ዳይሬክተር
አለሙ ቶሎሳ
ተወዳጅ ሚድያ እና
ኮሚኒኬሽን በሚድያው ዘርፍ የጎላ አሻራ ያኖሩ ባለሙያዎችን የህይወት ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ብዙዎቹ ከሀገር
በሙያቸው አንድ ቁምነገር ሰርተው ነገር ግን ያልተሰነደላቸው ወይም ያልተነገረላቸው ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ቃለ-ምልልስ እንኳን ሰጥተው አያውቁም፡፡ በዚህ
ምክንያት የሰሩት ስራ ይደበቃል፡፡ የሀገር ታሪክም እንደዋዛ ተረስቶ ይቀራል፡፡ ይህ ክፍተት እንዳይኖር ተወዳጅ ሚድያ እና
ኮሚኒኬሽን በሙሉ ፍቅር ፤ መሰጠትና ፍላጎቱ ተግባሩን እየተወጣ ይገኛል፡፡ የህይወት ታሪካቸው በዚህ ጽሁፍ የምናይላቸው አቶ
አለሙ ቶሎሳ በኢቲቪ ያገለገሉ ሰው ናቸው፡፡ ለዚያውም 44 አመት ፡፡ እዝራ እጅጉ ታሪካቸውን እንደሚከተለው ሰንዶታል፡፡
በህዳር ወር በ23ኛው ቀን 2015 ላይ ጠዋት 4:40 በብሔራዊ ቴአትር አካባቢ ከአቶ አለሙ ቶሎሳ ጋር ተገናኝተን ባደረግነው ቆይታ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለ44 ዓመታት ሲያገለግሉ ያበረከቱትን አስተዋፅኦ ብዙ ነው፡፡ ከልጅነት ከጀመረው የህይወታቸው መልክ አንድ ብለን
እንጀምራለን፡፡
ትውልድ እና ልጅነት
በቀድሞው አጠራር አዲስ ዓለም በአሁኑ ደግሞ ኤጀሬ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ በ1948 ዓ.ም ነበር የተወለዱት፡፡ የመጀመሪያ ትምህርታቸውን እስከ 4ኛ ድረስ ብቻ እዚያው የትውልድ ስፍራቸው ላይ ተምረዋል፡፡ ከ4ኛ ክፍል በኋላ እስከ 2ኛ ደረጃ ግን ወደጅማ ተጉዘው ከመምህርት እህታቸው ጋር ሆነው ነበር የተማሩት፡፡ወደ እህታቸው የመጡበትን ምክንያትም ሲያብራሩት አባታቸው ነጋዴ ስለነበሩና እርሳቸውን የማስተማሩ አቅም ስላልነበራቸው እንደሆነ ያስታውሳሉ።
አቶ አለሙ በሚያዝያ 27 ት/ቤት ከተማሩ በኋላ የ2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ከማጠናቀቃቸው አስቀድሞ በእድገት በህብረት ዘመቻ በኢሉባቡር አልጓጎ በምትባል ስፍራ ለዘመቻ ተልከዋል፡፡ በመምህርነትም ከሰሩ በኋላ ወደ አዲስ አበባ አቅንተዋል።
የፎቶ እና የካሜራ ስሜት
አቶ አለሙ በልጅነታቸው ለኳስ ያላቸው ፍቅር ከፍተኛ እንደነበር አይዘነጉትም፡፡ ለፎቶግራፍም እንዲሁ ተመሳሳይ ስሜት ነበራቸው፡፡ ምናልባትም እድሜ ዘመናቸውን ሁሉ ሲሰሩት የነበረው ስራ መነሻ ምክንያቱ የልጅነት መሻታቸው መነሻ ሆኗቸው ሳይሆን አይቀርም።
አቶ አለሙ ወደ ሥራው አለም የተቀላቀሉት በጉምሩክ ቢሆንም በ1970 ዓ.ም ግን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የስቱዲዮ ካሜራ ባለሙያ እፈልጋለሁ ብሎ ሲነሳ እነ ሙሴ መንግስቴ እና ስዩም በቀለን የመሳሰሉ ባለሞያዎች ባሉበት ተቋም ውስጥ የስቱዲዮ ካሜራ ማን በመሆን በ285 የወር ደመወዝ ሲቆራረጥ ደግሞ 185 ብር ሆኖ እጃቸው እንዲደርስ ተደርጎ ቅጥር ፈፀሙ፡፡ ለ2 አመታትም ስቱዲዮ ውስጥ ሆነው ሰሩ፡፡ ሙያቸውንም አዳበሩ፡፡
በዛ ወቅት ህብረትርኢትን ማቀነባበር፣ የዘፈን ቀረፃዎችን ማካሄድ
ቀዳሚ ተግባራቸው ነበር፡፡ በኋላም ከስቱዲዮ እየወጡ የመስክ ቀረፃንም እንዲያካሂዱ ተደረገ '' ኦቢ'' በተሰኘ ካሜራም መስራት ጀመሩ።
የኢቲቪ ቆይታ
በ1970ዎቹ አጋማሽ የቴሌቪዥን መምርያ ኃላፊነት ላይ የነበሩት አቶ ወሌ ጉርሙ ነበር፡፡ የማስታወቂያ ሚኒስትሩ ደግሞ
ዶ /ር ፈለቀ ገድለ ጊዮርጊስ ነበሩ፡፡ እነዚህ ስራ ሃላፊዎች በስራቸው የሚገኙት ባለሙያዎች
የስልጠና እድል
እንዲያገኙ ሲወሰኑ ወደ ቺኮስሎቫኪያ ከሄዱት መካከል አቶ አለሙ አንዱ ነበሩ፡፡ ስልጠናውም ዳይሬክቲንግ ላይ ያተኮረ ሲሆን በዲፕሎም ደረጃ የተሰጠ ነበር፡፡ ነገር ግን ወደ ዲግሪም የማደግ እድል ቢኖረውም በዛው በወሰዱት ደረጃ ብቻ በበቂ ሁኔታ ሰልጥነው ወደ ሀገር እንዲመለሱ ሆነዋል። ዳይሬክቲንግ ማለት ምን ማለት ነው ፕሮፌሽናል ሆኖስ እንዴት ይፈፀማል የሚለውን በሚገባቸው ልክ እውቀት ከገበዩ በኋላ ለ9 ዓመታት? በስቱዲዮ ውስጥ ለ2 አመት
በፊልድ ካሜራ፣ለጥቂት ጊዜ ደግሞ ቪድዮ ሚክሰር ላይ ከሰሩበት ተሻግረው ወደ ዳይሬክቲንግ ገቡ።
አቶ
አለሙ እስከዛሬ በስራ አለም ከገጠሟቸው ላይ ገጠመኞች መካከል አንዱን ፈጽሞ አይዘነጉትም፡፡
,በ1976 የደርግ 10ኛ አመት ሲከበር የቀረጻ ማስተባበሩን ስራ ከሰሩት መካከል አቶ አለሙና ጓደኞቻቸው ነበሩ፡፡
የማስታወቂያ ሚኒስትሩ ዶ/ር ፈለቀም በስራቸው ረክተው የቴሌቪዥን ሽልማት እንዲሰጣው ከውሳኔ ላይ ይደርሳሉ፡፡ ታድያ በጊዜው እንኳንስ ባለቀለም ቴሌቪዥን ይቅርና ጥቁርና ነጩም
እንደ ብርቅ የሚታይ ነበረና የተሸለሙት ሽልማት ምን አይነት ከበሬታን እንደሚያስገኝላቸው
ለመገመት አይከብድም፡፡ ታድያ ይሄ ደስታ የሚያዘልቅ አልነበረም፡፡ አለቃው በተባራሪ የሰሙት ወሬ አበሳጭቷቸው የሸለሙትን ቴሌቪዥን ሁሉ አሰባሰቡ፡፡ እና ለአርሶ አደሮች እንዲሰጥ አደረጉ፡፡ በጊዜው የወሰዳችሁትን ቴሌቪዥን መልሱ ሲባሉ አሻፈረኝ ብለው
ደመወዛቸውን ያስያዙ ጥቂቶች አልነበሩም፡፡ በኋላ አንድም ሳይቀር ሁሉም ሊመልሱ ግድ ብሏቸዋል፡፡ አሳዛኙ ጉዳይ ግን መብራት ለሌለው አርሶአደር የማይጠቀሙበትን ቴሌቪዥን መታደላቸው ነበር።
አቶ አለሙ ቶሎሳ በወጣትነት ዘመናቸው በተለያዩ አካባቢዎች በኪራይ እየተዟዟሩ ነው የኖሩት፡፡ በልደታ ፣አፍንጮበር ፣መገናኛ፣ ጎፋ፣ ወለቴና የመሳሰሉ በ1991ዓ.ም ታድያ ባለቤታቸውን እና የልጃቸውን እናት አግብተው
ፍራኦል አለሙ የተባለ ልጅ አፍርተዋል።
በወጣትነት የወለዷት ልጅም ነበረቻቸው፡፡ በሞት ተለየቻቸው እንጂ።አቶ አለሙ ዘመኑን መለስ ብለው ሲያስታውሱ ''በዛ ዘመን የነበረው የኑሮ ሁኔታ ከአሁኑ ጋር የሚነፃፀር አይደለም ዋጋውና የመኖር አቅሙ ለንፅጽርም አይመችም'' ይላሉ ፡፡
አስተዋጽኦ
የአቶ አለሙ ቶሎሳ ስራዎች ከሆኑት መካከል የጥላሁን ገሰሰ ‹‹ውብ አይናማ.›› ሙዚቃ ቀረፃ ፣የግሸን አባይ እና ጎንደር ሙዚቃዎችን ማስታወስ ይቻላል።ስራቸው በፈረቃ ሲሆን በሳምንት 2 ጊዜ ቀረፃ ነበር፡፡ ሙዚቃ ለመስራት ከምድር ጦር እና ከሌሎችም ስቱዲዮ እያስመጡ
ይሰሩ ነበር። ወልዲያ፣በባህርዳር ስቱዲዬ በ1973 የመስቀል በአል ሲከበር፣ ጅማ ዶክመንተሪ ሲሰሩ፣ '' ሀራምን'' የተባለ ዶክመንተሪ፣ አዲስ አለም የሴቶች ፕሮግራም እና የተለያዩ ጉዳዮችን አስመልክቶ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ዞረው የሰሩትን መጥቀስ ይቻላል። ዳይሬክት በማድረግ ስራቸው የህዳሴ ግድብ ምስረታን ቀጥታ ስርጭት ሰርተዋል።
አቶ አለሙ ስራ ሲጀምሩ
የ22 አመት ወጣት
ነበሩ፡፡ ታዲያ በዚያን ወቅት እነ ጌታቸው ሀ/ማርያም ዜና የሚያነቡበት ወቅት ነበርና የካሜራ ስራውን አቶ አለሙ ከባልደረቦቻቸው ጋር በጋራ በመከወን ተጠምደዋል።
ዳንጋ
መዝናኛ
እነ አቶ አለሙ በዘመናቸው ከሰሯቸው ስኬታማ ስራዎች መካከል አዲሱን የኦሮምኛ ዳንጋ መዝናኛ እንዲቋቋም ማድረጋቸው የሚዘነጋ አይደለም። በዛን ወቅት የነበሩ ሙያተኞች በ15 ቀን ውስጥ በፍጥነት ሰልጥነው አየር ላይ እንዲወጡ ማድረጋቸው አሁንም ድረስ እርካታ የሚፈጥርላቸው ስራቸው ነበር።
አቶ አለሙ ዳይሬክቲንግን በፍቅር የሚሰሩ ናቸው፡፡ አሁንም ቢሆን ልክ እንደ ጉብዝናቸው ወቅት በርትተው የመስራቱ አቅም እንዳላቸው ያምናሉ ።
''ዳይሬክተር የጋዜጠኛውን ስራ ውበት ፈጥሮ የሚያቀርብ ነውና የዳይሬክተር ሚና ከፍተኛ ነው። በዚህ ረገድ ዳይሬክተር የጀርባ አጥንት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ቴሌቪዥን ያለ ዳይሬክተር ምንም ነው ማለት ይቻላል''ይላሉ።አክለውም ''ዳይሬክተር የጋዜጠኛን ሀሳብ በተግባር የሚያወጣ ነውና ተናቦ መስራቱ የተሻለ ውጤት ይኖረዋል''ብለው ይናገራሉ።አቶ አለሙ ከ44አመት የስራ ቆይታቸው በተጨማሪ ከጡረታም በኋላ 5 አመት ተጨምሮላቸው ሰርተዋል።
ተተኪ ማፍራት
አቶ አለሙ ተተኪ በማፍራትም አይታሙም ከቀለም ትምህርታቸው በዘለለ በተግባር ካካበቱት የዳበረ እውቀት ቀድተው ለተተኪዎች አስተላልፈዋል፡፡ ብርቱ ሙያተኞችንም አፍርተዋል፡፡ ዛሬ ላይ የሚጠቅሷቸው እነ አስራት ንጉሴ፣ ወርቁ ጋዲሳ፣ ገብሬ ይግዛው፣ ሰራዊት ከበበው እና አበበ የእኔ ምትክ ናቸው ይሏቸዋል፡፡ ለእርሳቸው አርአያ የነበሯቸው ሙያተኞች ደግሞ አፈወርቅ ማና ፣ተስፋዬ ሀ/ማርያም፣ ጌታቸው ኀ/ማርያምና የመሳሰሉት ጎበዝ ዳይሬክተሮች እና ጋዜጠኞች ነበሩ።
ውጪ ሀገር ሄደው በመማራቸው እውቀት እንዲያገኙ ትልቁ ድርሻ ነበረው የሚሉት ካሜራማኑን ኤልያስ ሲሆን በችሎታና እውቀቱ ድንቅ የነበረ 'ቦሌክስ' በሚባል
ፊልም ይሰራ የነበረ ነው ብለው ያስታውሷቸዋል። ኤልያስ
ጥንቁቅ ሆኖ አስፈላጊውን ሁሉ ይዞ ይሰራ የነበረ የፊልድ ሰራተኛ ስለነበር አደንቀዋለሁ ይላሉ አቶ አለሙ። አቶ ካሳ ምህረቴንና
ጋዜጠኛ ታዬ በላቸውንም ያደንቋቸዋል። ጋዜጠኛ ህሊና ተፈራ ከየአቅጣጫው ስትሰራና ከሰለሞን ክፍሌ ጋር ' በላኸኝ አንጀቴን በላሽው አንጀቴን' የሚለውን ሙዚቃ ሲሰሩ እርሳቸው ነበር የሰሩላቸው።
የፀጋዬ ገ/መድህን ኢንተርቪው ላይ እርሳቸው ዳይሬክተር ነበሩና በዚህ መልኩ ይቀረፅ አይቀረፅ እየተባባሉ ክርክር ውስጥ ሲገቡ ከሚሊዮን ተረፈ
ክስ ቀርቦባቸው እንደነበረም አይዘነጉትም።
አቶ አለሙ ቶሎሳ በተለያዩ የዘመን ልዩነት በቴሌቪዥን ላይ ለ44 አመታት እንደሰራ ሰው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የዳይሬክቲንግ እድገትን ሲቃኙት ''ከዚህም በላይ ሊሆን በተገባው ነበር ነገር ግን እያንዳንዱን ጥቃቅን ነገር ጭምር ጠንቅቆ የሚያውቅን እንደነአቶ አማረ አረጋዊ አይነት መሪዎች በየጊዜው ያስፈልጉት ስለነበር
በቆይታው ይህንን ማግኘት የቻለ አይመስለኝም'' ይላሉ። ስህተት ሲፈጠር ማረም እንኳን የሚቻለው መሪው ሙያውን ጠንቅቆ ማወቅ ሲችል ብቻ ነው ብለውም ያምናሉ።
በአቶ አለሙ አስተያየት
ኢቲቪ ላይ የነበሩ አገልጋዬች ደክመው ብዙም አልታዩም፡፡ ጡረታው በትናንሽ ገንዘብ የወጡ ተጎድተዋል ይላሉ፡፡ እርሳቸው ግን አሁንም ለስራቸው ካላቸው ፍቅር የተነሳ
በግላቸው ለመስራት ዝግጁ ናቸው። ታዲያ ተቋሙ ሰውን ተጠቅሞ ከማሰናበት ይልቅ ከአዲሱ ጋር እያዋሀዱ ማሰራት ቢችል ውጤታማ ይሆናል ብለውም ያምናሉ፡፡
በጥቅምት 12/1948 የተወለዱት አቶ አለሙ ቶሎሳ በዘመናቸው ጉልበታቸውን እና እውቀታቸውን ሳይሰስቱ ሰርተዋል፡፡ ነገር ግን ያላቸውን እውቀት ይዘው ማለፍን አይሹም፡፡ ይልቁን የጎደላቸውንም አሟጠው፣ ለሚተኩ አስረክበው ማለፍን ይሻሉ፡፡ ማምሸት ካለመቻል ውጪ በጤናም በጉልበትም አሁንም ብሩቱ ናቸው። እንደ አቶ አለሙ አይነት ብርቱዎች ደግሞ በደንብ ሊነገርላቸው የተገባ ነው፡፡
ዓለሙ ቶሎሳ (ከኢቲቪ ምልክቶች አንዱ) የሺበሺ አለማየሁ ምስክርነት
በአንጋፋው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጎልተው ከሚጠቀሱ ባለሞያዎች አንዱ ነው - ዓለሙ ቶሎሳ። የመስክም የስቱዲዮም ዳይሬክተር ሆኖ ነው - የማውቀው። በተለይ የመዝናኛ ክፍሉ አዘጋጅ ፣ በኋላም አስተባባሪ ስለነበርኩ ከዓለሙ ቶሎሳ ጋር በርካታ የበዓል መድረኮችን የመስራት ዕድል ገጥሞኛል።
ዓለሙ ለቅድመ ቀረፃ (preproduction) ስራዎች ትልቅ ትኩረት ይሰጣል። ከይዘት ሰዎች ጋር ተመካክሮ ስለስራው መነሻና መድረሻ የተሟላ ግንዛቤ ይይዛል። ከዚያም እርሱ ወደሚመራው የቴክኒክ ቡድን ወስዶ በሚገባ ያስረዳል።ትልቁን ስራ በዋዜማው ስለሚጨርስ በቀረፃው ዕለት ብዙም አይቸገርም።
ዓለሙ ቶሎሳ ከልቡ ዳይሬክተር ነው።በቀጥታ ስርጭት ወይም በቀረፃ ጊዜ ልክ እንደ አዋጊ የጦር መኮንን ድምፁን ከፍ አድርጎ ትዕዛዝ ይሰጣል። ለቀረፃው ከተሰማሩ የካሜራ ባለሞያዎች ጋራ በሚገናኝበት መሳሪያ " ካሜራ1 ካሜራ2 ካሜራ3 ካሜራ4 " እያለ አሊያም በስማቸው " ታሜ ክሎዝ አፕ ስጠኝ...ዘሌ ሚዲየም ሾት...ወንዴ ፓን" እያለ ይሰራል። የሚበጀውን እየመረጠ አጠገቡ ከተሰደሩት የድምፅና የምስል ቅንብር ባልደረቦቹ ጋር እየተመካከረ የተጣራውን ለተመልካች ያደርሳል።
በዚህ ጊዜ ዓለሙ ጥሩ የሰራለትን ያወድሳል። የፈለገውን ካላገኘ ግን ቁጣው ኃይለኛ ነው። ቁጣው ላልለመዱት ያስደነግጣል።ያን የሚያደርገው ግን ለስራው ስኬት ነው።
ያ ልፋትና ያ ጭቅጭቅ አልፎ ስራው ከተጠናቀቀ በኋላ ዓለሙ ቶሎሳ ድምፁን ከፍ አድርጎ ለመላው የቡድኑ አባላት ምስጋና ያቀርባል።
በእረፍት እና በእራት ጊዜ ዓለሙ በጣም ተጫዋች ነው።ከሕይወትና ከስራ ልምዱ ብዙ ገጠመኞቹን ያወጋል። በነገራችን ላይ ዓለሙ የአማርኛን ብቻ ሳይሆን የአፋን ኦሮሞ በርካታ መድረኮችንም ዳይሬክት አድርጓል። ከአፋን ኦሮሞ ቀደምት የመዝናኛ ፕሮግራም ባለሙያዎች ከእነ ሳሙኤል ዳባ ጋር በርካታ መድረኮችን እንደሰሩ አጫውቶኛል።
ዓለሙ በስቱዲዮ ዳይሬክቲንግ ስራም ይታወቃል። አልፎ አልፎ ዛሬ እያየነው ባለነው የአለባበስ ስርዓት (Dressing Code) ችግር ዙሪያ ዓለሙ ቶሎሳ ወደኋላ የሚል ዳይሬክተር አልነበረም። አስታውሳለሁ በጣም ይፈራ ነበር። "ልብስሽ ገላሽን ያሳያል። በዚህ አለባበስ ለሕዝብ አትቀርቢም" ብሎ የመለሳቸው ወይም ልብስ ያስቀየራቸው የፕሮግራም መሪዎች (አስተዋዋቂዎች) እንደነበሩ አስታውሳለሁ።
ዓለሙ ቶሎሳ ዛሬም ጠንካራ ነው።ከየትኛውም የትምሕርት ተቋም ሊገኝ የማይችል ሰፊ የሕይወትና የስራ ልምድ አለው። እኔ ምን እመኛለሁ ዓለሙ ለዚህኛው ትውልድ ሙያውን ፣ የሙያውን ዲሲፕሊንና የሕይወት ልምዱን የሚያካፍልበት ወይንም የሚያሰለጥንበት ዕድል ቢመቻችለት..
ወዳጄ እዝራ እጅጉ በአንጋፋው ዳይሬክተር ዓለሙ ቶሎሳ ሕይወትና ስራዎች ላይ እንድተነፍስ ስለጋበዝከኝ አክባሪ ይስጥልኝ!
ሺበሺ ዓለማየሁ
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ