ነፃነት ፈለቀ
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን
በሚድያ ዘርፍ አስተዋጽኦ የነበራቸው ባለሙያዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ቅዳሜ ሀምሌ 30 2014 ዓ.ም የ180 የሚድያ
ሰዎችን ታሪክ መዝገበ-አእምሮ በሚል ርእስ በጠንካራ ሽፋን የተዘጋጀ መጽሀፍ አሳትሞም ማስመረቁ ይታወቃል፡፡ በቀጣይ መዝገበ -አእምሮ
ላይ ታሪካቸው ከሚሰነድላቸው የሚድያ ሰዎች መካከል ነጻነት ፈለቀ ትጠቀሳለች፡፡ ነጻነት ፈለቀ በሚድያው አለም ከ22 አመት በላይ
የሰራች ሲሆን በተለይ በኢትዮጵያ ሬድዮ የዜና ፋይልን ሌጋሲ በወጉ ካስቀጠሉት መካከል እንደ አንዷ ትቆጠራለች፡፡ የህይወት ታሪኳም
እንደሚከተለው ተሰናድቷል፡፡
ትውልድ እና ልጅነት
ጋዜጠኛ ነፃነት ፈለቀ አባቷ አቶ ፈለቀ ባልከው እናቷ ወይዘሮ አስቴር ደምሴ ይባላሉ፡፡ ነጻነት ጥቅምት 17 ቀን 1972 ዓ.ም ተወለደች። ውልደቷ እና እድገቷ በአዲስ አበባ ከተማ የባህልና የስፖርት ሚኒስቴር መስሪያ ቤት አካባቢ በተለምዶ ሰንጋተራ በሚባለው ሰፈር ነው።
አንደኛ ደረጃ ትምህርቷን ደጃዝማች በየነ መርዕድ (ዕድገት በህብረት) የተማረች ሲሆን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን የተከታተለችው በሽመልሰ ሀብቴ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው። ነፃነት ፈለቀ በአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የደረጃ ተማሪ ናት። ከ10 እስከ 12ኛ ክፍል የተማረችውም ጎበዝ ተማሪዎች ተለይተው በሚማሩበት ልዩ ክፍል (ስፔሻል ክላስ) ነው። ከትምህርት ዓይነቶች ውስጥ አማርኛ፣ እንግሊዝኛ፣ ሒሳብ፣ ኬሚስትሪ፣ ባዮሎጂ፣ ታሪክና ጂኦግራፊ የምትወዳቸው የትምህርት ዓይነቶች ናቸው።11ኛ ክፍል ላይም የተፈጥሮ ሳይንስ (ናቹራል ሳይንስ) ወይም ማህበረሰብ ሳይንስ (ሶሻል ሳይንስ) ለመምረጥ እንደተቸገረች ታስታውሳለች። መጨረሻ ላይ ግን የተፈጥሮ ሳይንስን መርጣለች።
ዩኒቨርሲቲ
የከፍተኛ ትምህርቷን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት በአሁኑ ስያሜው (አአዩ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ክፍል) ለመጀመሪያ ጊዜ ከ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን አወዳድሮ ሲቀበል እርሷም በነበራት ጥሩ ውጤት ወደተቋሙ ገብታ የመማር ዕድል አግኝታለች። በ1992 ዓ.ም በህትመት ጋዜጠኝነት ዲፕሎማ ያገኘች ሲሆን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሰቲ በውጭ ቋንቋና ሥነ ጽሁፍ 2000 ዓ.ም ላይ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ተቀብላለች። በዚሁ ዩኒቨርሰቲ ሁለተኛ ዲግሪዋን በብሮድካስት ጆርናሊዝም ተከታትላለች። አሁን ደግሞ በቻይናው ናንካይ ዩኒቨርስቲ በአለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል በፖለቲካል ቲዮሪ የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቷን እየተከታተለች ትገኛለች።
በሚዲያ አመራርና በጋዜጠኝነት ሙያ የተለያዩ አጫጭር ስልጠናዎችን በውጭ እና በሀገር ውስጥ ተከታትላለች።
ወደ ስራ አለም
ነጻነት ፈለቀ ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት እንደተመረቀች መስከረም 1993 ዓ.ም ላይ ሥራ የጀመረችው በአዲስ አበባ መገናኛ ብዙኃን በአሁኑ ስያሜው አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ አዲስ ልሳን ጋዜጣ ላይ በሪፖርተርነት ነበር። በጋዜጣው ላይ ለ5 ወራት ከሰራች በኃላ በግል ምክንያት በመልቀቅ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የተባለ ጋዜጣ ላይ ከ2 ዓመት በላይ ሰርታለች። ከዚያም በግል ምክንያት የለቀቀች ሲሆን ከ8 ወራት በኃላ ኢትዮጵያ ሬዲዮ ተወዳድራ ነሐሴ 1996 ዓ.ም. ላይ በሪፖርተርነት በኢትዮጵያ ሬዲዮ ዜና ክፍል ተቀጥራለች። ከዚያም በተቋሙ የደረጃ ዕድገት አሰራር መሰረት ተወዳድራ ከከፍተኛ ሪፖርተር እስከ አዘጋጅ በመሆን ያገለገለች ሲሆን 1998 ላይ ሚዲያ ሞኒተሪንግ ለመጀመሪያ ጊዜ ከትራፊክ ክፍል ጋር ሲደራጅ በኃላፊነት ተመድባ ሐምሌ 1998 ዓ.ም ላይ እስከ መጋቢት 17 ቀን 2001አ.ም አገልግላለች። ከመጋቢት 18 ቀን 2001 ዓ.ም. ጀምሮ አዲስ በተቋቋመው የኦንላይንና የሚዲያ ሞኒተሪንግ ክፍል ውስጥ የሚዲያ ሞኒተሪንግ ቡድንን በማስተባበር ለ3 ዓመታት ሰርታለች። በኃላም የኦንላይንና ሚዲያ ሞኒተሪንግ ክፍልን ለአንድ ዓመት በማስተባበር የሰራች ሲሆን ጥር 2005 ዓ.ም ላይ ሬዲዮ ስለተዳከመ ሬዲዮንን ለማጠናከር በሚል ወደምትወደው የሬዲዮ ዜና ክፍል በኃላፊነት ተመድባ ሰርታለች።
በዚህም የሰዓተ- ዜና ይዘትና አቀራረብ በማሻሻልና የአድማጮች አስተያየት በተገቢው መንገድ እንዲስተናገድ በማድረግ የዜና ፓኬጁ ተወዳጅ እንዲሆን አድርጋለች። ቴሌቪዥን ላይ እንዳይሄዱ የሚከለከሉ የመልካም አስተዳደር ችግር የሚያነሱ ዘገባ ሥራዎች ሙያዊ አሰራርን ተከትለው እስከተሰሩ ድረስ ዜናዎቹን ሬዲዮ ላይ በድፍረት ታስኬዳቸው ነበር። ለጋዜጠኞችም ተገቢውን ከለላ ታደርግ እንደነበር አብረዋት ይሰሩ የነበሩ ጋዜጠኞች ይመሰክሩላታል።
ነፃነት ሪፖርተር በነበረችበት ወቅት በተለይ ከ1997 ምርጫ ጋር የተያያዙ ዜናዎችን ሙያዊ በሆነ መንገድ ትሰራ ነበር፡፡ ሙያው ከሚፈቅደው ውጭ የሚመጡ ይዘቶችን አላነብም እስከማለት ትደፍር ነበር። በኤዲቶሪያል መድረኮችም ላይ ዜናዎች ሙያው የሚፈቅደውን ሥነ ምግባር ጠብቀው እንዲሰሩ ከኃላፊዎች ጋር በመሟገት ትታወቃለች።
ኢትዮጵያ ሬዲዮ በተቋሙ የበላይ አመራሮች ተገቢው ቦታ ባለማግኘቱ ለመዳከሙ ምክንያት እንደሆኑ በድፍረት ትናገራቸዋለች። ሊሻሻልበት የሚችልበትንም አቅጣጫ ታጠና ነበር። ኢቢሲ 2009 ዓ.ም ላይ ክፍተቱን በማጥናትና መጋቢት 2010 ዓ.ም ላይ በተተገበረው አዲስ የይዘትና አቀራረብ ላይ የኢትዮጵያ ሬዲዮ ዜናና ወቅታዊ፣ ትምህርታዊና መዝናኛ ፕሮግራሞች በበላይነት ጥናቱንና ትግበራውን መርታለች። በዚህም ኢትዮጵያ ሬዲዮ ላይ አዲስ የተቀረጹና ነባሮችን በማሻሻል ሊደመጡ የሚችሉ የዜና ፓኬጅና ፕሮግራሞች አስተግብራለች።
ነፃነት ዜና፣ ፕሮግራም፣ አጫጭር መልዕክት ያላቸውን ስፖት ከመስራትና ከማዘጋጀት ባለፈ የዜናና ፕሮግራም መግቢያ ሙዚቃዎችን በማዘጋጀትና የኢትዮጵያ ሬዲዮ የ24 ሰዓት ስርጭት መርሀ- ግብር ወይም ሎግሽት አዘጋጅታ እንዲተገበር አድርጋለች። የሬዲዮ ዜናና ፕሮግራም ስታንዳርድ የሚያስጠብቅ የአሰራር መነሻ ማንዋል አዘጋጅታም ተግብራለች።
ሬዲዮ ለሀገር ግንባታ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ቢሆንም በተለይ በመንግስት አካላት የሚሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ እንደሆነ የምታምነው ነፃነት ዓለም አቀፉ የሬዲዮ ቀን በኢትዮጵያ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲከበር በወቅቱ የቅርብ ኃላፊዋ ከሆነችው አስመረት ኃ/ስላሴ ጋር አብራ ሰርታለች። ዓለም አቀፉ የሬዲዮ ቀን ቀጣይነት ኖሮት በየዓመቱ በተለያዩ ዝግጅቶች እንዲከበር እና ሬዲዮ ለሀገር ያለው አበርክቶ እንዲጎላ መድረኮችን በማዘጋጀት በተለይ ለሁለተኛ እና ለሦስተኛ ጊዜ በኢትዮጵያ የተከበረውን ዓለም አቀፍ የሬዲዮ ቀንን በመምራትና በማስተባበር ሰርታለች።
ነፃነት ከጋዜጠኝነት ሥራው ጎን ለጎን በተቋሙ ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ላይ የራሷን አስተዋጽኦ አበርክታለች። በተቋሙ የስትራቴጂክ ዕቅድ፣ የይዘትና አቀራረብ ጥናት፣ የመዋቅር ጥናት፣ የችሎታ ወይም የታለንት ግዢ በመሳሰሉ የኮሚቴ ሥራዎች ላይም በአስተባባሪነት እና በአባልነት ጉልህ ተሳትፎ አድርጋለች። በተለያዩ ጊዜያትም የኢቢሲ ሬዲዮ ዘርፍ ተወካይ ሆናም አስተባብራለች።
ነፃነት በሥራ አጋጣሚ የተለያዩ ሀገራትን የማየት ዕድልም ገጥሟታል። ለአብነት ከአሜሪካ ግዛቶች ቴክሳስ፣ ሎስአንጀለስና ዲሲን፣ እንግሊዝ ለንደን፣ ኦስትሪያ ቪየና፣ ደቡብ አፍሪካ ጆሀንስበርግ፣ ሩዋንዳ ኪጋሊ፣ ታንዛኒያ ዳሬሰላም፣ ኡጋንዳ ኢንቴቬ እና ሶማሊያ ሞቃዲሾ ለዘገባ ሥራና ለሥልጠና የሄደችባቸው ሀገራት ናቸው።
ነፃነት ፈለቀ ባለትዳር ስትሆን ከባለቤቷ አቤል ሰለሞን ጋር ጥር 27 ቀን 1993 ዓ.ም ላይ ጋብቻ ፈጽማለች፡፡ ሁለቱ ጥንዶች አንድ ወንድና ሁለት ሴቶት ልጆች አሏቸው። የመጀመሪያ ልጅ የሆነው አማኑኤል አቤል በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የአራተኛ ዓመት የሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ ተማሪ ሲሆን ባርኮት አቤልና ፀባኦት አቤል ደግሞ በሚረር አካዳሚ የስምንተኛና ሰባተኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው።
ነፃነት ሥራዋን ከልብ ወድዳ የምትሰራ፣ ሬዲዮንን በፍቅር የምታዳምጥ፣ ከባልደረቦቿ ጋር በመግባባትና በፍቅር ሰርታ የምታሰራ ስትሆን ሁሉም ባልደረቦቿ ማለት ይቻላል እንደጓደኛቸው እንጂ አለቃቸው እንደሆነች እንደማያስቡ የሚናገሩላት ነች። አሁን በኢቢሲ ከትምህርት ጎን ለጎን በይዘት አማካሪነት እየሰራች ትገኛለች። ስለ ነጻነት ተገቢውን ሙያዊ ምስክርነት
እንዲሰጡ ካነጋገርናቸው መካከል የሚድያ ባለሙያ እንዲሁም የዋርካ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን መስራች እሸቱ ገለቱ አንዱ ነው፡፡ እሸቱ
ነጻነት ፈለቀ ኢትዮጵያ ሬድዮ በዜና ክፍል ውስጥ ትሰራ በነበረበት ጊዜ የዘርፉ ዳይሬክተር ነበር፡፡ በመሆኑም ነጻነት ገና በሪፖርተር
ደረጃ ሳለች ታደርግ የነበረውን ጥረት አደንቃለሁ ሲል ጋዜጠኛዋ ፕሮፌሽናል በሆነ መልኩ ትሰራ እንደነበር ያስታውሳል፡፡
‹‹ ነጻነት በጊዜው ሚዛናዊ እና ትክክለኛ የሆኑ ዜናዎችን ለአየር ለማብቃት ታደርግ የነበረው ጥረት በብዙዎቻችን ዘንድ
የሚደነቅ ነው፡፡ በተለይ በምርጫ 97 ጊዜ ፊት ለፊት ደፍራ ለመውጣት ትታገል እንደነበር አስታውሳለሁ›› ሲል እሸቱ ተናግሯል፡፡
እሸቱ በዛን ጊዜ ስለነበሩት የዜና ክፍል ሪፖርተሮች ሲነሳ አሸናፊ ሊጋባ እና ነጻነት ፈለቀ ይነሳሉ ሲል እንደ አለቃ
ትልቅ አፈጻጸም የነበራቸው ናቸው ሲል ሀሳቡን ሰጥቷል፡፡
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ