170.ሳሙኤል ፈረንጅ

 

 ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን፣ በቅርቡ ክምችተ-አእምሮ / ኢንሳይክሎፒዲያ / በሚል ርእስ የሚድያ እና የኮሚኒኬሽን ባለሙያዎችን ታሪክ በጠንካራ ሽፋን መጽሀፍ አሳትሞ ያስመርቃል፡፡ ታሪካቸው በመጽሀፉ ውስጥ ከሚሰነድላቸው አሻራ ካኖሩ የሚድያ ሰዎች አንዱ አቶ ሳሙሴል ፈረንድ ናቸው፡፡‹‹የመጀመሪያዊ ኢትዮጵያዊ ቴሌቪዥን ተናጋሪ›› ጋዜጠኛ ሳሙኤል ፈረንጅ ከዜና ተናጋሪነታቸው ባሻገርም የኢትዮጵያ ቲቪ የመጀመሪያው የስራ መሪ ናቸው፡፡ ፅሁፉንና  መረጃውን አሰባበስበው ያቀናበሩት  የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ኢንሳይክሎፒዲያ ፕሮጀክት የቦርድ አባል እና በወልድያ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነት መምህር እጩ ዶ/ር አየለ አዲስ ናቸው፡፡

 

  የአቶ ሳሙኤል ፈረንጅ ውልደት እና እድገት

የቀድሞው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዳይሬክተር፤ አቶ ሳሙኤል ፈረንጅ  ከቀኝ አዝማች ፈረንጅ ቦጡ አና ከእናታችው ከወ/ አበበች ገመዳ መጋቢት 27 ቀን 1929 በኢትዮጵያውያን ቀን አቆጣጠር በወለጋ /ሃገር  ውስጥ ተወለዱ፡፡ የአንደኛ አና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታችውን በደምቢዶሎ መንግስት ትምህርት ቤት እንዲሁም አዲስ አበባ ባላባት እና ተፈሪ መኮንን /ቤት ተምረው አጠናቀዋል። ተፈሪ መኮንን ተማሪ በነበሩበትም ወቅት ለአራት አመታት በዲያቆንነት ምስካዬ ኅዙናን መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን አገልግለዋል። ጂማ እርሻ ኮሌጅ ተምረው ከተመረቁ በኋላም በኢትዮጵያ አየር መንገድ በሂሳብ ሰራተኝነት አገልግለዋል። ለትምህርት ቤቱ ሬዲዮ ፕሮግራም ይሰሩ ነበር፡፡

1960 የኢትዮጲያ ቴሌቪዥን ዋና ዲሬክተር እንዲሆኑ በዓጼ ሃይለስላሴ ተሹመው በዚህ የኃላፊነት ቦታቸው ለሃገር የሚጠቅም በርካታ ስራ ሰርተዋል። የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከመቋቋሙም በፊት ነበር፤ አቶ ሳሙኤል የዓጼ ኃይለሥላሴ ልዩ ጋዜጠኛ ሆነው ሲሰሩ የነበረው፤ የንጉሱ ንግግር ፀሃፊም ሆነው አገልግለዋል። 1966 ደርግ ስልጣን ሲይዝ፤ለተወሰነ ጊዜ በነበሩበት የሥራ ኃላፊነት ከቆዩ በኋላ፤ የማስታወቂያ ሚኒስትር ኣማካሪ ሆነው ተሹመው ሰርተዋል። ከዚህ በተጨማሪ በፍርድ ሚኒስትር፣ በእርሻ ሚኒስትር እና በመሬት ይዞታ መስሪያ ቤት፤ እንዲሁም ታጠቅ ጦር ሰፈር የቁም እስረኛ ሆነው የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ዋና ኃላፊ ሆነው ሰርተዋል። 1970 .. ውድ ሃገራቸውን ትተው ከወጡ በኋላም በጀርመን ሃገር ከዘጠኝ አመታት በላይ በጣልያን ሀገር ደግሞ ከሁለት ዓመት በላይ ኖረው በመጨረሻም ወደ ቶሮንቶ ካናዳ በመሄድ ህይወታችው እስካለፈበት ድረስ በቶሮንቶ ኖረዋል። አቶ ሳሙኤል ፈረንጅ በነሃሴ 1995 በድንገት ታመው ሕይወታቸው እስካለፈበት እስከ ህዳር 20 ቀን 2010 (November 29, 2017 GC) ድረስ በቶሮንቶ በሕክምና ሲረዱ ነበር።

የአቶ ሳሙኤል ፈረንጅን የሕይወት ታሪክ በአጭር መግለጽ ከባድ ነው። ሆኖም ከጋዜጠኝነት ሙያቸው በተጨማሪ ለሃገራቸውና ለሕዝባቸው ጉልህ አስተዋፅኦ አድርገዋል። ከነዚህም በጥቂቱ 1966 ረሃብ ውሎንና በከፊል ትግራይን አጥቅቶ በነበረበት ወቅት፣ ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ ባቋቋሙት ኦርኬስትራ ድምፃዊ ሆነው በመስራት፤ በወቅቱ በረሃቡ ለተጠቁ ዜጎች አገዝ እንዲሆን በተዘጋጀው ዝግጅት ወደ 159 ሺህ ብር እንዲሰበሰብ አስተዋጽኦ አድርገዋል። የአክሱም ሃውልት ወደ ኢትዮጲያ እንዲመለስ ከእነ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት፤ / አበራ ሞላና ከሌሎች እውቅ ኢትዮጵያውያን ጋር በመስራት በተለይም የካናዳ መንግስት በጣሊያን መንግስት ላይ ተፅእኖ እንዲያደርግ የካናዳን ፓርላማ በማስተባበር ጉልህ ሚና ተጫውተዋል። የጣሊያንን ፓርላማ በማስተባበር ሮም የሚገኝው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ፊት ለፊት ከፓርላማው አባላት ጋር ደርግን በማውገዝ ሰላማዊ ሰልፍ መርተዋል።

የጀርመንም ሆነ የጣሊያን መንግስታት በኢትዮጲያዊያን ስደተኞች ላይ የሚፈጽሙትን በደል በማውገዝ እንደ ቺካጎ ትሪቡን ባሉ ጋዜጦችና በጀርመን ጋዜጦች ላይ ትችት ጽፈዋል ፡፡ቃለ መጠይቅም ሰጥተዋል። የኢትዮጲያዊያን የስፓርት ማህበር በሰሜን አሜሪካ፤ የቶሮንቶ ስታር ክለብ 9 ዓመቱን አዘጋጅ በነበረበት ወቅት ዝግጅቱን አስተባብረዋል። የኢትዮጵያውያን፤ የባሕል፤ የሃይማኖት፤ እንዲሁም የኪነ-ጥበበ ተቋማት በስደትም ቢሆን እንዳይጠፉ ተቋማቱን ከመመስረት ጀምሮ ቀጣይነት እንዲኖራቸው ጉልህ ተሳትፎ አድርገዋል፤ ከእነዚህም በጣሊያን የስደተኞች ማህበር፥ የኢትዮጲያውያን ማህበር በቶሮንቶ እንዲሁም፤ የኢትዮጵያውያን ዕድር በቶሮንቶ፤ በቶሮንቶ የኢትዮጵያውያን የስነጥበብ ስብስብ፤በቶሮንቶ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ጉልህ ተሳትፎ ነበራቸው። አቶ ሳሙኤል የጋዜጠኞች ማህበር እግር ኳስ ተጫዋች፣ በሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን በተደረሰውአጽም በየገጹ በተሰኘው ትያትር የጀነራል መንግስቱ ነዋይን ገጸ- ባህሪይ በብቃት ተውነዋል።የጥፋት መንትዮች እናመሰንበት ደጉ የተባሉ መጽሐፎችን ጽፈዋል።ወመኔው ሻለቃየዘመነ ደርግ ሰቆቃ እንዲሁምይሰቀል ይሰቀል የሚሉ ትያትሮችን ጽፈዋል።

ስለልዕልት ዲያናም (Princess Diana) የህይወት ህልፈት በእንግሊዘኛ የጻፉት “ IN MEMORIAM” የተሰኘው ግጥም “THE NATIONAL LIBRARY OF POETRY” በተባለው አለም አቀፍ ድርጅት ከመሸለሙም በላይ “THE WONDERFUL VERSES” ተብሎ ከሌሎች ግጥሞች ጋር “THE SOUND OF SILENCE” በሚል መጽሀፍ ታትሞ ወጥቷል። ከዚህ በተጨማሪ፥ እውቁ “TIME MAGAZINE” የአመቱ የታላላቅ ሰዎች ብሎ በጥር 3 1994 (የአውሮፓ አቆጣጠር) ለመረጣቸው መሪዎች ለመጽሄቱ ከተላኩ በርካታ ደብዳቤዎች መሃል ተመርጦ፥ የአቶ ሳሙኤል ጽሁፍየምርጥ ምርጥ ተብሎ በጉልህ የደብዳቤዎች ሁሉ አርእስት ሆኖ ታትሟል። በኦክላሖማው ገዥ(Oklohoma’s Governor David Walter) የኦክላሖማ የክብር ዜግነት ሲሰጣቸው፥ 1970 ደግሞ ከጣሊያን ፕሬዘዳንት ጅሴፔ ሳጋራት የክብር ኒሻን አግኝተዋል። የጣሊያንም የክብር ዜጋ ነበሩ።

ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያ የክብር ኮከብ የመኮንን ደረጃ ኒሻን እና ከተለያዩ አስራ ሰባት የዓለም መሪዎች የክብር ኒሻኖችን ተሸልመዋል። በቶሮንቶ የትዝታ መጽሔት ሲመሰረት ከመስራቾቹ አንዱ ከመሆናቸውም በተጨማሪ የመጽሄቱ ዋና ተቀዳሚ አዘጋጅ ሆነው አገልግለዋል። በስደት በነበሩበት ወቅትም ለአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ በሪፖርተርነት ሰርተዋል። በበርካታ መጽሄትና ጋዜጦች ላይ በስማቸውና በተለያዩ የብዕር ስሞች ብዙ መጣጥፎችና ግጥሞችን አሳትመዋል። አቶ ሳሙኤል ድምጽ ለሌለው የኢትዮጲያ ህዝብ ድምጽ፤ ለሃገራቸውና ለህዝባቸው ተሟጋች ነበሩ። 1983 በተለይም በመኤሶንና በኢሕአፓ መሃከል እርቅ እንዲፈጠር ጉልህ ሚና ተጫውተዋል፡ ከዚህም በተጨማሪ፤ 1982 መጨረሻ የእርስ በርስ ጦርነቱ እየተፋፋመ በመጣ ጊዜ፤ የሰላምና የእርቅ ድርድር እንዲደረግ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። በጥቅምት 1986 ኢትዮጵያ ውስጥ የሰላምና የእርቅ ጉባኤ እንዲደረግ የካናዳ መንግስት በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ተጽእኖ እንዲያደርግ ከካናዳ ፓርላማ ጋር በቅርበት ሰርተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፤ በወቅቱ የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ከነበሩት ለኪም ካምቤል (Kim Campbell) ኢትዮጵያ ውስጥ የሰላምና እርቅ ጉባኤ መካሄዱን አስፈላጊነት በመጻፍ፤ በወቅቱ -Foreign & Commonwealth  Office የአፍሪካ ጉዳይ ቢሮ ጋር በቅርበት ሰርተዋል።

እንዲሁም፤ ካናዳ ነዋሪ በነበሩበት ወቅት፤ ለካናዳ ፍርድ ቤቶች፤ አማርኛ፤ ኦሮሚኛና፤ ጀርመንኛ አስተርጓሚ ሆነው ከመስራታቸው በተጨማሪ፤ ለካናዳ Broadcasting Corporation 1960ዎቹን ሙዚቃዎች አስመልክቶ የዶክመንተሪ ፊልም በመስራት ላይ እንዳሉ ነበር በድንገት የልብ ሕመም አጋጥሟቸው ወደ ሆስፒታል የተወሰዱት፤ እኝህ ህይወታቸውን በሙሉ ለሕዝብ ድምጽ የነበሩ ኢትዮጵያዊ፤ ድምፃቸውን አጡ፤ ከነሃሴ 1995 ጀምሮ ሕይወታቸው እስካለፈበት እስከ ህዳር 20 ቀን 2010 ድረስም የአልጋ ቁራኛ ሆነው የሃገራቸውና የሕዝባቸው ሰላምና ፍትሕ እጦት እያብከነከናቸው ሕይወታቸው አለፈ። አቶ ሳሙኤል ፈረንጅ BBC በሬድዮ ጋዜጠኝነት ትምህርት ከመውሰዳቸው በተጨማሪ በቴሌቪዥን ጋዜጠኝነትና አስተዳደር እንግሊዝ አገር በሚገኘው Thompson Broadcasting College ትምህርትና ሥልጠናቸውን አጠናቀዋል።

አቶ ሳሙኤል 8 ልጆች አባት የስምንት ልጆች አያት አና የአንዲት ልጅ ቅድመ አያት ነበሩ\ የአቶ ሳሙኤል የቀብር ስነስራት በህዳር 23 ቀን 2010 (December 2, 2017) በቶሮንቶ ካናዳ ተፈጸመ።

ሳሙኤል ፈረንጅ ስመጥሩዉ ጋዜጠኛ እድምተኞቹን የማፍዘዝ አንዳች መግነጢሳዊ ኃይል፡

የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዓመታዊ በዓሉ በተከበረ ቁጥር፤ አቶ ሳሙኤል ፈረንጅ ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ምስረታና እድገት ያበረከቱት አስተዋጽኦ ሳይጠቀስ አያልፍም። ሆኖም፤ ስለ አቶ ሳሙኤል ሥራ በሰፊው የተዘገበው የደራው ጨዋታ በተባለው የሬድዮ ፕሮግራም ላይ ከዛሬ አራት ዓመታት ገደማ በፊት ነበር። ጋዜጠኛ ጌታቸው ደስታና ጋዜጠኛ ተክሉ ታቦር፤ ከአቶ ሳሙኤል ጋር ስለነበራቸው ግንኙነት፤ ስለ አቶ ሳሙኤል፤ ሥራና ባሕሪ፤ በተወሰነ ደረጃም ለአድማጭ አካፍለዋል፤ በዚሁ ዝግጅት ላይም ልጃቸው አቶ ነብዩ ሳሙኤል፤ ስለአባቱ የነበረውን ትዝታ በመጠኑ ለሕዝብ አካፍሏል።

በዚህ ዝግጅትም ላይ ነው የደራው ጨዋታ አዘጋጅ፤ አቶ ሳሙኤልን እድምተኞቹን የማፍዘዝ አንዳች መግነጢሳዊ ኃይል ያለው ሲል የገለጻቸው። ጋዜጠኛ ጌታቸው ደስታ አቶ ሳሙኤልን እንዴት ትገልጻቸዋለህ? ተብለው ሲጠየቁ፤ ሳሙኤል ፈረንጅ ቁመተ- ረጅም ረቂቅ የሆነ ሰው ነው ሲሉ በአጭሩ አቶ ሳሙኤልን ገልጸዋቸዋል። አዎ አቶ ሳሙኤል በርካታ ተሰጥኦ የነበራቸውና ያንን እግዚአብሔር የሰጣቸውን ፀጋ በሚገባ የተጠቀሙበት ብርቅዬ ኢትዮጵያዊ ነበሩ። አቶ ሳሙኤል ዲያቆን፤ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች፤ የዓፄ ኃይለሥላሴ ልዩ ጋዜጠኛና ንግግር ፀሃፊ፤ የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ የቴሌቪዥን ጋዜጠኛ፤ የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዋና ዳይሬክተር፤ ደራሲ፤ ገጣሚ፤ የቲያትር ተዋናይ፤ የቲያትር ፀሃፊ፤ ድምፃዊ፤ ሰዓሊ፤ ጋዜጠኛ፤ የሂሳብ ባለሙያ፤ እግር ኳስ ተጫዋች፤ ከሁሉም በላይ ግን ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያውያን መብት ተሟጋች ነበሩ። በእውነትም፤ አቶ ሳሙኤል ረቂቅ ሰው ነበሩ። አቶ ሳሙኤል የመጀመሪያዊ ኢትዮጵያዊ ቴሌቪዥን ተናጋሪም ነበሩ።

የመጀመሪያዊ ኢትዮጵያዊ ቴሌቪዥን ተናጋሪ።

አዲስ ዘመን ጋዜጣ ጥቅምት 23 ቀን 1957 . ባወጣው እትሙ፤ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አገልግሎት በጥቅምት 23 1957 . ሥራ ከመጀመሩ በፊት፤ አዲስ አበባ ውስጥ ለመጀመርያ ጊዜ የቴሌቪዥን አገልግሎት ተሰጥቶ እንደነበር ዘግቧል፤ ይኽውም የአፍሪካ አንድነት ሲቋቋም፤ የአፍሪካ መሪዎች ከፍተኛ ጉባኤ አዲስ አበባ ተደርጎ በነበረበት ወቅት፤ በጽጌረድ አደባባይ፤ በግዮን ሆቴልና በኢዮቤልዩ ቤተ መንግሥት፤ በፊሊፕስ ኩባንያ አማካይነት፤የቴሌቪዥን አገልግሎት ተሰጥቷል። እንደ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ዘገባ፤ በዚህ ጊዜ በቴሌቪዥን ዘጋቢነት ያገለገሉት፤ አቶ ሳሙኤል ፈረንጅና / ዓለም ሰገድ ኅሩይ ነበሩ።

የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አገልግሎት ከተቋቋመም በኋላ፤ ለአንድ ሰዓት ይሰጥ በነበረው አገልግሎት፤የአለም ዜናዎችን በመዘገብ፤ የባሕል ዘፈን ተጫዋቾችን ከነዘፈኖቻቸው በማስተዋወቅ ሰርተዋል። በወቅቱ የባሕል ዘፈኖቻቸውን የሚያቀርቡ የጥበብ ባለሙያዎች፤ ያለምንም ክፍያ ይሰሩ ስለነበር፤ለመጀመርያ ጊዜ በደሞዝ እየተከፈላቸው እንዲሰሩ ያደረጉት አቶ ሳሙኤል ፈረንጅ እንደሆኑ፤ እንደ አርቲስት አስናቀች ወርቁና አርቲስት አሰገደች ሃብቴ በተደጋጋሚ ገልጸዋል።

 

የባሕል አምባሳደር።

አቶ ሳሙኤል የባህል አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል። የኢትዮጵያ የባሕል ቡድን በየዓመቱ በተለያዩ ሃገራት እየሄዱ፤ የኢትዮጵያን ባሕል ያስተዋውቁ በነበረበት ወቅት፤ የቡድኑ መሪ አካል በመሆን አቶ ሳሙኤል ቻይና፤ሶቭየት ህብረት፤ ግብጽ፤ ታንዛንያና ወደ ሌሎች ሃገሮች ሄደዋል። የቻይና ጉብኝታቸውን አስመልክቶም ትዝታ በተባለ ካናዳ የሚታተም መጽሔት በሰፊው ዘግበውታል። የኢትዮጵያ የኪነት ባለሙያዎች፤ በተለያዩ የባህል አልባሳት ብሚያሳዩአቸው ትዕይንቶች ሁሉ አድናቆትን እንዳተረፉም ገልጸዋል፤ ቻይና በነበረው ትእይንትም፤ የወቅቱ የቻይና ፕሬዝዳንት፤ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤የመከላከያ ሚኒስትሩ፤ የባሕል ሚኒስትሩና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት መገኘታቸውንም ዘግበዋል። በእነዚህ ጉዞዎች፤ የቡድኑ መሪ አካል ከመሆን በተጨማሪም ለቡድኑ በእንግሊዝኛ አስተርጓሚነት አገልግለዋል።

ደራሲና ተዋናይ።

‹‹የደራው ጨዋታ›› በተሰኘው የሬድዮ ፕሮግራም፤ ጋዜጠኛ ተክሉ ታቦር፤ አቶ ሳሙኤል ከቴሌቪዥን አገልግሎት ስራቸው በተጨማሪ፤ መጽሔት ማሳተም ጀምረው ነበር፡፡ ሆኖም የመጀመሪያ የአቶ ሳሙኤል የመጀመርያ የሆነችው፤ የጥፋት መንትያዎች የተሰኘችው የሕትመት ሥራ በቅርቡ በአሜሪካን ሃገር ላይብረሪ ኦፍ ኮንግረስ በአቶ ፋንታሁን ጥሩነህ አገዝ ተገኝታለች። ይህች መጽሐፍ የታተመችው በጥር 1955 በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ነበር። ይህችን መጽሃፍ አስመልክቶም፤ መጽሐፏን የገመገሟት የሰንድቅ ጋዜጣ ምክትል አዘጋጅ የነበሩት ጋዜጠኛ አበበ ተጫነ ልብ ወለድ ድርሰቶችን ብዙ ጊዜ አንብብያለሁ፤ ይሁንና የጥፋት መንትዮች በሲኒማ በትያትርና በልዩ ልዩ ውጭ ሃገር መጽሐፍቶች እንዳየሁት፤ አቀራረቡ .. እንደ ዕንባ ደብዳቤዎች ነው…” አንባቢ ለማንበበ ሲጀምር እስከ መጨረሻው ገጹ መዝጊያ ድረስ እንዲደርስ የሚጎትት የደራሲው የቃላት ሥልጣን ያስገድዱታል ብለዋል።

አቶ ሳሙኤል በርካታ መጽሄቶችና ጋዜጦች ላይ ከመፃፍም ባሻገር፤ 1994 (እንደ አውሮፓ አቆጣጠር) መሰንበት ደጉ የተሰኘ የግጥም መድብልም ለሕትመት አብቅተዋል። የግጥም መደብሉ መታሰቢያነቱን ለቅርብ ጓደኛቸው ለአቶ መንግሥቱ ለማ ነው ያደረጉት።

መነጽር ይገዛል ሞኝ የጨዋ ልጅ፤

ሁሉን የሚያሳየው መሰንበት ነው እንጅ፤

ብላ ነው የግጥም መደብሏ የምትጀምረው። በዚህች ስብስብ መድብል ከተካተቱት ግጥሞች ውስጥ ብዙዎቹ እያዝናኑ የሚያስተምሩ ግጥሞች ናቸው። ‹‹አዳራሸ ሰፊ›› በሚል ርዕስ ከተጻፈው ግጥም በጥቂቱ እንዲህ ይላል፤

ጥንት በአባቶቻችን በአያቶቻችን ዘመን፤

የተለየ ነበር ሴትን ልጅ መለመን፤

ዓመት ሁለት ዓመት ከቶ ሳይሰለቹ፤

ደጅ ጥናት ማብዛት ነበር ቁልፉ ፍቹ፤

ደጅ ጥናት ብቻ ከግብ መች ያደርሳል፤

ሰጋር በቅሎ መስጠት ዕድል ያሻሻላል።

 

መሰንበት ደጉ በሚለው የግጥም መደብላቸው ካሳተሟቸው ግጥሞች በተጨማሪ፤ በትዝታ መጽሔት፤ በኢትዮጵያን ሪቪው መጽሔትና፤ እንደ ዕንቁጣጣሽ በተባሉ መጽሔቶች በርካታ ግጥሞችን አሳትመዋል። እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በኅዳር 15 ቀን 1994 በትዝታ መጽሔት ላይ ለክቡር አቶ ከበደ ሚካኤል ሙገሣ ባሳተሙት ግጥም እንዲህ ብለው ነበር።

 

ከበደ ሚካኤል ረቂቁ፤

የጥበበ መሶብ ወርቅ ሊቁ፤

የትምህርት ፈትፍት መረቁ፤

የነዲድ ብዕሩ ወላፈን ላንቃ፤

ሓብታም ድሓ ሳይል ሁሉን ያበቃ።

 

በዚሁ ዕትም፤ ይቅር በለኝ ጥቁር አባይ በሚል ርእስ ባሳተሙት ግጥም፤ የራሳቸውን ከዚህ ዓለም ስንብት በተነበየ መልኩ እንዲህ ብለው ነበር።

 

ለካስ አንተም እንደኔው ተከፍተህ፤

ከአገር መውጣትህ ነው ሸፍተህ?

አንሠራ አናሠራ ስላሉህ ነው?

አገርህን ጥለህ የኮበለልክው?

መቀበሪያ አፈርክን ያዘልከው?

ምንኛ ይመስላል ታሪካችን፤

በዚያው ተሰደን መቅረታችን።

አቶ ሳሙኤል፤ በግጥምና በስነጽሁፍ ብቻ ሳይሆን፤ በቲያትር ድርሰትም የተዋጣላቸው ነበሩ። ወመኔው ሻለቃ በሚል ርዕስ የጻፉት ቲያትር፤ በሓምዛ አብዶ አዘጋጅነት በቶሮንቶ ካናዳ ለዕይታ ቀርቧል። ይሰቀል ይሰቀል እና የዘመነ ደርግ ሰቆቃ የተሰኙት ቲያትሮችም እንደዚሁ ለእይታ ቀርበዋል። ዓጽም በየገፁ በተሰኘው የሎሬት ፀጋዬ ገብረመድኀን ቲያትር ላይም፤ የጄኔራል መንግስቱን ገፀ- ባሕሪ በብቃት በብሔራዊ ቲያትር መድረክ ላይ ተውነዋል። 

ምንጭ ልጃቸው

ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ

ዝክረ ሳሙኤል ፈረንጅ፤ ኅዳር 22 ቀን 2012 https://www.youtube.com/watch?v=GSgx9fwnWRw

 

የጋዜጠኛ ሳሙኤል ፈረንጅ አጭር የህይወት ታሪክና ልጃቸው አቶ ጥበበ ሳሙኤል የስጡት ምስክርነት/Journalist Samuel Ferenje's short bio.  https://www.youtube.com/watch?v=oXh81LuMvkY

መዝጊያ፣ ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የኢንሳይክሎፒዲያ  ቦርድ አባላትን አቋም የሚያንጸባርቅ ነው፡፡

 አቶ ሳሙኤል በኢትዮጵያ የሚድያ ታሪክ ደማቅ አሻራ ያኖሩ ታላቅና ድንቅ ሰው ናቸው፡፡ ስለ ቲቪ ሲነሳ የመጀመሪያው  የቲቪ ተናጋሪ ናቸው፡፡ ከላይ የተጠቀሰውን ታሪክ ብናጤን እኒህ ባለውለታ ለኢትዮጵያ ያልደከሙት ነገር የለም፡፡ ነገር ግን ብዙ ሲጻፍላቸው አናይም፡፡ ወይም አሻራ ባኖሩት ልክ እውቅና ሲሰጣቸው አላጋጠንም፡፡ ተሰጥቶም ከሆነ በቂ አይሆንም፡፡ ሳሙኤል ፈረንጅ የሀገራችን የቴሌቪዥን ታሪክ ሲነሳ በቀዳሚነት የሚነሱ ታላቅ ሰው ናቸው፡፡ ጥናት ለሚሰራ ሰው  የእርሳቸው ታሪክ ብዙ መነሻ ይሰጣል፡፡ ታሪካቸው በዚህ መልኩ መሰነዱ ለቤተሰቦቻቸው ኩራት ነው፡፡  ወደፊት ግለ-ታሪክን እንደሚሰንድ ድርጅት ተጨማሪ ጉዳዮችን አክለን እኒህ ታላቅ ሰው መዘከራችን አይቀርም፡፡

 / ፅሁፉንና  መረጃውን አሰባበስበው ያቀናበሩት  የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ኢንሳይክሎፒዲያ ፕሮጀክት የቦርድ አባል እና በወልድያ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነት መምህር እጩ ዶ/ር አየለ አዲስ ናቸው፡፡

 








  

 

 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች