ዘላለም ቱሉ
ተወዳጅ
ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ‹‹መዝገበ-አዕምሮ›› በሚል ርዕስ የ180
የሚድያ ሰዎችን ታሪክ በመጽሀፍ አሳትሞ ሀምሌ 30 2014 ዓ.ም
ማስመረቁ ይታወቃል፡፡ በቀጣይ ደግሞ መዝገበ-አዕምሮ ቅጽ ሁለት በሚል ርዕስ በቅጽ 1 ያልተካተቱ ሰዎች በቅጽ 2 ይካተታሉ፡፡
ከእነዚህም አንዷ ዘላለም ቱሉ ናት፡፡
የሬድዮ
አድማጮች በድምጽ ችሎታዋ አይዘነጓትም፡፡ በተለይ ፋና ሬድዮ በዓ.ም
ሲመሰረት ከመስራች ጋዜጠኞች አንዷ ነበረች፡፡ በፕሮግራምና ዜና አንባቢነት
የሙያ መስኩን በወጉ አሟሽታለች፡፡ በ27 አመት የጋዜጠኝነት ቆይታዋ
ከሬድዮ ዜና አንባቢነት እስከ ክፍል ኃላፊነት የዘለቀችው ጋዜጠኛ ዘላለም ቱሉ ዛሬም ለጋዜጠኝነት የጠለቀ ፍቅር እንዳላት ትናገራለች፡፡
በአሁኑ ሰአት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እያገለገለች ሲሆን ታሪኳም እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡
እንደመንደርደርያ
ጋዜጠኛ
ዘላለም የተወለደችው ሀምሌ 5 1967 ዓ.ም ሲሆን የትውልድ ስፍራዋም
አዲስ አበባ ነው፡፡
አባቷ በሶማሌና ኮርያ ዘመቻ ለአገር ክብር የዘመቱና በኋላም በጦርነት የተሰዉ
ነበሩ- የ10 አለቃ ቱሉ ገመዳ፡፡ እናትዋ ሙሉ ሮባ ይባላሉ፡፡ ጋዜጠኛ ዘላለም ለቤቱ አምስተኛ ልጅ ነች፡፡
በልጅነቷ
ፈጣን ፤ጨዋታ ወዳድ ፤ ከሰው ጋር ተግባቢ ፤ ከመሆኗ የተነሳ እኩዬቿን ካገኘች የምታጠፋው ረጅም ጊዜ ምንም አይመስላትም፡፡ ለቤተሰቦቿ ታዛዥ እናቷን አጥብቃ የምትወድ
ነች ፡፡
በጥበብና
ጥበበኞች መሀል ሽሮሜዳ የተወለደችው ዘላለም ቱሉ ከጎረቤት አልፋ ጓደኛ ብላ ለያዘቻቸው ሁሉ ፍቅሯ የተለየ ነው፡፡ ሁሉንም በዕኩል የምትመለከት ሳቂታና ደስተኛ ነች ፡፡ በስፔን ኤምባሲ አቋርጠው
ቁልቁለቱን መድሀኒለም ቤተክርስቲያንን ይዞ ዞሮ በአሜሪካ ኤምባሲ ቢመለሱ የዘላለም የልጅነት ባልንጀሮች መገኛ ነው ፡፡
ጨዋታ
ወዳድነቷ ሳይሆን አልቀረም በመጀመርያ ደረጃ የተማሪነት ጊዜዋ በዘፋኝነት
ስራ ቶሎ ድምጽዋን እንድታሟሽ እድል የፈጠረላት፡፡
ዘላለም
ከ1ኛ እስከ 8ኛ ያለውን የመጀመሪያና መለስተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህርቷን የተከታተለችው በቀድሞ አምሃ ደስታ በአሁኑ (እንጦጦ አምባ) ተብሎ በሚጠራው ትምህርት ቤት ነበር፡፡
ከመደበኛ
ትምህርት በተጓዳኝ በትምህርት ቤቱ የሙዚቃ ክፍልም ትሳተፍ ነበር፡፡ በሙዚቀኛነት በተለይም የዓመቱ ማጠቃለያ (የወላጆች ቀን) ዘላለም በጉጉት ከምትጠብቃቸው
ቀናት መካከል ቅድሚያ ይሰጣቸዋል፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ትምህርት ቤቱን ወክለው በሚቀርቡት የመድረክ ዝግጅቶች ከዕኩዮቿ ጋር
የመሳተፍ ዕድል ስለምታገኝ ነው፡፡
ጋዜጠኛ
ዘላለም ቱሉ፣ በትምህርት ቤቱ መድረኮች የወቅቱን ድምጻዊያን ዘፈኖች በልጅነት ቅላጼ ከሚያቀርቡት አንዷ ነበረች፡፡ ከጊዜ በኋላ
መክሊቷ ሆኖ በድምጻዊነት የዘለቀችው ህብስት ጥሩነህና መስከረም ጌታቸው ከተባሉ አጋሮቿ ጋር መድረኩን
ያደመቁበትን ጊዜ ስታስታውስ ከልጅነት ጊዜዋ ትልቁ ምዕራፍ አድርጋ
ነው፡፡
የዘላለም
የአንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቆይታ መደበኛውን ትምህርትና በተለያየ አጋጣሚ የሚገኘውን የመዝናኛ መድረክ ተሳትፎ
በማጣመር ተጉዛ በ1983 ዓ.ም የስምንተኛ ማጠቃለያ ፈተና ወስዳ
በማለፉዋ ተፈጸመ፡፡
የልጅነት
የትምህርትና የመዝናኛ (ሥነ-ጽሁፍ) ዝግጅት ተሳትፎዬ እንደተጠበቀ ሆኖ በመኖርያ ቤት እናቴን በማገዝ የነበረኝ ሚናም ቀላል አልነበረም
ትላለች ዘላለም፡፡
·
በልጅነት
አዕምሮ በጭላንጭል የታየው የሥነ-ጽሁፍና የሙዚቃ ተሳትፎ እንጦጦ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤት ስትገባም ይበልጥ ዳበረ፡፡
የጋዜጠኝነት ሙያን የምትቀላቀልበት አጋጣሚ የተፈጠረው የሁለተኛ
ደረጃ ትምህርቷን በመከታተል ላይ እንዳለች ነበር::
ጊዜው 1987 ዓ.ም ህዳር ወር ላይ ሬዲዮ ፋና ስርጭቱን በአዲስና በተሻሻለ አደረጃጀት ጀምሮ የነበረበት
ስለሆነ ለዘላለምም መልካም አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡ በልጅነት የተጀመረው ጥረት ዕውን ወደ መሆን ተሸጋገረና የሚዲያ ሥራዋንም በአንባቢነት
ጀመረች ፡፡
በዜናና ፕሮግራም አንባቢነት የጀመረው የሚዲያ ኢንዱስትሪ ሥራ
በሂደት አድጎ እስከ ህዳር 1997 ዓ.ም ረዳት አዘጋጅ ሆና እስከመስራት የደረሰችበት ሆነ፡፡
የፋና ሬዲዮ በወቅቱ አዳዲስ ፎርማቶች የቀረፀበትና ታታሪ በሆኑ
ባለሙያዎች መደራጀት የጀመረበት ስለሆነ በአድማጮች ዘንድ ተወዳጅ ጣቢያ ነበር፡ የጣቢያው ተወዳጅነት በህብረተሰቡ ውስጥ ያሉ አብይ
ጉዳዮችን የሚያስተጋባ መሆኑም ጭምር ነው፡፡
ዘላለምም ያንን ወቅት ስትገልጸው የጋዜጠኝነትን ሙያ የተማርኩበትና ከባልደረቦቼ ጋር ዘመን ተሻጋሪ ልምድ ያገኘሁበት ነው ትላለች፡፡ በቆይታዋም
በአድማጭ ዘንድ ታዋቂ የሆኑና አሳታፊ በሆኑ ፕሮግራሞች ዝግጅትና አቅራቢነት ተሳታፊ ነበረች፡፡
የማለዳና
ምሽት ዜና፣ የህግና ፍትህ ፕሮግራም የአርብ ምሽት፣ የቅዳሜ ማለዳ አብረን እናረፋፍድ ቅንብሮች በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩረው
ሳምንታዊው የሳሪሱ ስዩም የሃተታ ጽሁፍን በማቅረብ የሰራችበትን
ጊዜ የጋዜጠኝነት ዘመኔ መሰረቶች ብላ ከምትገልጻቸው ፕሮግራሞች መካከል ዋና ዋናዎቹ
ናቸው፡፡
በሴቶች
ፕሮግራም አዘጋጅነት ፣ የከርሞ ሰው የሚል መጠርያ የነበረውን የህጻናት ፕሮግራም በአስተባባሪነት መርታለች፡፡ ይህ ሬዲዮ ፋና ነው የሚለውን የጣቢያው የመክፈቻ ድምጽም በአንድ
ወቅት የእርስዋ ነበር፡፡ በእነዚህና በሌሎቹም የጣቢያው ዝግጅቶች ጊዜን፡ ጥረቴን ፡እንዲሁም ትጉህ ባልደረቦቼንና መስርያ ቤቴን
አስታውሳለሁ ትላለች፡፡
የፋና ቆይታዋ በልምድና የተፈጥሮ ተሰጥኦ ከመስራት ባሻገር በትምህርት
ራስዋን ያጎለበተችበት ጊዜም ነው፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ያጠናቀቀችው በስራ ላይ ሆና ነው ፡፡ ቀጥላም ከኢትዮጵያ መገናኛ
ብዙሃን ማሰልጠኛ ኢኒስቲቲዩት አሁን (አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) በሬዲዮ ጋዜጠኝነት (Radio Journalism) በዲፕሎማ ተመርቃለች::
ጋዜጠኛ ዘላለም ቱሉ አሁን ድረስ የምትታወቅበት ማራኪ ድምጽና
ቅላጼ በአማተርነት ጀምሮ በሂደት ተገርቶ በትምህርትም ዳብሮ በመታወስ የቀጠለው በተጠቀሱት ጅማሮና ሂደት አልፎ ነው፡፡
በፋና ሬዲዮ የጋዜጠኝነት ሥራዋን ጀምራ ያዳበረችው ጋዜጠኛ ዘላለም
ቱሉ በህዳር ወር 1997 ዓ.ም መስርያ ቤቱን ለቀቀች፡፡ ለአንድ
ዓመት ኢኒሼቲቭ አፍሪካ በሚባል መግስታዊ ባልሆነ ድርጅት ሴቶችና ምርጫ ላይ በሚያተኩር ስራ የፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ሆና በመቀጠር
ሰርታለች፡፡ በዚህ ስራዋ ተጨማሪ አቅም የሚሆናት አጋጣሚ እንደተፈጠረና ዳግም ወደ ጋዜጠኝነት ሙያ ለመመለስ መቻሏን ትናገራለች፡፡
ጊዜው 1998 ዓ.ም አጋማሽ ነበር፡፡
የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለዜና አንባቢነት የቅጥር ማስታወቂያ ያወጣል
፡፡ ይህን ማስታወቂያ የተመለከተችው ዘላለም ለመወዳደር ተመዘገበች፡፡ በወቅቱ እነ ተመስገን በየነ ፣ በላይ በቀለ፤ መሰለ ገብረህይወት እና ሌሎችም ለውድድር የቀረቡበት ነበር፡፡ ዘላለምም ፈተናውን
አልፈው ከተቀጠሩት መካከል አንዷ ለመሆን በቃች፡፡ በተቀጠረችበት የቴሌቪዥን የዜና አቅራቢነት የስራ መደብም ለዘጠኝ ወራት ያህል
ከሰራች በኋላ በጊዜያዊ ቅጥር የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን ተቀላቀለች፡፡ ጋዜጠኛ ዘላለም
በሂደት ቋሚ ሆና በፕሮግራም አዘጋጅነት ማገልገል ጀመረች፡፡
ከመስከረም 1999 ዓ.ም ጀምሮ በረዳት አዘጋጅነት ስታገለግል
ቆይታ በሂደት በዶክመንተሪ ፕሮግራም አዘጋጅነት በከፍተኛ ኤዲተርነት
ሰርታለች፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ዲፓርትመንት ኃላፊ ሆና በመስራት ላይ ትገኛለች፡፡
ዘላለም ቱሉ ከኃላፊነቷ በተጨማሪ ከሙያው ሳትርቅ በሬዲዮ ዜና አቅራቢነትና በቴሌቪዥን ፕሮግራም ዝግጅት አልፎ አልፎ ትሳተፋለች፡፡
የሬዲዮ ጋዜጠኛ ዘላለም ወደ ቴሌቪዥን ከመጣች ጀምሮ ከጊዜና
ሙያው ጋር የበለጠ ለመቀጠል በትምህርት ራስዋን ማብቃትን ቀጥላ በጋዜጠኝነትና ኮሚኒኬሽን ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በመጀመርያ ዲግሪ
ተመርቃለች፡፡
በሙያው
ሌላ ከፍታ
በዜና አቅራቢነት የተጀመረው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቆይታ በሂደት
ወደ መደበኛ ሳምንታዊ ፕሮግራሞች አሻገራት፡፡
ከሬዲዮና ቲቪ አንድ መሆን በኋላ ከምታዘጋጃቸው ፕሮግራሞች መካከል
ቱሪዝም ለልማትና በሬዲዮ ታዋቂው የኢትዮጵያን እንቃኛት ፕሮግራም
አንዱ ነበር፡፡
በዚህ ፕሮግራም የተለያዩ የአገራችንን አካባቢዎች መልከአምድር
፣ ገዳማትን የህዝቦች አኗኗር ባህላዊ እሴቶች ህዝባዊ በዓላትና የመሳሰሉትን
ርዕሰ- ጉዳዮች በፕሮግራሙ ስትሰራ ቆይታለች፡፡
በዚህ ፕሮግራም አብረዋት ሲሰሩ የነበሩ በተለይ በሙያው ረጅም
ጊዜ ካሳለፈው አስፋው ገረመውና፣ በቀለ መንገሻ እንዲሁም ከወጣቶቹ እሸቴ በቀለ፡ተስፋዬ ከበደና ዳንኤል ፀሀይ ጋር የነበራትን የቡድን ሥራ ብዙ የተማረችበት እንደነበር ታስታውሳለች፡፡
ሁለገቧ ጋዜጠኛ ዘላለም ቱሉ የበርካታ ውጤታማ አርሶአደሮች የግብርና
ሥራና ህይወታቸው የተዳሰሰበት ፕሮግራሞችንም በሰፊው ታዘጋጅ ነበር፡፡
የምስራቅ ሸዋ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች መስኖ ተጠቃሚ አርሶአደሮች የጂማና ጉራጌ
ዞን፣ የአርሲና የባሌ የተለያዩ ወረዳ አርሶአደሮች የሰርክ ሥራና
የቤተሰብ ኑሮ ሁኔታ የተዳሰሰበት በርካታ ፕሮግራሞችን ሰርታለቸ፡፡ አብዛኛዎቹ የመስክ ሥራዎች የተለያየ የአየር ንብረት ያለባቸውን
አካባቢዎች ያሸፈነ ሲሆን ረጅም የእግር ጉዞ ግድ በሚልበት ቦታዎችም ከሙያ አጋሮቿ ጋር በመሆን መወጣት የቻለች ነች::
በባህልና ቱሪዝሙ ዘርፍ የበለጠ በተሻለ አቅም እንድትሰራ ዕድሉን ያገኘችበት ነበር፡፡ በተቋሙ ከሚሰሩ
የቱሪዝም ፕሮግራሞች በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ትብብር ይሰራ የነበረው
ቱሪዝም ለልማት የበለጠ የምትታወቅበት ስራዋ ሲሆን በብዙዎችም
እንድትታወቅ የቻለችበት ነው ፡፡
ዘላለም ጆሮ
ገብ በሆነው ተስረቅራቂ ድምፅዋ የሃረሪ ክልል ባህላዊ እሴቶች የሆኑትን የጀጎል ገፅታ፣ የሀረሪዎች
ባህላዊ ምግቦችና የሠርግ ሥነ-ሥርአት ፤ የመኖሪያ ቤታቸው አሰራር እንዲሁም በዓመት አንዴ የሚከበረውን የሸዋልኢድ
በዓልና ሌሎችንም ቅንብሮች አዘጋጅታ አቅርባለች ፡፡ በዚህ ብቻ አታበቃም፡፡ በለምለምነቷ
ከምትታወቀው የደቡብ ክልል የጋሞዎች መንደር ዘልቃ አሉ የተባሉ ባህሎቻቸውን ከሴቻ እስከ ሲቀላ፡ ከቤሬ ተራራ እስከ ወረቴ መንደር በማስቃኘት የጋሞን ትውፊቶች ለተመልካች ያቀረበችበት ፤ የሃዲያ የዘመን
መለወጫ ያሆዴ በአል ከሀድያዎች መንደር የተዘገበበት ፤ ሞቅ ደመቅ ባለችው ወላይታ በባህላዊው አልባሳት ደምቃ የወላይታዎች እሴቶች
የሆኑትን ባህላዊ ሙዚቃና የአመጋገብ ሥርዓት የቃኘችበት ፤ የአርሲ ባህላዊ የሰርግ ስርዓት ፤ በቤንሻንጉል ክልል የሼህ ሆጀሌ ታሪክና በዓመት አንዴ በደማቅ ሁኔታ የሚከበረውን ያመሰራ በአል ያስቃኝችበት
ባህላዊ እሴቶችን የሚያንጸባርቁ ቅንብሮችንና ሲምፖዚየሞችን በተደጋጋሚ ያስተዋወቀች ናት ፡፡
የቢሾፍቱ ሀይቆችና ታሪካቸው ፣በደማቅ ሁኔታ የሚከበረው አመታዊው የእሬቻ በዓል የተለያዩ ገዳማትና አድባራት ሃይማኖታዊ
ስርአቶችና የደብሮች ኪነ- ህንጻ ጥበብን የተመለከቱ የዶክመንተሪ ቅንብሮችን በማዘጋጀት ተመልካቹ ስለ ጉዳዩ ግንዛቤ እንዲያገኝ
ጥረት ማድረግዋን ትናገራለች፡፡ ከእነዚህ መካከል በ4ተኛው መቶ ክፍለ-ዘመን እንደተቆረቆረ የሚነገርለት የዋሻ ሚካኤል፡ በአጼ ሚኒሊክ
ዘመነመግስት ለመጀመሪያ ጊዜ የመኪና መንገድ የተዘረጋላት በኪነህንፃ አሰራርዋ በቀደምትነት የምትታወቀዉ አዲስዓለም ማርያም ፤ በእንጦጦ
ማርያም የሚገኘዉ የአጼ መኒሊክ ቤተመንግስት፡ ከአለት ተፈልፍላ የታነፀችዉ አዳዲ ማርያም ይጠቀሳሉ፡፡
የማዜ ፡የነጭሳር፡የአብጃታ ሻላ፣ ብሄራዊ ፓርኮች፣ የዝዋይ የወፍ ጎጆና የገሊላ ደሴት፡ የሰንቀሌ የቆርኬዎች መንደር ነባራዊ ገጽታ በዘላለም
ተፅፈው በማራኪ ድምጽዋ ተተርከዋል፡፡
ዘላለም፣ በጋዜጠኝነት ያሳለፈችው ጊዜ የልጅነት ህልሟን ያሳካችበት
አድርጋ ትወስዳለች፡፡
ከባልደረቦቿ ጋር ሆና ያሳለፈቻቸው ጊዜያትም እጅግ ትዝታን የሚያጭሩ
በመሆናቸው ምንግዜም የማትረሳቸው ናቸው፡፡
እየተቀየረ በሚሄድ ጊዜና ሁኔታ ውስጥ በርካታ ማህበራዊ ግዴታዎችን
እየተወጣች የኢንዱስትሪውን ቆይታ በትምህርት ለመደገፍ ያደረገችው ጥረት ለጉዞዋ መሠረት እያጸና ያገዛት መሆኑን ትናገራለች::
ከእርሷ አልፋ ሌሎች በትምህርት እንዲተጉ አብዝታ ታነሳሳና ትመክር
ነበር::
ዘላለም በማህበራዊ ህይወቷ በመቀራረብና በመግባባት መርህ ታምናለች::
በትዳር ከ25 ዓመታት በላይ የቆየች ሲሆን ከባለቤቷ ጋዜጠኛ ተመስገን ገ/ህይወት አንድ ሴት ልጅ አፍርተዋል፡፡ እርሷንም አሳድገው እስከ2ኛ ዲግሪ አድርሰው ድረዋል፡፡
ዘላለም ቱሉ እዚህ እንድትደርስ ትልቁን ድርሻ የነበራቸው ባለቤቷ ተመስገን ገብረህይወት እዲሁም ቤተሰቦቿ ፤ የሥራ ባልደረቦቿ ዛሬ ቅርቤ የምትለው ገጣሚና ጋዜጠኛ መስፍን አሸብር ፣ጋዜጠኛ ተፈራ በፍቃዱ(በህይወት
የሌሉ) እንዲሁም አጋፋው ጋዜጠኛ አስፋዉ ገረመዉ ሁሌም ለኔ ስኬት
መሰረት ናቸውና አመስግናቸዋለሁ ትላለች ፡፡ ዘላለም ቱሉ በሚኖራት ቀሪ ግዜዋ
ከጋዜጠኝነቱ ሳትርቅ በእናቶችና ህፃናት
ላይ የሚያተኩር የበጎ አድራጎት ስራዎች ላይ ለማሳተፍ እቅድ አላት፡፡ ዘላለም ቱሉ በጋዜጠኝነት ሙያዋ በቆየችባቸው
27 አመታት ደከመኝ ሳትል ሙያዋን ወድዳ መስራቷን ብዙዎች ይመሰክሩላታል፡፡ ጋዜጠኛ ኢዮብ እሸቱ፤ ከኢቲቪ ፤ ጋዜጠኛ በቀለ መንገሻ
ከሬድዮ እንዲሁም ሺበሺ አለማየሁ ከፋና ቲቪ በሰጡት አስተያየት ዘላለም ብዙ የለፋችና የጋዜጠኝነት ታሪኳም አስተማሪ መሆኑን መስክረዋል፡፡
ጋዜጠኛ ተስፋዬ አበበ በኢትዮጵያ ሬዲዮ : በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን እና በኤፍ ኤም 97.1 ከሪፖርተርነት እስከ ማስተባበሪያ ባሉት
የስራ መደቦች ላይ ሰርቷል: አሁን በኤፍ ኤም 97.1 በልዩ ልዩ ማስተባበሪያ በኃላፊነት እየሰራ ይገኛል፡፡ ስለ ዘላለም ቱሉ የሚከተለውን
ሀሳብ ሰንዝሯል፡፡
‹‹…….ከጋዜጠኛ ዘላለም ቱሉ ጋር በትምህርታዊ እና ዶክመንተሪ
ክፍሎች ከ3 አመት በላይ አብረን ሰርተናል:: በተለይ ኢትዮጵያን እንቃኛት እና ቱሪዝም ለልማት የተሰኙ ባህል እና ቱሪዝም ላይ
ያተኮሩ ፕሮግራሞችን እንሰራ ነበር:: የምትሰራቸው ፕሮግራሞች ጥሩ እና በሰዎች ዘንድ የሚወዳዱ ነበሩ:: የስክሪፕት አፃፃፍ/ዝግጅቷ
እና አነባበቧ/አቅራረቧ ፕሮግራሞቿ በብዙዎች ዘንድ ተመራጭ እንዲሆኑ አድርጓል ብዬ አስባለሁ::
ከስራ ባልደረባዎቿም ሆነ በስራ ከምታገኛቸው የፕሮግራም አካላት
ጋር ያላት ተግባቦት እና ቀናነትም ውጤታማ ስራዎችን እንድትሰራ አድርጓታል፡፡ በተረፈ ያላወቀችውን ጠይቃ ለመረዳትም ሆነ ሀሳብ እና አስተያየቷን
በግልፅ የማቅረብ ክህሎቷ የሚደነቅ ነው፡፡ትሁት ፣ ቅን እና ስራ ወዳድ ስትሆን አሁንም ከጋዜጠኝነቱ ውጭ በኃላፊነት ቦታ ላይ ሆና
በኤፍ ኤም 97.1 ዜና መፅሄት ታነባለችና ይህ ለጋዜጠኝነት ሙያ ያላትን ፍላጎት እና ተነሳሽነት ያሳያል፡፡ በአጠቃላይ ዘላለም በተለይ ለቱሪዝም ጋዜጠኝነት የተፈጠረች ናት ማለት ይቻላል፡፡››
ሲል አስተያየቱን ለግሶናል፡፡
መዝጊያ…..
ዘላለም ቱሉ በአንድ በኩል ልጅ አሳድጋ ለቁምነገር አብቅታ ደግሞ ሙያዋን ወዳ
እየሰራ የቤተሰብ ኃላፊ ሆና ዛሬም ፈጣሪዋን ታመሰግናለች፡፡ ብዙ የለፋች ግን ብዙ ያልተነገረላት ዘላለም በሚድያው ዘርፍ ከዚህ
በላይ አቅሟን አጎልብታ ሀገሯን የማገልገል ህልም ሰንቃለች፡፡ ይህም ያለ አንዳች ጥርጥር ከፈጣሪ ጋር ይቻላል፡፡ ተወዳጅ ሚድያ
እና ኮሚኒኬሽን በሚድያው ዘርፍ ሌሎችን ሲያደምቁ የነበሩ ጠንካራ የሚድያ ሰዎችን በህይወት እያሉ ሊያስታውስ እነሆ በባለታሪኮች
ፈቃድ ላይ የተመሰረተውን የህይወት ታሪካቸውን እያቀረበ ይገኛል፡፡ ከእነዚህ አንዱ የዘላለም ቱሉ ነው፡፡
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ