ጥላሁን ጉግሳ አለሙ/ ሳላይሽ ኢንተርፕራይዝ/

 

በኢትዮጵያ ተጓዥ የቴአትር ታሪክ ውስጥ ብዙ ሊነገርለት የሚገባው ሠው ... ጥላሁን ጉግሳ አለሙ

 

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የቴአትር የፊልም እና የስነ-ጽሁፍ ባለሙያዎችን የህይወት ታሪክ ሲያወጣ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይህንን ተግባራችንን በመቀጠል በቴአትር ዘርፍ  ጉልህ አሻራ አበርክቶ ስላለፈው ደራሲና አዘጋጅ ጥላሁን ጉግሳ አለሙ ጥቂት ልንላችሁ ወደደን፡፡ ጥላሁን ጉግሳ አለሙ ከ10 አመት በፊት ህይወቱ ያለፈ ለ 34 አመታት በኢትዮጵያ የቴአተር ሙያ ላይ በትጋት  ሲሰራ የቆየ ባለሙያ ነው፡፡  ሳላይሽ የቴአትር ኢንተርፕራይዝን ከዛሬ 29 አመት በፊት መስርቶ  ሸፍጥ፣ ሰቀቀን፣ፍትህ፣ቃልኪዳን  እና እናት የተሰኙ ቴአትሮችን ለእይታ ያበቃ በሳል ባለሙያ ነው፡፡ ይህ ባለሙያ ብዙ የለፈ ግን ጥቂት ያልተነገረለት፤ ብዙ ሊጻፍለት ሲገባ ግን  ብዙ ያልታወቀ ታላቅ ሰው ነው፡፡ ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ለሀገር ሰርተው፣ በህይወት ቢኖሩም ባይኖሩም ስማቸው በደማቅ ቀለም ላልተጻፉት  ቅድሚያ በመስጠት ታሪካቸውን ለትውልድ ያቀብላል፡፡  ደራሲና የቴአትር ባለሙያ ጥላሁን ጉግሳ አለሙ ማን ነው? የሚለውን ለማወቅ ከቤተሰቦቹ የሚቀርብ የለምና ቤተሰቦቹ  ተገቢ መረጃ ሰጥተውናል፡፡/ ተጨማሪም መረጃ ይለግሱናል/ ለዚህም በቅድሚያ  የከበረ ምስጋናችንን ማቅረብ እንወዳለን፡፡

 

  ጥላሁን ጉግሳ አለሙ በ1941 አ.ም ተወለደ፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በንጉስ ሚካኤል 1ኛ ደረጃ ተማሪ ቤት፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን  ደግሞ  በደሴ ወይዘሮ ስህን ትምህርት ቤት ተከታትሏል፡፡ በንግድ ስራ ትምህርትም ዲፕሎማውን ተቀብሏል፡፡ ከ1971-1975 በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ አስተዳደር  ዲፕሎማ ተቀብሏል፡፡ ከ1961-1963 አ.ም የትምህርት ሚኒስቴር የአስተዳደር ረዳት ፤ በመቀጠልም ከ1963-1968 በጤና ጥበቃ  የሪከርድና ማህደር አገልግሎት ኃላፊ በመሆን ሀገሩን ያገለገለ ነበር፡፡ ከ1967-1969 በባህል ሚኒስቴር የማሰልጠኛ ዘርፍ ኃላፊ በመሆን የሰራ ነው፡፡  በሀገር ፍቅር ቴአትርም  ለ2 አመታት / 1969-1971 / በአስተዳዳሪነት  አገልግሏል፡፡

 በመቀጠልም ወደ ኢትዮጵያ ፊልም ኮርፖሬሽን በመዝለቅ  የአስተዳደርና ፋይናንስ አገልግሎት ኃላፊ በመሆን ሀገራዊ ግዴታውን ተወጥቷል፡፡ ከ1975-1978 ደግሞ በባህልና ስፖርት ጉዳይ ሚኒስቴር የአስተዳደርና ፋይናንስ  መምሪያ ኃላፊ በመሆን  አገልግሎአል፡፡

ከ1978 ጀምሮ ደግሞ ለ7 አመታት በባህልና ስፖርት ጉዳይ ሚኒስቴር  የስነ-ጥበባትመምሪያ ኃላፊ ሆኖ  በንቃት ማገልገሉን አብረውት የሰሩ ይመሰክራሉ፡፡

 ደራሲና አዘጋጅ ጥላሁን  በ1985 አ.ም ምናልባትም በሀገራችን የመጀመርያ ሊባል የሚችለውን  የቴአትር ኢንተርፕራይዝ ሳላይሽ  የስነ-ጥበባትና ማስታወቂያ  ድርጅትን መመስረት ቻለ፡፡ በዚህም በርካታ ወጣት የቴአትር አፍቃርያን ወደ ሙያው ዘልቀው እንዲገቡ አድርጓል፡፡

    ይህ ለሀገራችን ቴአትር ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል የተባለለት ሰው ከ1972-1980 ባሉት ጊዜያት በምስራቅ ጀርመን ፤ በሶቭየት ህብረት ፤ በምዕራብ ጀርመን ፣ በፈረንሳይ ፣ በቡልጋርያ  በቻይና በርካታ ሴሚናርና ጥናታዊ ጉብኝቶችን ሊያደርግ ችሏል፡፡ይህም የበርካታ ሀገራትን የስራ ተሞክሮ እንደምን እንደሆነ አሳውቆታል፡፡

  ደራሲ ጥላሁን ጉግሳ አለሙ  ‹‹ትዝብት.›› የተሰኘው ቴአትሩን በ1979 አ.ም የዛሬ 35 አመት ደርሶ ያዘጋጀ ሲሆን የታየውም በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ነበር፡፡ በወቅቱ ይህ ስራው እጅግ ተወዳጅ ከመሆኑ የተነሳ ለአንድ አመት ተኩል መድረክ ላይ በቆየበት ጊዜ ከ40,000 በላይ ተመልካች ደስ ብሎት ተመልክቶታል፡፡ በዚህ ቴአትር ላይ የመድረኩ ፀዳል ወጋየሁ ንጋቱ  በመሪ ተዋናይነት ድንቅ ክህሎቱን ያሳየበት ነበር፡፡

ትዝብት በታየ በ3 አመቱ ደግሞ  በ1982 አ.ም ተፈሪ አለሙ  ያዘጋጀው ‹‹ጽናት›› የተሰኘው የጥላሁን ጉግሳ አለሙ ድርሰት ይነሳል፡፡‹‹ ጽናት›› በሀገር ፍቅር መድረክ የታየ ቴአትር ሲሆን  ወደ ክልል ከተሞችም ወጥቶ ከ100,000 ሰው በላይ የተመለከተው ድንቅ ቴአትር ነው፡፡

 ጥላሁን ጉግሳ ከመንግስት የስራ ኃላፊነቱ ለቅቆ በ1984 ሳላይሽ የቴአትር ኢንተርፕራይዝን ሲመሰርት   በቅድሚያ ለመድረክ ያበቃው ቴአትር  ‹‹ሸፍጥ›› የተሰኘውን ነበር፡፡  ‹‹ሸፍጥ›› በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቴአትርና በራስ ቴአትር ከ20ሺህ ህዝብ በላይ ተመልክቶታል፡፡

 በመቀጠል በ1986 አ.ም መስፍን ጌታቸው የጻፈውና ጥላሁን ጉግሳ ለመድረክ እንዲሆን አድርጎ ያዘጋጀው ‹‹ሰቀቀን›› ቴአትር ከተመልካች አእምሮ የሚጠፋ አይደለም፡፡ ይህን ቴአትር በጠቅላላ  90ሺህ ህዝብ ተመልክቶታል፡፡  

ሳላይሽ የቲያትርና የፊልም ጥበብ ኢንተርፕራይዝ "ፍትህን በ1989 ሲያዘጋጅ"፤ ደራሲና አዘጋጅ፦ ጥላሁን ጉግሳ አለሙ፣ ተዋንያን፦ ፍቅርተ ጌታሁን፣ ሰለሞን ሀጎስ፣ ገሊላ መኮንን፣ አበበ ደምሴና  ሌሎችም የተወኑበት ድንቅ ቴአትር ነበር ፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ፋከልቲ  ለ7 ወራት የታየው ‹‹ፍትህ››  በሌሎች ክልሎችም እየተዘዋወረ የታየ ሲሆን ከ85,000 በላይ ህዝብ ተመልክቶታል፡፡

በ1992አ.ም  በደራሲ አብርሀም አማረ የተደረሰውና ጥላሁን ጉግሳ አለሙ ያዘጋጀው ሌላው  ተወዳጅ ቴአትር ‹‹ቃል ኪዳን›› ነው፡፡  ይህን ቴአትር በጠቅላላ 72ሺህ ተመልካች ተመልክቶታል፡፡

በአመቱ በ1993አ.ም  ለመድረክ እይታ የበቃው ቴአትር ደግሞ  ፍጹም ንጉሴ የደረሰውና ጥላሁን ጉግሳ ያዘጋጀው ‹‹እናት››  ቴአትር ነው፡፡ ይህ ቴአትር በቤተሰብ አኗኗ ር ላይ ትኩረቱን ያደረገ  የሀገር መሰረት ቤተሰብ ነው የሚለውን ጭብጥ የሚነግር የቴአትር ስራ ነው፡፡    

 የቴአትር አዘጋጅ እና ደራሲ ጥላሁን ጉግሳ አለሙ በህይወቱ ደስታን ከሚሰጠው ነገር አንዱ ቴአትርን ማዘጋጀት ነው፡፡ ይህን ውስጣዊ ስሜቱንም ለማርካት ለአመታት ታላቅ ተጋድሎ አድርጓል፡፡ ወጣቶች  የድርሰት ችሎታቸውን እንዲያወጡ እድል በመስጠት የታላቅ ሰውነቱን አደራ በሚገባ ተወጥቷል፡፡ ጋሽ ጥላሁን አቅማቸውን  እንዲያወጡ ከረዳቸው የቴአትር ባለሙያዎች መካከል ዶክተር ሱራፌል ወንድሙ ፤ ተዋናይ ተመስገን  አፈወርቅ ፤ አሁን በህይወት የሌለው መስፍን ጌታቸው ይገኙበታል፡፡ ቴአትርን በክፍለ ሀገር እየዞሩ በማሳየት ፈር ቀዳጅ የሆነው የጥላሁን ድርጅት ሳላይሽ በርካታ የክፍለ-ሀገር የቴአትር አፍቃርያንን ስሜት ያረካ ነው፡፡

 ጥላሁን አንድን ቴአትር ወደ ክፍለ ሀገር ከመውሰዱ በፊት በቂ ጥናት ያደርጋል፡፡ ቴአትሮቹ የሚታዩባቸው ከተሞች የህዝብ ቁጥራቸው ምን ያህል እንደሆነ  ጥላሁን ቀድሞ በጽሁፍ ያሰፍራል፡፡ለምሳሌ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል  ቴአትር ለማሳየት መርሀ-ግብር ነድፎ ከሆነ  በፍቼ ፤ በደብረማርቆስ ፤ በዳንግላ በጠቅላላ  በ26 ከተሞች  ምን ያህል ህዝብ እንደሚኖር ያሰፍራል፡፡ በ1990ዎቹ በጻፈው የእቅድ ሰነድ ላይ እንደሰፈረው ያኔ በ26ቱ ከተሞች ከ919 በላይ ህዝብ ይኖራል፡፡ በእንዲህ መልኩ የተመልካቹ ሁኔታ ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል ግምታዊ እሳቤውን ያስቀምጥ  ነበር፡፡ በተጨማሪም በወታደራዊ ተቋማት ፤ በዩኒቨርሲቲዎችና በፋብሪካዎች  ያለውን ተመልካች  ቀድሞ ለማጥናት የተቻለውን ያደርግ ነበር፡፡

 ጥላሁን ጉግሳ በሳላይሽ  ድርጅቱ ውስጥ ሲሰራ ወይም ሲያሰራ  ቴአትሮቹ ቀድመው የሚተዋወቁበትን የማስታወቂያ ስልት በወጉ ይነድፍ ነበር፡፡  ፖስተሮችን ፤ የጥሪ ወረቀቶችን፤  በማሰራጨት ሰው ቴአትር የማየት ጉጉቱ እንዲጨምር አድርጓል፡፡  ይህም ለኢትዮጵያ ቴአትር አንድ አስተዋጽኦ ነው፡፡

ጥላሁን ጉግሳ በ61   አመቱ መጋቢት 11 2003 አ.ም ከዚህ አለም በሞት የተለየ ሲሆን ከወይዘሮ ፒና ቪንቼንዞ ጋር ትዳር መስርቶ  5 ልጆችና 9 የልጅ ልጆች አፍርቷል፡፡ ጥላሁን ጉግሳ አለሙ ታላቁ የቴአትር ሰው ዛሬም አለ፡፡

 መዝጊያ፤ ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ የዊኪፒዲያ ወይም የመዝገበ-አእምሮ የቴአትር ዘርፍ የቦርድ አባላት አቋም የሚንጸባረቅበት ነው ፡፡

 ድርጅታችን ስለ አንጋፋው የቴአትር ባለሙያ ይህን  መጠነኛ የህይወት ታሪክ ሲያሰናዳ   ጋሽ ጥላሁን ጉግሳ አለሙ በዚህ ጽሁፍ ብቻ ተገልጾ ያበቃል ለማለት አይደለም፡፡ መነሻ ስራ እንካችሁ ለማለትና ታላቁ የጽሁፍና የዝግጅት ሰው የተዘነጋ ስለመሰለን ለማስታወስ ጭምር ነው፡፡  በሀገራችን  የቴአትር ሰዎች ህዝብ እንዲደሰት ብዙ ይጥራሉ፡፡ ህዝብ እንዲያውቅ ይፈልጋሉ፡፡ ቴአትር ጽፈው አንድ ለውጥ እንዲመጣ ይመኛሉ፡፡ የእነርሱ ታሪክ ግን ብዙ አይታወቅም፡፡ ያለፉበት መንገድ አይተረክም ፤ የወጡት ውጣ ወርድ ምን መልክ እንዳለው አይነገርም፡፡ የእኛ ድርጅት ደግሞ ሀገር ያለ ልጆቿ ታሪክ ባዶ ናት ብሎ ያምናል፡፡ እናት ልጆቿ ሲታወቁላት ፤ ሲሞገሱላት ፤ የሰሩት ስራ ደምቆ ሲነገር ደስ የሚላት እናት ስለሆነች ነው፡፡ የእነ ጥላሁን ጉግሳ ታሪክ የኢትዮጵያ የቴአትር ታሪክ ነው፡፡ ጋሽ ጥላሁን ጉግሳ ጋር ብቻ የሚገኝ እውቀት ወይም ታሪክ ይኖራል፡፡ ይህ ታሪክ ሊጻፍ ፤ ሊነገር ፤ ሊወጣ ይገባል፡፡ ይህ ሲሆን በቂ የምርምር ግብአት ይገኛል፡፡

 ጥላሁን ጉግሳ አለሙ በህይወት በቆየባቸው አመታት የሚችለውን ብቻ ሳይሆን ከአቅሙ በላይ ደክሞ ሰርቶ አይተናል፡፡  ስራው ደግሞ ፍሬ አፍርቶ ሌሎች በእርሱ ፈለግ ሄደው መክሊታቸውን አግኝተዋል፡፡ ይህ ታላቅ ሰው በቴአትር ቤቶች እና በሀገሪቱ የባህል ሚኒስቴር መስርያ ቤት በአስተዳደር ውስጥ በቂ ልምድ ያካበተ በመሆኑ ሰው እና ቴአትር ያላቸውን ቁርኝት በወጉ አጢኖ አዛምዷል፡፡ ጥላሁን ጉግሳ አለሙ ብዙ ሊጻፍለት ይገባ ነበር፡፡ ማህበራዊ ድረ-ገጽ ፤ ጎግል ላይ ስለ ጥላሁን ጉግሳ የተጻፈ ወይም የተሰራ ዘጋቢ ስራ አላገኘንም፡፡ ለዚህ ማንም ተወቃሽ አይደለም፡፡ እኛም ከወቀሳ ለመዳን  እነሆ  በዊኪፒዲያ ፤  በተወዳጅ ሚድያ የፌስ ቡክ ገጽ ፤ እንዲሁም በብሎጋችን  ጥላሁን ጉግሳ አለሙን  አስቀምጠናል፡፡ ይህም እየተጠናከረ የሚቀጥል ይሆናል፡፡

/ ይህ ጽሁፍ ከጥላሁን ጉግሳ አለሙ  ቤተሰቦች የተገኘውን መረጃ መሰረት በማድረግ የተጻፈ ሲሆን በዊኪፒዲያ ላይ ፤ በተወዳጅ ሚድያ የፌስ ቡክ ገጽ እና ብሎግ ላይ የተቀመጠ ነው፡፡ የጽሁፉ የዝግጅት እና የአርትኦት ስራ በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ የተሰራ ነው፡፡ አስፋላጊና፤ ተጨማሪ መረጃዎች በየጊዜው የሚታከልበት ሲሆን ጽሁፉም የጥላሁን ጉግሳ አለሙ ቤተሰቦችን ይሁኝታ ያገኘ በሁሉም የመገናኛ ዘዴዎች ለመሰራጨት የተፈቀደ ነው፡፡ /      

 












አስተያየቶች

  1. የውድ ወንድማችንን የጥላሁን ጉግሳ አለሙ የህይወት ታሪክ ስለ ጻፍችሁ እግዚአብሔር ይባርካችሁ ጥላሁን ሥራውን ከመውደድ የተነሳ ለራሱ ግዝ አይስጥም ነበር ጥላሁን ፌቅር የነበረ ሁሉን እኩል የሚያከብር ትሁት ደግ ስው ነበር መላው ለመላው ቤተስብ ከባድ ነው ነገር ግን ማንም ከዚህ የሚቀር የለም አሁንም በድጋሜ የውንድምችንን ታሪክ ስለጻፍችሁ እግዚአብሔር ይባርካችሁ

    ምላሽ ይስጡሰርዝ

አስተያየት ይለጥፉ

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች