ፀሐይ አክሊሉ ቢረሣው

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያው ዘርፍ ጉልህ አሻራ የነበራቸውን ጋዜጠኞች፣ የቴክኒክ ሰዎች ፣ የሚድያ መምህራን ፣ የማስታወቂያ ሚኒስቴር የሥራ መሪዎችን  እያፈላለገ የህይወት ታሪካቸውን እየሰነደ ይገኛል፡፡ ይህ የተሰነደ ታሪክ መዝገበ- አእምሮ መጽሀፍ ቅጽ 2 ላይ የሚወጣ ሲሆን ቅጽ 1 መዝገበ-አዕምሮ ከፍተኛ ተቀባይነት ማግኘቱ ይታወቃል፡፡  አሁን በዚህ ጽሁፍ   ታሪኳ የሚዳሰሰው ጋዜጠኛ ፀሐይ አክሊሉ ቢረሣው ናት፡፡ ፀሀይ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በእንግሊዝኛ ክፍል ከሪፖርተርነት እስከ ስራ መሪነት ለመድረስ የቻለች ናት፡፡ የህይወት ታሪኳን እንደሚከተለው እዝራ እጅጉ አጠናክሮታል፡፡

 

የትውልድ ዘመን 1970 ዓ.ም አዲስ አበባ

እናት ወ/ሮ ሲሳይነሽ ዓለሙ

አባት አቶ አክሊሉ ቢረሳው

የትዳር ሁኔታ- ያገባሁ (አቶ ተመስገን ዳምጠው) ፤ የ2  ልጆች እናት (አቤኔዘር 14 ዓመት እና ሀሌሉያ 9 ዓመት ተመስገን)

           ትምህርት

1-8 ኢትዮጵያ አንድነት የህዝብ ትምህርት ቤት

9-12 ኮከበ ጽባህ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት

በምኒሊክ መለስተኛ የጤና ባለሙያዎች ማሰልጠኛ ተቋም በጁኒየር አዋላጅነት- ዲፕሎማ

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በውጪ ቋንቋዎችና ሥነጽሁፍ / ማይነር ፖለቲካል ሳይንስ -የመጀመሪያ ዲግሪ

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ኮሚኒኬሽን - ሁለተኛ ዲግሪ/ ማስተርስ

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፒ ኤች ዲ ዲግሪ ትምህርት ጀምራለች

      የጤና ባለሙያነት ሥራ እና የሥነጽሁፍ ህልም

የጤና ባለሙያነት ፈልጋ የገባችበት ሙያ አልነበረም፡፡ ከ2ኛ ደረጃ ጀምሮ ዝንባሌዋ ወደ ሥነጽሁፍ ነበር፡፡ በወቅቱ በ12ኛ ክፍል ማትሪክ ፈተና የነበራት ውጤት   ወደ ጤና ባለሙያነት እንድታመራ አደረጋት፡፡ በ1992/93 ዓ.ም በአዋላጅነት እንደተመረቀች በወቅቱ ሀገራችን በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ላይ ነበረች፡፡ በጤና ጥበቃ ሚኒስትር ቢሮ በተለያየ ዘርፍ የተመረቁት እነ ጸሀይ  “ለምደባ እና ተያያዥ ጉዳዮች” በሚል ስብሰባ ተጠሩ፡፡ በወቅቱ የጠበቃቸው ግን ምደባ አልነበረም፡፡ ሀገራቸውን በተሻለ ለማገልገልና ሙያቸውንም በተግባር ለመፈተን ትልቅ አጋጣሚ እንዳገኙ ከተብራራላቸው በኋላ ፈቃደኛ ከሆኑ ወገኖቻቸውን ለመርዳታ በጦር ሜዳ እንዲሳተፉ የቀረበላቸው የግብዣ ጥሪ ነበር፡፡ በወቅቱ በሁሉም ዘርፍ ያሉ የጤና ባለሙያዎች የሚዘምቱበት ነበር፡፡

 ፀሀይ ያንን ዘመን ወደ ኋላ መለስ ብላ ስታስታውስ‹‹…… በተቆረጠልን ቀን (በትክክል ባላስታውሰውም)  አነስ ያለ ሻንጣ እና ልብስ ብቻ እንድንይዝ ተነገረን፡፡ ሆኖም ሻንጣችን ተፈትሾ ለመጫን ነው እንጂ የምንሄደው በዛው ቀን አለመሆኑንና ቀኑም ሻንጣ ስናስጭን እንደሚገለጽልን ተነገረን፡፡ አስገራሚው ነገር ግን “ ሻንጣ ለመጫን” ብለን ቤተሰቦቻችንን ነግረን የወጣን ሁሉ ያንኑ ቀን ወደ ዘመቻ ተላክን፡፡ ለካስ የውትድርናው ዓለም ምስጢር አካል ነበር፡፡  ነገሩን አሁን መለስ ብዬ ሳየው እጅግ አስደንጋጭ እና  አስደሳች የተምታታ ስሜት የሚያጭር  ነበር፡፡በወቅቱ መኪና ውስጥ የተላቀሱ  እንደነበሩ አስታውሳለሁ፡፡ በእንጥጮ ግንባር ለ3 ወራት ያህል የጤና ባለሙያነትን ጀመርኩ፡፡  በዙሪያዬ የማየው ፍጹም አስደንጋጭ፤ በአንድ በኩል የሚያኮራ ፍጸም የኢትዮጵያዊነት ጀብዱ፤ መስዋእትነት እና ከልክ ያለፈ መተሳሰብ  በህይወቴ አዲስ ምእራፍን ከፍቷል፡፡ በዚያን ወቅት የተሰማኝን እና ያስተዋልኩትን ማስታወሻ ደብተሬ ላይ እከትብ ነበር፡፡ በዚህ ሙያ በቆየሁበት ጊዜ በኮተቤ ጤና ጣቢያ እና በጋንዲ ሆስፒታል በአዋላጅነት፣ በብራስ የእናቶችና ህጻናት ሆስፒታል ደግሞ በክሊኒካል ነርስነት ሰርቼበታለሁ፡፡›› ስትል ፀሀይ በትዝታ ወደ ኋላ ሄዳ አጫውታናለች፡፡

 ፀሀይ ለ6 ዓመታት በጤና ባለሙያነት ብትቆይም ወደ ህልሟ መጓዝ እንዳለባት ግን በጠዋቱ ወስና ነበር፡፡ በስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርቷን ለመከታተል ያሰበችውም ወደምትወደው ሙያ እንዲያቃርባት በማሰብ ነው፡፡  ለፀሀይ የጤና ባለሙያነት ታልመው የነበረው ሙያ ባይሆንም በደስታ እና በፍቅር ያገለገለችበት ነበር፡፡   ዘወትር እንደምትለው  የጤና ሙያ በማንነቷ ላይ የራሱን አሻራ ያኖረ ነው  ፡፡ በጊዜው በሥራዋ ላይ የታዘበቻቸውን ጉዳዮች እንዲሁም እይታዎቿን ጨምራ በወቅቱ ትታተም በነበረችው “በሜዲካል” ጋዜጣ ላይ አልፎ አልፎ ለአንባቢያን ታቀርብ ነበር፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪ መመረቂያ ጽሁፏም በጤና ሙያ ላይ ያሉ የተግባቦት  ክፍተቶች በህክምና ላይ የሚፈጥሩትን ችግሮች የሚያሳይ ነበር፡፡

            ጋዜጠኝነት

የመጀመሪያ ዲግሪዋን ከያዘች ከጥቂት ወራት በኋላ  በቀድሞው የኢትዮጵያ ሬዲዮ ግቢ በሚገኘው የዓለማቀፍ አገልግሎት በእንግሊዝኛ ክፍል በ1999 ዓ.ም  በጥር ወር በዜሮ አመት የሥራ ልምድ ጀማሪ ጋዜጠኛ ሆና ተቀጠረች፡፡ ይህን ውሳኔ በወቅቱ እጮኛዋ ከነበረው እና ከአሁኑ ባለቤቷ ከአቶ ተመስገን ዳምጠው በቀር የደገፈው አንድም ሰው አልነበረም፡፡ ምክንያቱም ግልጽ ነው ፡፡ በየጊዜው  የፀሀይን ጽሁፍ ዘመም ፍላጎት ሲሰሙ የቆዩት  ቤተሰቦቿ ከጤና ጋር የተያያዘ ትምህርት እንድትቀጥል ማበረታቻ ቢሰጡም አልተሳካም፡፡ በጤና ባለሙያነት ዓመታትን ማስቆጠሯ እና ደስተኛ መሆኗን በማየት ጨክና የምተወው ሙያ  አልመሰላቸውም፡፡ እንዲሁም  በጊዜው ለሚድያ ሰዎች ይከፈል የነበረው ደሞዝ አነስተኛ ስለነበር ፀሀይ ለትንሽ ደሞዝ ብላ ወደ  ጋዜጠኝነት ሙያ  ትገባለች ብለው ግምት አላሳድሩም፡፡

ሆኖም ፀሀይ ህልሟን ተከትላ መጓዟ ትልቅ ርካታንና እፎይታ የሰጣት ጉዳይ ነበር፡፡

በወቅቱ በሬዲዩ ‘ፕረስ ሪቪው’ እና ‘ውሜንስ ፎረም’ የሚባሉ ፕሮግራሞች በመጀመሪያ ቀድመው ሥራውን ከጀመሩ ጋዜጠኞች ጋር በመሆን በኋላም ብቻዋን በማዘጋጀት እንድታቀርብ ተመድባ ጋዜጠኝነትን ተቀላቀለች፡፡ በወቅቱ ጋዜጠኝነትን ይበልጥ እንድትወደው ያደረጓት ባለወርቃማ ስብእና ሲኒየር ጋዜጠኞችን ምንጊዜም ታመሰግናቸዋለች፡፡ ከ1ዓመት በኋላም የኢትዮጵያ ሬዲዮ እና የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በመቀላቀላቸው በወቅቱ የእንግሊዝኛ ቴሌቪዥን ላይ ታዋቂ የነበሩ እንደ ‘ኢትዮጵያ ቱዴይ’፤ ‘ክሎዝ አፕ’ እንዲሁም ‘ኢሜጅ’ የተባሉ ወቅታዊ እና ዶክመንተሪ ቋሚ ፕሮግራሞችን ማዘጋጀት ጀመረች፡፡ በእነዚህ ሥራዎችም ከጀማሪ ሪፖርተር ፤ከፍተኛ ሪፖርተር፤ ረዳት አዘጋጅነት እና ኤዲተርነት ለ8 ዓመታት ሰርታለች፡፡

በኤዲተርነት ቆይታዋ በውጪ ቋንቋዎች የሚሰራ የኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያ ለመክፈት በመታሰቡ ከሶስት ኤዲተር ባልደረቦቿ ጋር ጣቢያውን ለማቋቋም ታስፈልጋላችሁ በማለት አዲስ ክፍል ለማቋቋም ተመደቡ፡፡ በወቅቱ ከምትወደው የቴሌቪዝን ፕሮግራም ዝግጅት መቀየሯ ባያስደስታትም ክፍሉን ለማቋቋም የዜና እቅድ ዝግጅቶችን በማሰናዳት፤ አዳዲስ የሬዲዮ ቶክሾው ፎርማቶችን በመቅረጽ፤ እንዲሁም የዜናና ቶክሾው ፕሮግራሞችን በበላይነት በመምራት ሙያዊ ኃላፊነቷን በሚገባ ተወጥታለች፡፡ ኤፍ ኤም 104.7 አሁንም በሥራ ላይ ያለ እና በእንግሊዝኛ፤ አረብኛ እና ፈረንሳይኛ የሚያሰራጭ ብቸኛ የኤፍ ኤም ጣቢያ ነው፡፡

በጋዜጠኝነት ብቻ በሰራችባቸው ዓመታት በርካታ የሀገራችንን ክፍሎች የማየት እድል አግኝታለች፡፡ በዚህም ኢትዮጵያዊነቷን ይበልጥ እንድትኮራበት እና እንድትወደው ሆናለች፡፡ ደረታቸውን እየመቱ በፍቅር የሚያዩዋት መልካም ሰዎችን ኢትዮጵያን በጎበኘች ጊዜ አስተውላለች፡፡  እናቶች ቤት ያፈራውን አውጥተው ብሉልኝ ብለው  ከአንጀት ሲማፀኑ ይህም ትልቅ ትርጉም ሰጥቷታል፡፡  በቀናት ቆይታ ብቻ እንባ ባቀረሩ አይኖች አንገት አቅፈው የሚሰናበቱ ኢትዮጵያውያንን በ4ቱም አቅጣጫ አውቃለች…. ለፀሀይ ይህ አጋጣሚ ሙያዋን ብቻ ሳይሆን ስብእናዋንም የገነባ ትልቅ እድል ነበር፡፡

እነዚህ ዓመታት ለዘገባ፣ በስብሰባ ተሳትፎ እና በስልጠና ወደተለያዩ ክፍለ- ዓለማትም እንድትጓዝ እድል ፈጥረውላታል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ኬንያ- ናይሮቢ፤ ዩጋንዳ-ካምፓላ፤- ዱብረንቪክ-ክሮሺያ፤ ጀርመን- (በርሊን እና ፍራንክፈርት) ፤በአሜሪካ -ሲያትል፤ በህንድ- ሙምባይ፤ በኳታር ወዘተ ይገኛሉ፡፡ ከዘገባ ውጪ በሄደችባቸው ሀገራት  ተሳትፎ ያደረገችባቸውን ርእሰ-ጉዳዮች ወይም እይታዎቿን አልፎ አልፎ በጋዜጦች የማውጣት/የማሳተም ልምድም ነበራት፡፡  እነዚህ ሁሉ ሙከራዎቿ የምትወደውን ሙያ ለማሳደግና የእውቀት አድማሷን እንድታሰፋና ሁሉን አቀፍ ልምድ እንድታዳብር ትልቅ ሚና አበርክቷል፡፡ በርካታ አለማቀፍና አንጋፋ የሙያ አጋሮቿን ለማግኘትም እድል ፈጥሮላታል፡፡ በአንድ ወቅት በበርሊን የጉዞ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ በሚሰራ ጋዜጣ ላይ ስለጉዞ ልምዷ ቃለ-መጠይቅ ተደርጋ ነበር፡፡ ጋዜጣው ሲወጣ የሰዎችን የጉዞ ልምድ በመቶኛ  ያስቀምጥ ነበር፡፡ የእርሷ የጉዞ ተሞክሮ በወቅቱ 5 ፐርሰንት የዓለማችንን ክፍል መጓዟን የሚያሳይ ነበር፡፡ ብዙ የተጓዘች  የመሰላት ለካስ ምንም ሳታይ ነበር?! እንድትልም አድርጓታል፡፡ ጋዜጠኝነት ሁልጊዜም ገና አላወቅኩም በሚል ሰብእና የሚጓዙበት ረጅም ጉዞም ስለሆነ በዚህ መርህ ፀሀይ ስትጓዝ ብዙ እውቀት ቃርማለች፡፡

 

      ጋዜጠኝነት እና መሪነት

ከጥቅምት ወር 2008 ዓ.ም እስከ የካቲት 2014 .ም ጸሀይ ጋዜጠኝነትን ከመሪነት ጋር የሰራችባቸው ጊዜያት ነበሩ፡፡ በዚህ የመሪነት ዘመኗ በሙያዋ እንደ ከዚህ ቀደሙ ረጅም ጊዜን የሚወስዱ ዶክመንተሪዎች እና ፕሮግራሞችን የመስራት እድል ባታገኝም ወደ ልዩ ኢንተርቪዎች (ኤክስክሉሲቭ ኢንተርቪውስ ) ፊቷን ያዞረችበት ነበር፡፡ በዚህም በርካታ ፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ተኮር ቃለ-መጠይቆችን ከፖለቲከኞች፤ ዲፕሎማቶች እና አለማቀፍ መሪዎች ጋር እንድታደርግ እድል ሰጥቷታል፡፡

 

የመጀመሪያው የመሪነት ቦታዋ የቴሌቪዥን የውጭ ቋንቋ ዲፓርትመንት ዳይሬክተርነት ነበር፡፡ በወቅቱ ክፍሉ በእንግሊዝኛ፤አረብኛ እና ፈረንሳይኛ ዜናና እና ፕሮግራምን ጨምሮ የ2 ሰአታት ብቻ የአየር ጊዜ ነበረው፡፡ ኃላፊነት በተሰጣት ወር አጭር ፕሮፖዛል አዘጋጅታ አቀረበች፡፡ የፕሮፖዛሉን ሀሳብ በአጭሩ ጸሀይ እንዲህ  ታስታውሰዋለች፡፡

‹‹……ኢትዮጵያ በአፍሪካ ያላት ሚና ትልቅ ነው፡፡ ጋዜጠኝነት በጀመርኩበት ጊቢ ውስጥ መላው አፍሪካ በአፓርታይድ ጭቆና ውስጥ እያለ ፤የተለያዩ ሀገራት ነጻ አውጪዎች ለሀገራቸው ህዝብ የጸረ- አፓርታይድ ቅስቀሳ ያደርጉበት እንደነበር ተረድቻለሁ፤ በወቅቱ አስተማማኝና ነጻ ሀገር ኢትዮጵያ ነበረች፡፡ የአፍሪካ ህብረት እንዲመሰረት የመጀመሪያውን ምእራፍ በብቃት ከተወጡት ሀገራትም ቀዳሚዋ ናት፡፡ እስከ አሁን ግን አፍሪካ የራሷን ድምጽ ለዓለም የምታሰማበት ሚዲያ የላትም፡፡ ሲ ኤን ኤን የአሜሪካ፤ ቢቢሲ የእንግሊዝ፤ ሲ ጂ ቲኤን የቻይና፤ አልጀዚራ የአረቡ አለም፤ አማካይ ድምጾች መሆናቸው ይታወቃል፡፡ በራሳችን ድምጽ ዓለም እንዲያውቀን ከማድረግ ይልቅ እስከመቼ ለራሳቸው ድምጽ በቆሙ አለማቀፍ ሚዲያዎች የኛ ጉዳይ በአግባቡ አልተወከለም/አልተደመጠም እያልን እንጮሀለን፡፡ እነዚህ አለማቀፍ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን የሚመጥን የአፍሪካ ድምጽ በኢትዮጵያ አለመከፈቱ ጋዜጠኝነት ከጀመርኩ ጀምሮ የሚቆጨኝ በመሆኑ ምክረ-ሀሳቡን አቀረብኩ፡፡ ይህ ምክረ-ሀሳብ  ከጥቅምት 2008 ዓ.ም ጀምሮ ኢቢሲን እስከአሁን ለመሩት ኃላፊዎች በየጊዜው እየዳበረ የቀረበ ቢሆንም ብልጭ ድርግም ከሚሉ የተለያዩ ሙከራዎች በቀር መተግበር ባለመቻሉ ይቆጨኛል፡፡ ሆኖም በጊዜው እውን እንደሚሆን ተስፋ አለኝ፡፡ ›› ትላለች፡፡

በ2009አ.ም ተቋማዊ የይዘት መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት በአቶ ስዩም መኮንን የወቅቱ ስራ አስኪያጅ በተመራው ሪፎርም 12 የሙያ አጋሮቿ የተካተቱበት እና ከአንድ አመት በላይ የቆየ የይዘት ፎርማት ቀረጻ ቲም መርታለች፡፡ በዚህም በ3 የውጪ ቋንቋዎች፤ በ4 የሀገር ውስጥ ቋንቋዎች ማለትም ኦሮምኛ ፤ትግርኛ፤ ሶማልኛ፤አፋርኛ እንዲሁም ቆየት ብሎ የተቀላቀለውን የምልክት ቋንቋን ጨምሮ የዜና ፤ወቅታዊ እና መደበኛ ፕሮግራሞችን  እንደ አዲስ ሲቀረጹ፤ የተወሰኑትንም ነባር ፎርማቶች ያሻሻሉ ሲሆን ይህ ከ400 በላይ ገጾች የያዘ ዶክምንት ተሰንዶ ይገኛል፡፡ የፎርማት ክለሳ እና ቀረጻ ስራውን አጠናቀው ፤አዳዲስ ባለሙያዎችን መልምለው በማሰልጠን፤ ነባር ጋዜጠኞችን ከተለያዩ ክፍሎች በመውሰድ፤ የዜናና እና ፕሮግራም ዝግጅቶችን በማድረግ በመስከረም 1 ቀን 2011ዓ.ም የኢቲቪ ቋንቋዎች(etv Languages)   ቻናል 8 ቋንቋዎችን ይዞ ለመክፈት በቁ፡፡ በዚህም ጸሀይ ቡድን መመስረትና ወደ ጋራ ግብ የመምራት ክህሎት፤ የተለያዩ ባህል እሴቶችን ለሙያዊነት ግንባታ የማዋል አቅም ያዳበረችበት ይልቁንም ሙያዊነትን እስከተቻለ ድረስ የመላበስ ስብእናን ለማካፈል እድል ያገኘችበት ነበር፡፡ ቋንቋዎች ቻናልን ከዝግጅት እስከ ምስረታ መምራት ብቻ ሳይሆን ከተከፈተ በኋላም የቻናሉ ስራ አስፈጻሚ በመሆን እስከ 2014 ዓ.ም ድረስ  አገልግላለች፡፡

 ጸሀይ ፤ሁልጊዜም ጋዜጠኝነት ፍጹም ሙያዊነትን ከስብእና ጋር እንዲላበስ በግሏ ጥረት ታደርጋለች፡፡ ዘገባዎች ከአንድ ወገን ድምጽ ይልቅ የተለያየ እይታ እንዲያካትቱና ሚዛናዊነትን መሰረት እንዲያደርጉ ጋዜጠኞች አተያያቸውን ያለስጋት እንዲገልጹ እና ሙያዊ ክርክር እንዲዳብር ጥራለች፡፡ ሆኖም ከግል አስተዋጽኦ ባለፈ ሙያው በሙያዊነት እና ተገቢው ስብእና በተላበሱ ጋዜጠኞች ተሞልቶ ፤ ሚዲያውም ከፖለቲከኞች ተላቆ ማየት  ህልሟ ነበር፡፡

 

                              ሴት ጋዜጠኛ አንደ መሪ

 በሀገራችን የጋዜጠኝነት  ታሪክ ውስጥ የሴት የሚድያ ሰዎች ቁጥር  አነስተኛ ነው፡፡ ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን እንኳን  መዝገበ-አእምሮ በተሰኘው መጽሀፍ ላይ የ52 ሴት የሚድያ ሰዎችን የህይወት ታሪክ ለማካተት ብዙ ተጉዟል፡፡ የሴት የሚድያ ሰዎች ቁጥር ማነስ  ምክንያቱ ብዙ ነው፤- ከስራው ጋር የተያያዘ ደህንነት ስጋት ፤ ስራው ብዙ ጊዜን የሚወስድ በመሆኑ በተለይ ደግሞ ሴት የቤተሰብ ኃላፊነትን  በብዙ መልኩ ስለምትሸከም በሙያው ላይ ለመሰማራት  አዳጋች ይሆንባታል፡፡

 ፀሀይ እንደምትናገረው  እግዚአብሄር ረድቷት  በሴትነቷ  ደረሰብኝ የምትለው ችግር አልነበረም፡፡ በየትኛውም የሙያ መሰላል ከወንድ ባልደረቦቿ  ጋር እየተወዳደረች አሁን ካለችበት ደረጃ ደርሳለች፡፡  በተለያዩ ቦታዎች ብቸኛ ሴት እየሆኑ  መስራትን ለምዳዋለች፡፡

ፀሀይ በጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ ገና ከጅምሩ በበርካታ ፈተና ውስጥ የሚያልፉ ባልደረቦቿን አይታለች፡፡ ሴት ጋዜጠኞች በሙያው ብዙ ቆይታ አለማድረጋቸውን  ስለምታይ  መሪ በነበረችባቸው ጊዜያት የበኩሏን ለመወጣት ትሞክር ነበር፡፡ ጀማሪ  ሴትጋዜጠኞችን ከወንዶች ለይታ  ተጨማሪ ገለጻ  ትሰጣለች፤ በሴትነት እና ጋዜጠኝነት ዙሪያ፤ የሙያው ተግዳሮቶች እና እንዴት ማለፍ እንደሚችሉ …. በግል እየጠራች ህይወታቸውን ለመጋራትእና  ምክር ለመለገስ ትሞክራለች-ምን ያህሉ እንደተሳካላት ሌሎች ሊመሰክሩት የሚችሉት ጉዳይ ሆኖ ፀሀይ ግን የሚጠበቅባትን በአቅሟ መወጣቷን ትናገራለች፡፡

           ተግዳሮት

 ፀሀይ ለሆነ ፖለቲካ አስተሳሰብ /አመራር ወገንተኛ የሆነ እና  ለህዝብ ያልወገነ ዘገባ አጥብቃ ትቃወማለች ፡፡ ይህንንም  ትመራው በነበረው ቻናል ላይ ለማሻሻል ከመጣር ባሻገር በተቋሙ ኤዲቶርያል ከሌሎች ጥቂት ሙያዊ አስተሳሰብ ካላቸው ባልደረቦቿ  ጋር በመሆን አጥብቃ ትከራከራለች፡፡

 ፀሀይ በግሏ እንደ ተግዳሮት የምትቆጥረው   በተለይ መሪ ከሆነች በኋላ ለልጆቿ  እና ለባለቤቷ  ምንም እንኳን  የሚረዱዋት ቢሆንም  ጊዜ አለመስጠት፤ በዓላት ፤እረፍት ቀናት ፤ማህበራዊ ህይወት ሁሉ ወዘተ ያለማቋረጥ ከጠዋት እስከ ምሽት …ቢሮ  መዋሏ ምናልባት እንደ ተግዳሮት የምትቆጥረው ነው፡፡

              ስለፎርማት ዝግጅት እና ንባብ በተመለከተ

 

           ፀሀይ በፎርማት ዝግጅት  ከ1 ዓመት በላይ ተሳትፋለች፡፡  የ7 ቋንቋዎች የዜና ፓኬጅ (እያንዳንዱ ቋንቋ ቢያንስ 2 የዜና ፓኬጅ አለው) ፤የወቅታዊ ፕሮግራሞች ፓኬጆች፤ እንዲሁም የመደበኛ ፕሮግራሞችን ፓኬጆች ለማዘጋጀት  ፀሀይ እና ባልደረቦቿ ደክመዋል፡፡  ይህ ሁሉ ሲሰራ የነበረው ከመደበኛ /እለታዊ ስራዎች ጎን ለጎን ነበር፡፡ አንድ ጊዜ  ፀሀይ ትዝ እንደሚላት  የመጀመሪያ ረቂቅ ዶክመንት ለማስረከብ ቀኑን ሙሉ ስራ ውላ እቤት ገብታ ስትሰራ አድራ ከንጋቱ 11፡30 ኢሜል አድርጋ በጧት ወደስራ ገብታለች፡፡

 

 ፀሀይ በየሚዲያው የሚታየውን የይዘት መቀራረብ ፤አሰልቺነት ለመፍታት በፎርማት ዝግጅቱ ላይ የራሷን ጉልህ አሻራ ለማኖር  ሞክራለች፡፡ በሀገር ወስጥ አሉ የሚባሉ ሚዲያዎችና እና ስራዎቻቸውን ቢያንስ ለ1 ሳምንት ያለማቋረጥ በመመልከት የዳሰሳ ጹሁፍ ታዘጋጅ ነበር፡፡፤ የውጪ ፤ አንጋፋ እና ከኛ ጋር በይዘት ወይም አቀራረብ ሊሄዱ የሚችሉ ሚዲያዎችን እንዲሁ ያለማቋረጥ መመልከት እና መመዘን መሰነድ፤ በርካታ ሰነዶችን ማገላበጥ የጥናቱ ዋነኛ ስራዎች ነበሩ፡፡ ፎርማት ቀረጻው የአጠቃላይ ስራውን ግማሽ ጊዜ ከወሰደው ዳሰሳ ጥናት በኋላ የተካሄደ ነው፡፡ ፎርማት ቀረጻው ከፕሮግራም ስያሜ ተነስቶ፤ የፕሮግራሙ ዓላማ፤ታላሚ ተመልካች፤ የፕሮግራሙ አቀራረብ እና የአቅራቢ ክህሎት እና ተፈላጊ ትምህርት፤ አስፈላጊ የሰው ሀይል ብዛት እንዲሁም የሰአት ምጣኔ ድረስ በዝርዝር የተተነተነበት ሰፊ ስራ ነው፡፡ ይህ ዶክመንት 402 ገጽ ያለው ነው፡፡  በዚህ ፈታኝ ስራ ውስጥ ፀሀይ ያለፈችው፡፡

 

ጋዜጠኝነት በየዕለቱ ከንባብ እና መረጃ ጋር የሚያስተሳስር ስራ ነው፡፡  እንደማንኘውም ጋዜጠኛ መሪ ዓለማቀፋዊ እና ወቅታዊ ጉዳዮችን መከታተል ፤ ይልቁንም የፖለቲካ ክስተቶችን ጀርባ ዳራዎች መተንተን/ ትንታኔዎችን ማንበብ ፤ ከባልደረቦቼ ጋርም መወያት  ፀሀይን ከምንም ነገር በላይ ደስታን ይሰጣታል፡፡

 

       ምስክርነት   ከቢንያም አለማየሁ

 

ከወ/ሮ ፀሐይ አክሊሉ ጋር ከ 2007 ጀምሮ በቅርበት ሰርቻለሁ፡፡ እስከ 2008 አጋማሽ ድረስ አዲስ በተመሠረተው (በወቅቱ) 104.7 ሬዲዮ ጣቢያ የዜና ኤዲተሮች ሆነን ሰርተናል፡፡ በወቅቱ እንደ ቅርብ የሥራ ባልደረባ ፀሐይ በቀላሉ ምንም ነገር የማታልፍ እና ለምትሰራቸው ነገሮች ኃላፊነትን የምትወስድ አርታኢ እንደሆነች ተመልክቻለሁ፡፡ ጥራቱን የጠበቀ እና ለሰዓቱ የሚመጥን ዜና በጫና ውስጥ ሆና መስራት እንደምትችልም አይቻለሁ፡፡ ፀሐይ በዚህ ወቅት ምን ዓይነት የሚዲያ አመራር ይኑረን በሚለው የውስጥ ጥያቄ ዙሪያ ጠንካራ ተሳትፎ ስታደርግ እንደነበረም ጭምር አስታውሳለሁ፡፡ በሥሯ በሚገኙ ፕሮዲውሰሮች ላይ የምትጠብቃቸውን እሴቶች በአመራሮችም ላይ ስለምትጠብቅ በዚህ ረገድ የሚሰማትን ፊት ለፊት በመናገርም ጭምር ትታወቃለች፡፡

ፀሐይ በዚህ የተነሳ በወቅቱ የተሻለ አመራር ይፈልግ ወደነበረው እንግሊዝኛ ቴሌቪዥን ተዛውራ በዲፓርትመንት ኃላፊነት ሰርታለች፡፡ 2010 ላይ የፎርማት ለውጥ ሲደረግም የ ETV Languages ቻናል ዋ/ሥ/አስፈጻሚ ለመሆን በቅታለች፡፡ የእንግሊዝኛ፤ ዓረብኛ እና ፈረንሣይኛ የዜና እና ፕሮግራም ፎርማት ለውጦችን ብዙ ዋጋ ከፍላ እና ከሚገባት በላይ በመስራት ለተቋሙ አበርክታለች፡፡ እውነት ለመናገር ቻናሉ ዛሬ ድረስ በዚሁ ፎርማት የሚጠቀም መሆኑ ፀሐይ የሰራችው ዘመን-ተሻጋሪ እና ደርዝ ያለው ሥራ መሆኑን መመስከር ይቻላል፡፡ ፀሐይ በአመራሯ በጣም በቅርበት ኃላፊዎችን እና በሥራቸው ያሉ ጋዜጠኞችን ትከታተላለች፡፡ ስህተት የማያልፋት ሲሆን መሻሻሎች እንዲኖሩ አበክራ ትሰራለች፡፡ ፀሐይ ፈርጣማ የመሆኗን ያህል በማኅበራዊ ነገሯ ደግሞ ትመሰገናለች፡፡ ሰውኛ የሆኑ ነገሮችን በአግባቡ የምታከብር እና እንደ አለቃ ሳይሆን እንደ ቅርብ የሥራ ባልደረባም ተደርጋ የምትታይ ናት፡፡ ዛሬ በሶስት የቻናል ሥራ አስፈጻሚዎች ተከፋፍሎ ያለውን ዜናና ፕሮግራም እንዲሁም 8 ቋንቋዎች የያዘ ብዙ ፍላጎቶች የሚንፀባረቁበት ውስብስብ ቻናል ፀሐይ ብቻዋን ለዓመታት ቀጥ አድርጋ መርታዋለች፡፡

በተለይ በዚህ ቻናል ቆይታዋ ከእንግሊዝኛ እና ምልክት ቋንቋ ውጭ ያሉትን መስማትና መናገር ሳትችል ግን በሚገርም ሁኔታ የይዘት፤ የአቀራረብ እና ሌሎች አመራሮችን ብሎም አቅጣጫዎችን ሰርታ ያለ መንገራገጭ መምራቷ ለሥራው ያላትን መሰጠት ያሳያል፡፡ ፀሐይ ቻናሉ ትኩረት እንዲያገኝ እና ዛሬ ተጠብቀው የምናያቸው አንዳንድ ጥቅሞች እንዲጠበቁ፤ የአሰራር ለውጦች እንዲደረጉም ከላይኛው አመራር ጋር በመሟገት ጭምር በደንብ ትታወቃለች፡፡

ቢንያም ዓለማየሁ

የእንግሊዝኛ ቴሌቪዥን ዜናና ወቅታዊ ም/ዋ/አዘጋጅ

 

       ባለቤቷ አቶ ተመስገን  ዳምጠው

    ከባለቤቴ ፀሐይ ጋር ስንተዋወቅ በሙያዋ ነርስ ነበረች፡፡ ለትውውቃችን መነሻ  የሆነንና በዘላቂነት እንድንቀጥል ያደረገን ግን ሁለታችንም መፅሃፍ አፍቃሪዎች መሆናችን ነበር፡፡ የባለቤቴ ፀሐይ የማንበብ ፍቅር ለየት የሚያደርገው በትርፍ ጊዜዋ ከማንበብ ባለፈ እጅግ አጥብቃ ትፈልግ የነበረው ንባቧን የሚያሳድግላት ከሥነ-ፅሁፍ ጋር ተያያዥነት ያለው ሙያ በቅጥርም ሆነ በትርፍ ጊዜ መሥራት መፈለጓ ነበር፡፡ ይህ ፍላጎቷ ግን ሙሉ ጊዜ ከሚጠይቀው የነርስነት ሙያ ጋር የሚጣጣም አልነበረም፡፡

 

እናም ይህ የሥነ-ፅሁፍ ፍቅሯ እያያለ መጣና የነርስነቱን ሙያ ወደ ጎን ትታ ወደ  ጋዜጠኝነት ሙያ ለመግባት  ስትወስን፣ ቤተሰቧን ጨምሮ በዙሪያዋ ያሉ ሰዎች ሁሉ አጥብቀው ነበር የተቃወሟት፤ "ያምሻል እንዴ?" የሚሉ ብዙ ነበሩ፡፡ በርግጥም የነርስነት ሙያ በመደበኛነት ከምታገኘው ወርሃዊ ደመወዝ ሌላ የተጨማሪ ሰዐት ክፍያና በግልም አልፍ አልፎ ትሰራ ስለነበር ክፍያው በጋዜጠኝነት ሙያ ከምታገኘው ጋር የሚነፃፀር አልነበረም፡፡

 

ነገር ግን  የባለቤቴ (የዛኔ እጮኛየ) ፀሀይ የማንበብና የመፃፍ ፍላጎቷን በቅርበት የሚረዳ ሰው እኔ ብቻ ስለነበርኩ ምርጫዋን ሳላቅማማ ነበር የተቀብልኩት፡፡ ከዛም ባለፈ እገፋፋት ነበር፡፡ እጮኛዋ ስነበርኩ የኔ ተፅእኖ ቀላል እንዳልነበር እገነዘባለሁ፤ ያም ሆኖ ግን የአብዛኛውን ሰው ተቃውሞ ቸል ብላ በመጨረሻ እንድትወስን ያደረጋት የውስጧ ጩኸት እንደሆነ  ነው የሚሰማኝ፡፡

ደስ የሚለው ግን በዚህ ውሳኔዋ አንድም ቀን ተፀፅታ አታውቅም፡፡

        ባለቤቷ አቶ ተመስገን  ዳምጠው

 መምህሯ ዶክተር አብዲሳ ዘርአይ በበኩላቸው ፀሀይ በተለይ ሙያዋን በትምህርት ለማዳበር የምታደርገው ጥረት ትልቅ መሆኑን ይመሰክራሉ፡፡ ጽናት ያላት እና ታታሪ በመሆኗም የፒኤችዲ ትምህርቷን ስትጀምር ፈተናውን በአንደኝነት ነበር ያጠናቀቀችው  ሲሉ ዶክተር አብዲሳ ዘርአይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሚኒኬሽን መምህሩ ስለ ፀሀይ ያላቸውን ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡

 

 

 

ተጓዳኝ ስራዎች

ከጋዜጠኝነት እና መሪነት ጎን ለጎን በተቋሙ የ5 ዓመት ስትራቴጂ ንድፍ ዝግጅት ሁለት ጊዜ፤ እንዲሁም በተለያዩ የውስጥ አሰራር ዝግጅቶች ላይም በመሳተፍ አገልግላለች፡፡ በተለይም ኢቢሲ ከውጪ ተቋማት ማለትም ዩ ኤን፤ ኢዩ / አውሮፓ ህብረት፤ኤምባሲዎች፤ ወዘተ… ጋር በሚያደርጋቸው ግንኙነቶች እና የአጋርነት ስራዎች ውስጥ በፕሮፖዛል ቀረጻ፤ ውይይቶች እና ጉብኝቶች በማቀናጀት እና በመሳተፍ አስተዋጽኦ  ስታደርግ ቆይታለች፡፡

ጸሀይ ለሙያዋ ትልቅ ፍቅር ያሳደረች መሆኑ ማሳያ ደህና ደሞዝ ከምታገኝበት የጤና ሙያ ለቅቃ ወደ ሚድያ አለም ስትገባ ነው፡፡ ባለፉት 16 አመታት በሚድያው አለም ስትቆይ ብዙ ለመማር ስትጥር የኖረችው ጸሀይ አየር ላይ ያዋለቻቸውን ፕሮግራሞች ስናጤን የእውነትም ታታሪ ባለሙያ መሆኗን መመስከር እንችላለን፡፡ ለትምህርት ያላት ፍቅር ማሳያ ደግሞ በአሁን ሰአት የፒኤችዲ ትምህርቷን እየተከታተለች መሆኗ ነው፡፡  ጸሀይ በተለይ በእንግሊዝኛ ጋዜጠኝነት ዘርፍ ላይ  በ2000 ከመጡ የሚድያ ሰዎች በተሻለ መልኩ የተንቀሳቀሰች በመሆኑ የስራ ልምዷን ትውልድ እየተቀባበለ እንዲያነበው የህይወት ታሪኳን ሰንደነዋል፡፡ 

ፀሀይ በኢትዮጵያ ቲቪ አየር ላይ ካዋለቻቸው መሰናዶዎች ውስጥ የተወሰኑትን ሊንክ እዚህ ጋር አስቀምጠናል፡፡


https://www.youtube.com/watch?v=B4gK5Tq608s&list=PLrUzFKu4uljsjGP9oTQktJAA4tUpxkKqO&index=3

 

https://www.youtube.com/watch?v=31SIrnst5Ns&list=PLrUzFKu4uljsjGP9oTQktJAA4tUpxkKqO&index=4

 

https://www.facebook.com/watch/?v=1106286629403212

 

https://www.youtube.com/watch?v=9ETnXbQ-MoE&list=PLrUzFKu4uljua1we5rzxa3oN-oVqObrX0&index=10

 

https://www.youtube.com/watch?v=7IthauA0bes&list=PLrUzFKu4uljua1we5rzxa3oN-oVqObrX0&index=9

 

https://www.youtube.com/watch?v=gz5vFzOg6eA&list=PLrUzFKu4uljua1we5rzxa3oN-oVqObrX0&index=8

 

https://www.youtube.com/watch?v=gC1EgsBcHlY&list=PLrUzFKu4uljua1we5rzxa3oN-oVqObrX0&index=7

 

https://www.youtube.com/watch?v=dWfl9QGekls&list=PLrUzFKu4uljua1we5rzxa3oN-oVqObrX0&index=6

 

https://www.youtube.com/watch?app=desktop&v=u-pomm-Sa0I&list=PLrUzFKu4uljsjGP9oTQktJAA4tUpxkKqO

 

https://www.youtube.com/watch?v=tK-EF6UqL50&list=PLrUzFKu4uljsjGP9oTQktJAA4tUpxkKqO&index=2











 

 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች