አይናለም ባልቻ 

 

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያው ዘርፍ ላይ የጎላ አሻራ የነበራቸውን ባለሙያዎች የህይወት ታሪክ እየሰነደ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከዚህ ቀደም መዝገበ-አእምሮ በሚል ርእስ የ180 የሚድያ ሰዎችን ታሪክ በመጽሀፍ አዘጋጅቶ ማስመረቁ ይታወቃል፡፡ በቀጣይ ቅጽ 2 ላይ ታሪካቸው ከሚሰነድላቸው መካከል አይናለም ባልቻ ትገኛለች፡፡ አይናለም ባልቻ  በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የልጆች ፕሮግራም ላይ አገልግሎት ሰጥታለች፡፡ የህይወት ታሪኳም እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡

 

አይናለም ባልቻ  ከቤተሰቦቿ ጋር የነበራትን ግንኙነት ስንመለከት አባቷን የማታውቅ እናቷ ደግሞ ገና ልጅነቷን ሳትጨርስ በሞት ያጣች ልጅ ናት፤ይህ ባሳሰባቸው በጎረቤቶቻቸው  አማካይት ከወንድሟ ጋር የታችኛው ቤተመንግስት ውስጥ በነበረ  የህጻናት ማሳደጊያ እንዲመዘገቡ ተደርገው የልጅነታቸውን ጊዜ አሳልፈዋል፡፡ አይናለም ባልቻ ሀምሌ 21 1952 ነበር የተወለደችው፡፡

አይናለም የህፃናት ማሳደጊያ ተቋምን ከተቀላቀለች በኋላ በወቅቱ እድሜዋ ለትምህርት ደርሷልና በእድገት በህብረት ዘመቻ በቀድሞ አጠራሩ በየነ መርዕድ የተሰኘ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገባች፡፡በትምህርቷ እሳት የላሰች ሆነችና በአንድ ዓመት ውስጥ በመጀመሪያው መንፈቀ- ዓመት 1ኛ ክፍልን ተሻግራ ወደ ሁለት ገባች፡፡ በዓመቱ መጨረሻም ወደ 3ኛ ክፍል ተዘዋወረች፡፡እስከ አራተኛ ክፍልም በዚሁ ትምህርት ቤት ትምህርቷን ተከታተለች፡፡

የአይናለም ባልቻ ሌላኛው የልጅነቷ ክፍል እና ያደገችው ደግሞ በህፃናት አምባ ነው፡፡ወደ ተቋሙ  የገባችበት ራሱ ሂደት ነበረው፡፡ይህም ህፃናት አምባ ሲቋቋምም ዓለምፀሀይ ወዳጆ ሙዚቃ ልታዘጋጅ ልጆችን በየህጻናት ማሳደጊያው በመዞር ታሰባስብ ነበር፡፡ ከእነዚህም ህፃናት መካከል ደግሞ አይናለም ካለችበት ፍልውሃ የህፃናት ማሳደጊያ ከተመረጡት ህፃናት መካከል አንዷ ሆነች፡፡

ለዚህም ዝግጅት በብሔራዊ እና  በአምባሳደር ቴአትር ቤት በፕሮግራም ስልጠናውን ከሚወስዱት ጋር አንድ ላይ ትሰለጥን ነበር፡፡

ህፃናት አምባ ከእነ አይናለም ቀድመው መግባት የነበረባቸው ልጆች ገብተውበት ነበር፡፡የሰለጠኑትን በዚያው በህፃናት አምባ የተለያዩ ያዘጋጇቸውን መዝሙሮች   እነ ጋሼ መንግስቱ አባታችን፣አባባ የወደቀለት ብሩህ ዓላማ የመሳሰሉትን ከፍተኛ ባለስልጣናት በተገኙበት አቅርበው ተደነቁበት፡፡

በዚህ መነሻነት  ትርዒቱ በቀረበበት አላጌ በሚገኘው ህፃናት አምባ ከወንድሟ  ቴዎድሮስ ሙሉጌታ ጋር ሳይለያዩ  እንዲኖሩ አመጧቸው፤ግን እሱ በሰብለ ከ1-7 ዓመት ድረስ ያሉ ህፃናት የሚኖሩበት መንደር እሷ ደግሞ በዘረዓይ ድረስ ከ7-18 ዓመት የሆኑ ልጆች በሚኖሩበት መንደር መኖር ጀመሩ፡፡

አምስተኛ እና ስድስተኛ ክፍልን በዚያው ከተማረች እና ሚኒስትሪን ከወሰደች በኋላም ወደ ጀርመን በመሄድ ለ20 ቀናት በተዘጋጀ ፌስቲቫል ላይ የመሳተፍ እድል አግኝታለች፡፡

ከጀርመን ከተመለሰች በኋላም በህፃናት አምባ ቆይታዋ የተለያዩ የውጭ ሃገራት ዜጎችን ጨምሮ ማዕከሉን በእንግድነት በሚጎበኙበት ጊዜ አስጎብኚም ሆነ አስተርጓሚ ሆና ተመርጣ ነበር፡፡

በዚህም ተግባሯን ስትከውን እንደ አጋጣሚ የቡልጋሪያ አባት ሀገር ግንባር ማህበር ፕሬዚዳንት እና ሌሎች አባላቶቻቸው ግቢውን ሊጎበኙ መጡ፡፡ይሄም አይናለምን ጨምሮ በማዕከሉ ላሉ ልጆች መልካም ዜናን ይዞ የመጣም ነበር፡፡ ምክንያቱም ከቡልጋሪያ የመጡት እንግዶች ግቢውን ጎብኝተው ሲያጠናቅቁ ጎበዝ ጎበዝ የሆኑ 2 ተማሪዎች በየዓመቱ ወደ ቡልጋሪያ ሄደው በማህበሩ አማካይነት የትምህርት እድል እንዲያገኙ የሚያደርግ ነበር፡፡

በግቢው በተዘጋጀ መስፈርት መሰረትም አይናለም እና የያኔው የትምህርት ቤት ጓዷ እንዲሁም የኋላ ባለቤቷ  የነበረው አደም ተመራጭ ሆነው  የፓርቲ ተማሪዎች ይሄዱበት በነበረው ቻርተር አውሮፕላን ወደ ቡልጋሪያ ከዋና መዲናዋ ሶፊያ 183 ኪ.ሜ ርቀት ካላት የቱሪስት መናኸሪያ ወደሆነችው ከተማ ወደ ቡርጋስ ለትምህርት  አመሩ፡፡

በቡልጋሪያም ሞግዚት ሆና በተመደበችላቸው እናት ልብስ እና ጫማ ተገዝቶላቸው የትምህርት ወቅት ሲጀመርም 2 ከህንድ፣2 ከቬየትናም እና ከኮንጎ የመጡ ልጆችን ጨምረው 10 በመሆን የቋንቋ ትምህርታቸውን ጀመሩ፡፡

መምህራቸው ፈፅሞ ከሃገሪቱ ቋንቋ ውጪ መግባባትን አትፈቅድም፡፡ እና አይናለምም እንደምትለው በሚደነቀው የቋንቋ የማስተማር ዘዴያቸው በ3 ወራት ምንም የማያውቁትን ቋንቋ መግባባት የሚችሉበት ሆነ፡፡

በዚህ ወቅትም በተለይ በመንገድ የሚመለከቷት የጸጉር አሰራሯን ተመልክተው እንዴት እንደሰራችው ሲጠይቋት እና መሰል ንግግሮችን ከሌሎች ጋር ማድረጓ ደግሞ ሰዎችን ከመተዋወቋም ባሻገር ቋንቋውንም ለማሳደግ ረዳት፡፡

ወደ ቡልጋሪያ በወሰዳቸው የቡልጋሪያ አባት ሀገር  ግንባር መሪ  አማካይነት በሃገሪቱ ምርጥ በሚሰኘው ትምህርት ቤት እንዲማሩ ተብሎ በተሰጠው ትዕዛዝ መሰረት  በታሪካዊው ጊዮርጊ ሳቫ ራኮቭስኪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማረች፡፡

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን እየተከታተለች በነበረበት ወቅት በ1977አ.ም የ10ኛ ክፍል ተማሪ ሆና በሀገራችን ተከስቶ በነበረው ድርቅ የሀገሬን ሰዎች መርዳት አለብኝ በማለት ትኖርበት ከነበረው ቡልጋሪያ ድጋፍ የሚሆን ምግብ እና ልብስ የተለያዩ ት/ቤቶች በመዘዋወር በሀገራችን የተከሰተውን ሁነት በመንገር አስቸኳይ እርዳታም ማግኘት ችላ ነበር፡፡በዚህም የተሰበሰበውን ዱቄት እና አልባሳት በመርከብ በማስጫን ለወገኗ በዛ እድሜዋ በምትችለው ሁሉ መድረስም ችላ ነበር፡፡

ከትምህርት ቤት ጓደኞቼ ጋርም ጥሩ እና  መልካም ትዝታዎች አሉኝ የምትለው አይናለም ባልቻ ሁለተኛ ደረጃን  ስታጠናቅቅ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቷን በዛው ቀጠለች፤አብዛኛውን የቡልጋሪያ አካባቢ እና ዘዬን ለይቼ አውቃለሁ የምትለው አይናለም በዩኒቨርሲቲ ቆይታዋም ጥቁር ነሽ ተብላ ተንቃ እና አድልዎ ደርሶባት ሳይሆን ተከብራ መማሯን ነው የምታስታውሰው፡፡

የሕክምና ትምህርትን መማር ምኞቷ የነበረ ቢሆንም 8ኛ ክፍል ተማሪ በነበረችበት ወቅት ላብራቶሪ ክፍል ውስጥ ከመምህሯ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት እና በሀገሪቱ ያለው ትምህርት ከባድ በመሆኑ የሃሳቧ መቀየር መነሻ ሆኗት፡፡ በዙሪያዋ የነበሩ ሰዎች ለምን ጋዜጠኝነትን አትማሪም የሚል ውትወታቸውን ተቀብላ የጋዜጠኝነት ትምህርትን መማር መረጠች፡፡

በቡልጋሪያ ለ 5 ዓመት በተማረችው የጋዜጠኝነት ትምህርት ክፍል ከሙሉ የመማሪያ እና አጋዥ መፅሀፍት አንስቶ የመምህራኖቻቸው የትምህርት ደረጃን እና  የትምህርት አሰጣጣቸው የተለየ መሆኑ ትምህርቱን ወድጄ እንድማር እና የበለጠ እንዳውቀውም ረድቶኛል ትላለች፡፡

በ1986 ዓ.ም የኢትዮጵያ ማስ ሚዲያ እና ኮሚዩኒኬሽን በሚል ወደ 59 ገፅ የሚጠጋ የመመረቂያ ፅሁፍንም ለመስራት ተባባሪ በማጣት እና በከባድ ፈተናም ቢሆን በጥሩ ውጤት የማስተርስ ዲግሪዋንም በቡጋሪያ አግኝታለች፡፡ በዚያን ወቅት እርግጥ ነው ታላቅ ውለታ የዋሉላትን አቶ ተሾመ ብርሀኑ ከማልን ማመስገን ትሻለች፡፡

                የሥራ ጅማሮ እና ጉዞ

አይናለም የዩኒቨርሲቲ ትምህርቷንም ካጠናቀቀች በኋላ  እናት አባት ሳይኖረኝ ያሳደገኝም ሆነ ቤተሰብ የሆነኝ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ነው በማለት የአምስት ዓመት ልጇን ይዛ ኑሮዋን በዚሁ ለማድረግ ወደ ሀገሯ ኢትዮጵያ ተመለሰች፡፡

ከተመለሰች በኋላም ወደ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ብታመለክትም ሳይጠሯት ቀረ፤በሜጋ ኪነ -ጥበባት ማዕከልም ያሏትን ሃሳቦች አቅርባ በመጠባበቅ ላይ ነበረች፡፡ ያሉትን ፈተናዎች አልፋ ጽፈሽ ነይ የተባለችውን ሁሉ አሟልታ በ1988 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ስራዋን ጀመረች፡፡

በዜና ክፍልም መልካም ሰው በምትለው አለቃዋ በነበረው ፍስሃ ገብርኤል አማካይነት የስክሪፕት ሃሳብ እና አፃፃፍን በሚገባ ተምራ ሥራውን በሚገባ ተላመደችው፡፡

የተለያዩ ክፍሎች ውስጥ ዜና፣መዝናኛ እና ህፃናት ክፍል ውስጥም የሰራች ሲሆን በርካታ ፕሮግራሞችንም ወደ ተመልካቹ ማድረስም ችላለች፡፡

የልጆች ፕሮግራም ላይ ደግሞ የምትሰራቸው ፕሮግራሞች እና ታደርጋቸው የነበሩ የማስተዋወቅ መንገዶች የተለዩ እና ተወዳጅም ነበሩ፡፡

በህፃናት ክፍል ቆይታዋም የአዋቂ ሙዚቃዎች እንደሚሰሩት ሁሉ የህፃናት ሙዚቃዎች እንዲሰሩ እና እንዲቀረፁ በማድረግ ቀዳሚ ናት፡፡ድራማዎች እንዲሰሩም በማድረግ በክፍሉ አዳዲስ ሃሳቦችን ማምጣትም ችላለች፡፡

ከ24 ዓመት የጣቢያው የሥራ ቆይታዋ ውስጥም ረዥሙ የሆነውን የሥራ ክፍል ያሳለፈችበትን ማለትም 15 ዓመትን የሰራችበት የህፃናት ክፍልን ወደ መጨረሻ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የሥራ ቆይታዋም የክፍሉ ዳይሬክተር በመሆን አገልግላለች፡፡   ቅኝት የሚባል ፕሮግራም ትሰራ ነበር፡፡  ይህ ፕሮግራም ባህል እና ታሪክ ላይ  የሚያተኩር  ሲሆን ፕሮግራሙንም ለ 4 አመታት ሰርታዋለች፡፡፤

          

 

        የቤተሰብ ሁኔታ

አይናለም ባልቻ ከቀድሞ ባለቤቷ አንድ ልጅ ያፈራች ሲሆን ልጇንም ለብቻዋ አሳድጋ በኮምፒውተር ሳይንስ አስመርቃለች:: ልጇም አፍሪካ ህብረት ውስጥ ለ2 ዓመት ካገለገለች በኋላ አሁን በተባበሩት መንግስታት ማህበራዊ ፈንድ (UNFPA) ውስጥ በመስራት ላይ ትገኛለች፡፡ ባለትዳር እና የሁለት ልጆም እናት በመሆን እናቷን አያት  አድርጋታለች፡፡

 

 












 

 

 

 

 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች