171.ዘሪሁን አሰፋ -zerihun assefa  

በመጽሔት፣ በጋዜጦች እና በድምፀ- መጻሕፍት ታሪክ ላይ እርሾ ያዋጣ ባለሙያ

 

 

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን፣ በቅርቡ መዝገበ-አእምሮ / ኢንሳይክሎፒዲያ / በሚል ርእስ የሚድያ እና የኮሚኒኬሽን ባለሙያዎችን ታሪክ በጠንካራ ሽፋን መጽሀፍ አሳትሞ ያስመርቃል፡፡ በተለይ ከመገናኛ ብዙሀን ዘርፍ ጋር በተያያዘ የግራፊክስ ባለሙያዎች፤ የፎቶ የቪድዮና የቴክኒክ ዘርፍ ሰዎች፤ የሚድያ አማካሪዎች የሙያ አበርክቷቸው በቀላሉ አይታይም፡፡ እኛም በዚህ ዘርፍ የላቀ አሻራ ያላቸውን እየሰነድን ለትውልድ ታሪካቸውን እናቆያለን፡፡   በግራፊክስ አማካሪነትና ባለሙያነት ባለፉት 20 አመታት የላቀ ተግባር ስላከናወነው ዘሪሁን አሰፋ   እዝራ እጅጉና ግርማ አድነው ይህን ሰንደዋል፡፡

    ልጅነት

 

የካቲት 29 ቀን 1969 . ዘሪሁን በጅማ ከተማ ተወለደ፡፡ ዘሪሁን ከ8ዓመቱ ጀምሮ የእናቱ ቤተሰቦች ጋር መኖር ጀመረ፡፡ በእናቱ አባት ስም በመጠራት ዘሪሁን አሰፋ ተብሎ ትምህርቱን ቀጠለ፡፡

ታዳጊነት

ዘሪሁን አያቶቹ ቤት ከአክስቶቹ፣ አጎቶቹና ሌሎች ዘመዶቻቸው ጋር ኖሯል፡፡ የዘሪሁን እናት / ፀሐይነሽ አሰፋ የቴሌኮሙኒኬሽ ኦፕሬተር ነበሩ፡፡ በየወሩ ቴሌ ነጋሪት መጽሔት ይመጣላቸዋል፡፡ ዘሪሁንም መጽሔቱን እያነበበ ነው ያደገው፡፡ አያቱ ሀምሳ አለቃ አሰፋ በዳኔ በኢትዮጵያዊነት የሚያምኑ አጉል ዕምነቶችን በመሸሽ ከተጉለትና ቡልጋ አውራጃ ተሰደው ጅማ የከተሙ ቆፍጣና ኢትዮጵያዊ ፖሊስ ነበሩ፡፡ ሴት አያቱ / አስካለ /ማርያም አራት ቋንቋዎችን መናገር የሚችሉ ከጣልያን የቦንብ ናዳ የተረፉ ኢትዮጵያዊ ናቸው፡፡ በዚያም ለሕይወቱ መሠረት የሆኑ ክህሎቶችን ጽንፍ ሳይዝ በመሀል መንገድ እሳቤ መጓዝን፣ ሥነ-ምግባር፣ ታዛዥነት፣ ሰውን ማገልገል፣ ከሰዎች ጋር ተግባብቶ የመስራት ችሎታን እና ፍጹም ኢትዮጵያዊነትን አግኝቷል፡፡

 ትምህርት

ዘሪሁን አፀደ ሕፃናት እያለ በልዩ ልዩ ቅርጻ ቅርፆችና ቀለማት ከተሰሩ የመማሪያ ቁሳቁሶች ጋር በትኩረት ያሳልፍ እንደነበር በወቅቱ ያስተማረችው መምህርት / ፀደቀች ታስታውሳለች፡፡ ዘሪሁን የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ተምሯል፡፡ የሰባተኛና የስምንተኛ ክፍሎችን በሰጦ ሰመሮ /ቤት ተከታትሏል፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በጅማ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በነበሩ ክፍሎች የደረጃ ተማሪ ሆኖ አጠናቋል፡፡

የእኔ ታሪክ ይበልጣል ከማትሪክ!”

ዘሪሁን አሰፋ 12 ክፍል የብሔራዊ ፈተና ውጤቱ አልተደሰተም፡፡የእኔ ታሪክ ይበልጣል ከማትሪክ!” ይህ ውጤት አንድ የሕይወት ምዕራፍ ቢከፍትልኝስ ብሎ ወደ ናዝሬት ቴክኒክ ኮሌጅ (አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ) ተመድቦ 1992 . ገባ፡፡ በኮሌጁ የነበሩት ጓደኞቹ በሁለተኛ ደረጃና በሌሎች ክፍሎች የነበረውን የሥነ-ጽሑፍ ተሳትፎና ተሰጥኦ በመገንዘብ የምርቃት መጽሔት ዋና አዘጋጅ እንዲሆን መረጡት፡፡ ስቴቨን በሚባል አሜሪካዊ ረዳትነትና ከኮሚቴው አባላት ጋር 1993 . የምርቃት መጽሔት ሌይ- አውት እራሱ በመስራት ዳንኤል ብርሃኑ በተሰኘ ሰው ረዳትነት አሳተሙ፡፡ በአውቶሞቲቭ ቴክኖሎጂም በዲፕሎማ ተመረቀ፡፡

ከምርቃቱ በኋላ ወደ ጅማ በመመለስ 1994 . ከልጅነቱ ጀምሮ ለመጻሕፍት፣ ለመጽሔትና ጋዜጦች ቅርብ በመሆኑ በጅማ የህዝብ ቤተ-መጻሕፍት እያዘወተረ በማንበብ እና ሁኔታቸውን በማጥናት ተጠመደ፡፡ በሀገሪቱ ጥሩ የተባሉ መጽሔቶችና ጋዜጦችን ለማዘጋጀት እቅድ ያዘ፡፡ ግን እንዴት?

ጎን ለጎን በማታው ክፍለ- ግዜ የፋርማሲ ትምህርቱን እየተማረ ጥሩ ውጤት ቢያመጣም ሁለተኛ ወሰነ ትምህርቱን 1994 . አጠናቆ ሳይገፋበት ቀረ፡፡ በቀጣይ 1995 . ኤሌክትሪካል ምህንድስና ለአንድ ዓመት ተምሮ ከፍተኛ ውጤት ቢያመጣም ከውስጣዊ ፍላጎቴ ጋር አልሄደልኝም በማለት አቋርጦ ወደ አዲስ አበባ ነሐሴ 19 ቀን 1995 . መጣ፡፡ አዲስ አበባ የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት ገብቶ የሥዕልና የግራፊክ ጥበብን ለመማር እንደሚፈልግ እና የልጆችን ክህሎት የሚያሳድግ መጽሔት ለማዘጋጀት ያደረገውን ጥረት የሚያውቅ ዘመዱ ከፎርቹን ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር ታምራት /ጊዮርጊስ ጋር አስተዋወቀው፡፡ 

 ፎርቹን ሣምንታዊ ጋዜጣ 

ዘሪሁን አሰፋ ከመስከረም 1996 . እስከ ጥር 1996 . በፎርቹን ሣምንታዊ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚታተም የንግድ ጋዜጣ ላይ ጀማሪ ሌይ አውት ዲዛይነር ሆኖ ሰርቷል፡፡ ለፎርቹን ጋዜጣ በመጣ እድል በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እና በኖርዌ ኤምባሲ ጥምረት ከውጭ ሀገር በመጡ (TIME መጽሔት፣ ዋና አዘጋጅ እና Norwegian Times ጋዜጣ ዋና ክሬቲቭ ዲዛይነር እና ሌሎች ታላላቅ ሰዎች) በተዘጋጀ የህትመት ሚዲያ ጽሑፍና የአርትኦት፣ የግራፊክ ዲዛይን፣ የፎቶግራፍ አጠቃቀም እና ሌሎች ተግባራዊ ሥልጠናዎችን በየዕለቱ ከሁለት ወራት በላይ ተከታትሏል፡፡ የህትመት ውጤቶች ወደ ዕይታዊ ጥበብ ከመቀየራቸው በፊት ቀድሞ ማንበብ እንደሚገባ፣ ሳምንታዊ መጽሔትና ጋዜጦች እንዴት እንደሚዘጋጁ ተምሯል፡፡ በቀጣይ ወራቶች ከመሰረታዊ የኮምፒዩተር፣ የግራፊክ ዲዛይን ዋና ዋና መተግበሪያዎች እስከ የድረ-ገጽ ዲዛይን ትምህርቶች፤  በኤአይቲ ኢንጅነሪንግ እና በሳይበርሲስ ቴክኖሎጂ ተቋሞች ተከታትሏል፡፡ በኋላ ላይ በግል ምክንያት ከፎርቹን ጋዜጣ ለቀቀ፡፡

ካፒታል ሣምንታዊ ጋዜጣ 

በሳምንቱ ሌላኛው ካፒታል ሣምንታዊ እንግሊዝኛ የንግድ ጋዜጣ ዲዛይነር እንደሚፈልግ ሰው ነገረው፡፡ ወደ ካፒታል ጋዜጣም አቀና፡፡ እዚያ ሳለ ሳም ከሚባል እንግሊዛዊ ጋር ጠለቅ ያለ ጥናት በማድረግ መሠረታዊ የአሰራር ሂደቶችን በመቀየስ ጋዜጣውን በብዙ መልኩ ከፍ አድርጎታል፡፡ የጋዜጣው አሳታሚ ተሸላሚ ባለሙያም ነበር፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ በሀገሪቱ ጥሩ የተባለ ጋዜጣ ለመስራት የያዘው እቅድ ተሳካ፡፡ ከጥር 1996 . እስከ ነሐሴ 1998 . ድረስ በግራፊክ ዲዛይነርነት አገልግሎ የግሉን ድርጅት ኳንተም ዲዛይንና ህትመት ክሊኒክ በማቋቋም ተሰናበተ፡፡

የዩኒቨርስቲ ቀን

ዘሪሁን አሰፋ 1998 . GTZ-ecbp ፕሮጀክት እገዛ በአዲስ አባባ ዩኒቨርስቲ በተከናወነውየዩኒቨርስቲ ቀንክብረ በዓል ሙሉ የዲዛይን ጥቅል ሥራዎች ማለትም የጥሪ ካርዶች፣ የበራሪ ወረቀቶች፣ የውስጥና የውጭ ፖስተሮች፣ ባነሮች፣ የፕሮግራም ሽፋኖች፣ የሌክቸር ሲሪየሶች፣ ፎልደሮች፣ ካላንደሮች፣ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተዘጋጀ The Bridge የተሰኘ የወጣቶች ጋዜጣ እና ሌሎች የዝግጅት ማድመቂያ ዲዛይኖችን በመሥራት ዝግጅቱ ሥኬታማ እንዲሆን አድርጓል፡፡

ከሮዝ እስከ አዲስ ጉዳይ

የሮዝ መጽሔት መስራች እንዳልካቸው ተስፋዬ በሀገሪቱ ጥሩ መጽሔት ለመስራት ያቀደውን ግብ ለማሳካት ጋዜጠኛ ታምሩ ጽጌ ከዘሪሁን አሰፋ ጋር በታኅሣሥ 1999 . አስተዋወቀው፡፡ ዘሪሁን ከዓለማየሁ ባዘዘውና እንዳለ ተሺ ጋር እጅግ አድካሚ በሆነ የሥራ ሁናቴ ሮዝ ወርሀዊ መጽሔት ሳትቋረጥ እንድትወጣ አደረጓት፡፡ ሮዝ መጽሔት ከምትይዘው ጭብጥና የሽፋን ገጽ መገለጫዋ አንጻር የሥም ለውጥ በማድረግ እንድትሰራ በተደረሰው ስምምነት ዘሪሁን ከጋዜጠኛ ጽጌረዳ ኃይሉ፣ ዮሐንስ ካሣሁን፣ አስማማው /ጊዮርጊስ፣ ቴዎድሮስ /አረጋይ፣ መስፍን አድነው፣ እንዳለ ሰለሞን፣ አዚዛ አህመድ፣ ሣሙኤል፣ ሲሳይ፣ ተከተልና ከሌሎች ባለደረቦቹ ጋር በመሆን ሮዝ መጽሔትን በጋራ ሥምምነት ወደ አዲስ ጉዳይ የካቲት 2003 . አሸጋገሩት፡፡ ወርሀዊ የነበረው አዲስ ጉዳይ በየ15 ቀኑ መውጣት ጀመረ፡፡ (አዲስ ጉዳይ- በዲያቆን ዳንኤል ክብረት የተጠቆመ መጠሪያ ነው)፡፡ 

አዲስ ጉዳይ ሣምንታዊ

አዲስ ጉዳይ ሣምንታዊ ባለቀለም መጽሔት እንዲሆን ዋነኛውን እርሾ ያዋጣው ዘሪሁን አሰፋ ነበር፡፡ መጽሔቱ በህትመት ኮፒ ብዛቱ፣ በሽያጭና በማስታወቂያ ገቢው የላቀ ነበር፡፡ በዐቢይ ጉዳይ፣ የታፈኑ እውነቶች፣ በቃለ-ምልልሱ እና በሌሎች ጥንቅሮቹ እንዲሁም በዐምደኞቹ በዕውቀቱ ሥዩም፣ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ / ብርሃኔ ረዳኢ እና በሌሎች ትጋት ወደ ሣምንታዊ ጉዞ ጀመረ፡፡ ከእንዳልካቸው በስተቀር ለሌሎች ባልደረቦቻቸው የሣምንታዊ ጉዳይ የማይቻል ውጥን ነበር፡፡ እንዳልካቸው በተደጋጋሚ በማቀድ ዘሪሁን ደግሞ የሥራ ልምዱን በመቀመር TIME መጽሔት ዋና አዘጋጅ ሳምንታዊ መጽሔት እንዴት እንደሚሰራ በሥልጠና ባስገነዘበችው መንገድ ሳምንታዊ መጽሔትን ለማዘጋጀት አይገደንም በማለት ባልደረቦቻቸውን አሳመኗቸው፡፡ ከበርካታ ዓመቶች በኋላም በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ሣምንታዊ ባለ ሙሉ ቀለም አዲስ ጉዳይ መጽሔት እውን ሆነ፡፡ ዘሪሁን በሀገሪቱ ጥሩ የተባለ መጽሔትን ለመስራት የያዘው እቅድ ተከናወነ፡፡ ከጥር 1999 . እስከ ጥር 2006 . ድረስ በትጋት ከሚሰራበት መጽሔት ባልደረቦች ጋር በወደረኛ ጉዳዮች ምክንያት ስላልተግባባ ተሰናበተ፡፡ መጽሔቱም ለወራት ቆይቶ ከሕትመት ወጣ፡፡













ጤና ይስጥልኝ፣ ዘመንና ጥብብ

ዘሪሁን ከንግድ፣ ከኢኮኖሚ እና ከፖለቲካ አውድ ወጣ በማለት የዌልነስና የጤና ጉዳይ የሚያነሳ መጽሔት እንዲኖር በመሻቱጤና ይስጥልኝየተሰኘ መጽሔትን ዲዛይን በማድረግ ከመስከረም 2006 . እስከ ጥር 2008 . ለንባብ አብቅቷል፡፡ በቀጠይዘመንና ጥበብመጽሔትን ዲዛይን በማድረግ ከአንድ ዓመት በላይ በጥሩ ሁኔታ እንዲታተም የበኩሉን በጎ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ምን አዲስየኢትዮጵያ እንስሳት ሀኪሞች ታሪክእና ሌሎች መጽሔቶችን ዲዛይን አድርጓል፡፡ 

መጻሕፍት

በአልአዛር አህመድ የተዘጋጀው በኢትዮጵያ ዩኒቨርስቲዎች የአካውንቲግ መማሪያ (Principle of Marketing) መጽሐፍ፤ ታክስ አካውንቲንግ፣ በገብሬ ወርቁ፤ ዘላለማዊ ጓደኝነት፣ የልጆች የተረት መጽሐፍ (በተስፋዬ አለነ) የማይጠፋው እሳት፣ የታሪክ መጽሐፍ (በደረጄ በላይነህ) የማንነት አደራ፣ ልቦለድ መጽሐፍ (በገነት አዲሱ) የአንኮበሩ ሰው ግለ-ታሪክ (በእዝራ እጅጉ) የሌሎችንም ዲዛይን ሠርቷል፡፡

2007 . USAID, RTI እና በትምህርት ሚኒስቴር ፕሮጀክት ሰባት ብሔሮች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ በታሰበ የመጽሐፍ ዝግጅት ላይ በአማካሪነትና በግራፊክ ዲዛይነርነት በመሳተፍ የሀዲያ ብሔረሰብ ቋንቋ መማሪያ መጽሐፍን ዲዛይን አድርጓል፡፡

ድምፀ መጻሕፍት

2008 . ድሬ ቲዩብምን አዲስየተሰኘ መጽሔት ለማሳተም ሲወጥን እዝራ እጅጉን በዋና አዘጋጅነት መደበው፡፡ ዘሪሁን አሰፋና እዝራ እጅጉ በዚሁ መጽሔት አማካኝነት ተዋውቀው ከአርባ በላይ ድምፀ መጻሕፍትን ዲዛይን በማድረግ እና ሲዲዎቹን በማተም ተወዳጅ ሚዲያ እና ኮሚኒኬሽን የተነሳበትን ተልዕኮ አግዟል፡፡

በእርጋታ መፍጠን!”

ዘሪሁን አሰፋበእርጋታ መፍጠን!” በሚል ፍልስምና ይመራል፡፡ አንድ የህትመት ሥራ የሚያስፈልገውን ሂደት ተከትሎ መውጣት አለበት ብሎ ያምናል፡፡ በጊዜ ከታቀበ የህትመት ኢንደስትሪ ባህርይ አንፃር መፍጠን ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን እሱ ለሥራው ተገቢውን ዝግጅት ያደርጋል፤ ያነባቸዋል፤ በቂ ጥናትም ይሰራል፡፡ ከዚያም ሀሳቦችን ይቀምርና በአዳዲስ ዕይታዊ ጥበብ መግለጫ መንገዶች ተጠቅሞ ያለ እንከን ለመስራትበእርጋታ መፍጠን!” በሚል እሳቤ በጣም በልዩ ትኩረት ከእራሱ ጋር አዋህዶ በእርጋታ ዲዛይን በማድረግ ስህተቶችንና ግድፈቶችን በመቀነስ በችኮላ የሚመጡ ችግሮችን የሚያስወግድበት መንገድ ልዩ ያደርገዋል፡፡ አብሯቸው ከሰሩ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ጋር በልዩ እርጋታ ሥራውን እንደሚያከናውን ይታወቃል፤ ጽንፍ ሳይዝ በመሀል መንገድ እሳቤ ከሁሉም ጋር ተግባብቶ ይሰራል፡፡ ቀደም ባሉት ጊዜያት የሌይ አውትና ሌሎች ዲዛይነሮች ስም በህትመት ውጤቶች ላይ አይወጣም፡፡ ዲዛይነሮች በየዝግጅት ክፍሉ ስብሰባዎች ላይ አይሳተፉም፤ የአንድ የህትመት ውጤት እርሾ ዲዛይነሮቹ መሆናቸው እየታወቀ በየቦታው ቁብ ሳይሰጣቸው የዋና አዘጋጆቹ ስሞች ብቻ እየታተሙ መኖራቸው ለባለሙያዎቹ ተገቢውን ዋጋ አለመስጠት እንደሆነ ይገነዘቧል፤ ቅርም ያሰኘው ነበር፡፡ ይህ ሙያ በራሱ ልዩ ተሰጥኦን የሚፈልግ እንጂ ቆርጦ መለጠፍ እንዳይደለ በሄደበት ሁሉ ለባልደረቦቹ እያስገነዘበ ተገቢውን ክፍያና የሙያዊ ልዕልና ማግኘት እንዳሚገባቸው ታግሏል፡፡

ማኅበራዊ አገልግሎት

1994 . በቤተሰብ መምሪያ የፀረ-ኤች አይ ኤድስ ክበብና በወጣት ማኅበር ላይ ዋና ተዋናይ በመሆን ወጣቶችን አደራጅቶ መጽሔት ለማሳተም ጣረ፤ በተከሰቱት የድርጅቱ ችግሮች ሳቢያ ሳይሳካለት ቀረ፡፡ በሰፈሩ ያሉ እድሮችና የቀበሌ ኃላፊዎችን በማስተባበር በጅማ ከተማ ከፍተኛ 1 ቀበሌ 03 የሕዝብና የቤቶች ቆጠራ አከናውኗል፡፡ የነዋሪዎቹን የኑሮ፣ የትምህርት፣ የሥራ፣ የጤና እና የሃይማኖት ሁኔታ ቤት ለቤት በመሄድ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ቆጠራ አካሄዶ ለቀበሌውና ለሚመራው ክበብ ሥራ ማከናወኛ ግብአት ሆኗል፡፡ ከውጤቱ በመነሳት ከአራተኛ ክፍል እስከ ስድስተኛ ክፍል የተማረበት የድል ፍሬ ትምህርት ቤትን የክፍል ችግር ለመቅረፍ አንድ የመማሪያ ክፍል ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ሰርቷል፡፡ በዚያው ዓመት በቀበሌው ተወልደው ያደጉት / ግርማ ከአሜሪካ መጥተው ለእናታቸው መታሰቢያ ወጣቶችንና ሕጻናትን የሚያጎለብት ግብረ-ሰናይ ድርጅት ለማቋቋም ፈለጉ፡፡ ዘሪሁንም ይህንን ግብአት አቀረበላቸው፡፡ ሰውየው ከእነ ዘሪሁን እና ጓደኞቹ ጋር ወጣቶችን ሰብስበው ሥራቸውን ጀመሩ፡፡ ለጥቂት ወራቶች እንደተጓዙ በወቅቱ በነበረው የብሔርና የባለሥልጣናት ፖለቲካዊ ተጽዕኖ ምክንያት ያንን ግዙፍ ተቋም እናታቸው ወደተወለዱበት መንደር ወሰዱት፡፡ ፕሮጀክቱም ተዘጋ፡፡ ዘሪሁንም ፖለቲካን ተጠይፎ ሁሉንም ነገር አላቆመም፡፡ የነበረውን ፖለቲካዊ ሥርዐት ጽንፍ ሳይዝ በመሀል መንገድ እሳቤ መታገል እንዳለበት ከራሱ ጋር ቃል ገባ፡፡ ይህንንም ትግል በመጽሔቶቹ ተግብሯል፡፡

ቤተሰብ

ዘሪሁን አሰፋ 2006 . ከወ/ ምሥራቅ አረጋ ጋር ትዳር መስርቶ ነባይ እና አሜን የሚባሉ ሴት ልጆችን አፍርቷል፡፡ ዘሪሁን ትዕግስት፣ ወይንእሸት፣ ቴዎድሮስ፣ ረድኤት፣ ብንያምና ምኞት የሚባሉ እህትና ወንድሞች አሉት፡፡

የወደፊት ሕልም

ዘሪሁን በኳንተም የዲዛይንና የህትመት ክሊኒክ ልዩ ልዩ የዲዛይን እና የህትመት ሥራዎችን ይሰራል፡፡ ከልጆቹ ጋር በድምጽና በምስል የተቀናበሩ የተረትና የመዝናኛ መጻሕፍትን ለማሳተም በጥረት ላይ ነው፡፡ የክህሎት ማበልጸጊያና አጋዥ መጻሕፍትንም ማተም የወደፊት ህልሞቹ ናቸው፡፡

 

 

 

        ዘሪሁን አሰፋ ላይ የተሰጡ ምስክርነቶች

 

ነጋሽ አበበ ከዘሪሁን አሰፋ ጋር ለ4 አመታት ሰርቷል፡፡ ስለ ዘሪሁን ሀሳቡን ሲሰጥ እንዲህ ይላል‹‹……..ከዘሪሁን ጋርአብረን ስንሰራ ያለውን ልዩ ክህሎት ለማየት ችያለሁ፡፡በተለይ ደግሞ አዲስ ጉዳይ ላይ ሳለ ይሰራቸው የነበሩ የፊት ገጽ ሽፋኖች በብዙዎች የሚደነቁ ነበሩ፡፡ ዘሪሁን አንድ ስራ ከጀመረ አጠናቅቀዋለሁ ባለው ቀን ይጨርሰዋል፡፡ ሀሳቡን ደግሞ  በግራፊክስ መግለጽ ስለሚችል የሚሰራቸው ስራዎች ሁሉም ማለት ይቻላል ደረጃቸውን የጠበቁ ነበሩ፡፡ ‹‹ጤናይስጥልኝ›› የተሰኘችውን ህትመት ሲሰራ በእንዴት ያለ መልኩ እንዳሳመራት ሁላችንም የምናውቀው ነው፡፡ በእኔ እምነት በግራፊክስ ዲዛይን የመጀመሪያ ወይም ሙያውን ፕሮፌሽናል በሆነ መልኩ አስተዋወቁ ከሚባሉት አንዱ ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ ራሱን ክርኤቲቭ ዲዛይነት ብሎ ሲያስቀምጥ የእውነት  ድንቅ የፈጠራ ክህሎቱን በሚታተሙት መጽሄቶች ላይ በግልጽ ማየት ይቻላል፡፡ወደፊትም ለሀገሩ ድንቅ ነገር መስራት የሚችል ታላቅ ሰዎ መሆኑን መመስከር እችላለሁ፡፡

      ነጋሽ አበበ የሚድያ ባለሙያ

 

አስራት ከበደ ከዘሪሁን አሰፋ ጋር የተዋወቀው በአዲስ ጉዳይ መጽሄት አማካይነት ነበር ፡፡ አስራት ስለ ዘሪሁን ሲናገር‹‹….. ከዘሪሁን ጋር በሌይ አውት ስራ በጣም እንግባባ ነበር፡፡ ራሱን ከዘመኑ የሌይአውት ዲዛይን አሰራር ጋር ለማስኬድ ይሞክራል፡፡ የሚሰራቸውም ዲዛይኖች ፈጠራ የታከለባቸው ስለነበሩ ህትመቶችን ማራኪ ያደረጉ ነበሩ፡፡ ዘሪሁን ለኤዲተሮች ሀሳብ ይሰጣል፡፡ የሰጡትም ሀሳብ ላይ አዲስ ነገር አክሎበት በነገሩ ላይ ነፍስ ይዘራበታል፡፡ እንዲህ አይነት  የግራፊክስ ዲዛይነሮች ሊኖሩን ይገባል፡፡    

  አስራት ከበደ /ደራሲና አርታኢ/

 

               🙏🙏🙏🙏🙏🙏🙏🙏




       መዝጊያ ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ የኢንሳይክሎፒዲያ ቦርድ አባላትን  አቋም የሚያንጸባርቅ ነው

 ዘሪሁን አሰፋ ለግራፊክስ ሙያ የተፈጠረ ሙያውንም ከልቡ የሚወድ ታላቅ ባለሙያ ነው፡፡ በተለይ የሌይአውት ፤ የግራፊክስ ሙያ ባለፉት 20 አመታት ትልቅ እመርታ እንዲያሳይ የራሳቸውን አሻራ ካኖሩ የሚድያ ሰዎች አንዱ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ስለ ህትመት ሚድያ ስናነሳ ዘሪሁን አሰፋን ማለፍ አንችልም፡፡ የመጽሄቶቻችን የንድፍ ስራዎች አለም አቀፍ ደረጃቸውን እንዲጠብቁ ዘሪሁን ሌት ተቀን ይለፋል፡፡ ይህ ልፋቱም በሌሎች ለመመስከር የቻለ ነው፡፡ ስለ ሀገራችን የህትመት ዘርፍ ስናነሳ የግራፊክስ ዲዛይን ባለሙያዎች እንዲሁም የሌይአውት ዘርፍ ሰዎች ሲያበረክቱት የነበረው ሚና ከጋዜጠኛው ወይም ከዋና አዘጋጁ እኩል የሚሆንበት ጊዜ አለ፡፡አንዳንድ ጊዜም የግራፊክስ ባለሙያው የተሻለ ሀሳብ የሚያፈልቅበት ወቅት አለ፡፡ የሚድያ ስራ የአንድ ወይም የሁለት ባለሙያዎች ድካም ውጤት ሳይሆን በቡድን የሚከወን ነው፡፡ ዘሪሁንም በሀገራችን ከ1994 በኋላ ሲታተሙ በነበሩ ህትመቶች ላይ  ያኖረው አሻራ ይነሳል፡፡ ብዙውን ጊዜ ከሙያዎች ጀርባ ያሉት ሰዎች ጎልተው በማይወጡባት በዚህች ሀገር ተወዳጅ ሚድያ ‹‹የሰራ ታሪኩ ይነገር›› በሚለው ህልሙ ወይም ራእዩ ከቅርብም ከሩቅም ያሉ የመገናኛ ብዙሀን ታታሪ ሰዎችን መሰነዱን ተያይዞታል፡፡ ዘሪሁን አሰፋ ከተወዳጅ ሚድያ ጋርም በቅርበት መስራት ብቻ ሳይሆን ሀሳቡ ሲጠነሰስ ከነበሩት ባለሙያዎች እና የግራፊክስ አማካሪዎች አንዱ ነው፡፡ ዘሪሁን አሰፋ፣ ተወዳጅ ሚድያ የሚሰራቸውን የታሪክ ስነዳዎች የምረቃ መርሀ-ግብሮች  በባነር እና ህትመት በማሳመር ከራሱ ወጪ በማድረግ የተወዳጅ ሚድያ አንደኛው አመታዊ  የትርፍ ተካፋይ / ባለ ድርሻ / ለመሆን የበቃ ነው፡፡ እናም ከተወዳጅ ሚድያ የታሪክ ፕሮጀክት ጀርባ ወይም ጎን ዘሪሁን አለ፡፡ አጠገባችን ያለን ሰው አጉልቶ ማውጣት ፍጹም ባልተለመደበት በዚህች ሀገር ዘሪሁን ለኢትዮጵያ የሚጠቅም ድንቅ ባለሙያ ስንል ታሪኩን ለትውልድ እንዲተላለፍ አስቀምጠናል፡፡   ዘሪሁን በሙያው ከዚህ በላይ ሰርቶ ድንቅ ነገር ሊያሳየን እንደሚችል እንተማመናለን፡፡ በተለይ በእርጋታ መፍጠን የሚለው መርሁ ሌሎችም ሊኮርጁት የሚገባ ነው፡፡ በርታ ዘሪሁን፡፡ ›      

      


 







 

 

 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች