አቢይ ደምለው

 

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያው ዘርፍ ጉልህ አሻራ የነበራቸውን ጋዜጠኞች፣ የቴክኒክ ሰዎች ፣ የሚድያ መምህራን ፣ የማስታወቂያ ሚኒስቴር የሥራ መሪዎችን  እያፈላለገ የህይወት ታሪካቸውን እየሰነደ ይገኛል፡፡ ይህ የተሰነደ ታሪክ መዝገበ- አእምሮ መጽሀፍ ቅጽ 2 ላይ የሚወጣ ሲሆን ቅጽ 1 መዝገበ-አዕምሮ ከፍተኛ ተቀባይነት ማግኘቱ ይታወቃል፡፡  አሁን በዚህ ጽሁፍ   ታሪኩ የሚዳሰሰ አው ጋዜጠኛ አቢይ ደምለው ነው፡፡ አቢይ በህትመትና በኤሌክትሮኒክስ ዘርፍ የራሳቸውን ጉልህ አሻራ ካኖሩት አንዱ ነው፡፡ የህይወት ታሪኩን እንደሚከተለው አጠናክረነዋል፡፡

 

                 ውልደትና እድገት

 

   ጋዜጠኛ አቢይ ደምለው  በመጋቢት 5 1966 ተወለደ፡፡የአቢይ ደምለው ውልደት፡ እድገትና የጋዜጠኝነት ሀሁ የሚጀምረው በሐረር ከተማ 1980ዎቹ መጨረሻ አካባቢ ነው፡፡ ወቅቱ በሐረር ከተማም ይሁን በመላ ሀገሪቱ የአማተሪዝም እንስቃሴዎች ጎልተው የወጡበትና የቀድሞው የኢህዲሪ መንግስት ለወጣቱ የተለያዩ የተሰጥኦ ማበልፀጊያዎች ያስፋፋበት ዘመን ስለነበር፤ በክልሉ የባህል ሚኒስቴር የተሰጡ የቴአትር፡ስነፅሁፍና የጋዜጠኝነት ስልጠናዎችን ገና በልጅነት ማግኘትችላል፡፡

 

በሁሉም ዘርፎች የነበረው ተሳትፎ እየጎላ ቢሄድም በተለይ ግን ወደ ጋዜጠኝነቱ የነበረው ጉዞ እየጎላ መጥቶ 80ዎቹ መጨረሻ በሐረር ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሚኒ ሚዲያ "አርብን ላንዳፍታ" የሚባል ከት/ቤቱ አልፎ በከተማው ህዝብ ይደመጥ የነበረ ዘግጅት አዘጋጅቶ በማቅረብ ይታወቃል፡፡

 

ታድያ የዝግጅቱ አቀራረብ የክፍለ ሀገሩን ትምህርት ቢሮ ብቻ ሣይሆን አዲስ አበባ ላይ ለነበሩትም የኢትጵያ ሬድዮ ሰዎች ጆሮ ደርሶ ነበርና በወጣቶች ፕሮግራም ላይ ትውውቅና ሽፋን ሊሰጠው ቻለ፡፡

 

            የሐረሩ አብይ"

 

"የሐረሩ አብይ" የሚለውን ስያሜ የሰጠው የወቅቱ የኢትዮጵያ ሬድዮ የእሁድ ፕሮግራም አዘጋጁ ታምራት አሠፋ ነበር። በየሳምንቱ በቋሚነት "እሁድ ፕሮግራም" "ፖሊስ" "ቅዳሜ መዝናኛ" "ቅዳሜ ምሽት ምርጥ ሙዚቃ" ፕሮግራሞች ላይ የተለያዩ የመዝናኛና ማህበራዊ ሂሶችን በመፃፍ በሳምንት ቢያንስ አራት ገዜ ስሙ የሚጠራለትና መጣጥፎቹ "የሐረሩ አብይ" በሚል ስም የሚቀርብላት ሆነ፡፡ ይሄ ለረጅም ጊዜ ቀጥሏል።

       አለም አቀፍ የሚዲያ ግንኙነት

       (Correspondence)

ገና ከልጅነት ጀምሮ አብረውት ካደጉትና ለበኋላው ፕሮፌሽናል ህይወቱ የተለያዩ በረከቶች ይዘው ከሚመጡት የህይወት መንገዶቹ አንደኛው የነበረው ከተለያዩ አለምአቀፍ ተቋማት፣ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም ከሚዲያ ተቋማት ጋር የመሰረተው የመፃፃፍ ግንኙነት አንዱ ነበር።

ቪኦኤ(እንግሊዝኛው) ቢቢሲ፣ UAE ሬድዮ በቋሚ ተሳታፊነት ሽልማት ካበረከቱለት ተቋማት ይጠቀሳሉ።

 

ይህ በዚህ እንደቀጠለ ከአለምአቀፍ የትምህርት ተቋማት ጋር የሚያደርገው ያልተቋረጠ  ግንኙነት በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ የትምህርት ዕድሎች ቢያስገኙም ይሁንና በተለያዩ ጥቃቅን ምክንያቶች ሲሰናከሉ ቆይተው፣ በስተመጨረሻው ግን ጋዜጠኝነትን በፕሮፌሽናል ተቋም ለማጥናት የሚያስችለው እድል ተገኘ።

 

           ፕሮፌሽናል ጋዜጠኝነት

 

የጋዜጠኝነት የመጀመሪያውን ፕሮፌሽናል የትምህርት እድል የተገኘው በደቡብ አፍሪካ ኬፕታውን ከሚገኘው Bush Radio ነበር። ሬድዮ ጣቢያው ለተለያዩ ሀገራት ጋዜጠኞች የሚሰጠው የትምህርትና ስልጠና ፕሮግራም መሰረታዊ የብሮድካስት ጆርናሊዝም ኮርሶችን፣ Analog & Digital Editing Radio Production የላይቭ ፕሮዳክሽን እና Hosting ጨምሮ በተግባር በተደገፈ ስልጠና ስለሚሰጥ፤ ይህ ዕድል ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጠውና በአብይ ደምለው ህይወት ውስጥም ከፍተኛ አቅም የፈጠረ ነበር።

ከዚያም በተከታታይ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ናይሮቢ ኬንያ፣ Media Ethics: Media & Human Rights: Conflict Reporting እና ተያያዥ ኮርሶችን በተከታታይ በመውሰድ ፕሮፌሽናል ጋዜጠኝነትን አጠናክሮ ጉዞውን ቀጠለ።

ከዚያም ወደ ሰሜን አውሮፓ በመጓዝ በኖርዌይ Mediēsköllen Shchool of Journalism ከፍተኛ የትምህርት ዕድል በማግኘት ብሮድካስት ጆርናሊዝም፣ Media Ethics Radio Production ፕሪንት እና ዌብ ጆርናሊዝምን አጥንቷል።

 

በመቀጠልም በአለም ባንክ የተዘጋጀ የምርመራ ጋዜጠኝነት (Investigative Journalism) በአፍሪካ ህብረትና ኬፕታውን ዩኒቨርስቲ የተዘጋጀውን አርት ጆርናሊዝም (Arts Journalism) ወዘተ በተከታታይ ከወሰዳቸው ፕሮፌሽናል ኮርሶች መካከል ይጠቀሳሉ።

 

ፕሮፌሽናል ጋዜጠኝነት

አዲስ ብሮድካስቲንግ ኩባንያ (አዲስዜና ጋዜጣ)

 

አብይ ደምለው በፕሮፌሽናል ደረጃ ጋዜጠኝነትን የሚጀምረው በሀገራችን የመጀመሪያው የግል ሬድዮ ሆኖ ተመስርቶ በነበረው አዲስ ብሮድካስቲንግ ኩባንያ ነበር።

በብዙዎች ከፍተኛ ተስፋ የተጣለበትና የሃገራችንን የሚዲያ ዘርፍ ላይ ትልቅ አሻራ ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቅ የነበረው ABC ሲቋቋም ከመጀመሪያዎቹ ጥቂት አባላቱ አንዱ በመሆን የኩባንያውን ሙሉ አደረጃጀት፣ የሰው ሀይል ስልጠና፣ ኤዲቶሪያል ፖሊሲ ወዘተ ከቀረፁት አንዱ ነበር።

 

የብሮድካስት ፈቃድ ለመስጠት በወቅቱ መንግስት ከፍተኛ ፍራቻና ዳተኝነት በማሳየት ድርጅቱን በተለያዩ ዘርፎች ከፍተኛ የማዳከም ስራ እየሰራበት ነበር። ካምፓኒው በወቅቱ በአገር ውስጥና ውጪ በሶስት ዙር ጋዜጠኞች አሰልጥኖ፣ በኖርዌጂያን የስቱዲዮ ግንባታ ኤክስፐርቶች የስቱዲዮ ግንባታ፣ የቴክኖሎጂ ዝርጋታና የማሰራጫ ማሽኖች ተከላ ጨርሶ ፍቃድ ብቻ ይጠባበቅ ነበር።

 

ስለዚህም የሬድዮ ፍቃድ ማግኘት እልህ አስጨራሽ እየሆነ ሲመጣና የሠለጠነ የሰው ሀይል ይዞ ያለስራ መቀመጥ ስለማይቻል በወቅቱ ከሬድዮ ጎን ለጎን በኩባንያው የተጀመረችው "አዲስ ዜና" ጋዜጣ አብይ ደምለው የጥበብና ባህል እንዲሁም የመዝናኛ ገፅ አዘጋጅ በመሆን በህትመት ጋዜጣ ዘርፍ ስራ ተጀመረ።

 

ከጋዜጣው ክፍሎች በተለየ የባህልና ጥበብ እንዲሁም የመዝናኛ ገፆች በርካታ ተከታታዮች የነበረውና ሁሉንም የጥበባት ዘርፎች በተለይም በወቅቱ ብዙም በሚዲያ ትኩረትና ሽፋን የማያገኙ የነበሩ እንደ ቪዡዋል አርትስ፣ የስነ ስዕልና ቀረፃ የመሳሰሉትን ዘውጎች ወደ አደባባይ በማውጣት የሚታወቅ አምድ ነበር።

ይህ የጥበብና ባህል አምድ በተለይም በከተማችን ውስጥ የሚካሄዱ የጥበብ እንቅስቃሴዎችን፣ ክንውኖችን፣ ኮንሰርቶችን፣ ኤግዚቢሽኖችን ወዘተ በመዘገብና በማስተዋወቅ ለአመታት የተወደደ ገፅ ሆኖ ቆይቷል።

በዚህ አምድ ላይ ጥበብና ባህልን በጥልቀት፣ በእውቀትና በምርምር ይሰሩ ነበር። እንዲሁም ሀገር በቀል እና አፍሪቃዊ እሴቶችን አጉልቶ ማውጣትና ለአንባቢው በሰፊው በማስተዋወቅ ትልቅ ስራ ተሰርቷል።

የሬድዮ ብሮድካስት ፈቃድ ለማግኘት በወቅቱ መንግስት በተፈጠረው ጫናና "አዲስ ዜና" ጋዜጣ ህልውና እስካከተመበት 1998 ድረስ ከዚሁ ተቋም ጋር አብይ ደምለው በርካታ ስራዎችን ሰርቷል።

ከህትመት ወደ ህትመት:

 

ቀጣዩም የጋዜጠኝነት ጉዞው የሚቀጥለው በእግሊዘኛ ቋንቋ በሚታተመው ሳምንታዊ ጋዜጣ "ፎርቹን" Fortune ላይ ነበር።

 

አብይ በፎርቹን የዜና ኤዲተር (News Editor) ሲኒየር ሪፖርተር እና የጥበብና ባህል አምድ አዘጋጅ በመሆን ሌላኛው የህትመት ሚዲያ ጉዞ ቀጠለ። በተለይም በኢትዮጵያ ሚሊኒየም ላይ በታተሙ የፎርቹን ህትመቶች ላይ የራሱ የሆነ አሻራ አስቀምጧል።

በተጓዳኝም አሜሪካን አገር ከሚታተመው ጎጆ ማጋዚን (Gojo Magazine) የሚሌኒየም እትሞች ላይ ትልልቅ የሃገሪቱን ባህል ለአለም የሚያስተዋውቁ ሥራዎችን ሰርቷል።

 

          ካፒታል ጋዜጣ Capital

 

በአንፃራዊነት ረዘም ላለ ጊዜ በዜና ኤዲተርነት፣ በባህልና ጥበብ ገፅ አዘጋጅነት እንዲሁም በኢንተርቪው (Interview) ገፆች ላይ በርካታ ስራዎችን በመስራት በሃገራችን ጋዜጠኝነት ብዙም (በወቅቱ) የማይደፈሩ የጋዜጠኝነት ስራዎች የሰራበት ተቋም ነው።

 

በተለይም ጉምቱ የመንግስት ባለስልጣናትን፣ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት፣ የሃገር መሪዎች፣ የአለምአቀፍ ተቋማት ባለስልጣናት ወዘተ በማቅረብ ጋዜጣው በብዙዎች እንዲነበብ የራሱን ትልቅ ድርሻ አበርክቷል።

 

ወቅታዊና አለምአቀፋዊ ጉዳዮችን በጥልቅ ትንታኔ በማየትና ከኢትዮጵያና አፍሪካ ጋር አንፃር በመተንተን በጣም ብዙ ደፋርና በሳል ስራዎች የተሰራበት ጋዜጣ ነው ካፒታል።

 

የተለያዩ ጉባኤዎች፣ ፌስቲቫሎች፣ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ኮንፍረንሶች የሚካሄዱባቸው ሀገራት ድረስ በመጓዝ የካፒታል ጋዜጣን አለምአቀፋዊ እይታ የጨመረ ስራ ሰርቷል። በዚህም ከተለያዩ ኤምባሲዎች፣ አገርአቀፍና አለምአቀፍ ተቋማት እና የመንግስት ክፍሎች ምስጋናና እውቅና አግኝቶባቸዋል።

 

በተጓዳኝም በእንግሊዝኛ ከሚታተሙት Addis Connexion እና Horizon Ethiopia መፅሄቶች ጋር እንዲሁ በተከታታይ ሰርቷል።

 

    ፓን አፍሪካን ጆርናሊዝም

 

አብይ ደምለው የመላው አፍሪቃ የፓን አፍሪቃ ጆርናሊዝም ኔትወርክ አባል በመሆን በተለያዩ ሀገራት ተጨማሪ ስልጠናዎችን በመውሰድ 2008 እ.ኤ.አ ጀምሮ አፍሪቃዊ ጋዜጠኝነትን ለማሳደግ በሚደረጉ ጥረቶች ውስጥ በተለያዩ አፍሪካ ሀገራት ከሚገኙ የተለያዩ ኔትወርኮችና ተቋማት ጋር ዛሬም ድረስ እየሰራ ይገኛል።

 

በዚህም አፍሪካ ህብረትን ጨምሮ ካሉት አህጉር አቀፍ የፓን አፍሪካ የሚዲያ ተቋማት ጋር በርካታ ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል።

 

ጉዞ ወደ ብሮድካስት ጆርናሊዝም

 

አብይ ደምለው ለረጅም ጊዜ ባብዛኛው በህትመትና ዌብ ጆርናሊዝም ላይ ሲሰራ ቢቆይም ቀድሞውንም ቢሆን በዋናነት የብሮድካስት ጆርናሊዝም ተማሪና ታሪክ የነበረ ሰው ስለነበር ወደ ሬድዮ ተመልሶ በመምጣት ሌላ ምዕራፍ ተጀመረ።

 


ሸገር ኤፍ ኤም 102.1

 

በሸገር ኤፍ ኤም ላይ ዛሬም ድረስ የሚተላለፈውን ‹‹አፍሪቃውያን›› የተሰኘውን በአፍሪካዊነት ዙሪያ የሚዘጋጅ ሳምንታዊ ዝግጅት ከቀፀላወርቅ ሠይፉ ጋር አዘጋጅና አቅራቢ በመሆን በአይነቱ ለየት ያለና ከፍተኛ አድማጭ የነበረውን ፕሮግራም ለ5 አመታት በማዘጋጀት ከፍተኛ ዝና፣ አድናቆትና ክብር ማግኘት ችሏል። ፕሮግራሙም በጣቢያው ከሚተላለፉ ፕሮግራሞች በጣም ተወዳጅና ተደማጭ ሊሆን ችሎ ነበር።

በዋነኛነት የመረጃና የመዝናኛ ይዘት ባለው በዚህም ፕሮግራም (በተለየ አቀራረብ) አፍሪካዊ ጉዳዮችን ከኢትዮጵያዊ እይታና ኢትዮጵያዊ ጉዳዮችንም በአፍሪካዊ ዕይታ በመተንተን በርካታ ድንቅ ስራዎች የተሰሩበት የሬዲዮ ዝግጅት መሆን ችሏል።

የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራትን የባህልና የጥበብ ስራዎችን በማስተዋወቅና ራሳቸውን አርቲስቶቹን ጭምር ስቱዲዮ በመጋበዝ ብዙ ግሩም ስራዎች ተሰርተዋል።

 

 

         አፍሮቴይነር_ ኤፍ ኤም አዲስ 97.1

 

የአብይ ደምለው ቀጣዩ የብሮድካስት ጆርናሊዝም ጉዞ ወደ ኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ይመጣና በየሳምንቱ እሁድ በጣቢያው የሚተላለፈውን "አፍሮቴይነር" ፕሮግራም አዘጋጅቶ በማቅረብ ወደ ሌላ ምዕራፍ ተሸጋገረ።

በተለየ አቀራረብ የሚዘጋጀው ይህ ፕሮግራም በአድማጮቹ ለመወደድ ብዙም ጊዜ ያላስፈለገው በሳል የሬዲዮ ፕሮግራም በመሆን በመላው ሀገሪቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ቋሚ ተከታታይ፣ አድማጭና ተሳታፊዎችን ያፈራ ዝነኛ ፕሮግራም መሆን ቻለ።

 

በተለይም ፕሮግራሙ የተጀመረበት ወቅት ሃገራችን ወደ ለውጥ እየተምዘገዘገችበት የነበረ ወቅት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ዛሬም ድረስ ዘልቀው የሚታዩ የጥላቻን፣ ሰላም እጦትና አለመረጋጋትን በእውቀት በመተቸት ፍቅር፣ መግባባትና ሰላም እንዲሰፍን የተለያዩ የአፍሪካ አገራትን ተሞክሮዎችን ጭምር በመተንተን በህዝብ ዘንድ በጣም ተወዳጅ ፕሮግራሞችን ሰርቷል።

 

በኢትዮጵያዊነት ውስጥ አፍሪካዊነትን፣ በአፍሪካዊነት ውስጥ ኢትዮጵያዊነትን በመተንተን እንደ አፍሪካውያን በአህጉሪቱ ታሪክ ውስጥ ያለንን ገናና የታሪክ ድርሻ ላይ ትኩረት በማድረግ ዙሪያ በኪነ-ጥበብ፣ በማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ ብዙ ስራዎች በአፍሮቴይነር ይሰራሉ።

 

የሃገራችንንና የአፍሪካችንን ተፅዕኖ ፈጣሪ የሙዚቃና የጥበብ ሰዎች ስቱዲዮ ጭምር በእንግድነት እየቀረቡ ከታሪካቸው፣ ከእውቀትና ልምዶቻቸው ለትውልዱ እንዲያስተምሩ ስለሚጋበዙ የፕሮግራሙ ተደማጭነት ከፍ ወዳለ ደረጃ ሊያድግ ችሏል።

 

አፍሮቴይነር ከዘመናዊው ኪናዊ ባህላችን በመነሳት የሃገራችንን ባንዶች ታሪክ በራሳቸው በባለሙያዎቹ አንደበት እንዲነገር በማድረግ የበለጠ ተወዳጅነት አፍርቷል። የኪነጥበብ ዘርፉ ጉምቱ ባለሙያዎች፣ ተቋማት፣ የሙያ ማህበራት ወዘተ በስፋት ይቀርቡበታል።

 

በተለይ ግን አገራችን በባለፈው ሶስት አመታት ከገባችበት የሠላም እጦት አኳያ አፍሮቴይነር የጀመራቸው "ሚዲያ ለሠላም" "ኪነ-ጥበብ ለሠላም ግንባታ" የተሰኙ የሚዲያ ተከታታይ ዘመቻዎች በመንግሥት ከፍተኛ አካላት፣ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤና ከተለያዩ ተቋማት ክብርና ምስጋና የተገኘባቸው ናቸው። አንዳንድ ያነሳናቸው ሀሳቦችም በተለያዩ የመንግስት ተቋማት፣ የሚዲያ ተቋማትና ማህበራት እንደምክረ- ሃሳብ የተወሰዱ ጭምር ይገኙበታል።

 

 

       ዶኩመንቴሽንና አርካይቭ

 

ዶኩመንቴሽን እና አርካይቭ በሀገራችን ትልቅና አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑ ይታወቃል። እንደ ሃገር ታሪኮቻችንን በወግና ስርዓት ሰንዶና አዘጋጅቶ ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፍ፣ ጥናትና ምርምር ለሚሰሩ በቀላሉ ሊገኝ እንዲችል አድርጎ ማስቀመጥ ላይ ከባድ ክፍተት ያለብን ህዝቦች ነን።

 

ይህ ደግሞ በየሙያ ዘርፉ በባለሙያዎች፣ በተቋማትና በግለሰቦች የተሰሩ ታሪኮች ተመዝግበው በአንድ ማዕከል መቀመጥ አለመቻላቸው መረጃን ፍለጋ ለሚታትሩ ግለሰቦች መንገዱን ከባድ አድርጎታል።

 

የሩቅ ዘመን ታሪኮች ብቻ ሳይሆን የቅርብ ጊዜያት ሰነዶቻችንም ጭምር ለማግኘት አስቸጋሪና አድካሚ መሆናቸው ይታወቃል። በተለይም በኪነ-ጥበብና በሚዲያው ዘርፍ ላይ ይህ ችግር ጎልቶ የሚታይ ነው።

 

በአንድ ወቅት በሬድዮና ቴሌቪዥን የተላለፉ፣ በጋዜጣና መፅሔት የታተሙ ፅሁፎችን ለማግኘት አድካሚነቱ የትየለሌ ነው። በመንግሥትና ስርዓት መለዋወጥ ብቻ እንኳን አላግባብ የሚጠፋው መረጃ በእጅጉ አሳዛኝ ነው።

የሃገሪቱን ትልቁን የምስልና ድምፅ ክምችት ይዟል ብለን የምንመካበት የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን EBC ላይ በተለያየ ሁኔታ የደረሰው የመረጃ ክምችት መበላሸት፣ መጥፋትና መዘረፍ እዚህ ላይ ጥሩ ምሳሌ ነው።

ስለዚህ የሃገራችን የሚዲያ፣ የኪነ-ጥበብ እና ሌሎችም ታሪኮች ከተቋም ይልቅ በግለሰቦች እጅ መገኘታቸው የሚያረጋግጠው ይህንኑ ሀቅ ነው።

ታዲያ አብይ ደምለው በዚህ ረገድ ከልጅነት ጀምሮ የሰበሰባቸውን የተለያዩ መረጃዎች አደራጅቶና አጠናቅሮ በመያዝ ከሚታወቅባቸው ዘርፎች አንዱ ሆኗል። በሰነድ፣ በድምፅና በምስል ያሉትን የሚዲያ፣ የኪነጥበብ እንዲሁም ሌሎች የሃገሪቱ ታሪኮች ዙርያ የሚዲያ ተቋማት ጭምር ማረጋገጫ ሲፈልጉ የሚጠይቁት ባለሙያ ሊሆን ችሏል።

 

የምርመራ (Investigative) ሪፖርቲንግ ተጠቃሽ ግኝቶች

 

በዜና ዘገባ ደረጃ የተሰሩ የምርመራ (Investigative Reporting) ደረጃ ብዙ ስራዎች የተሰሩ ቢሆንም፤ ተፅዕኖ ከፈጠሩት መሃከል የተወሰኑት እንደዚህ ተቀምጠዋል።

 

       ፓርላማ የደረሰ ሪፖርት EEPCO የቀድሞው ኤልፓ

 

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ኮርፖሬሽን በሀገሪቱ ለሚጠቅምባቸው የሀይል ማስላለፊያ ፖሎች (ግንዶች) በምስጥና እንዳይበሉና በሌሎች ነገሮች ጉዳት እንዳይደርስባቸው ኬሚካል እንዲነከሩ ማድረግ የዘወትር ተግባሩ ነው። ስለዚህም መንከሪያውን ኬሚካል ከተለያዩ ሀገራት በማስመጣት ሲጠቀም ኖሯል።

 

ይሁንና ጥቅምት 1995 ከስዊድን ተገዝቶ ጅቡቲ ወደብ የደረሰው በኮንቴይነሮች የተሞላ ኬሚካል አይነት የጅቡቲን የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ትኩረት ይስብና ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር ከፍተኛ ውዝግብ ያስነሳል። ይህ ጥቆማ ሾልኮ በወቅቱ አዲስ ዜና ጋዜጣ ለነበረው ለአብይ ደምለው ጆሮ ይደርሳል።

 

በተገጣጣሚ ጉዳዩ የቢቢሲ የኢትዮጵያ ሪፖርተር የነበረችው ኒታ ባላህ ጋር ደርሶ ስለነበር በጥምረት ምርምራ ይጀምራሉ።

በተደረገው ጥልቅ ምርመራ መብራት ሀይል በከፍተኛ ወጪ ገዝቶ ወደ አገር ውስጥ ሊያጓጉዘው የተዘጋጀው ኬሚካል በአለምአቀፍ ደረጃ ጥቅም ላይ እንዳይውል ከተከለከለ 30 አመት የሞላው መርዛማ ኬሚካል ነበር። የአለምአቀፉ አውቶሚክ ኤጀንሲ IAEA ለተፈጥሮ አካባቢና ለሠው ልጆች ከፍተኛ ጉዳት የሚያመጣ መሆኑን አረጋገጥን።

 

የጅቡቲ መንግስት በአስቸኳይ ከወደቡ ላይ ካልተነሳለት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን የዲፕሎማቲክ ግንኙነት እስከማቋረጥ የሚደርስ እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል ሲያስጠነቅቅ፤ በአቶ ግርማ ብሩ የሚመራ ልዑካን ቡድን ተወርውሮ ከጅቡቲ አቻዎቹ ጋር ቢነጋገርም አቋማቸው ቁርጥ ያለ ይሆናል።

 

ኬሚካሉ ከጅቡቲ ወደብ ቢነሳም እንኳን ተጓጉዞ የሚገባው አዲስ አበባ ሜክሲኮ አደባባይ የሚገኘው የኤብኮ መጋዘን ነበር።

 

ስለዚህ ዋናውን ጥያቄ ማንሳት ሲጀመር በጋዜጠኛውና በአዲስ ዜና ጋዜጣ ላይ ከተለያዩ ባለስልጣናት ማባበያ፣ ዛቻ፣ ማስፈራሪያ እና ማስጠንቀቂያ ይጎርፍ ጀመር። 

 

በዚህ ኬሚካል ግዢና ወደሃገር መግባት ምንም መረጃ ያልነበራቸውን የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ኬሚካል ዲፓርትመንት ጭምር ጥያቄው ሲቀርብላቸው ጫጫታው ተጀመረ።

ኬሚካሉ ስዊድን መጣያ አጥታ ከወደብ ወደብ ስታንከራትተው የከረመ እጅግ አደገኛ ኬሚካል መሆኑን ደርሰንበታል። የኤብኮ የግዢ ባለስልጣናት ደግሞ ይህንኑ እጅግ አደገኛ ኬሚካል ገዝተው አጓጉዘውት ጅቡቲ ላይ ደርሶ ሽብር ፈጥሯል።

 

በተለይም ፀሀይ ላይ የተሰጣው ኬሚካል ከኮንቴይነሩ አፈትልኮ መንጠባጠብ መጀመሩ በሁለቱ መንግስታት መካከል አለመግባባቱን እያጦዘው መጥቷል። ወደቡ ላይ ኮንቴይነሮቹ ያሉበትን ሁኔታ በፎቶ አስደግፈን መረጃውን በመያዝ የጅቡቲ ባለስልጣናትንም ኢንተርቪው በማድረግ ሪፖርቱ ሙሉ ቅርፅ ያዘ።

የስዊድኑ ኩባንያም ኤብኮ በነፃ ስላነሳለት በመደሰት የሰጠው እንጂ በአለም ክልክል ኬሚካል መሆኑን አምኖ ተቀብሏል።

አሁን ማስፈራሪያ የበረከተበት ሪፖርት  ሙሉ የኤዲቶሪያል ቡድኑንና የተቋሙን ሃላፊዎች ጭምር አሰባስቦ የጋራ ውሳኔ እየጠበቀ ባለበት ሁኔታ፤ ኬሚካሉ ከጅቡቲ ተነስቶ ወደ መሃል አገር መጓጓዝ መጀመሩ ተሰማና እኛም ቡድን አሰማርተን ጉዞውን ክትትል በማድረግ አዲስ አበባ ሜክሲኮ እስኪደርስ መቅረፅ ቻልን።

 

ሜክሲኮ የኤብኮ ሰራተኞችን ስናነጋግር ደግሞ የባሰ አስደንጋጩ ምስል ወጣ። ዜጎች ያለምንም ጥንቃቄ በተለመደው መልኩ ኬሚካሉን እንደሚነክሩ በፎቶ ጭምር ማረጋገጥ ተቻለ።

ይህን ከአንድ ወር በላይ በከፍተኛ ደረጃ የተደከመበትን ሪፖርት እንደ ሚዲያ ተቋም ማስፈራሪያና ዛቻ ስለበዛ ማለፍ አንችልም ብለን ወደ ህትመት ገባን።

 

እናም ሪፖርቱ ታትሞ እንደወጣ በዚያው ሳምንት የተጠራው የተወካዮች ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባም በሪፖርቱ የተጠቀሱትንና በአዲስ ዜና ጋዜጣ የወጡትን 29 ነጥቦች ሙሉ በሙሉ በማፅደቅ የኬሚካል ግዢ ጉዳዮች ላይ አዲስ ድንጋጌ ሊያወጣ ችሏል።

ድራጋዶስና የአለም ባንክ

 

ለከፍተኛ የኢትዮጵያ መንግስት የመንገድ ሥራ ፕሮጀክቶች የአለም ባንክና የአውሮፓ ህብረት በጀት አፅድቀው እንደተለመደው ለአውሮፓ የመንገድ ተቋራጮች ጨረታው ይወጣል።

 

በዚህም ጨረታ የስፔይንና የቱርክ ኩባንያዎች አሸናፊ ሆነው ሰፊ የመንገድ ሥራዎች ይጀመራሉ። ብዙዎቹ ከደብረዘይት፣ አዳማ፣ ጅማ ወዘተ የሚደርሱ አንደኛ ደረጃ የአስፋልት መንገዶች ነበሩ።

 

ድራጋዶስ (DRAGADOS) የሚባለው ተቋራጭ እየሰራ ባለው መንገድ ብቻ ሳይሆን ከአካባቢው ማህበረሰቦች፣ በሚቀጥሯቸው ሰራተኞቾች ላይ በሚያደርሱት በደል እንዲሁም በሴት ሰራተኞች ላይ በሚሰሩት ያልተገባ ድርጊት ስሙ በከፍተኛ ደረጃ መነሳት ጀምሮ በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድረስ ደርሷል።

በዚህ ወቅት ይህ ጭምጭምታ የደረሰው የአለም ባንክ ጉዳዩ እንዲጣራለት አምስት የምርመራ ጋዜጠኞችን ሲያሰማራ አንዱ አብይ ደምለው ነበር።

በዚህ ምርመራ ድራጋዶስ ከተሰጠው የአንደኛ ደረጃ አስፋልት ግንባታ ደረጃውን በማውረድ ከተመደበለት ባጀት የማይመጥን መንገድ መስራት ላይ ተጠምዷል።

ድራጋዶስ አንድ የጀመረው መንገድ ገና ሳያጠናቅቅ መንገዱ እየተሰነጣጠቀ መፍረስ ይጀምራል።

 

የመንገዶቹን ደረጃ እየተከታተለ መረከብ ያለበት የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ኃፊዎች ደግሞ ለቅኝት ሄደው የተሰነጣጠቀ መንገድ እያዩ በሚቀርብላቸው የገንዘብ ጉርሻ እየተገዙ መንገዱን ያለደረጃው ያፀድቃሉ።

ይህንን ሪፖርት ጨርሰን ኃላፊዎቹን መጠያየቅ ስንጀምር በተለይ የደራጋዶስ ሰዎች መጀመሪያ በንቀት በኋላ ላይ ደግሞ በሙስና በመደለል ሪፖርቱ እንዳይወጣ ሲታገሉ፤ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣናት ደግሞ ወደ ማስፈራራት ገቡ።

ይሁንና 150 ገፅ የያዘው የምርመራ ሪፖርት ለአለም ባንክ፣ አውሮፓ ህብረትና የኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ አመራሮች ጋር ደርሶ የድራጋዶስ ፍፃሜ በኢትዮጵያ ሊሆን ችሏል።

 

          ማጠቃለያ

ጋዜጠኛ አብይ ደምለው በፓን አፍሪቃ አስተሳሰብ ከሚሰሩ የአፍሪካ የኪነ-ጥበብ፣ የባህልና የሚዲያ ኔትወርኮች ጋር የአፍሪካን የባህልና ጥበብ ትንሳኤ ለማብሰር ብዙ ሥራዎችን ይሰራል። በባህል አክቲቪዝም ዙሪያ በአፍሪካ አሉ ከሚባሉ አንቂና የባህል ተከራካሪዎች አንዱ ነው።

 

በሙዚቃው ዘርፍም ሀገራዊ የሙዚቃ እሴቶችን ለማበልፀግና ለማሳደግ በደራሲነት፣ ፕሮዳክሽን እና ፕሮሞሽን ዙሪያ ከወጣት እስከ አንጋፋ ባለሙያዎች ጋር አብሮ ይሰራል።

ከአፍሪካ የሚዲያና የኪነጥበብ ሰዎች ጋር በመሰረተው ጠንካራ ትስስርም በሃገራችንና በተለያዩ የአፍሪካ ባለሙያዎች መሃከል የልምድ ልውውጦች እንዲካሄዱ መድረክ በማዘጋጀት ለዘርፉ እድገት የሚችለውን እያበረከተ ይገኛል።


 





 


 


አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች