ኢንጂነር ገሰሰ አባይ
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያው ዘርፍ ጉልህ አሻራ የነበራቸውን ጋዜጠኞች፣
የቴክኒክ ሰዎች ፣ የሚድያ መምህራን ፣ የማስታወቂያ ሚኒስቴር የሥራ መሪዎችን እያፈላለገ የህይወት ታሪካቸውን እየሰነደ ይገኛል፡፡ ይህ የተሰነደ ታሪክ
መዝገበ- አእምሮ መጽሀፍ ቅጽ 2 ላይ የሚወጣ ሲሆን ቅጽ 1 መዝገበ-አዕምሮ ከፍተኛ ተቀባይነት ማግኘቱ ይታወቃል፡፡ አሁን በዚህ ጽሁፍ
ታሪካቸው የሚዳሰሰው ኢንጂነር ገሰሰ አባይ ናቸው፡፡ እርሳቸውም በኢቲቪ ምስረታ ሰሞን በቴክኒክና በጣቢያው የምህንድስና
ሥራ ላይ ደማቅ አሻራ ያኖሩ ናቸው፡፡ በአሁኑ ሰአት የ88 አመት አዛውንት ናቸው፡፡ ባለውለታን ማሰብ፣ ሰርቶ ደክሞ የራሱን
ማንነት ያኖረን ሰው መዘከር ዋናው ግባችን ነውና የኢንጂነር ገሰሰ አባይን የህይወት ገጽ መፈተሸ እንጀምራለን፡፡ ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒሽን ከጥቅምት 21 2015 -ጥቅምት 30 2015
የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን 58ኛ አመት እያሰበ ስለሆነ ኢንጂነር ገሰሰ ደግሞ ከኢቲቪ ባለውለታዎች አንዱ ስለሆኑ በዚህ አጋጣሚ የእውቅና ማእረግን እናጎናጽፋቸዋለን፡፡ እዝራ እጅጉ ታሪካቸውን እንደሚከተለው ሰንዶታል፡፡
ማንነት ባጭሩ
ኢንጂነር ገሰሰ አባይ መስከረም 1927 ዓ.ም በአድዋ እንዳስላሴ ተወለዱ፡፡የአንደኛ
ደረጃ ትምህርታቸውን በንግስት ሳባ ትምህርት ቤት ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ያሁኑ ኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ተከታትለዋል፡፡ከዚያም ለከፍተኛ
ትምህርት ወደ ህንድ አመሩ፡፡ከህንድ ፑና ዩኒቨርሲቲ በቴሌኮሙኒኬሽን ኢንጂነሪንግ በባችለር ዲግሪ ተመርቀዋል፡፡ ወደ አገር ቤት
ተመልሰው በኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ከ1948-1970 አገልግለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በውሰት ከ1967-1968 ለአንድ
አመት ሰርተዋል፡፡በዝውውር ዋና መሀንዲስ ሆነው ደግሞ ከ1970-1985 አገልግለዋል፡፡ የ88 አመት አዛውንት የሆኑት ኢንጂነር ገሰሰ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዋና
መሀንዲስ በመሆን ከ 17 አመት በላይ ካገለገሉ በኋላ ሬድዮ ፋና ሲመሰረት በቴክኒካል ጉዳይ ከማማከር ጀምሮ በመስራችነት የሰሩ
ናቸው፡፡ በመቀጠልም የደቡበ አፍሪካው ኤምኔት ወይም ዲኤስቲቪ ሲጀመር ከመስራች መሀንዲሶች መካከል ቀዳሚው እርሳቸው ናቸው፡፡
ቀጥለውም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውስጥ በቴክኒካል አማካሪነት አገልግለዋል፡፡ በቶምሰን/ ታሌስ ኩባንያም ውስጥ
የኢትዮጵያ ወኪል ነበሩ፡፡የ3 ልጆች አባትና የ 10 የልጅ ልጆች አያት የሆኑት ኢንጂነር ገሰሰ ከባለቤታቸው ከወይዘሮ አበባ
ገብረስላሴ ጋር እየኖሩ ይገኛሉ፡፡
የኢቲቪ የስርጭት
አድማስ
ኢንጂነር ገሰሰ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሲመሰረት የስርጭት አድማሱ ምን ያህል እንደነበር
አይዘነጉትም፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት ያኔ የማሰራጫው አንቴና ከክብደቱ የተነሳ በአዲስ አበባ ሊተከል አልቻለም
ነበር፡፡ትራንስሚተሩ በትንሽ ጊዜያዊ አንቴና የስርጭት ጉልበቱን
ቀንሶ ሽፋኑ ለአዲስ አበባና አካባቢዋ ብቻ የተወሰነ ነበር፡፡ብዙ ሳይቆይ አንድ ባለ 10 ዋት የቲቪ ትራንስሚተር ቦኩ ተራራ
ላይ ተተክሎ ለአዳማ ከተማ አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡ ቦኩ ተራራ ከአዳማ ወደ ሶደሬ በሚወስደው መንገድ ሲጓዙ ቦኩ ተራራ
ይታያል፡፡
እንደ ኢንጂነር ገሰሰ አባባል እስከ 1967 ድረስ ማለትም ለ10 አመታት ያህል
የቴሌቪዥንን የቴክኒክና የስርጭት አቅም ለማጎልበት አልተቻለም፡፡ በ1955 ዓ.ም ከስዊድን ሀገር በቴሌኮሚኒኬሽን በኩል
ለቴክኒክ ማኔጅመንት የመጡ ሚስተር ሄርማን ሩድ የተባሉ መሀንዲስ በሄሊኮፕተር እየተዘዋወሩ የአካባቢ ጥናት አደረጉ፡፡ለኢትዮጵያ ሬድዮና
ለብስራተ ወንጌል ሬድዮ በጌጃ ዴራ የስርጭት ቦታዎችን መረጡ፡፡
በ1967 ዓ.ም በማስታወቂያ ሚኒስቴር ስር የኢትዮጵያ ብሮድካስት ድርጅት የሚባል
የሥራ ዘርፍ ነበር፡፡ድርጅቱንም ይመሩ የነበሩት አቶ ገዳሙ አብርሀ ነበሩ፡፡ እርሳቸው በኢትዮጵያ ቴሌኮሚኒኬሽን ታላቅ ስብሰባ
ላይ ‹‹ የሬድዮ ቴክኒክ ሥራ ከጥንት ጀምሮ በቴሌኮሚኒኬሽን ኢንጂነሪንግ ስር ስለሆነ በእርሱ በኩል ምንም ችግር
አልነበረብንም፡፡ ይሁንና የቴሌቪዥን ቴክኒክ ያቋቋመው የውጭ ሀገር ድርጅት ቶምሰን ቴሌቪዥን ኢንተርናሽናል ጥሎን
ሄዷል፡፡እንዲሁም ሚስተር ማክስ ቶምሰን የተባሉ ኩባንያው መድቧቸው የነበሩ ዋናው መሀንዲስ ከአብዮቱ ፍንዳታ በኋላ ወደ
ሀገራቸው ጠቅለው ሄደዋል፡፡እኛም የቴክኒክ ክፍሉን ሊመሩ የሚችሉ ባለሙያዎችን ቀድመን አላዘጋጀንም፡፡እንደምታውቁት በጣም ከባድ
ችግር ላይ ነበርን፡፡ስለዚህ ቴሌቪዥን ከሬድዮ ጋር ተቀናጅቶ አንድ ላይ በቴሌኮሚኒኬሽን ኢንጂነሪንግ ስር ይደረግልን ›› በማለት ጥያቄያቸውን አቀረቡ፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌኮሚኒኬሽንም ጥያቄውን
እንደማይቀበለው አስታወቀ፡፡የሬድዮ ብሮድካስት ከረጅም ጊዜ ጀምሮ በቴሌኮሚኒኬሽን የሚካሄድ ነበር፡፡ ቴሌቪዥን ሲቋቋም
ከቴሌኮሚኒኬሽን ምንም አይነት የስራ ግንኙነት አልነበረውም፡፡ ያስቸግረናል በሚል ጥያቄውን አልተቀበሉትም፡፡
ጉዞ ወደ ኢቲቪ
ኢንጂነር ገሰሰ አባይ ግንቦት 14 1967 ዓ.ም ከቴሌኮሚኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ
በተጻፈ ደብዳቤ በቦርዱና በሬድዮ እና ቲቪ ድርጅት መካከል በተደረገ ስምምነት በውሰት ለ6 ወራት ተመደቡ፡፡ አንደኛ ተጠባባቂ
ዋና መሀንዲስ ሆነው በጊዜያዊነት እንዲሰሩ ተደረገ፡፡ ከሥራው ጋር በተያያዘም አስቸኳይ ትእዛዝ ተቀበሉ፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን
ድርጅትን በ4 ወራት ጊዜ ውስጥ በቴሌኮሚኒኬሽን ቦርድ ስር ለማስተዳደር የሚያስፈልገውን ዝግጅትና የሚያስከትለውን ወጪ፣ አሁን
ባለበት አቋም የሚሻሻልበትን መንገድና ሌላም አማራጭ ቢኖር አጥንተው ሪፖርት አቅርቡ የሚል ጥብቅ መመርያ ተሰጣቸው፡፡መመርያውንም ተቀብለው ማስታወቂያ
ሚኒስቴር ሄዱ፡፡ መልካም የሚባል አቀባበል ተደርጎላቸው ሥራቸውንም ጀመሩ፡፡
ኢንጂነር ገሰሰ እንደሚናገሩት በ1950ዎቹ የቴሌቪዥን ስርጭት በጣም የተዳከመና የሚቆራረጥ ነበር፡፡በዚህ ምክንያት
አዲሱ የብሮድካስት ሥራ አስኪያጅ ለአዲስ አበባና ለአካባቢዋ ቴሌቪዥን ማሰራጫ መሳርያ የቴክኒክ ጥናት እንዲከናወን ጠይቀዋል፡፡
በጊዜው የመስክ ጥናት ተካሂዶ በቂ የስርጭት ሽፋን ሊሰጥ የሚችል ባለ አንድ
ኪሎዋት ማሰራጫ ትራንስሚተርና አንቴና ከተሟላ አባሪ መሳርያ እንዲገዛ ኢንጂነር ገሰሰ ጥያቄ አቀረቡ፡፡በጀቱም ወዲያው
ተፈቀደ፡፡ለመሳርያዎቹም የግዢ ጨረታ ወጣ፡፡ በጨረታውም አሸናፊ የነበረው የጃፓኑ ኩባንያ ነበር፡፡ የዚሁ የጃፓን ኩባንያ
ተወካዮች በወቅቱ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን መምሪያ ኃላፊ ከነበሩት ከአቶ አዛርያ ኪሮስ ጋር በመነጋገር የመሳርያዎች ግዥና አቅርቦት
በአጭር ጊዜ ውስጥ ተከናወነ፡፡ በዚያን ጊዜ የቴሌቪዥን የወደፊት እድገት ከቴሌኮሚኒኬሽን የማይክሮዌቭ ሪሌይ ሲስተም ጋር
የተያያዘ ነው፡፡ ከቴሌኮሚኒኬሽን ፈቃድ ተጠይቆ የስርጭት አንቴናው
በቴሌኮሚኒኬሽን የማይክሮዌቭ ምሰሶ ላይ ተገጣጠመ፡፡ማሰራጫ መሳሪያው በአካባቢው በነበረው ህንጻ ውስጥ
ተከላው ተካሂዶ ደረጃውን የጠበቀ የቲቪ ስርጭት በ1969 ዓ.ም
ተጀመረ፡፡ ከጥቂት ወራት በኋላም ኢንጂነር ገሰሰ በጊዜያዊ
ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰብሳቢ ፊርማ ከመስከረም ወር 1970 ጀምሮ የቴሌቪዥን ዋና መሀንዲስ ሆነው እንዲሰሩ ከውሳኔ ላይ ተደረሰ፡፡
ኢንጂነር ገሰሰ መመርያውን ለመቀበል እጅግ አዳጋች ቢሆንባቸውም የግድ ግን
መቀበል ነበረባቸው፡፡ ሀገራቸውን በቅንነትና በታማኝነት ለማገልገል ለራሳቸው ቃል ገቡ፡፡ ለ22 አመት ካገለገሉበት የኢትዮጵያ
ቴሌኮሚኒኬሽን መስርያ ቤት ወደ ማስታወቂያ ሚኒስቴር አመሩ፡፡
በኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም ምድብ ሥራቸውን ጀመሩ፡፡ በማስታወቂያ ሚኒስቴርም ጥሩ የሚባል አቀባበል ተደረገላቸው፡፡ስራቸውንም
ሲጀምሩ አስቀድመው ከእንግሊዙ መሀንዲስ ጋር ይሰሩ ከነበሩት
ባለሙያዎች ጋር ሌት ተቀን መከሩ፡፡ለወደፊት ሥራቸው በሚጠቅማቸው ጉዳይ ላይም መከሩ፡፡ ቴሌቪዥን በሙያ ፤ በመሳርያዎች
በአሰራር ስርአት ፤ በስርጭት ጥራትና እንዲሁም በስርጭት ስፋት ረገድ ካልተሻሻለ በስተቀር በወቅቱ ከነበሩት ጉራማይሌ የቴክኒክ
ችግሮች ሊወጣ እንደማይቻል ኢንጂነር ገሰሰ ከባለሙያዎቹ አረጋገጡ፡፡ ሙያተኞችም እጅ ለእጅ ተያይዘው የተሻለ ሥራ ለመስራት
ተነሱ፡፡
መሀንዲሶቼን
አትንኩብኝ
ኢንጂነር ገሰሰ እንደሚያስታውሱት በደርግ አስተዳደር ጊዜ ቴሌቪዥን ሲቋረጥ
የቴክኒክ ብልሽት ሳይሆን የጸረ- አብዮተኞች አሻጥር ወይም
ሳቦታዥ የሚል እጅግ አደገኛ ፍረጃ ነበር፡፡ ከዚህ አንጻር ኢንጂነር ገሰሰ ከማስታወቂያ ሚኒስቴር ተመድበው የመጡ ሚኒስትሮች
እንደ እድል ሆኖ በጣም ጥሩ አስተሳሰብ የነበራቸው ነበሩ ሲሉ ስማቸውን በበጎ ያነሱታል፡፡ ‹‹ እናንተ ሥራችሁን ስሩ ፡፡ እኔ
ከወዲያ የሚወረወረውን ድንጋይ እቋቋማለሁ፡፡.›› ይሉ ነበር፡፡
የቀድሞ ማስታወቂያ እና መርሀ-ብሄር ሚኒስትር ግርማ ይልማ‹‹ መሀንዲሶቼን
አትንኩብኝ ›› ቀጥለው የመጡት ሚኒስትር ዶክተር ፈለቀ ገድለጊዮርጊስ ፤ የቲቪ መምርያ ኃላፊ አቶ ኃይለማርያም ጎሹ
ባለሙያዎችን እንደ እንቁላል መያዝ አለብን ይሉ ነበር፡፡ ይህ
የጥቂት ግለሰቦች አስተሳሰብ በወቅቱ ከነበረው ውዥንብር አንጻር ሲታይ ለሥራው አስተዋጽኦ ማድረጉን ኢንጂነር ገሰሰ ይናገራሉ፡፡
ኢንጂነር ገሰሰ የዛሬ 50 አመት የቴሌቪዥንን ስርጭት በስፋትና በጥራት ለማሻሻል
በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ይናገራሉ፡፡ በወቅቱ የቴሌቪዥን መሰረተ-ልማትን ለመዘርጋት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ይጠይቅ
ነበር፡፡ታዲያ በየዓመቱ ለሚቀርበው እቅድ ማስፋፊያ የገንዘብ ሚኒስቴር ሰዎችን አሳምኖ ማስፈቀድ ከባድ ነበር፡፡ ታዲያ በእነ
ኢንጂነር ገሰሰ የሚመራው ቡድን ለአዲስ ቴክኖሎጂ ብቃት ያላቸው
ለጥገና ሙያ ዝግጁ የሆኑ ባለሙያዎችን ማፈላለግ ነበረባቸው፡፡የቴሌቪዥን ስርጭት ባህሪይ ከፍ ያለ ወይም ተራራማ ቦታ ስለሚፈልግ
በየክፍለ-ሀገሩ የመስክ ጥናት ለማከናወን የሚጠይቀው የሙያተኛና
የትራንስፖርት ውስንነት ለመቅረፍ ተሞከረ፡፡ የመሳሪያ ተከላ ሥራውም ተካሄደ፡፡ ቦታው በጣም አስቸጋሪ ቢሆንም የኦፕሬሽን እና
የጥገና ባለሙያዎች መመደባቸውን ኢንጂነር ገሰሰ ያስታውሳሉ፡፡ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ለሚጠይቁት ብሎም ከፍተኛ ከብደት ላላቸው
የአንቴና ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች መፍትሄ ተሰጠ፡፡
የስቱድዮ ጉዳይ
ኢንጂነር ገሰሰ የስቱድዮ ጉዳይን በተመለከተ የተሰራውን ሲያስረዱ‹‹….ለብዙ
ዘመናት ያገለገለውን የቴሌቪዥን ስቱዲዮ በወቅቱ በተደረሰበት ቴክኖሎጂ መሳሪያዎቹን በሙሉ መደበኛው ፕሮግራም ሳይቋረጥ መተካት
ችለናል፡፡ለፕሮግራም ዝግጅትና ስርጭት ምንጭ የሆነውን አሮጌውን ስቱዲዮ በአዲስ የመተካት ስራ በድርሻችን መስራት ጀመርን፡፡
ስቱዲዮ በአዲስ ለመተካትም አስፈላጊውን መስፈርት ፤ የመሳሪያዎች ዝርዝርና ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ በጀት፡ ለበላይ ቀርቦ
ተፈቀደ፡፡ከጨረታ ውድድር ጀምሮ እስከ ተከላ የነበሩትን ሂደቶች በማከናወን የተሻሻለው አዲሱ ስቱድዮ አሮጌውን ስቱዲዮ ተክቶ
በ1970 ዓ.ም አገልግሎት መስጠቱን ጀመረ፡፡.›› በማለት ተናግረው ነበር፡፡
ከ1970 በኋላ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የክልል ስርጭቱን ለማስፋት በርካታ
ተግባራትን ማከናወን ጀመረ፡፡ በግንቦት19 1971ዓ.ም በየሁለት ወሩ ሊተገበሩ የሚችሉ የ16 የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የተሟላ
የቴክኒክ፤የዋጋ፤የአፈጻጸም፤ዝርዝር ያካተተ የቴሌቪዥን ማስፋፊያ እቅድ በሚኒስትሩ በኩል ለበላይ ቀረበ፡፡ ከዚያም የሚመለከታቸው ባለስልጣናትና በማስታወቂያ ሚኒስትሩ
ግርማ ይልማ የተመራ ቡድን በተገኙበት ስለ እቅዱ ሰፊ ገለጻ ተሰጠበት፡፡ከውጪ ምንዛሪ አንጻር እየታየ በየበጀት ዓመቱ ተጠይቆ
መፈቀድ እንዳለበትም ተወሰነ፡፡ በዚሁ መሰረት የቢሾፍቱ፤ የአዳማ ፤ የጅግጅጋ ፤ የሀረር እና የድሬደዋ የቲቪ ጣቢያዎች
በየሁለት አመቱ በጀት እየተፈቀደ ጣቢያዎቹ ለስርጭት በቁ፡፡ ኢንጂነር
ገሰሰ ስለዚያ ዘመን ሲያስታውሱ ጣቢያውን ዕውን ለማድረግ የነበረው ታላቅ ርብርብ ድንቅ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡
ባለቀለም
ቴሌቪዥን
ይህ ርብርብ ወይም
ባለሙያዎች ያሳዩት የነበረው ትጋት ተጠናክሮ ቀጥሎ የኢትዮጵያ ቲቪ 20ኛ አመት የምስረታ በአሉን ሲያከብር ከጥቁርና ነጭ ወደ
ባለቀለም ቴሌቪዥን ሽግግር አደረገ፡፡ ስለዚህ ድንቅ ሽግግር ኢንጂነር ገሰሰ ሲያስታውሱ‹‹‹… በ1976 ዓ.ም የበጀት አመት ለቀጣዮቹ ሁለት ጣቢያዎች ስንዘጋጅ የደርግ
መንግስት 10ኛውን የአብዮት በአል ለማክበር ወሰነ፡፡ በሁሉም የሥራ መስክ ለዚሁ በአል ልዩ ዝግጅት እንዲደረግ ከደርግ
መንግስት የሱሪ በአንገት መመርያ ጎረፈ፡፡ የማስታወቂያ ሚኒስቴርም በድርሻው ከተሰጡት ጥብቅ መመሪያዎች አንዱ ሥራ ላይ ያልዋሉትን ጣቢያዎች በሙሉ ለ10ኛው የአብዮት በአል
ተተክለው ስርጭት እንዲጀምሩ የሚል ነበር፡፡በወቅቱ በቦታው የነበሩት ሚኒስትር ዶክተር ፈለቀ ገድለጊዮርጊስ አስቸኳይ ስብሰባ ጠርተው ዱብ እዳውን ገለጹ፡፡ ይህም ጥቁርና ነጭ
ሞኖክሮም ፤ ቴሌቪዥን ወደ ባለቀለም እንዲለወጥ ሁለት ባለቀለም መኪና ላይ የተጫኑ ስቱዲዮዎች አብረው እንዲገዙ የሚል
ነበር፡፡›› በማለት ሁኔታውን በትዝታ ያነሳሉ፡፡
ኢንጂነር ገሰሰ እንደሚናገሩት የቲቪ ስርጭቱን ለማድረስ የነበረው ወሳኝ ጉዳይ
ከዋናው የቲቪ ስቱድዮ የሚመነጩትን ኦድዮ ቪድዮ ሲግናል ፕሮግራሞች የሚያከፋፍል ኔትወርክ ጉዳይ ነበር፡፡ የቴሌኮሚኒኬሽን
መስሪያ ቤት ገና ከመነሻው ከነባሩ የማንዋል ቴሌፎን ወደ አውቶማቲክ ዲያሊንግ ሲስተም ደረጃ በደረጃ ለመለወጥ እቅድ ሲያወጣ
የወቅቱ ቴክኖሎጂ የማይክሮዌቭ ብሮድባንድ መስመሮች በአርቆ አስተዋይነት የቴሌቪዥን ሲግናል ማሳለፍ እንደሚችል ዲዛይን 1†1
በሚል አስተሳሰብ የተካተተ ነበር፡፡ እነዚህ መስመሮች ባሉባቸው አካባቢዎች በማስታወቂያ ሚኒስቴርና በቴሌ መካከል ስምምነት
ተደረሰ፡፡
የ10 ጣቢያዎች መከፈት
10 የስርጭት ጣቢያዎችን ለመክፈት ከጃፓኑ ማሩበኒ ኤን.ኢ ሲ እና ከፈረንሳዩ
ቶምሰን ብሮድካስት ጋር ስለተፈረመው የውል ሰነድ ምን ገጽታ እንደነበረው ኢንጂነር ገሰሰ ሲያስረዱ
‹‹…..የአስሩ ጣቢያዎች እቅድ ሰፋ ያለ የመስክ ጥናት ይፈልግ ነበር፡፡
በአስቸኳይም እንደየቦታው ሁኔታ በሰራተኛና ያለ ሰራተኛ አውቶሜትድ የማሰራጨት መሳሪያዎች አጠናን፡፡ በተጠናው የስርጭት ፓተርን
መሰረት የማሰራጫ አንቴናዎች የቲቪ ኦድዮ ቪድዮ ሲግናሉን ከማይክሮዌቭ ጣቢያዎች ወደ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች የሚያስተላልፉ መገናኛ
መሳሪያዎች ዘረዘርን፡፡ እንደ አስፈላጊነቱም የኤሌክትሪክ ማመንጫ ተጠባባቂ ጄኔሬተሮች፤ የጥገና መለኪያ መሳሪያዎች እንዲሁም
ለ2 አመት የጥገና ስራ የሚያስፈልጉ መለዋወጫ እቃዎችን አካተትን፡፡ በሁሉም ዘርፍ የተሟላ የመሳሪያዎች ይዘትና የቴክኒክ
የብቃት ደረጃ ከተሟሉ የጨረታ ሰነዶች ጋር ሌት ተቀን አዘጋጀን፡፡ በሙያው ታዋቂ ለሆኑት አምራች የውጭ ኩባንያዎች በአስቸኳይ
የማቅረቢያ የጊዜ ገደብ ተቀምጦ ላክንላቸው፡፡ የጃፓኑ ማሩበኒ
ኤን.ኢ ሲ እና የፈረንሳዩ ቶምሰን ብሮድካስት ተመርጠው ለፈጣን ስራ አመቺ በሆነ ሁኔታ በየክፍለ-ሀገሩ ከተሞች ለሁለቱ
ኩባንያዎች ተከፋፈሉ፡፡ ከእያንዳንዱ ኩባንያም ጋር ሁለት የኮንትራት ውል ተፈራረምን፡፡ ወዲያውኑ ኩባንያዎቹ በየድርሻቸው
እንዲሁም የማስታወቂያ ሚኒስቴርም በድርሻው ወደ ሥራ ገባን›፡፡›› በማለት ኢንጂነር ገሰሰ አስታውሰዋል፡፡
ባለ
ቀለም ተንቀሳቃሽ ስቱዲዮ አመጣጥ
ኢንጂነር ገሰሰ ሲናገሩ‹‹….የቴሌቪዥን ስቱዲዮውን ወደ ባለቀለም ለመለወጥ
የሚያስፈልጉ ተጨማሪ እቃዎች ጉዳይ ፣ የሁለት ባለ ቀለም ተንቀሳቃሽ ስቱዲዮዎች የመሳሪያዎች ይዘት ዝርዝር ወጥቶላቸው የደርግ መንግስት በፈቀደው የግዥ ስርአት መሰረት ከእንግሊዝ አገር
በአስቸኳይ እንዲመጡ ተወሰነ፡፡ የአስሩ ጣቢያዎች ፕሮጀክትና ስቱዲዮውን ወደ ባለቀለም የመለወጥ ሥራ እንዲሁም የተንቀሳቃሽ ስቱዲዮ ስራ ሙሉ በሙሉ ተጠናቀቀ፡፡ በጊዜው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከሁለት ያረጁ ሞኖክሮም ካሜራዎችና በየጊዜው
ከሚቋረጥ ያረጀ ባለ 500 ዋት ማሰራጫ ጣቢያ ተላቆ ባለ 5 ባለ ቀለም ካሜራ ስቱዲዮዎች እያንዳንዳቸው 3 ካሜራዎች የተጫኑ
ተንቀሳቃሽ ባለ ቀለም ስቱዲዮዎች በአዲስ አበባና እና በ27 የክፍለ-ሀገር ዋና ከተሞች የ22 ባለቀለም ማሰራጫ ጣቢያዎች
ባለቤት ሆነ፡፡›› ብለው ነበር፡፡
አቶ ሀብቴ ገመዳ ስለ ኢንጂነር ገሰሰ አባይ ጠይቀናቸው ሲናገሩ ለሙያው ከፍተኛ
መስዋእትነት የከፈለ የኢቲቪ ባለውለታ ነው ስሌ ነግሮናል፡፡ አቶ
ሀብቴ ከኢንጂነር ገሰሰ ጋር ለ15 አመት እንደ መስራቱ ባለሙያው ኢንጂነር ቴሌቪዥን ጣቢያውን አሁን ላለበት ደረጃ ለማድረስ
የከፈሉት መስዋእትነት በደማቅ ብእር መጻፍ ያለበት ነው ይላል፡፡
ምስጋና ለዚህ ጽሁፍ የረዱንን
ጋዜጠኛ ጌጡ ተመስገን ፤ የኢንጂነር ስ ገሰሰ ልጅ
ስምኦን ገሰሰ የኢቲቪ የስራ ሃላፊዎችን እናመሰግናለን፡፡
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ