አስናቀች ጸጋዬ/ ከመጀመርያዎቹ የኢቲቪ የቪድዮ ኤዲተሮች አንዷ  

 

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያ ሥራ ውስጥ የጎላ ሚና የነበራቸውን ባለሙያዎች የህይወት ታሪክ በመሰነድ ለታሪክ እያስቀመጠ ይገኛል፡፡ ቲቪ ሲነሳ የቪድዮ ኤዲቲንግ ዘርፍ ባለሙያዎች ፤ የማሰራጫእና የቴክኒክ  ትጉሀን ባለሙያዎች ሚናቸው ጉልህ ነው። ከጋዜጠኛው እኩል በሚባል ደረጃ ለስራው መሳካት አስተዋጽኦ ማበርከታቸው ይታወሳል፡፡ በመሆኑም መዝገበ አእምሮ ላይ የቲቪ እና የሬድዮ እና የኤዲቲንግ ባለሙያዎችን ከጋዜጠኛው ታሪክ ጎን ለጎን እያወጣን እንገኛለን፡፡ ከዚህ ቀደም መዝገበ-አእምሮ ቅዳሜ ሀምሌ 30 2014 ታትሞ መመረቁ ይታወቃል፡፡ በቀጣይ መዝገበ-አእምሮ ቁጥር 2 ላይ ታሪካቸው ከሚሰነድላቸው ጠንካራ የቲቪ የቪድዮ ኤዲተሮች አንዷ አስናቀች ጸጋዬ ናት፡፡ አስናቀች በዚህ ሙያ ከ1974 ጀምሮ የሰራች ስትሆን አጠቃላይ በሙያው ላይ የ40 አመት ልምድ ካካበቱ ጥቂት ጉምቱ ወይም ከመጀመርያዎቹ የቲቪ የቪድዮ ኢዲተሮች አንዷ ነች፡፡ የህይወት ታሪኳ ተግተው ለሚሰሩ ባለሙያዎች የሚጠቅም  ሆኖ ስላገኘነው ትውልድ እንዲያነበው ስንል ሰንደን አስቀምጠነዋል፡፡ ታሪኩን እዝራ እጅጉ እንደሚከተለው ያቀርበዋል፡፡

 

አስናቀች ፀጋዬ ነሲቡ  1953 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ በጉለሌ ወረዳ ተወለደች፡፡ ትምህርቷን በእቴጌ መነን እና በተፈሪ መኮንን ተምራ አካውንቲንግ ተመረቀች፡፡ 1971 ዓም አቡነ ጴጥሮስ በሚገኘው የሬድዮና  ዜና አገልግሎት ግቢ  በማስታወቂያ ሚኒስቴር ሂሳብ ክፍል ተመደበች

በተፈጥሮዋ ፈጣን እና ቀልጣፋ ስለሆነች በስራዋ ተመራጭ እና ተወዳጅ ሆነች፡፡ጋዜጠኞችም ለደሞዝ እና ለአበል ሲመጡ ሁኔታዋን ሲያዩ ‹‹ይህቺ በጣም ፈጣን ናት፡፡ የቪድዮ ኤዲተር ብትሆን ጥሩ ነው፡፡ ለምን ኢቲቪ ቅያሬ አትጠይቂም?›› በሚል ከተለያዩ የኢቲቪ ሰራተኞች እና ኃላፊዎች አስተያየት ይቀርብላት ነበር። 

ጋዜጠኞች ለዜናና ለበአል ዝግጅት መሳሪያችውን ይዘው ለዘገባ የሚያደርጉትን  እሩጫ አስናቀች  ስታይ እንደእነርሱ መሆንን ትመኝ ነበር፡፡ እና ለመሞከር ወሰነች፡፡ በጊዜው ኢቲቪ መምሪያ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ስለ ነበር ለቢሮዋም ቅርብ በመሆኑ ብቅ ጥልቅ እያለች ዝውውር ጥያቄዬን አቀረብኩ፡፡ ጥያቄዬም ተቀባይነት አግኝቶ  በ1974 ዓ.ም መጋቢት ወር ወደ ኢቲቪ ተቀየርኩ።

በወቅቱ ኢቲቪ በቪድዮ ኤዲተርነት  ሴቶች እንዲመደቡ  ይፈልግ  ነበር፡፡ ምክንያቱም ሴቶች ትእግስተኞች እና ቀልጣፋ ጣቶች አላቸው የሚል እምነት ስለነበር ነው፡፡  አስናቀች ኢቲቪ ስራ በጀመረችብት ወቅት 3 ሴት  ቪድዮ ኤዲተሮች ነበሩ፡፡ እነርሱም  ፍቅርተ ወልደየስ፣ መፍቱሀ በድሪ እና አሁን በህይወት የሌለችው ጥሩወርቅ አዛርያ ትጠቀሳለች፡፡ በጊዜው የነበሩት እነዚህ ኤዲተሮች  የሚሰሩት እርስ በርስ በመማማር እና በግል ጥረት ስለነበረ አስናቀችም የሚሰሩትን እያየች እውቀት ለመቃረም ታደርግ የነበረውን ጥረት ቀጠለች፡፡ በወቅቱ ኢቲቪ ስርጭት ጥቁርና ነጭ 16ሚሊሜትር ፊልም ነበር edit ሲደረግ ደግሞ በነጌቲቭ ፊልም ስለነበር መሳቅ እና ማልቀስን መለየት እንኳን ከባድ ነበር፡፡ ሆኖም አስናቀች  ስራ በጀመረች በሳምንቱ የስምንት ደቂቃ በመሰረተ- ትምህርት ላይ ያተኮረ ስራ ሰራች፡፡ ከያቅጣጫው የሚባል ሳምንታዊ ፕሮግራም ነበር፡፡ በሱላይ ተላለፈ፡፡ ስሟም በአቀናባሪነት ተነገረ፡፡ በተዛወረች በሳምንቷ ሰርታ በመተላለፉ አድናቆትን አተረፈች፡፡ ይህም በሙያው ላይ ጠንክራ ትበረታ ዘንድ በር ከፈተላት፡፡

በጊዜው እነ አስናቀች ይሰሩበት የነበረው የፊልም ማቀናበሪያ መሳሪያ STEENBECKይባላል፡፡                        ፊልም እየቆረጡ የሚቀጣጥሉበት Splicer  ይባል ነበር፡፡ በወቅቱ ስራው በጣም አድካሚ በመሆኑ የሚሰራው በፈረቃ ነበር፡፡ አስናቀች ግን  ስራውን በጣም ስለወደደችው በእረፍት ቀኗም የምትሰራው ነገር ስለሌለ እየገባች ሙያዊ ፍቅሯን ትወጣ ነበር፡፡ በዚህም አስናቀች ተመራጭ የቪድዮ ኤዲተር ለመሆን በቃች፡፡

በ1976 ከጀርመን ሀገር ከ Friederec Evert Foundation ከኬንያ  ፊልም ትምህርት ቤት ጋር በመተባበር የመጡ መምህራን   ለአንድ ወር  ያዘጋጁት ስልጠና ላይ ተሳተፈች፡፡ ይህም ስልጠና ፊልም ኤዲቲንግ ፤ ድምጽ እና የፊልም ላቦታቶሪ ስልጠናን ያካትት ነበር፡፡ አስናቀችም  በ1ኛነትም  ስልጠናውን  አጠናቀቀች፡፡ ለሙያዋ ትልቅ መሰረት የጣለላትን እውቀት አግኝታበት  በኤዲተርነት ለቀጣይ ስልጠና ተመረጠች።

 አስናቀች በቀጣዩ አመት ስላገኘችው ስልጠና ስታስረዳ ‹‹…..በ1977አ.ም  ከላይ በተገለፀው ድርጅት እስፖንሰርነት Kenya Mass Communication ፊልም በቡድን ስለሚሰራ ኤዲተር እና ላብራቶሪ ቴክኒሽያን ከ ETV አዘጋጅ ካሜራ አና ድምጽ ሶስት ሰልጣኝ ከ Mass media አምስት ሰልጣኞኝ ለሁለት ዓመት ለትምህርት ሄድን፡፡በስልጠናችን ወቅት ከኬንያ ከዚንባቡዌ እና ከታንዛንያ የመጡ ስለነበሩ ተደባልቀን በአንድ ካምፓስ በጥሩ አያያዝ ስልጠናውን ቀጠልን፡፡  ስልጠናው የተግባርና የንድፈ-ሀሳብ ነበር፡፡ በዚህም ሁላችንም በርትተን በመስራት ከ1 ሰልጣኝ በቀር በማእረግ  በአንደኛነት አጠናቀቅን፡፡ በቆይታዬም በኬኒያ ለኢትዮጵያ ኤንባሲ በሙያዬ አስተዋጽኦ አድርጌያለሁ፡፡ ኤምባሲያችንም በውጤታቸን በመደሰት የሽኝት ግብዣ ከኛጋር የሰለጠኑ ተማሪዎችንም  በመጨመር  አዘጋጅቶልን ነበር፡፡ በ 1979 ዓ.ም ጥቅምት ወር ላይ ሀገራችን ተመልሰናል።›› በማለት ተናግራ ነበር፡፡    

ከስልጠና ስትመለስ  ኢቲቪ ወደቀለም ሪቨርሳል ፊልም ተቀይሮ ነበር፡፡ በVHS ካሴት መስራትም እየተጀመረ ነበር፡፡ ከተመለሰች በኋላ ከበፊቱ  የበለጠ መስራቷን ቀጠለች፡፡  በተጨማሪም ከጣቢያው መደበኛ ስራ ባሻገር ከETV ጋር በትብብር የሚሰሩ ስራዎችን ሁሉ  እንድትሰራ ትታዘዝ ነበር፡፡ አስናቀችም ሙያዊ በልባዊ መሰጠት ትወደው ስለነበር በደስታ ስራዎችን ተቀብላ ትሰራ ነበር፡፡

በ 1980 ለ13ኛ ዓመት የአብዮት በአል በተለያዩ ርእሶች የተዘጋጁ  የዶኪመንተሪ ጽሁፎች አቀናብራ ከፍተኛ ከበሬታን አግኝታ ነበር፡፡ በዚህ ጥረቷም ሽመልስ ማዘንጊያ የኢሕድሪ የፕሮፓጋንዳ ባህል ኮሚቴ ሰብሳቢ የተፈረመ የምስጋና ሰርተፊኬት ማግኘት ችላለች፡፡

 በ1981 ደግሞ  ለ13ኛው የአለም ወጣቶችና ተማሪዎች ፌስቲቫል ዝግጅት ላይ የሚቀርብ ዘጋቢ ፊልም   በርካታ ካሴቶችን በመጠቀም ከሁለት ወር በላይ  የፈጀ ዶኪመንተሪ ሰራች፡፡ ለዚህም የላቀ አስተዋጽኦዋ በተመሳሳይ መልኩ የምስክር ወረቀት ማግኘት ችላለች፡፡

በዚሁ ዓመት በ ETV የሚቀርብ “እርስዎም ይሞክሩት” በሚል ርእስ በጋዜጠኛ ሚሊዬን ተረፈ እና በጋዜጠኛ መለሰ አወቀ የሚዘጋጅ ሳምንታዊ የጥያቄና መልስ  ውድድር በተከታታይ ለበርካታ ሳምንታት ኤዲት በማድረጓ በጣም ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚል የምስክር ወረቀት እና 300 ብር ሸልማት ማግኘት ችላለች፡፡

ኬንያዊው እውቁ ካሜራማን እና ፎቶግራፈር ጋዜጠኛ መሀመድ አሚን የንጉሳዊ ቤተሰብ ከእስር ሲፈቱ ከተገኙ ጋዜጠኞች መሀከል ስለነበረ እድል ገጥሟት የእርሱን ስራ አቀናብራለች፡፡

በተለያዩ ጊዜ በቀድሞ አፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁን አፍሪካ ህብረት  ሰብሰባ ለመሳተፍ  መሪዎችን ተከትለው የሚመጡ እንደ ግብጽ ኬንያ እና CNN ላይ የሚሰሩ ጋዜጠኞች ሀገራቸው እስከሚመለሱ ዜናሪፓርቱ እንዳያረጅ  ETV እየመጡ ስለሚሰሩ አስናቀች ጋር ይመደቡ ነበር፡፡ አስናቀችም ኤዲት አድርጋ እስቱዲዮ ገብታ አየር ላይ እስኪውል ድረስ እየረዳቻቸው አብራ ትሰራለች።

የተለያዩ ድምጻውያን የተሳተፉበት በዳይሬክተር አባተ መኩሪያ የተዘጋጀ የመጀመርያው  የሙዚቃ ቪዲዮ “ድንቡልቃ” በሚል ርእስ የሙዚቃ ቪዲዮ  ቅንብር ሰርታለች

ከ ሲኒማቶግራፈር ታፈሰ ጃራ ጋር የ CMC ቤቶች ግንባታ እና በ UNDP Program  ለመንግስት ሰራተኞች የመኖሪያ  ቤቶች አፓርታማ ግንባታ የስራ ሂደት የሚያሳይ Documentary Film አቀናብራለች፡፡

በድርቅ ምከንያት ዜጎችን ወደ ለም ቦታ ለማዘዋወር ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ተሳትፎ ጭምር የሚሰሩ የመኖሪያ መንደር ምስረታ ሂደትን እና የሰፋሪዎቹን አኗኗር የሚያሳይ Documentary Film በጋዜጠኛ መሀመድ ኢድሪስ አዘጋጅነት ኤዲት በማድረግ ሙያዊ ብቃቷን ማስመስከር ችላለች፡፡

” ንጋት “ በሚል ርእስ ከአፄ ኃይለስላሴ እስከ ደርግ ከደርግ እስከ ኢህአዴግ ያለውን የለውጥ ሂደት የሚያሳይ Documentary ከ ጋዜጠኛ እሸቴ አሰፋ እና ከሀብታሙ በቀለ ጋር ከክምችት ክፍል በተውጣጣ ቪዲዮ ተከታታይ  4 ክፍል ዘጋቢ ፊልም ሰርታለች፡፡

በኢቲቪ  ቋንቋዎች ስርጭት ሲጀመር ለኦሮምኛ እና ለትግርኛ የተቀጠሩ አዘጋጆች ስልጠና እንድታዘጋጅ በታዘዘችው መሰረት ስልጠናውን አዘጋጀች፡፡

 አስናቀች ስለስልጠናው ስታስታውስ ‹‹ እኔም ቀደም ሲል ኢቲቪ  ቼኮዝላቫኪያ ጀርመን እና ኬንያ  እየላከ ያስተማራቸውን ባለሙያዎች በማስተባበር  የ1 ወር  ስልጠና በማዘጋጀት መሰረታዊ የሆነ የፕሮዳክሽን አሰራርን አስጨበጥናቸው ።እነርሱም በስልጠናው ተጠቅመው  ከሰሩት ፕሮግራም ውስጥ ተወዳጅ የነበረው በኦሮምኛ  “ደንጋ”  የመዝናኛ ፕሮግራም እነሳሙኤል ዳባ ሰመኝ ቴሶ የሚያቀርቡት አለሙ ቶሎሳ የሚመራው በትግርኛ  “ ቀዳምሳና” በሚል የመዝናኛ ፕሮግራም አድናቆትን ያተረፈ ስራ ነበር።››  ትላለች፡፡ 

 አሁንም አስናቀች ትዝታዋን ቀጠለች ‹‹ በ1992 በአውሮፓ አቆጣጠር ከKenya Institute of Mass Communication በተመቻቸልኝ መሰረት በጀርመን ሀገር በተዘጋጀ International Agriculture Film Production Development Festival በርሊን ጀርመን ከተለያየ ሀገር ከመጡ የፊልም ባለሙያዎች ጋር ተጋብዤ የቀረበውን ፊልም ለመገምገም በዳኝነት ተሳትፌያለሁ፡፡ በፌስቲቫሉ የተገኘነው በሙሉ የየሀገራችን ባንዲራ ተውለብልቧል፡፡ በወቅቱ  ባንዲራ ማውለብለብ ማለት ትልቅ ነገር ስለነበረ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኝ ነበር።በዚሁም ፌስቲቫል ላይ በቆይታዬ ከካሜሩን, ከጋና ከኬንያ, ከናይጄሪያ   እኔ ከኢትዮጲያ ሆነን ሴት ጋዜጠኞች ተሰባስበን መክረን ተማክረን  AFRICAN WOMEN FILM AND VIDEO ASSOCIATION በሚል Munich, Germany የመመስረቻ መዋጮ ከየኪሳችን 30 ዶላር ከፍለን መሰረትን።  ሁላችንም በየሀገራችን ቅርንጫፍ ለማቋቋም ተስማምተን ተለያየን፡፡እኔም ይሄንኑ ለመተግበር የማስታወቂያ ሚኒስቴር መፍቀድ ስለነበረበት ስጠይቅ “ምን ያስፈልጋል የጋዜጠኞች ማህበር አለ አይደለም“ በሚል ተከለከልኩ። አንድ ሁለት ጊዜ ብቻ በናይሮቢ የተለያየ ጉባኤ ተሳትፌ በስሬ ያቀፍኩት አባል ባለመኖሩ ለብቻዬ መቀጠሉ ስላልወደድኩት  ቢመሰረት ሊጠቅም ሲችል ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት አቋረጥኩት። በተረኛነቴ መደበኛ ሥራዬን በማስተባበር እና ኤዲት በማድረግ እየሰራሁ በትርፍ ቀኔ ከአርቲስት ሙላቱ አስታጥቄ ጋር“ የቅኝት መረዋ“ በሚል ርዕስ በቤተክርስቲያን ላይ ባሉ ንዋየ- ቅዱሳን ፤ የዜማ እና ያቋቋም  እንዲሁም ከደቡብ ሀገራችን የሚገኙ የትንፋሽ  የሙዚቃ መሳርያዎች ላይ የሚያደርገውን  ምርምር ቪዲዮ  አቀናብሬአለሁ።ጥቅምት 30 ቀን 1988 ዓም ከ17 አመት  አገልግሎት በኋላ  በገዛ ፍቃዴ የ ETV ድርጀትን ለቅቂያለሁ።›› ትላለች የቪድዮ ኤዲተር አስናቀች ጸጋዬ፡፡

 አስናቀች እንደ አውሮፓ አቆጣጠር NOVEMBER 1 1995 ሻላ ማስታወቂያ በኋላ ሜጋ የተባለው ድርጅት ተቀጠረች።  በኢቲቪ በአብዛኛው የምትሰራው የመንግስት የእለት ከእለት እንቅስቃሴ ላይ ያተኮረ ስለሆነ ተመሳሳይነት ስለነበረው አሰልቺ ነበር። ነገር ግን በሻላ ማስታወቂያ ድርጅት የሚሰራው የተለያዩ ማስታወቂያዎች የተለያየ የፈጠራ ስራ ላይ ያተኮረ እና ደንበኞችን በማርካት ላይ ያተኩራል፡፡ እንዲሁም በርካታ ማስታወቂያዎች በሽያጭ ሰራተኞች ይመጣ ስለነበር ከፍተኛ የስራ እንቅስቃሴ ነበር ከነጋሽ ውብሸት ወርቅአለማው የተለያዩ ድርጅቶችን ማስታወቂያ፡ ከDAN TECHNOCRAFT ፡ከአምቼ፡ ከጉና ፡ከEAST AFRICAN TRADING HOUSE፡ከETHIOPIAN AIRLINES ፡ ከአሰፋ ጎሳዬ/ የአድማስ ጋዜጣ ባለቤት /ጋር እና ሌሎች የተለያዩ ማስታወቂያዎችን ሰርታለች፡፡

እነ አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴ ኦሎምፒክ አሸንፈው ሲመለሱ ለደስታ መግለጫ የተዘጋጀ በራሪ ወረቀት በአየር ሀይል ሄሊኮብተር ላይ ሆና በአዲስ አበባ ከተማ ላይ እየተሸከረከረች  የደስታ መግለጫ በራሪ  ወረቀት የበተነችው የማትረሳው የሜጋ ማስታወቂያ ትዝታ ነው።

 አስናቀች መሥራት የማትወደው ሥራ ሰርግ ብቻ ነው፡፡ የራሷን ሰርግ እንኳን አልሰራችውም፡፡ነገር ግን የኃይሌ ገብረስላሴን ሰርግ ኤዲት አድርጋለች፡፡

 “ሰናይት” በሚል ርእስ በማንያዘዋል እንደሻው አዘጋጅነት  በሜጋ ካሜራማኖች የተነሳ ፊልም ኤዲት አድርጋለች፡፡

 በተጨማሪም፣ ETHIO ERITREA FESTIVAL ላይ ለመሳተፍ አስመራ ሄዳለች፡፡ በመጨረሻ September 1997 በገዛ ፈቃዷ፡፡ ድርጅቷን ለቅቃ ወጥታለች፡፡

በ1997 ዓ.ም መስከረም ወር ሚድሮክ ኢትዮጵያ በህዝብ ግንኙነት መምሪያ የኦዲዮ ቪዥዋል ክፍል አቋቁሞ  ስለነበር  በቪድዮ ኤዲተርነት ተቀጠረች፡፡ በድርጅቱ ውስጥ ወደ 22 የሚጠጉ እህት ድርጅቶች ስለነበሩ የእነርሱን ማስታወቂያና ፕሮሞሽናል ቪድዮ ማቀናበር ትልቁ ስራዋ ነበር፡፡ በሥራዋም ደስተኛ የነበሩት አለቆቿ December 1‚ 1998 Senior Video Editor እና Audio Visual Coordinator አድርገው አዲስ የሥራ መደብ ሰጧት፡፡ ይህም የበለጠ እንድትተጋ አደረጋት፡፡ ሚድሮክ ኢትዮጲያ በሥሩ ብዙ ድርጅቶች ስላሉት የAudio Visual ሰራተኞችን በእቅድ በማሰማራት ለማስታወቂያ ለሰነድ ለመጽሔት የሚሆኑ ተንቀሳቃሽ እና የፎቶ ሥራዎች ከየእህት ኩባንያው በሚቀርብ ጥያቄ ለቀረጻ ታሰማራለች፡፡

  አስናቀች ጸጋዬ ‹‹…….የማስታወቂያ ሥራ ላይ ፈጠራዊ ጥበብ ስለሚያስፈልገው ሁላችንም በህብረት እየተመካከርን እንሰራለን። ፕሮሞሽናል ቪዲዮውን ባብዛኛው አለቃችን ትጽፋለች፡፡ ታነባለች፡፡ እኔ ባጠቃላይ አቀናብራለሁ፡፡ በድርጅታችን ውስጥ በየሶስት ወሩ የሚታተም መጽሄት አለ፡፡  በመጽሔቱ ላይ ለሚታተም ፎቶግራፍ መምረጥ እና ማዘጋጀት የክፍላችን የስራ ድርሻ ነው፡፡ በተጨማሪም የሚተላለፉ ማስታወቂያዎችን ለስርጭት ኢቲቪ መውሰድ በትክክል መተላለፉን መከታተል ኤግዚቢሽን እና የተለያዩ EVENT ማዘጋጀት የየድርጅቶቹን የሥራ እንቅስቃሴ እየተከታተሉ በካሜራ ማስቀረት እንደሀላፊነቴ በትክክል መሸፈኑን እከታተላለሁ ሪፖርት አቀርባለሁ። October 5‚ 1998   Bat Management/የሚድሮክ አካል ድርጅት/ ለሚሰራው ዘጋቢ ፊልም ለስራው እና ለባለሙያዎቹ እገዛ በማድረጌ የምስክር ወረቀት አግኝቻለሁ።በ1992ዓም ሜድሮክ ኢትዮጲያ ኢቲቪ ጋር በመተባበር የአዲስ አመት የዘመን መለወጫ ዝግጅት አስተባባሪ ኮሚቴ በመሆን ለሰራሁበት በሚድሮክ ኢትዮጲያ ምክትል ጄነራልማኔጀር የተፈረመ የምስከር ወረቀት ተሰጠኝ።ከ FEB 11-20‚ 2000 4th ADDIS CHAMBER INTERNTIONAL TRADE FAIR ላይ ሜድሮክን በመወከል ለተሳተፍኩበት ሜድሮክ ኢትዮጲያ ምክትል ጄነራልማኔጀር የተፈረመ የምስክር ወረቀት ተሰጠኝ።ሚድሮክ እየሰራሁ ቢሮዬ መካኒሳ ነበር፡፡  በምሳ ሰአቴ አቡነ ጴጥሮስ የነበረው የMass Media ማሰልጠኛ እየተመላለስኩ ከክልል ለሚመጡ ጋዜጠኞች ስልጠና እየሰጠሁ ተመልሼ ሥራዬ እገባ ነበር።›› ብላ ነበር አስናቀች፡፡ 

  አስናቀች ጸጋዬ ሀሳቧን በመቀጠል‹‹…..ሚድሮክ በነበርኩበት ወቅት ከጓደኞቻችን ጋር ያለንን አሰባስበን ኮስሞስ ኦድዮ ቪዥዋል የተባለ የፊልም ትምህርት ቤት አቋቁመን የትምህርት ቤቱን የማስተማርያ እቅድ በማውጣት ጥቁር ሰሌዳና የማሰልጠኛ ክፍል በማዘጋጀት ማስተማሩን ሳናጣጥም ካፒታላችንን በቤት ኪራይ ጨረስነው፡፡ ተዘጋ። የሚገርመው ነገር ኮስሞስን በሼር ያቋቋምነው በወቅቱ በሙያችን የሰለጠንን ትልቅ ቦታ የነበረን ግን የንግድ ሰው ያልነበርን በመሆኑ ህልማችን በአጭር ተቀጨ።  October 27‚ 2003 ዓ∙ም ከሚድሮክ ኢትዮጲያ 7 ዓመት ቆይታ በኋላ ባለቤቴ ወደ ውጪ ሀገር ሥራ ስለተቀየረ በገዛ ፈቃዴ ሥራዬን ለቅቄያለሁ።በግሌ በትርፍ ቀኔ የምሰራበት ፀጋ ማስታወቂያ የሚባል የማስታወቂያ ድርጅት ነበረኝ፡፡ ጥሩ ሥራ ለተለያዩ ድርጅቶች እሰራ ነበር በተለይ በምሰራው ማስታወቂያ መስማት ለተሳናቸው ተደራሽ እንዲሆን የምልክት ቋንቋን እጠቀም ነበር፡፡ ሆኖም ወደውጪ ስሄድ ዘጋሁት። በማላዊ ቆይታዬ SOCIETY FOR THE ADVANCEMENT OF WOMEN  እሚባል ድርጅት ውስጥ ከ2003 እስከ 2006ዓ∙ም INFORMATION OFFICER  ሆኜ ሰራሁ፡፡ የድርጅቱን Project ከMedia ጋር አገናኝ ነበር፡፡  በተጨማሪም ድርጅቱን የሚመለከት PRINT AND DIGITAL PUBLICATION አዘጋጅ ነበር።›› ብላለች አስናቀች፡፡

  አስናቀች፣ በማላዊ ቆይታዋ ቀደም ሲል የአፋን ኦሮሞ  የሬድዬ ጋዜጠኛ ከነበረችው ቢቂልቱ ተማም ጋር ስፖንሰር አፈላልገን የኢትዮጵያ ሚሊኒየምን  በማላዊ ካፒታል ሆቴል ከ250 ሰው በላይ ፈረንጆች ሀበሾች‚ ማላዊያኖች‚ ህንዶች በተገኙበት አከበሩ። 27 ዓይነት ምግብ አዘጋጅተው የኢትዮጵያን አለባበስ አኗኗር አመጋገብ ሙዚቃ የቡና ሥነስርአት  በአካል የሚያዩበትን መድረክ ፈጥረው የሀገራችንን ታሪካዊ ቦታዎችን በፕሮጀክተር እያሳዩ እንደ አምባሳደር በመሆን አከበሩ፡፡ዜናውም በETV አስተላለፉ፡፡ ከ7 አመት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ።

 ትቀጥላለች አስናቀች ‹‹…..በ2001 የካቲት 22 ሜጋ ኪነ-ጥበባት የኤዲቲንግ የአርካይቭ እና የካሜራ ባለሙያዎች ኃላፊ በመሆን ተቀጠርኩ። ከዛም ገመና የሚባለውን የመጀመርያ የቴሌቪዥን ተከታታይ ድራማ በፓስት ፕሮዳክሽን ማናጀርነት ብሎም በፕሮዳክሽን ማናጀርነት የመጀመርያውን የድራማ ክፍል ከክፍል 1 እስከ 25 ሰራሁ፡፡ በግሌም ከአርቲስቶች እንደ ፍቃዱ ተክለማርያም፡ ከመሰረት መብራቴ፡ ሜሮን ጌትነት እና ከፕሮዳክሽን ቡድኑ ጋር አስተዋወቀኝ ከሙዚቃ አቀናባሪዎች/ኤልያስ መልካ እና ቴዲ ማክ/  የማይረሳ ስራን ሰርቻለሁ። ስራዎቹን በምንሰራበት ወቅት በጀት ማዘጋጀት ትልቁ ስራመሆኑን ተገንዝቤበታለሁ። ስራውንም ሰራን ህዳር 4 ቀን 2002 ዓም ጀምሮ ሜጋ ማስታወቂያ ድርጅት ፈረሰ። በዚህ ስራዬ ከETV ምስጋና ተችሮኛል፡፡ እኔም በውጤቱ ደስተኛ ነበርኩ።በዚሁ ዓመት አስኒ መልቲ ሚድያ የሚል ድርጅት አቋቁሜ ከኢትዮጵያ ሬድዬና ቴሌቭዥን ድርጅት ጋር በመተባበር አኩኩሉ በሚል ርእስ የህጻናት ድራማ በመጻፍ፡በማዘጋጀት እና ፕሮዲውስ በማድረግ እስከ ክፍል 22 ድረስ በሳምንት ሁለት ቀን አስተላለፍኩ። ፕሮግራሙ ብዙ ህጻናት የሚመለከቱት ነበር እንዲሁም በድራማው ላይ በትወና ለመሳተፍ ይፈልጉ ነበር፡፡ ወላጆችም በርቱ ጥሩ ነው ይሉኝ ነበር። ሆኖም አስተማማኝ ስፖንሰር በሌለበት ዝምብሎ መስራት ስለማይቻል ስራዬን የሚረዳኝ ፈለኩ፡፡ ከብዙ ውጣ ውረድ በኌላ በፀረ ሙስና መርህ ላይ ያተኮረ 10 እስክረብት አቅርቤ 8ንቱን ሲቀበሉት 2ቱን አስተያየት ሰጥተው እንዳስተካክል ተደረገ ለ10 ድራማ 100 ሺህ ብር እስፖንሰር አደረጉኝ። ሚያዝያ 28/2002 በETV1  ውል ከፈጸምኩ በኌላ ETV2 ላይ እንጂ ETV1 አንሰጥም ብለው ሀሳባቸውን ቀየሩ፡፡ ስፖንሰሮቹ የፈለጉት ETV1 ስልነበረ በወቅቱ የቴሌቪዥን ጣቢያ አማራጭ ስላልነበረ ቀና ትብብር ባለማግኘቴ የፀረ- ሙስናን የስፓንሰር ገንዘብ መልሼ ስራውን ተውኩት ድርጅቴንም ዘጋሁት።“ሰው ለሰውበሚል ርዕስ ETV ሲተላለፍ የነበረ ተከታታይ ድራማ  ለለውጥ ይሆነኛል ብዬ ተቀብዬ በምክትል ስራ አስኪያጅእነት ተቀጠርኩ።›› ትላለች አስናቀች፡፡

            እነሆ አስናቀች ታሪኳን ትተርለች፡፡

በፕሮዳክሽን በኩልም ቀደም ሲል የለመዱት አሰራር ተከትለው የሚጓዙ ከሆነ ልክ አይመጣም በሚል  በተቻለኝ መጠን ፕሮፌሽናል በሆነ መልክ እንዴት መሰራት እንዳለባቸው በተደጋጋሚ  ከፕሮዳክሽን ማናጀሩ ጋር ውይይት አድርገናል።

የኢትዮጵያ ባለሙያ ሴቶች ማህበር 2010 እስከ 2014 የቦርድ ሰብሳቢ ሆኜ አገለገልኩ፡፡ በአሁኑ ወቅት የድርጅቱ ሙሉ አባልነቴን ይዤ ቀጥያለው።

2010 ሚዲያ ማኔጅመንት ስልጠና SOL PLAATJE MEDIA LEADERSHIP INSTITUTE RHODES UNIVERSITY PORT EIZABETH SOUTH AFRICA ከዋልታ ስራአስኪያጆች ወልዱ እና ብሩክ፡ ከዛሚ ሚሚ ስብሀቱ፡ ከሸገር እሸቴ አሰፋ፡ EMWA ጥሩወርቅ፡ አመለወርቅ፡ ገነት፡ ለምለም፡ እኔ እና ሌሎችም ስማቸውን የማላስታውሳቸው ባጠቃላይ 12 ተሳታፊዎች ሆነን ሄደን ሰለጠንን። በቆይታችን የተለያዩ ጉብኝቶች አዘጋጅተውልናል።

በመንግስት ኮምዩንኬሽን ጽህፈት ቤት አዘጋጅነት የቻይናን የሚዲያ ማህበራትን ጋብዞ ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ አድርገው ስለነበረ በምላሹ 2013 የኢትዮጵያ የሚዲያ ማህበራት አመራር በጋበዙት መሰረት የመንግስት ጋዜጠኞች ማህበር ፡የግል ጋዜጠኞች ማህበር፡ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ባለሙያ ሴቶች ማህበር እና ሌሎች ሁለት የተለያዩ የሚዲያ ማህበራት ጋዜጠኞችን እንዲሁም 1 የመንግስት ተወካይ ከዜና አገልግሎት ድርጅት  በአጠቃላይ 5 ጋዜጠኞች ኢትዮጵያን ወክለን ሄድን።

በቻይና ከፍተኛ አቀባበል ተደርጎልን ባለ5 ኮከብ ሆቴል አሳረፉን፡፡ በቆይታችን CHINA RADIO INTERNATIONAL‚ CCTV‚ BEIJING OPERA‚ HANGZHOU‚ DEVELOPMENT COMMITTEE IN BEIJING ‚ CHANGSHA‚ HANGZHOU CHINA‚ GREAT WALL OF CHINA‚ MODERN VILLAGE IN CHINA‚ AGRICULTURE ያልጠቀስኳቸው በጣም ብዙ የመኪና መገጣጠሚያ፡ የልብስ ማምረቻ፡ የመዝናኛና የቱሪስት መስህብ ቦታዎችን 2 ሳምንታት ትምህርታዊ ጉብኝት አድርገን ተመልሰናል።

በጉማ ፊልም አዋርድ 4ኛው ዙር ሽልማት ላይ በኤዲቲንግ  ዘርፍ ላሸነፈ ሽልማት እንድሰጥ ጋበዙኝ፡፡ ለተሳትፎ  የጉማ ሰርተፊኬት ተበርክቶልኛል።

በግሌ ካለኝ ሀገርን የመጎብኘት ፍላጎት በሀገር ውስጥ አርባ ምንጭ፤ ነጭሳር፤  ኮንሶ፤ ጨንቻ፤ አዋሳ፤ ወላይታ፤  ዝዋይ፤ ላንጋኖ፤ አዋሽ ፓርክ፤ ፈንታሌ፤ ሶደሬ፤ ናዝሬት፤ ደብረዘይት፤ ባሌ ዲንሾ ተራራ፤ አሰላ፤ ሀረር፤ ድሬዳዋ፤ ጅግጅጋ፤ ደብረብርሀን ፤ወሎ ፤ኮምቦልቻ፤ ደሴ፤ ጎንደር፤ ባህርዳር፤ መቀሌ፤  አድዋ ፤አክሱም፤ ፊቼ ፤ሱሉልታ አምቦ፤ ወንጪ፤ ደብረብርሀን ∙∙∙∙

ከውጪ ሀገር አስመራ ፤ኬንያ ሞምባሳ፤ ታንዛንያ፤ ኪሊማንጃሮ፤ ዩጋንዳ፤ ማላዊ፤ ቦትስዋና፤ ሀራሬ፤ ከጀርመን በርሊን፤ ሙኒክ፤ ዶቼቨሌ፤ ሀምቡርግ፤ ፍራንክፈርት፤ ከአሜሪካ ኒውዮርክ፤ ቺካጎ፤ ካሊፎርኒያ፤ ሳንፍራሲስኮ፤  ሚኒሶታ፤ ሚኒያፖሊስ፤ ዲሲ፤ ኦሪገን፤ ፖርትላንድ፤ ስያትል፤ ከቻይና፤ ቤጂንግ፤ ግዋንጅዝሁ፤ ሀቫና ፤ቲያንጅን ከሳውዝ አፍሪካ፤ ጆሀንስበርግ ፖርት ኤልዛቤት ፤ስዌቶ ለመጎብኘት ችያለሁ በሀገሬም በውጪ ሀገር ጉብኝቴን የመቀጠል እና መጽሀፌን የመጨረስ እቅድ አለኝ ፡፡

አቶ ሊበን ሰይፈስላሴ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለ14 አመት የሰሩ ባለሙያ ናቸው፡፡ አስናቀችን በፊልም ላቦራቶሪ ክፍል ሲሰሩ ያውቋታል፡፡ በጊዜው አቶ ጅብሪል አባዋሪ የፕሮዳክሽን ክፍል ሃላፊ ነበሩ፡፡  አቶ ሊበን የአስናቀችን የስራ ትጋት  ብትሰራ ብትሰራ ፈጽሞ የማይደክማት ሲሉ  ይገልጹታል፡፡

‹‹ አስናቀች ልዩ ችሎታዋ ከሰው  ጋር ያላት ልዩ የመግባባት ችሎታ ነው፡፡ ስራዋንም ጥንቅቅ አድርጋ በመስራት ማንም አይደርስባትም፡፡ በ35 ሚሊ ሜትር ያሉ ፊልሞችን ኤዲት ስታደርግ ብዙዎችን ታስደንቅ ነበር፡፡ በወቅቱ ስራዎች በማኑዋል የሚሰሩ በመሆኑ አስናቀች ፊልሞች ቢበላሹ እንኳን ከቴክኒክ አንጻር  ለምን ብልሽት ገጠማቸው ለሚለው በቂ ትንታኔ የመስጠት አቅም ያላት ናት፡፡ በዚህም አድናቆቴን ቸራታለሁ፡፡ ዛሬ ድረስ ለሙያው ያላትን የተለየ ተሰጥኦ ሁላችንም እናደንቀዋለን፡፡›› በማለት አቶ  ሊበን ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡

 የዜና ክፍል ባልደረባ በመሆን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ያገለገሉ ጋዜጠኛ ታዮ በላቸው በበኩላቸው አስናቀች ስራዎችን በፍጥነት በማድረስ የተመሰከረላት ብርቱ ባለሙያ ነች ሲሉ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡  

 

 


















 

                                     

 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች