ሸዋዬ ለገሠ
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የግለ-ታሪክ ላይ ምርምር የሚያደርግ የስነዳ ተቋም ሲሆን በልዩ ልዩ ሙያ ላይ ያሉ ሰዎችን የህይወት ታሪክ ያስቀምጣል፡፡ ቅዳሜ ሀምሌ 30 2014 ዓ.ም የ180 የሚድያ ሰዎችን የህይወት ታሪክ መዝገበ-አዕምሮ በሚል ጥራዝ ለህትመት ያበቃና የተመረቀ ሲሆን ወደፊትም የስነዳ ስራው በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ ከዚህ በታች ታሪኳ የሚቀርብላችሁ የሚድያ ሰው በአዲስ ድምጽ ፣ በፋና ሬድዮ እና በጀርመን ድምጽ አገልግላለች፡፡ አሁንም በጀርመን ሀገር ቦን ከተማ ሙያዊ ሥራዋን በብቃት እየተወጣች ትገኛለች፡፡ባለታሪኳ ጋዜጠኛ ሸዋዬ ለገሠ ስትሆን ጽሁፉን ደግሞ እዝራ እጅጉ እንደሚከተለው ሰንዶታል፡፡
ውልደትና ልጅነት
ሸዋዬ ለገሠ አዲስ አበባ በ1960 ዓ.ም ተወልዳ እዚያው በዋናው መዲና ከመጀመሪያ እስከ ከፍተኛ ትምህርቷን ስትከታተል ጋዜጠኛ እሆናለሁ የሚል ህልም አልነበራትም። ግን ራዲዮ ማድመጥን እጅግ ታዘወትር እንደነበርና ለሙያውም ታላቅ ክብር ትሰጥ እንደነበር ትናገራለች።
«በባትሪ ድንጋይ የምትሠራው የቤታችን ራዲዮ አብዛኛውን ጊዜ እኔ ባለሁበት ስፍራ መገኘቷ የተለመደ ነበር» የምትለው የዛሬዋ የጀርመን ዓለም አቀፍ ራዲዮ ዶቼ ቬለ ጋዜጠኛ በተለይ በ1983 ዓ. ም ግንቦት ወር በተደረገው የመንግሥት ለውጥ የኢትዮጵያ ራዲዮ ጣቢያ በኢህአዴግ መራሹ ኃይል ቁጥጥር ስር ሲውል እኒያ እሷ አዘውትራ ስታደምጣቸው የኖረችው አንጋፋ ጋዜጠኞች ወቀሳ ከሰሳ ያቀርቡበት የነበረው ተቀይሮ በሌላ ገፅ በዚያው በተለመደው የመገናኛ ብዙሃን በውዳሴ ሲቀርቡ ስትመለከትና ስታዳምጥ በእርግጥም «በጋዜጠኝነት የሚበላ እንጀራ በአፍንጫዬ ይውጣ» ማለቷን አትዘነጋውም። የሕይወት ጥሪዋ ግን በዚሁ መስመር ከዓመታት በኋላ መራት።
ከስቱዲዮ ትውውቅ
በ1980ዎቹ ትምህርት በራዲዮ የሚያቀርበው የለገዳዲ ራዲዮ ጣቢያ የቅዳሜ እና እሑድ መዝናኛ ዝግጅቶች የወጣቶችን ድምፅ ያካትቱ ነበርና ወደ ራዲዮ ስቱዲዮ ጎራ ማለት ጀመረች። እነ «ቅዳሜን ከእኛ ጋር» እና «እሑድን ላንዳፍታ» የወቅቱ ተደማጭ እና የአድማጭም ተሳትፎ የሚስተናገድባቸው አዝናኝ እንዲሁም አስተማሪ ዝግጅቶች ነበሩ። አዘጋጆቹ ወጣቶችን የሚያቀርቡ ነበሩ፡፡ እና ተመሳሳይ ዝንባሌ በነበረው አብሮ አደግ ጓደኛዋ አማካኝነት ወደዚህ ራዲዮ ጣቢያ በመሄድ ማንበብ ጀመሩ። በእነዚህ ዝግጅቶች የነበራት ተሞክሮና ተሳትፎም ወደ ራዲዮ ስቱዲዮ አቀረባት።
የሥነጽሑፍ ዝንባሌዋ ከማንበብ አልፎ ወደ መጻፉ መሸጋገር የጀመረውም በዚህ ጊዜ ነበር። ግጥሞችን በመሰደር ለመፍታታት የሞከሩ እጆች ወደ ልብ-ወለድ ስነጽሑፍ ለመሸጋገር መውተርተር ጀመሩ። ወጣትነት ከሚያላብሰው ድፍረት ጋር ተዳምሮ አንድ ታሪክ ተጻፈ። የአብሮ አደግ ጓደኛዋ ማበረታታት ታክሎበት ይኽን ለማሳተም ተወጠነ። ይሁንና ከውጥን የዘለለ አቅም አልነበረም። «እንኳንም ያኔ አቅም አልኖረኝ» ትላለች ዛሬ ባለታሪኳ። መጽሐፉ ምንም እንኳን የአንጋፋ እና ታዋቂ ደራስያንን እና የስነጽሑፍ ምሁራንን አዎንታዊ አስተያየት ቢያገኝም «ለአቅመ- ሕትመት ደርሷል» የሚል እምነት ግን ዛሬ መለስ ብላ ስታስታውሰው አታምንም። ግን ይኽ ድርሰት ለሌላ የሕይወት ምዕራፍ መክፈቻ ሆነ። መጽሐፉን በስፖንሰር ለማሳተም እንቅልፍ ያጣው አብሮ አደግ ጓደኛ ባመጣው መረጃ መሠረት ወደ ታምቤክ ኢንተርናሽናል ጎራ አለች።
ወቅቱ በኢትዮጵያ ነፃው ፕረስ ተፈቅዶ በርካታ ጋዜጦች እና መጽሔቶች ሀገሪቱ ውስጥ የፈሉበት ጊዜ ነው። ታምቤክ ኢንተርናሽናል «አዲስ ድምፅ» የተሰኘ የአማርኛ «አዲስ ትሪብዩን» የተባለ የእንግሊዝኛ ጋዜጦችን ለአንባብያን ያቀርብ የነበረ የግል ድርጅት ነው። ጸሐፍያንን ለማበረታታት በሚል ድርሰቶችን ለማተም መዘጋጀቱን የሚገልፅ ማስታወቂያ በማውጣቱ ነበር ወደዚያ የተሄደው። ከታምቤክ ጋር የሚሠሩ በወቅቱ የነበሩት የታወቁ ሃያስያን ድርሰቱን ተመልክተው አንድ ነገር አረጋገጡ፣ «መጻፍ ፣ መተረክ ትችያለሽ»፣ እናም የድርጅቱ ባለቤት አቶ ታምራት በቀለ (ነፍሱን በገነት ያሳርፋት!)፣ «ለምን ለእኛ አትሠሪም?፣ የሴቶች አምድን እንስጥሽ» የሚል ጥያቄ አቀረበ። በዚሁ የጋዜጠኝነቱ ሥራ ጉዞ በሕትመት መገናኛው ዘርፍ በ1985አ.ም ተጀመረ።
በዚህ አጋጣሚም ሸዋዬ በአዲስ ድምጽ ጋዜጣ የሴቶች አምድ ጥቂት የማይባሉ ጠንካራ ኢትዮጵያውያን ሴቶች መኖራቸውን የሚያሳዩ ቃለ-መጠይቆችን እና የሕይወት ተሞክሮዎችን ለማውጣት መሞከሯን ትናገራለች። ብዙዎቹም በንግዱ ዘርፍ ስኬት ላይ መድረስ የቻሉ ነበሩ። የአዲስ ድምጽ የሴቶች አምድ በተለይ በንግዱ ዘርፍ በተሰማሩ ሴቶች ላይ ትኩረት እንድታደርግ ከጋዜጣዋ አርታኢዎች ጋር የተስማሙትም፤ በተለያዩ የአፍሪቃ ሃገራት ሴቶች የራሳቸውን ሀብት የማፍራት መብት እንደሌላቸው በመረዳት ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ ያለ ገደብ ባለመኖሩ ሠርተው ለፍተው ለስኬት የሚበቁትን ማበረታታት ይገባል በሚል እንደነበር ታስታውሳለች። እንዲያም ሆኖ በሙዚቃው እንዲሁም በሌላው የጥበብ ዘርፍም የተሻለ እና ለሌሎችም አርአያ ከሚሆኑ ጠንካራ ሴቶችን ሥራዎች ለአንባብያን ስታቀርብ ቆይታለች። ታሪክ ተሞክሯቸውን ካጋራችን መካከልም የቤት ውስጥ ዲዛይን ባለሙያ፤ ከንግዱ ዘርፍ የሺ ቡና፤ በግዙፍ የመጓጓዣ ዘርፍ ከተሰማሩት ወይዘሮ ሀዲያ ጎንጂ፤ እንዲሁም ከሙዚቃው ዘርፍ አርቲስት ቻቺ ታደሰ ይገኙበታል።
አዲስ ድምጽ ጋዜጣ ላይ መሥራት በጀመረችበት በዚሁ ዓመት በማታው ክፍለ ጊዜ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ስነጽሑፍ የትምህርት ክፍልም ሌላኛው ጉዞ አሀዱ ተባለ። ከ4 ዓመታት ቆይታ በኋላም በወቅቱ ወደ መደበኛው የትምህርት ክፍለ ጊዜ እንዲዛወሩ በዩኒቨርሲቲው ዕድል ካገኙት ሁለት የዘርፉ ተማሪዎች አንዷ በመሆን ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት በቀን በመማር አጠናቀቀች።
ከትምህርቱ ጎን ለጎን በሕትመት የመገናኛው ዘርፍ የቀጠለው የጋዜጠኝነት ሥራ አዲስ ድምፅ ሕትመቷን እስክታቆም ከመዝለቁም ሌላ በግል «ጣይቱ» የተሰኘች በሴቶች እንቅስቃሴ ላይ ብቻ የምታተኩር ጋዜጣንም ለማሳተም ሞክራለች። የመጀመሪያው ሕትመት ዛሬ ድረስ በማትዘነጋቸው የሥራዋ አድናቂዎችና የሴቶችን ጠንክረው መውጣት በሚደግፉ ወገኖች ትብብር ለአንባቢ መቅረብ ችሏል። ያኔ የፖለቲካው ውዥንብርና ውጥረት የሕትመት መገናኛውን በመጫኑ ከተለመደው አርዕስተ ዜና ውጪ የማስተናገድ ፍላጎት ፍፁም አልነበረም። የጋዜጣ አከፋፋይ እና ሻጮች የዜና ርዕስ የሚሰጡበት፣ የዜናው ርዕስ ከዝርዝር ጉዳዩ የማይገናኝበት እጅግ የተደናገረ ወቅት እንደነበርም አትዘነጋውም። «ጣይቱ» በዚህ ፈታኝ ወቅት ብዙም ለመራመድ አልቻለችም። ከፍተኛ ልምድን ማስገኘቷ ግን አይታበልም። «ጣይቱ» ጋዜጣ በራሱ የሥራ ፈቃድ እንድትታተም ያደረገው «እንጎቻ» የተሰኘች ሳምንታዊ የፖለቲካ ጋዜጣ አርታኢ የነበረው ጋዜጠኛ መላኩ ደምሴ ነበርና ዛሬም ታመሰግነዋለች።
በራዲዮ የዘለቀው ሙያዊ ጉዞ
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጉዞ የመጀመሪያው ምዕራፍ ከ1990 የትምህርት ዘመን ማለቂያ ጋር አብሮ በምረቃ ሲያበቃ በዚሁ ዓመት ነሐሴ መባቻ ደግሞ የራዲዮ ጋዜጠኝነቱ በይፋ ተጀመረ።
ራዲዮ ፋና ለጋዜጠኛ ሸዋዬ ለገሠ የሙያ እና የሥራ ብቻ ሳይሆን መልካም ወንድም እና እህቶችን እንደ ቤተሰብ ያፈራችበት ቤት ነው። በማኅበራዊ ዝግጅት ዘረፍ ከሦስት ዓመታት በላይ በዘለቀው ቆይታዋም የቤተሰብ ጤና እና የልጆችን ጨምሮ ከትምህርትና ከተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮች ጋር የሚዛመዱ ዝግጅቶችን አሰናድታ አቅርባለች። ያኔ በልጆች ጊዜ ከእሷ ጋር ዝግጅት ያቀርቡ የነበሩት ተባባሪዎች ዛሬ አድገው በተለያዩ የሙያ እና የሕይወት መንገድ ጥሩ ደረጃ ላይ መድረሳቸው ከሚያስደስታት የሕይወት ገጠመኝ አካል ነው። ከእነሱ ውስጥ አሁን በጋዜጠኝነቱ የገፉም አሉ። የቤተሰብ ጤናን በሚመለከተው ሳምንታዊ ዝግጅት ከአካላዊ ጤና እስከ መልካም ቤተሰባዊ ሕይወት ባለሙያዎች እና አርአያ የሚሆን ተሞክሮ ያላቸው እንግዶች ይስተናገዱበት ነበር። በተለይ በጊዜው ኤችአይቪ ኤድስ የበርካቶችን ሕይወት የቀጠፈበት፤ የብዙዎም ቤት የሀዘን ድባብ ያጠላበት፤ እንዲሁም ጥቂት የማይባሉ ልጆች ወላጆቻቸውን በበሽታው ተነጥቀው ለችግር የተዳረጉበት ስለነበር በዝግጅቷ አማካኝነት ጉዳዩን አደባባይ ለማውጣት መቻሉን ጋዜጠኛ ሸዋዬ አትዘነጋውም።
ጋዜጠኛ ሸዋዬ ለገሠ ራዲዮ ፋና በሥራ ላይ ሳለች በተቋቋመው የኢትዮጵያ ሴት የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ማሕበር አማካኝነት ባገኘችው ዕድል ወደ ካምፓላ ዩጋንዳ ተጉዛ ለአንድ ዓመት በዩጋንዳ ማናጅመንት ኢንስቲትዩት የጋዜጠኝነት ኮርሶችን ተከታትላ በዘርፉ ዲፕሎም አግኝታለች። «ከዩጋንዳ መልስ በጋዜጠኝነት ለመቀጠል ለነበረኝ ተስፋና ፍላጎት ያልጠበኩት ሳንካ ተፈጥሮበት ነው የጠበቀኝ» ትላለች ጋዜጠኛ ሸዋዬ። በ1993 ዓ,ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተከሰተው የተማሪዎች ተቃውሞን የተመለከቱ ዘገባዎች በርካታ ጋዜጠኞች ከተለያዩ መንግሥታዊ መገናኛ ብዙሃን እንዲለቁ ምክንያት እንደነበር ሀገር ውስጥ ከቆዩት የሙያ አጋሮቿ ተረዳች። እናም ጋዜጠኝነትን በነጻነት የመሥራቱ ነገር ትልቅ ጥያቄ ወደቀበት፤ ለእሷም በሙያው የመቀጠል ፍላጎት ፈተና ገጠመው። «ሙያውን ብትወደውም፤ የመጀመሪያ የጋዜጠኝነት መድረኬ የምትለውን ራዲዮ ፋናንም መተው ባትፈልግም፤ በተጽዕኖ የሚሠራ ጋዜጠኝነት ለኅብረተሰቡም ሆነ ለመንግሥት አስተዳደር የሚጠቅመው ነገር አይኖረውም በሚል «ብተወውስ የሚል ውሳኔ ላይ» መድረሷን ትገልጻለች። ከዚያም ጋዜጠኝነቱን በመተው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ወዳወጣው የሕዝብ ግንኙነት የሥራ ማስታወቂያ ዓይኗ አማተረ። ሄዳ ተመዘገበች ተፈተነችም። ፈተናውን አልፋ ለቃለ መጠይቅ ከቀረቡት መካከል አንዷ ሆነች። ምንም እንኳን በቃለመጠይቁ ወቅት ጠያቂዎቿን በምላሿ ብታረካም «የእንዳትቀጥሯት» ትዕዛዝ መድረሱን ከፈተኗት መካከል እንደነገሯት ታስታውሳለች።
እንዲያም ሆኖ በኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት አማካኝነት እየተዘጋጀ በኤፍ ኤም 97.1 ይተላለፍ በነበረ ዝግጅት ላይ በትርፍ ሰአት እየሠራች ለሴት መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ማሕበር ከማሕበሩ የሥራ አስፈፃሚ አባላት ጋር በመተባበር ቢሮ በማቋቋምና የማሕበሩን እንቅስቃሴዎች በቅርበት በመከታተል ስትሠራ ቆየች። በዚህ ጊዜ በዩጋንዳ ቆይታዋ በነበራት ማኅበራዊ መስተጋብር በተፈጠረ ግንኙነት በተገኘ በአፍሪቃ ሃገራት መካከል በአንድ /ፍሬድስኮርፕሴት/ በተባለ የኖርዌይ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት አማካኝነት የልምድ ልውውጥ ዕድል ማሕበሩ እንዲያገኝ አስችላ በማሕበሩ የሥራ አስፈጻሚ አባላት የስብሰባ ውሳኔ ዳግም ለልምድ ልውውጥ ማሕበሩን ወክላ ዳሬሰላም ታንዛኒያ ሄዳ ለአንድ ዓመት ተልዕኮዋን በስኬት አጠናቅቃ ወደ ሀገሯ ተመለሰች። በቆይታዋ ከሌሎች ሃገራት የሴት ጋዜጠኞች ተሞክሮዎችን በመቅሰምም ኢትዮጵያውያን ሴት ጋዜጠኞች የተሻለ የስልጠና መድረኮችንና ዕድሎችን እንዲያገኙ የበኩሏን አስተዋፆኦ የማድረግ አጋጣሚ አግኝታለች።
ጋዜጠኛ ሸዋዬ ለገሠ በወቅቱ የነበረው የፖለቲካ ውጥረት በጋዜጠኝነቱ ለመግፋት በነበራት ፍላጎት ላይ የራሱን ጫና በማድረጉ እንደምትፈልገው በዘርፉ ለመንቀሳቀስ አላስቻላትም። በዚህ አጋጣሚ ከሙያው ለወራት የመራቅ ሙከራ ብታደርግም ጥሪዋ ይኸው ሆነና ዳግም በ1996 መገባደጃ ወራት ለዓለም አቀፉ የጀርመን ራዲዮ ከአዲስ አበባ የመዘገብ ዕድል በማግኘቷ ዳግም የጋዜጠኝነት ሥራዋን ጀመረች። ተገቢውን ፈቃድ ተቀብላ በሀገር ውስጥ በዘጋቢነት ሥራዋ ብዙም ሳትቆይ ለተወሰኑ ወራት ከዶቼ ቬለ በተደረገላት ጥሪ ባሕር ማዶ ተሻገረች።
ጋዜጠኛ ሸዋዬ ለገሠ እንደምትለው ቦን ከተማ በሚገኘው የጀርመን ድምፅ/ዶቼ ቬለ/ የሚኖራት ቆይታ በወራት ግፋቢል በጥቂት ዓመታት የተወሰነ ይኾናል የሚል ግምት ቢኖራትም ጋዜጠኝነት የሕይወት ጥሪና መስመሯ ሆኖ እስከዛሬ ዘልቋል። በ1997 ዓ,ም ኢትዮጵያ ከወትሮው ለየት ያለ እና የብዙዎችን ትኩረት የሳበ፤ ተስፋንም ያሳደረ ምርጫ ማካሄዷ ይታወሳል። በወቅቱ ከቦን ከተማ ፖለቲከኞችን እያነጋገረች ታቀርባቸው የነበሩ ዘገባዎች ክስን ያስከትሉ ጀመር። በተለይም በኮሎኝ ከተማ በጀርመን የኢትዮጵያ ኤምባሲ የምርጫው ውጤት ከተሰማ በኋላ የሰዎች መገደልን ተከትሎ አዘጋጅቶት የነበረውን እጅግ ጥቂት ሰዎች ብቻ የተገኙበትን መድረክ ተከታትላ ያቀረበችው ዘለግ ያለ መሰናዶ ጠንካራ ክስ አመጣ። ክሶች ሲበረክቱ እዚሁ ጀርመን ባገኘችው ዕድል በጋዜጠኝነቱ ለመግፋት ወስና ቀጠለች።
በዶቼ ቬለ ሳምንታዊ የጤና እና አካባቢ መሰናዶ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ስም በሚደረገው የደን ምንጣሮ ላይ ያተኮሩ የማንቂያ መሰናዶዎችን በስፍራው የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በማነጋገር አደጋዎችን አመላክታለች። «ፍላጎት እና ጥረቱ ካለ የቦታ ርቀት አይገድብም» የምትለው ጋዜጠኛ ሸዋዬ ጋምቤላም ሆነ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የደን ሀብት መመናመኑን ከቦታው እማኞችን በማነጋገር፤ የአካባቢ ተፈጥሮ ተቆርቋሪዎችን እንዲሁም የደን ባለሙያዎችን ድምጽ ያቀረበችባቸው መሰናዶዎች ዛሬም በዶቼ ቬለ ድረገጽ ላይ ይገኛሉ። በጤናው ረገድ ከአድማጮች ለሚላኩላት ጤና ነክ ጥያቄዎች የየዘርፉን የህክምና ባለሙያዎች ማብራሪያ ማስተናገድም የማትሰለቸው ለኅብረተሰቡ ይጠቅማል የምትለው የሥራዋ አካል እንደሆነ ታምናለች። በሳምንታዊው የእንወያይ መድረክም ወቅታዊ እና ሀገራዊ ጉዳዮችን በማንሳት ኢትዮጵያውያን እና በውጪ የሚኖሩው ትውልደ ኢትዮጵያ ምሁራን፣ ፖለቲከኞችን እና የመንግሥት ኃላፊዎችን በማቅረብ ውይይቶችን እያስተናገደች ትገኛለች። እንደ ዋዛ ለስድስት ወራት ከኢትዮጵያ ለሥራ ልምድ የወጣችው ጋዜጠኛ ሸዋዬ ለገሠ ለ18 ዓመታት ቦን ከተማ ከሚገኘው የጀርመን ዓለም አቀፍ ራዲዮ ዶቼቬለ በሁለገብ ጋዜጠኝነት በሙያው ቀጥላ በመሥራት ላይ ትገኛለች። በዚህ ጊዜ ውስጥም ስለዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ እንግሊዛዊው ፊሊፕ ማዝደን የጻፋትን አንዲት የታሪክ መጽሐፍ «መጫሚያ አልባው ንጉሥ» በሚል ተርጉሟ ለንባብ አብቅታለች።
ሸዋዬ ለገሰ ከወጣትነት ጀምሮ ለጋዜጠኝነት ታላቅ ፍቅር ያሳደረች በመሆኑ ያ ጽኑ ፍቅር ዛሬም መኖሩን ታምናለች፡፡ በሳል እና አርቆ አሳቦ ጋዜጠኛ መሆኗንም በቅርበት የሚያውቋት ይመሰክሩላታል፡፡ የወይ አዲስ አበባ የሬድዮ ፕሮግራም አዘጋጅ የሆነው ነቢዩ ግርማ የሸዋዬ ለገሰን ቡድን የመምራት ክህሎትን ያደንቃል፡፡ እንደ ነቢዩ አባባል ሸዋዬ ጥሩ የመግባባት ክህሎት የተላበሰች በመሆኑ አብረዋት ከተመደቡ ጋዜጠኞች ጋር በፍቅር ለመስራት አይቸግራትም ሲል ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡ የአሃዱ ሬድዮው ጥበቡ በለጠ ደግሞ ሸዋዬ በስነ-ጽሁፍ ትምህርት ጎበዝ ነበረች፡፡ ይህም አሁን ላለችበት ስራ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብሎ ጥበቡ ያምናል፡፡ በአሁን ሰአት ሸዋዬ ዶቸ ቨለ ላይ የምትሰራቸው መሰናዶዎች የቋንቋ ብስለት የታየባቸው ናቸው ሲልም ጥበቡ ያክላል፡፡
በስነጥበብ ብሎም በግጥም እና ዜማ ድርሰት የሚታወቀው ተስፋዬ ድረሴ ሸዋዬን የሚያውቃት የዛሬ 22 አመት ፋና ትሰራ በነበረበት ጊዜ ነው፡፡ በጊዜው ሬድ ባርና ይሰራ የነበረው ተስፋዬ በሸዋዬ ኢንተርቪው የመደረግ እድል ገጥሞት ነበር፡፡ ተስፋዬ ያኔ ሸዋዬ ለሙያዋ ታሳየው የነበረውን መሰጠት እና ትጋት ያስተውል ነበር፡፡ በተለይ አዲሱ ትውልድ ወደፊት በእንዴት ያለ መልኩ መገንባት አለበት? በሚለው ዙርያ ሸዋዬ አየር ላይ ያዋለቻቸው ፕሮግራሞች ቁምነገር የተላበሱና የተለፋባቸው እንደነበሩ ተስፋዬ ያስታውሳል፡፡ የህጻናት መብቶች ላይ በተደጋጋሚ ፕሮግራም ትሰራ የነበረችው ጋዜጠኛ ሸዋዬ በዚህ ጥረቷ ያኔም አሁንም አድንቃታለሁ ብሏል ተስፋዬ፡፡
ጋዜጠኛ ሸዋዬ የሚድያ ስራ ሀ ብላ ከጀመረች አዲሱ 2015 ላይ 30 አመት ይሞላታል፡፡ ይህች በጋዜጠኝነት ችሎታዋና ፤ በተለይም በቋንቋ አጠቃቀሟ የተመሰከረላት የሚድያ ሰው ዛሬም በጀርመን ድምጽ ለሌሎች ማስተማርያ የሚሆኑ መሰናዶዎችን አየር ላይ ታውላለች፡፡ የእነዚህን መሰናዶዎች ሊንክ ከዚህ ግለ-ታሪኳ ጋር አንድ ላይ የምናስቀምጥ ሲሆን ያደመጠ ስራዋን አይቶ መመስከር ይችላል፡፡ ተወዳጅ ሚድያም የሰራ አደባባይ ላይ ወጥቶ ለሌሎች መነሳሳት ይፍጠር የሚለውን መርህ ያነገበ ስለሆነ ሸዋዬም ከእነዚህ አሻራ ያኖሩ ሰዎች ተርታ የምትመደብ ነች፡፡ በ1980ዎቹ አጋማሽ ስራ ጀምረው ዛሬ ድረስ በጽናት ከቀጠሉት የማትዘነጋው ሸዋዬ ለገሰ የህይወት ታሪኳ ሲቀርብ ከላይ የተከተበውን ይመስላል፡፡
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ