58 ሻማዎች ክፍል 2 / በእዝራ እጅጉ

 

ውድ የዚህ ገጽ ተከታታዮች ፣ 50 ሻማዎች በሚል ርእስ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን 58ኛ አመት እያሰብን እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ተቋማት የህዝብ ሲሆኑ ውልደታቸውንም እድገታቸውንም ህዝብ ይዘክርላቸዋል የሚለውን መርህ አንግበን ከኢቲቪ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን እያወሳን ነው፡፡HISTORY OF ETHIOPIAN TELEVISION የሚል የቴሌግራም የግሩፕ ገጽ ከፍተንም ትዝታዎች ፤ ያልተነገሩ ታሪኮች፤ ምስሎች፣ እንዲላኩ እያደረግን ነው፡፡ በዚህም ብዙዎች ያላቸውን አድናቆት እየገለጹ ነው፡፡ እኛም ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የደከሙ ባለሙያዎችን ታሪክ እያሰባሰብን እንገኛለን፡፡ እነሆ አሁን ደግሞ የኢቲቪ ታሪክ በአጭሩ የሚለውን መጣጥፍ አበርክተናል፡፡

 

 

            ስድስቱ ሙከራዎች

 

ቴሌቪዥን   በኢትዮጵያውያን የታወቀው በ1948 ዓ.ም ነበር፡፡ በጊዜው የቀዳማዊ ኃይለስላሴ የዘውድ በአል ሲከበር በተዘጋጀ ኤግዚቢሽን ላይ የቴሌቪዥን ምንነት ታወቀ፡፡

ይህም ኤግዚቢሽን ከጣሊያን ወረራ በኋላ  የተመዘገቡትን ሥራዎች ለማሳየት በአሮጌ አውሮፕላን ማረፊያ ብስራተ-ገብርኤል አካባቢ የተዘጋጀ ነበር፡፡ ይህም ትርኢት በቢቢሲ አማካይነት ለእይታ የበቃ ነበር፡፡ በዚሁ ታሪካዊ ኤግዚቢሽን ላይ ቢቢሲ ያቀረበው ሁለት ኢሜጅ አርቲኮን ካሜራና አራት ሞኒተር ስክሪን ነበር፡፡ በዚያ ወቅት ነበር የቲቪ ምንነትና ስርጭት በኢትዮጵያውያን ዘንድ በይፋ የታወቀው፡፡

ለይኩን ብርሀኑ the Ethiopian television from 1957-1988 e.c በሚል ርእስ ባዘጋጀው  ጥናታዊ ጽሁፍ እንዳሰፈረው በቢቢሲ የቀረበው የቲቪ ኤግዚቢሽን  ምስል የሰይጣን ስራ ነው ተብሎ ውግዘት ደርሶበት ነበር፡፡

ሌላው ቲቪ የታወቀበት አጋጣሚ ደግሞ ደጃዝማች ዳንኤል አበበ የተባሉ ባላባት በግላቸው የንግድ ቴሌቪዥን ለማቋቋም ከ1952-1953 ዓ.ም ባለው ጊዜ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡ነገር ግን የቲቪ ጣቢያ በግለሰብ ደረጃ እንዲቋቋም  አንፈቅድም በሚል ምክንያት ተቀባይነት ሳያገኝ ቀረ፡፡

ሶስተኛውና በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እንዲቋቋም ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ የሚነገርለት ሙከራ ግንቦት 18 1955 አ.ም በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ወቅት የተደረገው ነው፡፡ወቅቱ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ነጻ የወጡበትና በአፍሪካ አዳራሽ  ቻርተሩን ለመፈረም የመጡበት ጊዜ ነበር፡፡መስራች ጉባኤው ከአዳራሹ ውጪ በአዳራሹና በብሄራዊ ቤተ-መንግስቱ  መካከል በሚገኘው ጽጌረዳ አደባባይ ለነበረው ህዝብ በስክሪን ታይቶ ነበር፡፡ ይህ የመጀመርያው ጉባኤ ሲካሄድ ፊሊፕስ ኢትዮጵያ ባዘጋጀው ስክሪንና የቴክኒክ ሥራ የጉባኤውን ሂደት አቶ ሳሙኤል ፈረንጅና ወይዘሮ አለምሰገድ ህሩይ  ዘግበውት ነበር፡፡ በ1955አ.ም  መጨረሻ ደግሞ ለአዲስ አመት ዋዜማ ፤በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቴአትር በተካሄደው  የወይዘሪት አዲስ አበባ የቁንጅና ውድድር በፊሊፕስ  ኩባንያ አማካይነት ከአዳራሽ ውጭ ለነበረው ታዳሚ በስክሪን ለማሳየት ተችሎ ነበር፡፡ ይህ ሙከራም የቴሌቪዥንን ግንዛቤና ጥቅም አጉልቶ አሳይቷል፡፡

የቴሌኮሚኒኬሽን ባለስልጣን የንግድ ቴሌቪዥን ለማቋቋም ያደረገው ጥረት መንግስት ባለመፍቀዱ እውን ሳይሆን ቀረ፡፡

በዋናነት ሀይማኖታዊ ትምህርት ስብከተ-ወንጌል ያሰራጭ የነበረው ብስራተ-ወንጌል የሬድዮ ጣቢያ የራሱን የቲቪ ጣቢያ ለመክፈት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ፕሮፖዛል አቅርቦ ነበር፡፡ነገር ግን ሳይፈቀድለት ቀረ፡፡ በአጠቃላይ ከ1948-1957 ባሉት 9 አመታት ውስጥ የቴሌቪዥን አገልግሎት እንዲቋቋም  የሚጠይቁ 6 ሙከራዎች ተደርገው ነበር፡፡

ሰባተኛው ሙከራ በፊሊፕስ ኢትዮጵያና ቶምሰን ቴሌቪዥን ኢንተርናሽናል የተባለ የእንግሊዝ ኩባንያ የቀረበው ፕሮፖዛል ነው፡፡ ይህም ፕሮፖዛል የሚድያ መሳሪያዎችን ለማቅረብና ለማሰልጠን በሚል የቀረበ ነበር፡፡ ፕሮፖዛሉ 247000 ብር አመታዊ በጀት አቅርቧል፡፡

 

  7ኛው ሙከራ 

ከብዙ ደብዳቤዎች መጻጻፍ በኋላ ሀምሌ 29 1956 ዓ.ም ለቀዳማዊ ኃይለስላሴ ቀርቦ ተፈቀደ፡፡በወቅቱ ወደ መጠናቀቁ ተቃረቦ የነበረው የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ህንጻ 4ኛ ፎቅ ላይ ቲቪ ጣቢያው እንዲሆን ተወሰነ፡፡ በመስከረም ወር 1957 አ.ም በቀጣዩ ወር ብሄራዊ የቲቪ አገልግሎት እንደሚጀመር መንግስት በይፋ አስታወቀ፡፡ጥቅምት 23 1957 አ.ም ምሽት የቴሌቪዥን አገልግሎቱ በንጉሰ-ነገስቱ ተመርቆ ስራውን ጀመረ፡፡

የንጉሱ ንግግር

‹‹….. ከህዝባችን በበለጠ ትምህርትና እውቀት ለማካፈል የሚችልበትን  ዘዴ በመሻት ከምናደርገው ጥረት ቴሌቪዥን ተጨማሪ መሳሪያ ስለሚሆን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጣቢያን መርቀን ስንከፍት ደስ ይለናል፡፡ትምህርት ለወጣቶችና ለልጆች ብቻ ሳይሆን ለሸመገሉም ነው፡፡የቴሌቪዥን አገልግሎት ለመጀመርያ ጊዜ  አነስተኛ ቢሆንም ወደፊት ድርጅቱ ተስፋፍቶ የሚሰጠው ጥቅም መላውን ህዝባችንን እንደሚያደርስ ተስፋ አለን፡፡ ካልተጀመረ አይጨረስም፡፡ ›› ብለዋል፡፡

የቲቪ ጣቢያው ተመርቆ ሥራ ጀመረ፡፡5 እንግሊዛውያንና 27 ኢትዮጵያውያን ሰራተኞች እንደነበሩ ለይኩን ብርሀኑ ባጠናው ጥናት ያትታል፡፡

የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አገልግሎት ሲጀመር አንድ ጠባብ ስቱዲዮ ብቻ ነበረው፡፡ ከስቱዲዮ በተጨማሪ የመቆጣጠሪያ ክፍል፦ስርጭት ክፍል ፤ ጥገና ክፍል፤ኤዲቲንግ ክፍል ፤ ፕሮሰሲንግ ክፍልና የተወሰኑ ቢሮዎች ይዟል፡፡

የኢትዮጵያ ቲቪ ሥራ ሲጀምር 80 ከመቶ የአየር ሰዓቱ በውጭ ሀገር ፊልሞች ይሸፈን ነበር፡፡ ጥያቄና መልስ፤ ህብረ-ትርኢት ፤ ውይይት ፤ጤና ፤ የህጻናት ፤ የእግር ኳስ ከመጀመርያዎቹ ዝግጅቶች ይጠቀሳሉ፡፡ ጣቢያው ሲመሰረት የነበረው ዓላማ ሁሉ የማሳወቅ ፤ የማስተማር እና የማዝናናት ነበር፡፡ የጣቢያው ቋንቋዎች አማርኛ እና እንግሊዝኛ ብቻ ነበሩ፡፡ በየቀኑም ከ40 ደቂቃ ያልበለጠ ስርጭት ነበረው፡፡

የመጀመርያዎቹ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ካሜራዎች ቪዲኮን ናቸው፡፡ያረጁና ደካማም ስለነበሩ ምስል በጥራት አያሳዩም፡፡ካሜራዎቹን በብርሀን ለመርዳት ሲባል ስቱዲዮ ውስጥ የተተከሉት የመብራት አምፖሎች /ፓውዛ / ሀይለኛ ሙቀት የሚረጩ ነበሩ፡፡

በዚህ ምክንያት ዜና አንባቢዎችና ለቃለ-መጠይቅ የሚመጡ እንግዶች በሙቀቱ ይቸገሩ ነበር፡፡ የቴሌቪዥን ጣቢያው ስርጭት ሲጀምር ፕሮግራሞቹ በሙሉ በቀጥታ ስርጭት የሚተላለፉ ነበሩ፡፡አቅራቢዎቹም አየር ላይ ስህተት እንዳይፈጠር ይረዳቸው ዘንድ አየር ላይ ከመውጣታቸው በፊት ብዙ ልምምድ ማድረግ ይጠበቅባቸው ነበር፡፡

ከ2 አመት በኋላ ኢሜጅ አርቲከን የተሰኙ ሁለት ካሜራዎች ተገዙ፡፡የነበረው ችግር በመጠኑም ቢሆን ተቃለለ፡፡በ1959 ድምጽና ምስልን የሚቀርጽ ካሴት ስራ ላይ በመዋሉ ጣቢያው ወደ ተሻለ ደረጃ አደገ፡፡ እስከ 1962 ዓም ባሉት 5 አመታት በሰው ሀይልና በቁሳቁስ የተወሰነ መሻሻል ተደርጓል፡፡ የጣቢያው ሰራተኞች ከአንድ የውጭ ሀገር ዜጋ በስተቀር ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሆነዋል፡፡ እስከ 1959 አ.ም የኃላፊነት ሥራውን  እንግሊዛውያን ሲያካሂዱት ከቆዩ በኋላ ከ1959 ዓ.ም በኋላ ጣቢያው በኢትዮጵያዊው ሳሙኤል ፈረንጅ እንዲመራ ተደርጓል፡፡

እስከ 1963 ዓ.ም ባሉት 8 ዓመታት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ‹‹ እናንተው ፍረዱ፤ ህዝብና ጤናው ፤ የጥያቄና መልስ ፤ የህጻናት ፕሮግራሞች  በተመልካች ተወዳጅ ነበሩ፡፡

በ1967 ዘውዳዊው ስርአት በወታደራዊ ስርአት ተተካ፡፡ በነጋሪት ጋዜጣ 3ኛ አመት ቁጥር 12 ፤ጥር 8 ቀን 1967 ዓ.ም ታትሞ በወጣ አዋጅ የኢትዮጵያ ቲቪ ከቲቪ ባለንብረቶች የፈቃድና አገልግሎት ክፍያ እንዲሰበስብ ስልጣን ተሰጠው፡፡ከ1968 ጀምሮም በብቸኝነት የቴሌቪዥን ፈቃድና አገልግሎት በየዓመቱ ከተጠቃሚዎች መሰብሰብ ጀመረ፡፡

የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እስከ 1968 ዓ.ም በመዋቅር ደረጃ ብዙም ለውጥ አልነበረውም፡፡ በ1969 መዋቅሩን በመለወጥ አዳዲስ የሥራ ክፍሎች እንዲዋቀሩ አድርጓል፡፡በመምሪያ ኃላፊ እንዲመራም ሆነ፡፡በስርጭት ረገድም ታህሳስ 1969 ዓ.ም አዲስ አበባ ከሚገኘው ዋናው ስቱዲዮ ኤርትራ ድረስ እንዲታይ ተደረገ፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የኦቢ ቫን ወይም የተንቀሳቃሽ ስቱዲዮ ስርጭት የጀመረው በ1971 ዓ.ም በአራት  የፒአይኢ ስሪት ካሜራዎች ነው፡፡ እነዚህ ካሜራዎች ከ2ኛው የአለም ጦርነት በኋላ ለገበያ የቀረቡ ናቸው፡፡  ካሜራዎቹ ከሀንጋሪ መንግስት የተበረከቱ ስጦታዎች ነበሩ፡፡በ1973 አ.ም ሁለተኛው ኦቢ ቫን ከአራት ካሜራዎች ጋር ከፖላንድ መንግስት ለኢትዮጵያ መንግስት ተሰጠ፡፡ ኦቢቫኑ ቪድዮ ቴፕ ሬከርደር ስላልነበረው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለስርጭት አገልግሎት ያውለው ነበር፡፡

በ1976አ.ም የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሁለት ባለ ቀለም  ኦቢቫን ለእያንዳንዳቸው  3 ካሜራ ያላቸው ገዛ፡፡ኦቢቫኖቹ ለስርጭትና ተያያዥ ስራዎች  የሚያገለግሉ ጀነሬተር ያላቸው ነበሩ፡፡

የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የገዛቸው ኦቢቫን የቴሌቪዥን መሳሪያዎች ባለቀለም ነበሩ፡፡ከ1977 አ.ም ጀምሮ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከጥቁርና ነጭ ወደ ከለር ባለቀለም እንዲሸጋገር አስችሏል፡፡መስከረም 2 1977 አ.ም ከተከበረው 10ኛው የደርግ ምስረታ በአል ጀምሮ  የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ባለ ቀለም ሆኖ ስርጭቱን ቀጠለ፡፡

ከ1976 ዓ.ም ጀምሮ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በስርጭት ሽፋን ከአዲስ አበባና ኤርትራ በተጨማሪ ጅማ፤ ባህርዳር ፤ መቀሌ፤ ጎንደር ፤ ነቀምትና መቱ ማሰራጫ ጣቢያዎች አማካይነት  አገልግሎት መስጠት ቻለ፡፡

 የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በ1983 አ.ም ለ3ኛ ጊዜ የመዋቅር ለውጥ አደረገ፡፡ በ1983 አ.ም የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን መዋቅር እንደ 1969 ሁሉ በመምሪያ ኃላፊ የሚመራ ሆነ፡፡ በስሩም የሽያጭና ፕሮሞሽን ክፍል ፤ የጠቅላላ አገልግሎት ክፍል ፤ የፕሮግራም ዋና ክፍል፤ የፕሮዳክሽን ዋና ክፍል የመሳሳሎ ዋና እና ንኡሳን ክፍሎች ነበሩት፡፡ የኢትዮጵያ ቲቪ ከ1983 በኋላ ቀደም ሲል ያልነበሩትን የኦሮምኛ እና የትግርኛ ፕሮግራሞችን ጀመረ፡፡  በጊዜውም በትግርኛ፤ በኦሮምኛ ፤ በአማርኛ እና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች ስርጭቱን ቀጠለ፡፡ በሽፋን ረገድም በተለያዩ የክልል አካባቢዎች የማሰራጫ ጣቢያዎች ተከላ ኣካሄደ፡፡ በ1984 አ.ም በአማርኛ የ120 የመዝናኛ ፕሮግራም ዘወትር እሁድ ከሰአት በትግርኛ ቋንቋ ‹‹ ቀዳም ምሳና›› ዘወትር ቅዳሜ፤ በኦሮምኛ ቋንቋ ‹‹ዳንጋ›› ዘወትር ቅዳሜ ይቀርቡ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እስከ 1990 አ.ም ድረስ በአንድ ቻናል ብቻ ሲሰራ ቆየ፡፡በ1990 አ.ም ወይዘሮ ሰሎሜ ታደሰ ዋና ስራ አስኪያጅ ከሆኑ በኋላ ሁለተኛው ቻናል ኢቲቪ 2 ተከፈተ፡፡ ቲቪ አፍሪካ ከተባለ የደቡብ አፍሪካ ቴሌቪዥን በሚገኙ ፊልሞችና ፕሮግራሞች ሥራ ጀምረዋል፡፡ የቲቪ አፍሪካ ስርጭት በ1993 ዓ.ም ተቋረጠ፡፡ቻናሉም ያለ አገልግሎት ቆየ፡፡አቶ ሀብቴ ገመዳ የሀብት ኪራይና ሽያጭ ቡድን መሪ እንደሚገልጹት የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን  በሳተላይት ከኢትዮጵያ ውጭ መታየት የጀመረው ጵዋግሜ 1 1999አ.ም  ነበር፡፡ ከ1999 በፊት ኢቲቪ በሀገር ውስጥ ብቻ ይሰራጭ ነበር፡፡

በኢትዮጵያ  ሬድዮና ቴሌቪዥን የመጀመርያዋ ሴት ዋና ስራ አስኪያጅ ሆነው የተሾሙት ወይዘሮ ሰሎሜ ታደሰ ናቸው፡፡አይናችን ፣ አውደ ሰብ ፣ ስኬት ፣ እና ሌሎችም በጣቢያው ባለሙያዎች የሚዘጋጁ  እንዲሁም የጥያቄና መልስ ፊት ለፊት ደግሞ በተባባሪ ድርጅቶች ከውጭ የሚሰሩ ተወዳጅ ዝግጅቶች አስጀምረው ነበር፡፡

ምስጋና … ይህን መጣጥፍ እንድናዘጋጅ የኢቲቪ ሰዎች ላሳዩት ቀና ትብብር ምስጋናችን ከፍ ያለ ነው፡፡ 









አስተያየቶች

  1. ትልቅ የሀገር ታሪክ ወቅቱ በሚጠይቀው በቴክኖሎጂ የመስነድና ለትውልድ የማቆየት ኃላፊነት የተሞላበ ታሪካዊ ሥራ ነው በርቱ 🙏🏼 it's great job ❤️

    ምላሽ ይስጡሰርዝ

አስተያየት ይለጥፉ

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች