" ሙያ በልብ ነው " - ባዩ

       ሺበሺ ዓለማየሁ ( ሺቦ ) ዊኪፒዲያ  ታረመ

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን፣ የሚድያ ሰዎችን ታሪክ በመጽሀፍ፤ በድምጸ -መጽሀፍ፣ በማህበራዊ ድረ-ገጾች እንዲሁም በልዩ ልዩ የመገናኛ ዘዴዎች እያቀረበ ይገኛል፡፡ በዚህ ስራውም ከፍተኛ ተቀባይነት ከማግኘቱ ሌላ የኢትዮጵያውያን የሚድያ ሰዎች የምርምር ማዕከልን እያቋቋመ ይገኛል፡፡ የሚድያ ሰዎችን በተመለከተና ከታሪክ ስነዳ ጋር ለሰዎች እውቅና ከመስጠት ጋር በተያያዘ ትውልድ የማይዘነጋውን ስራ በቅርቡ ይፋ ያደርጋል፡፡በዚህ መጣጥፍ ህይወት ታሪካቸውን ከምንዳስስላቸው ጠንካራ የሚድያ ሰዎች ተጠቃሹ ሺበሺ ዓለማየሁ ነው፡፡ሺበሺ በሚድያው አለም በቆየባቸው 26 አመታት ለብዙዎች መትረፍ የሚችል ልምድ አካብቷል፡፡ በኢቲቪ በዋልታ በአማራ ሬድዮ በፋና ቲቪና ሬድዮ በመስራት አቅሙን ያስመሰከረ የሚድያ ሰው ነው፡፡ በሀገራችን የኤሌክትሮኒክስ ሚድያ መስፋፋት በጀመረባቸው 1980ዎቹና መጨረሻ እና 1990ዎቹ አመታት ግንባር ቀደም ከነበሩና ትልቅ የትጋት አሻራ ካኖሩ ባለሙያዎች ዋነኛው ሺበሺ ነው፡፡ በተለይም በመዝናኛ እና በዘጋቢ ፊልም ስራዎች በጥልቀት የሚያውቁት ይመሰከሩለታል፡፡ የሺበሺ ታሪክ ለትውልዱ አንዳች ቁምነገር ያስጨብጣል ብለን ስላመንን  እንደሚከተለው አሰናድተነዋል፡፡

   ሕይወቱንና ሥራዎቹን በወፍ በረር ሊያጋራን ፈቀደ

አንገቱን ደፍቶ ከመሥራት ውጭ ስለራሱ ጥቂትም ቢሆን መናገር የማይሻው ጋዜጠኛ ሺበሺ ዓለማየሁ ዛሬ እጁን ሠጥቷል። ከእልህ አስጨራሹ ጉትጎታ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሕይወቱንና ሥራዎቹን በወፍ በረር ሊያጋራን ፈቅዷል። ተወዳጅ ሚዲያም ሺቦን በማግኘቱ ታላቅ ደስታ ተሰምቶታል።ምስጋናችን ይድረሰው።

የሚያውቁትና አብረውት የሠሩት በአንድ ቃል "ሺቦ" እያሉ ይጠሩታል። በእርግጥ " ሺቦ የሚለው አጠራር ምቾት አይሰጠንም" የሚሉ ሰዎች አልጠፉም።አብዛኞቹ ወዳጆቹ ግን  "ሺቦ" ቢሉት ይወዳሉ።ይህንኑ የቁልምጫ ስም እሱም አይጠላውም።እንዲያውም ይበልጥ ይመቸዋል።

      እንደመነሻ....

መምህር ዓለማየሁ ተፈራ ሐረር ተወለደው ሐረር ነው - ያደጉት። 1960ዎቹ መባቻ ከሐረር መምህራን ማሠልጠኛ ተቋም በመምህርነት ሙያ ተመረቁ። የስራ ቦታ ምደባ ዕጣቸውን ሲመዙ "ጎንደር" መዳረሻቸው ሆነች። በጎንደር የተለያዩ ትምህርት ቤቶች እያስተማሩ እዛው ከአደጉት ከወይዘሮ አታላ መብራቴ ጋር ተዋወቁ። ከዓመታት በኋላም ትዳር መሥርተው የበኩር ልጃቸውን ሺበሺ ዓለማየሁን ታኀሳስ 24 1967 . ወለዱ።

ሺቦ ሁለት ወንድሞችና ሦስት እህቶች አሉት። አባትና እናቱ 50 ዓመታትን እጅግ በሚያስቀና ትዳር ኖረዋል። ከሁሉም ልጆቻቸው 11 የልጅ ልጆችን አግኝተዋል ዛሬም በሕይወት አሉ። ፈጣሪ ረጅም ዕድሜንና የተሟላ ጤናን ያድላቸው!



            









                            ትምህርትና ዕድገት....

ሺበሺ ዓለማየሁ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለው ጎንደር ቀበሌ 04 በሚገኘው ፃድቁ ዮሐንስ ትምህርት ቤት ነበር።ፃድቁ ዮሐንስ ከሃገር ተሻግሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ አንጋፋና ስመጥር ምሁራንን ያፈራ ትምህርት ቤት ነው። ሺቦ በዚህ ትምህርት ቤት ንቁና የደረጃ ተማሪ ነበር።

በመቀጠል በተለምዶ "አቦ" እየተባለ ወደ ሚጠራው ዕድገት ፈለግ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አመራ። ከቀለም ትምህርቱ በተጓዳኝ በጎንደር ከተማና አካባቢዋ የኪነጥበባትና የሥነ ፅሑፍ እንቅስቃሴ መማረክ ጀመረ።ከመማረክ ተሻግሮም ገና በለጋ  ዕድሜው በቀጥታ መሳተፉን ተያያዘው። ያኔ ያቀርባቸው የነበሩት የግጥምና የሥነፅሑፍ ሥራዎች ዕድሜውን የማይመጥኑ እንደ አዋቂ ሥራዎች ከፍ ያሉ እንደነበሩ አብሮ አደጎቹ ይመሠክራሉ።

ገና 12 ዓመቱ፣የ7 ክፍል ተማሪ ሆኖ በሃገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደ የሥነ ፅሑፍ ውድድር በሕፃናት ምድብ አሸናፊ ሆነ። ይህ አጋጣሚ የሕይወቱ አንደኛው ትልቅ ምዕራፍ ሆኖ ይጠቀሳል። (ነፍሳቸውን ይማርና) በአዋቂዎች ዘረፍ አሸናፊ ከነበሩት ከመምህር ጥዑመ ልሳን ጋር በመሆን ከጎንደር ተነስተው በአውሮፕላን ተጉዘው አዲስ አበባ ደረሡ። ያኔ የሥርዓቱ የቅስቀሳና ፕሮፓጋንዳ ዘርፍ ኃላፊ ከነበሩት ከጓድ ሽመልስ ማዘንጊያ እጅ በደማቅና ከፍተኛ ሥነስርዓት ሽልማታቸውን ተቀበሉ።  የወላጆቹ፣የመምህራን እና የመላው ወዳጆቹ ኩራትና ደስታ እጅግ ልዩ ነበር። በወቅቱ በተለያዩ የዕድሜ እርከን ይገኙ የነበሩ ከሁሉም ክፍላተ ሃገራት የተውጣጡ በተለያዩ የኪነጥበባት ዘርፎች  ያሸነፉ ተወዳዳሪዎች ነበሩ። በዚያ የልጅነት ዕድሜው ከውድድሩ አሸናፊዎች መካከል የጣምራ ጦር መፅሐፍ ደራሲ ገበየሁ አየለን ደራሲ ውዳላት ገዳሙን ጋዜጠኛ ሶሎሞን ሹምዬንና በሥዕሉ ዘርፍ የሠዓሊ ለማ ጉያን ልጆች እንደሚያስታውሳቸው ይናገራል። እነ ወጋየሁ ንጋቱ የተሳተፉበትን ተውኔት ጨምሮ በሁሉም ቴኣትር ቤቶች የተለያዩ ትርዒቶችን መጋበዛቸውን አንጋፋውን ብርሃንና ሠላም ማተሚያ ቤት ፣ብሔራዊ ሙዚየምን እና ሌሎች ታላላቅ ተቋማትን የመጎብኘት ዕድል ማግኘታቸውን ያስታውሳል። በዚያ አይረሴ ድንቅ አጋጣሚ ሺበሺ  ከሌሎች ሁለት ታዳጊዎች ጋር በመሆን ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን "የልጆች ጊዜ" ዝግጅት ክፍል ተወዳጅ ባልደረባ ትሩፋት ገብረየስ ጋር ቃለ-ምልልስ አድርገዋል።በተመሳሳይ ጋሽ ሰለሞን  ገብረስላሴ ይመራውና ያዘጋጀው በነበረው የኢትዮጵያ ሬድዮ "ከልጆች ዓለም" ፕሮግራም ላይም ቀርበዋል።

ከአዲስ አበባ መልስ የሥነ-ፅሑፍ ሥራውንና ትምህርቱን የገፋበት ሺበሺ ፋሲለደስ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን ተቀላቀለ። ፋሲለደስ ደግሞ ሌላ ዓለም ነው።በትምህርታቸው የላቁ በሥነ-ፅሑፍ ክህሎታቸው የመጠቁ ተማሪዎች የሞሉበት። ሺቦ በአጭር ጊዜ የትምህርት ቤቱ ግንባር ቀደም የሚኒሚዲያ ተሳታፊና መሪ መሆን ቻለ። በመምህር ሺባባው አየለ አስተባባሪነት ከሌሎች ጓደኞቹ ጋር የግጥምና የአጭር ልቦለድ ሥራዎችን በብዛት ማቅረብ ቻሉ። ከሁሉም በላይ ግን መምህር ጎይቶም ኃይሌ ፅፎ በሚያዘጋጃቸው ተውኔቶች በፕሮግራም መሪነትና በተዋናይነት የነበረው ተሳትፎ አይዘነጋም። የመምህር ጎይቶም ሥራዎች ከትምህርት ቤቱ ግቢ ተሻግረው በከተማዋ ታላላቅ አዳራሾችም መቅረብ የቻሉ ነበሩ። ከጓደኞቹ ጋር "The Split" የተሰኘ የእንግሊዝኛ ቲያትር ለመድረክ ማብቃታቸውንም ያስታወሳል።

የሺበሺ ሕይወት ሲቃኝ ሳይጠቀስ የማይታለፈው ሌላው ጉዳይ "ጓደኝነት" ነው። የሺቦ ጓደኞች "መንትዮች" በሚል ነበር - የሚገለፁት።ፈፅሞ ተለያይተው አይታዩም።በሠፈርም በትምህርት ቤትም አብረው ነው።እስክንድር በለጠ ፍቅሬ ባዬ ሺፈራው ከበደ አሠፋ አያሌው ፣መላኩ ክብረትና ሺበሺ ዓለማየሁ አንድም ስድስትም ነበሩ። ወንድማማቾች እንጂ ጓደኛሞች አልነበሩም።በጋራ ሆነው ብዙ አልፈዋል።ብዙ አሳልፈዋል።

1982 . - ሺበሺ ዓለማየሁ ለከፍተኛ ትምህርት የሚያበቃ ውጤት አምጥቶ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስድስት ኪሎ ግቢን ተቀላቀለ። በዋናነት የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነፅሑፍ በንዑስ ደግሞ ታሪክ (History) አጠና።

ሺበሺ ዓለማየሁ ወደ ብላቴ በዘመተው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ቡድንም አባል ነበር። በብላቴ ወታደራዊ ማሠልጠኛ ከስድስቱ የጎንደር ጓደኞቹ ጋር ዳግም መገናኘቱ እስከዛሬ የሚገረምበት አጋጣሚ ነበር።ቀደም ሲል ሁሉም ወደ ተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ሲገቡ ተለያይተው ነበርና የጓደኝነት አምላክ መልሶ ሲያገናኛቸው ማንም ሊያምን አልቻለም።

"ብላቴ ለእኔ ዕድልም፤ አደጋም ነበር" ይላል - ሺበሺ። በተለያየ አጋጣሚ የታመሙ ትምህርታቸውን አቋርጠው በኬኒያ በኩል የተሰደዱ ሕይወታቸውን ያጡ በርካታ ጓደኞች እንደነበሩት በሀዘን ስሜት ያስታውሳል። በሌላ በኩል እንደ እነ መስፍን አሸብር ብሩክ ከበደ ዓለምፀሐይ መሠረት ከመሠሉ የተባ ብዕር ከነበራቸው የሥነ-ፅሑፍና የሠልጣኝ ተማሪዎች ተወካዮች በቅርበት ከሕይወት መማር መቻሉ ከሁሉም የሃገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች ከመጡ ተማሪዎች ጋር በአንድ ማዕከል ተገናኝቶ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በቅርብ መረዳቱ እንዲሁም ለአካላዊና ለአዕምሯዊ ጥንካሬ በሚሰጠው ወታደራዊ ሥልጠና መሳተፉ የብላቴ ዕድሎቹ እንደነበሩ በኩራት ይናገራል።

1986 . የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋዎችና ሥነፅሑፍ ትምህርት ክፍል የተማሪዎች ምረቃ መጽሔት ላይ ሺበሺ ዓለማየሁ "ሐውልቱ!" የሚል ርዕስ የሠጠውን አጭር ልቦለድ አስነበበ።የሐውልቱ መቼት "ብላቴ" ሲሆን ገፀ -ባህርያቱ ደግሞ ከጎንደር እስከ ብላቴ ያልተለዩት አምስቱ ጓደኞቹ ነበሩ።ስማቸው እንኳ አልተቀየረም።

ሺቦ ከዩኒቨርሲቲ ምረቃ በኋላ የተመደበው ተወልዶ ከአደገበት ጎንደር መቶ ኪሎሜትር ርቀት በምትገኘው ደባርቅ ከተማ ነበር። በደባርቅ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የአማርኛ ቋንቋና የታሪክ (History) መምህር ሆኖ አንድ ዓመት ሰራ።ከመደበኛ የመማር ማስተማር ስራው በተጓዳኝ እርሱ ባለፈበት መንገድ ጠንካራ የሚኒሚዲያ የቲያትርና የሥነፅሑፍ ክበብ አደራጀ።በተማሪዎችና በትምህርት ቤቱ ብቻ አልነበረም   በአካባቢው ማኀበረሰብ ዘንድም በአጭር ጊዜ  ተቀባይነትን ማግኘት ቻለ። የረጅም ዓመት ልምድ ያላቸው መምህራን በነበሩበት በደባርቅ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በተቀጠረ ገና በአራት ወሩ ከተማሪዎቹ በዕድሜ ብዙም የማይተናነሰው ሺበሺ ምክትል ርዕሠ መምህር ሆኖ ተሠየመ።

            ሺበሺና ሚዲያ (ሕልም ዕውን ሲሆን)

ሺበሺ ዓለማየሁ ከዩኒቨርሲቲ በተመረቀ በሁለተኛ ዓመቱ (መምህር ሆኖ በተቀጠረ ደግሞ በዓመቱ) ወደሚወደው የጋዜጠኝነት ሙያ አቀና። የዓመታት ሕልሙም ዕውን ሆነ።በጊዜው አጠራር የክልል ሦስት በኋላ የአማራ ክልል ባህል ቱሪዝምና ማስታወቂያ ቢሮ (..) ጋዜጠኛ ሆነ። ጊዜውም  1988 መሆኑ ነው፡፡በማስታወቂያ መምሪያ ሥር የምትታተመው "በኩር" ጋዜጣ ለሚዲያ ልክፍቱ የመጀመሪያዋ ማሟሻ ሆነች። ሺበሺ በበኩር ጋዜጣና መጽሔት ቆይታው በሙያቸው ሠፊ ልምድ ከነበራቸው ጀማል መሐመድ፣አበረ አዳሙ ጌታቸው ፈንቴና ከሌሎችም መልካም ልምድ መቅሰሙን ያወሳል።ያኔ "በኪነ-ጥበባት፣ በቱሪዝምና በባህል ጉዳዮች ዙሪያ የሠራኋቸው መጣጥፎች ለዛሬ እኔነቴ መሠረት ሆነውኛል" ይላል። በተለየ ሁኔታ ግን " ክህሎቱ ተዳፍኗል" በሚል ቁጭት በተዋናይ ሱራፌል ተካ ሕይወትና ስራዎች ላይ ያዘጋጀው ፅሑፍ ፈጣን ውጤት ማምጣቱ ያስደስተዋል። " ከሊስትሮነት እስከ ፊልም ተዋናይነት" ይል ነበርየፅሑፉ ርዕስ።በአርቲስቱ አስገራሚ የጥበብ ጉዞ መነሻ ላይ የተፃፈ ነበር። የራሱ ድንቅ ብቃት እንደተጠበቀ ሆኖ ሱራፌል በአማራ ክልል የባህል ቡድን ይቀጠር ዘንድ ፅሑፉ አስተዋፅኦ ነበረው።

በመቀጠል ሺበሺ ዓለማየሁ በአዲስ ቴክኖሎጂና አቀራረብ ስራ ወደ ጀመረው የአማራ ሬድዮ ተዛወረ። በስዊድን ባለሙያዎች የተሰጠውን ሥልጠና አጠናቀው የአማራ ሬድዮን ከጀመሩት መካከል ይመደባል። በወቅቱ የክልሉ ርዕሠ መስተዳድር አቶ አያሌው ጎበዜ ከባልደረቦቻቸው ጋር ስቱዲዮ ተገኝተው ጣቢያውን በይፋ ሥራ ሲያስጀምሩ የፕሮግራም መሪዎቹ ሺበሺ ዓለማየሁና አፀደ ውድነህ ፕሮዲዩሠሩ ደግሞ ዜና ታደሠ ነበሩ።

ሺቦ የባሕርዳር ቆይታውን ቋጭቶ ወደ አዲስአበባ ለመዛወር ወሠነ።ከባሕርዳር ጀምሮ እስከዛሬ እንደ ወንድም የሚቀርበው ወዳጁ ዑመር ማሕሙድ ቀድሞት አዲስአበባ ደርሶ ነበርና ተቀበለው።ዑመር ቤት ጥቂት ከሠነባበተ በኋላ ሬድዮ ፋና ያወጣውን የቅጥር ፈተና በአጥጋቢ ሁኔታ ካለፉት መሐል ሆነ። ጊዜውም 1990 ነበር፡፡ 1990 ሸዋዬ ለገሠ፣አርጋው አሽኔ፣ ትዕግስት ካሣ፣ስምረት ያሳቡ አብረውት የተቀጠሩ ጋዜጠኞች ነበሩ።ሬድዮ ፋና የጋዜጠኝነት ሕይወቱ ወሳኙ ቦታ መሆኑን የሚናገረው ሺበሺ በወቅታዊ፣ በሬድዮ ዶኩመንታሪና "ሕዝቡ ምንይላል?" በተሰኘው የምርመራ ዘገባ ብዙ እንደሠራ ያወሳል።ወደ ሁሉም የኢትዮጵያ አቅጣጫ ተጉዞም በርካታ የመስክ ሥራዎችን እንዳከናወነ ይናገራል። ከባልደረባው ወንድወሠን ከበደ ጋር በቡሬ ግንባር አይረሴ የበዓል መድረክ አዘጋጅተው ለአየር አብቅተዋል። ክበበው ገዳና ሌሎች ስመጥር ከያንያን የተሳተፉበት፣ ሠራዊቱ እጅግ የተደሠተበት ነበር - መድረኩ።

ሬድዮ ፋና ራሱ ተቋሙም ሆነ ሠራተኞቹ በፍጥነት የሚያድጉበት ቤት መሆኑን ይናገራል።"በእርግጥ ግምገማውን ብዙዎቻችን አንወደውም ነበር።ሥራ ላይ ያተኮረ ሒስ ወይም ግምገማ አይጠላም።የያኔው ግምገማ ግን ከዚያም በላይ ይሻገራል።በግለሰብ ጓዳ ጎድጓዳ ሳይቀር ይገባል።ያም ሆኖ ሬድዮ ፋና የሥራ ባሕሉ ልዩ ነው።የጣቢያው መሪዎችና ሠራተኛው እንደቤተሰብ ነበሩ። ለምሳሌ እኔን ከቤተሰቦቼ እኩል ደግሰው የዳሩኝ የፋና ኃላፊዎች፣ ሠራተኛውና ምርጦቹ ጓደኞቼ ናቸው፤ፋና ለሌሎችም እንደዛ አድርጓል" ይላል - ጋዜጠኛ ሺበሺ ዓለማየሁ።ሺበሺ ፋና በቆየባቸው 8 አመታት ብዙ ነገር መማሩን ያወሳል፡፡ 1990-1998 በፋና ያሳለፈው ጊዜ መልካም እንደነበር ሺበሺ ያስታውሳል፡፡

ቀጣዩ የሺበሼ ማረፊያ ... ( የኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ) ነበር። 1998 ኢቲቪን ተቀላቀለ፡፡ ከአዘጋጅነት እስከ መዝናኛ ክፍል አስተባባሪነት ሠርቷል። በቴሌቪዥን የመዝናኛ ዝግጅት ክፍል በባህልና ቱሪዝም፣በኪነጥበባትና የበዓላት ዝግጅቶች ላይ ትልቅ አስተዋፅኦ ነበረው።በተለይ 2000 የኢትዮጵያ ሚሌኒየም በተሠሩ በርካታ የዕቅድና የሁነት ፕሮግራሞች ላይ ከባልደረቦቹ ጋር ታላላቅ ስራዎችን ሠርተዋል።

የዛሬ 16 ዓመት በድሬዳዋ ድንገት የተከሰተውን ጎርፍ ተከትሎ በርካቶች ሕይወታቸውን ማጣታቸው፣ መፈናቀላቸውና ንብረት መውደሙ ይታወሳል። ክስተቱ የመላው ኢትዮጵያውያንን ልብ ሠብሯል።በዚህ ጊዜ የኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ገቢው ለጉዳቱ ሠለባዎች እንዲውል በተከታታይ ልዩ የዕርዳታ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ማቅረቡ ይታወሳል። በየቀኑ በቀጥታ ሥርጭት ይስተናገድ የነበረውን ያንን ፕሮግራም የመሩት ሺበሺ ዓለማየሁና ተመስገን /ሕይወት ነበሩ።ለዚህ ጥረታቸው የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዎች በተለያዩ አጋጣሚዎች ለሁለቱም ጋዜጠኞች  ምስጋናቸውን ቸረዋቸዋል።

በወቅቱ የኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥን ድርጅት  ዋና ሥራ አስኪያጅ (ነፍሳቸውን ይማርና) አቶ ዓለማየሁ አቶምሳ የውጭ ተባባሪ አካላት በግልፅ የሙያተኞች ኮሚቴ ተመዝነው እንዲገቡ ይወስናሉ።ፍላጎቱ ያላቸው የግል አመልካቾች ለመጀመሪያ ጊዜ በግልፅ ማስታወቂያ ይጠራሉ።ከ200 በላይ የፕሮግራም ሃሳቦች ገብተው ተመዘኑ።በዋና ስራ አስፈፃሚው የተሰየመውን የምዘና ኮሚቴ እንዲመራ ኃላፊነት የተሠጠው ሺበሺ ዓለማየሁ ነበር። ኮሚቴው ለወራት ሠፊ፣ጥልቅና ግልፅ ግምገማ አድርጎ ውጤቱን አሳወቀ። አባላቱ ለአከናወኑት ተግባር ከአቶ ዓለማየሁ አቶምሳ እጅ የምስጋና የምስክር ወረቀት ወስደዋል።

የሺበሺ ዓለማየሁ የሚዲያ ልክፍትና ጉዞ አሁንም አላቆመም ።እርሱም በአንድ አይረጋም።አኔልካ እንደተባለው ፈረንሳዊ የእግር ኳስ ተጫዋች የዝውውር መስኮቱ በተከፈተ ቁጥር ከአንዱ የሚዲያ ተቋም ወደሌላኛው ይዘዋወራል።አሁን ደግሞ ዕጣ ፋንታው ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ሆኗል። ጊዜውም 2003 ነበር፡፡ ዋልታ በርካታ የዶኩመንታሪ ፊልሞችን የሰራበት፤ ከሞላ ጎደል መላው ኢትዮጵያን ተዘዋውሮ የቃኘበት ቤት መሆኑን ይናገራል። "አዲስ አበባ ተቀምጦ ኢትዮጵያን አውቃታለሁ ማለት አይቻልም።ኢትዮጵያ ጥልቅና ሠፊ ነች። " እገሌ ከእገሌ " ሳይባል  ከጫፍ እስከ ጫፍ ያለው ኢትዮጵያዊ ባላገር ተመሳሳይ ነው - የዋህና እንግዳ ተቀባይ።አሁን የሚታየው  ውጥንቅጥ በማንና እንዴት እንደመጣ ለእኔ እንቆቅልሽ ነው " ይላል።

በዋልታ ቆይታው " እንደጠፍር አልጋ " የሚል ርዕስ የሠጠውን በመላው ኢትዮጵያ የመንገድ አውታር ላይ ያተኮረውን ዶኩመንታሪ ሰርቷል። የጃፓናውያን ድንቅ ተሞክሮ የሆነውን የካይዘን አመራር ፍልስፍናን በተገበሩ የሃገራችን ተቋማት ላይ ተከታታይ ዘጋቢ ፊልሞችን ለአየር አብቅቷል። በቤኒሻንጉል፣ በጋምቤላ በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች ተዘዋውሮ በአስቸጋሪው ባሕላዊ ማዕድን ቁፋሮ ላይ ያተኮረ ጥልቅ ዶኩመንታሪ አበርክቷል።ከኤርታሌ በርሃ እስከ ራስ ዳሸን ተራራ ባሉ የቱሪስት መስህቦችና ቱባ ባህሎች ላይ የሰራቸው ተከታታይ ዘጋቢ ፊልሞቹም የሚዘነጉ አይደሉም።እንደ አብነት እነዚህ ተጠቀሱ እንጂ የሺቦ ዶኩመንታሪ ስራዎች በርካታ ነበሩ።

ሺበሺ ዓለማየሁ በዋልታ ቆይታው ከተወዳጁ ጋዜጠኛ ጌታቸው ወልዩ እና ከካሜራ ባለሙያው ሃብታሙ ጥላሁን ጋር  ሱዳን ካርቱም፣ገድአሪፍና ከሠላ ተዘዋውረው በሁለቱ ሃገራት መንግስታትና ህዝቦች ታሪካዊ ትስስር ዙሪያ ፕሮግራሞችን ሰርተዋል።የአማራ ክልል የባሕል ቡድን አባላት ከድምፃውያን ሐሊማ አብዱራኽማንና ጌታቸው ኃይለማርያም ጋር ሱዳናውያንንና ኢትዮጵያውያንን ያስደሠቱ ሥራዎቻቸውን አቅርበዋል።እነ አምባሳደር መሐሙድ ድሪር ደግሞ የልዑካን ቡድኑን መርተው ከአቻዎቻቸው ጋር መክረዋል። ታዲያ ከሱዳን መልስ ሺቦ ሁነቱን አቀናብሮ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለተመልካች አድርሷል።

በኬኒያ፣ በዱባይ፣ በዶሃ፣ በኩዌትና በደቡብ ኮሪያ እስከዛሬ ከተመልካች አዕምሮ የማይጠፉ በርካታ ድንቃድንቅ ዜናና ፕሮግራሞችን ለአየር አብቅቷል ።በተለይ ከካሜራ ባለሙያው ኪሩቤል /ዮሐንስ ጋር በኮሪያ የነበራቸው ቆይታና ያዘጋጁት ዘጋቢ ፊልም ፈፅሞ አይዘነጋም። በሴዑል፣በዲያጉና በቡሳን ከተሞች በነበራቸው 2 ሳምንታት ቆይታ ኮሪያውያን 50 ዓመታት ብቻ ከፍፁም ድህነት ወደ ማይታመን ከፍታ ስለመጡበት ምስጢር በጥልቅ ጥናት ላይ የተመሠረተ ዘገባ አቅርበዋል። ስራውን የዋልታው ይበልጣል ጌጡ በድንቅ የቪዲዮ ኤዲቲንግ ጥበቡ ተጠቦበታል።በኮሪያ አፍ " ፓሊ ፓሊ" ወይንም በአማርኛ ቋንቋ " ቶሎ ቶሎ " የሚል  ርዕስ የተሠጠው  ይህ ሥራ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከተላለፈ በኋላ በአዲስ አበባና በክልሎች የተለያዩ መድረኮች እንደ ማስተማሪያ ታይቷል።

ሺበሺ ዓለማየሁ በሬድዮ ትልቅ ልምድ ያካበተበት ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ከአራት ዓመታት በፊት 2010 የቴሌቪዥን ሥርጭት ጀመረ።እናም ቀድሞ ወዳገለገለበት ቤት ዳግም ሊመለስ ግድ ሆነ። እንደ እርሾ ቀድሞ በሌሎች ጣቢያዎች የቴሌቪዥን ልምድ ከነበራቸው ጥቂት ጓደኞቹ ጋር የሬድዮ ልምድ ብቻ የነበራቸውን የፋና ጋዜጠኞች የቴሌቪዥን ጋዜጠኞች ጭምር እንዲሆኑ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል።ሺቦ ፋና ቴሌቪዥን ከሚታወቅበት የዜናና ወቅታዊ ፕሮግራሞቹ በተጓዳኝ በመዝናኛ ዝግጅቶቹም ተወዳዳሪ እንዲሆን ከጓደኞቹ ጋር ለፍቷል።ፋና ቀለማት፣ፋና ላምሮት፣ፋና ግለሰብ (በኋላ ፋና ከዋክብት) የተለያዩ የበዓላት የመዝናኛ ዝግጅቶች የሺቦና የባልደረቦቹ የልፋት ውጤቶች ናቸው።በነገራችን ላይ " ፋና ቀለማት እና ፋና ከዋክብት" ለተባሉት ፕሮግራሞች መጠሪያዎቻቸውን ያወጣው ሺቦ ነው።

ጋዜጠኛ ሺበሺ ዓለማየሁ የመዝናኛ ክፍሉን እየመራ ጎን ለጎን የዶኩመንታሪ ፊልሞችንም ያዘጋጅ ነበር። ለአብነት  የእንጦጦ ፓርክን የተመለከተው ተወዳጅ  የዶኩመንታሪ ስራው ተጠቃሽ ነበር።በኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና በፋና በርካታና ታላላቅ ስራዎችን ከአበረከተው፣ ከአንጋፋው የካሜራ ባለሙያ ታምራት ሰንበቶ ጋር የፓርኩ ግንባታ የመሠረተ ድንጋይ ከተቀመጠበት እስከ ፍፃሜው ድረስ 7 ወራት እዚያው ከርመው መነሻና መድረሻውን አሳይተውናል። ትሁቱና ትጉሁ የቪዲዮ ኤዲተር ሶሎሞን ገብረመድኅን በአማረ ምስልና ድምፅ አስውቦታል። የድሮን ካሜራ ባለሙያው የሚኪያስ ክንዱ ሚናና አስተዋፅኦም ቀላል አልነበረም። " ነገን ዛሬ ማያ " የሚል ርዕስ የተሰጠው ይህ ስራ ፋናን ጨምሮ በዋናዋናዎቹ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ተላልፎ ብዙዎች አድንቀውታል።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ፕሪሳይንስ ከተሠኘ ሃገር በቀል ተቋም ጋር  በመተባበር በኩዌት የኢትዮጵያውያን ሳምንት ፊስቲቫል አሰናድተው ነበር።ጋዜጠኛ ሺበሺ ዓለማየሁና የካሜራ ባለሙያው አሕመድ መሐመድ ከብሔራዊ ቴኣትር የባሕል ሙዚቃ ቡድን አባላት ጋር በኩዌት 10 ቀናት ቆይታ ነበራቸው።ድምፃውያን ስለሺ ደምሴ (ጋሽ አበራ ሞላ) ተስፋዬ ታዬም በተጋባዥነት ታድመው ተመልካቹን አስደስተዋል።የሥዕል ዐውደ ርዕይና ሌሎች ሁነቶችም የተስተናገዱበት ይህ መድረክ እጅግ ደማቅ ነበር።ከኩዌት መልስ ጋዜጠኛ ሺበሺ አንድ ፕሮግራም አዘጋጅቶ በፋና ቴሌቪዥን ለአየር አብቅቷል።

በእንጦጦ ፓርክ ላይ ያዘጋጀውን ፊልሙን የተመለከቱት የመከላከያ ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎች በአዲሱ ዋና መስሪያ ቤት (Head Quarter) ህንፃ ግንባታ ላይ ያተኮረ ዘጋቢ ፊልም እንዲያዘጋጅ በፋና በኩል ጋበዙት።ከካሜራ ባለሙያዎቹ ከአንተነህ ዘለቀ፣ ከደምስ መንግስቱ እና ከሚኪያስ ክንዱ ከታታሪውና ፈጣኑ ቪዲዮ ኤዲተር ከስንታየሁ ስርጋጋ ጋር በመሆን  "በሰራዊቱ ልክ" በሚል ርዕስ የተዘጋጀ መሳጭ ዘጋቢ ፊልም በዋናዋናዎቹ የሃገራችን ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ለአየር አብቅተዋል።

ሺበሺ በቅርቡ በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የሬድዮ ፕሮግራሞች ክፍልን መርቷል። ቀደም ብለው የተጠኑ ፎርማቶች ማሻሻያ ተደርጎባቸው በተሻለ አቀራረብ እንዲተገበሩ የበኩሉን ጥረት አድርጓል። ከክፍሉ ባልደረቦቹ ጋር በመሆን "ማረፊያ" የተሰኘ የቅዳሜ መዝናኛ ፕሮግራም በደማቅ የመክፈቻ ስነ ስርዓት አስጀምረዋል።ዛሬ ይህ ፕሮግራም በአድማጭም በገቢም እያደገ መምጣቱ እንደሚያስደስተው ይናገራል።ነባሮቹ "ካሉበት ይሞክሩ" "ፋና ትረካ" "ፋና ብፌ" እንዲሁም የማርፈጃ ፕሮግራሞች የተወሠነ ማሻሻያ ተደርጎባቸው የአድማጭን ቀልብ እንዲገዙ አድርገዋል። የሬድዮ የበዓላት ዝግጅቶች ይበልጥ ተደማጭ እንዲሆኑና የየክልሎች ተሳትፎ እንዲያድግ ሰርተዋል።

ሺቦ አሁን አብልጦ የሚወደውንና እንደ አዲስ የተደራጀውን የዶኩመንታሪና የምርመራ ዘገባ ቡድን እያስተባበረ ነው።ፋና እንደ ዜናና መዝናኛ ፕሮግራሞቹ በዶኩመንታሪና በምርመራ ዘገባዎቹ ተጠቃሽ ሚዲያ እንዲሆን እየሠሩ መሆኑን ይናገራል። "ውጣውረዶች ቢኖሩትም በጥልቅ ጥናትና ዝግጅት የሰራናቸውን ከፍ ያሉ የዶኩመንታሪ ፕሮግራሞች በቅርቡ ታያላችሁ" ብሏል። እሱ ራሱ በአራቱም የኢትዮጵያ አቅጣጫ ተዘዋውሮ ያቀናበረውን ሌላ ጥልቅ ዘጋቢ ፊልም አጠናቋል።በመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ የግንባታ ስራዎች ላይ የሚያተኩረው ይህ ሥራው በጣም የተደከመበት ነው። ፀባዬ ሸጋው፣ ደከመኝን የማያውቀውና ከዕድሜው አንፃር ተስፋ የተጣለበት የካሜራ ባለሙያው ያሬድ ሳህሉ አሳምሮ ሰርቶታል። የቪዲዮ ኤዲተሩ  ስንታየሁ ስርጋጋ ደግሞ እንደተለመደው ተጠቦበታል።

የሺቦ የሚዲያ አመራር ፍልስፍና ወጣ ይላል።  ሚዲያ እንደ ሲቪል ሰርቪስ ተቋማት አሊያም እንደ ፋብሪካ አይመራም" ባይ ነው። የሚዲያ መሪ እንደሌሎች ተቋማት መሪዎች የቢሮ ሰው መሆን እንደማይገባው ይልቁንም ወርዶ፣ ሰርቶ አሳይቶ ማሰራት እንዳለበት ሠርክ ይናገራል። ለዚህም ነው በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፣በዋልታና በፋና አብረውት የሰሩና የመራቸው ብዙዎቹ ጋዜጠኞች እንደ ታላቅ ወንድም ወይም እንደ አባት የሚያዩት። በእርግጥ እንዲህ ያለውን የአመራር ስልት ሽፋን አድርገው የሚያለምጡ አይጠፉም።ያኔ እነሱን ይቆጣል።ይቀጣል።

በሰራባቸው የሚዲያ ተቋማት ሁሉ ሺቦን የሚወደው ይበዛል።እሱም " ከሚገባኝ በላይ የሰው ክብርና መውደድ እንዳለኝ በተለያዩ አጋጣሚዎች ማረጋገጥ ችያለሁ። ከዚህ በላይ መታደል ምን አለ? " ብሏል - ለተወዳጅ ሚዲያ።

     ለእኔ ትልቁ ሃብትና ገንዘብ - ቤተሰብ!...

ጋዜጠኛ ሺበሺ ዓለማየሁ እንደሚለው የትኛውም ሙያ ውስጥ ፈተናዎች አሉ። የሚዲያ ሕይወት ደግሞ በብዙ በጎና ክፉ ገጠመኞች የታጀበ ነው። " በበጎ ገጠመኞቼ ከልከ በላይ አልቦርቅም በክፉ ገጠመኞቼም አብዝቼ አላዝንም " ይላል። እዚህም እዚያም እንቅፋቶች ቢገጥሙትም ሁሌም ደስተኛ ለመሆን እንደጣረ ነው። ከምንም በላይ የደስታው ምንጭ ቤተሰቡ መሆኑንም አስረግጦ ይናገራል።

ባለቤቱ ወይንሸት አዳሙ በእርሱ ሙያ ውስጥ ነች።ለረጅም ዓመታት በቪዲዮ ኤዲተርነት ሙያ ሰርታለች።አሁን በቅርቡ በአርትስ ቴሌቪዥን " ሀገርን በካሜራ " የሚል ፕሮግራም አዘጋጅታ እያቀረበች ነው። ወላጅ አባቷ ቄስ አዳሙ ተስፋው ከብቸና ደብር እስከ ካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ በተዘጋጀ አውደ ርዕይ  የተሳተፉ የባህላዊ አሳሳል ጥበብ ባለሙያ ናቸው ሺቦ ወይኗን ያገኛት ሬድዮ ፋና እየሰራ መቅረፀ ድምፁን አንግቦ ለቃለምልልስ ቄስ አዳሙ ቤት በሄደ ጊዜ ነበር። ከእርሳቸው ጋር ቆይታ አድርጎ ያዘጋጀውን ፕሮግራም ለአየር አበቃ።የወደፊት የትዳር አጋሩንና የልጆቹን እናት ወይንሸት አዳሙን ደግሞ በልቡ ቀርፆ አስቀመጠ። የሁለቱም ጓደኛ የካሜራ ባለሙያው ዑመር ማሕሙድ ሁለቱን በትዳር ለማጣመር ትልቁን ድርሻ ተወጥቷል። የወይኗ እናት ወይዘሮ ሙሉ ብርቄም ልጆቹን ተንከባክበው አሳድገዋል። 20 ዓመታት በላይ ለዘለቀው የትዳር ሕይወቱም ወሳኙን ድርሻ ተወጥተዋል።

የሺቦ የበኩር ልጅ እየሩሳሌም ሺበሺ ትባላለች። በትምህርቷ ከኬ. ጀምሮ ተሸላሚ ተማሪ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 3 ዓመት ጎበዝ ተማሪ ነች። ታናሿ ፋሲካ ሺበሺም ብሩህ አዕምሮ ያለው ታዳጊ ነው።በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የወጣቶች መዘምራን አባል ነው። በቅርቡ ደግሞ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ትምህርት መከታተል ጀምሯል። በጥቅሉ ጋዜጠኛ ሺበሺ በልጆቹ፣በቤተሰቡ በወላጆቹና በአማቾቹ መባረኩን ይናገራል።ለዚህም ፈጣሪውን ያመሰግናል።

      ዜና ታደሰ ስለ ሺበሺ አለማየሁ የሰጠው ምስክርነት

«…የሬዲዮ ስዊድንን ምርጥ ቴክኖሎጂና ሙያው ተሞክሮ ያካፈሉ የስዊድን ባለሙያዎችን ቃለ-መጠይቅ አድርጎ ለምሽት ሬዲዮ ፕሮግራም ፕሮዳክሽን ለመስራት ስክሪፕት ጽፎ ድምጽ የቀረጸበትን ካሴት በግብዓትነት ለመጠቀም በዘመናዊ መሳሪያ የተሞላው የአማራ ሬዲዮ ስቱዲዮ ተፍ ተፍ እያለ ነው፡፡ ጊዜው  1988 መሆኑ ነው፡፡እኔ ደግሞ ለምሽቱ አየር ላይ ቆይታ ዝግጅት እያደረግሁ ነው፡፡ ስቱዲዮ ውስጥ ካሉት መሳሪያዎች መካከል አነስ ያለ ሳጥን በሚመስል መሳሪያ ላይ ቀይ በተን በመጫን ካሴት ላይ ያለን ሙሉ ድምጽ በሰከንድ ማጥፋት የሚያስችል መሳሪያ አለ፡፡ በዚህ መሳሪያ ድምጽ የተቀረጸባቸውን ካሴቶች እየሰረዝን ለቀረጻ እያዘጋጀን፤ ሽቦ እስቲ የእኔንም እንደሱ አድርጉልኝ? ብሎ የስዊድን በለሙያዎችን ኢንተርቪው ያደረገበትን ካሴት ይሰጠናል፡፡ ካሴቱ ውስጥ ያለው ድምጽ በሰከንድ ጠፍቶ ካሴቱ ለሺበሺ ይሰጠዋል፡፡ ካሴቱን ተቀብሎ የዕለቱ ተረኛ ቴክኒሻን እሱ ከስቱዲዮ ስክሪፕት ሲያነብ ከካሴቱ ላይ ቆራርጦ ያዘጋጀውን ድምጽ ደግሞ ወረቀት ላይ በጻፈው ቅደምተከተል መሰረት እንዲያስገባለት ሲነግረው፡ ካሴቱን እኮ በነገርከን መሰረት ደምስሰነዋል! ብሎ ቀልቡን ግፍፍ ያደርገዋል፡፡ ሺበሺ ከስዊድን ባለሙያዎች ጋር ቆይታ ያደረገበትን ካሴት ሲሰጥ ድምጽ ያሳምርልኛል በሚል መነሻ ነበር፡፡ ለምሽት ይቀርባል ተብሎ የተያዘው ፕሮግራም በዚህ መልኩ ቢስተጓጎልም ፈጣኑ ሽቢሺ ለምን በቀጥታ አናቀርባቸውም? የሚል ሀሳብ አምጥቶ ባለሙያዎቹ ካሉበት ተፈልገውና አጋጣሚው ተነግሯቸው በቀጥታ ስርጭት ገብተው ፕሮግራሙን ባሰበው መንገድ አየር ላይ እንዲቀርብ አድርጓል፡፡»

ስለሽቦ ጥንካሬና ቅንነት አለመመስከር ንፉግነት ነው፡፡ ሺበሺ ዓለማየሁን ለመጀመሪያ ጊዜ የማውቀው በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት መገናኛ ብዙሃን በየሳምንቱ ለህትመት ይበቃ በነበረው በኩር ጋዜጣ ላይ ይጽፋቸው በነበሩ ምስል ከሳች አርቲክሎቹ እና በአብዛኛው ሰራተኞች ዘንድ በነበረው ተቀባይነት ነው፡፡  1988፡፡በወቅቱ እኔ ደግሞ ለቴሌቪዥን ሪፖርተርነት አዲስ ተቀጣሪ ነበርኩ፡፡ በኋላ የክልሉ መንግስት ከሲዳ ባገኘው ድጋፍ እጅግ በጣም ዘመናዊና ዲጂታል የሬዲዮ ስቱዲዮ በመገንባቱ ሺበሺ ከበኩር ጋዜጣ እኔም ከቴሌቪዥን ወደ አዲሱ ሬዲዮ ጣቢያ ተቀላቅለውን የመጀመሪያውን የሙከራ ስርጭት በጋር ስንመራ ግንኙነታችንና ጓደኝነታችን እየጠበቀ ሄዶ አንድ ቤት በጋራ እስከመኖር አድርሶናል፡፡

ሺበሺ ለጋዜጠኝነት የተፈጠረ ስለመሆኑ አብረውት የሰሩት ሁሉ የሚመሰክሩለት ነው፡፡ በጋዜጣ የሚጽፈው አርቲክል በኋላም በሬዲዮ የሚሰራቸው ፕሮዳክሽኖች በጆሮ የሚደመጡ ብቻ ሳይሆኑ እንደፊልም ቁልጭ ብለውየሚታዩ ነበሩ፡፡ የቋንቋ አጠቃቀሙ፣ ሃሳቡን እንደ ዘይት የሚያፈስበትና ነገሮችን የሚተነትንበት መንገድ ድንቅ ብቃቱን የሚያሳዩ መገለጫዎች ናቸው፡፡ ቴሌቪዥን ከገባ በኋላ ስለሚሰራቸው ዜናዎች፣ ፕሮግራሞችና ዶክመንተሪዎች ብስለት ደግሞ ባልደረቦቼ የሰጡት ምስክርነት በቂ በመሆኑ መጨመር አያስፈልግም፡፡ የቴሌቪዥን ስራ ከግለሰቡ ሙያዊ ብቃት በላይ ከካሜራ ማን፣ ከፊልም ኤዲተር፣ ከሾፌር እና ሌሎችልስ የስራ ቡድኖች   ጋር ጥሩ ተግባቦት ይፈልጋል፤ በዚህ ደረጃ ሺበሺ በቃላት ሊገለጽ የማይችል የተግባቦት ብቃት በመታደሉ ስራውን ይበልጥ ተወዳጅና ተናፋቂ እንዲሆን አድርጎታል ፡፡

ሺበሺ የሙያ ባልደረባዬ ብቻ ሳይሆን ከቤትና ከትውልድ አካባቢ ርቆ የበኩርነት ህይወት ፈተናን አብሮኝ የተጋፈጠ ወንድሜም ነው፡፡ በፋና በነበረን ቆይታም በተለያዩ የስራ ዘርፎች ላይ ከሁሉም ሰራተኞች ጋር በሚባል ደረጃ በተወዳጅነት ከመስራቱም በላይ በአድማጭ ተመልካቾች ዘንድ ተወዳጅ የሆኑ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች በመቅረጽና በማስፈጸም ረገድ ድንቅ አሻራውን ያኖረ ጋዜጠኛና የስራ መሪ ነው፡፡

ሺበሺ ያለውን ብቻ ሳይሆን ወደፊት ከሚኖረው ላይ የሚያካፍል፣ ክፋትም ሆነ ምቀኝነት የሌለው ፍጹም ቅን ጋዜጠኛና የስራ መሪ ነው፡፡ ወንድማችን ካለው የስነጽሁፍ ድንቅ ብቃት አንጻር ለብዙዎች የሚተርፈውን ልምድና ተሞክሮን በመጽሀፍ መልክ እንዲያቀርበው እያሳሰብኩ ረዥም እድሜና ጤና እመኝለታለሁ፡፡

                           ዜና ታደሰ በአሁኑ ሰአት በአራዳ ኤፍኤም 95.1 በስራ መሪነት በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡




                   ዘላለም ከበደ ስለ ሺበሺ አለማየሁ የሰጠው ምስክርነት

   ሺበሺ አለማየሁን የማውቀው 1999 . ጀምሮ ነው በሁለት የአገራችን ዕውቅ ተቋማት ማለትም EBC እና FBC ውስጥ አለቃዬ ሆኖ አብረን ሰርተናል እውነት ለመናገር ሺቦ ከሙያው ብቃቱ ባሻገር ምርጥ አባት ነው ጨዋታ ያውቅበታል ያምርበታልም መሪነትን ተክኖበታል ማድነቅና ማበረታታተት ለእሱ ቢተው ይሻላል ...ወዘተ ብቻ ምን ልበል አንድሆኖ ብዙ ሠው ነው

እኔ በግሌ የተገነዘብኩት ነገር ቢኖር በተለይ ለጀማሪ ጋዜጠኞች ምቹ አስተማሪና መሪ ሰው ቢኖር ሺቦ ነው እንዴት አድርጎ ሥራን ማስለመድና ማብቃት እንዳለበት ያውቅበታል ማን ምን የግል ችሎታ እንዳለውና ጉድለቱንም በመገንዘብ አስፈላጊውን እርምጃ በመውሰድ ብቁ ሠው ይፈጥራል ከዚያ በኋላ ታድያ ምኑ ይነገራል ? አቦ ረጅም እድሜ ከጤና ጋር ይስጥህ

እዝራ እጅጉ በተወዳጅ ሚድያ ድርጅትህ አማካይነት  ትልቅ ሥራ ነው የጀመርከው ልትበረታታ ይገባሃል ተባረክልኝ ያንተው ዞላ፡፡

    ዘላለም ከበደ በአሁኑ ሰአት በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን እያገለገለ ይገኛል፡፡ 

                    ሽቦ የእጅ ጽሁፉ 26 አመት ወደ ኋላ

 ስለ ሰዎች የህይወት ታሪክ ሲሰራ ከሚጠኑ ጉዳዮች አንዱ የእጅ ጽሁፍ ነው፡፡ የእጅ ጽሁፍ ውስጥ ሀሳብና ታሪክ አለ፡፡ ሺበሺ 26 አመት በፊት በአማራ ሬድዮ ይሰራ በነበረበት ጊዜ በቀጥታ ስርጭት ገብቶ ሲያስፈጽም የጻፈው ኦሪጅናል ስክሪፕት ከእጃችን ገብቷል፡፡ ይህ 26 አመት ተጠብቆ የቆየ ስክሪፕት 20 አመት እድሜ ከነበረው ሺበሺ የፈለቀ ሲሆን ወቅትን የመናገር አቅም ያለው ነው፡፡ ሺበሺ ያኔ አንድ ብሎ የጀመረው ጽሁፍን በቋንቋ የማስዋብ ጥረት ዛሬም ተጠብቆ መቆየቱን አብረውት የሰሩ ሁሉ በሙሉ አንደበታቸው ይመሰክራሉ፡፡   ይህ የእጅ ጽሁፍ ከዚህ ጽሁፍና ከምስሎች ጋር አብሮ ተያይዟል፡፡

                ዊት አለሙ ስለ ሺበሺ የሰጠው ምስክርነት

ሺበሺ አለማየሁን 2001 ጀምሮ ነው የማውቀው፡፡ በጊዜው ሽቦ የቲቪ የመዝናኛ ኃላፊ ነበር፡፡ እኔ ደግሞ ኢትዮጵያ ሬድዮ ነበርኩ፡፡ ስለዚህ  በስራ መገናኘታችን አይቀርም፡፡ ሽበሺ በእኔ እይታ ጥሩ ጋዜጠኛ ነው፡፡ ሺበሺ በዘጋቢ ፊልም ስራው ብዙዎች የመሰከሩለት ነው፡፡

  ሺበሺ አዳዲስ ፎርማቶች  እንዲቀረጹ ሁሉም ሰው በፎርማት ቀረጻው ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ የሚያደርገው ጥረት ይገርመኛል፡፡ እንደ ፋና ላምሮት ፋና ቀለማት ያሉ ፎርማቶች ሺበሺ ዳይሬክተር በነበረ ጊዜ የተቀረጹ ናቸው፡፡ የበላይ አለቆችን ወርዶ በማሳመን እንዲሁም አስተዳደራዊ ስራዎች በቶሎ ተጠናቀው  ስራ የሚጀመርመበትን ስልት የነደፈ አመራር ነው፡፡ ይህ ቀላል አይደለም፡፡ አንድ አዲስ ፎርማት ከተቀረጸ በኋላ ማኔጅመንቱን አሳምኖ  በጀት አስፈቅዶ ስራው በቶሎ  እንዲጀመር ማድረጉን  አደንቅለታለሁ፡፡  የዶክመንተሪ ስራዎቹ ደግሞ በብዙዎች የሚደነቁ በሳል የሚባሉ ናቸው፡፡ የአመራር ስልቱ ደግሞ ረጋ ብሎ የሚያነጋግር ቀለል ያለ እንደ አባት የሚታይ አይነት ሰው ነው፡፡ ብዙዎቻችን ጋር የሌለ ፖዘቲቭ ኢነርጂ ሺበሺ ጋር አለ፡፡ ነገሮችን በቀና ስለሚያይ ሰዎች ያከብሩታል፡፡  ከፋና የቲቪ ዲፓርትመንት  ወደ ሬድዮ ዳይሬክተር ሆኖ ሲመጣ አዳዲስ ፎርማቶች   ተቀርጸው ተግባራዊ እንዲሆኑ ያስቻለ ነው፡፡ ዛሬ በአድማጭ ዘንድ እጅግ ተወዳጅ የሆነው ማረፊያ ፕሮግራም ምርጥ መሆን የቻለው ሽበሺ ባኖረው አሻራ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ተገቢውን ክሬዲት መስጠት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ለሽቦ ያለኝን አክብሮት መግለጽ እወዳለሁ፡፡ ይህ የእርሱ ታሪክ መውጣቱ ምርምር ለሚያደርጉ ሰዎች ጠቀሜታው ትልቅ ነው እላለሁ፡፡

      ቤርሳቤህ ጌቴ ስለሺበሺ አለማየሁ የሰጠችው ምስክርነት 

ከሺቦ ጋር  በቅርበት የመስራት ዕድሉ የገጠመኝ የቅርብ አለቃዬ በመሆኑ ነበር። በሰራንባቸው ግዜያት  የማደንቅለት ነገር ደግሞ ውሳኔ ሰጪነቱን ነው። ስራን በተመለከተ በየትኛውም የስራ ደረጃ ላይ የሚገኝ ጋዜጠኛ የሚሰጠው ሀሳብ ለስራው  አስፈላጊ ነው ብሎ ካመነበት ፈጥኖ በመወሰን ወደስራ ያሰማራል ይህ ደግሞ በመተማመንና በተነሳሺነት ለመስራት የሚያደርግ ነው። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የፎርማት ቀረፃ እና ማሻሻያ የተደረገባቸው የሬድዮ ዝግጅቶች ተግባራዊ እንዲሆኑ  አድርጓል በተጨማሪም የረዥም ልብወለድ ትረካ በውስጥ ሰራተኞች አቅም ሊሰራ ይችላል ብሎ ለመጀመሪያ ግዜ ውሳኔ ያሳለፈ ሲሆን ይህም በሚመራቸው ጋዜጠኞች አቅም ላይ ያለውን እምነት የሚያሳይና ከፍተኛ ተነሳሺነትን የፈጠረ መሆኑን ማየት ችለናል። ሺቦ አብረውት ለመስራት የሚመች ፈጠራንና አዳዲስ ሀሳብን የሚያበረታታ ቀና አመለካከት ያለው ሰው መሆኑን በነበረን የስራ ግዜ ለመታዘብ ችያለሁ። የዶክመንተሪ ስራዎቹ ደግሞ  የተወደዱ ለመሆናቸው እኔም እንደተመልካች ምስክርነት የምሰጥበት ነው።


         ጌጡ ተመስገን ስለ ሺበሺ አለማየሁ

 

 ሽቦ ምርጥ አለቃዬ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ቲቪ እሰራ በነበረ ጊዜ የስራ መንፈሴን ከሚያነሳሱ የስራ መሪዎች ምናልባትም ጥቂት ከሚባሉት አንዱ ነው፡፡  ሺበሺ ጥሩ አለቃ ነው ብዬ የማናገረው አንደኛ ከስሩ ለሚሰሩ ሰዎች የሚያሳየው መልካም ስሜት ነው፡፡በዚህ መልካም ባህሪው ከልቤ አደንቀዋለሁ፡፡ ሺበሺ ዓለማየሁ ልዩ የሚያደርገው እቅድ ስናቅድ ልብ ብሎ ያደምጠናል፡፡ ከዚያም የእቅዱ ዝርዝር ሀሳብ ላይ ከጋዜጠኛው እኩል ሲገባው እቅዱ መጽደቅ አለበት ብሎ ያምናል፡፡ ሽቦ አንድ ጊዜ በእቅዱ ላይ ካመነበት ኤዲቶሪያል ሄዶ ከማጸደቅ ወደ ኋላ አይልም፡፡ ድሮ የነበሩ አለቆች እቅድ አቅደን ስነሰጣቸው  እቅዱ ይወድቃል፡፡ ሽቦ ከገባ ግን አጸድቆ ይመለሳል፡፡ ይህ ጥሩ ጎኑ ነው፡፡እኔ ብዙ ጊዜ እቅዴ ኤዲቶርያል ሄዶ አይሆንም ተብሎ ሲጣል በጣም እናደዳለሁ፡፡ ሽቦ የመዝናኛ ኃላፊ ከሆነ በኋላ ግን እቅድ መውደቅ የሚሉት ነገር ቀረ፡፡ እኔም ደስ ብሎኝ ስራዬን መስራት ጀመርኩ፡፡  ሽቦ በጣም ምርጥ አለቃ…..



    መስከረም ጌታቸው ስለ ሺበሺ አለማየሁ የሰጠችው ምስክርነት

ስክሪፕት ጽሑፉ መቼም ጉደኛ ነው። አማርኛን ይጠበብባታል። ሲተርከው ደግሞ ነፍስና ስጋ ይዋሃዳሉ። ድምጹን ለዘጋቢ ፊልም ከምመርጣቸው የመ ጀመሪያዎቹ 3 አንዱ ነው። ሽቦ እንደ አባት እየመከረ እንታላቅ ወንድም  እየተቆጣ ባለማወቃችን ሳያሳቅቀን እየሰራ ያስተማረን ታላቅ ሰው ነው። ኃላፊነት ከምርጥ ምግባር አዋህዶታል። ሰባዊነቱ ይገርመኛል። ሰው በድሎት ወይንም በስራ ወቅት አጥፍቶ መቀጣት እንዳለበት ቢያምንም ሕግ ቢያግዘው እንኳ ስለአጥፊው ሰው ከሰውየው በላይ አብዝቶ ይጨነቃል። ከላይ ያለበትን ጫና ተቋቁሞ ለእኛ ግን በነጻነት እንድንሰራ ዋጋ ሲከፍል አውቃለሁ። የመዝናኛ ክፍል ኃላፊያችን ሳለ ደግሞ ልጆች ናቸው ሳይል አብሮን እየወጣ እየገባ በጨዋታ የተዋዙ ተሞክሮዎቹን እያካፈለን ብዙ አይረሴ ጊዜያት አሳልፈናል። ወንድሜ  እዝራ እጅጉ     ጨዋታ የሚወደውን፣ እጅግ ትሁቱን፣ ሰው አክባሪውን ስላከበርከው እናመሰግናለን! ሺበሺ አለማየሁን ከዚህ የተሻለ እድል አግኝቼ ብመሰክርልህ በወደድሁ። በጤና በፍቅር ኑርልን! ሁሌም አከብርሃለሁ።

      ሳምራዊት ተወልደ  ስለ ሺበሺ የሰጠችው ምስክርነት

 ሽቦ እንደ አባት የምናየው ስራ አለም በገባን ጊዜ ዋና አለቃ ሆኖ የመራን ድንቅ ሰው ነው፡፡ ክፍላችን ውስጥ የቤተሰብ ስሜት እንዲሰፍን ያደረገ ሰው ነው፡፡ ስራችንን ቀርቦ  ይከታተላል፡፡ ጥሩ ስራ ሲሰራ ደግሞ አድናቆቱን አይቆጥብም፡፡ ወይ በስልክ አሊያ በአጭር የጽሁፍ መልእክት  ባየው ምርጥ ፕሮግራም ላይ ሀሳቡን ይለግሳል፡፡ ከመሪዎች መካከል በአንደኝነት ደረጃ የማስቀምጠው ሽቦን ነው፡፡ እኔ ብቻ ሳልሆን ብዙ ሰው ይህን ሀሳቤን ይጋራዋል፡፡ ሽቦ ሰውን ለመጉዳት የማይጥር  ሰው ነው፡፡ አለቃ ከምለው አባት ብለው ይስማማኛል፡፡ ከእርሱ ጋር አብረው የሚሰሩ ሰዎች እድለኛ ናቸው፡፡ ሌላው የሽቦ ጥሩ ችሎት የሰዎችን ዝንባሌ ማወቁ ነው፡፡  ማን ምን ቢሰራ ውጤታማ ይሆናል የሚለውን ጠንቅቆ የሚያውቅ ነው፡፡ ተወዳጅ ሚድያም በዊኪፒዲያ   ላይ የሽቦን ታሪክ በመስራቱ ላደንቀው እወዳለሁ፡፡   

መዝጊያ፤ ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ የመዝገበ-አእምሮ ወይም የዊኪፒዲያ መማክርት ቡድን አባላት አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡

ጋዜጠኛ ሺበሺ ዓለማየሁ " አሁንም የሰራሁ ያህል አይሰማኝም። ገና ብዙ እሰራለሁ " የሚል ቁርጠኛ አቋም አለው።  " ዕቅዴ ብዙ ነው። በረሃ ለበረሃ ስንከራተት ያልቋጨሁት ትምህርትም አለ" ብሎናል። ብዙም ስለራሱ መናገር የማይወደው ከአደባባይ ወይንም ከቴሌቪዥን መስኮት የሚሸሸው " ሙያ በልብ ነው" ባዩሺበሺ   ለመጀመርያ ጊዜ ዛሬ በግላጭ ተገኝቷል። ለዚህም ያለንን ታላቅ አክብሮት እንገልጻለን፡፡ ቢሆንም ግን ሀገራዊ ግዴታውን እንደተወጣ እናስባለን፡፡ ጋዜጠኞች በስም እንጂ በዝርዝር ምን ለሀገር እንዳበረከቱ በማይታወቅበት በሀገራችን እንደ ሺበሺ አይነት ሰዎች ታሪካቸውን ሲያጋሩ ብዙዎች እኔስ? ብለው ራሳቸውን ማየት ይጀምራሉ፡፡ ዘመናዊ ጋዜጠኝነት በሀገራችን ከተጀመረ 60 አመት በላይ ቢሆንም የህይወት ታሪካቸውን ሳያጋሩ ያለፉ ጥቂት አይደለም፡፡ ሩብ ክፍለ-ዘመን በሚድያው ዘርፍ በተለይም በኤሌክትሮኒክስ ሚድያ ያሳለፈው ሺበሺ በብዙዎች በጥሩ መልኩ የተመሰከረለት ብርቱ ጋዜጠኛ ነው፡፡ ይህንን ለማወቅ አየር ላይ ያዋላቸውን ፕሮግራሞች ማየት ይበቃል፡፡ እኔ ምን ሰርቼ ነው ታሪኬ የሚሰነደው? በሚባልበት ሀገር ታሪካቸውን ለመንገር ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች ለእኛ ትልቅ ውለታ እንደዋሉልን እናስባለን፡፡ ሺበሺም ከእነዚህ አንዱ ስለሆነ እናመሰግነዋለን፡፡ 29 በላይ ምስሎቹን ሰጥቶን 26 አመት የስራ ልምዱን አጋርቶን ቆም ብሎ ሲያስበው አንዳች ርካታ እንደሚሰማው እንገምታለን፡፡ የሰሩ ሰዎች ጎልተው እንዲወጡ ስንሻ ተከታይ እንዲያፈሩ እንሻለን፡፡ የሺበሺን የህይወት ታሪክ ከመስራታችን በፊት ቅደመ-ጥናት ላይ የተሳተፉ በቅርበት የሚያውቁት 13 ሰዎች እንደነገሩን ለሚድያ የተፈጠረ ሚድያን ለማሳደግ የሚተጋ መልካም ሰው ነው ብለውናል፡፡ እንዲህ አይነት ሰዎች እስከመቼ ታሪካቸው ይደበቃል? የዛሬ የሺበሺ ታሪክ የነገ የዩኒቨርሲቲ ማስተማርያ ይሆናል፡፡ ሺበሺ በህይወቱ ደስተኛ ባበረከተው ሙያ የሚረካ ህይወቱን ቀለል ብሎ የሚኖር በመሆኑ ነገሮች በጎ ይሆኑለታል-ሆነውለታልም፡፡ የዚህ ግለ-ታሪክ አዘጋጅ 4 አመታት ከሺበሺ ጋር እንደመስራቱ ሰብዕናውን አይቶታል፡፡ ሺቦ ብዙ ያልተባለለት እጅግ ሊከበር የሚገባ ሰው መሆኑን ይመሰክራል፡፡ ሀገራችን ለሰሩ ሰዎች እንዲህ መሰነድ ስትጀምር ታናናሾች ይነቃቃሉ- ቀናዎች ይማራሉ፡፡ እኛ ግን የሰሩ ሰዎችን እናጎላለን- ያልሰሩ ሰዎችን እስኪሰሩ ድረስ ታሪካቸውን እናቆያለን፡፡

/ ይህ ጽሁፍ ጋዜጠኛ ሺበሺ አለማየሁ የሰጠውን መረጃ መሰረት በማድረግ ተገቢውን የማጣራት እና የምርምር ስራ በማከናወን የተሰራ ነው፡፡ የምርምር የጽሁፍ እና የአርትኦት ስራው በጋዜጠኛ  እዝራ እጅጉ ተከናወነ፡፡ ይህ ጽሁፍ የባለታሪኩን ሙሉ ይሁኝታ ያገኘና በመጽሀፍ እና በልዩ ልዩ መገናኛ ዘዴዎች እንዲወጣ ተገቢውን ፈቃድ ያገኘ ነው፡፡ ይህ ጽሁፍ ዛሬ እሁድ ሰኔ 5 2014 በዊክፒዲያ ላይ በተወዳጅ ሚድያ ብሎግና የፌስ ቡክ ገጽ የወጣ ሲሆን አስፈላጊው ማሻሻያ እየተደረገበት በየጊዜው እንዲወጣ ይደረጋል







fasika shibeshi 












                       ዜና ታደሰ፤ ሺበሺ ዓለማየሁ ፤ ፋንታሁን ኃይለማርያም

 



                                               ሽቦና ባለቤቱ ወይንሸት አዳሙ








                     

 

      




          

 

 

 

 

አስተያየቶች

  1. ሽቦ ምርጥ ሰዉ። ማንንም የማይንቅ የማይከብድ ሰዉ ። ሽቦ ገና ብዙ ይሰራል

    ምላሽ ይስጡሰርዝ
  2. ሽቦ አመለ ሸጋ ባህሪው እና የሙያ ብቃቱ የሚገለፅበትን ቋንቋ ማግኘት ይከብዳል።
    በአጠቃላይ የእኛ አርአያ ነው።

    ምላሽ ይስጡሰርዝ
  3. ሺበሺ እራሱን ደብቆ የኖረ ትልቅ ባለሙያ ነው። በዚያ ላይ ቀና ሰው ነው።ዛሬ እሱን ስላስታወሳችሁት ደስ ብሎኛል። መልካም የስራ ጊዜ እንዲሆንለት እመኛለሁ። ሁኔ

    ምላሽ ይስጡሰርዝ
  4. የጥረትና የትግል ምሳሌ 💪 ይገባዋል። 🙏🙏😘

    ምላሽ ይስጡሰርዝ
  5. ለሙያው ያለው ድሲፕሊን፣ አክብሮት እጅግ ልዩ ነው! ስለራሱ ማውራት አይወድም ሥራዬ ይቅደም ይናገር ባይ ነው። ለእኔ ጥሩ ተወዳጅ የትዳር አጋሬ ነው። ሙያውንም ትዳሩንም አቻችሎ ለልጆቹ ጥሩ አባት የሆነ ሁሌም በኩራት የማየው ሁሌም ከጎኔ ቀድም የሚገኝ ወንድሜ የልጆቼ አባት ታታሪው ጋዜጠኛ ነው።
    በበረከት ይኑርልኝ
    ወይንሸት አዳሙ / ባለቤት/

    ምላሽ ይስጡሰርዝ

አስተያየት ይለጥፉ

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች