ያዕቆብ ወልደማርያም የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ የኢትዮጵያን ሄራልድ አዘጋጅ
የመጀመርያው የኢትዮጵያን ሄራልድ ዋና አዘጋጅ አቶ ያእቆብ ወልደ ማርያም በአሁኑ ሰአት የ93 አመት ሰው ናቸው፡፡ ይህ ጽሁፍ በተወዳጅ ሚድያ የፌስ
ቡክ ገጽ እና ዊኪፒዲያ የወጣ እለት እሁድ ሰኔ 12 2014 93 አመት ይሞላቸዋል፡፡ ተወዳጅ ሚድያ ሀምሌ 30 2014
በሚያስመርቀው መዝገበ-አእምሮ የ180 ሰዎች ታሪክ ውስጥ የአቶ
ያእቆብ ታሪክ እንዲካተት ተደርጓል፡፡ በእንግሊዝኛ የጽሁፍ ችሎታቸው በሳል የሆኑት አቶ ያእቆብ ለተከታታይ 50
አመት በጋዜጠኝነት ሙያ በመቆየት ጠንካራ ባለሙያነታቸውን ያስመሰከሩ ናቸው፡፡ ሲሳይ ገብረ ማርያም እነሆ ታሪካቸውን እንደሚከተለው ሰንዶታል፡፡
አንጋፋው ጋዜጠኛ ያዕቆብ
ወልደማርያም፣ ከአባታቸው ከአቶ ወልደማርያም ሹባ ሌቃ፣ እንዲሁም ከእናታቸው ከወ/ሮ ወለተሚካኤል ሰንቤቶ ጋርባ እንደ አውሮጵያኖቹ አቆጣጠር ሰኔ 19 ቀን 1929 ዓ/ም በነቀምቴ ከተማ ተወለዱ።
የትምህርት ህይወት
በነቀምት ተፈሪ መኮንን አንደኛ ደረጃ የመንግሥት ትምህርት ቤት ስለተቋቋመ እዚያ ገቡ፡፡ ይህን እንዳጠናቀቁ በአዲስ አበባ ኮተቤ የመጀመሪያው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከየክፍለ ሀገሩ ጥሩ ውጤት ያላቸው ተማሪዎች በፈተና ወደእዚህ ትምህርት ቤት እንዲገቡ ይደረግ ነበር። አቶ ያዕቆብም ፈተናውን በከፍተኛ ውጤት አልፈው ከስምንተኛ ክፍል ጀምሮ ዘመናዊ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ኮተቤ የመጀመሪያው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት
ጀመሩ። መንግስት ጥሩ ውጤት ያላቸው ተማሪዎችን መልምሎ ወደ አሜሪካና ወደ ታላቋ-ብሪታንያ ልኮ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ያደርግ ነበር። እንደ አውሮፓ በመስከረም ወር በ1950 ዓ/ም ተማሪው ያእቆብ ወደ ለንደን የሚወስደውን የማትሪክ ፈተና ተፈተኑ።
ከተፈተኑት 85 ተማሪዎች ውስጥ 2ኛ በመውጣት ከሌሎች 7 ተማሪዎች ጋር የውጭ እድል አገኙ፡፡
የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናውን በከፍተኛ ማዕረግ በማጠናቀቃቸው ላገኙት ከፍተኛ ውጤት ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ እጅ ሽልማት ተቀብለው ወደ ለንደን አቀኑ፡፡
ትምህርት
እና
ህይወት
በለንደን
አቶ ያዕቆብ ወደለንደን ሲያቀኑ የሚማሩት ትምህርት ተወሰነላቸው ።
የለንደን ዩኒቨርሲቲ አካል በሆነው «ኢምፔሪያል የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ ውስጥ ትምህርታቸውን በጥሩ ውጤት እየተማሩ የነበረ ቢሆንም፤ በኤሌክትሪካል ምህንድስና
ዘርፍ ገፍቶ የመቀጠል ፍላጎታቸው እየተቀዛቀዘ መጣ።
በኤሌክትሪካል ምህንድስና
ዘርፍ እንዲማሩ ቢመደቡም በሙያው በአዕምሮ ብቻ የሚሰራ ነገር የለም። ቴክኒካል ስራዎች የሚበዙበት ስለነበር ትምህርቱን ስላልወደዱት እና ነፍስ ጥሪዬ ነው ብለው ስላላሰቡ ወደለንደን
ከመጡት የትምህርት አላማ ጎን ለጎን በግላቸው የተለያዩ የፍልስፍና መጻሕፍትን ማንበብ ተያያዙት።
የእንግሊዝ፣ የፈረንሳይ፣ ወደ እንግሊዝኛ የተተረጎሙ የጀርመን፣ የራሺያና የግሪክ እንዲሁም የሌሎች አገራት የሥነ ጽሑፍ እና የፍልስፍና መጽሐፎች ታሪክ ተወሰዱ ። በሂደትም እንዲማሩ የተላኩበትን የኤሌክትሪካል ምህንድስና ትምህርታቸው
ይልቅ ስለጋዜጠኝነት የሚያወሱ ሙያዊና ታሪካዊ መጽሐፍቶችንም በተመስጥኦ ማንበብን ቀጠሉ። በዚያው
ሙያውን እየወደዱት መጡ። በዚህ ወቅት በኮሌጁ ኢትዮጵያውያን «ላየንስ ክለብ» በሚል መሰባሰቢያቸው ስር ያቋቋሙት መጽሔት ነበርና አቶ ያዕቆብም የተለያዩ መጣጥፎችን በማዘጋጀት ብዕራቸውን በዚህችው መጽሔት አሟሹ። ጥረታቸውን በመቀጠል የተለያዩ የእንግሊዝ ጋዜጦችና መጽሔቶች ላይ ሃሳባቸውን የማስፈር ጥረት አደረጉ ። «ኦብዘርቨር»፣ «ማንችስተር»፣ «ዴይሊ ቴሌግራፍ» የተሰኙ የህትመት ውጤቶች ላይ ጽሑፋቸው እንዲወጣላቸው መላክ ጀመሩ፡፡ የላኩት አብዛኞቹ ባይወጡላቸውም ወደ ሙያው ለመግባት ፍንጭ ያዩበት ሙከራ ነበር፡፡ በዚያን ወቅት ፕሮፌሰር ሲልቪያ ፓንክረስት በሚያዘጋጁት ‹‹ኒው ታይምስ›› የተሰኘ ጋዜጣ ላይም ፅፈዋል። አቶ ያዕቆብ በዚህ ስሜት ውስጥ ሆነው
ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደ አገራቸው ተመለሱ።
የስራ ዓለም
ህይወት
በመምህርነት
በአዲስ አበባ ሽሮሜዳ አካባቢ በሚገኘው የአምሃ ደስታ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት
300 ብር ወርሃዊ ደመወዝ እየተከፈላቸው ሒሳብና እንግሊዝኛ ቋንቋ ማስተማር ጀመሩ። ከማስተማሩ ጎን ለጎንም
በትምህርት ቤቱ የተማሪዎች ጋዜጣ አቋቋሙ። ከ2 ዓመት በኋላ፤ በ1950ዎቹ መጨረሻ ወደ ትውልድ አገራቸው ነቀምት ተዛውረው ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ማስተማራቸውን ቀጠሉ። በእዚያም በተማሪዎች የሚዘጋጅ
ጋዜጣ በማቋቋም ይበልጥ ወደ ከሙያው ጋር ዝምድናቸውን አጠነከሩ ። በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋ በሚዘጋጀው በዚህ ጋዜጣ የእርሳቸው ሚና የእንግሊዝኛውን ክፍል ማረም እና ርዕሰ- አንቀፅ ማዘጋጀት ነበር።
አቶ
ያእቆብ ውስጣቸው የሚነግራቸውን ሙያ ለመያዝ አሰቡ፡፡ ሀሳባቸውን እውን እንዲያደርጉ የረዳቸው ሰው ደግሞ እንግሊዝ አገር አብሯቸው የተማረው
ኃይለልዑል ጠብቄ የተባለ ጓደኛቸው ነበር፡፡ ʿለምን
ዘ ኢትዮጵያን ሄራልድ ጋዜጣ አትገባም? ዋና አዘጋጁ ዶክተር ዴቪድ ኤ ታልቦት ጋዜጠኛ ይፈልጋል፤ ሂድና ተፈትነህ ግባ አለኝ።ʾ
ሀሳቡን ተቀብለው ሄራልድ ዋና አዘጋጁን አናገሩ፡፡ ʿሄድና
ቤትህ ጽፈህ ናʾ ብሎ
ፈተናውን ሰጣቸው። ʿየለም?
እዚሁ እፅፋለሁʾ ብለው።ፅፈው
ሰጡ፡፡ ʿበእንግሊዝኛ አርቲክል ጻፍ ʾ
ተባሉ ጻፉ።
ከፈረንሳይኛ ወደ እንግሊዝኛ የሚተረጎም ጽሑፍ ሰጣቸው፡፡ በጥሩ ሁኔታ ተርጉመው
ስለሰጡ በጣም ተገረመ። ዋና አዘጋጁ ደስ ስላለው ʿእንፈልግሃለንʾ ብሏቸው በዛው ተቀጠሩ፡፡ በዚሁ ጋዜጠኛ ሆኑ፡፡
የጋዜጠኝነት ህይወት
በ1951ዓ.ም በ400ብር ደመወዝ ጋዜጠኝነት ሙያን ተቀላቀሉ፡፡ ጉዳዮችን እያነሱ በመፃፍ በፊት ገጽ ዜናዎችን፣ በውስጥ ገጽ ደግሞ መጣጥፎችን በአማረ እንግሊዝኛ ቋንቋ ማበርከታቸውን ቀጠሉ፡፡
በወቅቱ ከዋና አዘጋጁ ዶክተር ታልቦት ቀጥሎ ሁለተኛ ሰው መሆ ቻሉ ፡፡ አዘጋጅ ሆነው ጽሑፍ ያርማሉ፣ ሌሎች ጋዜጠኞችን ሥራ ያሰማራሉ፡፡ በፈረንሳይኛ እና በጣሊያንኛ ከውጭ የሚላኩ ዜናዎችንና ሌሎች ጽሑፎችን ይተረጉማሉ፡፡ ሥራው ፋታ የማይሰጥ ቢሆንም የሚወዱትና የሚመኙት ሙያ ነበርና በትጋት ቀጠሉ፡፡
በሂደት ይከፈላቸው ከነበረው ደመወዝ ላይ ብር 100 ተጨምሮላቸው ወደ ምሽት አርታኢነት ተዛወሩ፡፡ እዚያም ለስድስት ወራት ሰሩ፡፡ አራት ገጽ ያለው ጋዜጣ ለማዘጋጀት እስከ ንጋት 11፡00 ሰዓት ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ሆነው ጽሑፎችን የማረምና ለህትመት የማመቻቸት ሥራ ይሰራሉ። ምሽት ላይ የሚመጡ መግለጫዎችን በተለይም ከማስታወቂያ ሚኒስትሩ በቃል እየተቀበሉ በመስራት በማግስቱ እንዲወጣ አድርገዋል፡፡
የጋናው መሪ ኑኩርማ ዶክተር ታልቦትን ለጉብኝት ጋብዘዋቸው ለ3 ወር ወደጋና በሄዱበት ወቅት ግን የአቶ ያእቆብን ህይወት የሚቀይር ሌላ ነገር ተፈጠረ፡፡ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትሩ አቶ አምደሚካኤል ደሳለኝ ጋዜጣዋን በቅርብ ኃላፊነት ይከታተሉት ነበር፡፡ በውስጣቸው ለምን የጋዜጣው (ዘ ኢትዮጵያን ሄራልድ ጋዜጣ) ዋና አዘጋጅ አይሆንም የሚል ቁጭት ስላደረባቸው በዚህ አጋጣሚ ጥሩ ለሚሰራ ሹመት መስጠትን ፈለጉ፡፡ ለቦታው ይመጥናሉ ብለው ያሰቧቸውን አቶ ያዕቆብ ወልደማርያምን፣ አቶ ነጋሽ ገብረማርያምን እና አቶ አያሌው ወልደ ጊዮርጊስን ቢሯቸው አስጠርተው «በሉ ከሦስታችሁ አንዳችሁ ዋና አዘጋጅ ትሆናላችሁ፤ ፈተና ልስጥ ወይንስ እናንተ ከመሀላችሁ ትመርጣላችሁ? ሲሉ ጠየቁን» ሁለቱም አቶ ያዕቆብ እንዲሆኑ ተስማሙ፡፡ ምርጫው ፀደቀ፡፡ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የ«ዘ ኢትዮጵያን ሔራልድ» ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆኑ፡፡
የዋና አዘጋጅነቱን ቦታ እንደያዙ በጋዜጣው ቅርጽና ይዘት ላይ ለውጥ አደረጉ፡፡ ለወትሮው የውጭውን ዓለም ታሪክና ዜና ከማቅረብና የንጉሡ እንዲሁም የሹማምንቶቻቸውን አንዳንድ ክዋኔዎች በዜናነት ከማውጣት በዘለለ ሌሎች የማህበረሰቡን ክንዋኔዎች ዳስሳ የማታውቀው ሄራልድ ጋዜጣ እሳቸው ከተቀላቀሉ በኋላ የተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊና ሌሎች ሁነቶችን በስፋትና በጥልቀት መዘገብ ጀመረች፡፡ አገራዊ ጉዳዮች ላይ እንድታተኩር መደረጓ አቶ ያዕቆብን አስመሰገናቸው፡፡ «አይችሉም!» ተብሎ ተስፋ የታጣለባቸው ኢትዮጵያውያን አቅማቸው ምን ያህል ከፍተኛ እንደሆነም ታየ፡፡
በዚያን ወቅት አቶ ያዕቆብ የሌሎች አገራት መልካም ተሞክሮዎችን እየጠቀሱ ለአገሪቱ ሁለንተናዊ እድገት የሚበጁ ሃሳቦችን በርዕሰ አንቀጽ እና በሌሎች ገጾች ይጽፉ ነበር፡፡ በተለይ ስለ መሬት ከበርቴ፣ ስለ ሲቪል ሰርቪስ መቋቋም፣ ስለ ጡረታ ሕግ አወጣጥ ብዙ ወትውተዋል። ስለ ቤት ኪራይ እና ስለ ሹም ሽረት ሥርዓት ጉዳይም አበክረው ጽፈዋል፡፡
ከሄራልድ ወደ «አጃንስ»
ለሁለት ዓመታት በዚሁ ኃላፊነታቸው እንደሰሩ ለመልቀቅ ምክንያት የሆናቸውን እንዲህ ይገልጻሉ። «በዚሁ ኩዴታ ወቅት ሕዝቡ ʿእነ
ጀኔራል ጃገማ ኬሎ መንግሥት ሊገለብጡ ነውʾ እያለ
በመራበሽ ልጆቹን ከትምህርት ቤት ማውጣት ጀመረ፤ ታዲያ እኔ ʿዜና
በትክክል ቢሰጥ ኖሮ ይህ ሁሉ ውዥንብር አይፈጠርም ነበርʾ ስል
በርዕሰ አንቀፅ ጻፍኩኝ፡፡ በዚህ ጊዜ በመነን መጽሔት እንግሊዝኛው ውስጥ የሚጽፍ ስሚዝ የተባለ አፍሮ አሜሪካዊ ሃሳቤን ይዞ ለውጭ አገር ሚዲያዎች አስተጋባ። ይህ ሲሆን የውጭ ጋዜጦች በአገራችን የጋዜጠኝነት ነፃነት የሌለ መሆኑን በመግለጽ ማስታወቂያ ሚኒስቴርን በመተቸት ወሬውን ተቀባበሉት፡፡ በዚህ ጊዜ በመንግሥት ጥርስ ተነከሰብኝ፡፡ ወዲያውም ደጃዝማች ግርማቸው ወልደሐዋርያት ከጋዜጣው ሥራ እንድነሳ አደረጉ»።
ከዚያም ቀድሞ «አጃንስ» ተብሎ ወደሚጠራው በአሁኑ አጠራሩ «የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ኤጀንሲ» የእንግሊዝኛው ክፍል ተዛወሩ፡፡ እዚያም ትንሽ እንደሰሩ እንደገና ስለመዛወራቸው የገለጹት «... አንድ ቀን ከቢሮ ሥራ ጨርሼ ቤቴ ለመሄድ ወደ መኪናዬ ሳመራ ግቢው ውስጥ ቀድሜ ያላየኋቸው ማስታወቂያ ሚኒስትሩ ብላታ ግርማቸው ጠሩኝ። ምን ቁጣ ሊያመጡብኝ ይሆን ስል ʿበል
ና ይሄ ስሚዝ የሚባለው ሰው አይደለም ዜናውን ያስተላለፈው!?ʾ
በል አሁን መነን የእንግሊዝኛው መጽሔት ላይ ሂድና ሥራ ጀምር። ስሚዝን በስድስት ወር ውስጥ ከሥራ አባርረዋለሁ። ከዚያ አንተ በእርሱ ቦታ ዋና ኤዲተር ትሆናለህ አሉኝ» እንዳሉትም ሆንኩኝ፡፡ በማለት ነው፡፡
በመነን እና «ቮይስ ኦፍ ኢትዮጵያ»
በዚህ ሁኔታ በአገር ፍቅር ስር ትተዳደር ወደነበረው መነን መጽሔት የተዛወሩት አቶ ያዕቆብ፣ የመጽሔቷ ዋና አዘጋጅ ሲሆኑ ከአማርኛው ጋር ተዳብላ የነበረችውን መጽሔት ራሷን ችላ እንድትወጣ ማድረግ የመጀመሪያ እርምጃቸው ሆነ፡፡ በቅርፅና ይዘት ደረጃ ከሌሎች የውጭ አገር መጽሔቶች ባልተናነሰ ሁኔታ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ዘመናዊነትን ተከትለው ሲያዘጋጁ ብላታ ግርማቸውም ሆኑ ሌሎች ሹማምንቶች መደሰታቸው አልቀረም፡፡ መጽሔቷን ወደ ተሻለ ብቃት ሲያሳድጓት የውጭ መጽሔቶችን አርአያነት እየተከተሉ ነበር፡፡ ብዙ ማንበባቸውና ሙያውን ማፍቀራቸው ሁሌም የተሻለ ሥራ እንዲሰሩ ብርታት እየሆናቸው ቀጠሉ፡፡
በዚህ መጽሔት ለተወሰነ ዓመታት እንደሰሩ የእንግሊዝኛዋ «የቮይስ ኦፍ ኢትዮጵያ» ጋዜጣንም ደርበው እንዲያዘጋጁ ኃላፊነት ተሰጣቸው፡፡ አቶ ያዕቆብ እንደሚሉት፤ ያኔ በአገር ፍቅር ማህበር ያሉ ጋዜጦችንና መጽሔት በዳይሬክተርነት የሚመሩት አቶ ከበደ አበበ የሰጡት የመስራት ነፃነት ለህትመት ውጤቶቹ ጥሩ ደረጃ ላይ መድረስ አስተዋጽኦ ነበረው። በኋላም ሙሉ ለሙሉ ከመጽሔቷ ወደ ቮይስ ኦፍ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ተዛውረው ለሰባት ዓመታት ያህል ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡
የእንግሊዝኛው ቮይስ ኦፍ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ሲዘጋ በእዚያው ይከፈላቸው የነበረውን ደመወዝ ይዘው ወደ ዘ ኢትዮጵያን ሔራልድ ጋዜጣ ተመልሰው በአማካሪነት ተመደቡ። የደርግ መንግሥት እስኪመጣ ድረስ ከማማከሩ ጎን ለጎን በፍላጎታቸው ርዕሰ አንቀጽና መጣጥፎችን ያዘጋጁ ነበር፡፡ ደርግ ሥልጣን ሲይዝ የማስታወቂያ ሚኒስቴር የኤሌክትሮኒክሱንና የህትመት ጋዜጠኞችን እያዘዋወረ ሲደለድል አቶ ያዕቆብ የደረሳቸው በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ፐብሊኬሽን ዘርፍ ነበር፡፡ በዚያም የእንግሊዝኛው የየካቲት መጽሔት ዋና አዘጋጅ ሆነው አገልግሎታቸውን ቀጠሉ፡፡ እዚሁ እየሰሩ ጡረታ ሊወጡ ስድስት ወራት ሲቀራቸው በ1980 ዎቹ አጋማሽ ላይ በእዚሁ የጽሑፍ ሥራቸው ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይዛወራሉ። ያኔ ደመወዛቸው 950 ብር ደርሷል፡፡ በማስታወቂያ ሚኒስቴር በጋዜጠኝነት ሥራ ብቻ ከ34 ዓመታት በላይ የሰሩት አቶ ያዕቆብ በተለያዩ የአገሪቱ ወሳኝ የታሪክ ምዕራፎች ሳይቀር ሙያው ውስጥ ነበሩ።
በ1980 አጋማሽ ከማስታወቂያ ሚኒስትር ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተዛውረው በጽሕፈት ሥራ በማገልገል ላይ ሳሉ ጡረታ ቢወጡም ከዚያ ወዲህ ባሉት ዓመታትም አንድም ጊዜ አላረፉም፡፡ በሪፖርተር የእንግሊዝኛው ጋዜጣ ላይ የአርታኢነት ሥራን በፍሪላንሰነት ሰርተዋል፡፡
ሽልማት እና እውቅና
በተለያዩ ዘመናት ባከናወኗቸው ተግባራት ሽልማቶችን እና የምስክር ወረቀቶችን አግኝተዋል፡፡ በትምህርታቸውም ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገባቸውም እንዲሁ አሸልሟቸዋል፡፡ በቮይስ ኦፍ ኢትዮጵያ ጋዜጣ በሙያቸው ባሳዩት ትጋትና የአሥር ዓመት አገልግሎት የፈረሰኛ ኮኮብ ኒሻን ከንጉሡ እጅ ተቀብለዋል፡፡ በስጦታ ያገኟቸው ቤት መስሪያ ቦታና ርስትም ሽልማቶቻቸው ነበሩ፡፡
በደርግ ሥርዓተ መንግሥት የምስክር ወረቀት ተሸልመዋል ፡፡ በቅርቡ ግን በረጅም ሙያዊ አገልግሎታቸው የበጎ ሰው ሽልማትን ተቀብለዋል፡፡ «ይህ ሽልማት በሕዝብ ምርጫ ውጤት በመሆኑ ተደሳች ነኝ፡፡ ሥራዬንና ማንነቴን አክበረው ለዚህ ሽልማት ላበቁኝ ሁሉ አመሰግናለሁ» ነው ያሉት - አቶ ያዕቆብ፡፡
ከአሥር ዓመት በፊት ግለ ታሪካቸውን “Yacob Wolde-Mariam berif
Autobiograohy and Selected Article” ጽፈው
ለንባብ አብቅተዋል፡፡
በቤተሰባዊ ሕይወት
ትዳር የያዙት በአመሃ ደስታ ትምህርት ቤት መምህር ሳሉ ነበር፡፡ ትዳር መስርተው ልጆችን
አፍርተዋል፡፡
በርካታ የልጅ ልጆችንም አይተዋል፡
ዋና ምንጭ “Yacob Wolde-Mariam berif
Autobiograohy and Selected Article”
ተጨማሪ ምንጮቸ
http://
www.dw.com/am/ቆይታ-ከአንጋፋዉ-ጋዜጠኛ-ያዕቆብ-ወልደማርያም-ጋ
http://zarayakob.blogspot.com/2016/03/blog-post.html
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ