167.ዘሩ በላይ ዘገዬ ZERU BELAY ZEGEYE

 

 


 

      ብርቱ ጋዜጠኛ

 

 

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን፣ በቅርቡ ክምችተ-አእምሮ / ኢንሳይክሎፒዲያ / በሚል ርእስ የሚድያ እና የኮሚኒኬሽን ባለሙያዎችን ታሪክ በጠንካራ ሽፋን መጽሀፍ አሳትሞ ያስመርቃል፡፡ ታሪካቸው በመጽሀፉ ውስጥ ከሚሰነድላቸው አሻራ ካኖሩ የሚድያ ሰዎች አንዱ ዘሩ በላይ ነው፡፡

 

ዘሩ በላይ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በተለይ በአማርኛ ዝግጅት ውስጥ በተለያዩ የሥራ መስኮች 30 ዓመታት በላይ አገልግሎአል፡፡ በስራው ላይ የተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች በመጓዝ የተለያዩ ዜናዎችን ፤ፕሮግራሞችንና ልዩ ዝግጅቶችን ሰርቷል፡፡

 

ትውልድ እና እድገት

 

ከአባቱ አቶ በላይ ዘገየ እና ከእናቱ / አሰገደች ካሳ መጋቢት 12 ቀን 1957 . ተወለደ፡፡

የትውልድ ቦታው በቀድሞው ወሎ ክፍለ ሀገር ፤ወረኢሉ አውራጃ ፤ጃማ ወረዳ፤ በአሁኑ አጠራር አማራ ክልል፤ ደቡብ ወሎ ዞን፤ ጃማ ወረዳ፤ አለይ ከምትባል የገጠር መንደር ነው፡፡ ከሕፃንነቱ ጀምሮ ደጎሎ ከተማ ስለአደገ ደጎሎን እንደትውልድ ቀየው አድርጌ ነው ይቆጥረዋል፡፡ ምክንያቱም የገጠሩን ሕይወት ሳያውቅ ወደ ከተማ ስለገባ ነው፡፡

በዚህ አጋጣሚ ጥቂት ስለ ትውልድ አካባቢው እንበል፡፡ ጃማ ወረዳ ቆላ፤ደጋ እና ወይናደጋን ያካተተ በአብዛኛው መሬቱ ለእርሻ የሚስማማ ነው፡፡ ስንዴ እና ጤፍ በስፋት የሚመረትበት ወረዳ ነው፡፡

ጃማ ወረዳን ከአዲስ አበባ በሁለት አቅጣጫ ማግኘት ይቻላል፡፡ የቀድሞውና ረጅሙ በደሴ በኩል 510 ኪሎ ሜትርን መጓዝ የሚጠይቅ ነው፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በዓለም ከተማ የሚያቋርጠው መንገድ ርቀቱን ወደ 264 ኪሎ ሜትር አውርዶታል፤ (አሁን አብዛኛው ጉዞ በዚህ መንገድ የሚካሄድ ነው)፡፡

 

ትምህርት

 

የልጅነት ህይወቱ እንደማንኛውም የገጠር ልጅ ማለፍ ያለበትን ሁሉ አልፏል፡፡ በቄስ ትምህርት ፊደልን መቁጠር የጀመረ ሲሆን የአባቱ የቅስና እውቀት መኖሩ ለፊደል አጣጣልና ለመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት በር ከፋች ነበር፡፡ በቄስ ትምህርት የነበረው ሂደት በአግባቡ ሳያጠናቅቅ ገና በልጅነት እድሜው አባቱ ወደ አስኮላ ትምህርት ቤት አስገባው፡፡

የሕፃንነት ኑሮውን ከአባቱ ጋር ሲገፋ አባቱ ሚስት በማግባቱ በእንጀራ እናት ለማደግ ተገደደ፡፡ በእንጀራ እናትነት ያሳደገችውና ምንጊዜም ከህሊናው የማትጠፋው የእልፌ ፈለቀ (አሁን በሕይወት የለችም፡፡ ነፍሷን ይማረው) የሚወዳት እናት ነበረች ፡፡ በልጅነቱ ኃይለኛ ባህሪይ የነበረው በመሆኑ ብዙውን ጊዜ ከእንጀራ እናቱ ጋር አይስማማም ነበር፡፡ በተለይ ከትምህርት ቤት ሲመጣ የሚሰጠው ትዕዛዝ ያበሳጨው ስለነበረ ሁል ጊዜ በመካከላቸው ጭቅጭቅ ይፈጠራል፡፡

ዘሩ 8 ክፍል ብሔራዊ ፈተና በዝግጅት ላይ ነበር፡፡ አባቱምይህንን ትምህርት ስታልፍ ወረኢሉ ነው የምትማረው፡፡ ስለዚህ በደንብ አስተምርሀለሁየሚለውን ቃላቸውን ወደ ተግባር ሳይለውጡ ከንጉሱ ባለስልጣናት ጋር በተደረገው ውጊያ የመሞታቸው  ዜና ደረሰው፡፡ የአካባቢው ሰዎች እንደነገሩ አፈር ያለበሱት የአባቱ አስከሬን በእኅቱ / ሙልየ ዘገየ ጥረት ብዙ ገንዘባቸውን አፍስሰው አስከሬኑ ካለበት ተቆፍሮ እንዲወጣ አደረጉ፡፡ ከዚያም በጀግና ሥርዓት የአካባቢው ሰው በነቂስ ወጥቶ በሽለላ እና ፉከራ በደጎሎ ከተማ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን እንደገና እንዲቀበር አድርገዋል፡፡

እንዲህም ሆኖ ግን የአንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በደጎሎ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲከታተል የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ 30 ኪሎ ሜትር በመጓዝ በወረኢሉ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምሯል፡፡ ሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና በተለያዩ ምክንያቶች ጥሩ ውጤት ሊመጣ አልቻለም፡፡

 

ወደ ሌላ አቅጣጫ

 

ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት መጠናቀቅ በኋላ ለሥራ ፍለጋ ወደ አዲስ አበባ መጣ፡፡ አዲስ አበባ እንዳሰበው ሥራ ባያገኝም ራሱን ከአካባቢው ጋር ሲያላምድ የብሄራዊ ውትድርና ይታወጃል፡፡

 

በዚህ ሳቢያ እንደልብ ሥራ ለመፈለግ መንቀሳቀስ ተገደበ፡፡ በዚህ ላይ እያለ አንድ የተስፋ ጭላንጭል ማየት ጀመረ፡፡ አንድ ቀን ሲቪሎችን በአስተዳደርና ድርጅት ሙያ በማሰልጠን ወደ ስራ እንደሚያስገባ አንድ ወታደራዊ ተቋም ማስታወቂያ ያወጣል፡፡ ይህን ማስታወቂያ በማየት ተመዘገበ፡፡ ነገሩ አቅጣጫውን ቀየረና ራሱን ወታደራዊ ማሰልጠኛ ተቋም ውስጥ አገኘው፡፡ ከስልጠና በኋላ ወታደር ሆነ፡፡ ብዙም ሳይቆይ ለመኮንንነት ሥልጠና ታጨ፡፡ ስልጠናውን ወስዶ ተመረቀ፡፡ በተለያዩ የትግራይ ቦታዎች በመኮንንነት ሰርቷል፡፡ ከመኮንንነት በኋላም ወደ ጋዜጠኝነት እንዲቀላቀል እድል አገኘ፡፡

 

 

የጋዜጠኝነት ህይወት

 

‹‹…..ጋዜጠኛ የመሆን ህልም ባይኖረኝም ባገኘሁት እድል በመጠቀም ሙያውን ብየ ሀምሌ 1 ቀን 1983 . ጀመርኩ፡፡ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፡፡ ሥራ ስጀምር በአማርኛ ዜና ክፍል ሲሆን በሪፖርተርነት በርካታ የዜና ሥራዎችን ሸፍኛለሁ፡፡

የጋዜጠኝነት ህይዎት ከአዲስ ጉዳይ ጋር የሚያላምድ ከመሆኑም ባሻገር የሀገርን ገፅታ እንድታውቅና የህብረተሰቡን የአኗኗር ዘይቤ በአግባቡ ለመረዳት የሚያስችል በመሆኑ እኔም ከዚህ ዘርፍ ተጠቅሜአለሁ ለማለት እችላለሁ፡፡›› ሲል ዘሩ የሚድያ አጀማመሩ በእንዴት ባለ መልኩ እንደሆነ ይናገራል፡፡

 

 

ዜና ክፍል ገና ሲጀምር የነበረው የአሰራር ድባብ ቢያደናግውም ከነባሮቹ በመማር ሥራውን ጥንቅቅ አድርጎ ለመስራት ግን ብዙ ጥረት ያደርግ ነበር፡፡ በሪፖርተርነት የሥራ ጊዜው ሁሉንም ዓይነት ዘገባዎችን የሚሠራ ሲሆን ከፌደራል መንግስቱ እስከ ክልሎች ድረስ ብሎም እስከ ውጭ ድረስ ለመጓዝ ግድ ይላል፡፡

 

ዜና ሁልጊዜ አዲስ ነው ፡፡ በዚያው ልክም ጋዜጠኛው አዳዲስ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩር ይረዳዋል፡፡ ሌላው መጥፎ ነገሩ ግን ዜና የሁሉንም ትኩረት መሳቡ ነው፡፡ ከቀበሌ አስከ ጠቅላይ ሚኒስትሩ /ቤት ድረስ ዜና ትኩረት ያገኛል፡፡ በዚህ ሳቢያ ትንሽ ስህተት ቢኖር እንኳ የመታለፉ እድሉ ለጋዜጠኛው በጣም ጠባብ ነው፡፡

አዳዲስ ሀሳቦችን ማምጣት የዘሩ ፍላጎቱ  በመሆኑ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በፕሮግራም ክፍል የሠራቸው በርካታ ፕሮግራሞች  አንዳንዶቹን እንደሚከተለው ዘሩ ያቀርናቸዋል፡፡

 

‹‹….በሀገራችን ያለውን የመንገድ ትራፊክ አደ ለመቀነስና የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት የሚረዳጉዞውየተሰኘው ፕሮግራም እኔው ፈጥሬው ለአየር ያበቃሁት ፕሮግራም ነበር፡፡ በዚህ ፕሮግራም አሽከርካሪዎች እግረኞች በአጠቃላይ መንገድ ተጠቃሚዎች እንዲማሩበት ተገርጓል፡፡ ኋላ ላይ በተለያዩ ሰንካላ ምክንያቶች እንዲቆም ተደርጓል፡፡ (ዝርዝሩን በቅርቡ ባሳተምኩት ልደነዘ ስለት መጸሀፍ ላይ ማግኘት ይቻላል)፡፡

ሌላው በእኔ ተቀርፆ ለአየር የበቃውንና የጠመልካችን ቀልብ ከገዙ ፕሮግራሞች ውስጥየንግድ ሥራ ተሰጥኦ ውድድርነው፡፡ ይህ ፕሮግራም ሥራ ፈጣሪ ማህበረሰብን ለመፍጠርና የአካባቢያቸውን ችግር በማየት ችግር ፈቺ የሆኑ የፈጠራ ሥራዎችን የማበረታታት ዓላማ ነበረው፡፡ በህዝብ ተወዳጅ ሲሆን ሁሉም በአካባቢው ላይ እንዲያተኩርና ራሱን በሥራ ፈጠራ ጥበብ ላይ እንዲንቀሳቀስ መንገድ አሳይቶ ነበር፡፡ ይህም እንዲሁ ዳር ሳየርደርስ በልጅነቱ ተቀጨ ፕሮግራም ነው፡፡

በዘገባ ሥራዎቼ 1997 . ጉዳይ አልዘነጋውም ፡፡ ምርጫ 97 ከተጠናቀቀ በኋላ እና ከድምፅ ቆጠራ በኋላ በተነሳው አመፅ አዲስ አበባ የነበረችበት ሁኔታን አሁን ድረስ አስታውሰዋለሁ፡፡ መንገዶች ፀጥ ረጭ ብለው ተሸከርካሪዎች ሳይንፈላሰሱባቸው ሲታዩ ከተማዋ እጅግ አደጋ ላይ እንዳለች ያሳይ ነበር፡፡ እንደ እኔ ስራ ላይ የዋለ ሰው ብቻ ነበር በመንገድ ላይ በእግሩ ሲጓዝ የሚታየው፡፡›› ብሎ ነበር ዘሩ፡፡

 

 

ሙያን ማዳበር

 

 ሙያን ማዳበርን በተመለከተ ዘሩ እንዲህ ይላል..

 

‹‹……የጋዜጠኝነት ሙያ ከልምድ ባሻገር በስልጠና መደገፉ ይበልጥ እንዲዳብር ያደርጋል፡፡ በዚህ መነሻነትም እኔም ሙያውን በስልጠና ለማሳደግ ባለኝ ፍላጎት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ትምህርት በተለይ በቴሌቪዥን ዘርፍ የመጀመሪያ ዲግሪየን በጥሩ ውጤት አጠናቅቄአለሁ፡፡

 

ከዚህ በተጨማሪም መንግስት አቋቁሞት በነበረው መገናኛ ብዙሃን ማሰልጠኛ ኢኒስቲትዩት በቴሌቪዥን ጋዜጠኝነት በዲፕሎም የተመረቅሁ ሲሆን በሀገር ውስጥና በውጭ ተለያዩ አጫጭር ኮርሶችን ወስጃለሁ፡፡›› ብሎ ነበር፡፡

 

        የትዳር ሁኔታ

 

የልጅነት ፍቅረኛዬን ፀሀይነሽ አጥናፍን በማግባት የሁለት ልጆች አባት ነኝ፡፡ የዳዊት ዘሩ እና የዳግማዊት ዘሩ አባት፡፡ በትዳሬና በኑሮዬ ደስተኛ ነኝ፡፡

በእረፍት ቀኔ ከቤተሰቤ ጋር ማሳለፍን ስመርጥ መፀሀፍ ማንበብና ወቅታዊ ሁኔታዎችን መከታተል ቅድሚያ እሰጣለሁ፡፡

 

 

 

አዲስ መጽሀፍ

 

መጽሀፍ የመፃፍ ህልም ስለነበረኝ ባለኝ ጊዜ በመጠቀም የራሴን የህይወት ተሞክሮያልደነዘ ስለትብ? በመፃፍ ጥር 14 ቀን 2014 . አስመርቄ ለአንባቢዎች ገበያ ላይ እንዲውል አድርጌአለሁ፡፡

መፀሀፉ በተለይ ለጀማሪ ጋዜጠኞች እንደ መነሻ የሚሆናቸው ሲሆን በስራቸው ላይ የሚያጋጥማቸውን ችግር ለመፍታት የተለያዩ ዘደዎችን እንዲጠቀሙ መንገድ ያሳያል ብየ እገምታለሁ፡፡

 

 መዝጊያ፤ ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ የኢንሳይክሎፒዲያ ቦርደ አባላት አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡

 

 ዘሩ በላይ በጋዜጠኝነት ላለፉት 30 አመታት ያገለገለ ትጉህ ባለሙያ ነው፡፡ ዘሩ በተለይ በኢትዮጵያ ቲቪ የዜና ክፍል ውስጥ የራሱን አሻራ ለማኖር የቻለ የሚድያ ሰው ነው፡፡ በ1980ዎቹ ና በ1990ዎቹ መጨረሻ  የዘሩ በላይ ዜናዎችን በኢቲቭ መመልከት የተለመደ ነበር፡፡ ዘሩ ከከተማ ወጥቶ መስራት ደስ ያሰኘዋል፡፡ በዚህም ብዙ መረጃ እንደሚያገኝ ያስባል፡፡ ዘሩ ኢቲቪ በነበረበት ዘመን በርካታ የማይዘነጉ ባለሙያዎች አሉ፡፡ እርሱ ከእነዚህ አንዱ ነው፡፡   

 













 

 

 

 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች