ይድነቃቸው ሹመቴ
በአዲስ አበባ ከተማ ከሐብተጌዎርጊስ ድልድይ ገባ ብሎ በሚገኘው ሮዛ ሰፈር 1973 ዓ.ም ተወለደ። ይድነቃቸው ለፊልም ፍቅርና ቅርበት የነበረው ገና በልጅነት ዕድሜው ሲሆን እንደዛሬው በየቤቱ ቴሌቪዥን ባልገባበት ወቅት ከታናናሾቹ ጋር በመሆን ቴሌቪዥን እና PCR ባላቸው ዘመዶቹና ጎረቤቶቹ ቤት እየሄደ የፊልም ስራዎችን ይመለከት ነበር። በተጨማሪም የስዕል ዝንባሌ ስለነበረው ትኩረቱን በስዕሉ ላይ አድርጎ ሰርቷል።እንደ ፑሽኪን ባሉ እና በትምህርት ቤት በኩል የሚሰጡ የስዕል ስልጠናዎች ወስዷል ። ሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደደረሰ የቪዲዮ ትምህርት የተማረ ሲሆን ዩኒቨርሳል ኦዲዮ ቪዥዋል በሚባል ትምህርት ቤት ደግሞ አጠቃላይ ከካሜራና ካሜራ ኦፕሬሽን ጋር የተያያዘ ትምህርትን ተምሯል።
በቀለም ትምህርቱ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በአፍሪካ አንድነት አትክልት ተራ፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በአዲስ ከተማ ሲማር በእንጦጦ አጠቃላይ የሙያ ትምህርትቤት በጀነራል መካኒካል ዲፓርትመንት ጠቅላላ የብረት ስራ ለ 3 ዓመታት ተምሯል።
በቶም
ቪዲዮና ፊልም ማሰልጠኛ ገብቶ በትምህርትቤቱ የሚሰጡ ስልጠናዎችን ወስዷል።
የፊልም አፍቃሪው ይድነቃቸው ፊልም / ቪዲዮ ማከራያ ቤት ከፍቶ ከሚወደው ሙያ ጋር የበለጠ ቁርኝት ለመፍጠር እንዲያስችለው የእናቱን እገዛ በመጠየቅ ለስራው የሚያስፈልጉትን እንደ ፊልምና ካሴት የመሳሰሉ ግብዓቶች ሰብስቦ በ1993 ዓ.ም ስራ ጀምሯል።
በከፈተው ቪዲዮ ቤት ለ 9 ያህል ወራቶች እንደሰራ ከቶም የሚሰጡትን ስልጠናዎች በየጊዜው እየወሰደ በትምህርት ቤቱ ከ 1994 ዓ.ም ጀምሮ የፎቶግራፊ መምህር የሆነ ሲሆን በኋላ ቪዲዮ ካሜራ አሰልጣኝ በመሆን ለዓመታት አገልግሏል። ካሜራን ከቀረፃና ከስታይል ባለፈ እንዴት ታሪክ ነጋሪ አድርጎ መጠቀም ይቻላል?
ለሚለው የቀደመ ጥያቄ በራሱ መንገድ ኮርስ ቀርፆ በማውጣት የራሱን ንድፈ ሀሳቦች ወደተግባር በማምጣት እና
በማስተማር በትምህርት ቤቱ የነበረው ተሳትፎ የጎላ ነበር። ይህም በዳይሬክቲንግ
እና በፊልም ስራ ውስጥ የጎላ ተሳትፎ እንዲኖረው ያስቻለው ነበር፡፡
ልዩ ልዩ እውቀቶችን አጣምሮ ማስኬድ የሚቻልበትን አዲስ መንገድ ለመፍጠር በትምህርትቤቱ ጥሩ ተሳትፎ የነበራቸውን ተማሪዎች በመመልመል " የጭቃ ቀለበት " የተሰኘውን አጭር ታሪክ ነጋሪ ፊልም በዳይሬክተርነት ሰርቶ በ 1995 ለዕይታ አብቅቷል። ቀጥሎም ‹‹ሽልማቱ››ና ‹‹የቀለማት ፍቅር›› የተሰኙ ሁለት አጫጭር ታሪክ ነጋሪ ፊልሞችን ሰርቶ ለእይታ አቅርቧል፡፡
የፕሮዳክሽን ፕሮፖዛል ለሚያስተምርበት ቶም ፊልምና ቪዲዮ ማሰልጠኛ በማቅረብ በዳይሬክተርነት የሰራውና ታዋቂነት ያገኘበት " ስርየት " የተሰኘ ፊልሙ በ 1999 ዓ.ም ወርሃ የካቲት ላይ ለህዝብ ዕይታ በቅቷል። ይህ
‹‹ስርየት›› የተሰኘ ፊልም የይድነቃቸውን የዳይሬክቲንክ ችሎታ
ማውጣት እንደቻለም ይነገራል፡፡
ይድነቃቸው ‹‹ስርየት››
ፊልም በፈጠረለት ሰፊ ዕድል ከሀገር ውጪ በመውጣት ብዙ ልምዶችንና ስልጠናዎችን ያገኘ ሲሆን ወደ ቡርኪና ፋሶ በማቅናት በዓለምአቀፍ የፊልም ባለሙያዎች የሚሰጠውን Story teller ፊልም ስልጠና ለ 2 ወራት ወስዷል። ቀጥሎም በናይሮቢ የፊልም ጽሑፍ ስልጠና ያገኘ ሲሆን በደቡብ አፍሪካ የፊልም ሙያ ስልጠና ወስዷል። ከፊልም ፌስቲቫል ጋር ተያይዘው የሚመጡ ስልጠናዎችን በተደጋጋሚ የወሰደ ሲሆን ከሌላው የፊልም ዓለም ጋር ለመተዋወቅም ችሏል። በተጨማሪም
ሌሎች የፊልም ዳይሬክተሮች ያላቸውን ልምድ ለመቅሰም ችሏል፡፡
ይድነቃቸው፣ በ2003 ዓ.ም ኒሻን የተሰኘ ፊልሙ ሲወጣ በአፍሪካ ቀዳሚው በሆነውና ዓለም አቀፍ እውቅና በነበረው የቡር ፌስቲቫል ላይ ይዞ ተገኝቷል። ይህ ስራ በሀገረ አሜሪካን ዋሽንግተንዲሲ ፣ ኒዮርክ ፣ ደ/አሜሪካ ፣ አውሮፖና ብራዚል ለዕይታ ቀርቧል።
የፊልም ባለሙያው ይድነቃቸው በ2003 ዓ.ም ከባለቤቱ ጋር በመሆን በመሰረተው ኩራት Pictures Production ካምፓኒ የፊልምና ማስታወቂያ ስራዎችን በግሉ እየሰራ ሲሆን ከፊልም ጋር የተያያዙ አጫጭር ስልጠናዎችን ከወጣት ባለሙያዎች ጋር በመስጠትና ሀሳቦችን በማጋራት በዘርፉ ላይ ተሰማርቶ እየሰራ ይገኛል።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ