ፊልም ዳይሬክተር ቅድስት ይልማ 2000ዎቹ
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ‹‹መዝገበ-አዕምሮ›› በሚል ርዕስ የፊልም
ሰዎችን ታሪክ በመጽሀፍ አሳትሞ ለማውጣት እየተዘጋጀ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ቅዳሜ ሀምሌ 30 2014 መዝገበ-አእምሮ የሚድያ ሰዎች ታሪክ መመረቁ ይታወቃል፡፡ ታሪኳ በዚህ ጽሁፍ የሚሰነደው የቅድስት ይልማ ነው፡፡
የፊልም ባለሙያዋ ቅድስት ይልማ
1978 ዓ.ም በሀዋሳ ተወለደች ፡፡ እድገቷ ባሌ ጎባና ሌሎች ቦታዎችም
በመዘዋወር ሲሆን በአዲስ አበባ ከተማ ግን ረግታ ለመቆየት እና ትምህርቷንም ለማጠናቀቅ በቅታለች ፡፡ በትምህርት
ቤት ሚኒ ሚዲያ ክበባት ተሳታፊ የነበረች ሲሆን ከተውኔት ይልቅ ስክሪፕት መፃፍ እና ዳይሬክቲንግ የነፍሷ ጥሪ በመሆኑ የንባብ ክህሎቷን አባቷ ያነባቸዉ በነበሩ ጋዜጦች እና መጽሔቶች አዳብራለች ፡፡ ቅድስት ከህፃናት
አምባ እድገታቸውን ጨርሰው የወጡ ወጣቶች የሚጋፈጡት የህይወት ፈተና ላይ ትኩረቱን ያደረገ ” አሀዱ “ የተሰኘ የመጀመሪያ ፊልሟን
አባቷ በሰጣት ገንዘብ ሰርታ 2001 ዓ.ም በአንጋፋው ብሄራዊ ትያትር ቤት አስመርቃለች ፡፡
አሀዱ ፊልም ከሰዎች ጋር ትውውቅ የፈጠረላት እና ህልሟ እዉን ሆኖ ያየችበት በመሆኑ ለበለጠ
የስራ መነሳሳት ጥረት እንድታደርግ አግዟታል ፡፡ ከአሀዱ በመቀጠል
‹‹ፍቅርና ገንዘብ›› የተሰኘ ሁለተኛ ፊልሟን ስክሪፕት ፅፋ
ኤልያስ ወርቅነህ ዳይሬክት ያደረገዉ ሲሆን ረዳት ዳይሬክተር በመሆን ስለዳይሬክቲንግ የበለጠ ለማወቅ እና ስለ ካሜራ በቂ እውወቀት ለመቃረም ችላለች፡፡
ከዚያም በ 2003 ዓ.ም ጢባጢቤ የተሰኘ በወጣቶች ዳንስ ላይ የተመሰረተ
ፊልሟን ዳይሬክት ያደረገች ሲሆን ፍቅርና ገንዘብ ቁጥር 2 ላይ በድጋሜ በፅሁፍ እና ረ/ዳይሬክተርነት ተሳትፋለች ፡፡ ቅድስት ይልማ
የ 5 ዓመታት ልምድን በማዳበር ከቀድሞ ስራዎቿ በመማር እጅግ አስደናቂና
አነጋጋሪ የነበረ የተመልካችን ዓይን እና ጥርስ ያፈራረቀ ሀገረኛ ለዛ ያለው “ረቡኒ “ የተሰኘ ስራዋን ስክሪፕት በመፃፍና በዳይሬክቲንግ ተሳታፋ ለተመልካች አድርሳለች ፡፡ ይህ
ፊልሟ 2 ወራት የቀረፃ ጊዜን የወሰደ ፣ ከ 7 በላይ Location የነበረው ፣ ሙሉ የቀረፃ ወቅቱ ክረምት ላይ የነበረ ለዳይሬክቲንግ
ትንሽ ፈታኝ ቢሆንም በ 2005 መጨረሻ አካባቢ ተጀምሮ በ
2006 የካቲት 30 ለዕይታ በቅቷል ፡፡ ፊልሙ በ ዓለም አቀፍ ፊልም
ፊስቲቫል ፣ በጉማ ፊልም አዋርድ ፣ በለዛ ሽልማት ላይ በዳይሬክቲንግና
በስክሪፕት ተሸላሚ ለመሆን የበቃም ነበር ፡፡ በፊልሙ ላይ የተሳተፉ ምርጥ ተዋኒያንም የሽልማቱ ተቋዳሾች ነበሩ ፡፡
ከረቡኒ በኋላ “ ከዕለታት
“ የተሰኘ ፊልም የሰራች ሲሆን ቀጥሎም “ መባ “ፊልሟ ለተመልካች ቀርቧል
፡፡ በ 2009 “ ታዛ “ የተሰኘ ፊልም የሰራች ሲሆን
ፊልሙ በዳይሬክቲንግ በለዛ አዋርድ ፣ ጉማ ፊልም
አዋርድ እና ዞዳክ ላይ ተሸላሚ ሆኗል ፡፡ በፊልሙ ላይ የተሳተፉ
ምርጥ ተዋኒያንም ተሸላሚ ነበሩ ፡፡ 2009 ዓ.ም ላይ ተጀምሮ በ 2014 ዓ.ም በአርትስ ቲቪ በመተላለፍ ላይ የሚገኘው “ እረኛዬ
“ የተሰኘው የቴሌቪዥን ተከታታይ ድራማ በስክሪፕት ፅሁፍ እና ዳይሬክቲንግ ቅድስት ይልማ ተሳትፋበታለች ፡፡ የቅድስት ይልማ የፊልም ስራዎች የሀገራችን ገጠራማ አካባቢዎች የኑሮ ዘይቤን
የሚዳስሱ ፣ ባህሎችና ትውፊቶች ላይ ትኩረት ያደረጉ በመሆናቸዉ ተመልካቹ
በቀላሉ ከራሱ ማንነት ጋር ትስስር የሚፈጥርባቸዉና የማይጎረብጡት ናቸዉ ፡፡ ሀገር በቀል እዉቀቶችን የመጠቀም ፣ የራስን ነገር
የማክበርና መለስ ብሎ የማየትና የመሬት ሀብት አጠቃቀምን በፊልሙ
ተመላክቷል ፡፡ እረኛዬ በምርጥ ፊልም ስክሪፕት ተሸላሚም ሆኗል ፡፡
ቅድስት በፊልሙ ኢንዱስትሪ የራሷን ሚና እየተጫወተች ያለች ባለሙያ ስትሆን ምንም እንኳን በየመሀሉ የመከኑ ስራዎች ቢኖሩም 12 የሚሆኑ ፍሬያማ ፊልሞችን ስክሪፕት በመፃፍና በዳይሬክቲንግ ሰርታለች ፡፡ እረኛዬ የሀገራችንን የፊልም ኢንዱስትሪ ያነቃቃ ሀገር ሀገር ፣ ሰዉ ሰዉ የሚሸት ቁምነገር አዘል ተከታታይ ድራማ ነዉ ፡፡
ቅድስት ይልማ በመጪዉ 2015 ዓ.ም የሚለቀቅ ” ዶቃ “የተሰኘ አዲስ ፊልም ለፊልሙ ማህበረሰብ ይዛ እየመጣች ነዉ ፡፡
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ