159.ሺበሺ ለማ ደባልቄ

 

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን፣ በቅርቡ መዝገበ-አእምሮ / ኢንሳይክሎፒዲያ / በሚል ርእስ የሚድያ እና የኮሚኒኬሽን ባለሙያዎችን ታሪክ በጠንካራ ሽፋን መጽሀፍ አሳትሞ ያስመርቃል፡፡ ታሪካቸው በመጽሀፉ ውስጥ ከሚሰነድላቸው አሻራ ካኖሩ የሚድያና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች አንዱ  አቶ ሺበሺ ለማ ናቸው፡፡ አቶ ሺበሺ በ1970ዎቹ መጀመሪያና በ1960ዎቹ መጨረሻ ወደ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ስራዎች ብቅ ያሉ አንጋፋ ባለሙያ ናቸው፡፡ እዝራ እጅጉ ታሪካቸውን እንደሚከተለው አሰናድቶታል፡፡

 

 

አቶ ሺበሺ ለማ ደባልቄ፣ ከተጠቀሱት አባታቸውና ከእናታቸው ከወይዘሮ ብርቅነሽ ዳኜ ኅዳር 14 ቀን 1934 .. በቀድሞው የሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት፣ በጋራሙለታ አውራጃ፣ በግራዋ ከተማ ተወለዱ፡፡ በዚያችው የትውልድ ስፍራቸው ባህላዊውንና ዘመናዊውን ትምህርት ሲከታተሉ ቆይተው የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀቁ፡፡

1953 .. ሐረር መድኃኔዓለም ሁለተኛ ደረጃ በመግባት ሲማሩ ቆይተው፣ ከዚያም ወደ ሐረር መምህራን ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩት በመዛወር የመምህርነት ሙያን ተከታተሉ፡፡ 1956 .. ከኢንስቲትዩቱ ምሩቅ እጩ መምህራን አንዱ በመሆን ወደ ሥራ ዓለም ተሰማሩ፡፡ በቅድሚያ በቀድሞዋ የጅጅጋ (ዛሬ ጅግጅጋ) አውራጃ በጭናክሰንና በጅጅጋ ልዑል ራስ መኮንን አንደኛ ትምህርት ቤቶች በድምሩ ለአምስት ዓመታት በመምህርነት ካገለገሉ በኋላ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገቡ፡፡ የዩኒቨርሲቲውን ትምህርት አጠናቅቀውም 1965 .. በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ስነ ጽሑፍ የመጀመሪያ ዲግሪአቸውን አገኙ፡፡

ከዚያም በሚወዱት የመምህርነት ሥራ ላይ ዳግም በመሰማራት፣ በወንጂ ኤች... የማህበረሰብ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለሁለት ዓመት በማገልገል፣ በድምሩ በሰባት ዓመታት የመምህርነት ጊዜ ቆይታቸው የበርካታ ታዳጊ ሕፃናትና ወጣቶች የቀለም አባት በመሆን አገልግለዋል፡፡

 

አቶ ሺበሺ ለማ ሁለተኛውን የሥራ ዓለም ሕይወት የጀመሩት ያኔ የዕርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን (ዕማማኮ) በሚባለው መንግሥታዊ ሰብአዊ ድርጅት ውስጥ 1968 .. ነው፡፡ 1965/66 .. በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በደረሰው የድርቅ አደጋና በአደጋውም ለከፋ ጉዳት በተጋለጠው የወገን እልቂት መነሻነት፣ ኮሚሽኑ በአገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ 1966 .. ተመሠረተ፡፡ ተቀዳሚ ተግባርና ኃላፊነቱም በዋነኛነት ለአደጋ ተጋላጩ ወገን የሕይወት አድን የምግብ፣ የመጠለያ፣ የህክምናና የመሳሰሉት ዕርዳታዎች አቅርቦት ሲሆን፣ በቀጣይም የኑሮ ተፈናቃይ ጉዳተኞችን መልሶ የማቋቋም፣ ወደፊት የሚገጥሙ ተመሳሳይ አደጋዎችን የመተንበይና የመከላከል እንዲሁም ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ዕርዳታዎችን የማሰባሰብና የማስተባበር መሰል ግዙፍ ኃላፊነቶች ተጣሉበት፡፡

ያንን አዲስ ተቋም በኃላፊነትም ሆነ በአገልግሎት ሰጪ ሠራተኛነት ከተቀላቀሉት ቀደምት የኮሚሽኑ ባልደረቦች መካከል አንዱ አቶ ሺበሺ ለማ ነበሩ፡፡ አብዛኞቹን 17 ዓመታት የአገልግሎት ዘመናቸውን ያሳለፉትም በሕዝብ ግንኙነትና ማስታወቂያ አገልግሎት የሥራ ዘርፍ ውስጥ ነበር፡፡

ከሥራ ዘርፉ ዋና፣ ዋና ተግባራት መካከልም፣ በሀገር ውስጥ ስለደረሱና ስለሚደርሱ የተፈጥሮ አደጋዎች፣ አደጋዎችን ለመከላከልና ለመቋቋም ስለሚያስፈልጉ ዕርዳታዎች፣ ህዝቡ አደጋዎችን በመከላከል ረገድ መውሰድ ስለሚገባው ጥንቃቄና የመሳሰሉትን በሚመለከት የተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች (በመጽሔቶች፣ ጋዜጦች፣ በሬዲዮና ቴሌቪዢንወዘተ) በመጠቀም ለአገር ውስጥም ሆነ ለውጪው ዓለም መግለጽ፣ ለድጋፍና ትብብር እንዲነሳሱ ማድረግ የሚሉትን ያካትታል፡፡

የአገር ውስጥም ሆኑ የውጭ ጋዜጠኞች በተለያዩ ጊዜያት የሚያጋጥሙ አደጋዎችን፣  የአደጋ ጉዳተኞችንና በዚህ ረገድ የኮሚሽኑን የሥራ እንቅስቃሴ ተገንዝበው ዜናዎችን ለስርጭት ያበቁና የዕርዳታ ድጋፍ ያስገኙ ዘንድ ሥራውን የመምራትና የማስተባበር ተቀዳሚ ኃላፊነትም የዚሁ የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነትና ማስታወቂያ አገልግሎት የሥራ ዘርፍ ነበር፡፡

አቶ ሺበሺ ለማ በዚያ የሥራ ዘርፍ ውስጥ በህትመትና ስነጽሑፍ አገልግሎት፣ እንዲሁም በዋናው የሕዝብ ግንኙነትና ማስታወቂያ አገልግሎት ኃላፊነት ከቅርብ የሥራ ኃላፊዎችና የሙያ አጋሮች ጋር በመተባበር ባገለገሉባቸው ዓመታት በኮሚሽኑ መጽሔቶች በዋና አዘጋጅነት፣ እንዲሁም ለተለያዩ ሚዲያዎች የሚቀርቡ ዜናዎችን፣ መጣጥፎችን፣ ጋዜጣዊ መግለጫዎችንና ቃለ ምልልሶችን ...ወዘተ በሚመለከት በአዘጋጅነት፣ በአስተባባሪነትና በአቅራቢነት ሠርተዋል፡፡

 

የጋዜጠኝነት ሙያን ከንባብ ከመቅሰም ባሻገር በአገር ውስጥና በውጭ አገር በአጫጭር የሙያው ሥልጠናዎችና ውይይቶች ላይ በመሳተፍ የሙያ ክህሎታቸውን አዳብረዋል፡፡

በዚያ እናት መሥሪያ ቤታቸው እያሉም በድጋሚ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የድህረ ምረቃ ትምህርታቸውን በመከታተል በእንግሊዝኛ ስነ ጽሑፍ የማስተርስ ዲግሪ አግኝተዋል፡፡

አቶ ሺበሺ ለማ 1985 .. ዕማማኮን ከለቀቁ ከጥቂት ዓመታት በኋላ በትምህርት ሚኒስቴር ዋናው መሥሪያ ቤት በስዊድን መንግሥት በሚደገፍ ፕሮጀክት በአካባቢ እንክብካቤ ትምህርት ፕሮጀክት ስር በትምህርታዊ የህትመት ሥራዎች አዘጋጅነትና አስተባባሪነት፣ ከዚያም በአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት በምክር ቤቱ ንግድና ልማት ጋዜጣ ዋና አዘጋጅነት አገልግለዋል፡፡ በንግድ ምክር ቤቱ በቆዩባቸው ዘጠኝ ዓመታት ውስጥም ከጋዜጣው ዋና አዘጋጅነት በተጨማሪ በህዝብ ግንኙነትና ኔትወርኪንግ እንዲሁም በሚዲያ ዋና ክፍል ኃላፊነት ሠርተዋል፡፡ በዚህም ለንግድ ምክር ቤቱ አባላት መረጃ አቅርቦትና ንግድ መስፋፋት የበኩላቸውን ጥረት አበርክተዋል፡፡

አቶ ሺበሺ ለማ በእነዚህ በተጠቀሱትና ከዚያም በኋላ ቀጣይ ዓመታት በርከት ያሉ የሕፃናት መጽሐፍትንና መጽሔትን እንዲሁም የአንዳንድ ታዋቂ ሰዎች የሕይወትና ግለ-ታሪኮችን ጽሑፍ በማዘጋጀትና ለህትመት በማብቃት ጊዜአቸውን ፍሬአማ በሆኑ ሥራዎች ላይ ሲያሳልፉ ቆይተዋል፡፡

     የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ ዝግጅት

-     አቶ በቀለ ሞላ

-     /ጄኔራል ከበደ ገብሬ

-     ወይዘሮ ሸዋረገድ ገድሌ

-     ሜጀር ጄኔራል መርዕድ ንጉሤ (የከፊል ጽሑፍ ሥራዎች ጐስት ራይተርና ኤዲተር)

-     / ኃይለገብርኤል ዳኜ፣ ለህትመት የተቃረበ (ጐስት ራይተር)

     የሕፃናት መጽሐፍት

-     ለምለምና ጋሹ

-     ሰብሉ አንድ ማሳ፣ በላተኛው ኃምሳ

-     የቡሎ መላ

-     ሊንቻና ቢንቻ

-     አርአያዎች

-     የጦጢት መላ

-     ጣናን በቅምጫና

-     አፋኙ ቡድን

     የሕፃናትና ጐልማሶች መጽሔት

-     “ኩኩሉ” የሕጻናት መጽሔት

-     “አካባቢአችን” የሕፃናትና   

   ጐልማሶች መጽሔት፣

 

የመዝጊያ ሀሳብ ፤ ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የኢንሳይክሎፒዲያ ቦርድ አባላት አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡

አቶ  ሺበሺ ለማ ይህን የኢንሳይክሎፒዲያ ሀሳብ  ላመነጨውና እያዘጋጀ ለሚገኘው ጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ ትልቅ የመሰረት ድንጋይ ያስቀመጡ ሰው ናቸው፡፡ ከዛሬ 28 አመት በፊት ጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ የ9ኛ ክፍል ተማሪ ሳለ ኩኩሉ በተሰኘችው መጽሄት ላይ ሲሳተፍ የእኔ ምኞት በሚለው አምድ ስር ጽሁፉን ያወጡለት ሰው ናቸው፡፡ በተጨማሪም በኩኩሉ መጽሄት ላይ ጋዜጠኛ እዝራ ገና አንደኛ ደረጃ ተማሪ ሆኖ በጽሁፍ እየተከፈለው እንዲሰራ ያደረጉ በኋላም በሚድያ እና በጋዜጠኝነት እንዲቀጥል የረዱት የሙያ አባቱ ናቸው፡፡ አቶ ሺበሺ ለማ በህዝብ ግንኙነት ስራ የተካኑ በስነጽሁፍ እውቀታቸው በሳል ባለሙያ ናቸው፡፡ ስለ ሀገራችን የህጻናት መጽሄት አጀማመር ስናነሳ አቶ ሺበሺ በዋና አዘጋጅነት  ያሰናዷት የነበረችው ኩኩሉ ትጠቀሳለች፡፡ ይህቺን በሀገራችን ታሪክ የመጀመሪያ የሆነችን መጽሄት ለ4 አመታት ህትመቷን በማስቀጠል የደከሙ ባለውለታ ናቸው፡፡ አቶ ሺበሺ ዛሬም ከንባብ እና ከጽሁፍ ጋር ያላቸው ቁርኝትእንደጠበቀ ነው፡፡ ዛሬ አቶ ሺበሺ ወመዘክር የፈለገ አያጣቸውም፡፡ የንባብ እና የስነ-ጽሁፍ ፍቅራቸው ዛሬም ውስጣቸው እንደሰረጸ ነው፡፡ አቶ ሺበሺ በኢትዮጵያ የህዝብ ግንኙነት ሙያ ላያ የራሳቸውን አሻራ ያኖሩ ስለመሆናቸው ይነገራል፡፡ ብዙ ለመታየት ጉጉቱ ባይኖራቸውም ያከናወኑት ጉልህ ተግባር ግን በብዙዎች የሚታወቅ እና የማይደበቅ ነው፡፡ እኒህ ታላቅ ሰው ባለፈው ህዳር 14 የ 80ኛ አመት የልደት በአላቸውን ያከበሩ ሲሆን ዛሬም ሲታዩ መንፈሳቸው ከአካላች ጋር ሆኖ እጅግ ጠንካራ አድርጓቸዋል፡፡ አቶ ሺበሺ የእነ በቀለ ሞላን ታሪክ በመጽሀፍ ሲያቀርቡ በጥልቅ ጥናት ነው፡፡ እንዲህ አይነት ሰዎች ጋዜጣ መጽሄት  ቲቪ ሬድዮ ላይ ተጋብዘው ቢያወሩ መልካም ነው፡፡ የሚያስተላልፉት መልእክት ትልቅ ነው፡፡ እነ ጋሽ ሺበሺ ብዙ ሰርተው ታሪካቸው ግን  አይታወቅም፡፡ ለምን? አሁን ግን ዘመን መጣ፡፡ የሰራ ታሪኩ የሚሰነድበት ፡፡ ጋሽ ሺበሺ ለሰሩት ስራ እውቅና እየሰጠን እነሆ ታሪካቸውን ለሀገር ተረካቢው ትውልድ ተቀበል ብለናል፡፡ ለጋሽ ሺበሺ መልካም እድሜ እንመኛለን፡፡    

 











 

  

 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች