እታገኝ በቀለ

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያ ሥራ ውስጥ የጎላ ሚና የነበራቸውን ባለሙያዎች የህይወት ታሪክ በመሰነድ ለታሪክ እያስቀመጠ ይገኛል፡፡ ሬድዮ ሲነሳ የቴክኒክ ዘርፍ ባለሙያዎች ፤ የማሰራጫ ጣቢያ ትጉሀን ባለሙያዎች ሚናቸው ጉልህ ከጋዜጠኛው እኩል በሚባል ደረጃ ለስራው መሳካት አስታዋጽኦ ማበርከታቸው ይታወሳል፡፡ በመሆኑም መዝገበ አእምሮ ላይ የቲቪ እና የሬድዮ የቴክኒክ ባለሙያዎች ከጋዜጠኛው ታሪክ ጎን ለጎን እያወጣን እንገኛለን፡፡ ከዚህ ቀደም መዝገበ-አእምሮ ቅዳሜ ሀምሌ 30 2014 ታትሞ መመረቁ ይታወቃል፡፡ በቀጣይ መዝገበ-አእምሮ ቁጥር 2 ላይ ታሪካቸው ከሚሰነድላቸው ባለሙያዎች አንዷ እታገኝ በቀለ ትጠቀሳለች፡፡ እታገኝ ባለፉት 28 አመታት በቴክኒሻንነትና በአርካይቭ ባለሙያነት ያገለገለች  ሲሆን ታሪኳም ለአዲስ ባለሙያዎች አስፈላጊ ሆኖ ስላገኘው ሰንደነዋል፡፡ እዝራ እጅጉ የህይወት ታሪኳን እንደሚከተለው አሰናድቶታል፡፡

 

 

 እታገኝ በቀለ እናቷ ወይዘሮ አስካለ በየነ አባቷ ደግሞ አቶ ቢራቱ ሂርጶ ይባላሉ፡፡ የተወለደችው ሰሜን ሸዋ ሰላሌ ፌቼ ገንደጉዳ ቀበሌ ልዩ ስሙ ላንገኖ በሚባል አካባቢ በ1964ዓ.ም ነው። እስከ አምስት አመቷ እዛው በተወለደችበት አካባቢ ከቆየች በኋላ በአክስቷ ወይዘሮ ወይንሸት ገመዳ አማካይነት ወደ አዲስ አበባ ልትመጣ ችላለች:: አዲስ አበባ ከመጣች በኋላ የአባቷ መጠሪያ የአጎቷ በቀለ ደሙስም ሆኗል።

 እታገኝ  ስለልጅነት ጊዜዋ ስታወሳ ‹‹…..ያደኩበት አካባቢ ጉለሌ ከእንቁላል ፋብሪካ ከፍ ብሎ የሚገኝ ሰፈር እና ከመድሃኔ ዓለም አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀርባ ያለ አካባቢ ነው። እንደማንኛውም ልጆች የልጅነት ጊዜዬን ከእድሜ እኩዮቼ ጋር ደስ በሚል ሁኔታ አሳልፌያለሁ። በአካባቢው የነበሩ ጎረቤቶቻችን እንዲሁም የቅርብ ዘመዶቼ ከአሳዳጊ አክስቴ በተጨማሪ እንደእናት ተንከባክበው በፍቅር አሳድገውኛል።.›› ትላለች፡፡

 እታገኝ እድሜዋ  ለትምህርት ሲደርስ ከ0 እስከ 6ተኛ ከፍል ኢትዮጵያ እድገት የህዝብ ትምህርት ቤት የተማረች ሲሆን 7ኛ ክፍል እና 8ኛ ክፍል ቀለመወርቅ ትምህርት ቤት ከዘጠነኛ ክፍል እስከ 12 ክፍል  ደግሞ  መድሃኒ ዓለም አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምራለች። በመቀጠልም በኤሌክትሮኒክስ ዲፕሎማ እና በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ወይም በአይቲ በዲፕሎማ ተመርቃለች።

የትዳር ሁኔታን በተመለከተ እታገኝ ከአቶ አበራ ሀይሉ ጋር በ1985 አ.ም ትዳር የመሰረተች ሲሆን አንድ ወንድ እና ሁለት ሴት ልጆችን አፍርታለች።

 ህዳር 12 1987ዓ.ም ሬድዮ ፋና ሲመሰረት በቴክኒክ ዘርፍ ከሥራ ባልደረቦቿ ጋር ስልጠና ከወሰደች በኋላ ስራ ጀምራለች። ጣቢያው ያኔ ሲጠቀምበት የነበረው ማኑዋል የመቅረጫና የማሰራጫ ስቱዲዮ ሲስተም ሲሆን ትእግስት የሚጠይቅና ረዥም ጊዜ የሚወስድ ነበር። የቴክኒሻኑ ኃላፊነት ከድምፅ ጥራት መቆጣጠርና መቅረፅ ባሻገርም የቃላት ግድፈቶችን የማረምም ግዴታና ኃላፊነት ነበረበት። ለምሳሌ ጋዜጠኛው እስክሪፕት በሚያነብበት ጊዜ በጥሞና መከታተልና የቃላት ብሎም የሃሳብ ግድፈት ማረም የቴክኒሻኑ ኃላፊነት ነው የነበረው። ይህ አሰራር በርካታ የስራ ጊዜ ከማባከኑ በተጨማሪ በቴክኒሻንና በጋዜጠኛ መካከል ጭቅጭቅና አለመግባባት የሚፈጥር ከፍተኛ የሆነ ችግር እንደነበረ የማትረሳው የዘወትር ትውስታዋ ነው።

 እታገኝ መለስ ብላ ወደኋላ ስለነበረው አሰራር ስታስረዳ ‹‹….የቴፕ ማሽን መሰረት ያደረገ የስቱዲዬ የማንዋል አሰራር ከ10 ዓመት በላይ ከሰራንበት በኋላ ተቋሙ የቀየሰውን  የቴክኖሎጂ ለውጥ አካል ማጥናት እና መተግበር ነበረብን፡፡ ዲጂሚዲያ የሚባል አዲስ የስቱዲዮ ቀረፃና ኤዲቲንግ አውቶሜሽን ቴክኖሎጂ ሲስተም መጠቀም ሲጀመር ጋዜጠኛው እራሱን ችሎ ያነበበውንና የቀረፀውን እስክሪፕት ኤዲት ማድረግ ሲጀምር ቴክኒሻኑ ላይ የነበረው ጫና በከፍተኛ ደረጃ ቀንሶለታል። ከላይ የተገለፀው ችግር በዚሁ ሶፍትዌር ሲፈታ ሌላው የቴክኒሻኑ አዳጋች አሰራር የቀጥታ የሬዲዮ ውይይት የጀመረበት ወቅት ነበር። የሬድዮ ፋና የማይረሱ የቀጥታ ስርጭቶች መካከል ቴሌኮንፈረንስ፣ እርስዎ ቢሆኑ ምን ያደርጋሉ? የሚሉና ሌሎች ተወዳጅ የነበሩ የጣቢያው የቀጥታ ውይይቶችን እንድንመራ ከተመረጥነው ቴክኒሻኖች አንዷ ነበርኩ። በዚሁ ወቅት የነበሩ ፈታኝ ጊዜያት ወደኋላ ተመልሼ ሳስታውስ ልዩ ትዝታና ደስታ ይፈጥርብኛል።›› ትላለች እታገኝ ወደ ኋላ መለስ ብላ ስታስታውስ ፡፡

  እታገኝ በቀለ በአጠቃላይ በቴክኒክ ዘርፍ ከ1987 እስከ 2003 ዓ.ም ድረስ በቴክኒሻንነት አገልግላለች። ተቋሙ ከ2003 ጀምሮ አዲስ የሚዲያ ኮምሌክስ በመገንባት በዓይነቱ ለየት ያለ ብሎም ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የሬዲዮ አውቶሜሽን ሲስተም ተግባር ላይ ያዋለበት ጊዜ ነበር። ይህም ማለት አጠቃላይ የስቱዲዮ አሰራርን ዲጅታይዝ በማድረግ የቀረፃ፣ የኤዲቲንግ፣ የአርካይቭና የስርጭት አሰራሩን በመሰረቱ የቀየረ ሲስተም ነበር። ሲስተሙ ኔሽያ የሚባል የፈረንሳይ አገር አውቶሜሽን ሲስተም ሶፍትዌር  ሲሆን በዓለም አቀፍ ታዋቂ  ከሚባሉት ጥቂት የሬዲዮ የአውቶሜሽን ሲስተም አንዱ  ነበር  ። ሬድዮ ፋና ቀድሞ ይጠቀምበት የነበረው የአናሎግ አሰራር ወደ ዲጅታል ቴክኖሎጂ ሲስተም ሲቀይር እና ዲጂታል አርካይቭ ክፍል ሲቋቋም እታገኝ ወደ ክፍሉ በእድገትና ኃላፊነት ተዛውራ ከ1981ዓ.ም ጀምሮ በሪል እና በካሴት የነበሩ በርካታ ዶክመንቶች እንዲሁም ሙዚቃዎችን ወደዲጂታል ሲስተም እንዲቀየሩ በባለሙያነት በኃላፊነት ደረጃም የበኩሏን አስተዋፅኦ አድርጋለች።

 እታገኝ በቀለ ሬድዬ ፋናን ከመሰረቱት ጠንካራ ባለሙያዎች  አንዷ ስትሆን ተቋሙ አስረኛ ዓመቱን ሲያከብር ምስጉን ሰራተኛ ተብላ ሬድዬ ተሸልማለች። በወቅቱ ትልቅ ስጦታ ነበር። ሽልማቱ ሲሰጣትም በጣም ደስተኛ ነበረች።

በአሁኑ ወቅት የተቋሙ ሬዲዮ አርካይቭ ዋና የካታሎግ ባለሞያ ሆና እየሰራች የምትገኝ ሲሆን በስራዋና በቤተሰቧ  በጣም ደስተኛ ነች።

 

          ስለ እታገኝ በቀለ የተሰጠ ምስክርነት

ስሜ ደሜ አበራ ይባላል፡፡ የእታገኝ በቀለ  የመጀመሪያ ልጅ ነኝ:: ሀና አበራ እና ሜቲ አበራ የሚባሉ ሁለት ታናሽ እህቶችን አሉኝ:: እናቴ እኔን ስትወልድ በጣም ወጣት ነበረች::  በዚያን ጊዜ ሬድዮ ፋና ቴክኒሻን ሆና ትሰራ ነበረ::  ከልጅነቴ ጀምሮ አድጌ ዩኒቨርስቲ እስክገባ ድረስ ከእርሷ ጋር በጣም ቅርብ ግንኙነት ነበረን:: ቅርርባችን ከእናትነትና ከልጅነት አልፎ እንደ ጓደኛና እንደ ትልቅ ሰው  ነበር የምታየኝ:: እናቴ  በጥሩ ዲሲፕሊን ስላሳደገችን ዛሬ ላይ በራሴ የምተማመን እና ጠንካራ ሰራተኛ እንድሆን አግዞኛል:: ልጅ ሳለሁ የእታግ የሥራ ሰአት ከእኛ ጋራ ጊዜ ለማሳለፍ አይመችም ነበር:: አንዳንዴ ከሌሊቱ 11 ሰአት ከቤት መውጣት ይኖርባታል፡፡  ካልሆነ ደግሞ የማታ ሺፍት ሰርታ እኩለ- ሌሊት ነበር ወደ ቤት የምትገባው፡፡ አብዛኛውን የበዓል ቀናቶች በሥራ ላይ ነበር ታሳልፍ የነበረው፡፡ እኔና እህቶቼን  ከመንከባከብ ባሻገር በሥራዋ ላይ እንከን እንዳይፈጠር የተቻላትን  ታደርግ እንደ ነበር አስታውሳለሁ፡፡ የተረጋጋች እና ሁሉንም ነገር በቅንነት ነበር  የምታየው፡፡ እንደ ልጅ ጠዋት ከእንቅልፌ  ስነሳና እቤት ሳገኛት በጣም ደስ ይለኝ ነበር፡፡ የቴክኒሺያንነት ሥራዋ ያስደስተኝ ነበር፡፡ አንዳንዴ ፋና ሬድዮ ከፍቼ ሳዳምጥ በቴክኒኩ እታገኝ በቀለ አብራን ነበረች ሲል ጋዜጠኛው በጣም ነበር የሚያስደስተኝ፡፡ ትዝ የሚለኝ ትምህርት በሌለኝ ቀን ከእርሷ ጋር ቀኔን ለማሳለፍ ካለኝ ጉጉት የተነሳ ሥራ ቦታ አብሬያት ሄጄ ስጫወት እውላለሁ:: የልጅነት ትውስታዬ እርሷ ስትሰራ እኔም እሰራለሁ ብዬ ወደ ስቱዲዮ የሚመጡትን ጋዜጠኞች አነጋግር ነበር:: እርሷ የምትሰራውን ሥራ አይና እኔም እራሴን ቴክኒሻን ደሜ አበራ ብዬ እጠራለሁ ወይም ጋዜጠኞቹን ጥሩ ብዬ እንደነበር አስታውሳለሁ  አይ ልጅነት! በወቅቱ እዛ የነበሩ የፋና ሰራተኖች ጥቂት ሲሆኑ ሁሉም እንደቤተሰብ ስለሚተያይ በዓላት ሲኖሩ አብዛኛው ሰራተኛ ልጆቹን ይዞ ስለሚመጣ በጋራ እንጫወት ነበር፡፡ በእርግጠኝነት መናገር የምችለው በዛን ጊዜ ፋና  የነበሩ ባለሙያዎች ሁሉም ያውቁኛል:: እናቴ ለኔ እዚህ መድረስ ትልቁን ሚና ተጫውታለች :: እታግዬ ሁሌም እወድሻለሁ የኔ ቅን ደግ አሳቢ እናቴ ረዥም እድሜና ጤና ሁሌም አመኝላታለሁ::  ተወዳጅ ሚድያም የእናቴን የሚድያ አስተዋጽኦ ግምት ውስጥ በማስገባት የህይወት ታሪኳን ለመስራት በመነሳሳቱ አድናቆቴን ልቸረው እፈልጋለሁ፡፡

    ደሜ አበራ የእታገኝ ልጅ

ሙሉጌታ መሀሪ ነኝ፡፡ ፋና ሬድዮ ላይ የአይሲቲ ኃላፊ በነበርኩበት ሰአት እታገኝ በሙያዋ ላይ ታሳይ የነበረውን ጥረት አይቻለሁ፡፡ በተለይ ከሁሉም ጋር የነበራት  መልካም የስራ ግንኙነት  በብዙዎች የሚመሰከር ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ቴክኒሻን ማለት ለአየሩ ትልቅ ሃላፊነት የሚወስድ ጥንቁቅ ባለሙያ እንደመሆኑ መጠን እታገኝም ጠንቃቃነቷን እዚህ ጋር በጥሩ ሁኔታ መመስከር ይቻላል፡፡ እታገኝ ከቴክኒሻን የስራ መደብ ወደ ዲጂታል አርካይቭ ባለሙያነት ሽግግር ስታደርግ ጠንቃቃነቷና የሙያ ፍቅሯ በብዙዎች የተደነቀ ነበር፡፡ እታገኝ ነባር የፋና ባለሙያ እንደመሆኗ ለመስርያ ቤቷ ያላት ፍቅር ለአዲስ ገቢዎች አርአያ የሚሆን ነበር፡፡ አዲስ ገቢዎችንም ስራን በማልመድና ቀለል ብሏቸው እንዲሰሩ በማድረግ እታገኝ ትልቅ አደራ ተወጥታለች፡፡ በዚህም ምንጊዜም ምስጋናዬን ልቸራት እወዳለሁ፡፡ 

 ሙሉጌታ መሀሪ የፋና የስልጠና ማእከል የስራ መሪ

 

ጸሀይ አባቡ እባላለሁ ፡፡ እታገኝን ከልጅነት ጀምሮ አውቃታለሁ፡፡እታገኝ ሰው ትወዳለች፡፡ ለቤተሰቧም የተለየ ፍቅርና አክብሮት አላት፡፡ለሙያዋ ያላት ፍቅርና አክብሮት ለብዙዎች አርአያ የሚያደርጋት ነው፡፡ ለልጆቿም መልካም እና ስራዋንም በትጋት የምትሰራ ናት፡፡   

መዝጊያ ሀሳብ ፤ ሁልጊዜም የሚድያ ሰዎች ሲነሱ ቴክኒሻኖች በክብር መነሳት አለባቸው፡፡ በተለይ እንደ እታገኝ አይነት በትጋታቸው የተመሰከረላቸው ባለሙያዎች ብዙ ልምድ ያካበቱ በመሆኑ ብዙ ታሪክ አላቸው፡፡ ጋዜጠኛው ብቻውን ምንም አልሰራም-ከቴክኒሻኖች ጋር እንጂ፡፡ እንደ እታገኝ አይነቶቹ ደግሞ በብዙዎች የተከበሩ ዛሬም በትኩስ የስራ መንፈስ የተሰጣቸው ሀገራዊ አደራ እየተወጡ ይገኛል፡፡ የሰራ ደግሞ ተደብቆ አይቀርም መዝገበ-አእምሮ ላይ ታሪኩ ይሰነዳል እንጂ፡፡













  

 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች