178.ጣሰው
ተፈራ ዘለቀ
የለጌው ባለሟል
ጣሰው ተፈራ ፣ መምህርና ጋዜጠኛ ነው፡፡
በአሁኑ ሰአት መኖሪያውን በአሜሪካ ያደረገ ሲሆን ለ20 አመታት በለገዳዲ ሬድዮ በቅዳሜና እሁድ የመዝናኛ ፕሮግራሞች ላይ
ያገለገለ ባለሙያ ነው፡፡ ብዙዎች ገና በተማሪነት ዘመናቸው የለገዳዲ ደጃፍ የረገጡ ሲሆን በትህትና እነዚህን ወጣቶች ካሳተፉ
ባለውለታዎች አንዱ ጣሰው ተፈራ ነው፡፡ የመዝገበ-አእምሮ የሚድያ ሰዎች ታሪክ አዘጋጅ እዝራ እጅጉ ገና በታዳጊነቱ የመጀመሪያውን ተሰጥኦ እንዲያወጣ በር
የከፈተለት ጣሰው ተፈራ ነው፡፡ ታዲያ ይህ ለብዙዎች ስኬታማ መሆን ምክንያት የሆነ ሰው ማነው? የሚለውን እንደሚከተለው
እናቀርባለን፡፡
ትውልድ እና እድገት
ጣሰው ተፈራ የተወለደው በአሩሲ ከሁሩታ
ከተማ 12 ኪ.ሜ ያህል ርቃ በምትገኘው ሎዴ ጫንጌ በምትባል ቦታ ነው ።ጊዜውም ጥቅምት 27 ፤1950 ዓ.ም ነበር ። የሬዲዮ
ፕሮግራም አዘጋጁ ጣሰው የአርሶ አደር ልጅ ሲሆን፣ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በአርብ ገበያ በአሁኑ ሎዴ ጫንጌ አንደኛ ደረጃ
ትምህርት ቤት ተከታትሏል ።
የአንደኛ ደረጃ ተማሪ እያለ የመምህር
ብርሃኑን እና የመምህር አሰፋን ውለታ የሚረሳ አይደለም ።ፊደል እንዲለይ ከማድረግ ጀምሮ እስከ ወስጄው ላስተማረው ድረስ
ከፍተኛ ፍቅር ነበራቸው፡፡
ስድስተኛ ክፍል ሲደርስ የምንጊዜም የማይረሳው
የህብረተሰብ ትምህርት መምህሩን መምህር ተክለብርሃን ነው።መምህሩ በሚያምር ድምጹ ከጠረጴዛው ላይ በመቀመጥ ስለሜሶፖታሚያ ታሪክ
የሚያነብላቸውን ዛሬው ድረስ አይረሳውም ።
መምህር ተክለብርሃን ከማንበብ ችሎታው
በተጨማሪ ግጥም የመግጠም ችሎታም ነበረው ።በክፍሉ ለነበሩት እያንዳንዳቸው
በስማቸው ግጥም ይገጥም ነበር። ለአብነት ያህልም በራሱ በጣሰው ላይ የተገጠመውን እንዲህ በማለት ያስታውሰዋል ።
" አሁን ምን አለበት አቅመቢስ ነው
ቢሉት
ጣሰው ብለው ጠሩት በስም ሲደልሉት
"
ብሎታል ።
ጣሰው 7ኛ እና 8ኛ ክፍልን በሁሩታ ንጉስ ኃይለመለኮት ትምህርት ቤት
ከተከታተለ በኋላ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ለመማር ያቀናው ወደ
አሰላ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው። የሬዲዮ ባለሙያው ከፍተኛ ትምህርቱን የተቀላቀለው ደግሞ በኮተቤ መምህራን
ትምህርት ኮሌጅ ሲሆን ለሁለት ዓመት ከተማረና ከተመረቀ በኋላ በትምህርት ሚንስትር ዕጣ በማውጣት ወደ ትግራይ መቀሌ አቀና ።
መቀሌ በሚገኘው አፄ ዮሐንስ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለአምስት ዓመታት ያህል በመምህርነት አገልግሏል ።
የሬዲዮ ፕሮግራም ጅማሮ
አፄ ዮሐንስ እያስተማረ ሳለ ለ 20 ዓመታት
ላገለገለበት ለገዳዲ ሬዲዮ ጣቢያ መነሻ የሆነውን መቀሌ ለሚገኘው ትምህርት መገናኛ ዘዴዎች ለጎልማሶች ትምህርት እና ለቅዳሜ
እና እሁድ መዝናኛ ፕሮግራም ለመስራት ፍላጎት ያላቸውን ባለሙያዎች ለመመልመል ባወጣው ማስታወቂያ መሰረት ተወዳድሮ በማለፍ
ለስልጠና ወደ አዲስ አበባ ትምህርት መገናኛ ዘዴዎች በመምጣት በትምህርት መገናኛ ዘዴዎች ባለሞያዎች እና ከቢቢሲ በመጣ ባለሙያ
የሬዲዮ ፕሮግራም ስልጠና ወስዶ በማጠናቀቅ ወደ መቀሌ ተመልሶ ስራውን ' ሀ ' ብሎ ጀመረ። ቅዳሜና እሁድ መዝናኛ ፕሮግራም
እና የጎልማሶች ትምህርት ማዘጋጀት ያዘ።
ጣሰውና ለገዳዲ ሬዲዮ ጣቢያ
ደርግ መቀሌን ሲለቅ ወደ አዲስ አበባ
በመምጣት በለገዳዲ ሬዲዮ ጣቢያ በ " ቅዳሜን ከእኛ ጋር " እና " እሁድን ለአንድ አፍታ "
ፕሮግራም ውስጥ መስራቱን ጀመረ ። ቅዳሜን ከእኛ ጋር ፣ በትምህርት አምባ ፣ ጥያቄና መልስ ፕሮግራም ለበርካታ ዓመታትም
ሰርቷል ። በተለይም ጥያቄና መልስ ፕሮግራም ከበርካታ ደንበኞች ያስተዋወቀው ሲሆን የተወዳጅ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን መስራችና
ባለቤት ሆነውን እዝራ እጅጉ የተዋወቀበትና ቋሚ ደንበኛ የሆነበት ወቅትም ነበር ። እዝራ እጅጉ 300 ያህል ደብዳቤዎች
በጥያቄና መልስ ፕሮግራም አየር ላይ ውለዋል ቢልም አዘጋጁ ግን ቁጥሩ አንሷል በትንሹ ከ 500 በላይ ደብዳቤዎች አየር ላይ
ውለዋል ሲል ይናገራል ።
መቼም የጥያቄና መልስ ነገር ሲነሳ ጣሰው
ትዝ የሚለው የአባይ ወንዝ እርዝመት ስንት ነው ? የሚለው ጥያቄ ሲሆን የመልሱ ማጣቀሻ በወቅቱ የነበረው ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ፣ ኢንሳይክሎፒዲያ አሜሪካ ነው። ታዲያ አንዳንድ ጊዜ የቁጥር መዛነፍ ይስተዋላል ። ቅዳሜ
መልስ ተነግሮ ሰኞ ጧት መስሪያ ቤቱ ስልክ በስልክ ይሆናል ። መልሱ ትክክል አይደለም የሚል ነበር ። ጣሰው መልሱን በስልኩ
ለጠየቁት ሰዎች መልስ ከመስጠት ይልቅ ወደ ቤተመጻሕፍት ያቀናና ሁለቱንም ኢንሳይክሎፒዲያዎች አውጥቶ መመልከት ይጀምራል ።
መልሱንም በወረቀት ጽፎ ለጠያቂዎች መልስ ለመንገር ይደውላል ። በኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ ይህን ያህል በኢንሳይክሎፒዳያ
አሜሪካ ይህን ያህል ነው በማለት የጥያቄ ደንበኞቹን አስደስቷል ።
በእሁድን ለአንድ አፍታ የደብዳቤዎች
ማህደር በየሳምንቱ በርካታ ደብዳቤዎች ከአድማጮች የሚመጡ ሲሆን
ለብዙዎች መልስ ይሰጣል ። ከሚጠየቁ ጥያቄዎች ውስጥ አስገራሚ ናቸው ያላቸውን ሁለቱን የአድማጭ ጥያቄዎች እንዲሁ ያስታውሳቸዋል
።
" ቢላ ስለት እንዲያወጣ ይሳላል
። ጥርስ ግን አይሳል ወይ ሌላ ነገር አይደረግም ግን ሁልጊዜም
እንደ ስለታም ቢላ ሲፈጭ ይኖራል ። ምክንያቱ ምንድን ነው ? "
ሌላው ደግሞ
" ከሞተውና በህይወት ካለው የቱ
ይበልጣል ? " የሚሉት ናቸው ።
ጣሰውና አሰልጣኝነት
ጣሰው ለአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት
መምህራን በአምቦና በናዝሬት ለበርካታ ዓመታት ስልጠና ከመስጠቱም ባሻገር የትምህርት መገናኛ ዘዴዎች ከሚገኙና ከሬዲዮ ጣቢያው ተመልምለው ለሚመጡ ፣ አንዳንዴም በቦታው በመሄድ የሬዲዮ ፕሮግራም
ስልጠናዎችን ሰጥቷል ።እንዲሁም ለአዲስ አበባ ብዙሃን መገናኛ ገና ስራውን ሲጀምር ለባለሙያዎች እና የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጆች
ስልጠና ይሰጥ እንደነበር ይናገራል ። ጣሰው በአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ለ 3 ዓመታት ያህል የስርዓተ-ትምህርት ዝግጅት
ባለሙያ በመሆንም አገልግሏል ። ጣሰው ከቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በBED( Bachelor of Education) የተመረቀ ሲሆን
እንዲሁም ወደ ሃምሳ ገደማ የሚሆኑ ግጥሞችም አሉት፡፡
ማጠቃለያ
የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጁ ጣሰው ተፈራ
በልጅነቱ የተመኛቸውን ሁለት ነገሮች ለማሳካት የበቃ ሰው ነው።አንደኛው የመምህር ብርሃኑና መምህር አሰፋን አርአያ በመከተል
መምህር በመሆን ምኞቱን ያሳካ ሲሆን የኢትዮጵያ ሬዲዮ አዘጋጆቹ ታደሰ ሙሉነህ ፣ ተክሉ ታቦርና ንጉሴ አክሊሉን አርአያ
በመከተል ሁለተኛውን የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅነቱን አሳክቷል ። እነታደሰን ሲያስብ ትዝ የሚለው ከአባቱ ጋር ድርቆሽ ሳር
እያጨዱ የቅዳሜን መዝናኛ ፕሮግራም እያደመጡ ሳለ ትኩረቱ ወደ ፕሮግራሙ ስለነበር እጁን በማጭድ የመቁረጡ ነገር የሬዲዮ ጉዳይ
ሲነሳ ከአእምሮው የማይጠፋ ትዝታው ነው ። ጣሰው ከ 2004 ዓ.ም ጀምሮ ከባለቤቱ እና አንድ ልጁ ጋር ኑሮውን በአሜሪካ ሀገር
አድርጓል ።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ