177.እዝራ እጅጉ

በሀገራችን የመገናኛ ብዙኃን ታሪክ ህትመት ሚዲያው ፈርጣማ ክንዱን ባሳየበት 1980ዎቹ መጨረሻ፣ ትታተም በነበረችኩኩሉየልጆች መጽሔት ላይ አንድ 15 ዓመት ብላቴና የወደፊት ምኞቱን አሰፈረ። በየትኛው የትምህርት ተቋም ምን መማር እንደሚፈልግ፣ ምን ዓይነት መጽሐፍ ማሳተም እንደሚሻ፣እግዚአብሔር ብሎለትሃብታም ቢሆን መክፈት ስለሚፈልገው ድርጅት... የመሻቱን ሁሉ መጽሔቷ ላይ በዝርዝር አሰፈረ። ምንም እንኳ  የዚህ ጽሁፍ አቅራ ቢበዘመኑ ለአቅመ ንባብ ባልደርስም ምኞቱን ያነበቡ አዋቂዎች ግንያሳድግህከማለት አልፈውየምኞቱን ቢያሳካስብለው ያሰቡ አይመስለኝም።

ይህ ከሆነ ከሶስት አስርታት በኋላ፣ የያኔው ብላቴና አሁን ባለው ዘመኑ የሆነውንና በለጋ እጁ ከትቦ የልጆች መጽሔት ላይ ያኖረ የልጅነት ምኞቱን ብናስተያይ መስመር በመስመር ይገጥማሉ። የፈለገውን ተምሮ፣ ያሻውን ጽፎ፣ ያሰበውን ድርጅት ከፍቷል።  ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ተመርቆ፣ የተፈጥሮ ውበት ስለሆነው የሰው ልጅ መጽሐፍትን ጽፎ፣ የሥነ ጽሑፍ ፍቅርና ችሎታ ላላቸው ልጆች የስራ እድልን የፈጠረተወዳጅ ሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን አቁሟል፦ እዝራ እጅጉ። የስራ እድሉ በረከት ከደረሳቸው አንዱ ነኝ  እኔ አማረ ደገፋው፤ ዛሬ ሌላ እድል ደርሶኛል፦ የታሪክ ሰናጁን ሰው ታሪክ መሰነድ።

የተወዳጅ መነሻ 1996 . የካቲት ወር ቢሆንም ለታሪካዊ ስራዎች ትኩረት መስጠት የጀመረው 2008 . ወዲህ ነው። ያለፈውን አንድ አመት ደግሞዘመነኞቹን በዊኪፒዲያበሚል ፕሮጀክት በሀገራችን ባልተለመደ መልኩ ሰዎች በህይወት እያሉ ታሪካቸውን በወጉ ሰድሮ ስላበረከቱት በጎ ተፅዕኖ ማመስገን ጀመረ። 170 የሚደርሱ የሚዲያ ሰዎችን ታሪክ ሰንዶ ጠንካራ ሽፋን ባለው መዝገበ አዕምሮ(ኢንሳይክሎፒዲያ) ለማሳተም ሲሯሯጥ ከግማሽ በኋላ ያለውን መንገድ አብሬው ስለሮጥኩየዚህን ሁሉ ሰው ታሪክ እየሰራ እንዴት የራሱን አይጽፍም...? ለራሱ እንዴት ሰነፈ?’ የምትል የጎን ሃሜት ነበረችኝ። መዝገበ አዕምሮ ወደ ማተሚያ ቤት ለመግባት ሳምንት ሲቀረው የእርሱም ታሪክ መሰነድ እንዳለበት ተማምነን ለቃለመጠይቅ ተቃጠርን። ወደ ቤቱ ሄድኩ፤ ላፕቶፑ ላይ ሆኖ ከጽሁፉ ጋር ግብ ግብ ይገጥማል፡፡

ከልጅነቱ ጀምሮ ይይዛቸው የነበሩ ዲያሪዎች ልቅም ባለ የኮምፒውተር ጽሑፍ ተተይበው በዘመን ቅደም ተከተላቸው የሰፈሩበት ዳጎስ ያለ ጥራዝን ሳይ፣ ከአመታት በፊት ለህትመት የበቁ ስራዎቹን የያዙ ባለጠንካራ ሽፋን መዝገቦችን ሳገላብጥ፣ በቃለመጠይቁ ወቅት ከሃያና ሰላሳ አመት በፊት የነበሩ ክስተቶችን ትላንት የሆኑ ያህል ሲያስታውስና ልክ ቅድም ያገኛቸው ይመስል የሰዎችን ስም ድንቅፍ ሳይል መጥራቱን ስታዘብ፤ለራሱ እንዴት ሰነፈየሚል ትዝብቴን ሽሬ ለረዥም አመታት በትጋት ከተሰነደ ሰፊ ታሪኩ ለአንባቢ እንዲሆን መቀንጨቡን ማሰብ ጀመርኩ።

 እነሆ የታሪክ ወዳዱ እዝራ እጅጉ ቅንጭብ ታሪክ፦

የታሪክ መውደዱ ማሳያ መቼ እንደተወለደ ሲጠየቅየደርግ መንግስት የድል በዓልን ባከበረ በሁለተኛው ቀን እሁድ መጋቢት 30 1971 . ተወለድኩነው መልሱ። በዚያው 1971 አመት ግንቦት ወር  የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ይሰሩ የነበሩት አባቱ አቶ እጅጉ ሙላት  ወደ ጅቡቲ በመዛወራቸው እትብቱ የተቀበረባትን መሬት ሳይድህባት በእናቱ ወይዘሮ በለጥሻቸው ስዩም እቅፍ ሁኖ አባቱን ተከትሎ  ጅቡቲ ገባ። 4 እመት ልደቱን እስኪያከብር በቆየባት የጎረቤት ሀገር ትዝታዎች መካከል አንዱ እሳት ነው። በልጅነት የመመራመር መንፈስ ሁኖእሳት ያቃጥላል አያቃጥልም?’ የሚለውን ለማረጋገጥ ያደረገው ሙከራ ሙሉ ቤቱን በልቶ አሳይቶታል።

ከጅቡቲ መልስ 1976 .ማርች ኤይትትምህርት ቤት ገብቶ ለሁለት አመታት የመዋእለ ህጻናት ትምህርቱን ተከታትሏል። ቀጥሎ ወደቦሌ ህብረተሰብአቅንቶ 1978 . 1 ክፍል ገባ፤ እስከ 4 ክፍል በዘለቀ ቆይታው ዝምተኛና ፈሪ እንደነበር ያኔ አብረውት የተማሩ ጓደኞቹ ያስታውሳሉ፤ እርሱም የያኔ ጭምትነቱን ያምናል።

1981 . ክረምት አባቱን ድጋሜ የምስራቁ ማግኔት ስቧቸው ወደ ድሬደዋ ሲያቀኑ እርሱም ከታናሽ እህቱ ጋር ሁኖ ተከተላቸው። እርሱም እህቱም ዛሬም ድረስልዩብለው የሚገልጿቸውን ሁለት አመታት በድሬደዋ አሳለፉ። ቦሌ ህብረተሰብ እያለ የተረት መጽሐፍትን ማንበብ ድረስ ብቻ የነበረ የሥነ ጽሑፍ ቅርበቱ፤ በድሬዳዋ ቆይታው በብዙ እጥፍ አድጎ ልቦለዶችን እስከመጻፍ ደረሰ። ጥበብ ትጣራ ከሆነ በሥነ ጽሑፍ በኩል የጠራችው በዚህ ዘመን እንደነበር ራሱም ያምናል።  ዛሬም ድረስ በቃሉ የሚወጣቸውን ግጥሞች የያዘችው የክፍሌ አቦቸርየኔ ጋሻመድብልን ደጋግሞ ማንበቡን ያስታውሳል። አባቱ ቢሮ ይመጡ የነበሩ አዲስ ዘመንና የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጦችንና የካቲት መጽሔትን የማንበብ እድሉም ነበረው።

ልዑል መኮንን የተማሩትና በጅቡቲ አመታትን የሰነበቱት አባቱ ለፈረንሳይኛ ቅርብ ስለነበሩ የፈረንሳይኛ ኢንሳይክሎፒዲያ ነበራቸው። ብላቴናው እዝራ ገና ያኔ ይህን መጽሐፍ ሲያገላብጥ ነበር አሁን እያሰናዳ ያለውን መዝገበ አዕምሮ(ኢንሳይክሎፒዲያ) የማዘጋጀት ሃሳብ የመጣለት። እንዲህ ባለ የመነቃቃት መንፈስ ውስጥ ሁኖ 5 እና 6 ክፍልን በድሬደዋ ከተማረ በኋላ ወደ አዲስ ተመልሶ 7 ክፍል ትምህርቱ በድጋሜ ወደ ቦሌ ህብረተሰብ አቀና። የቀድሞ ወዳጆቹ የቀደመ ጭምትነቱን ሲያጡበትእዝራ ፈነዳአሉ። አብሮ አደጉ ናይእግዚ ህሩይ ይህን ጊዜ ሲያስታውስድሬደዋ ምን አግኝቶ እንደመጣ ገርሞናልይላል።

ከመፈንዳቱእኩል ንባቡን አበረታ፤ ግቢያቸው ተከራይ ከነበሩ ሰዎች እየተዋሰ፣ የቅባት ጠርሙሶችን ለቆራሊዮ ሽጦ መጽሔት እየገዛ፣ ናይእግዚና ፍቃዱ ሞላ የተባሉ ጓደኞቹ የሚያመጡለትን መጽሐፍት እየተቀበለ ለንባብ አቀረቀረ፤ እናቱ ወይዘሮ በለጥሻቸውእስኪ እንደልጆቹ ወጣ ብለህ ተጫወትእስኪሉት ድረስ ከወረቀት ጋር ተዋደደ። 8 ክፍል ሲደርስ ለተለያዩ መጽሔቶች አስተያየትና ስራዎቹንእዝራ እጅጉ ከቦሌበሚል አድራሻ መላክ ጀመረ። 42 የዩኒቨርስቲ መምህራን ሲባረሩ ስሜቱን ጽፏል፤ በቃሉ ከያዘው የክፍሌ አቦቸር ግጥም አንዱንአፍሪካ ቀንድለተባለ መጽሔት ምንጭ ሳይጠቅስ ልኮ በመታተሙ እንደተከሰሰም ያስታውሳል። በንባቡና በተሳትፎው ከእኩዮቹ ተለየ፤

9ነኛ ክፍል ሲሻገር ቦሌ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት ገባ። 1986፡፡ ንባብና ተሰጥዖውን ለማሳደግ ሚኒ ሚዲያ ለመግባት ቢያመለክትም ሳይጠራ ይቀራል። በዚህ ተናዶ የሚኒ ሚዲያው በር ላይ ያገኘው አንተነህ ዓለሙን እንዴት በጉልበት ገፍቶት እንደገባ ሲያስታውስምን አለ ካሜራ ኑሮ ሁኔታውን ይዞት በነበርይላል፤ ሳያልፍ በጉልበት በገባበት ቤት ችሎታውን በሚገባ አሳይቶ 4 ወሩ የሚኒ ሚዲያው ምክትል ሊቀ መንበር ለመሆን በቃ።

በዚያው አመት ወደ ለገዳዲ ሬዲዮ ጣቢያ አቅንቶ መሳተፍ ጀመረ። ለመጀመሪያ ጊዜ ለገዳዲ ሲደርስ ተቀብለው፤ ሻይ ጋብዘው፤ ቤተ መጽሐፍቱን አስጎብኝተው ያበረታቱት መምህራንን ዛሬም ድረስ ከነስማቸው ያስታውሳል።ጣሰው ተፈራ፣ ሃይሉ ማሞ፣ ኤርሚያስ ተገኝ፣ ህሊና ማሞ፣ ከድጃ ሰይድእያለ ሲዘረዝራቸው ትላንት ያገኛቸው እንጂ 30 አመት በፊት ያዋራቸው አይመስሉም። ቤተ መጽሐፍቱን በአግባቡ ተጠቅሞበታል፤ ወርልድ ቡክ ኦፍ ኢንሳይክሎፒዲያ... ብሪታኒካጋር ተዋውቆበታል፣ ለገዳዲ ሬዲዮ የጥያቄና መልስ ዝግጅት 300 ያላነሱ ጥያቄዎችን አዘጋጅቶበታል።

1989 . 12 ክፍል ተማሪ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ይተላለፍ የነበረአካፑልኮ ቤይየተሰኘ ፊልምን ወደ አማርኛ መልሶ ከያኔ የትምህርት ቤት ተጋሪው አርቲስት ስናፍቅሽ ተስፋዬ ጋር በመሆን በቦሌ ሚኒ ሚዲያ ተረከ። በወቅቱ ብቼኛ የመዝናኛ አማራጭ በነበረው ኢቲቪ የሚተለለፈው ይህ ፊልም የብዙዎች መነጋገሪያ እንደነበር ያስታውሳል፤ እግር በእግር እየተከታተለ ተርጉሞ ሲተርክ ተማሪዎች በተለየ ጉጉት ነበር የሚከታተሉት። የትምህርት ቤቱ አስተዳደርተማሪ እንዳይፎርፍ ስላደረክብሎ አመስግኖታል።

ከፊልሙ ትረካ መጠናቀቅ በኋላ የሚዲያዎችን ትኩረት ሳበ። ፋንታሁን ኃይለማርያም ከኢቲቪ፣ መስፍን አሸብር ከሬዲዮ ፋና፣ ሰለሞን ጥዑመልሳን ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ስለሰራው የትርጉም ስራ በየተራ አነጋገሩት። መስፍን አሸብር የፋና ስቱዲዮ ድረስ ወስዶ ቃለመጠይቅ እንዳረገውና ከብዙ ጋዜጠኞች ጋር እንዳስተዋወቀው ያስታውሳል። ከቴሌቭዝን ከሬዲዮና ከጋዜጣ በመጡ ጋዜጠኞች ቃለመጠይቅ ተደርጎ ከትምህርት ቤት ውስጥ ዝናው ከፍ አለ። እንዲህ ያለ አድናቆትና መወደድ ያተረፈለትን የትርጉም ስራ በመጽሐፍ መልክ ቢያሳትመው ምን ያህል ገዥ ሊኖረው እንደሚችል ጥናት አደጎ አጥጋቢ ውጤት በማግኜቱ ለማሳተም ቢጥርም አሳታሚ በማጣቱ ደብተሩን ቅርጫት ውስጥ ወረወረው።

1990 . የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍን ለመማር በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የማታው መርሃ ግብር ተመዘገበ። ከአብሮ አደጉ ናይእግዚ ጋር በመሆን የሚዲያ ፈቃድ አውጥተው  ልጅነትየምትል የልጆች መጽሔት ለማሳተም ቢሞክሩም በስፖንሰር ማጣት ምክንያት  ሀሳባቸውን ሳያሳኩ ቀሩ። በተመሳሳይ አመት ወደ ሪፖርተር ጋዜጣ አምርቶ ቅጥር ጠይቆ ስላልተሳካ በነፃ ማገልገል ጀመረ። ለወራት በዘለቀ የነፃ ግልጋሎቱ ደረጀ ደስታ፣ ከበደ ደበሌ ሮቢ፣ ሰለሞን አባተ፣ እሸቴ አሰፋና አብዱ አሊ ሂጅራን ጨምሮ ከሌሎች አንጋፋዎች ጋር ቢሮ ተጋርቶ ጽሑፎቻቸውን አርሟል፣ ዝንቅና ሌሎች አምዶችን አዘጋጅቷል፣ ደሞ በልጅ እግሩም ለአንጋፋዎቹ ተላልኳል። ከሪፖርተር ጋዜጣ በኋላ በተመሳሳይ ግልጋሎት እፎይታ መጽሔትንም ለጥቂት ወራት አገልግሎ፣እፍታየተሰኘች የወጎች መድብል ላይ ስራው ወጣለት።

ቀጥሎ አዲስ ልሳን ጋዜጣ ላይ አመለከተ፤፤ ከብዙ መቶዎች ተወዳድሮ ሃይለ ገብርኤል ይመርን ተከትሎ፣ ታገል ሰይፉን አስከትሎ፣ በሁለተኝነት አለፈና ጋዜጠኛ ሆነ። 1992 . መስከረም ወር ላይ 21 አመቱ፣ ገና 3 አመት የዩኒቨርስቲ ተማሪ እያለ፣ 347 ብር የሙሉ ጊዜ ጋዜጠኛ ሲሆን የተሰማውን ደስታ ሲገልጽአሁን ላይ ማርስ ብሄድ የሚሰማኝ ስሜት ነበር ያኔ የተሰማኝይላል።

መዝናኛ ክፍልን እየፈለገ ዜና ክፍል ሲመድቡት መጀመሪያ ላይ አልከፋውም ነበር፤ እንዲያውምበሳምንት 4 ዜና ማምጣት አለብህያለ አለቃውን በተለየ ጉጉት ሁኖ “7 አይቻልም?” ብሎ ጠይቆት ነበር። የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ሳምንታትን ሰባትም ስድስትም ዜናዎችን መስራት ቢችልም እየቆየ ሲሄድ ግን እንዳሰበው ቀላል ሊሆንለት አልቻለም። በዜና እጦት ራሱን እያመመው ሻሽ አስሮ ቢሮው ይገባ እንደነበር ያስታውሳል። ከስድስት ወራት ቆይታ በኋላ የአዲስ ልሳን ጋዜጠኝነቱን ተወ።

አዲስ ልሳኖች የጻፉበትን ደብዳቤ ይዞ ከአዲስ አድማሶች ደጅ ደረሰ።ለኔ የሚሆን ትክክለኛ ሰውበማለት የሚገልፀው አሰፋ ጎሳዬ በጥሩ ፊት ተቀብሎ 400 ብር ቀጠረው። ከነብይ መኮንን፣ ኤፍሬም እንዳለ፣ ሰለሞን /እግዚአብሔር እና ሌሎችም ጋር ባልደረባ ሁኖ ሲሰራ ዜናንም መዝናኛንም አቀላጥፎ ሰርቷል። አዲስ አድማስ ለአንድ አመት ከሰራ በኋላ ወደ ሩህ ጋዜጣና መጽሄት አቀና፡፡

1994 . ከተመረቀ በኋላ 500 ብር ደመወዝ ፕሬስገባ። በዚያ ጋዜጠኝነትን ብቻ ሳይሆን ማስታወቂያ የማፈላለግ ስራንም ሰርቶ ዳጎስ ያለ ኮሚሽን እንደተቀበለ ያስታውሳል። ምን አልባት ይህቺኛዋ ኮሚሽን ሳትሆን አትቀርም ወደ ቢዝነሱ ዓለም ቀልቡ እንዲሳብ ያደረገችው። በዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ማርኬቲንግን መማር ጀምሮ ነበር። ዮቴክ ኮንስትራክሽን ውስጥ በፐርሶኔልነት 11 ወራት እንዳገለገለም ይናገራል። የቁምነገር መጽሔት ምክትልዋና አዘጋጅና ሴልስ ሁኖም ሰርቷል።

በዚህ ሁሉ የስራ ዙረት ውስጥ ልምዶችን ሲቃርም የሰነበተው እዝራ በየካቲት 2 1996 .ተወዳጅብሎ የሰየማትን ጋዜጣውን ማሳተም ቻለ። ማስታወቂያዎችን ብቻ ይዛ የምትወጣው ይህች ጋዜጣ በነፃ ነበር የምትታደለው። ማስታወቂያ መፈለጉ አያስቸግርም ወይ ተብሎ ሲጠየቅለጥረት ነው የተፈጠርኩትነው ምላሹ። ገቢዋ ከሽያጭ ሳይሆን ከማስታወቂያ አስነጋሪዎች ቢሆንም ከመጀመሪያ እትሟ ብቻ 10 100 በብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን ያስታውሳል። በዚያው ሰሞንአካፑልኮ ቤይየትርጉም መጽሐፉ ታትሞ 36 ብር አጠቃላይ ትርፍ 30 በመቶውን እንደወሰደ አይዘነጋም። 

1997 . ሲገባ አየሩን ሁሉ ፖለቲካ ሲሞላው የተወዳጅ ገበያም እየቀነሰ መጣ።ጋዜጠኛ ፖለቲከኛ መሆን የለበትምብሎ ስለሚያምን ነው እንጂ ተወዳጅን የፖለቲካ ጋዜጣ ማድረግ ይችል እንደነበር ያስረዳል። ቀጥሎ ለቢዝነስ እየሸፈተ ያለ ልቡን ጠቅልሎ የወሰደ ድርጅትን በሞክሼ ጓደኛው እዝራ /ሥላሴ አማካኝነት ተቀላቀለ።ጎልድ ኩዌስትየተባለው ይህ የሆንግ ኮንግ ድርጅት በኔትወርክ ማርኬቲንግ  ላይ ትኩረቱን አድርጎ የሚሰራ ሲሆን መንግስት እስኪያግደው ድረስ በሀገራችን ተንቀሳቅሷል። እዚሁ ድርጅት ውስጥ እያለ በእንግሊዝኛ ብቻ የነበሩ የኔትወርክ ማርኬቲንግ ማንዋሎችን ወደ አማርኛ ሲመልስ ከቆየ በኋላ በመጽሐፍ መልክ አሳተመው። ከመጽሐፉ ህትመት ማግስትኢትዮ ቪዥን የችሎታ ማግኛየሚል የስልጠና ማዕከል ከፍቶ በርካቶችን ከችሎታቸው ጋር ማገናኘት ቻለ።

የጥረት ሰው ስለሆነ አደርገዋለሁ ያለውን ሁሉ አድርጓል። ይህች ዓረፍተ ነገር የወዳጅ የተጋነነ አድናቆት እንዳልሆነች መግቢያዬ ላይ ያሰፈርኩት የኩኩሉ መጽሔት እትም በቂ ማሳያ ቢሆንም ሌላ ምሳሌ እጠቅሳለሁ። መስከረም 22 2000 . 22 ወደ ፒያሳ ይጓዝ በነበረ ታክሲ ውስጥ ያገኛትን ወጣት ጥቂት ካዋራት በኋላ ሰባ ደረጃ ላይ ከመድረሱ ቀድሞኔትወርክ ማርኬቲንግየሚል መጽሐፉን እየሳጣትአንቺን ነው የማገባውብሏት ወረደ። ከሁለት አመታት በኋላ የሰርጉ ቀን ከጎኑ የቆመችው ሙሽራ የያኔ ታክሲ ተጋሪው  የዛሬ ባለቤቱ አመለወርቅ ወልደኪዳን ነበረች።

2000 . ጥር ወር ላይ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የቅጥር ማስታወቂያ አውጥቶ ቢወዳደርም ተጠባባቂ ነበር መሆን የቻለው። ከወራቶች ቆይታ በኋላ ከፋና ተደውሎለት ከፍተኛ ሪፖርተር ሁኖ 1415 ብር ተቀጠረ። የራሱ ትርፋማ ተቋም እንደነበረውና ማሰልጠኛ ከፍቶ ሰዎችን ከተቀጣሪነት ውጡ እያለ ሲመክር መክረሙን የሚያውቅ ግማሽ ልቡለምን ትቀጠራለህ?’ ቢለውም ሌላኛው የልቡ ክፍል ደግሞዓላማህን ይዘህ ተቀጥረህ ሞክረውይለዋል፤ ሁለተኛውን ሰማና ተቀጠረ። ተቀጠረና 13 ከዓመታት 5ወር  ፋና ቤት መቆየት ቻለ።ከጥር 19 2019 በኋላ ግን ፋና እና እዝራ ተለያዩ፡፡

በእነዚህ 13 ዓመታት ብዙ ከፍና ዝቅታዎችን አሳልፏል። 2001 . የአባቱን ማለፍ ተከትሎ ከሃዘኑ በኋላ ወደ ቤተክርስቲያን ተጠጋ። የትኛውም እምነት ውስጥ ቢሆን የሰው ልጅ መንፈሳዊ መሆን አለበት ብሎ ያምናል። እስከ 2006 . ያሉትንናየዝምታ ጊዜብሎ በሚገልጻቸው ዓመታት መንፈሳዊነቱ ላይ አብዝቶ ሰራ፤ ብዙ ሃይማኖታዊ ትምህርቶችንም ተማረ። ፋና ውስጥ ቀድመው ያልነበሩ ፎርማቶችን ጀምሯል፣ የሀገር ውስጥ ታሪኮች እንዲለመዱ አድርጓል፣ ቴሌቭዥኑ ሲጀመር ደግሞ በርከት ያሉ አጫጭር ታሪካዊ ተንቀሳቃሽ ምስሎችንና ዶክመንተሪዎችን  ሰርቷል።ለብዙዎች የሬድዮ ኤዲቲንግ ስልጠና ሰጥቷል፡፡

ለታሪክ ያለው ፍቅር የተለዬ ነው፤ ይህ ፍቅሩ ለሀገር መልካም የሆነ አበርክቶን እንዲያኖር ረድቶታል። ራሱም ሲናገርአንዳንዴ ያንተ ፓሽን የሀገሪቱ ክፍተት ይሆንና መሻትህን በመኖር እግረ መንገድ ሀገርህን ትጠቅማለህይላል። እዛው ፋና ቤት እያለ የጀመረው የታሪክ ፍቅሩን መወጣት ቢያስቀጣውም ቢያስነቅፈውም በረታበት እንጂ አልቆመም። ጎን ለጎን በአንጻራዊነት የተሻለ ነጻነት ላለው ድሬ ቲዩብ ታሪካዊ ጽሑፎችን ማድረስ በመጀመሩ ብዙ ትውውቆችን ፈጠረለት።

2008 . የግለሰቦችን ታሪክ በሲዲ የመሰነድ ሀሳቡን ሲያነሳ ብዙዎች እንደ እብደት ቢቆጥሩበትም፤ ያለውን ከማድረግ ሰንፎ አያውቅምና የተሾመ /ማርያም ታሪክን በሲዲ በማውጣት ትርፋማ መሆን ቻለ። የጸሃፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሃብተወልድ፣ የአርቲስት ተስፋዬ ሳህሉ፣ የአማረ አረጋዊን ጨምሮ 44 ሲዲዎችን ለማውጣት በቃ። ማማ በሰማይ፣ የኤርትራ ጉዳይ፣ ማህሌት፣ ምንትዋብና ሌሎች 10 የሚደርሱ መጽሐፍትን በኦዲዮ አሳተመ። ከአካፑልኮ ቤይና ኔትወርክ ማርኬቲንግን በተጨማሪ ‘10 ነገሮች አለኦቲዝምእናየአንኮበሩ ሰው በጄኔቭየሚሉ ሌሎች መጽሐፍትን ለንባብ አብቅቷል።

ፋና በቆየባቸው ጊዜያት 1476 ፕሮግራሞችን አየር ላይ ሲያውል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 67 ያህሉ ለቲቪ የተሰሩ ናቸው፡፡ ስራዎቹን ሰንዶ የማስቀመጥ ባህል ያለው እዝራ በየጊዜው ያለፉ ስራዎቹን የማየት ልምድ አለው፡፡

ያለፈውን አንድ አመት 170 የሚደርሱ የሚዲያ ሰዎችን ታሪክ በመዝገበ አዕምሮ ለማስፈር ደፋ ቀና ሲል ከርሞ አሁን ለማሳተም ችሏል።ለሚዲያ ሰዎች ብቻ ሳይሆን በእያንዳንዱ ሙያ መዝገበ አዕምሮ እንዲኖር እፈልጋለሁይላል፤ ካለ ደግሞ ያደርገዋል። ገንዘብ አያስገኝም በሚባልለት የሀገር ውስጥ ታሪክ ስነዳ በትጋት 5 አመታትን ብቻ ተመላልሶ ትርፍ ማግኘቱን በኩራት ይናገራል። ይህ ሁሉ እንዲሆን ከፈጣሪ ቀጥሎ ዋጋ የምትከፍለው ባለቤቱ ድርሻዋ የጎላ መሆኑን ያወሳል። በመጀመሪያ ትውውቃቸውአንቺን ነው የማገባውያለው ሰምሮለት በጥቅምት 7 2002 . በመሰረተው ትዳር ክርስቲያን እዝራ እና ካሌብ እዝራ የተባሉ ሁለት ልጆችን አፍርቷል።

ወደ ሰላሳ ለሚደርሱ ጸሐፍትና ሌሎች ባለሙያዎች የስራ እድል ፈጥሮ ትርፉን እያጋራ ይገኛል፤ አብረውት የሰሩት ሁሉ ስለእዝራ ሲናገሩ ባንድ ድምጽ ስለትጋቱና አንድ ነገር ከጀመረ ሳያሳካ አለመልቀቁን ያወራሉ። ታሪካቸውን ከሰነደላቸው ሰዎች አንዷ ዝናሽ ማሞ ስለእዝራ ስትናገርሀሳቡን ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚያሳየውን ትጋትና ጥረትን አስተውያለሁ። እዝራ ከጀመረ አይለቅም ደጋግሞ ለመደወል አይታክትም፤ ለማሳመን አይደክምም፤ ተከታትሎ ታሪኩን በእጁ ለማስገባት አይሰለችም፤ ምንም የሚፃፍ ታሪክ የለኝም፣ ስራ ይበዛብኛል፣ ጊዜ የለኝም የመሳሰሉት መልሶች ተስፋ አያስቆርጡትም። በጥበብ አስተናግዶ የማሳመን ተሰጥኦ አለው።ትላለች።

ቅድስት ወልዴ የተባለች ባልደረባውም ትናገራለችየእዝራ ትልቁ ጥንካሬው ራዕዩ ነው፤ እውቀትም ሆነ ገንዘብ  ያለውን የሚያካፍል ነው፤ ሌላው እና ትልቁ ነገር  በእግዚአብሔር ማመኑ ነው። ራዕዩን ለማሳካት እንቅፋቱን አልፎ የትም መድረስ የሚችል እና እሱን እያሳየ ያለ መሆኑ ነው። በታሪክ ስራዎቹ ብዙ ያልተነገረላቸውን የሀገር ባለውለታዎችን ከተረሱበት ታሪካቸውን በመፈልፈል በኦዲዮ ሲዲ እና በዶክመንተሪ ያለመታከት  በመስራት  በሀገራችን ቀዳሚው ባለሙያ ይመስለኛል።

“38 ዓመታት በትምህርት አብረን ነበርንየሚለው አብሮ አደጉ ናይእግዚ ህሩይ፤ የእዝራ ንባቡ ላይ የሙጥኝ ማለት እንደእናቱ ሁሉ ይገርመው ነበርእንደልጅም እንደጎረምሳም ሳይሆን ማሳለፉ ይገርመኛልይላል። የራሱን ስራዎች፣ ታሪካዊ ብሎ የሚያምንባቸውን ነገሮች እና በቴሌቭዥን ይተላለፉ የነበሩ ዜናዎች በካሴት ቀርጾ ማስቀመጡን እያስታወሰበወቅቱ የግሉ ዩቲዩብ ነበረው ማለት እንችላለንይላል።

በርካታ ወዳጆች በተለይ አብረውት የሚሰሩ ከእዝራ ባህሪ የሚገርማቸውን ሲጠየቁ ሁሉም ሊባል በሚችል መልኩ የሚጠቅሱት የጀመረው ስራ እስኪያልቅለት እረፍት ማሳጣቱናችክማለቱን ነው፤ እኔ ግን ይህን ችክታ ትጋት ነው የምለው። ትጋቱ ደግሞ አሁን ላለበት የስኬት ደረጃ ሊያቃርበው ችሏል፡፡

መዝጊያ፦

ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን የመዝገበ አዕምሮ(ኢንሳይክሎፒዲያ) ቦርድ አባላት አቋም የሚንጸባረቅበት ነው። እዝራ እጅጉ በጋዜጠኝነት ሙያ በተለያዩ ሚዲያዎች ሀገሩን በርከት ላሉ ዓመታት ሲያገለግል ከቆየ በኋላ በተወዳጅ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን በኩል የተዘነጉ የሀገር ባለውለታዎችን ታሪክ በመሰነድ ለሀገር ከፍ ያለ ውለታን አኑሯል። በዚህ ሳይቆም በህይወት ያሉ የዚህ ዘመን የሀገር ወለታ ዋይ የሚዲያ ሰዎችን ታሪክ ሲሰንድ የደጋሽ ነገር ሁኖበት የራሱን ታሪክ ሳይሰንድ ቢቆይም በመጨረሻ በአማረ ደገፋው እንዲህ ባለ መልኩ ተሰንዶለታል። በህይወት ያሉ ሰዎች ሳያመልጡን ስላበረከቱት መልካም ስራ በቁማቸው ማመስገንን እንድንለምድ የእዝራ ስራ በትልቁ ያስተምረናል። ቀደም ባሉት ዓመታት የሰዎችን ታሪክ በሚዲያዎቻችን ስንሰማ ቀድመንሞተ እንዴ?” እያልን ሙት አመስጋኝ ለነበርነው ሁሉ አይን ገላጭ ስራን እየሰራ ስላለ በመንግስትም በግለሰብም ደረጃ መመስገንና መበረታታት አለበት ብለን እናምናለን።

 







አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች