ብርሀኑ ዘሪሁን 1960ዎቹ
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ‹‹መዝገበ-አዕምሮ›› በሚል ርዕስ የ180 የሚድያ ሰዎችን ታሪክ በመጽሀፍ አሳትሞ ማስመረቁ ይታወቃል፡፡ በቀጣይ ደግሞ መዝገበ-አእምሮ ቅጽ ሁለት በሚል ርእስ በቅጽ 1 ያልተካተቱ ሰዎች በቅጽ 2 ይካተታሉ፡፡ ከእነዚህም አንዱ ብርሀኑ ዘሪሁን ነው፡፡ ስለ ብርሀኑ ዘሪሁን ታምሩ ከፈለኝ አጠር ያለ መጣጥፍ አዘጋጅቷል፡፡
“…ስጦታ ኖሮኝ ያቺ መጀመሪያ የፃፍኳት ጽሁፍ ባትታም ወይም ጋዜጣ ላይ ገብቼ ባልጽፍ ስጦታው ላይወጣ ይችላል፡፡ ተደብቆ ይቀር ነበር፡፡” ብርሃኑ በአንድ ወቅት ተናገረው
ጣልያን ዳግም ጦሯን አደራጅታ ከመምጣቷ 2 አመት ቀድሞ በ1926ዓ.ም ጎንደር ከተማ ነው ደራሲ ብርሃኑ ዘርይሁን የተወለደው፡፡ አባቱ ዘሪሁን መርሻ የቤተክህነት ሰው ናቸው፡፡ ቤተክርስቲያንን በዜማ ከማገልገል በተጨማሪ የብራና መፅሃፍትንም ይገለብጡ ነበር፡፡ እናቱ ወይዘሮ አልጣሽ አግደህ የቤት እመቤት እንደነበሩ መዛግብት ያመክላታሉ፡፡ ብርሃኑ ለቤተሰቦቹ የመጨረሻ ልጅ ሲሆን ከእርሱ በፊት 5 እህትና ወንድሞች አሉት፡፡
ስድስት አመት ሲሆነው ብርሃኑ በዘመኑ ልማድ ወደአብነት ትምህርት ቤት ገብቶ መማር ጀመረ፡፡ አባቱ የቤተክህነት አገልጋይ ቢሆኑም በዘመኑም ለቤተክህነት ትምህርት ከፍ ያለ ዋጋ ቢሰጥም ብርሃኑ ለትምህርቱ የሰጠው ዋጋ ከፍ ያለ አይመስልም፡፡ በአብነት ትምህርት ቤት ውስጥ እስከ አስራ ሁለት አመቱ ድረስ ቢዘልቅም እውቀቱ እምብዛም ነበር ይላሉ፡፡ የግእዝ እውቀቱም ወንዝ የሚያሸግር አልሆነም፡፡
የአብነት ትምህርቱን ከመማር ጎን ለጎን ቤተሰቦቹን በስራ ያግዝ ነበር፡፡ ቤት ውስጥ ያሉትን እንስሳት እያገደ ውሎ ሲመለስም እንጨት ለቅሞ ይመጣ ነበር፡፡
ከመፅሃፍ ጋር ትውውቅ
ብርሃኑ የአብነት ትምህርቱን እየተማረ ባለበት ጊዜ ንባብን ስለተለማመደ ከስነፅሁፍ መጻህፍት ጋር መተዋወቅ ችሏል፡፡ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ልቦለድ የሚባለውን የአፈወርቅ ገብረእየሱስ “ጦቢያ” (ልቦለድ ታሪክ) የደብተራ ዘነብ “መፅሃፈ ጨዋታ ስጋዊ ወመንፈሳዊ”ን ማንበብ ችሏል፡፡
እነዚህን መፅሃፎች ብርሃኑ ያነበባቸው ገና በአስራ አንድ አመቱ አካባቢ ነው፡፡ መፅሀፎቹን ያመጣለትም አዲስ አበባ የሚኖር አጎቱ ነው፡፡
የዘመናዊ ትምህርት ፍላጎት
የአብነት ትምህርቱን ሊጠቃልል አካባቢ ቀዳማዊ ንጉስ ሃይለስላሴ ወደጎንደር ሄዱ፡፡ በዛን ጊዜም የዘመናዊ ትምህርት (የመንግስት ተማሪዎች) ተማሪዎች ጃንሆይን ለመቀበል አንዳይነት ልብሳቸውን (ዩኒፎርም፤ የደንብ ልብስ) ለብሰው ሲዘምሩ ሲያያቸው ልቡ ለዘመናዊ ትምህርት ጓጓ፡፡ በዘመኑ የመንግስት ትምህርት ቤቶች የፈረንጅ ተፅዕኖ ስላለባቸው የሃይማኖት መበረዝን ያመጣሉ “ፀረ-ማርያም ናቸው” ተብሎ ይታመን ስለነበር ቤተሰቦቹ ፈቃደኛ ሆነው ወደትምህርት ቤት ሊልኩት አልቻሉም፡፡ ብርሃኑ ግን ለመንግስት ትምህርት የነበረው ጉጉት ከፍ ያለ ስለነበር በልቡ ሲያሰላስለው ቆይቶ አንድ ቀን በኪሱ 50 ሳንቲም ብቻ ይዞ ጉዞ ጀመረ፡፡ እራሱ ብርሃኑ በዚህ ጉዳይ ላይ እንዲህ ብሏል
“ምንም እንኳ ቤተሰቦቼ ሃሳቤን እንደተቃወሙት ቢገባኝም የፈለገው ይሁን ብዬ በልጅነቴ መኮብለል አለብኝ አልኩና ወሰንኩ፡፡ ሃምሳ ሳንቲም አጠራቅሜ ወደባህርዳር ከተማ አቀናሁ፡፡ ባህርዳር ከተማ ስደርስም በጉዞ በጣም ተዳክሜ ስለነበር አረፍ አልኩ”
ከጎንደር የተጀመረው የእግር ጉዞ ባህርዳር ሲያደርሰው ብርሃኑ ደክሞት ስለነበር ወደአንድ ቤተክርስቲያን ደጃፍ ተጠግቶ ዕረፍት አደረገ፡፡ (ምናልባትም ወደጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ሳይሆን አይቀርም) በዛም በትውልድ ቀዬው የጀመረውን የአብነት ትምህርት መከታተል ጀመረ፡፡ ለነፍስ መያጃ የምትሆን የዕለት ጉርሱን ፍለጋም ከሌሎች የአብነት ተማሪዎች ጋር እየወጣ “በእንተ ማርያም ተዘከሩኝ” እያለ እየለመነ ያገኝ ጀመር፡፡ (ይህ አይነቱ ልምድ በተማሪ ቤት ዛሬም ድረስ ያለ ነው፡፡ እንደውም ተማሪ በማርያም ስም ለምኖ ካልበላ ትምህርት አይገለፅለትም ይባላል)
በዚህ ሁኔታ በባህርዳር አራት ወር ከቆየ በኋላ ከቤቱ የኮበለለለት ዘመናዊ ትምህትን መቀላቀል አልቻለም፡፡ ጎንደር ያሉት ቤተሰቦቹ ናፍቆትም በልጅነት ልቡ ላይ እየበረታበት ሲመጣ ወደ ጎንደር ተመለሰ፡፡
ጎንደር ሲደርስ እናቱ በፅኑ ታመው አገኛቸው፡፡ የህመማቸውም መነሾ ልጄ ብርሃኑ ሞቷል ከሚል ጭንቀት ነውና ብርሃኑ ተበሳጨ፡፡ እናቱም ብዙም ሳይቆዩ አለፉ፡፡ የብርሃኑ ፀፀትም ተባባሰ፡፡ አባቱም የብርሃኑን ከፍተኛ የዘመናዊ ትምህርት መሻት ለዛም ያለውን ቁርጠኝነት ስላዩ ወደ ዘመናዊ ትምህርት ቤት እንዲገባ ፈቀዱለት፡፡ ብርሃኑ በዚህን ጊዜ በነጦቢያ የጀመረውን ንባብ ተያያዘው፡፡ በተለይ ወንድሙ የሚያመጣለትን ጋዜጦች በስስት ያነባቸው ጀመር፡፡ በዛን ጊዜም የከበደ ሚካኤል መፅሃፎች ለንባብ መቅረብ ጀምረው ስለነበር እየተከታተለ ያነባቸው ጀመር፤ ወደዳቸውም፡፡
ወደ መፃፍ
ብርሃኑ በልጅነቱ የገባበት የአብነት ትምህር ቤት ከፊደል ጋር በሚገባ አስተዋውቆት ስለነበር ትምህርቱን የጀመረው ከሁለተኛ ክፍል ነው፡፡ የቀለም አቀባበሉ ጥሩ ስለነበረም በእጥፍ በእጥፍ ከክፍል ክፍል እየተሸገር በአራት አመት የትምህርትር ቆይታው ስምንተኛ ክፍል ደረሰ፡፡
ስድስተኛ ክፍል በነበረበት ጊዜም ስለአንድ አቶ ብሩ ስለሚባሉ ሙሰኛ ሰው ግጥም ፃፈ፡፡ ግጥሙም በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ላበ ታትማ ለአንባቢ በቃችለት፡፡ በዚህ ብርሃኑ በጣም ተነቃቅቶ ሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮችን እየተንተራሰ ግጥሞችን መፃፍ ጀመረ፡፡
አዲስ አበባ ለከፍተኛ ትምህርት
ብርሃኑ በጎንደር የትምህርት ቆይታው ባሳየው ከፍተኛ የቀለም አቀባበል ተመርጦ በነፃ የትምህርት አድል ወደ አዲስ አበባ መጣ፡፡ ይህ የሆነውም በ1945 ዓ/ም ነው፡፡ በዚህን ጊዜም አስቀድሞ ይፅፍበት ከነበረው ማህበራዊ ጉዳይ ጎን ለጎን የፍቅር ግጥሞችን መጻፍ ጀመረ፡፡ እድሜውም ወደ 20ዎቹ እየተጠጋ ነበር፡፡
በአዲስ አበባ የብርሃኑ ፍላጎት የከፍተኛ ትምህርት መከታተል ነበር፡፡ በዚህም የቴክኒክ ትምህርት ቤት እንዲገባ ተፈቀደለት፡፡ ትምህርት ቤቱ ውስጥ በርካታ አሜሪካውያን መምህራን የነበሩበት ሲሆን አልፎ አልፎም ህንዳውያን መምህራንም ይገኙበት ነበር፡፡ በትምህርት ቤቱ ውስጥም ራዲዮ መካኒክ መማሩን ተያያዘው፡፡
የብርሃኑ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታ ጥሩ መሆኑን ያስተዋለው አንድ ኢራናዊ መምህሩ ደግሞ ከእንግሊዝና ከአውሮፓ ስነፅሁፍ ጋር አስተዋወቀው፡፡ በዛን ጊዜም እን ሼክስፒርን አሌክሳንደር ዱማስን የመሳሰሉ ፀሃፍያንን ማንበብ ጀመረ፡፡ ፅሁፎቻቸውንም በጣም ወደዳቸው፡፡ ወዲያው በትምህርት ቤቱ ውስጥ “ቴክኒ-ኤኮ” የምትል ወርሃዊ መጽሄት መታተም ጀመረ፡፡ ብርሃኑም የመፅሄቷ ዋና አዘጋጅ ሆነ፡፡ በዚህ ጊዜም በአማርኛም በእንግሊዝኛም እየጻፋ በመፅሄቷ ላይ ፅሁፎችን ያሳትም ጀመር፡፡ (የእንግሊዝኛ ፅሁፎቹን መምህራኑ አርትኦት ይሰሩለት ነበር) ከዚህ በተጨማሪም ለአዲስ ዘመን ለዛሬይቱ ኢትዮጵያና ለኤርትራ ድምጽ ጋዜጦች ፅሁፎችን ይሰጥ ጀመር፡፡ በዛው ትምህርት ቤት ውስጥም ተውኔት ጽፎ ለግቢው ማህበረሰብ ለዕይታ አበቃ፡፡ በዚህ ጊዜ ብርሃኑ ማንም ስለተውኔት አፃፃፍ አላስተማረውም ነበር፡፡ በዛው ትምህርት ቤትም ጓደኞቹ ልባቸው ለከጀለቻት እንስት ደብዳቤ መፃፍ ሲፈልጉ ብርሃኑ ይፅፍና በመልሱ እንቁላል ይጋብዙት ነበር፡፡
የቅጥር ስራ
ብርሃኑ የቴክኒክ ትምህርቱን በ1948አ.ም አጠናቅቆ ከክፍሉ አንደኛ ወጥቶ ስለነበር በዛው በቴክኒክ ትምህርቴ ቤት ውስጥ የሰርቶ ማሳያ ክፍል ረዳት ኃላፊ ሆኖ ስራ ጀመረ፡፡ ብዙም ሳይቆይ ይህንን ስራውን ለቅቆ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስር በሚገኘው ካርታ ስራና ጂኦግራፊ ተቋም ውስጥ ስራ ጀመረ፡፡ በዛም ለሁለት አመታት ሰራ፡፡ በ 2 አመት ቆይታው ውስጥም በዛ ይሰሩ ከነበሩት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ጋር ተዋወቀ፡፡ በካርታ ስራና ጂኦግራፊ ተቋም ውስጥ ለ2 አመት ከቆየ በኋላ ጥሩ ደሞዝ ስላገኘ በመከላከያ ሚኒስቴር ውስጥ አስተርጓሚ ሆኖ ተቀጠረ፡፡ በአስተርጓሚነት ስራው ግን ከ3 ወር የዘለለ መቆየት አልቻለም፡፡
ብርሃኑ በልጅነቱ የተጣባው የስነጽሁፍ ፍቅር ስለነበር ፅሁፎችን በፖስታ ቤት በኩል ለዛሬይቱ ኢትዮጵያና ለአዲስ ዘመን ጋዜጦች ይልክ ነበር፡፡ አንድ ቀን እራሱ ፅሁፉን ይዞ ወደ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ቢሮ ሄደ፡፡ ዋና አዘጋጅ የነበሩትን አሃዱ ሳቡሬን አገኛቸው፡፡ እርሳቸውም በወቅቱ አዲስ ዘመንና ኢትዮጵያን ሄራልድን ዕለታዊ ጋዜጣ ለማድረግ ጎበዝ ፀሃፍያንን እያፈላለጉ ስለነበር ሲያገኙት በማስታወቂያ ሚኒስቴር ከፍተኛ ሪፖርተር ሆኖ እንዲሰራ ጠየቁት፡፡ ብርሃኑም ያላንዳች ማወላወል ስራው ተቀበለ፡፡ በ1952 ስራውን ጀመረ፡፡ በዛም ሆኖ 347 ብር እየተከፈለው በጋዜጣው ላይ እየጻፈ የሚወደው ፅሁፍ የሙሉ ጊዜ ስራው ሆነ፡፡ ብርሃኑ ከ1952 እስከ 1954 ዓ/ም ድረስ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ላይ በከፍተኛ ሪፖርተርነትና በምክትል አዘጋጅነት ከሰራ በኋላ በ1954ዓ/ም the voice of Ethiopia /የኢትዮጵያ ድምፅን በዋና አዘጋጅነት ተቀላቀለ፡፡በ1957 ብርሃኑ የአዲስ ዘመን ዋና አዘጋጅ ሆኖ ሲቀላቀል ኢትዮጵያ ድምጽ ጋዜጣን ለቀቀ፡፡ በዚህ ስራውም እስከ 1959 ቆየ፡፡ በ1959 ዓ/ም፣ ግን ከስራው ታግዶ እስከ 1966 ድረስ ደሞዙ ብቻ እየተከፈለው ያለ ስራ ቆየ፡፡ ከዚህ በፊት በ1957 ዓ/ም በሃገር አቀፍ ደረጃ ቁንጅና ውድድር እየተዘጋጀ ነበር፡፡ በወቅቱ እየተቀጣለ ካለው የተማሪዎች እንቅስቃሴ ጋር ይህ የቁንጅና ውድድር የወቅቱ የሀገሪቱ አንገብጋቢ ጉዳይ አይደለም ብሎ ያምን ነበርና ውድድሩ ንጉሱን ድጋፍ ቢያገኝም ከመቃወም አልቦዘነም ነበር፡፡ ቆይቶም በጋዜጣው ላይ በደቡብ አፍሪካ ይደረግ ስለነበረው የእንቁራሪቶች የቁንጅና ውድድር ፅፎ በጋዜጣው ላይ አሳተመው፡፡ ይህ የአሽሙር ጽሁፍ ለስራ ስንብቱ ምክንያ ሆነ፡፡
በ1959ዓ/ም ከስራ ለመሰናበት መነሾው ደግሞ በአቤ ጉበኛ “አንድ ለናቱ” መፅሃፍ ላይ በሰራው የመፅሃፍ ዳሰሳ ነበር፡፡ መፅሃፉ የዳግማዊ ቴዎድሮስን ህይወት የሚቃኝ ታሪካዊ ልቦለድ ነው፡፡ በመፅሃፍ ዳሰሳውም ለንግስና የዘር አጥንት ከሶሎሞን ስርወመንግስት መመዘዝ እንደሌለበትና አቤ በመፅሃፉ ደምና አጥንት ከንጉስ ዘር መመዘዝ አስፈላጊ ስለመሆኑ ስለሚያትት እሱንም ይተቻል፡፡ በወቅቱ የነበረው የንጉሱ ስርአት ደግሞ ከንጉስ ዘር ተመዘዘ ይንገስ የሚል እምነት ስለነበረው ብርሃኑ ከስራው ሊታገድ ችሏል፡፡
ከስራው ከታገደ በኋላ በ1965/66 አካባቢ በሃገር አቀፍ ደረጃ የተከሰተው ድርቅ አሳሰበውና ጉዳዩን በቅርበት ይከታተል ጀመር፡፡ እርሃብተኞች አዲስ አበባ መግቢያ ለገዳዲ አካባቢ ተጠልለው ስለነበር ወደዛው እየሄደ መረጃ ይወስድ ጀመር፡፡ ከዛም ከፍ ሲል ወደወሎ ሄዶ መረጃ መሰብሰብና ማጠናቀር ጀመረ፡፡ ብርሃኑ መረጃዎቹን አሰባስቦ መፅሃፍ ለመፃፍ ሲያውጠነጥን በ1966 ዓ/ም ዳግም የአዲስ ዘመን ዋና አዘጋጅ ሆኖ ወደስራው ተመለሰ፡፡ ተመልሶ በ1970 መኢሶንን የሚደግፍ ፅሁፍ ፅፈሃል ተብሎ ከስራው ታገደ፡፡ መታገድ ብቻም ሳይሆን ታሰረም፡፡ ከእስር ሲፈታም የየካቲት መፅሄት ዋና አዘጋጀ ሆነ፡፡
ስነፅሁፋዊ ስራዎች
ብርሃኑ በማስታወቂያ ሚኒስቴር ተቀጥሮ የሙሉ ጊዜ ስራው ፅሁፍ ብቻ ሲሆን ጎን ለጎን ሌሎች መጽሃፎችን ለመፃፍ ጊዜ አገኘ፡፡ በዚህም በርካታ መጽሃፎችን ጽፎ ለህትመት አበቃ፡፡ በዚህም የእንባ ደብዳቤዎች(?)፣ ድል ከሞት በኋላ (1955)፣ የበደል ፍጻሜ(1956)፣ አማኑኤል ደርሶ መልስ (1956)፣ የቴዎድሮስ እንባ (1958)፣ ጨረቃ ስትወጣ (1959)፣ ብር አምባ ሰበረልዎ (1960)፣ ማእበል የአብዮት ዋዜማ()፣ ማእበል የአብዮት መባቻ (1973)፣ ማዕበል የአቢዮት ማግስት (1974)፣ የታንጉት ሚስጢር (1978) ስራዎቹ ናቸው፡፡
ብርሃኑ፣ በስነፅሁፍ ስራዎቹ ውስጥ የሚከሰት የራሱ ሆነ ዘይቤ አለው፡፤ በተለይም የሚጠቀማቸው አጫጭር አረፍተ ነገሮች መገለጫዎቹ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ስነፅሁፍ ታሪክም ከእርሱ በፊት ተከታታይ መፅሃፍቶችን መፃፍና ማሳተም የተለመደ አልነበረም፡፡ እርሱ በማዕበል ተከታታይ 3 መፅሃፍ የጀመረው ስራ አሁን በሃገራችን ስነ-ፅሁፍ እየተለመደ መጥቷል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ብርሃኑ በተለይም ማዕበልን በሚፅፍበት ጊዜ ነገሩን በደንብ ለመመልከት ሲል እስከ ወሎ ድረስ ደጋግሞ ይሄድና ሁኔታውን ያጠና ነበር፡፡
ብርሃኑ ከመጽሃፍ ስራዎቹ በተጨማሪም የጻፋቸው ተውኔቶች ነበሩት፡፡
ብርሃኑ ለመጻፍ የሚመቸው ብዕር እንደሆነ በአንድ ወቅት ተናግሯል፡፡ በእስኪርብቶ መፃፍ እንደማይወድ በእርሳስ ደግሞ በጭራሽም እንደማይፅፍ እንዲህ ሲል ነበር ተናገረው፡፡
“አንድ ደራሲ ነበረ፡፡ ወለል ላይ ተደፍቶ ካልሆነ በስተቀር መፃፍ ደስ አይለውም፡፡ ተደፍቶ ነው የሚፅፈው…አንዳንዶች ደግሞ .. መፀዳጃ ቤት ገብተው የሚፅፉ አሉ፡፡ እንደዚህ አስደናቂ ልምዶች አሉ፡፡ ሌላው ጂዋጂዌ ላይ ካልተቀመጠ የማይፅፍ አለ፡፡ እኔ እንኳ በአብዛኛው ጠረጴዛ ላይ ቁጭ ብዬ ነው የምጽፈው፡፡ የምፅፍበት ጊዜ ግን ከጊዜ ጊዜ ሊለያይ ይችላል፡፡ በፊት ለምሳሌ ከአራት እስከ ስድስት እፅፍ ነበር-ማታ፡፡ አሁን ግን በተለይ ደግሞ ሰአቱ ከተለወጠ በኋላ .. በአስር ሰአት የገባሁ ጊዜ እስከ አስራአንድ እስከ አስራ ሁለት አርፋለሁወይም በግሬ ትንሽ እጓዛለሁ፡፡ ከአንድ ሰአት እስከ ሶስት ሰአት እፅፋለሁ፡፡ ሌላ ፀባይ ቢኖረኝ በብእር ጉዳይ አስቸጋሪ ፀባይ አለኝ፡፡ ብእር ካልሆነ በስኪርብቶ መፃፍ አልችልም፡፡ በእርሳስማ አልሞክረውም፡፡ አይመጣልኝም፡፡ አረፍተነገሩም አይያያዝልኝም፡፡ ብእሩም ወፍራም ሆኖ ለስላሳ መሆን አለበት፡፡”
የትዳር ህይወት
ብርሃኑ ወደወዳጁ አጥናፍ ሰገድ ቢሮ ጎራ ሲል የአጥናፍ ሰገድ ይልማ ፀሃፊ ሆና የምትሰራውን የሺን ተመለከተ፡፡ እሷም አስቀድማ በስራዎቹ ታውቀው ነበርና ሲመጣ ትደሰታለች፡፡ የሺ ብርሃኑ ይወደኛል ያፈቅረኛል ለትዳርም ይከጅለኛል የሚል እምነት የነበራት አትመስልም፡፡ ብርሃኑ ግን ለአጥናፍ ሰገድ ፤ልጅቷን እንደወደዳት ተናገረ፡፡ አጥናፍ ሰገድም ብርሃኑ ለትዳር እንደከጀላት ነገሯት፡፡ ያልገመተችው ነገር ቢሆንም ከዛን በኋላ ከብርሃኑ ጋር እየተገናኙ ሻይ ቡና መባባል ጀመሩ፡፡ ፍቅራቸው ሲደረጅ ተጋቡ፡፡
ሞት
ብርሃኑ የታንጉት ሚስጢር የታተመ ሰሞን ታሞ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ገባ፡፡ አንድ ወር ከግማሽ አካባቢ ከተኛ በኋላ ከሆስፒታል ወጣ፡፡ ከሆስፒታል እንደወጣ “መንታ መንገድ” የሚል መፅሃፍ መፃፍ ጀምሮ ነበር፡፡ ነገር ግን መፅሃፉ ለህትመት ሳይበቃ ድጋሚ ታመመና ሆስፒታል ገባ፡፡ እለተ አርብ ሚያዝያ 17/1979 አም ከዚህ አለም በሞት ተለየ፡፡
ለዚህ ጽሁፍ ግብአት መረጃ የተሰበሰበባቸው
ማዕቀብ፤ እንዳለጌታ ከበደ (2006)
Black lion; ሬዱልፍ ኬ. ሞልቬር
በፋና ራዲዮ የተተላለፈ ስለደራሲው ህይወት ታሪክ የሚያጠነጥን ዝግጅት (በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ