ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ወየሳ   

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያው ዘርፍ አንዳች አሻራ ያኖሩ ሰዎችን ለታሪክ እያስቀመጠ ይገኛል፡፡ ከዚህ ቀደም መዝገበ-አእምሮ በሚል በጠንካራ ሽፋን የተሰናዳ መጽሀፍ ታትሞ መመረቁ ይታወቃል፡፡ በቁጥር 2 መዝገበ አእምሮ እንዲሁም በተወዳጅ ሚድያ የብሎግና የፌስ ቡክ ገጽ ታሪካቸውን ከምንሰንድላቸው የሚድያ ሰዎች መካከል ዳዊት ከበደ ወየሳ ይጠቀሳል፡፡ ዳዊት ከበደ ከሩህ መጽሄት እስከ ሞገድ ጋዜጣ፤ ከለገዳዲ እስከ ትንሳኤና አድማስ ሬድዮ፤ የሄደባቸውን መንገዶች በህይወት ታሪኩ እናያለን፡፡ አንተነህ ደመላሽ እና እዝራ እጅጉ ታሪኩን አሰናድተውታል፡፡

         ውልደት እና ልጅነት 

  ዳዊት ከበደ ወየሳ የኤምባሲዎች መናገሻ የሚል ስያሜ ከወጣላት አዲስ አበባ ቄራ አካባቢ፤ ልዩ ስሙ ኬላ በር በሚባል ሰፈር፤ ታህሣሥ 19 ቀን፣ 1961 . ተወለደ፡፡ እድሜው ለትምህርት ሲደርስ በእውቀት ምንጭ /ቤት ፊደል ቆጠረ። ከዚያም 1 ክፍል ገብቶ የተማረው፤ 1969 . በካቴድራል ወንዶች የግል ትምህርት ቤት ነበር። በደርግ ዘመነ መንግስት የሶሻሊዝም አብዮት ሲቀጣጠል፤ ትርፍ ቤቶች ሲወረሱና የሃብት ሚዛን ሲዋዥቅ፤ ወንድም እና እህቱ በካቴድራል ትምህርታቸውን ሲቀጥሉ፤ ዳዊት ከበደ ወየሳ የህዝብ /ቤት ወደነበረው፤ ፈለገ ዮርዳኖስ ትምህርት ቤት እንዲገባ ሆነ። 2 ክፍል ጀምሮ፤ በኋላም 4 5 ክፍልን በአንድ አመት አጥፎ በመማር እስከ 8 ክፍል ትምህርቱን የተከታተለው በዚሁ በፈለገ ዮርዳኖስ /ቤት ነው። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በዳግማዊ  ምኒልክ  ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፤ ከዚያም የተግባረ- ዕድ የቴክኒክና ሙያ ለመከታተል በምስራቅ አጠቃላይ ትምህርት ቤት 1979 . በኤሌክትሪክ ሙያ ተመረቀ።

2 ደረጃ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ፤ በመብራት ኃይል መስሪያ ቤት ተቀጥሮ ስራ ከመጀመሩ በፊት ያሉት ጥቂት አመታት፤ አማተር ከያኒ ሆኖ የሰራበት፤ በአጫጭር የሬዲዮ ድራማ ጸሃፊነት የተካፈለበት፤ ከቀበሌ 38 ጀምሮ እስከ ከፍተኛ 20 እና ቀጣና 2 ድረስ፤ ከዚያም እስከ አዲስ አበባ ከተማ ድረስ የነበሩ የወጣት ከያኒያን ክበቦችን ያደራጀበት እና የተሳተፈበት ጊዜ በመሆኑ፤ በህይወቱ ውስጥ ልዩ ስፍራ እንዳላቸው ይገልጻል። በወቅቱ ከነበሩ የልጅነት ባልደረቦቹ አብሮ አደጎቹ መካከል አብዱራህማን አህመዲን፣ አየለሸጉ፣ ሙሼ ሰሙ፣ ታገል ሰይፉ፤ ሁለቱም ደረጀ ኃይሌዎች፤ ሀብቴ ምትኩ፤ እስጢፋኖስ ጸጋዬ፤ ሰራዊት ፍቅሬን፤ ሰለሞን አለሙ፣ ድርብወርቅ ሰይፉ፣ እስጢፋኖስ ባልቻ፣ ሳሙኤል አዳል፤ ውድነህ ክፍሌ እና ተመስገን መላኩ የሚጠቀሱ ናቸው።

ዳዊት ከበደ በተመረቀበት የኤሌክትሪክ ዘርፍ፤ በኢትዮጵያ የመብራት ኃይል መስሪያ ቤት ተቀጥሮ ሰርቷል። በዚያን ወቅት... የመብራት ኃይል ልሳን ለሆነው ፈለገ ብርሃን ጋዜጣ በመጻፍም ይታወቃል። ይህ በኢሊባቦር ክፍለአገር፤ በሶር ሃይድሮ ኤሌትሪክ ፕሮጀክት ሰራተኛነት ያገለገለበት ጊዜ፤ በዳዊት የህይወት ታሪክ ውስጥ... የቅጥር ውል ፈርሞ በሰራተኛነት ተቀጥሮ የሰራበት  የመጀመሪያ እና የመጨረሻው  ዘመን ሆኖ አልፏል።  በዚህ ስራ ላይ እያለ ሚያዝያ 28 ቀን 1983 . በመስሪያ ቤቱ ውስጥ የመጨረሻው ደብዳቤ፤ ለመጨረሻዎቹ ሰራተኞች ተላከ።

በወቅቱ የነበረው ጦርነት እየገፋ፤ በሚያዝያ ወር 1983 . ኢህአዴግ በተለያዩ አቅጣጫዎች ጥቃት ሲከፍት፤ የሶር ሃይድሮ ኤሌክትሪክ ፕሮጀክት ሰራተኞች በተከታታይ ሳምንታት እየተቀነሱ ሄደዋል። ኮንትራቱን የያዙት ጣሊያኖች እና ዋና ዋና መሃንዲሶች፤ ካምፑንም መቱ ከተማንም ለቀው ከሄዱ ሰነባብቷል። ዳዊት ከበደ እና ጥቂት ሰራተኞች በካምፑ ውስጥ ቀሩ። በወቅቱ የኦነግ ሃይል በደምቢዶሎ በኩል አድርጎ መግባቱ ተሰምቷ ል፤ ትግራይ ከመንግስት ቁጥጥር ውጪ ነው፤ የጎንደር፣ የጎጃም እና የወሎ ክፍላተ አገራት በከፊል በኢህአዴግ ቁጥጥር ስር ውለዋል። ዳዊት ከበደ እና ጥቂት ሰራተኞች በዚህ የደከሙበት ፕሮጀክት ውስጥ ለመቆየት ቢያቅዱም፤ ሚያዝያ 28 ቀን 1983 . ከዋናው መስሪያ ቤት የተላከው ደብዳቤ፤ በካምፑ ውስጥ በመቆየት ለሚደርስ ማንኛውም አደጋ ተጠያቂ እንደማይሆኑና ከጥበቃ በስተቀር ሰራተኞች ሙሉ ለሙሉ ካምፑን ለቀው ሲወጡ፤ ዳዊት ከበደም ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ።

         ልጅነት እና ዝንባሌ

ከሜክሲኮ አደባባይ ከፍ ብሎ የሚገኘው፤ በትምህርት ሚንስቴር ስር የሚተዳደረው፤ የለገዳዲ ሬዲዮ ዋና መስሪያ ቤት በወቅቱ ለነበሩት እንደዳዊት ከበደ ወየሳ ላሉ ወጣት ጸሃፍያን በሩን ከፍቶ ያስተናገደ የመገናኛ ብዙሃን ነበር። የፕሮግራም አዘጋጆቹም መምህራን በመሆናቸው፤ በዚያ የሚመጡ ወጣቶችን በስነ ጽሁፍ የሚያንጹበት ጥሩ አጋጣሚ መፍጠሩ አልቀረም። በተለይም በለገዳዲ ሬዲዮ ጣቢያ፤ የቅዳሜ እና እሁድ ዝግጅት በማህበራዊ ህይወት ላይ ያተኮረ በመሆኑ፤ አጫጭር ድራማዎች እና ግጥሞችን እየጻፉ ለማቅረብ፤ በጊዜው ለነበሩ ወጣቶች ሌላኛው ምርጫቸው ስለነበር፤ ዳዊት ከበደ 16 አመቱ ጀምሮ በዚህ ስፍራ ያሳለፈውን ጊዜ፤ እንደትምህርት ቤት አድርጎ ይወስደዋል።

በተማሪነት ዘመኑ... ከሰኞ በስተቀር በየቀኑ የሚታተመውን የአዲስ ዘመን ጋዜጣ መግዛት እና ማንበብ ያዘወትር እንደነበር፤ በምስራቅ አጠቃላይ አብረው የተማሩ ጓደኞቹ ዛሬም ድረስ ያስታውሳሉ። ከታዋቂ ብዕረኞች መካከል፤ ጳውሎስ ኞኞ፣ በአሉ ግርማ እና ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን በዳዊት ልብ ውስጥ ልዩ ስፍራ አላቸው። የደራሲ ንጉሴ አየለ ተካ፣ አውግቸው ተረፈ እና አዳም ረታ አጫጭር ልቦለድ ታሪኮች፤ ወጣትነቱ ያሻገሩት ናቸው። በዚያን ዘመን የራሺያ ደራሲዎችን ስራ ሳያነቡ እና ሳያደንቁ ማለፍ አይቻልም። እንደ ዳዊት አባባል፤ የጎጎል፣ የማክሲም ጎርኪ እና የዲዮስቶቭሽኪን የትርጉም ስራዎች ማንበብ የህሊናን አይን የሚያበራ፤ አንዳች አስማታዊ ሃይል የነበራቸው መሳጭ ስራዎች ናቸው። ይለናል።

ዳዊት የስነጽሁፍ ችሎታውን በተመለከተ፤ በቅድሚያ አባቱን፣ ጓደኞቹን እና መምህራኑን ያመሰግናል። ከምንም በላይ ግን በጉልምስናው ወቅት፤ ደራሲ ስብሃት / እግዚአብሔርን በአካል አግኝቶ ግጥም አንብቦላቸው የሰጡት አስተያየት፤ በጥንቃቄ ነገር ግን ያለፍርሃት መጻፍን እንዳስተማሩት ይመሰክራል። ምንም ይሁን ምን ግን የአባቱ አቶ ከበደ ወየሳ አንባቢነትና አበረታችነት ለዳዊት የጽሁፍ ዝንባሌ ትልቅ ሚና ማበርከቱ የሚካድ አይደለም፡፡

የልጅነቱን ዘመን የሚያስታውሰው... በደርግ ዘመን የነጻ ፕሬስ ህትመቶች ስላልነበሩ፤ በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘመን ይታተሙ የነበሩ መጽሄቶች እና ጋዜጦች... ፖሊስ እና እርምጃው፣ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ፣ መነን፣ ቁምነገርና ፀደይ መጽሔቶችን፤ እንደጊዜ ማሳለፊያ ያነባቸው እንደነበር፤ ምናልባትም ይህ በፕሬሱ ላይ የነበረው ፍቅር፤ የኋላ ህይወቱን ሳይቀይረው አልቀረም። ለዚህም ምስክር የሚሆነው፤ ይህ የህይወት ታሪኩ እስከተጻፈበት ጊዜ ድረስ፤ ላለፉት 30 አመታት ያለማቋረጥ በፕሬስ ህትመት እና በሬዲዮ ዝግጅት ክፍል ውስጥ ዋና አዘጋጅ ሆኖ መቆየቱ ነው።

 




































    ታሪካዊ ጉስቁልናችን እና ሞገድ

1983 . የኢህአዴግ መንግስት የሚያንሰራራበት የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ ታሪካዊ ጉስቁልና ብሎም ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ የገባበት፤ የቀድሞ ወታደሮች በየመንገዱ ቆመው የሚለምኑበት፤ አዲስ አበባ ማህበራዊ ትርምስ ውስጥ የምትናጥበት፤ በመገናኛ ብዙኃን (በብሔራዊ ሚዲያ) የኢትዮጵያ ታሪክ ተዛብቶና ከተፈለገበት የታሪክ አንጓ ላይ ተነጥሎ የኢትዮጵያ ነገስታት፣ የሀገር ህልውናን ያቆዩ ጀግኖች የሚዋረዱበት ዘመን ነበር፡፡ ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ወየሳ ይህ ድርጊት እረፍት ይነሳው ጀመር፡፡ ቀደሞ የምናውቀው የኢትዮጵያ ሬዲዮ የቀድሞ ፕሮግራሞቹን አጥፎ፤ አንድን ብሔር የሚያዋርድ፤ የኢትዮጵያን ታሪክ የሚያንጓጥጥ ጽሁፎችን ማስተናገድ ስራው ሆነ።

በየቀኑ በሬዲዮ ለሚቀርቡት የውሸት ትርክቶች እና ስድቦች ምላሽ ተሰጥቶ የሚዘለቅ አልነበረም። እናም ዳዊት ለነኚያ ጽሁፎች ምላሽ ከመስጠት ይልቅ፤ እውነተኛውን ታሪክ እንደወረደ መንገሩ ጠቃሚ ይሆናል በሚል የኢትዮጵያ ነገሥታትን ሚና በተከታታይ ለማቅረብ አስቦ፤ ጽሁፉንም በስሙ ሳይሆን፤ ዴቪድ ካርል በሚል የብዕር ስም አሰናድቶ፤ አቡነ ጴጥሮስ ወደሚገኘው የማስታወቂያ ሚንስቴር መስሪያ ቤት ሄደ። አዳዲሶቹ ሹሞች ጽሁፉን ከተመለከቱ በኋላ፤ ስለምኒልክ የተጻፈው መልካም ነገር አሳቃቸው። ሆኖም የጽሁፉ አቅራቢ ዴቪድ ካርል የተባለ ጸሃፊ መሆኑ አስገርሟቸዋል።

ጽሁፉን ተወው። ማነው ግን ዴቪድ ካርል? አሉት።

እኔ ነኝ ብሎ ሌላ ስላቅ ውስጥ መግባት አልፈለገም።

ታዋቂ የታሪክ ጸሃፊ ነው በሚል የተጀመረው ጨዋታ የትም ሳይደርስ፤ እንደዚህ አይነት ጽሁፍ እንደማይቀበሉና ካስፈለገ ግን ዴቪድ ካርል ራሱ በፖስታ ቤት መላክ የሚችል መሆኑን ንገረው አሉት።

ያቺ አጋጣሚ የዳዊትን የታሪክ መንገድ ቀየረችው። ያንጊዜ ጽሁፉን ይዞ፤ ከአቡነ ጴጥሮስ ወደ ምኒልክ አደባባይ፤ ከዚያም ከጊዮርጊስ ተሻግሮ ሽቅብ ሲያቀና፤ ASK ኮምፒዩተር የሚል መስሪያ ቤት ተመለከተ። በዚያን ጊዜ ኮምፒዩተር ቤቶች እና የህትመት ስራዎች አብረው የሚሄዱ ነገሮች ነበሩ። እናም ጽሁፉን ይዞ ወደ ውስጥ ሲዘልቅ፤ እውነትም የህትመት ስራ የሚተየብበት፤ ሞገድ የተባለ ጋዜጣ የሚዘጋጅበት... ASK የሚለውም ምህጻረ ቃል፤ አንተንሳይ፣ ሰለሞን እና ክንፉ በጋራ የጀመሩት የንግድ ስራ መሆኑን ተገነዘበ። ያን ጊዜ እጁ የያዘውን ሰጣቸው። ከዚያ በኋላ በዚያ የብዕር ስም በተከታታይ ታሪካዊ ጽሁፍ በሞገድ ጋዜጣ ላይ፤ በኩራፒታ አምድ ስር ይታተም ጀመር።

ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ሞገድ ጋዜጣ ውስጥ ኩራፒታ አምድ ላይ አዘጋጅ በመሆን በኢህአዴግ እስኪታገድ ድረስ በብዕር ስም በተሳሳተ ትርክት ሲጎሳቆሉ የነበሩ ታሪኮችን ሲጠግን ቆይቷል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም ‹‹ፈለግ›› መጽሔት ላይ መጀመሪያ ላይ ቦምባርድ አነሳሱና አወዳደቁ የሚል ጽሁፍ ጽፎ ተወዳጅነት አገኘ። ቀጥሎም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለመጀመሪያ ጊዜ የተማሪዎችን የተቃውሞ እንቅስቃሴ ሲደረግ፤ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችንና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነሩን በማነጋገር፤ ከመጀመሪያው ፉጨት እስከ መጨረሻው ጥይትና የዩኒቨርስቲው መዘጋት"  የሚል በዘመኑ ድፍረት የሚጠይቅ አስደናቂ ሪፖታዥ ሰርቶ ነበር። በዚህ ዘገባው ምክንያት ከአቶ ሙሉጌታ ሉሌ፣ መጽሐፈ ሲራክ እና አሁን ስማቸውን የማያስታውሳቸው ጋዜጠኞች ጋር በጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉዳያቸው መታየት ጀምሮ ነበር። የክስ ጥሪውም የተደረገው በፖሊስ ሳይሆን፤ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ነው።

የነዚህ ጋዜጠኞች ጉዳይ በጠቅላይ ፍርድ ቤት በሚታይበት ወቅት፤ የፕሬስ ህጉ ገና አልወጣም፤ አልጸደቀም። እንደእውነቱ ከሆነ ተከሳሾቹም ቢሆኑ፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ስለተነሳው ረብሻ እና አመጽ፤ እንዲሁም በመንግሥት በኩል ስለተወሰደው ተመጣጣኝ ያልሆነ እርምጃ ዘገቡ እንጂ፤ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚያደርስ  ወንጀል አልፈጸሙም። ለዚህም ይመስላል... በወቅቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ፤ ለምንድነው እንዲህ ያለ የሃሰት ዜና ያቀረባችሁት? ብሎ ሲጠይቃቸው፤

ምናልባት አለማችን በወሬ ድርቅ እንዳትመታ አስበንላት ይሆናላ በማለት፤ ድፍረት የተሞላበት ምላሽ ሰጡ። ይህ ምላሽ በወቅቱ ይታተም በነበረው አዲስ ዘመን ጋዜጣ እና የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዜና ላይ ተላልፎ ነበር። በወቅቱ ከሁሉም ተከሳሾች እድሜው አነስተኛ የነበረው ዳዊት ከበደ ሲሆን፤ 24 አመት እድሜ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ውስጥ በፕሬስ ምክንያት ለመከሰስ የመጀመሪያው ወጣት ጋዜጠኛ ያደርገዋል።

በሌላ ክስተትም ለመጀመሪያ ጊዜ ደቡብ ክልል ተወስዶ የታሰረ ጋዜጠኛም ነበር፡፡

ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ በሩህ፣ በፈለግ፣ በሞገድ፣ መጽሄትና ጋዜጦች ላይ በአምድ አዘጋጅነት ብቃቱን አሳይቷል፡፡ በመብረቅ፣ በማዕበል እና ሌሎች የነጻ ፕሬስ ጋዜጦች ላይ ሳይበዛ የራሱን አበርክቶ አድርጓል። ከምንም በላይ ግን ራሱ አዘጋጅ ሆኖ የሰራባቸው ታደለች፣ ወይ ፍቅር እና ብሌን መጽሄቶች የራሳቸው ቀለም የነበራቸው ብርቅዬ መጽሄቶች ናቸው። ታደለች  በሴቶች ህይወት ላይ የምታተኩር በወንድ የምትዘጋጅ የመጀመሪያዋ የሴቶች መጽሄት ስትሆን፤ ወይ ፍቅር ደግሞ እውነተኛ የፍቅር ታሪኮች ላይ ያተኮረና ምርጥ የፍቅር ታሪክ ያቀረቡ ሰዎች የገንዘብ ሽልማት የሚያገኙበት በአይነቱ ለየት ያለ መጽሄት ነበር። ብሌን የተሰኘው መጽሄት ደግሞ ታዋቂ ብዕረኞች እነታገል ሰይፉ፣ ውድነህ ክፍሌ፣ ደምሴ ጽጌ፣ አውግቸው ተረፈ፣ ፀሃዬ መሰለ፣ ስብሐት ገብረእግዚአብሔር እና ሌሎችም እውቅ ጸሃፊያንን ያሰባሰበ፤ በአብዛኛው አጫጭር ታሪኮች የሚወጡበት፤ ምናልባትም የመጀመሪያው የአጫጭር ልቦለድና ግጥሞች ቅይጥ መጽሄት ነበረ ለማለት ይቻላል።

እዚህ ላይ ሳይጠቀስ መታለፍ የሌለበት አጋጣሚ አለ። ዳዊት ይሰራበት ከነበረው መጽሔት ጎን ለጎን፤ ገና ስያሜ ባልተሰጠው፤ በሙሉጌታ ገሠሠ በሚመራው የሬዲዮ ጣቢያ ላይ፤ የሙከራ ስርጭት በሚል፤ በኋላ ፋና ሬዲዮ ተብሎ በተጠራው ሚዲያ ላይ ድብልቅልቅ የተባለ ተከታታይ የሬዲዮ ድራማ በማቅረብ ይታወቃል። ገና ስም ባልተሰጠው፤ ነገር ግን በቅርቡ ስለሚጀመረው ሬዲዮ በተለይ ከጋሽ መስፍን አለማየሁ ጋር ተመድቦ፤ አዲሱ ሬዲዮ ምን አይነት መልክ እና ቅርጽ እንደሚኖረው አብረው ሲሰሩ ቆይተው፤ በመጨረሻ ሬዲዮኑ በግል ቢቋቋምም፤ አላማው አንድ የፖለቲካ ድርጅት መጥቀም መሆኑን ሲያውቅ፤ በሐመልማል እና በራሱ ጓደኞች የተጠናከረ ግምገማ ሲደረግ፤ ከምረቃው በፊት በራሱ ፈቃድ፤ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከአካባቢው እራሱን አገለለ።

ከላይ ከተጠቀሱት መጽሔቶች መካከል በአንደኛው ላይ ሰላማዊ ሰልፍ እንዲወጣ ሲደረግ፤ የሴቶች ጉዳይ ቢሮም ለፍርድ ቤት ያልበቃ ክስ መስርቶ ነበር። በአንደኛው መጽሔት ላይ ደግሞ በጊሚራ ህዝብ ዘንድ ስለሚዘወተር መጥፎ ባህል በመጻፉ፤ የደቡብ ህዝቦች ምክር ቤት መግለጫ አውጥቶበት ነበር። ስለዚህ አጋጣሚ ሲነግረን፤ አንድ ቀን ከሰአት በኋላ... የኢትዮጵያ ሬዲዮ ዜና እየሰማሁ ሳለ፤ የሙያ ጓደኛዬ አለምነህ ዋሴ በሚያስገመግም ድምጹ፤ የታደለች መጽሔት ዋና አዘጋጅ የሆነው ዳዊት ከበደ፤ በጊሚራ ብሔረሰብ ላይ ላይ ያልተገባ የስም ማጥፋት በማድረጉ፤ የደቡብ ህዝቦች ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ አሳውቋል። በማለት ሙሉ መግለጫውን ሲያነብ መስማት የሚያስደነግጥም የሚያሰቅቅም ነበር።

ከምንም በላይ ግን... የመጽሔቱ አሳታሚ በዚህ ጉዳይ ተጠይቀው፤ በፕሬስ ህጉ መሰረት ኀላፊነቱ የዋና አዘጋጁ የዳዊት ከበደ ይሆናል የሚለው አባባል፤ የዳዊትን የፕሬስ ጉዞ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ቀየረው።  ከዚህ በኋላ ለማንም አሳታሚ ወይም ድርጅት ዋና አዘጋጅ ሆኜ አልሰራም፤ እራሴን ችዬ መስራት አለብኝ። የራሴን ሰንደቅ አላማ እያውለበለብኩ፤ ለትልቅ አላማ መዋደቅን መረጥኩ ይላል። ይህ አዲስ ጉዞ ከባድ ሊሆን ይችላል፤ መንገዱም አባጣ እና ጎርባጣ ይኖረዋል። ሆኖም እራስን ለመስዋዕትነት በማቅረብ፤ ስምን ከመቃብር በላይ የሚያውል ስራ ሰርቶ ለማለፍ ወሰነ። ከዚያ በፊት ግን ፊያሜታ ጋዜጣን አርግዞ፤ ከራሱ ጋር የጽሞና ጊዜ ለማድረግ ተዘጋጀ።

     

 

   መርሳት የማይዳብሳቸው ትዝታዎች

            

               አፉድ አጉዋ

 

1982 . ኢሊባቡር ሶር/Sor/ ሀይድሮ ኤሌክትሪክ ፓወር ፕሮጀክት ላይ ከተራራው ማዶ ትልቅ ብርሃን ይታያል፡፡  በሰአቱ ጋዜጠኛ ዳዊትና ጓደኞቹ የተለያዩ መላምቶች ይሰነዝራሉ፤ ወቅቱ ኢትዮጵያ በጦርነት የምትናጥበት፤ የኢራቅ እና የኩዌት ጦርነት የተጀመረበት ወቅት ስለ ነበር በስፍራው የነበሩ ሰዎች የየራሳቸውን ሃሳብ ይሰጡ ጀመር፡፡ጋዜጠኛ ዳዊት ከዚህ በፊት ከንባብ ካገኘው ግንዛቤ ተነስቶ የታየው ትልቅ ብርሃን በራሪ አካላት /ዩፎ/ የሚባሉት እንደሆኑ ይገምታል፡፡ ይህን ግምቱን የሚያጠናክር ደግሞ  በአካባቢው ለብዙ ዓመታት የቆየ ግለሰብ አፉድ አጉዋ ' ያገኛል፡፡ይህ ግለሰብ እንደ እሱ አጠራር የፈረንጅ አስማተኞች የሆነ ቦታ ወስደው እንደመለሱት ይናገራል፡፡ ይህን ቃለ ምልልስ እሁድ ፕሮግራም ከታምራት አሰፋ ጋር እና 1985 በወጣችው ሩህ መጽሔት ላይ ጋዜጠኛ ዳዊት ያወጣዋል፡፡ በወቅቱ ግራ አጋቢ ተአማኒም ነበር፡፡ ሆኖም 1959 . ጀምሮ በኢትዮጵያ በራሪ አካላት /ዩፎ መታየታቸውን፤ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ጭምር መዘገቡን ልብ ይሏል፡፡

ወይ ፍቅር በተሰኘ መጽሔት ላይ መርሳት የማይዳብሳቸው ድንቅ የፍቅር ታሪኮች ተከትበዋል፡፡ከእነዚህም መካከል የአቢሎ ካሳ፤ ሞቶ የተነሳው ደራሲ /ውድነህ ክፍሌ/ የመቃብር ላይ ጽጌረዳ፤ የሩሲያዊቷ እውነተኛ የፍቅር ታሪኮች ተጠቃሽ ናቸው፡፡በዚህ መጽሔት ላይ ተወዳድረው ያሸነፉ የፍቅር ታሪኮች ተሸላሚ ነበሩ፡፡ የህትመት ዋጋ መናር፤ ካለ በቂ ክፍያ መስራት፤ የነጻ ፕሬሱ መዋዠቅ፤ ህይወትና ምኞት እንዳሰቡት አለመሄድ፤ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ "የኢትዮጵያ ቋንቋዎች እና ስነ ጽሁፍ በሜጀር፤ በማይነር ደግሞ የኢትዮጵያን ታሪክ መማርና ጥልቅ ግንዛቤን ማዳበር ጋዜጠኛ ዳዊትን ወደ ውስጡ እንዲመለከት ብሎም  ከራሱ ጋር አርምሞ እንዲያደርግ ምክንያት ሆነውት ለተከታታይ አመት የዘለቀች የራሱን ፊያሜታ መጽሔት አምጦ እንዲወልድ አድርገውታል፡፡

 

 ዳዊት ከበደ ፊያሜታ  ጋዜጣን ከመሰረተ በኋላ በህወሃት የደህንነት አባላት ታድኖና ታፍኖ ካዛንቺስ በሚገኘው የደህንነት መስሪያ ቤት ህንፃ ስር በተሰራ ምድር ቤትታስሮ መንፈሳዊ ስብራት ደርሶበታል። በዚያ የሲኦል እስር ቤት ይደርስ የነበረው  ኢሰብአዊ ድርጊት እና በለሊት እየተወሰዱ የሚገደሉ ሰዎች ሁኔታ በቃላት ለመግለጽ አስቸጋሪ እንደሆነ ይገልጻል፡፡  በወቅቱ በነበረው የደህንነት ኃላፊ ክንፈ /መድህን የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት በተፈታ ማግስት ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ሳይወድ በግድ እራሱን እንዲመረምር ሆኗል። ስራውን ለማቆም የመጨረሻ ስንብት ብሎ ባሳወቀ ጊዜ፤ የስራ ባልደረቦቹ  እነ ግሩም ተክለሃይማኖት ፊያሜታ ጋዜጣን ለማስቀጠል ያደረጉትን ሙከራ ዛሬም በትዝታ አፅናፍ ያደንቃል፡፡ ወደታች ወረድ ስንል ፊያሜታ እና ዳዊት በምን ልክና መልክ እንዳለፉ እናያለን፡፡ ችግርና መከራ የማይበግሩት ዳዊት  ረጅሙ ብረት ሲሉ ብዙም ይጠሩታል፡፡ ምክንያት ነበራቸው፡፡

ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ወየሳ 14 ዓመቱ ጀምሮ በፍሪላንሰር ጋዜጠኛነት አብዛኛውን ዓመታት ሰርቷል፡፡ በዚህ የጋዜጠኝነት ዑደቱ ላይ ባሳለፋቸው ውጣው ረዶች  የበዙ ሁነቶችን ታዝቧል፡፡ የሚጠቅሙትን ደግሞ ቃርሟል፡፡ በተለይ  ሀሳብን በነጻነት መግለፅ ከመንግስት ትይዩ በህትመት ባለቤቶች  ሊታፈን እንደሚችል በተግባር የዘለቀ ትዝብት አለው፡፡

 

የታደለች ጋዜጣን በሚያዘጋጅበት ወቅት እንደ ወንጀለኛ ለመጀመሪያ ጊዜ በሬዲዮ ስሙ ተዘግቧል፡፡ የደቡብ ህዝቦች ምክርቤት ተሰብስቦ የታደለች ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ወየሳ ስም በውሳኔ መግለጫቸው መሀል ሲብጠለጠልና ሲመነዘር መስማት ርትዕ ናፋቂው አንባቢም ለጋዜጠኛ ዳዊት ከበደም አስደንጋጭ ነበር፡፡

በዘመኑ ምን አልባትም ዛሬም ያሉ የህትመት ባለቤቶች ለቀጠሩት ጋዜጠኛ ዋስትና መሆን ይቅርና እንደ ሰበዝ መዘው አሳልፈው ለአፋኝ መስጠት ሰብዓዊ ስህተትም ደርሶበታል፡፡ ይህን መሰል ጽዋ አብሯቸው በመኖሩና በመስራቱ ሲጎነጭ ራሱን በራሱ ለመሸከም ጥያቄ ጫረበት፡፡

 

1986 . አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የምሽት ትምህርት / Extension/ ፕሮግራም Major የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ -ጽሁፍ Minor ደግሞ የኢትዮጵያን ታሪክ ሲማር አለማወቁን በዕውቀት ያወቀበት በዕድሜውም ሃያዎቹን ያጋመሰበት፤ 1988 . ጽሞና ወሰዶ ወደ ውስጡ እንደገና ያለፈበትን ሁነቶች መመልከት መጠየቅ የጀመረበት ዘመን ነው፡፡ ትኩረት አደረገና ከዚህ በኋላ ራሱን ሆኖ በሙያው መውጣት እንዳለበት ያን ጊዜ የፈለገውን እንደ ልቡ ማድረግ፣ መደመጥ እንደሚችል  አመነ፡፡ በዚህ ሙያዊ ቀኖናው መስዋእትነት ቢከፍል፣ ቢሞት እንኳን እራሱን ይዞ እንደሚያልፍ ውሳኔ አሳረፈ፡፡ የራሴን ሰንደቅ ቀለም መያዝ አለብኝ ሲል ግንዛቤውን አደደረ፡፡ ፊያሜታን ለመጀመር ቅድመ-ዝግጅቱን አሀዱ አለ፡፡

 

የነበረውን 500 የኢትዮጵያ ብር  በወጉ ያዘ፡፡  ይህ ብር በወቅቱ ብዙ የመግዛት አቅም ነበረው፡፡  የኮምፒዩተር ትየባን ጨምሮ፤ አንዳንድ ቁሳቁሶችን ለማሟላት 200 ብር ያህል አጠረው፡፡ ከአንድ ጓደኛው ለመበደር ይፈልጋል፡፡ እርሱ ጋር  ይሄድና ጋዜጣ ልጀምር ነውና እንዲህ አይነት እጥረት ገጠመኝ ሲለው.." ውው..አይገርምህም ትናንትና ለራሴ ሳስበው የነበረው ነገር ነው። እናም ትላንት ምን እንደሆንኩ ታውቃለህ? ሁለተኛ ለሰው ገንዘብ የሚባል ማበደር ማቆም አለብኝ እያልኩ ነበር፡፡ ልክ ማበደር ማቆም አለብኝ ብዬ ስወስን ነው የመጣኸው" የሚል በጊዜው ወሽመጥ ቆራጭ ምላሽ ሰጠው፡፡  ያሰበውን እውን ከማድረግ ወደ ኋላ የማይለው ትንታጉ ጋዜጠኛ ዳዊት ከአባቱ ከአቶ ከበደ ወየሳ ጋር ተማክሮ እንዲሁም ከሌሎች ጓደኞቹ ጋር በመሆን ፊያሜታ ጋዜጣን ወለደ፡፡ የፊያሜታ ጋዜጣ የመጀመሪያው ምክትል አዘጋጅ ኮሜዲያን ተመስገን መላኩ መሆኑን ልብ ይሏል  ፡፡

ዳዊት ከበደ የመጀመሪያውን ጋዜጣ፤ ፊያሜታ ብሎ ሲሰይም፤ ትንሽ እና የምታምር እሳት ነበልባል ማለት መሆኑን ታሳቢ በማድረግና የበአሉ ግርማን ተወዳጅ ገፀባህሪን፤ በጋዜጣው ህያው ሊያደርጋት ፈልጎ እንደሆነ ደጋግሞ ተናግሯል። የሆነስ ሆነና ጋዜጣውን ሲያሳትም፤ እራሱ አሳታሚ እና ዋና አዘጋጅ ሆኖ ስራውን ጀመረ። ሆኖም በህጉ መሰረት ምክትል አዘጋጅ መቅጠርና ስሙን መጻፍ ስላለበት፤ በቅርብ ያገኘውን ተመስገን መላኩን፤ “”ምክትል አዘጋጅ ብትሆነኝ ምን ይመስልሃል? አለው።

በደስታ ብሎ ስራው ተጀመረ።

በኋላ ላይ ጋዜጣው ታትሞ እንደወጣ ወዲያውኑ አለቀ። ወሬው ስለአዲሷ ጋዜጣ ብቻ ሳይሆን ስለአዳዲሶቹ አዘጋጆች ይወራ ጀመር። ተመስገንን ምን ብለው እንዳስፈራሩት ወይም እንዳስደነገጡት አሁን ድረስ አያውቅም። ነገር ግን ተመስገን ዳዊት ይገኝበታል በተባለበት ቦታ ሁሉ አሰሰው፤ ሊያገኘው ግን አልቻለም። በኋላ ላይ ሽማግሌዎች ይዞ ዳዊት ጋር በመሄድ፤ ሁለተኛ ስሜን እንዳታወጣ አለው።

ዳዊትም አንደኛው በአንዱ ላይ በሚነሳበት ዘመን፤ ሰው ፖሊስ ይዞ ሰው ቤት ገብቶ በሚሄድበት ዘመን እግዚአብሔር ይመስገን አንተ ሽማግሌዎች ይዘህ በመምጣትህ አመሰግንሃለሁ። በማለት ነገሩን በሳቅ ቀየረው። ከዚህ በኋላ ዳዊት ሁለተኛ እና የመጨረሻ አማራጩን አየ። ወንድሞቹን ምክትል እና የአምድ አዘጋጅ አድርጎ፤ አብሮ መስራት የተሻለ መሆኑን በማመን ሃብታሙ እና ብሩክ ፊያሜታ ጋዜጣን ገና ከጅምሩ ተቀላቀሉ። 

         ፍርሀት የገራቸው ምንደኞች

 

ምክትል ዋና አዘጋጁ ተመስገን መላኩ ገና በመጀመሪያው የፊያሜታ ጋዜጣ እትም በተፈጠረው ጫና ሥራውን ሲለቅ ጋዜጠኛ ዳዊት የታናሹን ታናሽ ብሩክ ከበደ ወየሳን ምክትል ዋና አዘጋጅ፤ ከእሱ ጀርባ ደግሞ ከሳምንት እስከ ሳምንት የሚለውን አምድ አዘጋጅ ሀብታሙ ከበደ ወየሳን በማድረግ ፊያሜታ ጋዜጣን እንዲያስቀጥሏትታሳቢ አድርጎ አዋቀራት፡፡

 

 ፊያሜታ በትክክለኛ መንገድ ዋና አዘጋጅ እገሌ ብለው እየጻፉ እራሳቸው ኃላፊነት ከሚወስዱ ጋዜጦች ተርታ ትመደባለች፡፡ ያኔ አሳታሚዎች ዋና አዘጋጅ የሚሆኑበትን አጋጣሚ እምብዛም ነበር፡፡

 1980ዎቹ አጋማሽ አሳታሚው ሲያዝ በነጋሪት ጋዜጣ ላይ የታወጀውን የፕሬስ ህግ እየጠቀሱ"ይሄ ጉዳይ እኔን አይመለከትም፡፡ ዋና አዘጋጁን ነው የሚመለከት በሚል ጋዜጠኛውን አሳልፈው የሚሰጡትን ፍርሃት የገራቸውን [ኃላፊዎች ፣የህትመት ባለቤቶች]  ጋዜጠ ዳዊት ከበደ ሲታዘብ ከራርሟል፡፡ እርሱ ፊያሜታን ከጀመረ በኋላ ግን አሳታሚም ዋና አዘጋጅም ሆኖ  ኃላፊነት መውሰድን አስተምሮበታል፡፡

 

 በዛን ወቅት የኢትዮጵያ ቴሌኮሚኒኬሽን ተደራሽነት ገና በዳዴ ላይ ስለ ነበር በኢንተርኔት መረጃዎችን ለማግኘት  ለብዙ ደቂቃዎች በትእግስት መጠበቅ ያስፈልግ እንደነበር እነ ዳዊት ያስታውሱናል፡፡ በኢንተርኔት ዜናዎችን ለመልቀም ከመጀመሪያዎቹ ተርታ የሚሰለፉት የፊያሜታ ጋዜጣ አዘጋጆች፤ በሚላኩላቸው ደብዳቤዎች፤ በውጭ ሀገር ከሚታተሙ ህትመቶች፤ ከውጭ ሀገር የሚላኩ ደብዳቤዎችን በፋክስ በመቀበል የሚድያ ስራውን ለማቀላጠፍ እነ ዳዊት ላይ ታች ይሉ ነበር፡፡

 በተጨማሪም ደግሞ የብሪቲሽ ካውንስል ለጋዜጠኞች በሚሰጠው ነፃ ኢንተርኔት  በመጠቀም፤  ፊያሜታን በመረጃ የተደገፈች ከአለም ጋር አብራ የተጓዘች ለማድረግ ጥረት አድርጓል፡፡

 

               የልብስ ፍልስፍና

ዳዊት ከበደ የጋዜጠኛ አለባበስ ስርአቱን የጠበቀ መሆን አለበት ብሎ ያምናል፡፡ እርሱ ራሱ ካፖርትና ሱፍ ከስካፍ ጋር በማድረግ ይታወቃል፡፡ ጋዜጠኛ በልብሱ መከበር እንዳለበት ዳዊት ያምናል፡፡ አንዳንድ ጋዜጠኞች አለባበሳቸው ሙያውን ከማስከበር ይልቅ ግዴሾች የሚገቡበት ሙያ ያስመስለዋል፡፡ ከዚህ አንጻር ዳዊት በጋዜጠኝነቱ ለእስር ይዳረግ በነበረበት ጊዜ ካፖርቱን ለብሶ ሲሄድ ከሳሾቹ ራሱ አንተ ጋዜጠኛ ነህ ? ብለው ጥያቄ ያቀረቡበትን ጊዜ ያስታውሳል፡፡    

 

 

                ፍም ግፎች

                    

               -ፍሳዊ ዜናዎች

 

ጋዜጠኛ ዳዊት በሙያው ፈታኝ ፍም ግፎችን ውጧል፡፡ የጀነራል ኃየሎም አርአያን ግድያ እስከ ገዳዩ ጀሚል ያሲን ድረስ ያለውን የፍርድ ሂደት ተከታትሎ ዘግቧል፡፡  ጀሚል ከታሰረበት፤በቀነ ቀጠሮው ፍርድ ቤት ድረስ እየሄደ  መረጃዎችን ከዋናው ምንጭ ለማግኘት የተቻለውን አድርጓል፡፡ በጊዜው የሞት ፍርድ ቢፈረድበትም  ብሎም የወቅቱ ፕሬዚዳንት / ነጋሶ ጊዳዳ ስላልፈረሙበት ሳይሞት በመቆየቱ፤ ከጀሚል ከራሱ አንደበት ጄነራል ሃየሎምን እንዴት እንደገደለውና የመጨረሻ ኑዛዜው ድረስ የምርመራ ዘገባ ሂደትን በመጠ ቀም የሰራውን ዘገባ ፈጽሞ አይረሳውም፡፡

 

የፓትሪያርኩ ተከታታይ ታሪክ፤ የአርበኞች ጉዳይ፤ በጋምቤላ ስለ ነበሩ ግድያዎች፤ አሰፋ አብርሃ የኮካ ኮላ ቅሌት፤ የሱር ኮንስትራክሽን እቃዎች ምዝበራ፤ የሚሸሹ ገንዘቦች የተለያዩ የክስ አይነቶችን እያስነሱ ጋዜጠኛ ዳዊትን አባትለውታል... ገሚሶቹ ክሶች በሚያቀርባቸው ተጨባጭ ማስረጃዎች ከሳሾችን አንገት አስደፍተዋል፡፡ የደቡብ ክልል ፕሬዚዳንትየ17 አመት ልጃገረድ  ጠልፈው አገቡ የሚለውን ዜና አዋሳ ድረስ ተወስዶ እንዲታሰር አድርጎታል፡፡

 ዳዊት በሚሰራቸው ዜናዎች ላይ የሚቀርቡት የክሶች ይዘት የሃሰት ዜና የሚል ሳይሆን የድርጊቱን ፈጻሚ ክብር ይነካል  በሚል ማዕቀፍ ውስጥ የታካተቱ ነበሩ፡፡

ዳዊት ከበደ ወየሳ ከአገር ከወጣ በኋላ፤ አቶ አባተ ኪሾም፣ አቶ አሰፋ አብርሃም  ፊያሜታ በተደጋጋሚ ትዘግባቸው በነበሩ የሙስና ጉዳዮች ተጠርጥረው ህግ ፊት ቀርበዋል፡፡

 

 ዳዊት የመጀመሪያ አምዱን በሞገድ ጋዜጣ ላይ ኩራፒታ/ አትሮንስ/ ላይ ነበር  የጀመረው፡፡ ታሪካዊ ጽሁፎችን ሰንጠረዥ/ የቃላት ጥልፍልፎሽ/ ጨዋታ ከፍላጎት ጋር እያቀረበ አንባቢውን ያዝናና ነበር፡፡ ፊያሜታ ጋዜጣን በባለቤትነት እና በዋና አዘጋጅነት ይዞ ከመጣ በኋላ በሀሳብ ገበያው ላይ በነበረችበት ወቅት ሁለት ክስተቶች ተከስተዋል፡፡ ግንባር ቀደሙ ክስተት የጠቅላይ ሚኒስትር ታምራት ላይኔ ከስልጣን መነሳት ነበር፡፡ ይህ አጋጣሚ ጠቅላይ ሚኒስትር ታምራት ላይኔ በስልጣን እስከ ነበሩ ድረስ የደፈጠጡትን የኢትዮጵያን ነፃ ፕሬስ በመታሰራቸው ውለታ ውለውለታል፡፡ ይህን አጋጣሚ ተከትሎ ጋዜጦች ከነበራቸው የመሸጥ ሀቅም 8 9 እጥፍ ጨምረው ተቸብችበዋል፤  የሚገኘው ገንዘብም ጋዜጠኞች ሲታሰሩ ከዋስትና ክፍያ እስከ እስር ቤት ስንቅ ድረስ ሸፍኗል፡፡ የተበታተነውን የአሰራር ሂደት ቁሶችን በማሟላት ወደ ወጥ አሰራር ቀይሮታል፤ መነቃቃትን ቀስቅሷል፡፡

 

ሁለተኛው ክስተት ደግሞ ግንቦት 4/1990 . የተቀሰቀሰው የኢትዮጵያና ኤርትራ ጦርነት ሲሆን ይህ ምዕራፍ ደግሞ መራገፍ ያለባቸው ጋዜጦች ተራግፈው መቀጠል ያለባቸው ጋዜጦች ደግሞ በአንባቢው ዘንድ ህልውናቸውን አገኙ፡፡ከላይ የተጠቀሱት አበይት ሁነቶች የኢትዮጵያን ፕሬስ ከነበረበት አዘቅት አንስተው ወደ ሌላ ምዕራፍ አሻግረውታል፡፡ ጋዜጦች የራሳቸው ቢሮና ሰራተኛ ቀጥረው፣ ቁሳቁስ አደራጅተው በተቋም ደረጃ ራሳቸውን አዋቅረው እስከ መሥራት አስችሏቸዋል፤ የገንዘብ ክምችት ማደግ በህትመት ባለቤቶች ላይ የኑሮ ዘይቤን ለውጧል፤ ፒያሳ ማዕከል ባህረ ነጋሽ ያለበት ህንፃ ሁለተኛ ፎቅ ላይ ፊያሜታ ጋዜጣም የተደራጀ ቢሮ ነበራት፡፡

ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ 12 በላይ ክሶችን ተሸክሞ የቀጠሮ ክፍለ ጊዜ እየመጠነ አፈራርቆ ችሎት ፊት ተሰይሟል፡፡ ዜጎች በድንገት ታፍሰው የሚደበደቡበት፤ ለዓመታት የሚታሰሩበት፤ በህይወት እያሉም እየተገደሉም ድራሻቸው የሚጠፉበት፤ ቀን ይሁን ሌሊት የማይታወቅበት በእየሰዓቱ አሰቃቂ ትዕይንት የሚፈፀምበት የምድር ቤት ሲኦል ውስጥ ታስሯል፡፡ ሰው እንደ ተራ ቡትቶ ተሰብስቦ በጅምላ ተረሽኖ ከሚጣልበት የሞት ክፍል ተቆራኝቶ ግፋቸውን አይቷል፤ ተካፍሏል። በዚህ ገፍታሪ አመክንዮ ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ወየሳ አንባቢዎቹን የሚወደውን ሙያ በሚተገብርባት ፊያሜታ ጋዜጣ ላይ ስንብቱን በአንቀጾች አወራርዶና አስነብቦ አሳርጓል፡፡ 1992 . ከኢትዮጵያ ከመውጣቱ አንድ ቀን አስቀድሞ፤ በማዕከላዊ ፖሊስ ዳግመኛ ለጥያቄ ሲጠራ፤ ነገ እመጣለሁ ብሏቸው፤ በሚቀጥለው ቀን ኬንያ ገባ - አለቀ።

 

      ከኬንያ  እስከ ሀገረ አሜሪካ

 

በዕለተ- ሐሙስ የካቲት ወር 1992 . የፌዴራል ፖሊስ ለጥያቄ እንደሚፈልገውና በነገው እለት መጥቶ ቃሉን እንዲሰጥ፤ ያለበለዚያ አድነው እንደሚያስሩት የሱ መርማሪ የነበረው ጌታሁን የተባለ ፖሊስ ነገረው። ዳዊት እንደሚመጣ ነግሮት ስልኩን ከዘጋ በኋላ፤ ወደ አባቱ ጋር ደውሎ፤ በአስቸኳይ መጥቶ በነገው እለት ወደኬንያ የሚሄድበትን የአውሮፕላን ቲኬት እንዲቆርጡ ነገራቸው። አባቱ ቮልስ መኪናቸውን እያሽከረከሩ ሒልተን ሆቴል ሄደው ቲኬት ከቆረጡ በኋላ፤ አባት እና ልጅ ለመጨረሻ ጊዜ አብረው ቡና ጠጡ - የመጨረሻ ስንብታቸውም ሆነ።

አርብ ቀን በማዕከላዊ ፖሊስ ጣቢያ የተደገሰለትን ባያውቅም፤ ሊሸልሙ እንዳልጠሩት ግን እርግጠኛ ሆኖ ነበር። እናም ማዕከላዊ እመጣለሁ ባለበት ሰአት የሻላ ሃይቅን ወደታች እያየ፤ የኦሞ ወንዝ እና የኦሞ ደኖችን እያደነቀ፤ በዚያው ናይሮቢ ኬንያ ገባ። እየተፈለገ ጋዜጠኛ ዳዊት ወደ ኬንያ በረረ፡፡ ኬንያ የሚገኘው UNHCR ዳይሬክተር የሆነችውን ጃኩሊንን ሰኞ ጠዋት ላይ ለማነጋገር እድል አገኘ። እንዳጋጣሚ በፈረንጆቹ 2000 . ከዚህ በፊት ባልተሞከረ Urgent Pilot Project በተባለ የአሰራር ሥርዓት በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ወደ -ሀገረ ካናዳ ሄደ፡፡ ካናዳ መኖሪያውን አድርጎ Memorial ዩኒቨርስቲ of Newfoundland ገብቶ Information Technology እየተማረ እያለ; በፊት የሚያውቃት አሜሪካ የምትኖር ዕንስት ኢንተርኔት አለም ይተዋወቅና እረፍቶቹ በአንዱ ወደ ሀገረ- አሜሪካ ሄዶ በዚያው ልጅ ወልዶ ቤተሰብ መሰረተ፡፡ በዚህ መሀል የፊያሜታ ጋዜጣ ባለቤትና አዘጋጅ፤ እንዲሁም የኢትዮጵያ ነፃ-ፕሬስ ጋዜጠኞች ማህበር እንደገና ሲደራጅ፤ ጋዜጠኞችን ያሰባሰበ፤ እነአቶ ክፍሌ ሙላት በፕሬዘዳንትነት እንዲመሩ ሲመረጡ ዳዊት ከበደ በህዝብ ግኑኝነት ኃላፊነት ሰርቷል።

 ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ የእድሜ ልክ እስራት በሌለበት ፍርድ ቤት ውሳኔ ማሳለፉን ልብ ይሏል፡፡

 

1983. ክረምት ኢህአዴግ እንደገባ ጓደኞቹ ሙሼ ሰሙ፤ አብዱራሃማን አህመዲን ጋር በመሆን የኢትዮጵያ ወጣቶች ህብረትን መስርቶ ነበር፡፡ በተለያዩ ግፊቶች ህብረቱ ቢፈርስም ከተወሰነ ጊዜ በኋላ አቶ ልደቱ አያሌው፣ አቶ ታምራት ታረቀኝ፣ ሙሼ ሰሙ፣ አብዱርሃማን አህመዲን በጋራ በመሆን፤ ኢዴፓ ፓርቲን ከመመስረታቸው በፊትም ሆነ በኋላ አብሯቸው ቢሆንም፤ የጋዜጠኝነት ስነ ምግባር ስለማይፈቅድለት ፊት ለፊት ለመሳተፍ ሳይችል ቀርቷል። ፓርቲው ከተመሰረተም በኋላ ጋዜጠኛ ዳዊትም በሌላ ነገሮች እንረዳዳለን የሚል ምላሽ ሰጥቷቸዋል። እንዳለውም የኢዴፓ መመስረት የምስራች የተነገረውና የመጀመሪያዎቹ ቅስቀሳዎች የተደረጉት በፊያሜታ ጋዜጣ ላይ ነበር። እናም ከሀገር ከመውጣቱ ሶስት ወራት በፊት ፓርቲው እውን ሆነ ፡፡

 

ፓርቲው ተመስርቶ በጊዮን ሆቴል መግለጫ ከተሰጠ በኋላ፤ ሙሼ፣ አብዱራህማን፣ ልደቱ እና ታምራት በቀጥታ ወደ ዳዊት ወይም ፊያሜታ ቢሮ በመሄድ ነበር፤ የደስታ ጽዋቸውን በጋራ ያነሱት። ያኔ እንደዘበት የስልጣን ሃላፊነት ሲሸላለሙ፤ ምናልባት ከመካከላችን ወደ ውጭ የመውጣት አጋጣሚ የተፈጠረለት ሰው የውጭ ኃላፊ ይሆናል፡ አሉ እንደቀልድ። ንግርታቸው በጋዜጠኛ ዳዊት ላይ ሰመረና በአሜሪካ የኢዲፓ የህዝብ ግኑኝነት ኃላፊ ሆነ፡፡ የኢዴፓን የውጭ ጉዳይ ክንውን እየተቆጣጠረ ከነ ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ እና አትላንታ ከሚገኙት አቶ ቸሩ ተረፈ ጋር በማገናኘት፤ ኢዴፓንና መድህን ፓርቲን የማዋሃድ ስራ ሰርቷል። እንዲሁም የኢዴፓን መገናኛ ድረ ገፅ በዋናነት ይመራ ነበር፡፡

 ከዚህ ጎን ለጎን በስደት ላይ ካሉ  ጋዜጠኛ ክንፉ አሰፋ፤ ግርማ እንድርያስ፣ አትክልት አሰፋ፣ ሉሉ፣ ሰይፉ፣ ክብረትና አክሊሉ ታደሰ ጋር በመሆን በስደት የሚገኙ የኢትዮጵያ ነጻ-ፕሬስ ጋዜጠኞችን ፎረም መሰረተ፡፡ ከእለታዊ ችግሮችን ከመፍታት ጀምሮ ጋዜጠኞች ከሙያቸው እንዳይርቁ በርካታ ሙያዊ እና ሰብአዊ ሥራዎችን ሰርቷል፡፡ በዚህ የስደት ዘመን እንደአሜሪካ አቆጣጠር 2002 እስከ 2005 ድረስ የህብረት ድምፅ መጽሔት፤ ድምፅ ጋዜጣን በዋና አዘጋጅነት ለህትመት አብቅቷል። የስራ እና የሙያ ባልደረባው ለነበረው ጓደኛው ቴዲ  ቃል በገባው መሰረት፤ ቴዲ ካለፈ በኋላ፤ በሰሜን አሜሪካ በየወሩ የምትታተመውን ባለ 80 ገጽና ባለ ሙሉ ቀለም መጽሄት ሳያቋርጥ አስቀጥሏል። ይህን ጥንቅር በምንሰራበት ወቅት 237ተኛዋ ወርሃዊ የድንቅ መጽሄት በአትላንታ ጆርጂያ ተሰራጭታለች። 

 

ዳዊት ከኦሃዮ ወደ አትላንታ ሲዛወር፤ ከሙያ አጋሮቹ ቴዲ፣ መልካምዘር እና ዳኔል አሰግድ ጋር በመሆን፤ 2006 አድማስ ሬዲዮን መጀመሪያ 1010 Am Radio ቀጥሎም 1100 Am Radio ላይ ሲሰራ ከቆየ በኋላ፤ 2009 በኋላ በግል ስራው ላይ በማተኮሩ፤ አድማስ ሬዲዮ ሙሉ ለሙሉ በቴዲ ሃላፊነት እንዲሰራ ሆኗል። ሌላው መጠቀስ የሚገባው 2005 ጀምሮ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ በየቀኑ ወደ አገር ቤት ይገባ የነበረው የትንሳኤ ሬዲዮ ነው። ትንሳኤ ሬዲዮ የመጀመሪያው የተቃዋሚዎች ድምጽ የሚስተጋባበት የሬዲዮ ጣቢያ ሆኖ 3 አመታት ያህል ቆይቷል።

ዳዊት ከበደ ወየሳ የትንሳኤ ሬዲዮ ሃላፊ ሆኖ ሲሰራ፤ መጀመሪያ በመለስ ዜናዊ ሚስት አዜብ መስፍን፤ ቀጥሎም በስብሃት ነጋ፣ በመለስ ዜናዊ፣ በበረከት ስምኦን እና በሌሎች አስር ከፍተኛ ባለስልጣኖች በአሜሪካ ክስ ተመስርቶበት ነበር። ይህ ክስ በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ፡አንድ የውጭ አገር መንግስት እና ባለስልጣናት፤ በስደት ላይ የሚገኝ ጋዜጠኛን ሲከሱ፤ የመጀመሪያዎቹ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። ክርክሩ በቨርጂንያ ፍርድ ቤት ሲካሄድ ቆይቶ የዳዊት ከበደ ወየሳ ጠበቃ የነበረው ሼክስፒር ፈይሳ ጉዳዩን አሸንፎ መዝገቡ ተዘግቷል።

ከትንሳኤ ሬዲዮ ጀርባ በተለይ በገንዘብ ይደግፉ የነበሩ ኢትዮጵያዊያን እና ዋናውን ክፍያ ይፈጽም የነበረው አቶ ሰለሞን በቀለ አይዘነጋም። በዋሺንግተን ዲሲ እና በአውሮጳ የነበሩ የትንሳኤ ሬዲዮ የቦርድ አባላትም አይዘነጉም። በወቅቱ የቅንጅት ፓርቲ አመራሮችን ለማስፈታት የኢህአዴግ መንግስት እንዲዘጋለት መደራደሪያ ነጥብ ካደረ ገው መካከል የትንሳኤ ሬዲዮ አንደኛው ነበር።  በድርድሩ መሰረት የቅንጅት መሪዎች ከተፈቱ ጥቂት ወራት በኋላ የትንሳኤ ሬዲዮ ከሰመና እንደኢሳት አይነት ጠንካራ ሚዲያዎች ተፈጠሩ። 2005 የቅንጅት መሪዎች እና ጋዜጠኞች ሲታሰሩ፤ ዳዊት ከበደ ወየሳ በሌለበት ተከሳሽ ሆኖ እድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበታል።

ይሄ ሁሉ እየተሰራ ከዚህ ጎን ለጎን በኋላ ላይ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ በተራ ቁጥር አንድ ላይ ስሙ ሰፍሮ ከተከለከሉ ጠንካራ ድረ ገጾች መካከል  ኢትዮ ሚዲያ ፎረም www.ethioforum.org ዋነኛው ነበር። ዳዊት ከበደ ወየሳ ከክንፉ አሰፋ ጋር ይህን የኢትዮፎረም ድረ ገጽ ከአስር አመት በላይ ከሰሩበት በኋላ፤ በሁለቱም ላይ በደረሰባቸው የስራ ጫና ምክንያት ድረ ገጹን 2019 ጀምሮ አክስመውታል። ዳዊት ከበደ ወየሳ አሁን 2006 . ከቴዲ እና ከጓደኞቹ ጋር በመሰረተው አድማስ ሬዲዮ በሃላፊነት ያገለግላል። እንዲሁም የፈረንጆቹ 2023 ሲመጣ ሃያኛ አመት የሚሞላት፤ በህይወት የሌለው የጓደኛው እና የአትላንታ ህዝብ ኩራት የሆነው ድንቅ መጽሔት ዋና አዘጋጅ እና አሳታሚ ነው።

 

              ?  ተጠየቅ  

አንድ አንድ ሰዎች እንዲያ ለአንገላቱህ ባለ ጊዜዎች የይቅርታ ልብ ይኖርህ  ይሆን...?ብለው ህሊናውን በተጠየቅ ሲዳብሱት ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ወየሳ

" እነርሱ ይቅርታ የሚገባቸው ሰዎች ሆነው ሳይሆን " እኔ " ይቅርታ የማድረግ

ሀቅም ስላለኝ ይቅር እላቸዋለሁ"ሲል ንጹህ የሰብዓዊነት ጥጉን አሳይቶናል፡፡

ዳዊት ከበደ በቅርብ ሰዎቹ ሲመሰከርለት ያመነውን ለማድረግ ወደ ኋላ የማይል ቆራጥ ሰው ነው ይሉታል፡፡ ትንሽ ሀይለኛ ነው ሲሉም ሀሳብ ይሰጣሉ፡፡ ይህ ሀይለኝነቱ አስከብሮታል፡፡ ዳዊት በንባብ የሚታማ ሰው አይደለም፡፡ ገና በልጅነቱ እድሜ ለአባቱ አቶ ከበደ ይሁንና ከመጽሀፍ ጋር ተጎዳኝቷል፡፡ ታገል ሰይፉ ገና በታዳጊነቱ በእነዚህ መጽሀፎች አእምሮውን አጎልብቷል፡፡ ዳዊት ከበደ ጋዜጠኝነት የጽሁፍ ሰውነትን በየትኛውም ጊዜ ሲከውን ኖሯል፡፡ ባህርማዶ ከገባ በኋላ እንኳን ማንም ሆነ ምንም ምክንያት ከሚድያ አይነጥለውም፡፡ ዳዊት በራሱ መንገድ ጥሞና ለራሱ እየሰጠ በብዙ ውጣውረዶች እያለፈ ዛሬም ለሚድያው እድገት ይታገላል፡፡ በአሁኑ ሰአት በመዝናኛው ዘርፍ ትልቅ አሻራ እያኖሩ ያሉት እነ ሰይፉ ፋንታሁን ሰራዊት ፍቅሬ ታገል ሰይፉ ደረጀ  ሀይሌ ከዳዊት ጋር በወጣትነት የተጉ በመሆናቸው የዳዊትን ጠንካራ ሰውነት በሙሉ አንደበት የሚመሰክሩ ናቸው፡፡ ዳዊት ከበደ ብዙ ስለራሱ መናገር የሚወድ አይደለም ልታይ ልታይ የሚል አይደለም፡፡ ስራው ላይ ይተከላል፡፡ ከዚህ ግለ-ታሪክ አዘጋጅ ጋር በድምሩ 6 ሰአታት ጭውውት ያደረገው ዳዊት ከሀገር  ቤት ብወጣም ኢትዮጵያ ከእኔ አትወጣም የሚል የጸና እምነት አለው፡፡ዳዊት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚያውቀው ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ ትንታጉ ዳዊት ሲል ይገልጸዋል፡፡ ዳዊት ግን ዛሬ ቤተሰብ መስርቶ ዳግም በሚድያው አንድ ነገር ለመስራት ሌላ ዙር ሱባኤ የገባ ይመስላል፡፡የህይወት ታሪኩ ግን ለአዲሱ ትውልድ የሚያስተምር ነው፡፡ 

 ስለ ዳዊት የቅርቦች ምን ይላሉ  ?

   / ከሸዋዬ ለገሰ / 

ዳዊት ከበደ ወየሳ ያለውን እምቅ አቅም ደብቆ "በአሜሪካን ጫካ" የመሸገ ድንቅ ብእረኛ ነው። ትውውቃችን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ይጀምራል በ1980ዎቹ ። በአንድ ክፍልም ለአራት ዓመታት አብረን ተምረናል። ያኔ ዳዊት የነበረውን ጫና ተቋቁመው በግል ጋዜጦች ላይ ከሚጽፉ አልፎም የራሳቸውን ጋዜጣ አዘጋጅተው ለንባብ ያቀርቡ ከነበሩት አንዱ ነው። "ፊያሜታ" የጋዜጠኛ ዳዊት ተነባቢ ጋዜጣ ነበረች። ቁምነገርን ከጨዋታ አካትታ የምትታተም የፖለቲካ ጋዜጣ። እኔና ዳዊት የምንግባባቸው ሀገራዊ ሀሳቦች ብዙ ሆነው ከሃይማኖት በተነካኩት ላይ እንለያይ ነበር።  ከዳዊት አንባቢነቱን፣ ታሪክ አዋቂነቱን፣  በሁሉም ርዕሰ ጉዳይ መወያየት መቻሉን፣ ልበ ሰፊነቱን አደንቃለሁ፣ አከብራለሁም። በጋዜጣ ሥራው ምክንያት የነበረበት ጫና ገፍቶት አሜሪካ የሚሉት ውቅያኖስ ውስጥ ከከተተው ወዲህ በሌሎች ኃላፊነቶች ተያዘና ያለውን አቅም በጋዜጠኝነቱም ሆነ በስነጽሑፉ ዘርፍ ማድረግ በሚችለው መጠን ማድረግ አለመቻሉ ግን ይቆጨኛል። በዚህ አጋጣሚ ተወዳጅ ሚዲያ ይህን ግሩም ታሪክ አዋቂና የተባ ብእር ባለቤት የቀበረውን መክሊቱን አውጥቶ ሌሎች እንዲያውቁ እንዲማሩበት እርሱም ያተርፍበት ዘንድ ወደ መድረኩ እንዲመለስ እንዲገፋፋው በትህትና ለማሳሰብ እወዳለሁ። ወንድሜ ጋዜጠኛ ዳዊት ዛሬም ከሚያከብሩህ አንዷ ነኝ። ለማንኛውም "አባታችን አካፑልኮ ጀመረ!" መቼም በዚች ካርቱን ጉዳይ ጥያቄ አይቀርልህም ሰማይ ቤት! 

 

 /ከድርብ  ወርቅ ሰይፉ

ከዳዊት ከበደ ወየሳ ጋር ከ4ኛ ክፍል ጀምሮ ነው የምንተዋወቀው ፡፡ ዳዊት ከልጅነት ጀምሮ የጥበብ ፍቅር ያደረበት ሰው ነበር፡፡ያኔ ድራማዎችን በመጻፍ ለስነ-ጽሁፍ ያለውን ፍቅር ያሳይ ነበር፡፡ ዳዊት ፊያሜታ ጋዜጣን ከጀመረ በኋላ ምን ያህል ቀን ተሌት ይለፋ እንደነበር እኔ ምስክር ነኝ፡፡ አፍለኛው የቴአትር ቡድን ቢሮ ባልነበረው ሰአት ቢሮ በመስጠት ትልቅ ትብብር ያደረገው ዳዊት ከበደ ነው፡፡ ለዚህ ቅን ውለታውም ላመሰግነው እፈልጋለሁ፡፡ዳዊት የሚመኩበት ጥሩ ወንድም ነው፡፡አሁንም በሚድያ ላይ በፍቅር እየሰራ ሳየው እደነቃለሁ፡፡ ዳዊት ከእነ መላ ቤተሰቡ መልካሙን ሁሉ እመኝለታለሁ፡፡   

 








 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች