169 አሸብር ጌትነት
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን፣ በቅርቡ መዝገበ-አእምሮ / ኢንሳይክሎፒዲያ / በሚል ርእስ የሚድያ እና የኮሚኒኬሽን ባለሙያዎችን ታሪክ በጠንካራ ሽፋን መጽሀፍ አሳትሞ ያስመርቃል፡፡ ታሪካቸው በመጽሀፉ ውስጥ ከሚሰነድላቸው አሻራ ካኖሩ የሚድያ ሰዎች አንዱ አሸብር ጌትነት ነው፡፡
የአራቱ
ሳምንታት ውድድር
በየሳምንቱ
ሰኞ በደብረ ማርቆስ የንጉስ ተክለሀይማኖት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሶስተኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል የሚደረገው የንባብ ውድድር ሊጀመር አንድ
ሳምንት ብቻ ቀርተውታል፡፡አራቱም ሴክሽኖች ተወዳዳሪዎችን እያስመረጡ ናቸው፡፡ የያኔውን ልጅ እግር አሸብር ጌትነትን ጨምሮ
አርባ ሶስት ተማሪዎች የሚገኙበት የሶስተኛ A ክፍልን ለንባብ ውድድሩ በፍላጎት የሚወክሉትን ለመምረጥ የክፍሉ ኃላፊ መምህር እድሉን
ሰጡ፡፡ ዝምታ ሰፈነ፡፡ “ካሸነፋችሁ ትልቅ ሽልማት ነው የሚሰጣችሁ” ቢሉም እጁን የሚያነሳ ተማሪ ጠፋ፡፡ ድንገት ፊት ለፊት
ከተቀመጡ ተማሪዎች መካከል “እኔ ጋሼ” የሚል ድምጽ ተሰማ፡፡ “እሺ አሸብር አንድ” ብለው መዘገቡ፡፡
ሁለት
ተወዳዳሪ ተማሪዎች ይቀራሉ፡፡አሁንም ክፍሉን ዝምታ ውጦታል፡፡ “እንግዲህ ካልሆነ እኔ ራሴ እመርጣለሁ” አሉና ጋሽ ድልነሳው ተጨማሪ
አንድ ወንድና አንድ ሴት ተወዳዳሪዎች መዘገቡ፡፡ የውድድሩ ቀን ደረሰ፡፡ ለአራት ተከታታይ ሳምንታት ተደረገ፡፡ለመጨረሻው ዙር
አሸብርን ጨምሮ ከሌላ ሴክሽን የመጡ ሁለት ተማሪዎች ቀረቡ፡፡አሸብርም የውድድሩ አጠቃላይ አሸናፊ ሆነ፡፡በዚያው ትምህርት ቤት
ያስተምሩ የነበሩትን የአሸብር አባትም ውድድሩን እየተከታተሉ ነበር፡፡ ልክ ውድድሩ ሲያበቃ የነ አሸብር ከፍል ሃላፊ የነበሩት
መምህር ድልነሳው ወደ ጋሼ ጌትነት ጠጋ ብለው “ልጅህ እኮ አኮራን፡፡ ሲያድግ የአደባባይ ሰው ነው የሚሆነው፡፡ ጠበቃ ወይንም
ጋዜጠኛ መሆኑማ አይቀርም፡፡”አሏቸው፡፡
ይህች
ንግግራቸውም በአሸብር የልጅነት ልቦና ውስጥ ቀርታለች፡፡“ምን
መሆን ትፈልጋለህ?” ሲባል ጠበቃ ወይንም ጋዜጠኛ፡፡ሌላ አይታየውም፡፡ደግሞ ከዚህ ሀሳብና ምኞት እንዳይላቀቅ የሚያደርጉ
ሁኔታዎች ተከትለው መጡ፡፡ ተማሪዎች ከጋዜጣ ወይንም መጽሄት ያነበቡትን ወይንም ከሬዲዮ የሰሙትን ጠቃሚ ጉዳይ ሁልጊዜ ጠዋት ጠዋት
የሰልፍ ፕሮግራም ላይ ማቅረብ እየተለመደ መጣ፡፡ አንድ ቀን ታዲያ አሸብር እድሉን አገኘ፡፡ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ “ስማኝ ልጄ”
የሚል ርዕስ የተሰጠውንና በሀገር ፍቅር ላይ የሚያተኩረውን ግጥም አቀረበ፡፡አጨበጨቡለት፡፡ጎበዝ የሚሉት በዙ፡፡ከዚህም በኋላ
በትምህርት ቤቱ የሚከበረው የወላጆች ቀንና ሌሎች ሁነቶች አሸብርን ከድምጽ ማጉያ ጋር እንዲለማመድ እድሉን አሰፉለት፡፡
ከትምህርት ቤቱም ውጭ ተሳትፎው ቀጠለ፡፡የያኔው የደብረ ማርቆስ ቀይ መስቀል ቅርንጫፍ ለማህበረሰቡ በሚሰጣቸው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት
መሳተፍና የተለያዩ ጹሁፎችን ማቅረብ ጀመረ፡፡ ብዙዎች ወደዱለት፡፡ጋሼ ድልነሳው ያሉት ነገር እውነት ሊሆን ነው መሰል?
ትውልድና የሙያ ጉዞ
ሚያዚያ
27/ 1973 ዓ.ም ከአቶ ጌትነት ህብስቱና ከወ/ሮ ረከብኪ ጸጋ የተወለደው ጋዜጠኛ አሸብር ጌትነት ከመጀመሪያ እስከ ሁለተኛ
ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለው እዛው ደብረ ማርቆስ ነው፡፡ “ለቤተሰቤ የመጨረሻ ልጅ ስለነበርኩ ነጻነቴ ልክ አልነበረውም፡፡
ልጅ እያለሁ በሰዎች መሀል ያለ ምንም ፍርሀት ሀሳቤን እንድገልጽና እንድናገር አባቴም ሆነ እናቴ በጣም ያበረታቱኝ ነበር፡፡”
በማለት ያ ሁኔታ ለዛሬው ማንነቱ የተጫወተውን ከፍተኛ ሚና ያስታውሳል፡፡ አሸብር በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ በቋንቋና ስነጹሁፍ የመጀመሪያ
ዲግሪውን ካጠናቀቀ በኋላ የስራ ዓለሙን አሀዱ ያለው በያኔው የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት በአሁኑ የኢትዮጵያ
ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ነበር፡፡ እስከ 1997 ዓ.ም የተለያዩ ሀገራዊ ሁነቶችን በመዘገብና የውጭ ዜናዎች አዘጋጅ በመሆን
ሲሰራ ከቆየ በኋላ ከ1998 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ የጣቢያው የዜና ክፍል ኃላፊ ሆኖ እንዲሰራ ተመደበ፡፡ “ወቅቱ በሚዲያው ላይ
ከውጭም ከውስጥም እጅግ ጫና የበዛበት፤ጋዜጠኞችም በጥርጣሬ የሚታዩበት ሁኔታ በከፍተኛ ደረጃ የጨመረበት ስለነበር አስቸጋሪነቱ
ይጎላል” የሚለው አሸብር በርካታ ፈታኝ ሁኔታዎችን ያሳለፈበት ጊዜ እንደነበር ያስታውሳል፡፡
በዘገባ
ሂደት አሸብር ያልነካው ርዕሰ- ጉዳይ የለም ማለት ይቀላል፡፡በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ በኢንዱስትሪ ፤ግብርና
፤ትምህርት፤ጤና፤መሰረተ ልማት፤ዲፕሎማሲ፤ሳይንስና ቴክኖሎጂ ወዘተ ድረስ ዘገባዎችን ሰርቷል፡፡ ዶክመንተሪ ፕሮግራሞችን
አዘጋጅቷል፡፡የዜና ትንታኔዎችን አቅርቧል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ዳካር ሴኔጋል ያደረገው የመጀመሪያ በረራ አሸብር
የውጭ ዘገባ አሀዱ ያለበት ስራው ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ከሀገሪቱ መሪዎች ጋር አብሮ በመጓዝ እነሱ የሚሳተፉባቸውን
የሁለትዮሽና የባለ ብዙ ወገን መድረኮች መዘገብ ጀመረ፡፡ እ.አ.አ ከጥቅምት 2007 ጀምሮ “ዓለም ዓቀፉን ሥርዐት ያመሰቃቀለው
የኢኮኖሚ ቀውስ በምን መንገድ መከላከል ይቻላል?” በሚል የቡድን 20 አባላት ሀገራት በለንደን፤እንግሊዝ ያደረጉትና የቀድሞው
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የተሳተፉበት ስብሰባ የአሸብር የዓለም ዓቀፍ መድረኮች ዘገባ ጅማሮ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ለተከታታይ
ዓመታትም
v አሜሪካ፤ፈረንሳይ፤ጣሊያን፤ሰሜን አየርላንድ (እንግሊዝ) ወዘተ ያዘጋጁትን የቡድን ስምንት
አባል ሀገራትን ስብሰባዎች
v በእንግሊዝ፤አሜሪካ፤ካናዳ፤ደቡብ
ኮሪያ፤ፈረንሳይ፤ሩሲያ ወዘተ የተካሄዱትን የቡድን ሀያ አባል ሀገራት ስብሰባዎች
v በኒዮርክ፤አሜሪካ
በተለያዩ ጊዜያት የተካሄዱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤዎችን
v በኮፐን
ሀገን ዴንማርክ፤በካንኩን ሜክሲኮ፤በሪዮ ዲጂኒሪዮ ብራዚል ወዘተ የተካሄዱትን አለም አቀፍ የአየር ንብረት ኮንፈረንሶች
v የዳቮስ
የአለም የኢኮኖሚ ፎረም ስብሰባዎች
v በቤልጂየም
በተለያዩ ዓመታት የተከናወኑ የአፍሪካና የአውሮፓ ህብረት የጋራ ስብሰባዎች
v የተለያዩ
የአፍሪካ ሀገራት ያዘጋጇቸው የአፍሪካ ህብረት መደበኛና ልዩ ጉባኤዎች
v እንዲሁም
በቻይና፤ኦስትሪያ፤ጀርመን፤ስዊዲን፤ስፔን፤ፖላንድ፤ኔዘርላንድስ፤ስዊዘርላንድ፤
ኖርዌይ፤ቱርክ፤ኩባ፤ህንድ፤እስራኤል፤ኩዌት፤
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፤ ደቡብ
አፍሪካ፤ዚምባቡዌ፤ኮንጎ ዴሞክራቲክ፤ሩዋንዳ፤ኡጋንዳ፤ኬንያ፤ ሴኔጋል፤ሊቢያ፤ኮትዲቯር፤ጋና
ወዘተ በመጓዝ የዜናና ትንታኔ ዘገባዎችን ለህዝብ አድርሷል፡፡
በአጠቃላይ አሸብር ከአህጉረ አውስትራሊያ ውጭ በሁሉም
ክፍለ ዓለሞች በመጓዝ ልዩ ልዩ ዘገባዎችን መስራት የቻለ ጋዜጠኛ ነው፡፡በሀገር ውስጥ የተከናወኑ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ስብሰባዎችና ኮንፈረንሶችም የአሸብር ጌትነት
አሻራ ያረፈባቸው ነበሩ፡፡ ምንጊዜም ጥር አጋማሽ ጀምሮ በአዲስ አበባ የሚካሄደው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤን ጨምሮ
በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ሁነቶችን በመዘገብ የፊት መስመር ላይ የሚሰለፍ ነው፡፡ በማህበረሰብ ጥናትና ልማት
ሁለተኛ ድግሪውን የሰራው አሸብር ሙያዊ አቅሞቹን ለማሳደግ የሚያግዙትን እንደ ቢቢሲና ቻናል ፍራንስ ኢንተርናሽናል ያሉ አለም
አቀፍ ሚዲያዎች የሚሰጣቸውን ስልጠናዎች በሀገር ውስጥና በውጭ
ተከታትሏል፡፡
የቀጥታ ስርጭት
የቀጥታ ስርጭት ዘገባዎች ከአሸብር ጋር ያላቸው
ቁርኝት እጅግ ጥብቅ ነው፡፡ከሀገር ውስጥ እስከ ባህር ማዶ ድረስ የተከናወኑ ድርጊቶችን የቀጥታ ስርጭት ሽፋን ላይ ተሳትፎ
ነበረው፡፡“በጋዜጠኝነት ህይወቴ ውስጥ የቀጥታ ስርጭትን ያህል የሚያስደስተኝ ነገር የለም፡፡ ያኔ ነው በእርግጥም ጋዜጠኛ
እንደሆንኩ የሚሰማኝ፡፡ ምን አለፋህ የቀጥታ ስርጭት ዘገባ ስሰራ ነፍሴ ደስ ትሰኛለች፡፡ በተቻለኝ አቅም በደንብ ተዘጋጅቼ
ለመቅረብ እሞክራለሁ፡፡ አብዛኛውን ጊዜም በስኬት ተወጥቸዋለሁ፡፡” ይላል አሸብር ጌትነት፡፡
ጥቂት ዓመታት ከሚዲያ ውጭ
ለአስራ
አንድ አመታት በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ያገለገለው አሸብር ጌትነት ላለፉት ሶስት አመታት በኢፌዴሪ ፕሬዝደንት ጽ/ቤት ቃል አቀባይ
በመሆን ሰርቷል፡፡ በእነዚህ አመታት የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ማሽን እንዴት እንደሚሰራ በቅርበት ለማየት እድሉን ከማግኘቱም በላይ
“ሙያ ፤ብስለትና አርቆ አስተዋይነት የዲፕሎማሲ የጀርባ አጥንት መሆናቸውን በፕሬዚደንት ሙላቱ ተሾመና በፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ
ዘውዴ አይቻለሁ” ይላል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ጉዞ ውስጥ የመጀመሪያ ተሰላፊ በሆነው ኢስት አፍሪካን
ሆልዲንግ ኩባንያ ውስጥ እየሰራ ይገኛል፡፡
ጋዜጠኝነት
ክፉ ነገሩ የልክፍት ያህል ነው፡፡ምንም ቢርቁት አይተውም፡፡አሸብርም ከዚህ አላመለጠም፡፡ከጥቂት ሳምንታት በፊት ከስራ አጋሮቹ
ጋር በመሆን ብሉ 24 በሚል የሚታወቀውንና በተለያዩ የሀገር ውስጥና የውጭ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩረውን የማህበራዊ ሚዲያ
ቻናል አቋቁሟል፡፡
ስለ አሸብር
ጌትነት የተሰጡ አስተያየቶች
ከ10
አመት በፊት በኢቲቪ ዜና ክፍል የአሸብር አለቃ ነበርኩ፡፡ አሸብር በቀዳሚነት የማነሳለት ጠንካራ ጎኑ ፈጣን ነው፡፡ ለዜና ደግሞ እንደ አሸብር አይነት ፈጣን ሰው የግድ ያስፈልገን
ነበር፡፡ አሸብር የተሰጠውን ስራ ኤዲተሩ በሰጠው አቅጣጫ መሰረት ጥንቅቅ አድርጎ ይሰራል፡፡ ከእርሱ ጋር መስራት ምቾት ይሰጠኝ
ነበር፡፡ አሸብር ሲጀምር ሪፖርተር ነበር ፡፡ ነገር ግን ፈጣንና ቶሎ ስራ ለመልመድ የቻለ ስለነበር በአጭር ጊዜ ውስጥ ነበር ያደገው፡፡
11 አመት ሰርቶ ሲለቅ የዜና ክፍል ዳይሬክተር ነበር፡፡ አሸብር
ጋር መጨቃጨቅ የለም፡፡ የሚሰራውን ስራ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ አሁን ላለበት የስኬት ደረጃ የበቃውም በኢቲቪ ጥሩ ትጋት ስላሳየ ነው፡፡
አሸብር ጥሩ ቦታ ደርሶ ስመለከተው በጣም እኮራለሁ፡፡ የእኔ አስተዋጽኦ እርሱ ጋር ያለ በመሆኑ በዚያ አቅም ተጠቅሞ ሀገሩን በሙያው
ሲያገለግል ከማየት በላይ ምን ደስ የሚል ነገር አለ?
ዘሩ በላይ የኢቲቪ ባልደረባ የአሸብር አለቃ የነበረ
ከ10 አመት በፊት በኢቲቪ በዜና ክፍል አሸብር ጌትነት አለቃዬ
ነበር፡፡ በእኔ እምነት አሸብር ትክክለኛ የኤዲተር ቁመና ከነበራቸው አንዱ ነው፡፡ በየጊዜው ከወቅቱ ጋር ራሳችንን እያሳደግን መሄድ
እንዳለብን ምክር ይለግሰን ነበር፡፡ የማኔጅመንት ችሎታውም በጣም የሚደንቅ ነው፡፡ ዜና እና ወቅታዊ ክፍል በአንድ ላይ ይዞ ሲሰራ
ብዙ ሰዎችን ለማብቃት ታላቅ ጥረት ያደርግ ነበር፡፡ ሌላው ፈታኝ በሆነው በውጭ ጉዞ ላይ አሸብር ትልቅ አሻራ ለማኖር ችሏል፡፡ የውጭ ጉዞ ላይ የሚሰራ ዘገባ ምን ያህል
ከባድ እንደሆነ ያወቅሁት ባለፉት 3 አመታት እኔም ስራው ውስጥ ከገባሁ በኋላ የስራውን ከባድነት በቀላሉ መረዳት ችያለሁ፡፡ እነ አሸብር በዚህ ሁኔታ ውስጥ መስራታቸው ሊያስመሰግናቸው የሚገባ ነው፡፡
ጋዜጠኛ አስማማው አየነው በኢቲቪ የዜና እና ወቅታዊ ክፍል ምክትል ዋና አዘጋጅ
መዝጊያ
፤ ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የኢንሳይክሎፒዲያ ቦርድ አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡
አሸብር
ጌትነት 1990ዎቹ ላይ ብቅ ካሉ የዜና ሰዎች አንዱ ነው፡፡ አሸብር ጌትነት በኢቲቪ ዜናዎቹ ይታወቃል፡፡ በተለይ አለም አቀፍ ስብሰባዎችን
በመዘገቡ ከተመልካች የሚጠፋ አይደለም፡፡ አሸብር ጌትነት ፣ በአለቃውም በሚያሰራቸውም ሪፖርተሮች ከላይ በተቀመጠው መልኩ ተመስክሮለታል፡፡
በተለይ ራስን ከወቅት ጋር ማዛመድ በሚለው ጉዳይ አሸብር የራሱን አሻራ አኑሯል፡፡ በተጨማሪም፣ አሸብር ከስር የሚመጡ ሪፖርተሮችን
በማብቃት ሙያውን በፕሮፌሽናሊዝም ቅኝት እንዲያዩት ለማድረግ የራሱን ጥረት አድርጓል፡፡ ነገር ግን የአሸብር ታሪክ ተሰንዷል ወይ ብለን ብንጠይቅ መልሱ አልተሰነደም ይሆናል፡፡ በኢቲቪ
የ57 አመት ታሪክ ውስጥ በርካታዎች ሰርተው እንደዋዛ ያልፋሉ፤ ያኖሩት አሻራ በውል ሳይታወቅ ከታሪክ መዝገብ ላይ ይፋቃሉ፡፡ ይህ
እንዳይሆን እኛ ይገባቸዋል ብለን ያመንባቸውን ትጉሀን እነሆ ሰንደናል፡፡ ከእነዚህ አንዱ ደግሞ አሸብር ጌትነት ነው፡፡
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ