149.ሻምበል አፈወርቅ ዮሀንስ -ህይወታቸው ካለፈ ዛሬ 42
አመት ሆነ
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን፣ በቅርቡ ክምችተ-አእምሮ / ኢንሳይክሎፒዲያ / በሚል ርእስ የሚድያ እና የኮሚኒኬሽን
ባለሙያዎችን ታሪክ በጠንካራ ሽፋን መጽሀፍ አሳትሞ ያስመርቃል፡፡ ታሪካቸው በመጽሀፉ ውስጥ ከሚሰነድላቸው አሻራ ካኖሩ የሚድያና
የጥበብ ሰዎች አንዱ ሻምበል አፈወርቅ ዮሀንስ ናቸው፡፡ ሻምበል አፈወርቅ ዮሀንስ በጋዜጠኝነትና
በደራሲነት እውቅና ያተረፉ በ1972 የካቲት 25 ህይወታቸው ያለፈ ታላቅ ሰው ናቸው፡፡ ዛሬ የካቲት 25 2014 ይህ ታሪክ በተወዳጅ
ሚድያ ድረ,ገጽ ላይ ሲወጣ 42ኛው የሻምበል አፈወርቅ ዮሀንስ ሙት አመት ይታሰባል፡፡ ጋዜጠኛ መላኩ ደምሴ ሻምበል አፈወርቅን ከዚህ በታች እንደተከተበው ሰንዶታል፡፡
እንደ መነሻ
ወፍ ሲጮህ ዶሮ ንጋትን ሲያውጅ ከእንቅልፌ ነቃሁ፡፡ ፊቴ በደሰታ ተሞልቶ ነው የተነሳሁት ምክንያቱም ዘወትር እሁድ ማለዳ ስለ ትላንት፣ ስለ ታሪክ የምሰማበት ቀን ነው፡፡ በቅዱስ ቀን በየሳምንቱ ታሪክ እሰማለሁ፡፡ ሁሌም ታሪክ የሚነግሩኝ ግቢያችን ውስጥ ያሉ አዛውንት ናቸው፡፡ ዛሬ ስለ አንድ ጀግና ኢትዮጵያዊ ሊነግሩኝ እንደፈለጉ ፊታቸው ያስታውቅ ነበር፡፡የማለዳዋ ጸሐይ ደስ ትላለች ሰፈሩን ብርሃን ሞልታዋለች፡፡ ደጃፋችን ላይ ካለ አንድ ዋርካ ስር ተቀምጠው መጽሐፍ ሲያነቡ አየኋቸውና ወደ እሳቸው አመራሁ፡፡ ጉልበታቸውን ስሜ ግንባሬን ስመውኝ ተቀመጥኩ፡፡
ደህና እደሩ አባባ
እግዚአብሄር ይመስገን እንዴት አደርክ ልጄ
ደህና ነኝ! ጠዋት እነግርሃለሁ
ያሉኝን ታሪክ ለመስማት ነው የመጣሁት አባባ፡፡
እሺ ልጄ እነግርሃለሁ፡፡
ታሪክን ማወቅ መልካም ነው፡፡ ስለ ትላንት አባቶቻችን ጀግንነትና ብርታት ማወቅና መረዳት ያስፈልጋል፡፡
ዛሬ የምነግርህ ስለ
ብርቱ ጋዜጠኛው እና ስለ ግጥምና ዜማ ደራሲው ስለ አፈወርቅ ዮሐንስ ነው፡፡ በኋላ ላይ ሻምበል ሆኗል፡፡ እንዴት ይሄንን የሻምበልነት
ማዕረግ እንዳገኘ እነግርሃለሁ፡፡
ታሪኩ አንድ ሲል
በ1919 ዓ/ም ግንቦት
13 ቀን ፍል ውሃ አካባቢ አንድ ህፃን ተወለደ፡፡ ኢትዮጵያም በዚህ ቀን ብርቱ ሰው አገኘች፡፡ ያ ብርቱ ሰው ግንቦት 13 የተወለደው
ሻምበል አፈወርቅ ዩሐንስ ነበር፡፡ አባታቸው አቶ ዩሐንስ ገ/ማርያም ሲባሉ እናታቸው ደግሞ ወ/ሮ ቦጋለች ወልዴ ይባላሉ፡፡
የማወቅና የመስራት ፍላጎታቸው
ከልጅነታቸው ጀምሮ አብሯቸው ነበር፡፡ በኋላም የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን
በፈረንሳይ ሚሲዮን፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በስዊዲሽ ሚስዮን ትምህርት ቤት አጠናቀዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በ1937
በዚያን ጊዜ ክቡር ዘበኛ ተብሎ ይጠራ በነበረው አሁን ደግሞ ማዕከላዊ ዕዝ ተብሎ በሚጠራው ገብተው በተግባረ- ዕድ ክፍል ተመድበው
የሙያ ትምህርት አጥንተዋል፡፡ ስራ እና ትምህርት ላይ እንዴት አይነት ትጉህ ሰው መሰለህ፡፡
2 ጊዜ ኮራያ ዘምተዋል፡፡
ሁለተኛውና አራተኛው ዘመቻ ላይ ተሳትፈው ዘምተዋል፡፡ ከኮርያ ዘመቻ ከተመለሱ በኋላ በሰራዊቱ መደበኛ ሆነው ተቀጥረው
እስከ ሻምበልነት ደርሰዋል፡፡ የሻምበልነት ማዕረጋቸውም የጠንካራነታቸው ማሳያ ነው፡፡ የክቡር ዘበኛ ሙዚቀኛ ክፍል ተዘዋውሮ የቲያትር ክፍል ሃላፊ ሆነው መርተዋል፡፡ በዚህም ጊዜ ውስጥ የጠቅል ሬዲዮ ጣቢያ ተቋቁሞ ነበር፡፡ በዛ የሬዲዮ ጣቢያም የተለያዩ ዝግጅቶችን ያቀርብ ነበር፡፡ እንደገና በክቡር ዘበኛ ውስጥ ዘመናዊ ሙዚቃ ሲቋቋም የዘመናዊ ሙዚቃ ክፍሉ ኃላፊ ሆኖ የመጀመርያው የክብር ዘበኛ መድረክ አስተዋዋቂ ነበሩ፡፡ አሁን ላይ መድረክ መሪ ነው እንላለን፡፡ የመጀመርያው መድረክ መሪ ሻምበል አፈወርቅ ዩሐንስ ነበሩ፡፡
ታሪኩ 2 ሲል
የመጀመርያውን የሙዚቃና ዳንስ ውህድ የኮሮግራፈር ኢትዮጵያ ውስጥ የጀመሩትም ሻምበል አፈወርቅ ዩሐንስ ነበሩ፡፡ ለሁሉ ነገር የመጀመርያው ሰው ናቸው፡፡ ለዳንሱ ለሙዚቃው! ሻምበል አፈወርቅ ዩሐንስ የውትድርና ጉዞአቸው፣ የሻምበልነት
ጉዞው የተቋረጠው በ1953 ዓ/ም በተደረገው መፈንቅለ መንግስት ላይ ነው፡፡
በክቡር ዘበኛ በሰራዊቱ
ውስጥ ላሉ ለግጥምና ለሙዚቃ ኪነጥበብ እንዲሁም ለመድረክ የሻምበል አፈወርቅ ዩሐንስ መኖር አስፈላጊ ነበር፡፡ ስለ ሰው ልጆች ህልውና፣
ስለ ቅንነት፣ ስለ ተፈጥሮ፣ ስለ ፍቅር በጠቅላላው ስለ ስነ ጥበብ ያላቸው ቦታ አመለካከት እጅግ የተደነቀና እጅግ የሚወደድ ነበር፡፡
በ1940ዎቹና በ1950ዎቹ
ዓ/ም ለዘመን መለወጫ ለገና በዓል እንዲሁም የተለያዩ ዝግጅቶች ላይ ‹‹የክቡር ዘበኛ የሙዚቃ ቡድን›› አለበት ሲባል የነበረው
ትርምስ ትንግርት ሲሆን ለዚህም የሙዚቃ ውጤት ዋናው የደም ስሩ ሻምበል አፈወርቅ ዩሐንስ ናቸው፡፡
በተጨማሪም በወቅቱ ለቅስቀሳ
እንዲያመች ተቋቁሞ በነበረው የሬዲዮ ጣቢያ ‹‹የእወጃ መኮንን በመሆን ስለ ሃገርና ስለ ወገን ፍቅር ከፍተኛ ቅስቀሳ አድርገውበታል፡፡
ከዚህም በላይ ‹‹ወታደርና ጊዜው›› በተባለው የክብር ዘበኛ ጋዜጣ ላይ የተወሰነ አምድ ተሰቷቸው ሰፊ ትንተናዎችና ጽሁፎችን ያቀርቡበት
ነበር፡፡ ‹‹የሰው ልጅና የእንስሳት አፈጣጠር ተመሳሳይነት አለው፡፡ በተለይም ሰው፣ ዶሮ፣ አይጥና አህያ አፈጣጠራቸው ተመሳሳይነት
አለው፡፡›› የሚለውን የአንዳንድ ሳይንስቶችን አስተያየት ሲያቀርቡ በወንበሩ በንግስናው ዙርያ የነበሩ ባለስልጣኖች በእነዚህ እንስሳት
የሚመስለን እኛን ነው በማለት ከፍተኛ ተቃውሞ አቅርበውባቸው ነበር፡፡ እንዲያውም የእድገት ደረጃቸው እንዳይጠበቅ እስከማድረግ ድረስ
ተጽዕኖ ተደርጎባቸዋል፡፡ ሻምበል አፈወርቅ ዩሐንስ ግን ከጠንካራ ስራቸው እንዲሁም ከመልካም አስተሳሰባቸው ማንም ሊለያቸው አልቻለም፡፡
እስከ 1953 ዓ/ም ድረስ
በክቡር ዘበኛ ውሰጥ ቆይተዋል፡፡
ደራሲ ብርሃኑ ዘሪሁን
ሻምበል አፈወርቅ ‹‹ግጥሞችና ፍቅር›› በሚል ርዕስ በጻፉት መጽሐፍ መግቢያ ላይ እንዲህ ሲሉ ስለ ሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስ ተናግረዋል፡፡
‹‹የሻምበል አፈወርቅን የግጥምና ቅኔ ችሎታቸው ማድነቅ የጀመርኩት ስማቸውን እንጂ መልካቸውን ሳላውቅ ገና በትምህርት ቤት በነበርኩበት
ጊዜ ነበር፡፡ የዘፈኑ የግጥም ደራሲ ሻምበል አፈወርቅ ዩሐንስ ሲባል በቅርብ ከተዋወኳቸው በኋላ የበለጠ ላደንቃቸው ወደድኩ፡፡ በስነ-
ጽሑፍ እንደሚገልጡት በፍቅር ለፍቅር፣ በቅንነት፣ ስለ ቅንነት የሚጥሩ ሰው ናቸው፡፡ በዚህ የይምሰል፣ የመመጻደቅና የግብዝነት ኑሮ
መካከል እንደሳቸው ያሉ ራሳቸውን ያገኙ በጣም ጥቂት ሰዎች ናቸው፡፡›› በማለት ለሻምበል ያላቸውን ክብር ገልጠዋል፡፡
በኃላም የቲያትርና የኪነ
ጥበብ ዝግጅት በሰራዊቱ ውስጥ ሲስፋፋ ሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስ የሁሉም አውራና እና ቀዳሚ ነበሩ፡፡ ቻቻ፣ ማርንጌ፣ ሮክ፣ ትዊስት፣
ራምባ፣ ሳምባ፣ ቧልስ የተባሉትን ዘመናዊ የሙዚቃ ስልቶችን በማስተማር ለሁሉም ግጥም በተስማሚ መልክ በማዘጋጀት በውል አስተምረዋል፡፡
በዚህ ዘመን የሚወደዱትን
አብዛኛዎቹን ሙዚቀኞች ወደ መድረክ እንዲወጡና አቅማቸውን እንዲጠቀሙ ከማድረግ አንፃር ሻምበል አፈወርቅ ዩሐንስ ድርሻ ትልቅ ነበራቸው፡፡
እነ ብዙነሽ በቀለ፣
እነ ጥላሁን ገሰሰ፣ እነ ተፈራ ካሳ፣ እነ ማህሙድ አህመድ ሌሎች የመድረክ ሰዎች ለመሆን የበቁት በአብዛኛው በገጣሚ አፈወርቅ ዩሐንስ
የፈጠራ ችሎታ ነው፡፡
አስናቀች ወርቁ፣ አስቴር አወቀ የሰሯቸው አብዛኛው ሙዚቃዎች ግጥምና ዜማቸው
የሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስ ናቸው፡፡
ጥላሁን ገሰሰ አምሳሉ፣ እኔ ያላንቺ አልኖርም፣ መለያየት ሞት ነው፣ ካንድም ሁለት ሶስቴ፣ እዩአት ስትናፍቀኝ የሚሉትና በጊዜው አሁንም ድረስ ተወዳጅ
የሆኑ የሙዚቃ ስራዎች ግጥምና ዜማቸው የተሰራው በሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስ ነው፡፡
ኩኩ ሰብስቤ በጉንጮቼ ወለል ሲፈስ የሚታየኝ፣ እባክህ አስረዳኝ ውሃ ነው እንባ ነው የሚለው ተወዳጅ ሙዚቃም ግጥምና ዜማው የሻምበል ነው፡፡
1972 ሻንበል ሊሞት ሲል መጨረሻ የሰጠው ዘፈን ሙሉ ካሴቱ የጠላሽ ይጠላ ወይም ውበትሽ ይደነቃል የሚለው አልበም የሻምበል አፈወርቅ
ዮሐንስ ነው፡፡ ለሃገር ዝፈን ብለውኝ መጨረሻ የሰራሁት ስራ ነው ይላል ጥላሁን ሻምበልን ሲያመሰግን፡፡
ሻምበል አፈወርቅ ዩሐንስ
አጫጭርና ረዣዥም ድራማዎችን ወይም ተውኔቶችን በመጻፍ ለህዝብ ያሳዩም ነበር፡፡ በተለይም በ1953 ዓ/ም በታህሳስ ወር የክብር
ዘበኛ መፈንቅለ መንግስት ሊሆን በመስከረም ወር ‹‹እምነት አትሞትም›› በሚል ርዕስ ባሁኑ ብሄራዊ ቲያትር አዳራሽ ያሳዩት ተውኔት
የመፈንቅለ መንግስቱ ፋና ወጊና ለሂደቱም ትክክለኛው ግልባጭ ነው ተብሏል፡፡
ሻምበል አፈወርቅ ዩሐንስ
ከታህሳሱ ሙከራ በፊት እጅግ የታወቁት ‹‹አልቻልኩም፣ የታወቀ አበባ፣ እግሯን እንዳይነካ፣ እንዋደድ ነበር..›› የተባሉ ግጥሞቻቸው
እጅግ የተደነቁ ነበር፡፡
ከመፈንቅለ መንግስት
ሙከራ በኋላ በተለይ ‹‹አልቻልኩም›› ብሎ የገጠመው ከሴራው ውስጥ ቀደም ብሎ ተካፋይ በመሆኑ ነው ተብሎ የእስራትና የግዞት ጽዋ
ቀምሰዋል፡፡ አብዛኛውን የግዞትና የእስራት ጊዜ ያሳለፉት በሸዋሮቢትና በሰበታ ነበር፡፡
ሻምበል አፈወርቅ ዩሐንስ
ከእስራትና ከግዞት ከተመለሱ በኋላ ፊታቸውን ያዞሩት አሁንም ወደ ስነ ጽሑፍ ነበር፡፡ ለጊዜው እንደ ብርቅ ይታዩ የነበሩት ደራሲ
መኮንን ‹‹የዙፋን ከሃዲ›› ተብለው ከተጉላሉት አንዱ ሆነው ብዙ ችግር ቢደርስባቸውም ስለታም ብዕራቸውን ይዘው ብቅ ያሉት ‹‹የኢትዮጵያ
ድምጽ›› እየተባለ ወደሚጠራው ክፍል ነበር፡፡ ከዚያም ‹‹እንዴት ሊሆን ቻለ›› በሚል ርዕስ ሳይንስ ወለድ የሆኑትን አንዳንድ የምርምር፣
የፍልስፍና ውጤቶችን በጋዜጣ እያወጡ ያስነብቡ ነበር፡፡ ቀጥሎም ወደ ሬዲዮ ተዘዋውረው ‹‹ሳይንስና ሕይወት›› በሚለው ቋሚ ርዕስ
ለአድማጭ የማይረሳ ትምህርት በማቅረብ ተወዳጅነት አትርፈfው ነበር፡፡ ይህ ‹‹ሳይንስና ሕይወት›› የተሰኘው የሬድዮ ዝግጅት በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ከፍተኛ አድማጭ የነበረው የሬዲዮ ዝግጅት ነበር፡፡
በ1960 ዓ/ም በውጪዎቹ
አቆጣጠር ጀግናው አትሌታችን አበበ ቢቂላ በሮም አደባባይ በባዶ እግሩ ማራቶንን አሸንፎ የሀገሩን ባንዲራ ከፍ ሲያደርግ ድሉን ለመጀመርያ
ጊዜ ለኢትዮጵያዊያን ያበሰረው ሻምበል አፈወርቅ ዩሐንስ ነው፡፡
ሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስ
አንባቢን በሚስብ ቋንቋ ብዙ መጽሐፍትን ጽፈዋል፡፡ እስካሁንም የሕትመት ብርሃን አግኝተው ለንባብ የበቁ መጽሐፎቻቸው 18 ናቸው፡፡
ጄንጅስ ካን፣ ዛዲግ ወይም ዕድል፣ ችግረኞቹ፣ ታላላቅ አስደናቂ ታሪኮች፣ ፍቅር በሰዎቸ ዘንድ፣ ጥበብና እድገት፣ ጠቅላላ እውቀት፣
የማፍቀር ጥበብ፣ ታላላቅ የፍቅር ታሪኮች፣ እየሳቁ ማልቀስ፣ አንድ እፍታ፣ ግጥሞችና ፍቅር ከሞት ያድናሉ፣ ግጥሞችና መጠጥና ሰው፣
ግጥሞች ለሐዘን ለትካዜ፣ የኔ ግጥሞች፣ ስሜታዊ ግጥሞች፣ ሃዘንና ደስታ የመጽሐፍቶቻው ርዕስ ናቸው፡፡
በግጥም ይዘቶቻቸው ብዙዎች
ይደነቃሉ፡፡
‹‹ቦንብ ቢፈነዳ መርዝ
ቢበተንም
ልጆችሽ ተርብ ነን ጠላት
አይደፍረንም፡፡
ሃገሬ አካሌ ነች ስጋዬና
ደሜ
ምንጊዜም የሷው ነኝ
ሞቼም ይሆን ቆሜ›› ብለው ለሃገራቸው ያላቸውን ጥልቅ ፍቅር ገልጠዋል፡፡
‹‹የሰው ልጅ አዕምሮ
ጠልቆ ተመልክቶ
ከዋክብትን አይቶ አካልን
አጥንቶ
ኃይል ማግኘት ሲችል
አቶምን ፈንክቶ
በከንቱ ነው እኮ አዋቂ
መድከሙ
ትምህርት ምንድነው ይላል
እንቅልፋሙ?
ይህን ቀላል አርጎ ምንድነው
መድከሙ?
ትምህርት ዋጋ የለው
ይላል እንቅልፋሙ›› በማለትም የመጽሐፍ አፍቃሪና የጥበብ ፈላጊ መሆናቸውን አሳይተዋል፡፡
‹‹ግድ የለኝም እኔ
ቢፈስ በረዶ
ሰዎችን ጎዳ የሚል አይምጣ
እንጂ መርዶ
ግድየለኝም እኔ ውቅያኖስ
ቢሞላ
ሰዎች ይኑሩ እንጂ በደስታ
በተድላ›› በማለትም ስለ ሰው ልጆች ፍቅርና ምቾት ያላቸውን ፍላጎት በሰፊው ጽፈዋል፡፡
‹‹ነፍሶች አንድ ሆነው
ጠልቀው ሲዋደዱ
ተንሰፍስፎ ሲያብብ አንደኛው
ሰው ለአንዱ
በጣም ከመዋደድ ግለት
የተነሳ
የሰው ልብ ተመስጦ ራሱን
ሲረሳ
ያለ ልክ ደግሞ ሲንጠፈጠፍ
ወዙ
በግልጽ ይታወቃል በፍቅር
መያዙ›› እያሉ ለፍቅር የሰጡት የስነ ጽሕፈት ቦታ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡
‹‹ክፋት አበጣጥራ ቆንጆ
ሆና ወጣች
አላፊ አግዳሚውን በአይኗ
እየቀጣች
እንዳልነበር ሁሉ ከሲታ
ሾካካ
ተንኮል ወፈረና በሃይሉ
ተመካ
የቅንነት ጎጆ ጥቀርሻ
ለበሰ
ሥራም አረጀና ደክሞ
አጎነበሰ›› ብለው በሰው ልጆች መካከል ክፋት እንደማያስፈልግና ክፋት መልካምነትን እንደሚገድለው በግጥማቸው አሳይተዋል፡፡
‹‹ከሃዘን በስተ ግራ
ከደስታ በስተቀኝ
እኔስ በመሃሉ ማለፉ
ጨነቀኝ›› በማለትም ምርምራዊ ስንኝ አቅርበዋል፡፡
ሻምበል አፈወርቅ ዩሐንስ ከመግጠማቸው ሌላ በርከት ያሉ መጽሐፍትን ለአንባቢ አበ
ርክተዋል፡፡ የሕትመትን ብርሀን ያላገኙ በርካታ መጽሐፍም እንዳላቸው በአባታቸው ስም የሚጠራው ልጃቸው ዮሐንስ አፈወርቅ ይናገራል፡፡
ሻምበል አፈወርቅ እንግሊዘኛ ኢጣሊያንኛ ፈረንሳይኛ ቋንቋዎች መናገር የሚችሉ ነበሩ፡፡ ሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስ ባለትዳርና 9 ልጆች
ነበሯቸው፡፡ አብይ አፈወርቅ የሚባል ልጃቸው የእርሳቸውን ፈለግ በመከተል የነጻ ፕሬስ ጋዜጠኛ ነበር፡፡ አሁን በስደት በአውስትራልያ ይገኛል፡፡
ሻምበል አፈወርቅ ጊዜያቸውን
በብዙ ለመጸሐፍት ፍቅር አውለዋል፡፡ ለመጻሕፍትና ለንባብ ጊዜያቸውን የሰው የቀለም ሰው ናቸው፡፡
በመጨረሻም ከመኖርያ
ቤታቸው አንዱን ክፍል ለመጻሕፍቶቻቸው ለቀው በተወለዱ በ53 ዓመታቸው የካቲት 22 ቀን 1972 ዓ/ም አርፈዋል፡፡
ሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስ በኖሩበት ሰዓት በብዙዎች የሚታወቁ፣ ለብዙዎች ተምሳሌት የሆኑ፣
ብዙዎች መክሊታቸውን ተጠቅመው ራሳቸውንና ሃገራቸውን እንዲያገለግሉ ለፍቅር ኖረው በፍቅር የሞቱ ብርቱ ጋዜጠኛ የዜማና የግጥም እንዲሁም
የበርካታ መጽሐፍት ደራሲ ናቸው፡፡
በመቃብራቸው ሐውልት ላይ የተጻፈው እራሱ ይሄን ስብእናቸውን የሚገልጥ ነው፡፡ ሐውልታቸው ላይ የተጻፈው ግጥም እንዲህ
ይላል፡፡
‹‹መሆኗን አውቄ አለም ወረተኛ
መኖር አልፈልግም በምድር ዳግመኛ
ሰዎች አትቀስቅሱኝ አርፌ ልተኛ
ሳቅ ለቅሶ አታሰሙኝ በዚህ የምታልፉ
ይሄ ስለሆነ የድካሜ ትርፉ›› ይላል ሐውልታቸው ላይ የተጻፈው ጽሑፍ፡፡
እንግዲህ የሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስ ታሪክ በጥቂቱ ይሄን ይመስላል፡፡ አሉኝ ረዥም ነጭ ጺማቸውን በእጃቸው እየዳሰሱ፡፡
እኔ የምለው አባባ ይሄን ያህል ስራ ለሰሩ አባት ምን ያህል ክብር ተሰጣቸው ይሆን? በማለት ጠየኳቸው፡፡
‘’ምንም የለም፡፡ አይ ልጄ እኛ እኮ የመመሰጋገን ችግር አለብን፡፡ የሰራን ሰው አመሰግናለሁ ማለት እንደ ትልቅ ነውር
መቁጠር ጀምረናል፡፡‘’ ብለው ትክዝ አሉ፡፡
ጉልበታቸውን ስሜ ስለነገሩኝ ታሪክ አመስግናቸው የሰማሁትንም ታሪክ ለሌሎች ላጋራ ተነሳሁ፡፡
አዎ የመመሰጋገን ችግር አለብን፡፡ ባልተመሰጋገንን ቁጥር መገፋፋታቸው ይበዛል፡፡ የሰራን ሰው እናመስግን፡፡ ለማመስገን
እንወቅ፡፡ ለማወቅ እናንብብ፡፡ ለማንበብ ትላንትን ዞር ብለን አባቶቻችንን እንመልከት፡፡ ታሪካችን ውስጥ ብዙ እውቀት አለ፡፡
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ