አቶ ሀብቴ ገመዳ

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያው ዘርፍ ጉልህ አሻራ የነበራቸውን ጋዜጠኞች፣ የቴክኒክ ሰዎች ፣ የሚድያ መምህራን ፣ የማስታወቂያ ሚኒስቴር የሥራ መሪዎችን  እያፈላለገ የህይወት ታሪካቸውን እየሰነደ ይገኛል፡፡ ይህ የተሰነደ ታሪክ መዝገበ- አእምሮ መጽሀፍ ቅጽ 2 ላይ የሚወጣ ሲሆን ቅጽ 1 መዝገበ-አዕምሮ ከፍተኛ ተቀባይነት ማግኘቱ ይታወቃል፡፡  አሁን በዚህ ጽሁፍ  ታሪካቸው የሚዳሰሰው አቶ ሀብቴ ገመዳ ናቸው፡፡ እርሳቸውም ከ40 አመት በፊት  በጣቢያው በቴክኒክና በፕሮሞሽን ክፍል ደማቅ አሻራ ያኖሩ ናቸው፡፡  አቶ ሀብቴ በአሁኑ ሰአት የ70 አመት ሰው ናቸው፡፡ ባለውለታን ማሰብ፣ ሰርቶ ደክሞ የራሱን  የስራ ማንነት ያኖረን ሰው መዘከር ዋናው ግባችን ነውና የኢንጂነር ገሰሰ አባይንየአቶ ሀብቴ ገመዳን የህይወት ገጽ መፈተሸ እንጀምራለን፡፡  ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒሽን ከጥቅምት 21 2015 -ጥቅምት 30 2015 የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን 58ኛ አመት እያሰበ ስለሆነ አቶ ሀብቴ ገመዳ ደግሞ ከኢቲቪ ባለውለታዎች አንዱ ስለሆኑ  በዚህ አጋጣሚ የእውቅና ማእረግን እናጎናጽፋቸዋለን፡፡  እዝራ እጅጉ ታሪካቸውን እንደሚከተለው ሰንዶታል፡፡

 

 

            ልጅነት

የተወለዱበት ዘመን ሰርተፍኬትም ልደትም አይታወቅም፡፡ ሆኖም በግምትና ትምህርት በተመዘገቡበት ወቅት ለማስላት ጊዜውን መለስ ብለን እናስታውስ። ትውልዳቸው ሰላሌ አውራጃ   ደገም ወረዳ ገንደ ሸኖ ቀበሌ 1945 . ለአባታቸው 2 ወንድ ልጅ በመሆን ነበር።  ጊዜው ፊደል ሰራዊት የተጀመረበትና ትምህርት የሚበረታታበት  በመሆኑ እንደነ  ጀነራል ታደሰ ብሩም  ዓይነት ታጋዮች የኢጀሬ ሰው ቢሆኑም እነርሱ ይኖሩበት ከነበረበት አካባቢ መጥተው ወላጆችን ያበረታቱ ነበርና ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት እንዲልኩ ከሌሎች ጋር ሆነው ቅስቀሳ ሲያደርጉ እርሳቸውም  በዚህ አጋጣሚ ወደ ቄስ /ቤት የመላክ እድል አገኙ።

 

             እድገት

 አሁን በሂዳቡ አቦቴ አስተዳደር ስር የሚገኘው ስሬ መድሀኒያለም  ሀሁ የጀመሩባት የየኔታ ቤታቸው ነበረች ፡፡ እዚያ ትምህርታቸውን ከየኔታ እንግዳ ጋር ፊደል ቆጠሩ። እስከ 1959 . መስከረም ወር ድረስ ሀገር ቤትም እየተመላለሱ እስከ ዳዊት ቆጠሩ። ያኔ እከኩና ሙጀሌው እያሰቃያቸው በጉስቁልና ውስጥ ቢሆኑም ግን ጠንክረው ነው ከጥጃ ጥበቃ ወደ ቆሎ ትምህርታቸው ይሄዱ የነበረው። 1959 . የቤተሰብ ወዳጅ የሆኑና ጎሐ ፅዮን የሚኖሩ ኑሩ ዑመር የተባሉ  ባለ መሬት ነበሩ ፡፡ አቶ ሀብቴ በትምህርት ፍቅር ተነድፈዋልና በህዳር አካባቢ ከደገም ጠፍተው በጫካ ውስጥ አቆራርጠው ገብረጉራቻ፣አቦቴ ብለው ቱሉሚልኪ በብዙ ድካም ደረሱና የቱሉሚልኬ ነዋሪዎች ወዴት መሄድ እንደፈለጉ መዳከማቸውንም አይተው ወተት ሰጥተው አበረቷቸው፡፡ በኋላም ወደ ደካቦራ ጊዮርጊስ የሐጂ ኑሩ ሹም አባ አበራ  ቤት ሄደው ከመነሻው ሊያገኟቸው በማሰብ  ከቤተሰብ የጠፉበትን ምክንያት ያገናኙኛል ብለው ተስፋ የጣሉባቸውን ሼህ ኑሩ ዑመርን እንዲያገኙ መክረው ሸኟቸው። አቶ ሀብቴ በተባሉት መሰረት ሄደው ሀጂ ኑሩን ለማግኘት በቁ። ሀጂ ኑሩ ጋር አብዱልሰመድ እና ኢብራሂም ኑሩ የሚባሉ ልጆች እንደነበሯቸው አቶ ሀብቴ ያስታውሳሉ። የመሄዳቸው ዋነኛ አላማ የአስኳላ ትምህርት እንዲያስተምሯቸው በመሻት መሆኑን ሲያስረዷቸው ፈቃደኛነታቸውን ባይከለክሉም ግና የሄዱበት ወቅት በህዳር በመሆኑ ትምህርት ቤት መቀበል በማችሉበት ጊዜ ላይ አለመሆናቸውን ነግረው አሰናበቷቸው።ሼህ ኑሩ ዑመር አባታቸውን ሄደው ልጃቸውን አስኳላ እንዲልኩ ካነጋገሯቸው በኋላም አባታቸው ጋሽ ገመዳ  ቶላ በጊዜው የፍቼ ጊዮርጊስ ቄስ የነበሩትን አጋፋሪ ወልደፃዲቅ ጂማን  አነጋገሩላቸውና ፈቃድ በማግኘታቸው እርሳቸው ጋር እንዲሆኑ ያደርጋሉ። በዚህም ትምህርታቸውን ጀመሩ፡፡  እነ የኔታ ዘዉገ የቅኔምህራኖችንም ተዋወቁ። አቶ ሀብቴ እስከ 61 ዓመተምህረት ድረስ በዚህ ሁኔታ ከቆዩ በኋላ 15 አመታቸው አካባቢ 1962 . መሆኑ ነው አበራ አስፋወሰን የተባለ /ቤት ለመመዝገብ ፍላጎት ነበራቸው፡፡ አሁንም ግን አስኳላው እንዳሰቡት በቀላሉ የሚያገኙት አልሆነላቸውም መላከ-ገነት ከፍ አለ በየነ የተባሉ የፍቼ ጊዮርጊስ የደብር አለቃ የትምህርት ቤቱ የሥነ-ምግባር መምህርም ሲሆኑ የኔታ አስፋውም የሰዋሰው መምህር ነበሩ። እነዚህን ተዋውቀው እድሉን ለማግኘት ደግሞ ሞከሩ፡፡ በመሆኑም  ሳይመዘገቡ አስኳላውን ተቀላቅለው መማር ጀመሩ፡፡ ነገር ግን ''እንዴት አድርጌ ነው በቋሚነት የአስኳላውን ትምህርት መማር የምችለው ማንስ ሊያግዘኝ ይችላል ከቤተሰብ ምግብ እያመላለስኩ መማር እንዴት እችላለሁ?'' እያሉ ከመብሰልሰል አልዳኑም፡፡ ስለዚህ አንድ ውሳኔ ማድረግ ነበረባቸው፡፡  ወደ ደብረሊባኖስ ጠጋ ማለት ፡፡













                የጫማ ጠረጋ ስራ

 

 1962 ዓ.ም  ጠፍተው ደብረ-ፅጌ ሄዱና ራሳቸውን እየደገፉ መማር እንዳለባቸው ስላሰቡ የሽርክና የጫማ ጠረጋ ስራ በመጀመር 10 ሳንቲም ቢጠርጉ አምስቷን የግላቸው እያደረጉ መሥራት ጀመሩ። በፀባይም ጠጋ ብሎ ማደርና ሰዎችን መተዋወቅ ይችሉበታል።'' ጊዜው ፀባይ ካለ ሁሉም የሚያበላ ሁሉም ወዳጅ የሆነበት ነበርና በልቶ ለማደር ያንን ያህል አስቸጋሪ አልነበረም'' ይላሉ። ቢሆንም በዚህ መዝለቅ እንደማልችል ስለገባቸው ማድረግ የሚገባቸውን ማሰብ ነበረባቸው። አንድ ቀን ታድያ አቶ ወልደአረጋይ የተባሉ የታወቁ የመርካቶ ሀብታም ነጋዴ ልጅ በመዳሯ ደብረሊባኖስ ጉብኝት ምክንያት ሙሽሮች ጭቃ ነክቷቸው መስታወት የሆነች ጫማቸውን እንዲወለውሉላቸው ሲጠይቋቸው ፅድት አድርገው ሲሰጧቸው ለሰራኸው የሥራ ክፍያ ብለው 25 ሳንቲም ይሰጧቸዋል፡፡ አቶ ሀብቴ ታዲያ ቀለም ላላወጣሁበት ሂሳብ አልቀበልም ብለው አሻፈረኝ ይላሉ፡፡ በዚህ የተደነቁት ሙሽሮች ደግሞ እንደዚህ ዓይነቱንማ ወደ ከተማ ይዘን መዝለቅ አለብን በማለት ስለ ሀብቴ እናውቃለን ያሉትን በመጠየቅ ፀባየ ሸጋ መሆናቸውን ሲረዱ ወደ አዲስ አበባ ይዘዋቸው መጡ።

 በ1963 ዓ.ም ሀምሌ 5 ቀን  ከሙሽሮች ጋር በመሆን አዲስ አበባ የዘለቁት አቶ ሀብቴ መሳለሚያ አካባቢ  ሳንባ ነቀርሳ በሚገኘው የአቶ ሰሜነህ ሰማ ቤት ግቢ ውስጥ እያገለገሉ መኖራቸውን ቀጠሉ። '' አዲስ አበባ ከመጣሁ በኋላ ቴሌቪዥን ባለ ጥቁርና ነጭ ቀለም ነበር፡፡ የተለያዩ ሰዎችን እመለከት ነበር፡፡  በተለይም እነአሳምነዉ ገብረወልድ የቴሌቭዥን ዜና አንባቢ በነበሩበት አቡነ ባሲሊዎስ  ሲሞቱ  ዜናውን እያየሁ አዝን ነበር።'' እያሉ ያን ዘመን ያስታውሱታል፡፡ አክለውም '' እኔ ከመነሻውም  ፍላጎቴ ትምህርት ነበርና አሁንም ህዳር አካባቢ የመማር መሻቴን ለጌቶች ስነግራቸው ካገኘህ ግባ አሉኝ፡፡ ታድያ አንድ ቀን አትክልት ገዝቼ ስመለስ  መሳለሚያ አካባቢ ወሰንሰገድ የሚባል ትምህርት ቤት አገኘሁና ቅርጫቴን ይዤ ሄድኩ፡፡ እና ኃላፊውን አገናኙኝ፡፡ ገብቼ አሳዳሪዎቼ ማታ ላይ እንድማር ፈቅደውልኛል እና እባኮትን ባክዎን ያስመዝግቡኝ ብዬ ስለምናቸው በነፃ ተማር አሉኝ'' ብለውናል። አቶ ሀብቴ በሰሙት መልካም ዜና ተደስተው ለመመዝገብ ሳምንት ሲቀራቸው እንግዳ ሲመጣ በር ማን ይከፍታል ተብለው ተከለከሉ፡፡ ይህን ጊዜ መላ መዘየድ እንደሚገባቸው አሰቡ። አቶ ታደሰ ይርዳው የተባሉ  በወቅቱ የጠቅላይ ንጉሰ ነገስት ፍርድ ቤት ዳኛ የነበሩ ሰው ጩሎ (የወንድ ሰራተኛ) ይፈልጋሉ የሚባል ወሬ እንደሰሙ ተነስተው እርሳቸው ጋር ገቡ። ''አቶ ታደሰ ጋር ስገባ የህግ ሰው ናቸውና ማን ይነካኛል?  ስለዚህ አንገቴን ደፍቼ እየሰራሁ ልጆቻቸው እና የልጆቻቸው ጓደኞች ሲመጡ ስጦታ እንደ ካኒቴራ፣ ሸሚዝ ስጦታ ሲሰጡኝ እየተቀበልኩ በደስታ ኑሮዬን ቀጠልኩ። ድሮ በሆድ ብቻ ያሰሩኝ የነበረበት ጊዜ አልፎ 10 ብር ተከፋይ ለመሆንም በቃሁ።''  ይላሉ፡፡

      የትምህርት ጥማት 

የአቶ ሀብቴ ልብ ውስጥ ያለው የትምህርት ፍቅር በጊዜያዊ መደላድል የሚዳፈን አልሆነምና ከዕለታት በአንዱ ቀን ጌቶችን ዋሽተው በአባት ሞት አመካኝተው 20ብር ካፒታል 1.25 ብር  በማሞ ካቻ አዉቶቡስ ተሳፍረው ወደ ሀገራቸው ደብረ-ፅጌ አቀኑ። ከአመዴ የገዟትን ጫማ ተጫምተው በአደራ ያቆዩትን ልብስ ከስጦታዎቻቸው ጋር ይዘው ወደ ደብረ-ፅጌ ሲደርሱ መመለሳቸውን የሰሙ ጫማ ይጠግኑላቸው የነበሩ መምህራን ቀድሞውንም ያውቋቸው ስለነበር በታህሳስ ወር ቢሆንም እንኳ 1963 4 ክፍል እንዲጀምሩ አደረጓቸው። በ1964 ዓ.ም በአንድ ዓመት 5ኛ እና 6ኛ ክፍልን የመማር ዕድል ተሰጥቷቸዉ የ6ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናም በጥሩ ነጥብ አምጥተው በ1965 .  7 ክፍልን ፍቼ 2 ደረጃ ትምህርት ቤት የመማር እድል አገኙ።'' ቀን እሰራለሁ ማታ እስከሌሊት አጠናለሁ፡፡ በጥሩ ውጤት ትምህርቴን ቀጥዬ 1966 . 8 ክፍል  ለመፈተን ስደርስ ሀገር ተረበሸ፡፡ በዚህ ጊዜ አሁንም ተስፋ አልቆረጥኩም፡፡ ኑሩ ኡመርን ፍለጋ የሄድኩበት ጉሐጽዮን ሁለተኛ ደረጃ ርእሰ- መምህር አቶ ታደስ የተባሉትንና የደብረጽጌ ልጅ የነበረች መምህርት ያውቁ ስለነበር ሰው ጋር ጠጋ ብዬ ማጥናቴን ቀጠልኩና ሲረጋጋ ተመልሼ ለአንድ ወር ፍቼ ረብሻዉ እስኪቆም  ጉሐጽዮን መለስተኛ  ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት እያጠናሁ በሰኔ 1966 ፊቼ ትምህርት ቤት 8ኛ ክፍል ሚኒስትሪ በመፈተን  100 ከመቶ አምጥተው  መስከረም 18/1967 . ለተግባረዕድ መታጨት ስችል የት እሆናለሁ የሚል ሀሳብ ነበረብኝ፡፡ ግን አበረታቱኝና ሄድኩ ከማውቃቸው ጋር የመኪና አውታንቲ እየሆንኩ ጭምር ተግባረ-ዕድ እየተመላለስኩ መማሬን ቀጠልኩ '' ሲሉ አቶ ሀብቴ ያለፉበትን መለስ ብለው ያስታውሳሉ። ከዚህ በኋላ ሰው ጋር ጠጋ ብሎ መኖር የሚያዋጣ አይሆንምና የሚያውቋቸውን አውታንቲዎች አስተባብረው  ቀለመወርቅ ት/ቤት ጀርባ ሾላ ለ4 ሆነዉ በ3 ብር  ቤት ተከራዩ፡፡ ይህም እራሳቸውን የቻሉበት የመጀመሪያው አጋጣሚ ሆነ።

 

 እንቁላል እያዞሩ መማር 

''እሁድ ቅዳሜ ከደብረፅጌ እየተመላለስኩ እየሰራሁም እየተማርኩም መኖርን ቀጠልኩ ፡፡ እንቁላልና ጨው እያዞርኩ የትምህርት ህይወቴን አጠናክሬ ቀጠልኩ። በጊዜው ሁሉም ለእድገት በህብረት ሲሰማራ የተግባረዕድ የአንደኛ አመት ተማሪ ብቻ ነበር ያልወጣነው። የወቅቱ ወከባም ለእኔ ንቃት ጨመረልኝና እስከ 1970 ዓ.ም ድረስ በተግባረ-ዕድ መማር ቀጠልኩ።'' ሲሉ መለስ ብለው ያንን ዘመን ያስታውሱታል፡፡

  ታድያ በንግዱም በትምህርቱም በቅጥሩም ሁሉ እየተሯሯጡ ጥሩ ይሰሩ ነበርና በጊዜው / አሻግሬ ይግለጡ የተባሉት የንግድ ሚንስቴርነበሩበት ወቅት እርሳቸው እንጦጦ ላይ ሁለትም ሶስትም ኩንታል ጨው ይዘው ሲመጡ እየተያዘባቸው በመቸገራቸው ለምን የንግድ ፈቃድ አላወጣም በማለት በድፍረት / አሻግሬ ጋር ገቡ። ዶክተር አሻግሬ ታድያ አንድ ሰው ጋር ደውለው አሁን አንድ ልጅ ይመጣል ንግድ ፍቃድ ስጠው አሉት፡፡ ወዲያው በደብረ-ፅጌ  የጨው ንግድ ፍቃዱን አገኘ፡፡ ከዚህ በኋላ ብርሀን ታየኝ ይላሉ፡፡ በዘመናቸው ሥራን ሳይንቁ ተግተው በሠሩት ሥራ ያጠራቀሟትን ሰባስበው ንግዱን 1968 . መጨረሻ ላይ በስፋት ፋቃዳቸውን ተቀብለው መስራታቸውን ቀጠሉ፡፡ 1969 . ታድያ እስከ 8 ሺህ ብር አካባቢ በእጃቸው ገባ። በዚህ አላበቁም ንግዱን ማሳደግ አሰቡ፡፡ ስለዚህ ፒካፕ ዳትሰን 10 ሺህ ብር አካባቢ ካላቸው ላይ በብድርም ጨምረው ገዙና ንግዱ ተጧጧፈ፡፡ የኋላኋላ ግን የኢህአፓን ፋንፍሌት ያከፋፍላል፡ ተብለው የውሸት ዜና ተሰራጨባቸው፡፡ እርሳቸው ግን እንደዚህ አይነት እንቅስቃሴ ውስጥ የመሳተፍ ፍላጎት የሌላቸው የትጋት ሰው ናቸውና ስራቸው ላይ ብቻ ማተኮርን ይመርጣሉ፡፡ ታዲያ በዚህ ሰበብ ጓደኞቻቸው ታስረው እርሳቸውም በዕለተ- ሀሙስ ሰላሌ እንደሚፈለጉ ይነገራቸዋል፡፡ በዚህ ሰዓት ለብርጋዴል ጀነራል ለገሰ በወቅቱ ሻምበል ነበሩ ( የተግባረዕድ ሰርቬይን ተማሪ ነበሩ ) የተፈጠረውን ሲያስረዱ እርሳቸው ከእንደዚህ ዓይነት እንቅስቃሴ ነፃ የሆኑ ሰው በመሆናቸው  ሕዝብ ድርጅት ጽ/ቤት ወስደዉ በማስረዳት የህዝብ ድርጅት ሰራተኛ የተሰኘ መታወቂያ ተሰጣቸው። በዚህ መሠረት ከፖለቲካ ራሳቸውን አግልለው በስራቸው ላይ ብቻ ትኩረት ማድረግን አጥብቀው ያዙ።

                         ጉዞ ወደ ኢቲቪ

የንግድ ሥራቸው የተጧጧፈላቸው አቶ ሀብቴ ከዚህ ስራቸው ጎን ለጎን በታህሳስ  ወር 1970   በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በትርፍ ጊዜያቸው በቴክኒሻንነት እየተለማመዱ ለሚሰሩ በወር 100 ብር ቅጥር  ለ6 ወር ተሰጣቸው፡፡ ይህም የአቶ ሀብቴ እድል ነበር።  በሰንጋተራ ማሰራጫ ሲገቡ ተቀጥረው ቢሰሩ ቤተሰቦቻቸውን ሊደጉሙ እንደሚችሉ በማሰብ  የሬድዮ ቴክኒክ ተመራቂ መሆናቸውን መሰረት አድርገው በኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም 1970/ም ሐምሌ ወር  በፕሮዳክሽን ቴክኒሽያንነት 285 ብር ደሞዝ ተቀጠሩ። በቅጥር ሂደቱ ኢንጅነር ገሠሠ አባይ የጊዜው የቴሌኮሙኒኬሽን የሥራ ኃላፊ የነበሩ ትጉህ ሰው ነበር ፈትነው ያስገቧቸው። ፈተናው ኤሌክትሮኒክስ የተማረ ሰው በትክክል ማወቁን በተግባር የሚያረጋግጥ ከባድ ፈተና እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ ሀብቴ በጊዜው ከተወዳደሩት 4 ሰዎች መካከል አንደኛ በመውጣት ኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን ተቀላቀሉ።

       ቪድዮ ራይደር ወይም ቪድዮ ኢንጂነሪንግ የሚባለውን የጥራት ቁጥጥር ሥራ ላይ በተራ መሥራት ተመደቡ፡፡ እስከ 1975. ባለው ይሄንኑ ሲሰሩ ቆይተው ሱፐርቫይዘር ደረጃ ላይ ደረሱ። በተመደቡበት ሥራ ላይ እንዳሉ የቴክኖሎጂ ልቀታቸው እየተሻሻለ በመምጣቱ ሥራቸውን አጠናክረው ቀጠሉ፡፡ በቀጥታ ስርጭት አየር ላይ የሚወጡ ሥራዎችን በስኬት ለመፈፀም የተቻላቸውም ጊዜ ነበር። በየሀገሪቱ በተተከሉ ማሰራጫዎች እና ማስፋፊያ ሥራዎች መካሄዳቸው ሥራቸውን እንዳሳደገላቸው ያምናሉ፡፡ ትጋትም እንደነበራቸው ጭምር። ካሜራ ፣ቪድዮ እና ኦድዮ ራይደር እንዲሁም ሱፐርቫይዘር በመሆን እስከ አ.ም ነሀሴ ወር ድረስ የሰሩት አቶ ሀብቴ የሚድያ ስራ በአንድ ሰው ትከሻ ብቻ የሚፈፀም ሳይሆን የጋራ ስራ ውጤት ነውና በኢትዮጵያ የሚድያ ታሪክ በተለይም ለሀገሪቱ አንድ ለእናቱ በነበረው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከብላክ ኤንድ ኋይት ጀምሮ ወደ ከለርም ባደገበት ወቅት ደግሞም ከዛ ወዲህ ለህዝብ ይደርሱ የነበሩ ታላላቅ በዓላት እና ሁነቶች ብሎም ወቅታዊ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች በሙሉ በቴክኒኩ ዘርፍ ሲከወን እነ ሀብቴ ገመዳ ሚናቸው የጎላ እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም። ሥራው በቀላሉ የሚታይ አልነበረም፡፡ ብዙ ውጣ ውረዶችም ያሉበት ነው፡፡ እንደምሳሌ አቶ ሀብቴ ሱፐርቫይዘር በነበሩበት ወቅት ሮበርት ሙጋቤ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ዜናው አጋርፋ ባሌ ውስጥ የነበረውን ጉብኝት ጋዜጠኛው ቀርፆ ሲመጣ ሁለቱም ምስሎች ሙጋቤ የሄዱበትን ሂሊኮኘተር ይዞ ነበርና የተቀመጠው ሲሰራጭ አንባቢው ግራ ተጋባ፡፡ ምክንያቱም ሁለቱም መግቢያ ተመሳሳይ ምስል በመሆኑ ነበር።''አርሲን የእርሻ ማሰልጠኛ ሲጎበኙ ወታደር ካምፕ  ደግሞ እሱን ቆርጠን ድምጽ አጥፍተን ወደ ባሌ ወስድነው''ብለውናል።  ይህ ብቻ አይደለም መንግስቱ /ማርያም ወደ ኮርያ ሄደው መብራት ጠፋና ጣቢያው ፀጥ አለ፡፡ ጊዜው ደግሞ በሰሜን ውጣ ውረድ የነበረበት ጊዜ ነው፡፡ ታድያ ይህ ሲሆን ጣቢያው ተያዘ ተባለና ደህንነት ወረራቸው ''ኢንጅነራችን እና / ፈለቀ  ገድለ ጊዮርጊስ ተከታትለው ሲገቡ ደህንነቶች ቀድመው ገብተው ነበር እና / ፈለቀ ሲመጡ እናንተ ማናችሁ ደርግ እኔን ነው የሾመው እነዚህ በሙሉ ደግሞ የእኔ ሰራተኞች ናቸውና ከቤት ውጡ ችግሩን እነርሱ ይፈቱታል ብለው አስወጡልን። '' 1981 አካባቢ ተፈጥሮ የነበረው ችግር መብራት ጠፍቶ ሲመጣ ኬብል ተቃጥሎ ስርጭት እንዲቋረጥ በመሆኑ ነበር እነ ሀብቴ ግን ያለውን ቁሳቁስ ተጠቅመው ችግሩን በፍጥነት መፍታት ችለዋል::

ጋሽ ጳውሎስ ኞኞ በውይይት ክለብ ማርክሲዚም ሌኒኒዝም ላይ ይሰጥበት የነበረው ውይይት ላይ ይሳተፉ በነበረበት በጥሩ ምክር ሰውን ይገሩ የነበሩ ሰው ጋር በመስራቴ ደስ ይለኛል የሚሉት አቶ ሀብቴ የስፖርት ጋዜጠኛው ጋሽ ሰለሞን  ተሰማ አቶ ተክሉ ታቦር ጋሽ ጌታቸው ኃይለማርያም፣ሰለሞን ክፍሌን የመሰሉ የበቁ ሙያተኞች በነበሩበት ሰዓት መሥራታቸውን በአድናቆት ያስታውሳሉ።

1970ዓ.ም ስራ ሲቀጠሩ 20 አመቴ ነው ብለው ፎርም የሞሉት አቶ ሀብቴ 13 አመት በቴክኒሻንነት እና በሱፐርቫይዘርነት ከሰሩ በኋላ 27 ዓመት ደግሞ ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የማርኬቲንግ ባለሙያ በመሆን ነው የሰሩት። 1983 ግንቦት 20 ኢህአዴግ ሀገሪቷን ሲቆጣጠር ህዝቡን እንዴት አድርገን መድረስ እንችላለን? ብለው ሲጠይቁን ኦሮምኛ እና ትግርኛ መጀመር አለበት ተባለ፡፡ ይቻላል ወይ ብለውም ሲጠይቁ አቶ ሀብቴን ጨምሮ የተወሰኑ ሰዎች እንደሚችሉ ተስፋን አሳዩዋቸው። ሰኔ 16/1983 ዓ.ም በቴሌቭዥን አፋን ኦሮሞ ፕሮግራም ፣ሰኔ 24/1983 ዓ.ም በትግርኛ  ሰኔ 24 /1983 ዓ.ም  በቀን 30 ደቂቃ ያልበለጠ ፕሮግራሞች ተጀመሩ፡፡ለሙያው እድገት ሲሉም በትጋት አዲስ ዓመትን በጥሩ ሁኔታ ለመጀመር በሚል ቀዳም ምሳናን እና ደንጋን የመሰሉ ፕሮግራሞች አየር ላይ እንዲወጡ መስራት ጀመሩ፡፡ ደግሞ በአጋጣሚ አቶ ሀብቴ በስልጠና እድል ከመስከረም 1984 ዓ.ም  6 ወር ወደ ግብፅ ተላኩ፡፡ ይህንንም በአግባቡ ቀስመው ለመምጣት ከወዲሁ ቆርጠው ተነሱ። ሄደውም ከጋዜጠኝነት እስከሳተላይት እና የገበያ ሥራውን ሁሉ በሚገባ ተከታተሉ፡፡ እነዚህን በሙሉ ለመፈፀም ባይቻለን እንኳን የተወሰነ መነሻዎች ያስፈልጉናል ብለው ስላመኑ በጊዜው ኃላፊነት ላይ የነበሩትን በማማከር በፅሁፍ የተዘጋጀውን የገቢ ማመንጫ መንገዶች አጠናቅረው ሰሩ፡፡ ለውሳኔም እስከጠቅላይ ሚንስትሩ ድረስ ውሳኔ ሊሰጥበት የሚችል ነው ተብሎ ታይቶ ውሳኔው ተፈፀመ። ከተወሰነ ጊዜያት በኋላ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን በራሴ የሚያዝበት የገቢ ምንጭ ተፈቅዶለት የሥራ መደብና በጀት ያልተያዘላቸዉ አዳዲስ የቋንቋ ስርጭት ሰራተኞች ደመወዝ ከገቢ እንዲከፈል ተወሰነ፡፡   በዶ/ ነጋሶ ጊዳዳ ደብዳቤም አቶ ሀብቴ  የፕሮሞሽኑን ቢሮ በኃላፊነት እንዲመሩት የተነገራቸው አቶ ሀብቴ የሚያግዛቸውን ታማኝ ሰው ሲፈልጉም በደርግ ስትገረፍ እግዚአብሔርን አልክድም ያለች ከበቡሽ ለገሠ የተባለችን የጠቅላላ አገልግሎት ሰራተኛ እና ሌላ ተጨማሪ ሰው ተሰጥቷቸው 1985 አካባቢ ሞቢልን በማነጋገር የመጀመሪያውን የፋክስ ማሽን ለዜና ማዕከል፣ፊልም በአጂፕ እግርኳስም እንዲሁ እንዲያመጣላቸው እና አዲስ ለተቋቋሙት ፕሮግራሞች ገንዘብ መክፈል ቻሉ። 1986 ለሬድዮ በወር 40 ሺህ ብር በመመደብ  ፍሪላንስ መቅጠሪያ እና ሬድዮን መደጎም እስከመቻል የደረሰ ሆነ።

'በዚህ አጋጣሚ የኢትዮጵያ የጥበብ ባለሙያዎች ነፃ ጉልበት ሰጥተው ነውና ሚድያውን ያቋቋሙት በእውነቱ የሚድያው ባለውለታዎች ናቸው።'' አቶ ሀብቴ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ገቢ እንዲያገኝ በሰሩበት ወቅት የፕሮሞሽን ክፍል እስከ 2010 . ድረስ ኃላፊ ሲሆኑ ጋዜጠኝነቱን ምሰሶ በመሆን ለማቆም የሚያስችልን ክፍል የሰሩ ነበሩ።

በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን 40 አመት ቆይታቸው በቅን ልቦና ተምረው ቤቱን ከባልደረቦች ጋር በመሆን ለማሳደግ ከቴክኒክ አንስቶ በገበያ ልማትም እራሱን እንዲችል ከዜሮ ጀምረው ከእነ ውጣውረዱ የአየር መቆራረጥን ለመሸፈን ደግሞ በገበያው የማስታወቂያ ሥነ-ምግባርን በተከተለ መልኩ ለመስራት ማወቅና መታረም የሚገባቸውን ማረም ይገባ ነበርና በዚህ ሁሉ መሀከል የገባው ሲያግዛቸው ያልገባው ሲወቅሳቸው በብዙ መውጣት መውረድ ነበር ሲሰሩ የቆዩ ሲሆኑ ከኤዲቶሪያል ፓሊሲ በፊት የማስታወቂያ መመሪያንም 1995. በማስወጣት ሥራውን ሥርዓት በማስያዝ ቀዳሚ ለመሆን የቻሉ ከመሆናቸው በላይ እርሳቸውም ከውንጀላ ድነዋል።

አቶ ሀብቴ በሥነ-ምግባር እና በትጋት የተመሰገኑ ጣቢያውን እንደቤታቸው በተቆርቋሪነት የሰሩ ሲሆን በቴሌቪዥን ፕሮሞሽን ሥራ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመማማሪያ መነሻ እንዲሆን የበቁ ሀሳቦችን እና አሰራሮችን ያስጀመሩ ያከናወኑም ናቸው።

  አቶ ሀብቴ በአሁኑ ሰዓት ላይ በኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ (OBN) በኤክስፐርትነት  በማገልገል ላይ ይገኛሉ በሥራ ዘመናቸውም ለመንፈሳቸው እርካታን የፈጠረላቸው ትጋት የነበራቸው ሲሆን የቤተሰብ ኃላፊና 3 ሴት ልጆች አባት ናቸው በልጆቻቸው የትምህርት ደረጃ እና ስኬትም ፈጣሪያቸውን ያመሰግናሉ













አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች