165. አላዛር አስገዶም
---የታላቆቹ እኩያ
ተወዳጅ ሚድያ እና
ኮሚኒኬሽን፣ በቅርቡ መዝገበ-አእምሮ
/ ኢንሳይክሎፒዲያ / በሚል ርእስ
የሚድያ እና የኮሚኒኬሽን
ባለሙያዎችን ታሪክ በጠንካራ
ሽፋን መጽሀፍ አሳትሞ
ያስመርቃል፡፡ ታሪካቸው በመጽሀፉ
ውስጥ ከሚሰነድላቸው አሻራ
ካኖሩ የሚድያ ሰዎች
አንዱ ጋዜጠኛ
አላዛር አስገዶም ነው፡፡
ተወዳጅ ሚዲያና
ኮሚዩኒኬሽን እስከ አሁን ታሪካቸውን ከሰነደው የሚዲያ ሰዎች በእድሜ ትንሹ እርሱ ነው። ከልቡ መሻት ጋር የገጠመ የጋዜጠኝነት ስራው
የታላቆቹ እኩያ እንዲሆን ስለበቃው በልዩ መስፈርት ታሪኩን እንደሚከተለው እንሰንዳለን። ጋዜጠኛ አማረ ደገፋውና ጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ
የአልአዛርን ግለ ታሪክ እንደሚከተለው አጠናክረውታል፡፡
በሁሉም ዋጋ ጋዜጠኛ መሆን አለብኝ
የ2005 ዓ.ም መስከረም ከጠባ ጥቂት ከራርሞ.... የሙዚቃው ሰው ሰርፀ ፍሬስብሃት ለፋና ኤፍኤም አንድ ሰው ጠቆመ። "ይህን ወጣት ብትቀጥሩት ታተርፋላችሁ" አለ። ፋናዎች ሰርፀን ሰሙና ለወጣቱ የ20 ቀናት የሙከራ ጊዜ ሰጡት። ተሞካሪው እነዚህን 20 ቀናት በትጋት ሁኖ ፈፀመ። ሞካሪዎቹ ዝም አሉ፤ እርሱ ግን ትጋቱን ቀጠለ። ከተቀጣሪ ሰራተኞች እኩል ስራም ስምሪትም ይሰጠዋል፤ በብቃት ይሰራል.... አሁንም ዝም። በዚህ የዝምታና የትጋት መንገድ ሳይደነቃቀፍ 90 ቀናትን በፅናት ተጓዘ። ድፍን
3 ወራት ቤሳ ቤስቲን አልተከፈለውም። ከዩኒቨርስቲ በጥሩ ውጤት መመረቁን እያሰበ 'በመምህርነት እዛው መቅረት እችል ነበር' ብሎ አላማረረም፤ ሌሎች የስራ እድሎችን በመተውም አልተቆጨም፣ ምክንያቱም በሁሉም ዋጋ ጋዜጠኛ መሆን አለብኝ ብሎ ወስኖ ነበር።
በመጨረሻም በጥር 2005 ዓ.ም ከሞካሪዎቹ አፍ የ"ተሳክቷል" ቃል ወጣና ፋና ወደ ቀጣሪነት ተሞካሪውም ወደ ሙሉ ጋዜጠኝነት አደጉ። ከ8 ዓመታት በላይ በዘለቀ የፋና ቆይታው በስፖርት ይግዘፍ እንጂ ያልሰራው ስራ የለም። ያነበበው ዜና ሁሉ ተቃንቶለት፣ የተነተነው ስፖርት ሁሉ ሰምሮለት፣ የመራው ዝግጅት ሁሉ አምሮለት...
ጋዜጠኛስ እንደእርሱ አስባለ፦ አላዛር አስገዶም።
ትውልድና ልጅነት
ከአሰላ ጥቂት ወጣ ብላ ባለች ቀርሳ ነው ትውልዱ፤ በ1982 ዓ.ም። እስከ 4ኛ ክፍል ያለ ትምህርቱን እዚያው ባለ ጭቄ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት በኦሮምኛ ቋንቋ ተምሯል። የቀሩትን የመጀመሪያ ደረጃ ክፍሎች ወደ አሰላ ተሻግሮ ሃምሌ 19 የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት በአማርኛ ቋንቋ አጠናቋል። ጭላሎ ተራራ ት/ቤት የዘጠነኛና አስረኛ ክፍል ትምህርቱን፤ አሰላ መሰናዶ ደግሞ የመሰናዶ ትምህርቱን የተከታተለባቸው ተማሪ ቤቶች ናቸው። በ2002 ዓ.ም ዲላ ዩኒቨርስቲ ተመድቦ እስከ 2004 በዘለቀ ቆይታው የመጀመሪያ ዲግሪውን ተቀብሏል። 2005 ዓ.ም ሲሆን ደግሞ ፋና ገባ።
አባቱ ሥነ ህይወታዊ ዝምድናን ብቻ ሳይሆን የሬዲዮ አድማጭነትንና አንባቢነትን አጋብተውበት ነበር። ገና ሰው በመሆኛ ማለዳው ጆሮዎቹን ለሬዲዮ አሰልጥኖ አድጓል። ከኤፍኤሞች ልደት ቀድሞ በአጭርና መካከለኛ ሞገድ ያገኛቸው የነበሩ የኢትዮጵያ ሬዲዮ፣ ፋና፣ ለገዳዲ፣ ቪኦኤ፣ ዶቸቬሌ፣ ቫቲካን ሬዲዮን አድምጧል። ስለዓለም አቀፍ የፖለቲካ አሰላለፍ እና ስለእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታው ብሎ በትንሿ ሬዲዮው በኩል ጆሮውን ባህር አሻግሮ ቢቢሲ ወርልድ ሰርቪስን ከስድስተኛ ክፍል አንስቶ አድምጧል።
አድማጭነት………አንባቢነት
ከሁለት አስርታት ቀድሞ ኤፍኤም አዲስን ተከትለው የመጡ ኤፍኤሞችንም በታዳጊነት ዘመኑ ልቅም አድርጎ አዳምጧል። ቤት የመዋል ከፍተኛ ዝንባሌው ለሬዲዮ ማድመጥ ሰፊ ጊዜን አስገኝቶለታል። "ሁሉንም ጣቢያና ፕሮግራም እሰማ ነበር"
የሚለው አላዛር የሚዲያን ጣዕምና ኢመደበኛ አቀራረብን ተማርኩባቸው ከሚላቸው ኤፍኤሞች በስም እየጠራ የሚያከብራቸው ጋዜጠኞችም ዝግጅቶችም አሉት። በወቅቱ የቅንጦት እቃ ቢሆንም ቴሌቭዥንንም የመከታተል እድል ነበረው።
በጆሮዎቹ መሰልጠን የቀኑ የሚመስሉት ዓይኖቹም በንባብ በርትተዋል። በዘመኑ ይታተሙ የነበሩ ጋዜጦች፣ መጽሔቶችና መጽሐፍትን አገላብጧል። የንግድ ሰው የነበሩት አባቱ ስለንባቡም እጃቸው አለበት። ለስራ ጉዳይ አዲስ አበባ ደርሰው ሲመለሱ ጋዜጦችን እና ዓለማዊም መንፈሳዊም መጽሐፍትን አስከትለው ነበር። ገና የ12 ዓመት ልጅ እያለ ጋዜጣ ሻጭ ወዳጆች ነበሩት። በግዥም በኪራይም ንባቡን አሳድጓል። ከአባቱ አነስተኛ ግሮሰሪ አስመጭና አከፋፋዮች ጋዜጣና መጽሔቶቻቸውን ሲያሳድሩ እርሱ ለሊቱን ሙሉ ያነብ ነበር።
ከሚዲያ ፍቅሩ እኩል ለእግር ኳስም ልቡ የደነገጠው በልጅነቱ ነበር። የዓለምና የአፍሪካ ዋንጫን በማየት የተጀምረ የእግር ኳስ ትውውቁ አድጎ ገና አስራዎቹ ቤት እያለ ለሀገራችን ተመልካች ያስቸግሩ የነበሩ የእኩለ ሌሊት የላሊጋና ሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያዎችን ይመለከት ነበር። የንባብ ፍቅሩን ከኳስ መውደዱ ጋር አስተባብሮ ተጓዘ። በየሚዲያዎቹም ስፖርትን በአንክሮ ይከታተል ነበር። "በሳምንት 10
የስፖርት ጋዜጣ ቢወጣ አስሩንም ከገፅ እስከ ገፅ አነብ ነበር" ይላል ጊዜውን ሲያስታውስ።
ከህትመትና ከኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ጋር የነበረው የረዥም ጊዜ ወዳጅነት አውቆት ይሁን ሳያውቀው ወደ ጋዜጠኝነት ሳይስበው አልቀረም። ይሰማቸው የነበሩ ጋዜጠኞችን አነባበብ ደጋግሞ ሲለማመድ ራሱን አግኝቶታል። ለዪኒቨርስቲ ትምህርቱ ወደ ዲላ ሲያቀና ሬዲዮና ጋዜጦቹ የአሰላን ያክል ተደራሽ ስላልነበሩ መጽሐፍት ንባብ ላይ የበዛ ጉልበቱን ጨርሷል። ከዲላ መልስ አሰላን አልፎ አዲስ አበባ ደርሶ ፋና ቤት 3 ወራትን ከተፈተነ በኋላ የልቡ መሻት ሆኖለት ጋዜጠኛ ሆነ።
ፋና እና አላዛር
እድሜ ለረዥም ጊዜ የሬዲዮ አድማጭነቱ ይሁንና የፋና ቤት የመጀመሪያዎቹ ወራት ቆይታው እንዲያምሩለት ሆኗል። በአድማጭነት ዘመኑ አብዛኛዎቹ ጋዜጠኞችን ያውቅ ስለነበር ለመዋሃድ አልከበደውም። "ለእነሱ ነው እንጂ እንግዳ የሆንኩት፤ ማንም ለኔ እንግዳ አልነበረም" ይላል። በመስማት ብዛት ያዳበረውን አቅም ይዞ 'ጎበዝ' ከሚላቸው ጋዜጠኛና ኤዲተሮች ልምዳቸውን እየቀሰመ ራሱን አሰለጠነ። በመጀመሪያዎቹ አራት ዓመታት ፋና ውስጥ አንድ ጋዜጠኛ ሊሰራቸው የሚገቡ ሁሉንም የጋዜጠኝነት ስራዎች ሰርቷል።
ከስድስተኛ ክፍል ጀምሮ መከታተሉና ከአባቱ ጋር እያለፈ እያለፈ መወያየቱ ምርኩዝ ሁኖት በጋዜጠኝነት ዘመኑ ዓለም አቀፍ ትንታኔዎችን በተለየ ጣዕም ለአድማጮቹ አድርሶ ከመወደድም በላይ ሁነውለታል። ለዚህ ማሳያው የእርሱ አድናቂዎች ሰብሰብ ብለው ሲጨዋወቱ...
ከአመታት በፊት አየር ላይ የዋለ ትንታኔን አስታውሰው "ስለዚህ ጉዳይ" የሰራው እያሉ በልዩነት ማስታወሳቸው ነው።
የመጀመሪያ ቅጥሩ ስፖርት ጋዜጠኝነት አልነበረም። ፋና ቤት በነበረ የመጀመሪያውን አንድ አመት ቆይታው ስፖርት በደረሰበት አልደረሰም። የኋላ ኋላ በምሳና በሻይ ሰዓት ከስፖርት ክፍል ባልደረቦቹ ጋር ሲጫወት ስፖርት ላይ ያለውን እውቀት ታዝበው አብሯቸው እንዲሰራ አድርገው በምሳ ሰዓት የፋና የስፖርት ፕሮግራም ላይ የተጀምረ ጉዞው ዛሬ ላይ ግዙፍ የእግር ኳስ ጋዜጠኛ እንዲሆን አስችሎታል።
በዚህ ጊዜ ነው የጀመረው ልለው አልችልም የሚለው የእግር ኳስ ፍቅሩ ነፍስ ካወቀ በኋላ አስተውሎ የተከታተለው የ1990ው የፈረንሳይ የዓለም ዋንጫን እንደሆነ ግን አይዘነጋም። ዲኤስቲቪ መርጦ
ከሚያስተላልፍበት ዘመን አንስቶ እግር ኳስን ሳይሰለች ተከታትሏል፤ ከወዳጆቹ ጋር ስለሚወዳቸው ቬንገር እየተከራከረም እየተወያየም አድጓል። እድሜው ከፍ እያለ ሲመጣ ልዩ ፍቅሩን በንባብ አጀበው። ከየእለት ዜናዎች እኩል እውቀት ነክ ነገሮችን አሳዶ አንብቧል።
እንጀራ እበላበታለሁ ሳይል ያሳደገው ክህሎት ስራው ሁኖ ሲገኝ ልክ ለክተው እንደቆረጡለት ልክክ አለለት።
"ጋዜጠኛም ባልሆን ንባቤን አላቆምም" የሚለው አላዛር አብሮት ያደገ ፍቅሩን ሬዲዮ ላይ ይዞት ሲወጣ ግን ተጨማሪ ሃላፊነት እንዳለው ያስረዳል። አድማጩ ከፍተኛ የእግር ኳስ ፍቅር ያለውና ስፖርቱን ከእጆቹ መዳፎች እኩል ማወቁ ከፍ ያለ ዝግጅትና የበዛ የንባብ ቁፋሮ እንዲያስፈልገው ያደርጋል።
ከዓለም አቀፍ ትንታኔዎቹና ከስፖርቱ እኩል 120 እና 90 ደቂቃን በመምራትም ደምቋል። ከእርሱ ቀድሞ አዘጋጆች ብቻ ይመሯቸው የነበሩ እነዚህን የፋና ተወዳጅ ዝግጅቶት እርሱ ገና ዓመት ሳይሞላው ሪፖርተር እያለ በተደማጭ ድምፁ በቀጥታ ስርጭት መርቷቸዋል።
የቋንቋና የአገላለፅ ሃብታምነቱን እና የማዕዘን አመራረጡን የታዘቡ "ለቤተ ክህነት ቅርብ ሁኖ ነው ያደገው"
በሚል የሚሰጡትን አስተያየት አይቃወምም። መጽሐፍ ቅዱስንና ሌሎች መንፈሳዊ መጽሐፍትን ከጋዜጦች መሳ ለመሳ ማንበቡን ያነሳል። በእግረ መንገድ መጻፍ ይሞክር እንደሁ ሲጠየቅ ግን ይሁነኝ ብሎ ለመጻፍ ሞክሮ እንደማያውቅ ነገር ግን ለወደፊት "ከኖርኩና ከሰራሁ በኋላ ብፅፍ ደስ ይለኛል"
ይላል።
አላዛር እና ካናል ፕላስ
"ሬዲዮ አስማት ነው... ምትሃታዊ ስሜት ይሰጣል"
እያለ በሚያንቆለጳጵሰው ሬዲዮ..... ፋና ቤት ውስጥ ለ8 ዓመታት ከሰራ በኋላ በመንሱር አብዱልቀኒ ጠቋሚነት ወደ ካናል ፕላስ ተዛውሮ በእግር ኳስ ጋዜጠኝነትና ኮሜንታተርነት እየሰራ ይገኛል። በሳምንት ሁለት ቀናት ደግሞ እዛው ፋና በስፖርት
365 ዝግጅት ብቅ ይላል። ለልቡ ቅርብ የሆነንና ነፍሱን የሚያስደስታት ስራን ሲሰራ ስለኖረ "አንድም ቀን ደስ
ሳይለኝ
ሰርቼ አላውቅም"
ይላል።
ሲያነብ ወሰን ስለሌለው እውቀትን ከትህትና ጋር አጣምሯል። ስለትህትናው ሲጠየቅ አሁንም ወደ አባትና ቤተሰቡ ዙሮ እነሱ ናቸው መሰረቶቼ ለማለት "በስክነት የሚያምን ቤተሰብ ውስጥ ነው ያደግኩት" ይላል።
ተወዳጅ ሚዲያና ኮሚዩኒኬን እንዲህ የሚዲያ ሰዎችን ታሪክ መሰነድ መጀመሩን በበጎ አይን ነው የሚያየው። ትርጉም ያለው ስራ የሰሩ ሰዎችን ህያውን እንደሚያደርግና ጋዜጠኞቹን እንደ አርኣያ ለሚያዩ ታዳጊዎች በአንድ የጎግል ፍለጋ ርቀት ላይ ታሪኩን ማግኘታቸው ያበረታቸዋል ይላል።
አላዛርን ደገኛ ስራ ሰርተሃልና እናመሰግንሃለን ከማለታችን መሳ ለመሳ ስለልከኛ ጥቆማው ሰርፀን፣ ስለቀናኢ አቀባበላቸው ፋናዎችን ማመስገን ይገባናል። ወደ ደመቀበት ስፖርት ስለሳቡልን ደግሞ ዮናስ አዘዘ፣ ዘርአይ እያሱንና ቤተማርያም ሃይሉንም ማመስገን የተገባ ነው ። በቀላሉ እናገኘው የነበረን ተወዳጅ ጋዜጠኛ በክፍያ ወደሚታይ ጣቢያ ወስዶ አላዛርን በስፖርቱ ዘርፍ አንድ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት በር ለከፈተለት መንሱር አብዱልቀኒም ምስጋናው ይድረሰው፡፡
አላዛር አስገዶም ወደፊት እድልና ሁኔታዎች ምቹ ከሆኑለት ከዚህ በላይ የመስራት እቅድ አለው፡፡ ይቅናው-አሌክስ፡፡
መዝጊያ ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ የኢንሳይክሎፒዲያ ቦርድ አባላት አቋም
የሚንጸባረቅበት ነው፡፡
አላዛር ተስፋ ከሚጣልባቸው የሚድያ ሰዎች ቀዳሚው ነው፡፡ ስራዎችህ እንዴት ብስለትን ተላበሱ ተብሎ ሲጠየቅ የምወደውን ነገር በመስራቴ ነው ብሎ መልስ ይሰጣል፡፡ እርግጥም አላዛር የሚወደውን እንደሚሰራ በቅርበት የሚያውቁት ይመሰክራሉ፡፡ አላዛር አንድ ነገርን ከመስራቱ በፊት ቀድሞ ያስተውላል፡፡ ቆም ብሎ ስለሚያስተውል ስራዎቹ በአቀራረብ ፤ በቋንቋም በይዘትም ብስለትን የተላበሱ መሆን ችለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ተስፋ የሚጣልባቸው የሚድያ ሰዎችን ከስር ከስር እያወቀች ካልሄደች ነገ የሚደርስላትን አንጋፋ በቀላሉ አታገኝም፡፡ ዛሬ የዘራነውን ነገ ለማጨድ የዛሬውን ዘር ማወቅ አለብን፡፡ አቅምና እውቀትን ከጥሩ ስነ-ምግባር ጋር የተላበሱ እንደ አላዛር አይነት ሰዎችን ስናገኝ ታሪካቸውን መዝገብ ላይ እናሰፍራለን፡፡ ተረካቢው ትውልድ ደግሞ ከእነ አላዛር እየተማረ የራሱን አክሎ በጥረት ማደግን ይማራል፡፡ ተወዳጅ ሚድያ በመዝገበ-አእምሮ ይህን የአላዛርን ታሪክ ሲሰንድ ትልቅ ሃላፊነት እየጣለበት ነው፡፡ በስራው በርትቶ ለሀገር አንድ ቁምነገር እንዲሰራም መልካም ምኞታችንን እንገልጻለን፡፡
Ante tileyaleh
ምላሽ ይስጡሰርዝ