162.ነብዩ ግርማ ስጦታው - Nebiyu Girma Sitotaw

 

 

 

 

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን፣ በቅርቡ መዝገበ-አእምሮ / ኢንሳይክሎፒዲያ / በሚል ርእስ የሚድያ እና የኮሚኒኬሽን ባለሙያዎችን ታሪክ በጠንካራ ሽፋን መጽሀፍ አሳትሞ ያስመርቃል፡፡ ታሪካቸው በመጽሀፉ ውስጥ ከሚሰነድላቸው አሻራ ካኖሩ የሚድያ ሰዎች አንዱ ነቢዩ ግርማ ስጦታው ነው፡፡

 

ከ1990ዎቹ ወዲህ በሬድዮ ጋዜጠኝነት ዘርፍ ላይ ከተሠማሩ ስመ-ጥር ጋዜጠኞች መካከል ተጠቃሽ ነው - ነብዩ ግርማ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህም በሕትመቱ የሚዲያ ዘርፍ ላይ ተሰማርቶ የተሻለ አማራጭ በመሆን የሙያውን ውጤት በተሻለ ከፍታ ለአንባቢያን በማቅረብ ላይ ይገኛል።

 

ልደትና ልጅነት

 

ነብዩ ግርማ የተወለደው በምሥራቅ ሐረርጌዋ ደደር ከተማ ነው፤ መስከረም 21ቀን 1964 ዓ.ም.። አባቱ መቶ አለቃ ግርማ ስጦታው፣ እናቱ ደግሞ ወይዘሮ ጎሳዬ ቸርነት ይባላሉ። ቤተሰቦቹ የመኖሪያ አድራሻቸውን በመቀየራቸው ምክንያት ልጅነቱን እስከ ስድስተኛ ዓመት ዕድሜው ድረስ በጂጅጋ ከተማ ያሳለፈ ሲሆን፣ በ1969 ዓ.ም. ወራሪው የዚያድ ባሬ ጦር ያካሄደው ወረራ በፈጠረው ቀውስ ሰበብ ከልጅነት እስከ እስከ ዕውቀቱ ድረስ የማንነቱ መሠረት ወደ ሆነችው አዲስ አበባ ከመላው ቤተሰቡ ጋር ከተመ። የቤታቸው ቅጥር ያረፈበት “ጌጃ ሰፈር”ን ጨምሮ "ልደታ"፣ "አብነት"፣ "ሰባተኛ"፣ "አውቶብስ ተራ" እና ዙሪያ ገባውም የትዝታው ድር የተዳወረበት፣ ሕልሙንም የወጠነበት ለመሆን በቁ። "ጨፌ" ሜዳ ላይ ኳስን ከመመልከት አንስቶ በ"ፒቲ ጎል" እስከ መጫወት፣ በ"ቡሄ" ላይም "ሆያ ሆዬ"ን ጨፍሮ  የ"ሙልሙል" እና የገንዘብ ስጦታ በመቀበል የልጅነት ነፍሱን አስደስቷል።

 

አባቱ መቶ አለቃ ግርማ ስጦታው ከምሥራቅ ግንባር እስከ ሰሜን ኢትዮጵያ (አሥመራና ትግራይ) ድረስ ተንቀሳቅሰው፣ ቁርና ሐሩር ሳይበግራቸው፣ በቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ ሆነው እናት ሀገራቸውን ለመታደግ ሲማስኑ በቀኝ እጃቸው ላይ ጉዳት ደርሶባቸው ከሠራዊቱ እስኪሰናበቱ ድረስ የቀጠለ ነበር።

 

የትምህርት ሕይወት

 

“የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን ከ1ኛ እስከ 6ኛ ድረስ የተማርኩት በ‘እናት ኢትዮጵያ’ ትምህርት ቤት ሲሆን 7ኛ እና 8ኛ ክፍልን ደግሞ የተማርኩት በ‘ተስፋ ኮከብ’ ትምህርት ቤት ነው።” ይላል ነብዩ፤ ስለ ትምህርት ሕይወቱ ጅማሮ ሲያወሳ። በትምህርቱም ጎበዝ ከሚባሉት ተርታ የሚሰለፍ በመሆኑም የመጀመሪያ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና (ሚኒስትሪ)ን በጥሩ ውጤት አልፎ “አዲስ ከተማ” ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመደበ። ለአራት ዓመታት በ“አዲስ ከተማ” ከነበረው የትምህርት ቆይታ በኋላም በ“ማትሪክ” ውጤቱ መሠረት “Foreign Language and Literature”ን ለማጥናት ሻንጣውን ሸካክፎ ወደ “ባህር ዳር መምህራን ኮሌጅ” አቀና። በዲፕሎማ ተመርቆም ወደ ሥራው ዓለም ተሰማራ። ይሁን እንጂ ከሥራው ጎን ለጎን በትምህርት ራሱን ማሻሻል እንደሚገባው የሚያምነው ነብዩ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲም በ“Foreign Language and Literature”  በመጀመሪያ ዲግሪ የተመረቀ ሲሆን “Journalism and Communication”ንም የድህረ-ምረቃ ትምህርት ተምሯል።

 

“ሰውን ሰው ያደረገው ሥራ ነው!”

 

 “በላብና በወዝህ ጥረህ፣ ግረህ ብላ” በሚለው መለኮታዊ ፍርድ ሰበብም ይሁን “ሰውን ሰው ያደረገው ሥራ ነው፤” በሚለው ኮሙኒስታዊ ብያኔ ምክንያት፣ ዘራሰብ በሙሉ ‘ሠርቶ መብላት’ን፣ ‘ለፍቶ ማደር’ን ‘የሕልውናዬ ምሰሶ ነው’፣ ብሎ ካመነ፣ አምኖም መተግበር ከጀመረ አእላፍ ዘመናት አልፈዋል። እነሆ ነብዩም ሰው ነውና እንደ ሰው ይህን ሰብዓዊ መርህ አንግቦ ወደ ሥራ ተሰማራ። ያውም ምኔም ወደማይሞት የተባረከ ሥራ !

 

በ1982 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ 194 ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኘውና  “ዝዋይ”ን አልፈው፣ በ“ቡልቡላ” ታጥፈው፣ “አላጌ” የሚባል አካባቢ ወደሚያገኙት “የአብዮታዊት ኢትዮጵያ ሕፃናት አምባ” መረሸ፤  በመምህርነት ሊያገለግል። ለስምንት ዓመታት ያህልም በአምባው ትምህርት ቤት ውስጥ የእንግሊዝኛ ቋንቋን ሲያስተምር ቆየ። ሀገር ያቀበለችውን የዕውቀት ብርሃን በፈንታው ለብዙ ዜጎች በማስተላለፍ ያለማወቅን ዳፍንት ይገፉ ዘንድ አደረገ። ከመደበኛ የማስተማር ኃላፊነቱ ባሻገርም የተጓዳኝ ትምህርት አካል የሆነውን “የሚኒ ሚዲያ” ክበብን ሲያስተባብርም ቆይቷል። ራሱ ጽሑፍ አዘጋጅቶ በንባብ ያቀርብ ስለነበርም ዛሬም ድረስ እየሠራው ወደሚገኝበት የጋዜጠኝነት ሙያ እንዲሳብ ሆነ። በየጊዜው ይወጡ የነበሩ ማስታወቂያዎችን በመከታተልም በጊዜው ከተመሠረተ ሁለት ዓመታት ወዳስቆጠረው "ሬድዮ ፋና" በጋዜጠኝነት ተቀጥሮ አዲስ አበባ መጣ።

 

ለአራት ዓመታት ያህል በሬዲዮ ፋና በነበረው ቆይታ በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅነትን ያተረፉለት ፕሮግራሞችን አዘጋጅቶ በማቅረብ እውቅናን አተረፈ። “የአርብ ምሽት መዝናኛ ፕሮግራም”፣ “የጥበባት ዓለም”፣ “አፍላነት”፣ “ከእንስሳት ዓለም” ዝግጅቶች ለምሳሌ ያህል የሚጠቀሱለት ናቸው።

 

በ1994 ዓ.ም. "ሬድዮ ፋና"ን ከለቀቀ በኋላ ተመልሶ የመምህርነት ሥራውን በ“Gibson” እና “Ethio-Parents” ትምህርት ቤቶች ሲሠራ ቆየ። ይሁን እንጂ ከሚዲያው ላለመራቅ ካለው መሻት የተነሳም ለውሱን ጊዜያትም ቢሆን በ“አዲስ አድማስ” እና “Ethiopian Herald” ጋዜጦች ላይ መጣጥፎችን ያስነብብ ነበር።

 

በ2000 ዓ.ም.  የናንተው ሬድዮ “ሸገር ኤፍ ኤም 102.1” ምሥረታን ተከትሎም ከስድስት ዓመታት መጥፋት በኋላ በሚዲያው አምባ ላይ፣ ከጣቢያው መሥራች ጋዜጠኞች መካከል አንዱ  ሆኖ ተከሰተ። አዲስ መንገድና የራሱን ቀለም ይዞ ከመጣው ተወዳጅ የጣቢያው ዜና አቀራረብ በኩል ዳግም ከሚወዱት አድማጮቹ ጋር ተገናኘ። “የታላቋ ኢትዮጵያ ማለዳ”፣ “አንዳንድ ነገሮች”፣ “ሸገር ካፌ”፣ “ጨዋታ”፣ “ሽርሽር በሸገር”፣ “ስንክሳር” አዘጋጅቶ ከሚያቀርባቸው ፕሮግራሞች መካከል ነበሩ። በ“ሸገር” ውስጥ ‘የመጀመሪያው የዜና አንከር’ ነብዩ እንደነበርም ይታወቃል፡፡ 

 

በ2004 ዓ.ም. ለአራት ዓመታት ከቆየበት የ“ሸገር ሬድዮ” ከወጣ በኋላ ፊቱን ያዞረው የራሱን የግል ድርጅት ወደ ማቋቋሙ ነበር። “ብርቧክስ ሕትመትና ማስታወቂያ …” የተሰኘ ድርጅት መሥርቶም በ“FM Addis 97.1” ላይ “መናፈሻ” የተሰኘ ተወዳጅ የመዝናኛና የመረጃ ሰጪ ፕሮግራም ሬድዮ ፋና ሳለ የሥራ ባልደረቦቹ ከነበሩት ዮናስ አብርሃምና እማዋይሽ ዘውዱ ጋር በመሆን ማቅረብ ጀመረ። የብዙዎችን ጆሮ መቆጣጠር የቻለና በጉጉት የሚጠበቅ ፕሮግራም ሆኖም ለሦስት ዓመታት ያህል (እስከ 2007 ዓ.ም. ድረስ) ዘለቀ።

 

ከ2007 ዓ.ም. እስከ አሁን ድረስ ደግሞ እናት ጣቢያው በሆነው “ሸገር ሬድዮ” ላይ “ወይ አዲስ አበባ” የተሰኘ ‘የቁምነገር፣ የመረጃና የመዝናኛ’ ፕሮግራም እያዘጋጀ በማቅረብ ላይ ይገኛል።

“ወይ አዲስ አበባ” የሬድዮ ፕሮግራም ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ለሁለት ዓመታት ያህል በየሳምንቱ ሰኞና ማክሰኞ ከምሽቱ 3:00 እስከ 5:00 ሰዓት ድረስ ሲተላለፍ የቆየ ሲሆን ከ2009 ዓ.ም.  ጀምሮ እስካሁን ድረስ ደግሞ ዘወትር ሰኞ ከ10:00 - 12:00 ሰዓት ፣ ማክሰኞ ከ8:00 - 9:00 ሰዓት ላይ ለአድማጮች እየቀረበ ይገኛል።

 

ነብዩ ስለ ፕሮግራሙ አስተያየቱን ሲሰጥ “‘ወይ አዲስ አበባ’ የሬድዮ ፕሮግራም ከሌሎች የተለየ መንገድን ተከትሏል። ቁም ነገርን ከመረጃና መዝናኛ ጋር አዛንቆ ለአድማጮች ከማቅረቡ ባሻገር ከአንድ ሺህ በላይ በዝግጅት ክፍሉ የተሰናዱ ፕሮግራሞችን አቀናብሯል (Produce) አድርጓል። ከምንም በላይ ለአድማጮቻችን ካለን አክብሮት የተነሳም ያልተዳሰሱ ጉዳዮችን ከምንጩ ለማቅረብ ጥረት እናደርጋለን፣” ይላል።

 

“አዲሳውያን መልቲ ሚዲያና ኤቨንት” የተሰኘ እህት ድርጅት በማቋቋምም፣ ከ2013 ዓ.ም. ወርሀ-መስከረም ጀምሮ ደግሞ “ወይ አዲስ አበባ” መጽሔትን በአሳታሚነትና በማኔጂንግ ኤዲተርነት ለንባብ ያበቃው ነብዩ ግርማ በሕትመቱ ሚዲያ ዘርፍ ላይም የተሻለ አማራጭ ለመሆን በመሥራት ላይ መሆኑን ይናገራል። “በእውነት ለዕውቀት እንሠራለን” መርሃችን ነው፤ ብዙዎቹን የኅትመት ውጤቶቻችንን ብንቃኝ  ወይ እውነት አልያም ዕውቀት ይጎድላቸዋል። ዜናዊ ባህሪያቸውም ያደላል። ይህም በወቅት እንዲገደቡ ያደርጋቸዋል። በመሆኑም እኛ ዕውቀትን ከእውነት ጋር አስታርቀን፣ መጽሔታችን በማንኛውም ጊዜ ተነባቢ ይሆን ዘንድ ዘመን ተሻጋሪ ይዘት ያላቸው ጽሑፎችን ነው የምናስተናግደው።” በማለት ሙያዊ ደረጃቸውን የጠበቁ ሥራዎችን ለአንባቢያኑ ለማቅረብ ያለውን ቁርጠኝነት ይገልጻል። ጥሩ ምላሽ እያገኘበት መሆኑንም ይናገራል። ማስታወቂያዎቹን ሲሠራም እንዲሁ ጥራትና ደረጃቸውን የጠበቁ፣ የማኅበረሰቡን ልማዶች (Norms) እና የሀገሪቱን ሕግጋት የጠበቁ አድርጎ መሆኑንም ያብራራል።

 

በተጨማሪም ሁለገቡ ነብዩ፣ በ“ጋለሪያ ቶሞካ” የቀረቡ 32 የሥዕል ትርዒቶችንና የሥዕል ካታሎጎችን በእርሱ ማኔጂንግ ዳይሬክተርነትና በታዋቂው ሠዓሊ እሸቱ ጥሩነህ ‘አርት ዳይሬክተርነት’ ለ‘ቶሞካ’ እድምተኞች እይታ እንዲቀርብ አድርጓል። በዚህም ብዙ አንጋፋ እና ወጣት ሠዓሊያን አንዳች ወጪ ሳያወጡ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። ይህ ሥራ “ሥዕልን በባህላችን እጅግ ከሚወደደውና የተለየ ቦታ ከሚሰጠው ቡና ጋር አንድ ላይ በማቅረብ ኅብረተሰባችን ከሥዕል ጋር ያለው ቅርርቦሽና ዕውቀት ጠንካራ እንዲሆን የሚያደርግ በመሆኑ” የሚወደው እንደሆነም ይናገራል።

 

ሠርቶ የማሠራት መንገዱ

 

በሥራ በኩል ለቀደምት ባለሙያዎች አክብሮት የሚሰጠውን ያህል ለአዳዲስና ተስፋ ያላቸው ወጣቶች ዕድል በመስጠት ያምናል። በዚህም ተጠቅመው ለጥሩ ውጤት የበቁም መኖራቸው ይነገራል። ሥራዎች በተቻለ መጠን በፍጽምና ቢፈፀሙ የሚወደውን ያህል ሲጓተቱና ተገቢ ያልሆኑ ጥፋቶች ሲፈጸሙ ይቆጣል። አብረውት የሠሩ ሲናገሩ “‘Over Ambitious’ እስኪያስመስሉት ድረስ የሃሳብ ሀብት እና አዳዲስ ዕይታዎችን በማመንጨት በኩል የታደለ ነው” ይሉታል።

 

የወደ ፊት ሕልሙ

 

በብሮድካስትም ይሁን በሕትመት ሚዲያው ዘርፍ ተጠቃሽ የሆነና ትልቅ ሀገርን የሚመጥን፣ በተቻለ አቅምም በሌሎች የሀገራችንና የውጭ ቋንቋዎች ተደራሽ መሆን የሚችል ተቋም መመሥረት ሕልም ያለው ነብዩ፣ የተለያዩ ኩነቶችን (event) እሴት ጨማሪ (Value Add) በሚያደርግ መልኩ የማዘጋጀት ሀሳብ እንዳለው ይናገራል።

 

ቤተሰባዊ ሁኔታው

 

ነብዩ ባለ ትዳርና የሦስት ልጆች አባት ነው። ለቤተሰቡ እጅጉን ስሱ ነው። የቤቱ ታላቅ ልጅ ዳሪክ ነብዩ ይባላል። መንትያ ሴት ልጆቹ ደግሞ በእምነት እና በአምላክ ነብዩ ይሰኛሉ። ባለቤቱ ወ/ሮ መዓዛ ይልማ ከቤተሰባዊ ኃላፊነቷ በተጨማሪ የድርጅቱ ማርኬቲንግ ኃላፊነትን ደርባ በ“ጀርባ አጥንትነት” የምታከናውን ብርቱ ሴት መሆኗንም ይመሰክራል። በዚህም ምክንያት “My Premier” በሚል ቅጽል ስም እንደሚገልፃትም ይናገራል። በሥራ ካልተጨናነቀ በስተቀር በሳምንት ውስጥ ሁለት ሦስት ቀናት ወላጆቹን ካልጠየቀ አይሆንለትም። በበዓልም ይሁን በአዘቦት አብሯቸው ማዕድ የመጋራት ልማድም አለው።

 

“በጥቅሉ መላው ቤተሰቤና በዙሪያዬ ያሉ ወዳጆቼ ሕልሜን ለማሳካት በማደርገው ጉዞ ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስዱ በመሆኑ ሁልጊዜም ምስጋናዬ አይለያቸውም” ይላል።

 

“የምኖርለት ዓላማ”

 

ነብዩ ስለሚኖርለት ዓላማ ሲናገር፣ “በሀገራችንም ይሁን በመላው ዓለም የምናያቸው ስልጣኔዎችም ይሁኑ መንፈሳዊ ብልፅግናዎች የትውልድ ቅብብሎሽ ውጤት መሆናቸው እሙን ነው። ትናንት ለዛሬ መሠረት እንደሆነው ሁሉ፣ ዛሬ ከዛሬነቱ ባሻገር ነገን መተለሚያ ሊሆን ይገባዋል። አንዱ ላይ ብቻ ተቸክሎ መቅረት አዋጭ አይደለምና” በማለት ገልፆ “ዕቅዶቼም ሆኑ ተግባራቴ ትናንትን ከዛሬና ከነገ ጋር በሚያስተሳስር ሁኔታ የሚወጠኑ ናቸው” ይላል። “ውሸት” በጣም ከሚጠላው ነገር ዋነኛው እንደሆነና ነገሮችን በአንድ ወገን እውነትና እምነት መበየን እንደማይሆንለት ይናገራል።

 

የመዝጊያ ሀሳብ ፤ ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የኢንሳይክሎፒዲያ ቦርድ አባላት አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡

 

 ነቢዩ ግርማ ባለፉት 21 አመታት በሚድያው ዘርፍ አንድ አሻራ ለማስቀመጥ ይተጉ ከነበሩ የኤሌክትሮኒክስ ባለሙያዎች አንዱ ነው፡፡ በተቻለው አቅም አንድ ቁምነገር ት ቶ ለማለፍ ሲሞክር የነበረ ባለሙያ ነው፡፡ ነቢዩ በፋና የጥበባት አለም እና በመሳሰሉ ተወዳጅ የሬድዮ ፕሮግራሞች ሲሰራ የኖረ በቀላሉ የሚታወስ ለዛ ባለው ድምጹ ጎልቶ የወጣ በሳል ባለሙያ ነው፡፡  ሸገር ሬድዮ በ2000 መስከረም ወር ላይ ሲጀመር ከመስራች ጋዜጠኞች አንዱ ነበር፡፡ ከያኔ ጀምሮ እስከአሁን የቀን የሌት ልፋቱን አላቋረጠም፡፡ ወይ አዲስ አበባ የራሱ የአየር ሰአት ሲሆን ብዙ ማህበራዊ ጉዳዮችንም ያነሳበታል፡፡ ፕሮፌሽናሊዝምን በተከተለ መልኩ እየሰራ የሚገኘው ነቢዩ ከ2 አመት ወዲህ ወደ ህትመት ሚድያው በመቀላቀል ወይ አዲስ አበባን በጥራትና ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እየሰራ ይገኛል፡፡ በዚህም በህትመትም ሆነ በኤሌክትሮኒክስ ሚድያ ክህሎት እንዳለው መገንዘብ ይቻላል፡፡ የሚድያ  ሰዎች ስለ ራሳቸው በማይናገሩበት በዚህ ጊዜ የእነ ነቢዩ አይነት ባለሙያዎች ብዙ ልምድ የማካፈል ሃላፊነት አለባቸው፡፡ ነቢዩ 1990ዎቹን በመወከል በሙያው የራሱን ቀለም ለመፍጠር በመሞከሩ የመዝገበ -አእምሮ ስብስብ ውስጥ ታሪኩ ሊካተት ችሏል፡፡ እኛም እንዲህ አይነት ታሪክ ያለው ሰው ለኢትዮጵያ ሚድያ ጠቃሚ ስለሆነ ያለፈበትን ለአዲሱ ትውልድ ያካፍል ስንል ሀሳባችንን እንሰነዝራለን፡፡ 











 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች