187ክብሬ ተስፋዬ አበበ
በታላላቅ ሁነት አዘጋጆች
የምትመረጥ ባለሙያ
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን
በሚድያ ዘርፍ ለሀገራቸው አንድ አሻራ ያኖሩ ሰዎች እየሰነደ ለመጪው ትውልድ እያስቀመጠ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከ1950 ጀምሮ በየዘመኑ
በሀገሪቱ የሚድያ ኢንዱስትሪ ውስጥ ገብተው የራሳቸውን ቀለም ፈጥረው የተገኙ ሰዎችን ከያሉበት ፈልገን የህይወት ታሪካቸው እንዲታወቅ
፤ ራሳቸውም ራሳቸውን እንዲያውቁ ወደ ኋላ መለስ ብለው ምን አበርክቼ ይሆን እንዲሉ መንገዱን እያመቻቸን ነው፡፡ መዝገበ-አእምሮ
የ180 የሚድያ ሰዎች ታሪክ የሚለው ባለ 600 ገጽ መጽሀፋችንም ሀምሌ 30 2014 በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቴአትር ይመረቃል፡፡
ታሪካቸው በዊኪፒዲያ፤ በተወዳጅ ሚድያ ድረ-ገጽና በልዩ ልዩ መንገድ ከሚሰነድላቸው
ብርቱ የሚድያ ሰው ፤ የመድረክ መሪ የኮሚኒኬሽን ባለሙያ የሆነችው
ክብሬ ተስፋዮ ናት ፡፡
ክብሬ ተስፋዬ በመድረክ
መሪነት ትታወቃለች፡፡ በጦቢያ ዝግጅትና በቀደመ ስሙ ጣይቱ እና በአሁኑ ስሙ የእቴጌ እልፍኝ በተሰኙ ሁለት ሴቶችና ሃገር ላይ በሚያተኩሩ ፕሮግራሞቿ ተመልካች በደንብ
ያውቃታል፡፡ በሬዲዮ ፋና እርስዎ ቢሆኑ ምን ያደርጋሉ? በተሰኘው ተወዳጅ ፕሮግራምም የመጀመሪያዋ ሴት አወያይ በመሆን በሩን ለሴቶች
ከፍታለች፡፡
ትውልድ ልጅነትና ትምህርት
ጋዜጠኛ ክብሬ ተስፋዬ
ህዳር 27 ቀን 1972 ዓ.ም ከአባቷ ከመምህር ተስፋዬ አበበ እና ከእናቷ ከወ/ሮ መሰለች ፈለቀ በአዲስ አበባ ከተማ በቂርቆስ
ክፍለ ከተማ ልዩ ስሙ ቡልጋሪያ ማዞሪያ በሚባለው አካባቢ ተወለደች፡፡
ስድስት ወንድሞች እና
ሁለት እህቶች ያሏት ሲሆን በቤተሰቧ ውስጥ 7ኛ ልጅ ናት፡፡ ከአንድ እስከ ስምንት በተማረችበት እውቀት ምንጭ ትምህርት ቤት ጀምሮ
ዝንባሌዋን በማየት በቋንቋ መምህሮቿ እገዛ በየሳምንቱ አርብ አርብ በሰንደቅ ዓላማ መስቀያ መድረክ ላይ ከመፅሐፍ ገጾች ንባብ በማቅረብ
እና የራሷንም ግጥም በማንበብ መድረክን የተለማመደችው ክብሬ ተስፋዬ ትምህርት ቤቷንም በመወከል በአጠቃላይ ትምህርት ትወዳደር ነበር፡፡
በክፍል ትምህርቷ ያላት ጉብዝና የኪነ-ጥበብ ፍላጎቷንም እንድታሳካ በሩን ከፍቶላታል፡፡ በልጅነቷ በክረምት ከአብሮአደጎቿ ጋር ባላት
ፉክክራዊ ጨዋታ መፅሐፍትን የማንበብ ልምዷ በትምህርት ቆይታዋም ጠቅሟታል በቋንቋ ትምህርት ክፍለ-ጊዜም መፅሐፎችን ለክፍል ተማሪዎች
በማንበብ ተደጋጋሚ ዕድል በማግኘቷ ለሚዲያ ህይወቷ ትልቅ እገዛ አድርጎላታል፡፡
የታዳጊነት ጥረት
ክብሬ ተስፋዬ ይህ የመጀመሪያ
ደረጃ ትምህርት ቤት መሰረቷ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ባጠናቀቀችበት አብዮት ቅርስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚኒሚዲያ አባል
በመሆን ይበልጥ አጠናክራዋለች፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን በቂርቆስ ቤተሰብ መምሪያ ቅርንጫፍ ውስጥ ተመስርቶ በሚንቀሳቀሰው ብሩህ አማተር
የጋዜጠኞች ክበብ ውስጥ ከፕሮግራም አቅራቢነት እስከ ምክትል ሊቀመንበርነት ድረስ በማገልገል በአካባቢው ወጣቶች ላይ በጎ ተጽእኖ
ማሳደር ችላለች፡፡ በጊዜውም ከፍተኛ ማህበራዊ ቀውስ ያስከተለውን ኤች.አይ.ቪ ኤድስን በመከላከል ረገድ ትልቅ ሚና ከተጫወቱ ወጣቶች መካከል
ተብላ ቤተሰብ መምሪያ እውቅና ሰጥቷታል፡፡ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ቅዳሜ መዝናኛ በጊዜው የኪነጥበብ ተሰጥኦ እና የሚዲያ ፍላጎት ላላቸው
ልጆች ባመቻቸው ዕድል በመጠቀም ከሰፊው የሬዲዮ አድማጭ ዘንድ የመድረስ ዕድሉን ተጋርታለች፡፡ በሩሲያ የሳይንስና የባህል ማዕከል
በተቋቋመው ቀንዲል ቤተ-ተውኔትም ስነ-ጽሁፍ በከተማው እንዲጀመርና እንዲጠናከር በጎ ሚና ከነበራቸው ወጣቶች መካከል ተጠቃሽ ነበረች፡፡
በተለይም የግጥም ስራዎቿን በብዛት በማቅረብ መድረኩን በመምራት ታዋቂ ሰዎችን ቃለ-መጠይቅ በማቅረብም የጋዜጠኝነት ሙያውን በሰፊው
የተለማመደችበት መድረክ ነበር፡፡ ዛሬ ስመ-ጥር የሚባሉ በየዘርፉ የሚመድቡ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችን ባፈራ መድረክ ላይ መስራቷ
ለሚዲያውና ለጥበቡ ቅርብ አድርጓታል፡፡
በኋላም በዩኒቲ ዩንቨርሲቲ
በዲፕሎማ በጋዜጠኝነትና ኮምዩኒኬሽን ፣ በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ በትያቲሪካል አርት ትምህርት ክፍል በዲግሪ ተመርቃለች፡፡ የማኔግመንትን
እውቀት ሰው ሁሉ ማወቅ አለበት የሚል መርህ ያላት ጋዜጠኛ ክብሬ ተስፋዬ በቅድሰተ-ማሪያም ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በማኔጅመንት የትምህርት
ክፍል ዲግሪዋን ይዛለች፡፡ ከዓመታት የሚዲያ የስራ ልምድ በኋላም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማስተርስ ዲግሪዋን በጋዜጠኝነትና ኮምዩኒኬሽን
ተምራ አጠናቃለች፡፡
የጋዜጠኝነት ጉዞ
በትምህርት ቤት እና በቤተሰብ
መምሪያ ህትመት ሚዲያ ላይ መሰናዘሪ በተባለ ብዙ ገጽ ባለው ጋዜጣ ላይ ስራ የጀመረች ሲሆን የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ጅማሮዋ በሬዲዮ ፋና አንድ ብሏል፡፡ በሬዲዮ ፋና መስከረም
9 ቀን 1999 በሪፖርተርነት የስራ መደብ በ739.00 ብር ተቀጠረች፡፡
በሬዲዮ ፋና መልካም ስም ባተረፈችበት እርስዎ ቢሆኑ ምን ያደርጋሉ? በሚለው ፕሮግራም እንደ አድማጭ በቀጥታ የስልክ ውይይት ስትሳተፍ
ባሳየችው የነቃ የመናገር ችሎታ እንዲህ ያለ አቅም አወያይ መሆን ነው ያለበት ብሎ ያመነው የወቅቱ የፕሮግራም ኃላፊ አቶ ብሩክ
ከበደ በውስጥ መስመር እንድትቆይና እንድታናግረው በማድረግ ነው ለሬዲዮ ፋና ጋዜጠኝነት ቅጥር የበቃችው፡፡ በቃለ-መጠይቅ ወቅትም
እርስዎ ቢሆኑ ምን ያደርጋሉ? እና ገስት ዲጄን እና ፋና ጥበባት ላይ መስራት እንደምትፈልግ በተናገረችው መሰረት በራዲዮ ፋና ሀገር
አቀፍ ስርጭት የመዝናኛ ክፍል ባልደረባ በመሆን ተቀጠረች፡፡ በሬዲዮ ፋና በቆየችባቸው 4 ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ከጀማሪ ሪፖርተርነት
እስከ የመዝናኛ ክፍል አርታኢ ኃላፊነት ድረስ አገልግላለች፡፡ በእነዚህም ጊዜያት እርስዎ ቢሆኑ ምን ያደርጋሉ? የመጀመሪያዋ ሴት
አዘጋጅና የቀጥታ ስርጭት መሪ በመሆን ተወዳጅነትና በሬዲዮ አድማጭ በኩልም ጥሩ ተደናቂነት ያተረፈችበት ልብ ለልብ ፕሮግራም የኪነ-ጥበባት
ዝግጅት ክፍል የሆነው የመፅሐፍ ትረካ ችሎታዋም መልካም ስም አጎናፅፏታል፡፡
እርስዎ ቢሆኑ ምን ያደርጋሉ? ዛሬ ደረስ አድማጮች እንደ ቅፅል ስም እርሷን የሚጠሩበት ስያሜ ሆኖላታል፡፡ ገጠመኝና ማስታወሻንም
ከጋዜጠኛ ደመቀ ከበደ ጋር በመሆን የመጀመሪያዋ የፕሮግራሙ አዘጋጅ በመሆንም ትጠቀሳለች፡፡ ጣቢያውን እስከለቀቀች ጊዜ ድረስም በዚሁ
ፕሮግራምም በርካታ አድናቂዎች ነበሯት፡፡
ከፋና በኋላ
በሬዲዮ ፋና ያካበተችው
ልምድና ያተረፈችው መልካም ስም በቴሌቪዥኑ መስክም የኢትዮጵያን አይዶል
የመጀመሪያው መድረኳ ነበር፡፡ በፕሮግራሙም የቴሌቪዥን አቅራቢ በመሆንና እና ከልዩ ልዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተገኙ ተወዳዳሪዎችን
ታሪክ በመሰነድና ቃለ-መጠይቆችን በማደራጀት የጎላ ሚና ተወጥታለች፡፡ በቴሌቪዥኑ ዓለምም ጥሩ ተቀባይነት በማግኘቷ የራሷን የማስታወቂያ
ድርጅት ለማቋቋም ችላለች፡፡ ከኢትዮጵያን አይዶል በኋላ በቁጥር ብዙ የሚባሉ መድረኮችን በመላው ሀገሪቱ መርታለች፡፡ አስተባብራለች፡፡
በመድረክ መምራቱ ዓለም በርካታ ሰዎች የሚስማሙባት ባለሙያ ናት፡፡ በታላላቅ ሁነት አዘጋጆች የምትመረጥ ባለሙያም ናት፡፡ ከዚሁ
ጎን ለጎን የምታምንበትን ብቻ እንደምትሰራ የሚያውቁ ሰዎችም የሚጋብዙበትን ሁነቶች ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ መድረኩን የሚመራው ማነው?
ለሚለው ጥያቄ ክብሬ ተስፋዬ ናት የሚል ምላሽ የሚያገኙ አስተባባሪዎች ይረካሉ፡፡ የሚፈጠሩ ድንገታዊ ችግሮችን የአዘጋጆቹን ገበና
ሸፍና ታዳሚውም ጉዳዩን ረስቶ ቀጣዩ ፕሮግራም ላይ እንዲያተኩር ማድረግ መቻሏን በርካቶች እንደተለየ ክህሎት ይቆጥሩላታል፡፡ ስህተትም
ስትሰራ ያንኑ በይቅርታ ከማረሟም በላይ ይቅርታ የምትጠይቅበት ለዛ
እና በቀልድ የተዋዛ አቀራረብ ብዙ ሰው የማይረሳውና የተወደደችበት አቀራረቧ ነው፡፡ መድረክ መምራትን አሳላፊነት ብላ የምትጠራዋ
ክብሬ ሙያው ትልቅ ኃላፊነት ነው ትላለች፡ ደጋሽ የለፋበትን አሳምሮ ማቅረብም ዋና መርኋ ነው፡፡
አቤቱ ሞገስን ስጠኝ አብረኸኝ ቁም
ክብሬ አንድ መድረክ ከመምራቷ
በፊት በጉዳዩ ላይ ልታምንበት ይገባል፡፡ አንዴ ካመነችበት በቂ ዝግጅት ታደርጋለች፡፡ ደስ ብሏት ስለምትዘጋጅ መድረክ አመራሯ የተዋጣ ይሆናል፡፡
ክብሬ ስለመድረክ ስራ
ስታወራ አንድ ዋና እና መሰረታዊ ጉዳይ ማንሳት ትፈልጋለች፡፡ ይህን ታላቅ ሚስጢር በዚህ ህይወት ታሪኳ ላይ ማካፈል ትሻለች፡፡
ይህም ታላቅ ሚስጥር ፀሎት ይባላል፡፡ አቤቱ ሞገስን ስጠኝ አብረኸኝ
ቁም ብላ ትማጸናለች፡፡ ችሎታዋን ለሚያደናንቁ ሁሉ ክብሩን እግዚአብሔር ይውሰድ ትላለች፡፡ ይህ አባባሏ በብዙዎች ዘንድ ይወደድላታል፡፡
በዚህ መልኩ የፖኤቲክ ጃዝ መሰናዶ፤ የዓመቱ በጎ ሰው፣ የአዲስ አበባ
ዩንቨርሲቲ የምርቃት ሥነስርዓት፣ አርአያ ሰው ሽልማት፣ ለዛ ሽልማት፣ አድዋ አዋርድ፣ የህዳሴውን ግድብ በተመለከተ በጉባ በብሄራዊ ቤተመንግስት እና ሌሎችም የአስተባባሪ
ፅ/ቤቱ ፕሮግራሞች። በጎ አድራጎት ግሎባል አሊያንስ የኢትዮጵያ ኮሚቴ አባል፣ ባዩሽ ኮልፌን ገንዘብ በማሰባሰብ እና ሙያዊ ድጋፍ
በማድረግ ማገዝ የመሳሰሉት። የአጣዬን ማህበረሰብ ለማቋቋም ሸራተን የተካሄደ ቴሌቶን መድረኩን በማስተባበርና በመምራት ኢትዮጵያዊት
ሽልማት፣ የእናቶች ቀን፣ የአባቶች ቀንን የመሳሰሉ ዓመታዊ ከሆኑ ሁነቶች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ የብዙ የትምህርት ተቋማት የተማሪዎች
ምረቃ ሥነስርዓት፣ የተቋማት ምስረታ እና ብራንዲንግ፣ የፋብሪካዎች እና የንግድ ተቋማት ምስረታዎችና ዓመታዊ ክብረ በዓሎች እንዲሁም
በልማትና በማህበረሰብ አገልግሎት ብሎም በበጎ አድራጎት ዘርፍ የተሰማሩ ተቋማትን ፕሮግራሞችን ፊት አውራሪ በመሆን መርታለች፡፡
ለምሳሌ ያህልም ሜሪ ጆይ፣ ኦስትሪያን ዴቨሎፕመንት፣ ኢትዮጵያ ስኩል
ሚል ኢንሼቲቭ፣ ጤና ጥበቃ፣ ትምህርት ሚኒስቴር፣ ግብርና ሚኒስቴር . ወዘተረፈ በርካቶቹ የቀጥታ ስርጭት ጋር የተያያዙ መድረኮች ላይ ደጋግማ
ከህብረተሰቡ ጋር ተገናኝታ ከበሬታና አድናቆትን አትርፋበታለች፡፡
ክብሬና ብስራት ሬድዮ
በግል የሚዲያ እና የኮምዩኒኬሽን
ዘርፍ ሁነቶችን እየሰራች ብስራት ኤፍ.ኤም 101.1 በ2007 ሲጀምር ተወዳጅነትን እንዲያተርፍ አበርክቶ ከነበራቸው ባለሙያዎች
መካከል ነበረች፡፡ ብስራት ማለዳን በመምራት እየሰራች ጎን ለጎን የዘመን መልክ የተሰኘ የግሏን
ፕሮግራም ታዘጋጅ ነበር፡፡ በእሁድ ማለዳ በጥበባት ዝግጅቶች በየዘመኑ የነበሩ የጥበብ ስራዎችን በማቅረብ እሁድ ማለዳን በአድማጭ
ዘንድ ተደማጭና ተወዳጅ እንዲሆን የበኩሏን ድርሻ ተወጥታለች፡፡
ከ2007 -2008 ማብቂያ ድረስ በብስራት ቆይታዋ ጣቢያው የመሸኛ ፕሮግራም
አዘጋጅቶ ወርቅ ሸልሞ አሰናብቷታል፡፡
ጄቲቪ ኢትዮጵያ
ከብስራት ኤፍ.ኤም 101 .1 እንደለቀቀች አዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ለሁለተኛ
ዲግሪ በማታው ትምህርት ክፍል ትምህርቷን እየተከታተለች ጄቲቪ ኢትዮጵያ ፕሮግራም ዳይሬክተርነት በመወዳደር ተቀጥራ በጣቢያው የፕሮግራም
ኃላፊ በመሆን ለ8 ወራት፤ በሳምንት 4 ፕሮግራሞችን እያዘጋጀች ጣቢያውን በፕሮግራም ኃላፊነት እየመራች በቆየችባቸው ጊዜያት አብረው
የሰሩ በብዛትም የአየር ሰዓት ወስደው ከሚሰሩ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ጋር ባደረገችው የስራ ግንኙነት የመሰከሩላት በብዙሃን መገናኛ
ታሪክ ውስጥ ተስፋ ያላት መሪ መሆኗን አረጋግጣለች፡፡ጣቢያውም በወቅቱ
ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘበት ወቅት መሆኑን ታሪክ ይጠቅሷል፡፡
ሁለተኛ ዲግሪ
ጋዜጠኛ ክብሬ ተስፋዬ
የሁለተኛ ዲግሪዋን የጥናት ወረቀት ለመስራት ሙሉ ለሙሉ ከጣቢያው በመልቀቅ የጥናት ወረቀቷን በፍኖተ ሰላም ከተማ በ4 ቀበሌዎች
ላይ ቢቢሲ ሚዲያ አክሽን በሚያሰራጨው በስነተዋልዶ ጤና እና በቤተሰብ ምጣኔ ላይ አተኩሮ በሳምንት አንድ ቀን በሚያስተላልፈው ፕሮግራም
ላይ በፈጠራ ጽሁፍ ደራሲነት፤ በግጥም በትረካና በሌሎች አዝናኝ የማዋዣ ፕሮግራሞች ላይ ስትሳተፍበት በቆየችው ጀንበር የሬዲዮ ፕሮግራም
ላይ የአድማጮች ቡድን በባህሪይ ላይ ያመጣውን ለውጥ በመገምገም ጥናቷን አጠናቃ ተመርቃለች፡፡ በመሰል የፈጠራ ጽሁፎች እና የመድረክ
መምራት ስራዋን በመቀጠል ወደ ኮምዩኒኬሽን ባለሙያነት ተዛውራለች፡፡
እንደ ኮሚኒኬሸን ባለሙያ
በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ
ስኩል ሚል ኢኒሼቲቭ በተባለ ሀገር በቀል ግብረ- ሰናይ ድርጅት ውስጥ ‹‹ልጆች ባሉበት ሁሉ ምግብ ይኑር›› በሚለው መርሁ የሚታወቀው እና በትምህርት
ቤት ምገባ ላይ በሚሰራው ግብረ-ሰናይ ድርጅት ውስጥ የህጻናት መብት አድቮኬተር ነች፡፡ በድርጅቱ በኮምኒኬሽን ኃላፊነት መደብ ላለፉት 5 ዓመታትም እየሰራች ትገኛለች፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎን በሳምንት አንድ ቀን በሚተላለፈውና በአርትስ ቴሌቪዥን በሚቀርበው የእቴጌ እልፍኝ በተሰኘው እና ሃሳብ እንግዳ
ሁኖ ሃሳብተኞች በሚቀርቡበት በሃገር እና በሴቶች ሁለንተናዊ ለውጥ ላይ አተኩሮ በሚሰራ ፕሮግራሟ ትታወቃለች፡፡ እንዲሁም በጦቢያ
ፖየቲክ ጃዝ ፕሮግራምም ከለውጡ ወዲህ ባገኘው የቴሌቪዥን ስርጭትም በአዘጋጅነት በመስራት ላይ ትገኛለች፡፡
ቤተሰባዊ ህይወት
ህይወት የትጋት ወጤት
ናት የምትለዋ ክብሬ ከ18 ዓመታት በፊት ትዳር የመሰረተች ሲሆን የ ሦስት ልጆችም እናት ናት፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ ትዳርም ልጅ
ወልዶ ማሳደግም እግረ ሙቅ አልሆነብኝም አንዱን አንስቼ አንዱን ጥዬ አልሮጥኩም ጥሩ እናት፣ መልካም ሚስት፣ ጎበዝ ተማሪ እና ብርቱ
ሰራተኛ ለመሆን አልቸገረኝም፡፡ የህልም ሩጫ ብርቱ እንጂ ደካማ አላደረገኝም የሰልፌን ብዛት ስላወቅሁት ፈጣሪን አስቀድሜ ባጭሩ
ታጥቄ እዚህ ድርሻለሁ ትላለች፡፡
መዝጊያ፦ ይህ መዝጊያ
የተወዳጅ ሚድያ የዊኪፒዲያ / የመዝገበ -አእምሮ ./ ቦርድ አባላት አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡
ክብሬ ተስፋዮ በጥረት ማደግ እንደሚቻል በተግባር ያሳየች ለብዙዎች አርአያ
የምትሆን ጠንካራ ባለሙያ ናት፡፡ በቲቪ ላይ የምናያቸው አንደበተ-ርቱእ መድረክ መሪዎች ከዛም በላይ ድንቅ አቅም ያካበቱ ናቸው፡፡
ለዚህም ከቀዳሚዎቹ ውስጥ እንደ ዋቢ የምትወሰደው ክብሬ ናት፡፡ የክብሬ የኪነጥበብ ዝንባሌ በቅርቡ የመጣ ሳይሆን በታዳጊነት አሃዱ
ያለ ነው፡፡ ያኔ ህልሟን ለማሳካት ብዙ መጣር ነበረባት-ጣረች፡፡ ያኔ ሚድያን ለማወቅ ዘልቃ መሳተፍ እንዳለባት አመነች-ተሳተፈች፡፡ ያኔ ጥረቷ ሲታይ ቀላል ይመስላል፡፡ ነገር ግን ተግዳሮትን አሸንፋ ዛሬ ላይ
ደርሳለች፡፡ ዛሬ ክህሎቷ ሲታይ ጠንካራ መሰረት እንደነበራት ያሳያል፡፡
እንዲህ አይነት በትጋት ያደጉ ሰዎች ታሪካቸው ለምን አይጻፍም? የተወዳጅ ሚድያ ጥያቄ ነው፡፡ ክብሬ ለሚድያ ነው የተፈጠረችው ፡፡
ለዚህም ነው መድረክ ስትመራ የሚቃናላት፡፡ አዲሱ ትውልድ ከክብሬ ብዙ ይማራል፡፡ ማንበብ ፤ የተመልካችን ፍላጎት በፍጥነት ማወቅ፤
ከብርሀን የፈጠነ ቅልጥፍና ፤ ሳይታክቱ መስራት እነዚህ ሁሉ በክብሬ የሚድያ ህይወት ውስጥ ነፍስ ዘርተው ሲኖሩ ታይተዋል፡፡ ክብሬ
ለኢትዮጵያዊነት ቅድሚያ ትሰጣለች፡፡ አንድ መሆንን ፍቅርን ትሰብካለች፡፡ ይህን የህይወት ታሪክ ለማጠናከር ስንል ብዙዎችን አነጋግረን
ሁለ-ገብ ችሎታ ያካበተች መሆኗ ተነግሮናል፡፡ በቲቪ አየር ላይ ያዋለቻቸው
ቃለ-መጠይቆችም በይዘት ጠንካራ የሚባሉ በልዩ ለዛ ጣፍጠው የቀረቡ ነበሩ፡፡ ክብሬ ከሁሉ በላይ ሀይልን የሚሰጥ እግዚአብሄር
ስለሆነ ክብሩን እርሱ ይውሰድ ትላለች፡፡ ሞገስ ከወደየትም እንደማይገኝ ታውቃለች -ከጌታ ብቻ……. ይህ ሞገስ ደግሞ ወደፊትም ተጨምሮ
እንደሚሰጥ ታምናለች፡፡ በዚህ መልኩ ሀገር እያገለገሉ ያሉ ሰዎችን ታሪክን መሰነድ ለአዲሱ ትውልድም እጅግ ጠቃሚ ነው እንላለን
እንደተወዳጅ ሚድያ-ክብሬና ቤተሰቧ በርቱ ---- ትቀጥላላችሁ፡፡ /
ይህ ጽሁፍ ከጋዜጠኛ ክብሬ ተስፋዬ የተገኘውን መረጃ መሰረት በማድረግ የተጻፈ ሲሆን ከዚህ ቀደም የመራቻቸውን መድረኮችና የቲቪ መሰናዶዎች በማየት
የተሰራ ነው፡፡ ይህን ጽሁፍ ለማጠናከር ስንል ወደ 40 የሚጠጉ የክብሬን ችሎታ የሚያሳዩ ቪድዮዎችን ተመልክተናል፡፡ ይህ የህይወት
ታሪክ በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ የተጠናከረ ሲሆን ዛሬ ሰኔ 14 2014
በዊክፒዲያ ላይ በተወዳጅ ሚድያ የፌስ ቡክ ገጽ እና በተወዳጅ ብሎግ ላይ የወጣ ነው፡፡ አስፈላጊው ማሻሻያ እየተደረገ በየጊዜው እንዲወጣ ይደረጋል፡፡
ከክብሬ መድረኮች በጥቂቱ
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ