ሰብለወንጌል አሰፋ 2000ዎቹ 

 ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ‹‹መዝገበ-አዕምሮ›› በሚል ርዕስ የ180 የሚድያ ሰዎችን ታሪክ በመጽሀፍ አሳትሞ ሀምሌ 30 2014 አ.ም  ማስመረቁ ይታወቃል፡፡ በቀጣይ ደግሞ መዝገበ-አዕምሮ ቅጽ ሁለት በሚል ርዕስ በቅጽ 1 ያልተካተቱ ሰዎች በቅጽ 2 ይካተታሉ፡፡ ከእነዚህም አንዷ ሰብለወንጌል አሰፋ ናት፡፡ ሰብለ በኢቲቪ ፤ በኤልቲቪ በአሁኑ ሰአት ደግሞ በዲኤስቲቪ አቦል ቲቪ ላይ በመስራት ላይ ትገኛለች፡፡ የስራ ታሪኳ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

 

 

     የጣና ውሀ እና ሰብለ 

 ሰብለወንጌል  አሰፋ  በ1978 አ.ም ነበር የተወለደችው፡፡ትውልድና እድገቷ  ባህርዳር  ልዩ ስሙ ‹‹ፋሲሎ›› አካባቢ ቀበሌ 15 ነበር፡፡ ሰብለወንጌል ፣ የጣናን ውሃ እየጠጣች ዘንባባዎችን እየተጠለለች አባይን ጠዋት ማታ እያየች የልጅነት ጊዜዋን አሳለፈች።

 አባቷ አሰፋ በቀለ እናቷ ደግሞ እሌኒ መኮንን ይባላሉ፡፡  ሁለቱም የመንግስት ሰራተኛ ናቸው፡፡ ለትምህርት ልዩ አመለካከት  ያላቸው ወላጆች  ስለነበሩ  ሰብለወንጌል በትምህርቷ ብርቱ እንድትሆን ሰርክ ምክር ይለግሱ ነበር፡፡

 ሰብለወንጌል ለቤተሰቡ የመጀመርያ ልጅ ስትሆን አንድ ወንድም እና አንድ እህት አላት፡፡

       ዶርም ቁጥር 304

  ሰብለ እድሜዋ  5 አመት  ሲሞላ  በታሪካዊው አጼ ሰርጸ ድንግል ትምህርት ቤት ፊደልን ሀ ብላ ጀመረች፡፡

  ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷንም በአንጋፋው ጣና ሀይቅ  ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማረች፡፡  እንደሀገሬው ልጆች ብስክሌቷን እያሽከረከረች እንደጣና ልጅነቷ እየዋኘች ድንቅ ጊዜን አሳልፋለች በባህርዳር፡፡

  የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን እንዳጠናቀቀች አንጋፋው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስድስት ኪሎ ካምፓስ ነበር ለመጀመርያ ዲግሪ በመደበኛ የትምህርት ፕሮግራም የገባችው በ1995 ፡፡   ዶርም ቁጥር 304 እና እነዛ ድንቅ ም መቸም የማትረሳውን  የዩኒቨርሲቲ ቆይታዋን ሁሌም እንድትደሰትበት ያደረጉ ነበሩ፡፡ ሰብለወንጌል  እነዚያ ቆይታዎች ከዲግሪው እኩል ብዙ የተማርኩባቸው ናቸው  ትላለች ማስተርሷንም እዛው አዲስ አበባ ዪኒቨርሲቲ  ሰራች፡፡

 

           ህልም መኖር

ጋዜጠኛ የመሆን  የልጅነት ህልሟ  ገና የአምስተኛ ክፍል ተማሪ እያለች ነበር የመነጨው፡፡ ለተማሪዎች አንዳንድ  ጽሁፎችን  እያነበበች ዝንባሌዋን አዳበረች፡፡

 ተጨማሪ ማጠናከርያ ትምህርት የሚሰጣት አንድ የሰፈሯ አስተማሪ  ሁሌም አንብባ ስትጨርስ ‹‹….አንቺ  ወደፊት ጋዜጠኛ ነው የምትሆኚዉ›› ይላትነበር፡፡ በወቅቱ ከትምህርት ዉጭ ያሉ ማንኛውንም ነገሮች ማንበብ ክልክል ነበር፡፡   ሰብለወንጌል አሰፋ ግን  ብዙ ልቦለድ መጽሀፎችን ማንበብ አጫጭር ታሪኮችን መጻፉን ስራዬ ብላ ተያያዘችው፡፡  ያባቷን ሬዲዮ በድብቅ ድምጹን ቀንሶ ማዳመጥ  ጥቁርና ነጭ ቴሌቪዥኑ አሳይቶ   እስኪያበቃ  ማየት ሰብለን የሚያስደስታት ነገር ሆነ፡፡ ቤተሰብ ግን ትምህርቱ ላይ በርቺ እያሉ ይገስጹዋት ነበር፡፡

 

       ሰብለ በቲቪ 

 ሰብለወንጌል  የመጀመርያ ዲግሪዋን  በ1998አ.ም ካጠናቀቀች  በኃላ ለመጀመርያ ጊዜ  ስራ የጀመረችው   በኢትዮጵያ ቴሊቪዥን ነበር፡፡ ጊዜውም በ1999፡፡ የተመደበችውም በዋናነት በሴቶች ፕሮግራም ላይ ቢሆንም በወቅቱ ጣቢያዉ የሴቶች ፕሮግራም ላይ ብዙ ስራዎች የሚሰራ ባለመሆኑ እና በተደጋጋሚ የአየር ሰአቱ በተለያዩ ወቅታዊ ስራዎች ይታጠፍ ስለነበር   በተለያዩ  የዶክመንትሪ ዝግጅቶች፣ የመድረክ ስራዎች ውይይቶች  ላይም በመሳተፍ የተለያዩ የአገራችን ከተሞችም  ተዘዋውራ  ስራዎችን ሰርታለች፡፡

በኋላ ላይ ግን በጣቢያው የሴቶች እና የወጣቶች ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑ ስለታመነበት አዲስ ፎርማት ተቀርጾለት የስያሜ ለውጥ አድርጎ ‹‹ስለሷ›› በሚለው የመጽሄት ፎርማት መሰራት ተጀመረ፡፡  በጊዜው  በነበረው የሴቶች ፕሮግራም ላይ በአዘጋጅነት እና በፕሮግራም መሪነት ለአመታት ሰርታለች፡፡ ይህም ጊዜ ከተመልካቾች ጋር ያገናኛት፣ እንዲሁም በሴቶች ፖለቲካዊ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ ላይ አሻራ  ማኖር እንድትችል በር የከፈተላት አጋጣሚ ነበር፡፡

 የገጠር ሴቶች ህይወት፣ የሴት ልጅ ግርዛት፣ ያለእድሜ ጋብቻ ጠለፋ ባጠቃላይ በበርካታ የሴቶች ጉዳይ ላይ ብዙ ሰርታለች፡፡  ላጭር ጊዜ ቢሆንም በኤፍ ኤም አዲስ እና በኢትዮጵያ ሬዲዮም ላይ ጥቂት ጊዜ ሰርታለች፡፡ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከሪፖርተርነት እስከ አዘጋጅነት ደረጃ ሰርታለች፡፡

  ሰብለወንጌል ኢቲቪ ትሰራ በነበረበት ጊዜ መስሪያ ቤቱ  በየአመቱ የላቀ ዉጤት ያስመዘገቡ ሰራተኞችን በሚሸልምበት  ጊዜም  ጥሩ አፈጻጸም በማስመዝገብ የደረጃ እድገት ብሎም የገንዘብ ሽልማት እና የውጭ ሀገር የስልጠና እድል አግኝታ በጃፓን ቶኪዮ በታዋቂው NHK ቲቪ ለመሰልጠን በቅታለች፡፡ በሀገር ውስጥም በርካታ ሙያዋን ሊያሳድጉ የሚችሉ ስልጠናዎችን አግኝታለች፡፡ BBC አንዱ ነበር፡፡ ኢቲቪ  ከሚያስተላልፋቸው የሴቶች ዶክመንተሪ  ፕሮግራሞች መካከል በአንዱም ከቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ሜዳልያ ሽልማት አግኝታለች ፡፡

 ሰብለወንጌል አሰፋ  ሴቶች አርአያ እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ ብዙ ውጤታማ ስራ አከናውናለች፡፡  በተጨማሪም ፤ያለዕድሜ ጋብቻ  እና የሴት ልጅ  ግርዛትን ፣የህጻናት ጉልበት ብዝበዛ ፣ ከደቡብ ክልል እስከ ሽሮሜዳ በዘለቀ ቆይታ የችግሩን ስፋት ማሳየት ችላለች፡፡ አስከፊውን የስደት ጉዞ የሚያሳይ ዶክመንተሪ ለጣቢያው አበርክታለች፡፡

          አርትስ ቲቪ እና ሰብለወንጌል

 ሰብለ ከ 10 አመት በላይ የሰራችበትን ተቋም ኢቲቪን በሰላም ተሰናብታ  ኤልቲቪን በአርታኢነት እና በፕሮግራም ክፍል አስተባባሪነት ተቀላቅላ  ስራ ጀመረች፡፡ ኤልቲቪ ሞዛይክ የመዝናኛ ፕሮግራም ላይ በፕሮግራም መሪነት  እና በተመልካች ዘንድ ተወዳጅነትን ያተረፈው ኢትዮ ሌዲስ ላይ ሙሉ አቅሟን ለማሳየት ሞክራለች፡፡

በዚህ ጣቢያ ስትሰራ   ባሳየችው የስራ አፈጻጸም ምክንያት ወደ ቱርክ ተልካ በታዋቂው TRT  ቴሌቪዥን እና ሬዲዮ ጥሩ እውቀትን ለመገብየት ችላለች፡፡

ተቋሙ በግል ጉዳዩ ከተዘጋ በኋላም MultiChoice Ethiopia  አቦል ቻናል executive program acceptance ሆና እየሰራች ትገኛለች፡፡

 ሰብለ እዚህ ተቋም  ውስጥ ስትሰራ አለማቀፍ ልምዶችን  ለማግኘት ችላለች፡፡ የአሰራር ስልቶችንም ለማጤን የቻለችበት አጋጣሚ ነበር፡፡  ወደ ኬንያ አቅንታም  multichoice  Kenya  ስልጠና የማግኘት እድል ገጥሟታል፡፡  በአሁኑ ሰአት ከዚህ በተጨማሪም በመንሽ ፕሮዳክሽን ውስጥ ‹‹የማማ አፍሪካ›› ፕሮግራም አዘጋጅና አቅራቢ በመሆንም እየሰራች ትገኛለች፡፡ይህ ኩባንያ ትልቅ ህልም ያለው ሲሆን ትልቅ ለማድረግም እየሰራች ነው ፡፡ ሰብለ ወንጌል በዚህ ፕሮግራም ላይ ከባልደረቦቿ ጋር በመሆን ብዙ ሀሳቦችን በማንሳት ፕሮግራሙን ይበልጥ ተወዳጅ ለማድረግ ጥረት አድርጋለች፡፡ ‹‹ማማ አፍሪካ›› በአርትስ ቲቪ የሚቀርብ ሳምንታዊ መሰናዶ ነው፡፡

 ሰብለወንጌል አሰፋ ከጋዜጠኝነቱ ጎን ለጎን የተለያዩ አካላት ጋር ስልጠና  ትሰጣለች፡፡ከብሄራዊ ምርጫ ቦርድ እና ጋር በመሆን የሲዳማ ሪፈረንደም ምርጫ ላይ አስፈጻሚ አካላትን በማሰልጠን ተሳትፎ አድርጋለች፡፡

ማንጎ ፕሮዳክሽን  ከCDC ጋር በመሆን ይሰጥ የነበረውን የግንዛቤ ማስጨበጫ ላይ በእናቶችና ህጻናት አስተዳደግ  ላይ ስልጠና ሰጥታለች፡፡

ሰብለወንጌል በሚዲያው ቆይታዋ በተለይ በሴቶች ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ጉዳይ ላይ ብዙ ስርታለች፡፡ ለምሳሌ አሁን እንደ አገር ትልቅ እንቅስቃሴ የተጀመረበት ህጋዊ ማእቀፍ እንዲኖረው እየተሰራበት ያለው አስተናጋጅ ሴቶች የሥራ ላይ  አለባበስ የማማ አፍሪካ ፕሮግራም ትልቅ ሚና ነበረው ‹‹

 ይህች  ጋዜጠኛ  ሴቶችን ወደ ሚዲያ በማምጣት  ብዙ ሰርታለች፡፡

‹‹ስለሷ›› የሴቶች ፕሮግራም  ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሚዲያ የመጡት ፐሮፌሰር ፈቴን አባይ በዚህ ፐሮግራም ላይ ከቀረቡ በኋላ በያመቱ ታላላቅ ሴቶችን በሚያወዳድረው የኤዉብ ዝግጀት ላይ ታጭተዉ የሁለተኛ ደረጃን አግኝተዋል፡፡ ሰብለወንጌል አርታኢ በነበረችባቸው ጊዜያት ሰርቶ በማሳየት ታምናለች፡፡ የሚድያ ስራ በቡድን የሚከወን በመሆኑ ይህንኑ አውቃ ስራዋን በመልክ በመልኩ ለማስኬድ ትጥራለች፡፡ ሰብለወንጌል አንድ ስራ አየር ላይ ለመዋሉ በፊት ወረቀት ላይ ዝርዝር ጥናቱ ተጽፎ ማለቅ አለበት ትላለች፡፡ በዚህ መንገድ ስትሰራ የሰራችው ትልቅ ርካታን ይፈጥርላታል፡፡ በአሁኑ ሰአት  በአቦል ቲቪ ላይ የሚተላለፉ ፕሮግራሞች ከመረጣው ጀምሮ እስኪተላለፉ ድረስ ያለው ሂደት ላይ በመሳተፍ ሰብለወንጌል የጎላ ድርሻ አላት፡፡

 ሰብለወንጌል ባለትዳርና የሁለት ልጆች እናት ናት፡፡

 ‹‹….በህይወቴ ያገኘሁት ትልቅ ቁምነገር የተፈጥሮ ጸጋ  ቢሆንም እናትነት ብዙ የሰራሁበት ብዙ የተደሰትኩበት የምኮራብት ነው፡፡ ትላለች ሰብለ

  በተጨማሪም  ስለ ህይወት መርኋ ስትናገር ‹‹ እኔ  ብሆን በዚህ ቦታ ብሎ ማሰብ  በየትኛዉም አጋጣሚ ላይ የምመራበት መርህ ነው እስከቻልኩ ድረስ የሰዎችን ነገ የሚከፍቱ እድሎች  ላይ ሁሉ የበኩሌን ለማበርከት እጥራለሁ፤፤ በተለይ በየትኛውም ሁኔታ ላይ ያሉ ነገን አሻግረዉ የሚያዩ ሰዎችን መንገዱ  ሲቃናላቸው ደስታዬ ወደር አይኖረውም›› ትላለች ሰብለወንጌል ፡፡ በሚድያው ስራ ከዚህ በላይ ሰርታ ለውጥ ለማምጣት ትልቅ ህልም ሰንቃለች፡፡








አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች