ ጎሬ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማረ፡፡ በጊዜው በኢሉባቡር ጫራ ወረዳ የእድገት በህብረት ዘማችም ሆነ፡፡ ዘካርያስ በወጣትነቱ በኢህአፓ ውስጥ በነበረው ተሳትፎ ለ 5 አመታት ያህል ለእስር ተዳርጎ ነበር፡፡ ከእስር ቤት ወጥቶም የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ማትሪክንም ወስዶ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ጥበባትን በመቀላቀል ለ4 አመታት ተምሮ በ1978 ዓ.ም በከፍተኛ ማዕረግ ተመርቋል፡፡

ኢቲቪ

ዘካርያስ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን አጠናቅቆ እንደተመረቀም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ተቀጠረ፡፡ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቆይታውም በስክሪፕት ጸሀፊነት፣ በፕሮግራም አዘጋጅነትና በዳይሬክተርነት ትልቅ አሻራ ለማኖር ችሏል፡፡ በተለይም በ1980ዎቹ በቲቪ ይቀርቡ የነበሩ የመዝናኛ ዝግጅቶችን ዳይሬክት በማድረግ ፣እንደ ህብረ -ትርኢትን የመሰሉ ዝግጅቶች ደረጃቸውን ጠብቀው አየር ላይ እንዲውሉ በመጣር ዘካርያስ የአንበሳውን ድርሻ ተወጥቷል፡፡ ልመንህ ታደሰና አለባቸው ተካ ወደ ሚድያው ሲመጡ የእነርሱን የመዝናኛ መሰናዶ በማዘጋጀት ዘካርያስ አስተዋጽኦ ነበረው፡፡
በ1984አ.ም የዛሬ 31 አመት 120 የመዝናኛ ፕሮግራም አንድ ተብሎ ሲጀመር ከመስራች ባለሙያዎች አንዱ የነበረው ዘካርያስ በተለይ አጫጭር የቲቪ ድራማዎች ሙያዊ በሆነ መልኩ ወደ ተመልካች እንዲቀርቡ አድርጓል፡፡ ዘካርያስ በኢትዮጵያ ቲቪ ይሰራ በነበረበት ጊዜም ስራውን በጥንቃቄ ለመከወን ብሎም በኃላፊነት መንፈስ ለመመራት የተቻለውን ያደርግ ነበር፡፡ ዘካርያስ፣ በሚድያው ዘርፍ ላይ የነበረውን እውቀት ለማሻሻል በሚልም በሌጎስ ለአንድ አመት ትምህርት ተከታትሏል፡፡
ሜጋ
በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለ10 አመት ያገለገለው ዘካርያስ ቀጣይ መስሪያ ቤቱን ያደረገው ሜጋ ኪነጥበባት ማእከልን ነበር፡፡ በሜጋ ቆይታውም ከ500 ያላነሱ የቲቪና የሬድዮ ማስታወቂያዎችን አዘጋጅቷል፡፡ ዘለላም ኩራባቸው ስለ ዘካርያስ ችሎታ ሲናገር በስራ ላይ ቀልድ የማያውቅ ጠንቃቃ ሰው ሲል ይገልጸዋል፡፡ ‹‹…. አሁን ለደረስኩበት ስፍራ ትልቁን ሚና የተጫወተው ዘካርያስ ነው፡፡ ፈትኖኝ አንተ ጥሩ የማስታወቂያ ባለሙያ ነህ ብሎ ብርታት የሰጠኝ እርሱ ነው ›› በማለት ዘካርያስ የዋለለትን ውለታ ዘላለም ኩራባቸው ዛሬ ድረስ ያስታውሳል፡፡
ብዙዎች እንደሚናሩት ዘካርያስ ፍጼም ቅንነት አለው፡፡ ዘላለምም ይህን ቅንነቱን በሚገባ አይቷል፡፡ አንድ ስራ በጥሩ ሁኔታ ከተሰራ ለማድነቅ ዘካርያስ ወደ ኋላ አይልም፡፡ ካልተመቸው ግን ስሜቱን ያለ አንዳች ይሉኝታ ሳይደብቅ ይናገራል፡፡

ፊልም እና ዘጋቢ ስራዎች

ዘካርያስ ከማስታወቂያ ዝግጅቱ ባሻገር ደግሞ ዘጋቢ ፊልሞችን ሲሰራ ይዋጣለታል፡፡ ከዳሎል እስከ ራስ ዳሸን በመጓዝም ከ200 ያላነሱ ዘጋቢ ፊልሞችን ለእይታ አብቅቷል፡፡ በዘካርያስ የዶክመንተሪ ችሎታ በልዩ ሁኔታ ከሚደነቁት አንዱ የዩኒቨርሲቲ ጓደኛው አለማየሁ ገብረህይወት ነው፡፡ አለማየሁ እንደሚለው ዘካርያስ ፈታኝ በሆነ ሁኔታ ለእይታ ያበቃቸው ዘጋቢ ስራዎች ምንጊዜም ቢታዩ የማይሰለቹ ናቸው ሲል ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡ ዘካርያስ ‹‹የመከራ ቋት›› የተሰኘ ልቦለድ ድርሰት ጽፎም ለህትመት ያበቃ ባለሙያ ነበር፡፡
ዘካርያስን ደግሞ እንደ ፊልም ሰሪ ስናየው ፀማኮን፣ሰናይትን፣የገና ሙሽራን እውን በማድረግ የተመሰገነ የኪነጥበብ ሰው ነበር፡፡ በተለይ ፀማኮን ከ700 ኪሎ ሜትር ርቀት በላይ በርካታ አርቲስቶችን ይዞ በመሄድ ለአንድ ወር ቆይታ በማድረግ የሰራው በመሆኑ በብዙዎች እንዲደነቅ ያስቻለው ስራ ነበር፡፡ ይህም ለሙያው ያለውን ፍቅር የሚያሳይ ሲሆን በማይመች ሁኔታ ውስጥ አንድን ስራ መስራት እንደሚቻልም ያሳየበት ነበር፡፡

‹‹አጭልጉ ጎሽሜ››

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከዘካርያስ ጋር ለ4 አመታት ቴአትር ጥበባትን የተማረው አለማየሁ ገብረህይወት ዘካርያስ በትምህርት አቀባበሉ ጎበዝ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ ዘካርያስ 3ኛ አመት ሳለ ከክፍል ጓደኞቹ ጋር አንድ ላይ በመሆኑ ‹‹አጭልጉ ጎሽሜ›› በሚል ርእስ የሞልየር ድርሰትን ተውነው ነበር፡፡ዘካርያስ በጊዜው ትምህርቱን ሲያጠናቅቅ ከፍተኛ ውጤት ያመጣ ሲሆን ከጓድ መንግስቱ ኃይለማርያም እጅም ሜዳልያውን ለመቀበል የቻለ ነው፡፡ በጊዜው ከዘካርያስ ጋር የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት ተማሪዎች ኤፍሬም በቀለ፣አለማየሁ ገብረህይወት ፣አሰፋ ወርቁ፣ፋንታሁን እንግዳ፣ሞሲሳ ቀጀላ፣ብርሀኑ ወንዳፍራሽ፣ጌታቸው ማንጉዳይ፣አስፋው ወልደገብርኤል እና አለማየሁ መኮንን ይገኙበታል፡፡አንጋፋው የኪነ-ጥበብ ሰው ዘካርያስ ኃይለማርያም በ1993 የዛሬ 22 አመት መሆኑ ነው ከቅርብ የሙያ ጓደኞቹ ጋር በመሆን ሀሌታ ሚድያ እና ማስታወቂያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበርን በማቋቋም በርካታ ስራዎችን መስራት ችሏል፡፡ በእነዚህ 5 አመታት ጊዜያትን እንደ በፊቱ በርካታ የቲቪና የሬድዮ ማስታወቂያዎችን የሰራ ሲሆን ፊልሞችን ለእይታ በማብቃት ሙያዊ አደራውንም የተወጣ ሰው ነው፡፡

ዘካርያስ በ1998 ዓ.ም በውጭ ሀገር ባገኘው የሥራ እድል ወደ ባህር ማዶ ከባለቤቱና ከልጆቹ ጋር በማቅናት ቀሪ ህይወቱን በዚያው አሳልፏል፡፡ ዘካርያስ ባለትዳርና የ2 ሴት ልጆች አባትም ነበር፡፡ ይህ በጥበቡ አለም ባለፉት 37 አመታት የደከመ ሰው ሀሙስ ህዳር 23 2015ዓ.ም በተወለደ በ62 አመቱ ያረፈ ሲሆን የቀብር ሥነ-ሥርአቱም ቅዳሜ ህዳር 24 2015 በለቡ ገብርኤል ከቀኑ 8 ሰአት ጀምሮ ይፈጸማል፡፡


















አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች