173 አንተነህ ደግፌ ደጀኔ2000ዎቹ

ጋዜጠኛ፣ የሚዲያ፣ ኮሙኒኬሽን ባለሙያና የሁነት አዘጋጅ  አንተነህ ደግፌ በሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ዘርፍ የራሱን አሻራ ያኖረ ነው፡፡  መዝገበ -አእምሮ ላይ ታሪካቸው ከሚሰፍርላቸው አንዱ አንተነህ ደግፌ ነው፡፡ 

ልጅነት

ታህሳስ 10/1977 ዓ.ም በአዲስ አበባ የካቲት 12 ሆስፒታል የተወለደው አንተነህ ደግፌ እድገቱ በተለምዶ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ጀርባ 41 እየሱስ መንገድ ተብሎ ከሚጠራው ሰፈር ነው፡፡

የፈረንሳይ ኤምባሲ ጫካ፣ የቀበና ወንዝ፣ የሃምሌ 19 መናፈሻ ጥዶች እና ከጋራው ላይ የጭቁኑ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ጋዜጠኛ አንተነህ ልጅነቱን ያሳለፈበትን መንደር የከበቡ ታሪካዊ ቦታዎች ናቸው፡፡ ተፈሪ መኮንን ት/ቤት አጠገብ የሚገኘው ምስካዬ ሃዙናን መድኃኒዓለም ገዳም ኪዳን ያደረሰበት፤ ቅዳሴ ያስቀደሰበት የሃይማኖት መሰረቱን ያጸናበት ቅዱስ ቤቱ ነው፡፡

አባቱ አቶ ደግፌ ደጀኔ እና እናቱ ወ/ሮ አዲስ ዓለም ከበደ በመንግስት መስሪያ ቤት የሂሳብ ባለሙያነት አገልግለዋል፡፡ የጋዜጠኛ አንተነህ ደግፌ አንድ ብቸኛ እህቱ ወ/ት ሰላማዊት ደግፌ ትባላለች፡፡ በሙያዋ የጤና ባለሙያ ስትሆን ሶስት የመጀመሪያ ዲግሪ እና አንድ ማስተርስ አላት፡፡ እድሜ ዘመኗን ብትማር የማትሰለች የቀለም ቀንድ ነች፡፡

ልጅነቱን እንደ ልጅ በልጆች ጨዋታ ያላሳለፈው ጋዜጠኛ አንተነህ ደግፌ ለሙዚቃ ነፍሱ መክነፍ የጀመረችው ገና የመዋዕለ ህጸናት ትምህርት ቤትን ሲረግጥ ነው፡፡ ኳስ፣ የቡሄ ጭፈራ፣ ወንዝ ወርዶ ዋና እና መሰል የልጅነት ትዝታዎች ብዙም የሉትም፡፡  

ዕድገትና ከትምህርት ዓለም

ጋዜጠኛ አንተነህ ደግፌ መነን መዋዕለ ህጻናትን አገባዶ የፊደል ዘርን ሲለይ 5 ኪሎ የሚገኘው መካነ እየሱስ ትምህርት ቤት 1ኛ ክፍልን ቢጀመርም ብዙም አልገፋበትም ፡፡ ወደ መጽሀፍ ቅዱስ ትምህርትና መዝሙር ማጋደሉ አባቱ አልተስማማቸውምና ከዛ አስወጥተው እየሩሳሌም አንደኛ እና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አስገቡት፡፡

አሜሪካ ኤምባሲ አጠገብ የሚገኘው እየሩሳሌም ት/ቤት ጋዜጠኛ አንተነህ ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ያለውን የእውቀት ደረጃ ያለፈበት ብቻ ሳይሆን የዛሬውን ማንነቱን ፈልጎ ያገኘበት የእውቀት ቤቱ ነው፡፡

በአማርኛና እንግሊዝኛ የትምህርት ክፍለ ጊዜያት ምንባቦችን ድምጹን ከፍ አድርጎ ማንበብ እንዲያም ሲል በቃል ማንበብ፣ በሙዚቃ ክፍለ ጊዜ ደግሞ መዝፈንና አጫጭር ድራማዎችን መጫወት ፣ በሚኒ-ሚዲያ ማታ በቴሌቪዥን መስኮት ላይ የተመለከታቸውን ዘገባዎች መልሶ ጽፎ  በጋዜጠኛ ድምጽት ለተማሪዎች ሰልፍ ላይ ማቅረቡ በመምህራኑ ዘንድ ወደፊት ጋዜጠኛ ወይም የኪነ-ጥበብ ሰው ከመሆን ውጭ ምርጫ እንደሌው ይተነብዩ ነበር፡፡

በተለይ በ19 90 ዓ.ም 7ኛ ክፍል ተማሪ እያለ የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት መቀስቀስ ማታ ማታ ጋዜጠኛ ጌታቸው ኃይሉ ከግንባር ጽፎ የሚልከውን ግሩም ዘገባ ጋዜጠኛ አለምነህ ዋሴ በነጎድጓዳማ ድምጹ ሲተርክ በመስማት እሱኑ ደግሞ በማጻፍ የጋዜጠኝነትን ዳዴ ጀመረ፡፡

19 91 ዓ.ም የሚኒስትሪ ውጤትን በከፍተኛ ነጥብ  አልፎ ከትምህር ቤቱ የእጅ ሰዓት ተሸልሞ ወደ ዝነኛው ተፈሪ መኮንን ት/ቤት 9ኛ ክፍልን ሲቀላቀል ግን ጋዜጠኝነትን ችላ የሚያስበል አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡ የት/ቤቱ TMS የሙዚቃ ባንድ መሳሪያ ተጨዋቾችና ድምጻዊያንን ለማሰልጠን የለጠፈው ማስታወቂያ ልቡን አነሆለሉት፡፡

ወትሮንም የልጅነት ጨዋታ የማያወቀው አንተነህ የባልዲና የሶፋ ጀርባ እየቀጠቀጠ ድራም ለመጫዋት የሚያደርገው ጥረት ዕውን ሊሆን ነው ብሎ አመነ፡፡ ለመመዝገብ ሲሄድ ግን ወረፋው ተስፋውን አሰለሉት፡፡

አንዴ ቆርጦ ስለነበር ሰው ያልተመዘገበበትን ዘርፍ መርጦ በግጥምና ዜማ ደራሲነት ብሎ ተመዘገበ፡፡ በተደራቢነትም ትራምፔት ለመማር ወሰነ፡፡ ይሄንም ብዙ አልገፋበትም፡፡ ሙዚቃ ለማጥናት በሚል የሚያሳልፋቸው ጊዜዎች የመጀመሪያ መንፈቅ ዉጤቱን አሽቆለቆሉበት ፡፡ ቤተሰብም ክፉኛ ተቆጣ፡፡ ፍራሹ ሲገለጥ የዘፈን ግጥሞችና የከበሮ መምቻ የእንጨት ቆርጥራጮች ተገኙ፡፡ አይቀጡ ቅጣት ተቀጣ፡፡ ሙዚቃ የሚባል ነገር ጋር ድርሽ እንዳይል ቢሰማ እንኳ አንገቱን እንዳይሰብቅ ማስጠንቀቂያ ተሰጠው፡፡ እሱም የቤተሰቦቹን ቃል የሚሰማና ድንጉጥ ቢጤ ስለነበረ ሙዚቃና አንተነህ በጎሪጥ እየተያዩ ተላለፉ፡፡

11 እና 12ኛ ክፍልን በየካተቲት 12 መሰናዶ ትምህርት ቤት ሲማር ደግሞ ከአርቲስት ቶማስ በየነ ጋር ቲያትርን መስራት ጀመረ፡፡ ሌላኛው ተሰጥኦ ተገለጠ፡፡

1995 ዓ.ም ማትሪክ ተፈትኖ ውጤት በመጠባበቅ ላይ ሳለ በክረምት ወራት ራስ ቲያትር ባህል ክፍል ውዝዋዜ ለመስራትም ሞክሯል፡፡ ውጤት ሲወጣ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባ ነጥብ ቢያመጣም የተመደበበት ዩነቨርሲቲና የትምህርት ዓይነት ግን አልተዋጡለትም ነበር፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቲያትር ጥበባት ለማጥናት ያለመው አንተነህ ባህርዳር ዩኒቨርሲቱ social science and teaching የሚል ነበር የደረሰው ፡፡

መምህር መሆን ህልሙ አልነበረምና እጅግ ተበሳጨ፡፡ ድምጹን አጥፍቶ ወደ ያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት ደመነፍሱን ገሰገሰ፡፡ በወቅቱ ድራም በትምህርት ደረጃ ስለማይሰጥ ሳክስፎን ለመማር አመለከተ፡፡ ምን ዋጋ አለው ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ለተመደቡለት ተማሪዎቹ ጥሪ ሲያደርግ አባቱ አቶ ደግፌ ደጀኔ ከአዲስ አበባ ወጥቶ የማያውቀውን ልጃቸውን አንጠልጥለው ወደ ባህር ዳር አቀኑ፡፡

በዩኒቨርሲቲው ቆይታውም pedagogical science and composite major English አጥንቶ በመጀመሪያ ዲግሪ በ1998 ዓ.ም ተመረቀ፡፡ የዩኒቨርሰቲው ባህል ማዕከልን በመቀላቀል ቲያትሮችን መጫወት ፣ መድረክ መምራትና ግጥም ማቅረብ ዩኒቨርሲቲውን ብሎም የባህርዳር ሕይወቱን አስደሳች አደረጉለት፡፡

የ1997 ምርጫና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን አርድ አንቀጥቅጥ ተቃውሞ በግንባር ቀደምትነት በመቀላቀል በወቅቱ የነበረውን ገዥው ፓርቲ በንጹሃን ላይ የፈጸመውን ዘግናኝ ግድያ በመቃወሙና አውጋዥ መፈክር በማሰማቱ አንተነህ ደግፌ ለአጭር ጊዜም ቢሆን ዘብጥያ አስወርውሮታል፡፡ ያኔ ታዲያ የባህርዳር ህዝብ ያደረገላቸውን እንክብካቤ እያስታወሰ ዛሬም ድረስ ለባህርዳር ያለውን ልዩ ፍቅር አውርቶ አይጠግብም፡፡












የስራ ዓለም

መምህሩ አንተነህ

በጥቅምት 1/1999 ዓ.ም ዳግማዊ ሚኒልክ መሰናዶ ት/ቤት እንግሊዝኛን በማስተማር የስራን ዓለም አሃዱ ያለው መምህር አንተነህ ደግፌ ፒያሳ ከአርሾ ላቦራቶሪ ዝቅ ብሎ በሚገኘው የካቲት 66 ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት በእንግሊዝኛ መምህርነትና ዩኒት መሪነት የማስተማር ስራውን ገፋበት፡፡ በፈጣን እርምጃውና በቄንጠኛ አለባበሱ ማይክል”  እያሉ ነበር ተማሪዎቹ የሚጠሩት፡፡

በሙዚቃው ዓለም በተለይ ድራመር የመሆን  ህልሙ እንደከሰመ የተረዳው አንተነህ ዛሬም ድረስ ወደ ሚታወቅበት የጋዜጠኝነት ሙያ ለመግባት ሬዲዮ ፋና ያወጣውን ማስታወቂያ ተመልከቶ ልቡ ተነሳሳ፡፡

ጋዜጠኛው አንተነህ

የቀድሞውን ሬዲዮ ፋና የአሁኑን ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን በ2000 ዓ.ም በከፍተኛ  ሪፖርተርነት ተቀላቀለ፡፡ መሰረታዊ የሬዲዬ ጋዜጠኝነት ስልጠና ወስዶ እንዳጠናቀቀ የመጀመሪያ ምርጫው ወደ ሆነው ዜና ክፍል ተመደበ፡፡

ከአጫጭር ዜና ወደ ዜና መጽሄትና ዜና ማህደር ያሉ የዜና ማዕቀፎችን በቀጥታ መምራት በፍጥነት ከገቡት መካከል አንዱ ሆነ፡፡ የቢዝነስ ዘገባዎች፣ የትምህርት፣ መከላከያና ኪነ-ጥበብ ነክ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረጉ ዘገባዎችን በስፋት ይሰራ ነበር፡፡ የድህረ ምረቃ ትምህርቱንም በቀኑ መርሃ ግብር በመቀጠል በ Teaching English as foreign language (TEFL)  ሁለተኛ ዲግሪውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ2002 ዓ.ም ተቀበለ፡፡

የሙዚቃን ነገር እርም ማለት ያቀተው ጋዜጠኛ አንተነህ ደግፌ ለማስተርስ መማሪያው ወጪ አድርጎ ከተረፈው ገንዘብ ላይ ለልምምድ ብቻ የሚሆን ሙሉ የድራም መሳሪያ ገዝቶ ተፈሪ መኮንን ሲማር ከሚያውቃቸው ባልንጀሮቹ ጋር የንግድ ፈቃድ አውጥቶ ባንድ በማቋቋም ፋናን በ2004 ዓ.ም ተሰናበተ፡፡

ነገሮች ግን እንዳሰበው አልሆነለትም፡፡ ባንዱም ፈረሰ፡፡ ድራሙን ሰብስቦ ከቤተሰቦቹ ቤት አስቀምጦ ወደ ባህርዳር በማቅናት አማራ ቴሌቪዥን በዜና ክፍል ዜና አርታኢነትና አንባቢነት ተቀጠረ፡፡ ከወር በላይ ግን አልቆየም ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ለማህበረሰብ ሬዲዬ ማናጀርነት ያወጣውን ማስታወቂያ ተመልክቶ አመለከተ፡፡ ቃለ-መጠይቁንም ከሆላንድና እንግሊዝ የመጡ የአሜሪካ ኤምባሲ ሰዎች አድረገውለት በብቃት አልፎ ወደ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጓዙን ጠቀለለ፡፡

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሀዋሳ ድምጽ ኤፍ ኤም 97.7 ሬዲዬ ጣቢያን በማናጀርነት እያስተዳደረ communicative English I &II ኮርስን ይርጋ ዓለም ከተማ በሚገኘው የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ፋኩልቲ ማርኪቲንግ ማኔጅመንትና አካውንቲንግ ተማሪዎችን አስተምሯል፡፡

በሁለት ዓመት ቆይታው ሬዲዬ ጣቢያው የስርጭት ግብዓት እንዲሟላ በማድረግ ፣ አዝናኝና አስተማሪ የፕሮግራም ይዘቶችን በመቅረጽና በጎ ፈቃደኛ ወጣት ጋዜጠኞችን በመመልመልና በማሰልጠን ሬዲዮ ጣቢያው በአጭር ጊዜ ተወዳጅና ተደማጭ እንዲሆን አብረውት ከተቀጠሩት የይዘትና የቴክኒክ ኃላፊዎች ጋር የአንበሳውን ድርሻ ተወጥቷል፡፡ የሬዲዮ ጣቢያው መክፈቻና መዝጊያም የእሱ ድምጽ ሆኖ ማገልገሉንም ልብ ይሏል፡፡

ሁሌም የተሻለ ነገር በመፈለግና በመሞክር የሚያምነው አዲስ ነገር ናፋቂው አንተነህ 2006 ጥር ወር ላይ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ (ECX) በኮሙኒኬሽን እስፔሻሊስትነት ተቀጥሮ ከሀዋሳ ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ፡፡

በምርት ገበያው ቆይታው የህዝብ ግንኙነት ስራውን ለማሳደግና አዳዲስ እውቀቶችን ለመቃረም ብዙ ጥሯል፡፡ በተለይ በዘመናዊ ግብት ሰርዓት የቡና እና ሰሊጥ ግብይት እንዲመራ ማድረግ ለሀገራችን አዲስ እንደመሆኑ የውጭ ሀገር የቢዝነስና የባለስልጣናት ልዑክ ቡድን ሲመጡ የግብይት መድረክ ድረስ ወስዶ በማስጎብኘትና  ገለጻ በመስጠት ረገድ አዲስ የስራ ልምድ ያካበተበት የስራ መስክ ነበር፡፡

2007 ዓ.ም አጋማሽ ላይ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ለአማርኛ ዜና አንባቢነት  ባወጣው የፍሪላንስ ቅጥር ካመለከቱት 900 በላይ ተወዳዳሪዎች በብርቱ ፉክክር በቀዳሚነት አጠናቆ የቴሌቪዥን ዜና አንባቢ ለመሆን በቃ፡፡

በብሄራዊ ቴሌቪዥን ጣቢው በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰበር ዜና፣ የመንግስት አዋጆችና ጠንከር ያሉ መግለጫዎችን በማንበብ፤ በቀጥታ ዜና ስርጭት የሚጋበዙ እንግዶችን በተለይ የመነግስት ሹመኞችን  ከህብረተሰቡ ችግር ጋር በተያያዘ የሚነሱ ቅሬታዎችን በተድሰበሰ መልስ እንዳያልፉ ሞግቶ በመያዝ በአጭር ጊዜ በተመልካች ዕይታ ውስጥ እንዲገባ አስችሎታል፡፡ቀለል ያለ ዜና አቀራረቡንም የሚወዱለት ብዙዎች ናቸው፡፡

ጋዜጠኛ አንተነህ ደግፌ ከልጅነቱ ጀምሮ ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የተለየ ፍቅር ነበረው፡፡ አባቱ በዚሁ ተቋም የሂሳብ ባለሙያ ሰለነበሩ ተፅእኖ አሳድረውበት ይሆናል የሚል ግምት ሊሰት ይችላል፡፡ ሆኖም አንተነህ ታሪክ ወዳድ በመሆኑ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አንደ ቀዳሚነቱ የሀገሪቱን ታሪክ ሰንዶ የያዘ ተቋም በመሆኑ አጥብቆ ይሳሳለታል፡፡ የቀድሞ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋዜጠኞችን ባወሳ ቁጥር አክብሮቱ በጣም ከፍ ያለ ነው፡፡

ማህበራዊ ሚዲያ ፍጹም የማይጠቀመው አንተነህ ስለ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋዜጠኞችና ስለ ጣቢያው የሚፃፉ ፈር የለቀቁ ስድቦችና ዘለፋ ክፉኛ ያበሳጨዋል፡፡ የሚሄድ የሚመጣው የመንግስታት ጨቋኝነት እና የካድሬዎች ማን አለብኝነት የጣቢያውን ጋዜጠኞች ልጆቼን ላሳደግበት በሚል ፍርሃት አንገቱን ደፍቶ እንዲኖር አሰገድዶታ፡፡

ጋዜጠኛው የህዝብ ቁስል የሚያመው ነጻነት የተጠማ ስለመሆኑም ሽንጡን ገትሮ ይከራከራል፡፡ ስለሆነም የህዝቡ ወቀሳና ዘለፋ ለጋዜጠኛው ሳይሆን ለመንግስትና እጃቸውን ለሚያረዝሙ አጎብዳጅ ካድሬዎች ሊሆን ይገባል የሚል ግትር አቋም አለው፡፡

ጣቢያው ሁሌም በህዝብ ዘንድ ተወዳጅ፣ ታማኝና ተፅዕኖ ፈጣሪ እንዲሆን ይመኛል፡፡ ከአለቆቹና ከጣቢያው ጋዜጠኞች ጋር እጅግ መልካም ግንኙነት ያለው ሲሆን አንባቢ ሲጠፋ ወይም አስቸኳይ መግለጫና ሰበር ዜና ሲኖር ግባ ከተባላ ፈጥኖ በመድረስ ምስጉን ነው፡፡

መድረክ መሪው አንተነህ

ገና ከትምህርት ቤት ብሎም በዩኒቨርሲቲ የባህል ማዕከል መድረክ የመምራት ክህሎቱን ያሳየው ጋዜጠኛ አንተነህ ደግፌ ዛሬ ላይ በርካታ ትላልቅ ሁነቶችን ከአብሮ አደጉና የሙያ ባልደረባው የማስታወቂያ ባለሙየያው ይድነቃቻው ጋሻው ጋር በጋራና በተናጥል መድረኮችን ይመራል፡፡ ቀንጅና ውድድሮች፣ የሙዚቃ ኮንሰርቶች፣ ባዛርና ኤክስፖዎች፣ የመጽሀፍትና ፊልም ምረቃ፣ የተቋማት ዓመታዊ በዓላት፣ የባንኮችና ተሌኮም ኩባንያ ምርተርና አገልግሎት ማስተዋወቂያ መድረኮችን፣ ጋዜጣዊ መግለጫዎችን (press conference) የገቢ ማሰበሳቢያ ቴሌቶኖችንና መሰል መድረኮችን በብቃት መርቷል፡፡

በመድረክ መምራት የተሳተፈባቸው ሁነቶች በጥቂቱ፡-

     ላለፉት 9 ዓመታት በየዓመቱ የአዲስ ዓመት፣ የገናና ፋሲካ ባዛሮችን ከእዮሃ ኤቨንትስና ኢንተርቴይመንት፣ ከሲሳይ አድርሴ ፕሮሞሽን፣ ከአሜዚንግ ፕሮሞሽንና ከአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል እና ገበያ ልማት ደርጅት

     የሚስ አዲስ እና ሚስ ሀበሻ ቁንጅና ውድድሮች

     የኢትዮጵያ ግብርና ኢኒስቲቲዩት 50ኛ ዓመት ክብረ በዓል

     የጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊ ፣ ከተወዳጅ ሚዲያነ ኮሙኒኬሽን ጋር የሪቻርድ ፓንክረስትና የአሰብ ወደብ መሀንዲስ በየነ ወልደገብርኤል ፣ የዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ግለታሪክ መጽሀፍት ምረቃ ሁነቶች

     የኢትዮ ቴሌኮም ዓመታዊ የሰራተኞች በዓል፣ የ4ጂ ኔትወርክ ማስመረቂያ ፕሮግራም በ16 ሪጂኖችና የተቋሙን በርካታ ጋዜጣዊ መግለጫዎች

     የአንጋፋዋ አስቴር አወቀ የአዲስ አመት የሙዚቃ ኮንሰርት በሸራተን አዲስ

     የኢሬቻ የሙዚቃ ኮንሰርት በጊዮን ሆቴል

     የፐብሊክ ሰርቪስና ትራንስፖርት አገልግሎት ዓመታዊ ክብረ በዓል በየዓመቱ

     የሲፒዩ ኮሌጅ ዓመታዊ የተማሪዎች ምረቃ በዓል

     የሆራ ኮርፖሬት ግሩፕ ዓመታዊ የሰራተኞች ቀን

ግለ-ታሪክ ጸሀፊው አንተነህ

ጋዜጠኛ አንተነህ ደግፌ መጽሀፍን እንደ አስቤዛ በየወሩ ከደሞዙ ላይ ቢያንስ አንድ መጽሀፍ የመግዛት ባህል አለው፡፡ በየትኛውም ሙያ ለስኬት በቅተው ግለ-ታሪካቸውን የጸፉ ወይም የተጻፈላቸው ኢትዮጵያዊያን፣ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው መጽሃፍት ላይ የያተኩራል፡፡

ይህ ግለ-ታሪክ መጽሀፍትን የማንበብ አባዜው እሱም ግለ-ታሪክ ለመጻፍ ሀሳብ አሳደረበት፡፡ እናም በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የኤሌክትሮኒክስ ነግድ ፈርቀዳጅ የሆኑትነ የመዲና ህንጸ ባለቤት የሀጂ ዑመር ኢማመነምን ግለ-ታሪክ ለአንባ አበቃ፡፡ ከዛም በሻገር ለአንባቢ በይፋ ዔቀርብ አንጂ ድሬደዋ ከተማ የሚገኘውን ዴልት የማርየያም ወረቅ ሆስፒታል መሰራች ሰልገሆነው ፋራሚስት ዳዊት አበበ ግለ ታሪክ አጭር መግለተሪከ እና ዘጋቢ ፊል ስረቶ በግለሰቡ ስም ለሚቋወቃመው ፋወወንዴሽን አንዲወል አድርጓል፡፡

በቀጣይም በሀገራችን የፖለቲካ ታሪክ ጉልህ አሻራ ያሳረፉ በደማቅ ቀለም ታሪካቸው ሊጻፍላቸው ይገባል ብሎ የሚያስባቸውን ሰዎች ለማሰናዳት ውጥን ላይ ነው፡፡

ቤተሰብ

ጋዜጠኛ አንተነህ ደግፌ ከባለቤቱ ወ/ሮ ብሌን አበራ ጋር ጥር 25/2006 ዓ.ም ጋብቻ ፈጽመው ሎዛ አንተነህ እና ስኂን አንተነህ የተባሉ ሁለት ሴት ልጆችን አፍርቷል፡፡ በትዳሩም እጅግ ደስተኛ እና እግዚአብሄርን አብዝቶ በእንባ የሚያመሰግንበት ህይወት እየመራ ይገኛል፡፡

 

 

መዝጊያ ፤ ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ የመዝገበ አእምሮ / ኢንሳይክሎፒዲያ / ቦርድ አባላትን አቋም የሚያንጸባርቅ ነው፡፡

አንተነህ ደግፌ በሚድያው አለም በቆየባቸው 14 አመታት በብዙ መስርያ ቤቶች ውስጥ በመዝለቅ ልምድ ለመቅሰም የቻለ ባለሙያ  ባለሙያ ነው፡፡ ለኮሚኒኬሽን እና ለጋዜጠኝነት የተሰጠ ሰብእና የተላበሰ ነው፡፡ አንተነህ ከዩኒቨርሲቲ ጀምሮ በኮሚኒኬሽን ላይ ጥሩ ግንዛቤ ስለነበረው በሚድያው ላይ እንደልቡ ለመስራት አዳጋች አልሆነበትም፡፡ አንተነህ በአሁኑ ሰአት የዜና አንከር ብቻ ሳይሆን መጽሀፍትን አድኖ በመግዛትና በማንበብ ይታወቃል፡፡ ለዛ ባለው ድምጹ ዜና ሲያነብ አመታት ተቆጠሩ፡፡ አንተነህ በዚህ ግለ-ታሪክ አዘጋጆች እምነት መልካም ሰብእና የተላበሰ በሰዎች የሚወደድ ጥሩ ማህበራዊ ግንኙነት ያለው ሰው ነው፡፡ ይህንን አብረውት የሰሩ በግልጽ ለዚህ ግለ-ታሪክ አዘጋጅ መስክረዋል፡፡ አንተነህ ከመድረክ መሪነቱ፤ ከኮሚኒኬሽን ባለሙያነቱ ባሻገር የሰዎችን ግለ-ታሪክ በጥናት ላይ ተመስርቶ በመስራት እውቅና አትርፏል፡፡ እንዲህ አይነት ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች ደግሞ ከተወዳጅ ሚድያ ራእይ ጋር ይጣጣማሉ፡፡ አብረው ቢሰሩም ቋንቋ ለቋንቋ መግባባቱ ይኖራል፡፡ አንተነህ ተወዳጅ አሁን ያለበት ደረጃ ከመድረሱ  በፊት መድረኮቻችንን ጥሩ አድርጎ በመምራት በማማከር እዚህ ለመድረሳችን የበኩሉን ድርሻ የተወጣ ሰው ነው፡፡ ታዲያ ይህ ስረ-መሰረታችንን የሚያውቅና ራእያችንን የተጋራ ሰው በምን መንገዶች እንዳለፈ ማሳየት ከእኛ ይጠበቃል፡፡ አንተነህ ብዙ አድናቂዎች ያሉት ብቻ ሳይሆን በእውቀት ተሞልቶ የሚሰራ ስለሆነ እንዲህ አይነት ሰዎች ታሪካቸው ከስር ከስሩ ቢሰነድ የሚኖረው ጠቀሜታ ትልቅ ነው፡፡ መዝገበ-አእምሮ እንደ አንተነህ ላሉ ሰርተው ለማይደክማቸው ብቁዎች ስፍራ አላት፡፡ ኢትዮጵያ ከስር ከስር  በእንዲህ  መልኩ ልጆቿን ከፊት ብታመጣ የት ትደርስ ነበር፡፡ እኛ ግን ጀምረነዋል፡፡











አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች