179. እመቤት ደመቀ
ለኪነ
ጥበብና ለማህበራዊ ጉዳዮች ነፍሷ የሚደነግጥ ጋዜጠኛ ነች።
ልቧ ውስጥ የሚንቀዋለል ሀሳብ ማረፊያ እስኪያገኝ አታሸልብም፣ በሙያው ይደረስበት ጫፍ ድረስ መሄድ ህልሟ የሆነው እመቤት፣ በጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ከዲፕሎማ እስከ ሁለተኛ ዲግሪ ተምራለች፣ በአማተር የጋዜጠኞች ክበብና የራዲዮ ተሳትፎ የጀመረው የጋዜጠኝነት ሙያ ፍቅር በትምህርት ተደግፎ ከሪፖርተርነት እስከ ዋና አዘጋጅነት ዘልቋል። ይህ የሙያ ፍቅር በህዝብ እና በግል የመገናኛ ብዙሀን
በህትመትም ሆነ በብሮድካስት ሚዲያ የሙያ ግልጋሎት ከመስጠት ባለፈ የራስ ሚዲያ ፕሮዳክሽን እስከ መመስረት ደርሷል።
መንሽ ፕሮዳክሽንን ከመሰረቱት አንዷ እመቤት ደመቀ ድርጅቱን በስራ አስኪያጅነት እየመራች ትገኛለች።
የልጅነት ህይወት
የወርሀ መስከረሟ እመቤት የአዲስ አመት መባቻ ወርን በጉጉት ከሚናፍቁ ሰዎች አንዷ ናት፤ መስከረም 7 1972 ተወለደች፡፡ መስከረም 7 ይህቺን አለም የተቀላቀለችበት ብቻ ሳይሆን ከባለቤቷ ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ካሣዬ ጋር ትዳር የመሰረተችበት ቀን ነው።
ልጅነቷን ማህበራዊ ህይወት ከደመቀበት፣ አራዶች ሲጠሩ ቀድመው አቤት ከሚሉበት ሰፈር ፣ ከፖለቲካ መናኸሪያው አራት ኪሎ ነው ያሳለፈችው።
አራት ኪሎ ጉርብትና ያየለበት፣ አብሮነት የጎለበተበት ሰፈር ነው። እመቤት ሰፈር ውስጥ አብረዋት የሚጫወቱ እና ቄስ ትምህርት ቤት አብረዋት የሚማሩ ጓደኞቿ ትምህርት ሊጀምሩ መመዝገባቸውን ስትሰማ ከዚህ አብሮነት ተለይቶ መቅረትን አልቀበለው ብላ እድሜዋ ባይደርስም መደበኛ ትምህርት ለመጀመር ቤተሰቦቿን ወተወተች፡፡ መዝጋቢዎች ሲያዩዋት እድሜዋ ለትምህርት አለመድረሱን ተገንዝበው
አንመዘግብም ቢሉም ልጂት በጄ የምትል አልሆነችም። የ5 አመቷን ህጻን እመቤት መማር እፈልጋለሁ ብላ ለተግሳጽ በማይመች መልኩ አምርራ እያለቀሰች በአካባቢው ያሉትን ሁሉ ቀልብ ገዛች፡፡ ጉዳዩን ቆመው ከሚመለከቱት ውስጥ ፈተናውን ከቻለችው ትሞክር የሚል ሀሳብ ቀረበ፡፡
መዝጋቢዎቹ ተመካከሩና ፈተናውን ላታልፍ ትችላለች በሚል ግምት ፈተኗት፡፡ እመቤት የንባብ ፈተናዋን በሚገባ አለፈች፡፡ በጊዜው በዳግማዊ ምኒልክ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀማሪ ከነበሩት የአንደኛ ክፍል ተማሪዎች በእድሜ ትንሿ ሆና መደበኛ ትምህርትን ጀመረች፡፡
እመቤት ከእድሜ እኩዮቿ በተለየ የማንበብ ፍቅር ነበራት፡፡ ከንባብ ጐን ለጐን
ለሬዲዮ የነበራት ፍቅር አይጣል ነው፡፡ ሬዲዮ ለማዳመጥ ጊዜ ለማግኘት ስትል በቤት ውስጥ የምትታዘዘውን ስራ
ቀድማ ጨርሳ ፣ ጥናቷን አጠናቃ የምትወዳቸውን ፕሮግራሞች በጉገት ትከታተላለች፡፡
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በተማረችበት በዳግማዊ ምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሚኒ ሚዲያ ፍላጐት ያላቸው ተማሪዎች ክበቡን እንዲቀላቀሉ ጥሪ ሲቀርብ እመቤትም ከመጀመሪያዎቹ ተሰላፊዎች ቀዳሚ ነበረች፡፡ ሚኒ ሚዲያ ውስጥ የነበራት ቆይታ ለጋዜጠኝነት የነበራት ፍቅር እንዲያድግ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ የምትናገረው እመቤት በኋላም በወቅቱ በወጣቶች ይዘወተሩ ከነበሩ የአማተር ክበባት እንቅስቃሴ ውስጥ ተቀላቀለች፤
በጊዜው ዝነኛ ከሆኑቱ አንዱ የሆነውን የጳውሎስ ኞኞ አማተር የጋዜጠኞች ክበብ አባልም ሆነች፡፡ ትምህርትሽን አርፈሽ ተማሪ በሚል በቤተሰቦቿ ብርቱ ተቃውሞ ቢገጥማትም ከምትወደው ሙያ ላለመራቅ ቤተሰቧን ለማሳመን ብዙ ጥረት አድርጋለች፡፡ በክበብ ቆይታዋ ከጀማሪ እስከ አንጋፋ ባለሙያዎችን የማግኘት፣ ልምድ የመቅሰም እድል ከማግኘቷም ባሻገር
የተለያዩ ጽሁፎችን ለሬዲዮ ጣቢያዎች እና ለጋዜጦች በመላክ ትሳተፍ ጀመር፡፤ በኋላም በሬዲዮ ጣቢያዎች የነበራትን ተሳትፎ በማጠናከር ከራሷ ስራዎች በተጨማሪ የሌሎችንም ጽሑፎች በድምጽ ማቅረብ ቻለች፡፡ ይህም ሌላ ተጨማሪ ጉልበት ሆናትና በፖሊስ እና ህብረተሰብ ለሚቀርቡ አጫጭር የራዲዮ ድራማዎችን እና መጣጥፎች በአቅራቢነትም በጸሀፊነትም ተሳታፊ ሆነች። እነዚህ ሁሉ የወጣትነት ሩጫዎች ፣የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ ድረስ የዘለቁ ራስን የመፈለጊያ ሩጫዎች ናቸው።
ትምህርት
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ በቀድሞው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት በህትመት ጋዜጠኝነት በዲፕሎማ ተመረቀች፡፡ በቀጣይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪዋን በጆርናሊዝም ኤንድ ኮሙኒኬሽንስ አግኝታለች፡፡
የሙያ ክህሎት እና የስራ ቦታ
የመጀመሪያ ስራዋን ሀ ብላ የጀመረችው በአዲስ አበባ መገናኛ ብዙሃን ውስጥ ነበር፡፡ ተቋሙን የተቀላቀለችው በፕሩፍ ሪደርነት ቢሆንም ከነፍሷ የምትወደው የጋዜጠኝነት ሙያ ስለሚስባት በወቅቱ ተቋሙ በሚያሳትማቸው ጋዜጣና መጽሄት፣ በሬዲዮና በቴሌቪዥንም ትሰራ ነበር፡፡
በቀጣይም የኢትዮያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ያወጣውን የቅጥር ማስታወቂያ ከ3ዐዐ ተወዳዳሪዎች በአንደኝነት በማሸነፍ ኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ን ተቀላቀለች፡፡ በኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ስራ እንደጀመረች የሬዲዮ ዘርፍ ስራ አስኪያጅ የነበሩት ኃላፊ ቢሯቸው ጠርተው በጣቢያው የሴቶች ፕሮግራም ስለሌለ አንቺ ብትጀምሪ ምን ይመስልሻል? ሲሉ ጥያቄ አቀረቡላት፡፡ እኔ በምፈልገው ፎርማት ከተሰራ ደስ ይለኛል ስትል መለሰች እመቤት፡፡ አንቺ የምትመርጪው ፎርማት ምንድነው ? ጠየቁ ኃላፊው ሴቶችን የተመለከቱ ሀሳቦች እያነሳን የቀጥታ ውይይት ቢደረግባቸው እመርጣለሁ ስትል መለሰች፡፡ ኃላፊው በሀሳቡ ተስማሙ ፡፡ ፕሮግራሙ ‹‹አዲስ ሴ››ት በሚል ስያሜ በየሳምንቱ መተላለፍ ጀመረ፡፡
በኤፍ ኤም አዲስ 97.1 በሪፖርተርነት ፣ በፕሮግራም አዘጋጅነት እና በአርታኢነት ሰርታለች፡፡ በኤፍ ኤም አዲስ በነበራት የ5 አመታት ቆይታ ዜናና ወቅታዊ ዝግጅቶችን ጨምሮ የተለያዩ ፕሮግራሞችን ለማዘጋጀትና በሙያው ውስጥ ለማደግ እድል አግኝታለች፡፡ በቀጣይም ወደቴሌቪዥን ዘርፍ በመዛወር በማህበራዊ ዘርፍ በተለያዩ ፕሮግራሞች አዘጋጅና አርታኢነት ነበረች፡፡ በወቅቱም በማህበራዊ ዘርፍ ስር ያሉ የወጣቶች፣ የሴቶችና የህጻናት ፕሮግራሞች አርታኢና አስተባባሪ ሆና ሰርታለች፡፡
ከሚዲያ ኢንዱስትሪው መስፋፋት ጋር ተያይዞ የግል የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ብቅ ብቅ ማለት ሲጀምሩ ከ1ዐ አመታት የስራ ቆይታ በኋላ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን በመልቀቅ በኤልቲቪ የዜና ክፍል ኃላፊ በመሆን ስራዋን ጀመረች፡፡ በኋላ ላይም ወደ ፕሮግራም ክፍል በመዘዋወር የፕሮግራም ክፍል ኃላፊ ሆና ሰርታለች፡፡ በወቅቱም በጣቢያው የቢዝነስ ፕሮግራም እና የኢትዮ ሌዲስ ፕሮግራም አዘጋጅና አቅራቢ ነበረች፡፡ በሚያነሳቸው ጾታዊና ቤተሰባዊ ጉዳዮች በብዙዎች የሚታወቀው ኢትዮ ሌዲስ ፕሮግራም መነጋገሪያ መሆን የቻለና ድጋፍና ተቃውሞን ያስተናገደ ፕሮግራም ነበር፡፡
ከኤልቲቪ በኋላም ከሙያ አጋሮቿ ጋር በመሆን መንሽ ፕሮዳክሽንን አቋቋሙ፡፡ ዛሬ በመዲናዋ ስመ ጥር የፕሮዳክሽን ካምፓዎች መካከል አንዱ ለመሆን የቻለው መንሽ ፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችና ተከታታይ ድራማዎችን፣ ዶኩመንተሪዎችን እየሰራ ይገኛል። ማማ አፍሪካ የተሰኘውን ፕሮግራምም የዚሁ የመንሽ የእጅ ስራ ውጤት ነው። ይህንን ድርጅት ዘዋሪዋ ደግሞ ከደርዘን አመታት የተሻገረ የጋዜጠኝነት ልምድ ያካበተችው
እመቤት ናት።
ማማ አፍሪካ ቀደም ሲል በዋልታ ቴቪ አሁን ደግሞ
በአርትስ ቴቪ እየተላለፈ የሚገኝ በማህበራዊ ጉዳይ ላይ አተኩሮ የሚሰራ የቴሌቪዥን ሾው ሲሆን በተለይም በቤተሰባዊ ጉዳይ ላይ ሰፊ ሽፋን ይሰጣል። ሶስቱ ሴቶች ሰብለ፣ ቤዛ እና እመቤት በዚህ መሰናዶ የማይመዙት የህይወት ሰበዝ የለም ፤ ለዛም ይመስላል ፕሮግራሙ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጥሩ ተከታታይ ማትረፍ የቻለው።
እመቤት ከጋዜጠኝነት ባሻገር የተለያዩ ስልጠናዎችን ለተለያዩ አካላት በመስጠት ረገድም አስተዋጽኦ አበርክታለች፡፡ በተለይም ከምርጫ ጋር በተያያዘ በሚሰጡ ስልጠናዎች በሲዳማ ሪፈረንደም እና በ6ኛው ሃገር አቀፍ ምርጫ መሪ አሰልጣኝ/ Lead Trainer እና
ዋና አሰልጣኝ/ Master Trainer በመሆን አሰልጣኞችን በማሰልጠን ሰርታለች፡፡ በዚህም ለምርጫ ቦርድ፣ ለአውሮ ፓሴንተር ፎር ኢሌክቶራል ሰፖርት /European Centere for Electoral
Support –ECES/ እና
ለኢንተርናሽናል ፋውንዴሽን ፎር ኢሌክቶራል ሲስተም /The International foundation for
Electoral System -IFES/ ሰርታለች፡፡
የጋዜጠኝነት
ሙያ ተገቢው ትኩረት እንዲያገኝ ፣ ሙያተኞቹም የሚደርስባቸውን ሙያዊ ጫና መቋቋም እንዲችሉ
የሙያ አጋሮቿ በመሰረቱት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያ ሴቶች ማህበር እና በሃገር አቀፍ ወጣት ሴቶች ማህበር በቦርድ አባልነት በማገልገል ለሙያው መጎልበት የበኩሏን አስተዋጽኦ ተወጥታለች።
እመቤት አሀዱ
ብላ ጋዜጠኝነትን በሙሉ ስራነት
በጀመረችበት በአዲስ አበባ መገናኛ ብዙሃን ድርጅት ነበር ከአሁኑ ባለቤቷ ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ካሳዬ ጋር የተዋወቁት፡፡ ከጥቂት የአብሮነት ቆይታ በኋላም በ1999 ዓ.ም ከሙያ አጋሯና ፍቅረኛዋ ቴዎድሮስ ጋር ትዳር መሰረተች። እመቤት ከትዳር አጋሯ ጋር ሁለት ልጆችን አፍርታለች፡፡







አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ