164. ጥበቡ በለጠ-tibebu belete
ተወዳጅ ሚድያ እና
ኮሚኒኬሽን፣ በቅርቡ መዝገበ-አእምሮ / ኢንሳይክሎፒዲያ / በሚል ርእስ የሚድያ እና የኮሚኒኬሽን ባለሙያዎችን ታሪክ በጠንካራ
ሽፋን መጽሀፍ አሳትሞ ያስመርቃል፡፡ ታሪካቸው በመጽሀፉ ውስጥ ከሚሰነድላቸው አሻራ ካኖሩ የሚድያ ሰዎች አንዱ ጋዜጠኛ ጥበቡ
በለጠ ነው፡፡ 2 ዓመት ቀደም ብሎም በዚሁ ስራው በበጎ ሰው ሽልማት እጩ ሆኖ መቅረብ ችሎ ነበር፡፡ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ የተወዳጅ ሚድያ
የኢንሳይክሎፒዲያ ቦርድ አባል እና ቀዳሚ አበረታች ሲሆን እዝራ እጅጉ ታሪኩን እንደሚከተለው አሰናድቶታል፡፡
ውልደት እና የትምህርት ጊዜ
‹‹ስነፅሁፉ ላይ ያለኝን የበሰለ እውቀት ያመጣሁት እጅግ በተመስጦ
በማድመጥ ነው፡፡››
ጥበቡ በለጠ፣ ሚያዝያ 8 1966 ዓ.ም
ከእናቱ ከወ/ሮ ወደርየለሽ ፋንታሁን እና ከአባቱ ከአቶ በለጠ ተፈራ ተወለደ፡፡ እስከ 1937 ዓ.ም ድረስ አዶላ
ተብላ በምትጠራውበሁዋላም በታዋቂው አርበኛ በደጃዝማች ከበደ ብዙነሽ ክብረመንግስት በተባለች ከተማ ነው፡፡
አራት ልጆች ቤት ውስጥ ይኑሩ እንጂ በርካታ የቤተ ዘመድ ልጆች በሚኖሩበት ቤት ያደገ
ሲሆን ወላጆቹም የተማሩ ነጋዴዎች ሲሆኑ በክብረ መንግስት ከተማ ጎንደር የተባለ ሆቴል ባለቤትም ናቸው፡፡
አዲስ አበባ እና በክብረመንግስት ቤት ስለነበራቸው ትምህርታቸውን በሁለቱም ከተሞች
እየተዘዋወረ ነው የተማረው፡፡በመዋእለ ህፃናት ፋንታ የቄስ ትምህርት ቤቱን ጨምሮ ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ክፍል በራስ ብሩ
ወ/ገብርኤል የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት በክብረመንግስት ከተማ ተምሯል፡፡
ሦሰተኛ ክፍል ተማሪ እያለም ሰንደቅ ዓላማን የሚሰቅል ተማሪዎችንም በሰልፍ ሰዓት ብሔራዊ
መዝሙርን የሚያዘምርም ነበር፤በተጨማሪም በዚሁ ወቅት በአስደናቂ ሁኔታ ከሰርቶ አደር እና ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ዜናዎችን
በማጠናከር ዜናዎችን ለትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ማንበብ ጀመረ፡፡ለዚህ ሁሉ መነሻው የሆኑት እና ተፅዕኖ ያሳደሩበት የስፖርት ሳይንስ
መምህሩ ለስነፅሁፍ ልዩ ፍላጎት እና ፍቅር የነበራቸው አጎቱ ድንበሩ
ስዩም ናቸው፡፡
የስድስተኛ ክፍል ትምህርቱን ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በልደታ ሚሲዮን ትምህርት ቤት
ተማረ፤በዚህም ወቅት ለልጆች ፕሮግራም ሃሙስ ሃሙስ ይቀረፅ ነበርና ለሚፅፋቸው ነገሮች በደንብ ማንበብ ጀመረ፡፡በመጀመሪያ
ያነበበው ትልቅ መፅሀፍም አጎቱ ያመጡለትን ‹‹እንደ ሠው በምድር እንደ አሳ በባህር››የሚል ርዕስ ያለውን የሩሲያ ትርጉም ነበር፤ቀጥሎም ዛሬ በአማርኛ የስነፅሁፍ ታሪክ ትልልቅ
የሚባሉ ልብወለድ መፃህፍትን ማንበብ ችሏል፡፡
ክብረመንግስት ከተማ በወቅቱ የተዘጋጀ የአውቶብስ መናኸሪያ ባለመኖሩ እነሱ ቤት አጠገብ
ነበር አውቶብሶች ይቆሙ የነበረው፤የእነርሱ ሆቴል ደግሞ በዚህም ምክንያት ብዙዎች የሚስተናገዱበት እና ጥበቡም ከብዙ ሰዎች ጋር
ገና ከህጻንነቱ ጀምሮ ይገናኝ እና ከሰዎች ጋር የቀረበ ግንኙነት እንዲኖረው ያደርገው ነበር፡፡
እዚሁ አዲስ አበባ ላይ ደግሞ ከፖሊስ ፕሮግራም አቅራቢው ሰለሞን አምባቸው ጋር በሰፈር
እና በትምህርት ቤት በርካታ የልጅነት ጊዜያቸውን አብረው ማሳለፍ የቻሉ መንትያ ጓደኛሞች የሚሰኙም ነበሩ፡፡
ክብረመንግስት በአውራጃ ኪነት ውስጥ በታዳጊ ቡድን ውስጥ በተዋናይነት፣ሙዚቃ መሳሪያ
ተጫዋችነት፣በተወዛዋዥነት የተለያዩ አካባቢዎችን አብሮ በመዘዋወር ከታላላቅ ባለሙያዎች ጋር መስራት ችሎ ነበር፡፡
በዚሁ እርሱ በነበረበት በታዳጊ ክፍልም ውስጥም የተለያዩ መዝሙሮች ይሰሩ የነበሩ ሲሆን
‹‹በቡቢባቤብቦ (2) ማህይምነት ወድሞ ኢሰፓኮ አብቦ››ኢሰፓኮ (የኢትዮጵያ ሰራተኛ ፓርቲ አደራጅ ኮሚሽን ሲሆን ሌላው ደግሞ
‹‹ጓድ መንግስቱ ኮሚኒስቱ መሪያችን ቆራጥ አብዮተኛ የኛ አለኝታችን የአብዮቱ ወገን እልል እንበል ጸረ አብዮተኛ በትግል
ይቃጠል›› እና ሌሎችም በርካታ መዝሙሮችን ዛሬም ድረስ ለስነፅሁፍ ስራው እና ለጋዜጠኝነቱ መሰረት ናቸው እናም ከነ ዜማቸው አንድም
ሳይዘነጋ ያስታውሳቸዋል፡፡
በክብረመንግስት እና በአዲስ አበባ በተለያዩ ጊዜያት ትምህርቱን የተማረው ጥበቡ በንፋስ
ስልክ ደግሞ ከዘጠነኛ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል ተማረ፡፡
ገና በልጅነቱ ለስነ ፅሁፍ ልዩ ፍላጎት ስለነበረው ይፅፍ እና በዙሪያው ላሉ ያነብላቸው
ነበር፤የእነርሱም ግብረ መልስ አበረታች እና በዚሁ እንዲገፋበት የሚያደርግ በመሆኑ ይህ የሞራል ስንቅ ሆኖለታል፡፡በዚህ
መነሻነት በኢትዮጵያ ራዲዮ የወጣቶች ፕሮግራም ላይ የተለያዩ ፅሁፎቹን መላክ ጀመረ፤ፅሁፎቹም ጥሩ ስለነበሩ ይነበቡለትም
አንዳንዴም እንዲያነባቸው ይጠራም ነበር፡፡
ጥበቡ ስነፅሁፉ ላይ ያለው የበሰለ እውቀት የመጣው እጅግ በተመስጦ በማድመጡ ነው፤‹‹ራዲዮ
ማድመጥ ከመፃፍም በላይ የምወደው ነው›› የሚለውም ለዚህ ነው፡፡ሱስ የሆነበትን ራዲዮ ማድመጥን ንጉሴ አክሊሉ፣ታደሰ
ሙሉነህ፣ታምራት አሰፋን የመሳሰሉትን አንጋፋ ጋዜጠኞችን ጨምሮ የጳውሎስ ኞኞ አስደናቂ ፅሁፎችን እየሰማ የሁለተኛ ደረጃ
ትምህርቱን ያሳለፈ ሲሆን ይህ ደግሞ ከፍ እንዲል በእነርሱ ደረጃ እንዲመጣ ትልቁን አስተዋፅኦ አድርጎለታል፡፡
ጋዜጠኝነት ሕልሜ ነው መማር አለብኝ ብሎ ሲወስን አባቱ ሕክምና እና መሰል ሙያዎችን
እንዲያጠና ይፈልጉ ነበር፡፡
በጊዜውም ደግሞ በተለያዩ ጋዜጦች በተለይ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ላይ ተከታታይ ፅሁፎቹ
ይታተሙለት ጀመር፡፡
በተጨማሪም ከ1984 በኋላም የሕትመት ሚዲያው የበዛበት እነ ቢቢሲ ራዲዮ፣ዶቼቬሌ፣የአሜሪካን ራዲዮ የዘፈን ምርጫን
እናም በተለያዩ የሀገራችን ጋዜጦችን እንደ እጅ ማፍታቻ ይፅፍባቸው በነበሩት እነ ወርልድ ስፖርት ላይ ጨምሮ በርካታ የጥበቡ ስራዎች
ይነበቡለት ነበር፤ይህ ደግሞ ገና ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ላለው ወጣት ልቡን ይሞላለት የነበረ ትልቁ ብርታት ነበር፡፡
የዪኒቨርሲቲ ሕይወት
‹‹መምህራኖቼ ጓደኞቼ ጭምር ነበሩ፡፡››
በ1985 ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች እና ስነ ጽሀፍ ትምህርት ክፍል ተቀላቅሎ የከፍተኛ
ትምህርቱን ብቸኛው የመረጠው የትምህርት ክፍል የደረሰው ተማሪ ሆኖ በዚህ ትምህርት ክፍል መማር ጀመረ፡፡
ጥበቡ ትምህርት ክፍሉን ከመቀላቀሉ ቀድሞ በስም ያውቃቸው ከነበሩት ከእነዶ/ር ፈቃደ አዘዘ፣ዘሪሁን አስፋው፣ሳሙኤል
አዳል፣ዮናስ አድማሱ እና አምሳለ አክሊሉ የመሰሉ ምሁራን የሚያስተምሩበትን ክፍል ተቀላቅሎ መማር ብቻ ሳይሆን ከመምህራኖቹ ጋር
በመቀራረብ ጓደኛም መሆን ቻለ፡፡
በልጅነቱ በክብረ መንግስት የጀመረው ከሰው ጋር በቅርበት የመግባባት ባህሪው በዩኒቨርሰቲ ቆይታውም በእጅጉ የሚታይ
በአጠቃላይ ከተማሪ እና ከመምህራኖቹ ጋር ተባብሮ የሚሰራ ተማሪም ነበር፤ከዚህም በላይ ጥበቡ በተማሪ እና በመምህራን መካከልም እንደ
ድልድይ መሆንም የቻለ እና የተመሰገነም ነበር፡፡
እነ እመቤት አብዲሳ፣ብሩክ መኮንን፣አለምሰገድ ባስሊዮስ እና የዴይሊ ሞኒተር አዘጋጁ አበራን ጨምሮ የሚያስታውሳቸው
አብረውት የተማሩ ናቸው፡፡
ጥበቡ ከመምህራኖቼ ጋር ጥሩ ቅርበት ለትምህርቱም ልዩ ፍላጎት ቢኖረኝም በጋዜጠኝነት መምህሩ ዶ/ር አብዲ አሊ አማካኝነት
ከኢትዮጵያ ቋንቋዎች እና ስነ ጽሀፍ ትምህርት ክፍል ተፈልቅቄ የትምህርት ዘርፌን ቀይሬያለሁ ይላል፡፡
በ ዶ/ር አምሳሉ አክሊሉ አጭር የኢትዮጵያ የስነ ፅሁፍ ታሪክን ሲያስተምሩት የስነ ፅሁፍ ታሪክ ኢትዮጵያ ውስጥ፣ከየት
እና በየትኛው ፊደል የሚለውን ጨምሮ ምን ላይ እንደተፃፈ ሁሉ በመማሩ እና በመፅሃፋቸው በማንበቡ ለስነ ፅሁፍ የነበረው ፍላጎት
በልዩ ሁኔታ እንዲጨምር እና እንዲያድግ አግዞታል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ መምህሩን ዶ/ር አብዲን ባስደነቀ መልኩ ‹‹የሕትመት መገናኛ
ብዙሃን በኢትዮጵያ›› በሚል በመረጃ በዳበረ መልኩ ያስደነቀ ጥናታዊ ፅሁፉን መስራች ችሎ ነበር፡፡ይሄንን ከመስራቱ በፊት ግን ርዕሱ
በመምህሩ ተጥሎበት ‹‹የኢትዮጵያ ራዲዮ የዜና አቀራረብ››የሚል ርዕስ ፀድቆለት ቢጀምርም ምንም አይነት አጋዥ እና ማጣቀሻዎችን
በማጣቱ ረዝም ጊዜ ቢቆይም የሺጥላ በተሰኘ ሰው አማካይነት አዳዲስ በመጡ መፃህፍት አማካይነት ባገኘው የጥናቱ ግብአቶች ኤ ያገኘበትን
እና በአማካሪው ሆነ በፈታኞቹ የተወደደለትን ጥናታዊ ፅሀፍ ሰርቷል፡፡
ዓለም ዓቀፍ ተሞክሮ
‹‹በተለያዩ ዓለም ዓቀፍ መምህራን በመማሬ ዕውቀቴን
አስፍቻለሁ፡፡››
ጥበቡ ከአዲስአበባ ዩኒቨርሲቲ ተመርቆ ከወጣ በኋዋላ በ‹‹ኤቢሲ›› እና በኢትዮጵያ ራዲዮ ስራ ጀመረ፡፡በኋላ ግን
ስራው ወደ ‹‹ኤቢሲ›› ሲያመዝን ጊዜውን በእርሱ ስራ ላይ ያሳልፍ ነበር፡፡
የ‹‹ኤቢሲ›› ጅማሮው የሆነው ደግሞ በመምህሩ ዶ/ር ፈቃደ አዘዘ አማካይነት ከአሜሪካ የመጡት እና የሚዲያ አብዮትን
ለመፍጠር ስራ ያልጀመረ ተማሪ ይፈልጉ ከነበሩት ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ጋር አስተዋወቀው፡፡
ትላልቅ ደረጃ ላይ ከነበሩት በክፍሉ ታደሰ ፣በዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ፣በዶ/ር ቆንጂት፣በብርሃነ መዋ፣በሃይሉ ሻወል፣በአበበ
ወርቄ፣ እና በፕሮፌሰር መስፍን አሜሪካ በተፀነሰው ‹‹ኤቢሲ›› ላይ በተቀረጸው ሃሳብ መሰረት አብሮ ከተጨማሪ ሌሎች ልጆች ጋር
መስራት ጀመረ፡፡
‹‹ኤቢሲ›› ውስጥ መሳተፍ በመቻሉ የተለያዩ ዓለም ላይ ትላልቅ በሚባሉ መምህራን መማር ከመቻሉምበላይ የተለያዩ እድሎችን ማግኘት ችሏል፡፡ በናይሮቢ አድርጎት በነበረው ቆይታ በዛ
ያለው የዴይሊ ኔሽን አሰራርን በሚገባ ከ‹‹ኤቢሲ››መስራቾች ጋር ተመልክተው እና ተምረውበት መጥተዋል፡፡
ለንደን በሚገኘው ሮይተርስ አማካይነት በደቡብ አፍሪካ ለትምህርት በ‹‹ኤቢሲ›› አማካይነት የሄደ ሲሆን በጀርመኑ ጎተ ኢንስቲትዩት በወ/ሮ ተናኜ አማካይነት ደግሞ በዶቼ ቬ ኃላፊው እዚሁ
ስልጠናንም ማግኘት ችሏል፡፡ከስልጠናው በኋላም ከሰልጣኞቹ ውስጥ ጥበቡ ተመርጦ በጀርመን በርሊን የመማር እድልም አግኝቶ ነበር፡፡
ኖርዌይ እንደራሷ ድርጅት ታየው በነበረው እና ከፍተኛ እገዛ ታደርግበት በነበረው ‹‹ኤቢሲ››አማካይነትም በኖርዌጂያኖች
ደግሞ ትምህርትን ማግኘት በመቻሉ በሚወደው የስራ መስክ ላይ ዕውቀቱን በተለያዩ የዓለም አቀፍ መምህራን በመማር ማስፋት ቻለ፡፡
አዲስ ዜና ጋዜጣ
‹‹በጋዜጣው አማካይነት በኢትዮጵያ ፖለቲካ፣ኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ሕይወት ውስጥ ትልቅ ለውጥን ማምጣት ችለናል››
በአዲስ ዜና ጋዜጣ ላይ ከምስረታው ጀምሮ በዕውቀት የተመሰረተ የጋዜጠኝት መርህን በመከተል በተለይ በኢትዮጵያ ፖለቲካ፣ኢኮኖሚ
እና ማህበራዊ ሕይወት ውስጥ ትልቅ ለውጥን ማምጣት ችለዋል፡፡
ጥበቡ በለጠ ከእነ ክፍሉ ታደሰ ፣ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ፣ዶ/ር ቆንጂት፣ብርሃነ መዋ፣ሃይሉ ሻውል፣አበበ ወርቄ፣ እና
ፕሮፌሰር መስፍን ጋር መስራት ሃሳብን ከማንሸራሸርም በላይ የዳበሩ ሀሳቦች ላይ እንዲጽፍ አስችሎታል፡፡
መለስካቸው አምሃ በዋና አዘጋጅነት እንዲሁም ሙሉጌታ አያሌው ደግሞ በምክትል ዋና አዘጋጅነት ይሰሩበት ነበር፡፡ በአዲስ
ዜና ጋዜጣ ላይም ይሰራቸው ከነበሩት ዜናዎች በተጨማሪ የታሪክ አምድ፣የባህል እና የኪነ-ጥበብ አምድ እና የተለያዩ የታዋቂ ሰዎችን
ታሪክ ቃለ- መጠይቅ በማድረግ ይሰራ ነበር፡፡
ጥበቡ በለጠ የራሱን አሻራ ያሳረፈበት እና የራሱ አንባቢዎችን በብዛት ማፍራት የቻለው የአዲስ ዜና ጋዜጣ ኢትዮጵያ
ውስጥ ከነበሩት ሌሎች በተሻለ በፖስታ ቤት አማካይነት ወደ ተለያዩ የአፍሪካ ሀገራትን ጨምሮ ኢትዮጵያዊያን ወዳሉበት ሁሉ በብዛት
ይላክ ነበር፡፡
በዚህ ውስጥ ትልቁ እና ጠቃሚ የነበረው በየጊዜው ይሰጥ የነበረው ከኖርዌይ እና ከቢቢሲ በመጡ አሰልጣኞች የተሰጠው
ስልጠና ነው ብሎ የሚያነሳው ጥበቡ በዚህም ተተኪ ልጆችን በሚገባ ማፍራት መቻላቸውም ጥንካሬያቸውን እንደሚያሳይ ያነሳል፡፡
ጥበቡ በለጠ
( 1996-2014 )
ምንም'ኳን አዲስ ዜና እየታተመ ቢገኝም በወቅቱ በነበረው
ሬዲዮ የማግኘት ትልቅ ህልም እና የጋዜጠኝነት ሙያውን ይበልጥ የማሳደግ ፍላጎት ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠን በመካከለኛው አውሮፓ
ወደ ምትገኘዋ ጀርመን ሀገር ለጋዜጠኝነት ሙያ ትምህርት እንዲያቀና አድርጎታል ።
በሀገረ ጀርመን ተገኝቶ የጋዜጠኝነት ሙያን በተለይም ደግሞ በኮሙኒኬሽን ዙሪያ በብሮድካስት እና ህትመት ሚዲያው ዘርፍ
አንድ ጋዜጠኛ እንዴት አድርጎ ልዩ ልዩ መጠይቆችን በማድረግ በተሰጠው ገጽ ላይ መስራት እንደሚችል እና በወቅቱ የነበረውን ዲጂታል
ቴክኖሎጂውን እንዴት መጠቀም እንደሚችል እንዲሁም ደግሞ ስቲዲዮን እንዴት መቆጣጠርና የዜና ክፍሎችን መምራት እንደሚቻል የሚያስተምሩ
ሌሎች በርካታ ትምህርቶችን ያካተተ ( Course) በስፋት ወስዷል።
በቃል ከሚሰጡ ሥልጠናዎች በተጨማሪ የተለያዩ ሚዲያችን እየተዘዋወሩ የማየትና በተግባር የመሰልጠን ዕድል ስለነበረው
ሚዲያዎቹ ሥራዎቻቸውን እንዴት እንደሚሰሩ በምን መልኩ እንደሚያቀናብሩ
በህዝብ ዘንዳ እንደሚደመጡ ፣ እንዴት ለህዝባቸው እንደሚደርሱና እንደሚነበቡ በተግባር ቃኝቷል። የልቡንም በልቡ
አድርጎ የቻለውን ሰንቋል ። በጀርመን የሚገኙ ትልልቅ መፅሔቶች የሚታተሙባቸው
ቦታዎችን እና የህትመት ውጤቶችን በአካል ተገኝቶ በማየት በቂ ልምድ ቀስሟል።
በወጣትነት ዕድሜው ባህር ማዶ
ተሻግሮ
የጋዜጠኝነት እና ኮሙኒኬሽን ሙያን እየተማረ የነበረው ባለትልቅ ህልሙ ጋዜጠኛ ጥበቡ ስለጀርመን ባህልንና ታሪክ እንዲሁም ታሪክ እንዴት መዘገብና መፃፍ እንዳለበት የአንዲት ሀገርን ቅርስ እንዴት
ለትውልድ ማቆየትና ከዘመን ወዲያ ማሻገር እንዲሁም ለቀጣዩ ትውልድ ማስረከብ እንደሚቻል ተምሯል።
እግረመንገዱንም በሀገሪቱ በቆየባቸው ወራቶች ውስጥ
መሰረታዊ የሆኑ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ጫናን ለማቅለል እና ችግሮችን ለመቅረፍ ከማህበረሰቡ ጋር በቀላሉ ለመግባባት
የሚረዱ የጀርመነኛ መሰረታዊ ቋንቋዎችንም ተምሯል።
ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ በወራቶች ቆይታ ጀርመን የቋጠረችለትን የእውቀት አገልግል በአዕምሮው ውስጥ ጠፍሮ የጀመረውን
ትምህርት ሰባት ወራት እና ጥቂት ቀናቶች ሰውቶ ካጠናቀቀ በኋላ ወደ እናት ሀገሩ ኢትዮጵያ ምድር ተመለሰ። በሺህ ዘጠኝ መቶ ዘጠና ዘባት (1997) ሲሰራበት ከነበረው አዲስ ብሮድካስቲንግ
ካምፓኒ ጋር በመሆን የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣንን የሬዲዮ ፈቃድ እንዲሰጣቸው ጠየቀ። ቢሆንም ግን ከባለስልጣኑ ፈቃድ ማግኘታቸው የህልም እንጀራ ሆነ። ብዙ ዝግጅት
ያደረገበት ፣ ወንዝ የተሻገረለት ፣ ገንዘብና ጊዜ የከፈለበት ይህ
ትልቅ ህልም ቀስ በቀስ በሀገሩ ኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን አማካኝነት
እንደጨው እየሟሟ ፣ እንደጉም እየተነነ፣ እንደአቧራ እየበነነ አይኑ እያዬ እንደ እንዶድ አረፋ ከሰመ። ከሀገረ ጀርመን የቀሰመው
ዕውቀት መሬት ይዞ ሳያፈራ ቀረ።
ይህም በርካቶችን መስመራቸውን ቀይረው አፋኝ ስርዓቱን ለመታገል ሲሉ ወደ ፓለቲካ እንዲገቡ ያስገደደ ሆነ። በተለይም ደግሞ የአዲስ ብሮድካስቲንግ
ኩባንያ መስራችና ባለቤቶች የሆኑት እና ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ፣ ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም ፣ ሽመልስ ተክለፃድቅ መኩሪያ፣ ሀይሉ
ሻውል እና ሌሎችም ይህን ስርዓት ለመፋለም ወደ ፖለቲካው ገቡ ።
ሙያቸውን ለማሻሻል ፣ በሙያቸው ሀገራቸውን ለማገልገል ትልቅ ተስፋ
የሰነቁትን ለሀገራቸው ብዙ መስራት የሚችሉ እንደነ ጥበቡ በለጠ ያሉ ወጣት ጋዜጠኞችን ለማምከን የጣረ ስርዓት ነበር።
ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ ከፋሲል የኔዓለም እና ሌሎች የአዲስ
ዜና ልጆች ጋራ በመሆን በአልሞት ባይ ተጋዳይነት በአዲስ ዜና ጋዜጣ ላይ ብዙ ሰርተዋል። በተለይም በምርጫው ወቅት ከፍተኛ ተነባቢነትን
ያገኘ ብዙ ቅጂዎችን በማሳተም ትልቅ የለውጥ እንቅስቃሴ የፈጠረ ህትመት
ነበር። ዳሩ ግን እያነከሱ ብዙ መራመድ አይቻልምና አዲስ ዜና ብሮድካስቲንግ ካምፓኒ ቀስበቀስ ወደመዘጋቱ አመራ።
በዚህ ምርጫው ወቅት ሀገሪቱ አይታ ወደማታውቀው ምስልቅልቅ ውስጥ ገብታለች ።ሺህ ዘጠኝ መቶ ዘጠና ሰባት
(1997) ዓ.ም በጋዜጠኝነት ሙያ ታሪክ ውስጥ The Dark
Age ወይም የጨለማው ዘመን በሚል የሚታወቅ ጥቁር ጠባሳን ጥሎ አልፏል።
በሙያው ላይ ያሉ በርካቶች ለስደትና ለእስር ተዳርገዋል ። የሚዲያ ኩባንያዎች ተዘግተዋል ። በመካከል ከሞት የገዘፈ ዝምታም ሰፍኗል።
ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠም ከዚህ ውሽንፍር አላመለጠም ።
ምንምኳን ጥበቡ ለእስር ባይዳረግም አለመታሰር የሚያመጣው መዘዝ ከመታሰር የከፋ ነውና ለጊዜውም ቢሆን ከድመቱ የመንግሥት
ጥርስ ለመትረፍ ሲል በጎጆው ለመደበቅ ተገዷል።
ይሁን እንጂ ጥበቡ ስለተደበቀ ብቻ በፍርሃት እጁን አጣጥፎ አልተኛም። ፈጽሞ አልቆዘመም ነበር። "ጀግናና ጪስ
መውጫ አያጣም " እንዲሉ እንዲያውም እማኝ በመሆን በሀገሪቱ እየሆነ ያለውን ነገር ፣ እየተሰራ ያለውን ደባ የሰብአዊ መብት
ጥሰት እና በሀገሪቱ የሚታየውን የፖለቲካና ማህበራዊ ኑሮ ምስቅልቅሎሽ ከሀገር ውጪ ላሉ የተለያዩ ሚዲያዎች ድምፁን ቀንሶ በሚስጢር
በማቀበል ሴራቸውን በማጋለጥ ጋዜጠኞች እንዲዘግቡት በማድረግ ዓለም ስለኢትዮጵያ እንዲያውቅ በዚያ ጨለማ ወቅት መረጃ በመስጠት በሙያው
ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
በኋላ ጉዳዩ ትንሽ መረጋጋትና መርገብ ሲጀምር ደግሞ ከኤሚ እንግዳና አመለወርቅ ታደሰ ጋር በመሆን የንግድ ፈቃድ
አውጥተው በፊልም ኢንዱስትሪ ላይ ተሰማርተው በሥራ ላይ ቆይተዋል። አዲስ ፊልምና ፕሮዳክሽን በኢህአፓ ዘመን የነበረ አንድ ታሪክ
ላይ የሚያጠነጥን በክፍሉ ታደሰ ፕሮዲውስ የተደረገ ያልደረቀ እንባ የተሰኘ
ፊውቸር ፊልም ሰርተዋል።
ብዙ ጊዜን የፈጀ ፣ብዙ ገንዘብ የወጣበት በርካታ ጥናቶች
የተካሄዱበት ባለሞያዎች የተሳተፉበት የታሪካዊው ቅዱስ ላሊበላ ዶክመንተሪን በመስራት በሺህ ዘጠኝ መቶ ዘጠና ዘጠኝ (1999) ዓ.ም በለንደን የሚገኘው የብሪቲሽ
ሙዚየም አፍሪካ ላይ የተሰሩ ባህል፣ ታሪክ በእምነት ላይ የተመሰረቱ ሥራዎችን ሲመርጥ የላሊበላው ዶክመንተሪ ፊልም አሸናፊና ተሸላሚ
ለመሆን በቅተዋል። ይህ ዶክመንተሪ ከፍተኛ የሆነ እውቅናን አግኝቶ በብሪቲሽ ለንደን ሙዚዬም ውስጥ ለመታየት የቻለ ሲሆን እነጥበቡ
በለጠን ለዓለም ህዝብ ያስተዋወቀ ነበር።
አዲስ ፊልም ፕሮዳክሽንና ጥበቡ በዚህ አላቆሙም፡፡ ወደ ጎንደር ተጉዘው ቀዳማይ የአፍሪካ ስልጣኔ በሚል አስደናቂ
ዶክመንተሪን በመስራት በአፍሪካ፣አሜሪካና የተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት በማሳየት ከፍተኛ አድናቆትን ለማግኘት ችለዋል። ባላሰቡት መንገድ
ወደፊት እየገሰገሱ ያሉት እነጥበቡ በዶክመንተሪ ፊልሙ ሀገራቸውን ለዓለም በማስተዋወቅ ትልቅ አሻራን አሳርፈዋል ።
የሰውልጅ እና ጅብ በሐረር ኢትዮጵያ የሚል የሐረር
ህዝብንና የጅቦቿን ቁርኝት የማህበረሰቡን እምነትና ባህል
ለዓለም ህዝብ በስራቸው እንካችሁ ሲሉ በማሳየት እጅ ባፍ አስጭነው አስደምመዋል።
ለኡጋንዳው ፓኖስ ደግሞ በአፍሪካ ውስጥ በአራት ሀገራት
ላይ የተመሰረተ ማለትም በኢትዮጵያ፣ ኡጋንዳ፣ ኬንያና ታንዛኒያ ላይ
የሚያጠነጥን የሴቶች እና የህፃናት ታሪክን በዶክመንተሪ ፊልም በአማርኛ ፣ እንግሊዝኛ እና ኬስዋሊ ቋንቋዎች ሰርተው ለምስራቅ አፍሪካው
ኡጋንዳው ፓኖስ አስረክበዋል። ይህም በኡጋንዳ፣ ታንዛኒያና ኬንያ
መታየት ችሏል። በኡጋንዳ ውስጥ ካለ ኩባንያ አክሲዎን ገብተው ባለድርሻም ሆነዋል።
የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበርና የኢትዮጵያ ስነጽሑፍ ታሪክ
ዶክመንተሪ ፊልም ፣ ክርስትና በኢትዮጵያ ዶክመንተሪ ፊልም ፣ በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያንን የእግር ኳስ ውድድርን 17ኛ ዓመት ታሪክ አንጋፋው ሙዚቀኛ
ጥላሁን ገሰሰ በተገኘበት ዶክመንተሪ ፊልም ሰርተው ለታሪክ አስቀምጠዋል።
አዲስ ፊልም ፕሮዳክሽን የቀድሞውን የአዲስ ብሮድካስቲንግ ኩባንያ ህንፃ በፊልም ስራዎቹም ወቅት ሲገለገልበት ከቆየ
በኋላ የኢህአደግ መንግሥት አሸባሪ በማለት በአንድ ቀን ውስጥ ወታደሮችን አሰማርቶ ለዓመታት የደከሙበትን ጥሪት ሳይቋጥሩ ነገ እንሰራዋለን
ያሉትን ሳይሰበስቡ መንግሥት ንብረቴ ነው ሲል ባዶ እጃቸውን አስቀርቷቸዋል ።
በዚህ ጊዜ ሀገራቸውን በዶክመንተሪ ፊልም ለዓለም ያስተዋወቁት እነ ጥበቡ በለጠ ከዘጠና ሰባቱ ቀጥሎ ሁለተኛው ምስቅልቅል
ደርሶባቸዋል ። መኪናዎቻቸውን ፣ ንብረቶቻቸውንና ህልሞቻቸውን ወርሰዋቸዋል ።
እያፈረሷቸው ያልፈረሱት እየበተኗቸው ያልተጠፋፉት እያራቋቸው ያልተነጣጠሉት ሙያ ያዋደዳቸው እነጥበቡ በለጠ ዳግም
ተሰባስበው ነፍስ መዝራታቸው አልቀረም።
ተደራጅተውም የጥናትና ምርምር ሥራዎችን እና የትልልቅ ሰዎችን የድርሰት ሥራዎች አርትኦት በመስራት ማሳተም ጀመሩ።
የክፍሉ ታደሰን 'ያ ትውልድ ' የተሰኘ ቁጥር 1, 2, 3 ሲያሳትሙ በህይወታቸው ትልቁ ሥራ ሲሉ የሚኮሩበትን የተመስገን
ገብሬን ህይወቴ የተሰኘ መጽሐፍት እንዲሁም የቀድሞውን የኢፌድሪ ፕሬዚደንት የግርማ ወልደጊዮርጊስ 'አየር እና ሰው' የተሰኘ መፅሐፍ
አሳትመው ለንባብ ሲያበቁ የሕይወት ታሪካቸውን የተመለከተ መፅሄት ማዘጋጀት ችለዋል ። በተጨማሪም በርካታ የኩባንያ ፕሮፋይል መጽሔቶችን
ሰርተዋል።
ወደ ኋላም መለስ ብለው ኡጋንዳ ከገቡት የአክሲዮን
በፊልም ሰሪዎች ተጠርተው ዶ/ር ዶሚኒኪ ከተባለች የህክምና ባለሙያ
ጋር በግርዛት ላይ ያተኮረ ዶክመንተሪ ፊልም ሰርተዋል። ሺህ ዘጠኝ መቶ ዘጠና ሰባት (1997) ዓ.ም ያመጣው የፖለቲካ ጎርፍ ሳቢያ
ከሀገራቸው የተሰደዱ ኢትዮጵያውያንን ጉዳይ የሚያሳይ ትልቅ ዶክመንተሪ ፊልም ሰርተዋል። ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ የሰው መጽሐፍ ከማሳተም
ያለፈ ከኤሚ ጋር በጋራ በመሆን የፈላስፎች ጉባኤ የተሰኘ የአጫጭር ልቦለዶች መድብል በሁለት ሺህ ሦስት (2003) ዓ.ም ለማሳተም
በቅቷል።
ሰንደቅ ጋዜጣን በማቋቋም ዋና አዘጋጅ በመሆን አርቲክሎችን
ይዞ በመጻፍ ጋዜጣው ተነባቢ እንዲሆን እና በእግሩ መሬት እንዲይዝ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል ።
ከዚህ ሁሉ መገለባበጥ በኋላ ከባህር ማዶ ያመጣውን ዕውቀት የሚዘራበትን በብዙም ለማጨድ የሚያስችለውን የሚወደውን
የጋዜጠኝነት ሙያ በፋና ሬዲዮ ከዳንኤል ወርቁ ጋር በመሆን ጥበብና እፎይታ የሚል ሰኞና አርብ ከምሽት 2:00 ሰዓት እስከ
6:00 ሰዓት ድረስ የሚሰራጭ ትኩረቱን በንባብና መፅሐፍት ላይ ያደረገ ፕሮግራም ሰርቷል።
ይህ ፕሮግራም ሲቋረጥ ከቢኒያም ከበደ ጋር በመሆን
ከማስተርስ ፊልምና ኮሙኒኬሽን ጋር በመተባበር አዲስ ጣዕም የተሰኘ አዋጭ የሬዲዮ ፕሮግራም የሰራ ሲሆን በ2004 ለ2005 የአፍሪካ 50ኛ ዓመትን አስመልክቶ በሚዘጋጅ ፕሮግራም ላይ የአፍሪካ ህብረትና
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አዘጋጅነት በወጣው ውድድር አሸንፈው የሀምሳ አራቱን የአፍሪካ ሀገራት ታሪክና የአፍሪካ ህብረትን
አስመልክቶ ትልቅ ሥራን ሰርቷል። በዚህም ዝግጅት ላይ ጁቢድ (Jubidi) የተሰኘ መጽሔትን አሳትመው በሁሉም የአፍሪካ መሪዎች
እጅ አስገብተው በድምቀት አስመርቀዋል።
የብዙዎች ምሳሌ ልበ ቀና ባለዕራዕዩ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ "ኢትዮ ኮን" የተሰኘ አለማቀፍ የኮንስትራክሽን
ኤግዚብሽን ዋና አዘጋጅ በመሆን ሰርቷል።
ንባብ ለሕይወት የመፅሐፍት አውደ ርዕይ ላይ ከአዘጋጆቹ አንዱ ሲሆን የኢትዮጵያ ደራሲያን ማሕበር ዋና ፀሐፊም ነው።
በህትመቱ የክፍሉ ታደሰን ኢትዮጵያ ሆይ ቁጥር አንድና ሁለት አርትኦት እና ህትመት ከኤሚና አመለወርቅ ጋር መሆን ሰርቷል ።
Cooperative Water በሚል ርዕስ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚወጣ የአሥርቱን ተፋሰስ ሀገራት ጉዳይ እና የህዳሴውን
ግድብ በተመለከተ ብዙ ምሁራኖች የሚፅፉበት በየስድስት ወሩ የሚታተም መፅሔት አቋቁሞም ነበር። ይሁን እንጂ የተለያዩ በኃላፊነት
ቦታ ላይ ያሉ ሰዎች በሚያነሱት ጥያቄና አትፅፉም ሲሉ በሚፈጥሩት
ወከባ ሳቢያ ብዙ እርቆ ሳይጓዝ ለመቋረጥ ተገዷል ።
በጋዜጠኝነት ሙያ በቆየባቸው ጊዜያት በርካታ ትልልቅ ሰዎችን ኢንተርቪው ማድረግ ችሏል ። ጥቂቶቹን ለማስታወስ ያህል
ደራሲ ሀዲስ አለማየሁ ፣ አንጋፋው ሙዚቀኛ አለማየሁ እሸቴ ፣ አንጋፋው የኢትዮጵያ ሙዚቀኛ ጥላሁን ገሰሰ፣ አስናቀች ወርቁ ፣ እና
የትዝታው ንጉሥ ጋሽ ማህሙድ አህመድ እና ሌሎችም የኪነጥበብ ሰዎች በጠበብ ዙሪያ ይታወሳሉ ።
በኋላም ለዓመታት ተረግዞ በውስጣቸው አድጎ የነበረው አሀዱ ሬዲዮ ቀኑን ቆጥሮ ተወለደ። የወለዱትና የዘሩት ማደጉ
አይቀርምና ከአቶ እሸቱ በላይ ጋር በመሆን አሀዱ ሬዲዮን አስቀጥለው
ጣቢያው በጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ መመራት ጀመረ ።
ይህ ብርቱ ጋዜጠኛ የብዙ ሰርተፊኬቶች ባለቤት እና
ብዙ እውቅናዎችን ያገኘ ሲሆን
በሁለት ሺህ አሥር (2010) ዓ.ም የበጎ ሰው እጩ
ተሸላሚ ለመሆን በቅቷል ። በቅርቡ ደግሞ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ማሕበር ፕሬዚደንት በመሆን ተሹሟል ። የኢትዮጵያ
ቅድስት ቤተክርስቲያን በኩረ ትጉኃን የሚል ማዕረግንም አጎናጽፋዋለች።
ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ በአሁኑ ሰዓት የአሀዱ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆኖ እያገለገለ ያለ ጠንካራ እና ትጉህ ባለሙያ ነው።
ይህ የሚመራው የመገናኛ ብዙሃን ተቋም በአይነቱም ሆነ በይዘቱ በብዙዎች ዘንድ ተመራጭና ተደማጭ የሆነ ጣቢያ መሆኑ
የማይካድ ሐቅ ነው። ይህ እንዲሆን ያስቻለውም ጥበቡ በህይወት መንገዱ ይዞት ከመጣው የዳበረ ልምድና አቅም መሆኑ አያጠራጥርም ።
ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ ከተወዳጅ ሚዲያ ጋር በነበረው ቆይታ እንዲህ ይላል።
' የሀገሬ ኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ሙያ ጉዳይ ፤ የህትመት
ሚዲያው መቀዛቀዝ ፤ የብሮድካስት ሚዲያዎቹ ሰብሮ መውጣት አለመቻል ያሳስበኛል ። ነገርግን አንድ ቀን ትንሳኤያቸው ይመጣል የሚል
ተስፋ አለኝ። እኔም በሙያዬ እያገለገልሁ እቆያለሁ ።
በዚህ ሁሉ ችግር ውስጥ እየታገልኩ ህይወቴን ያቆየሁት ሙያውን ስለምወደው ነው ። በህይወት በሙያዬ አብራችሁኝ የተጓዛችሁትን
ሁሉ አመሰግናለሁ ። ኤሚ እንግዳ፣ እሸቱ በላይነህ ፣ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ ዶ/ር ቆንጅት ፈቀደ ፣ ዶ/ር ሽመልስ ተክለጻድቅ ፣
ሙሉጌታ አያሌው ፣ አብይ ደምለው ፣ አዳነች አበራ ፣ የተወዳጅ ሚዲያ ዋና ሥራ አስኪያጅ እዝራ እጅጉ እጅግ አመሰግናለሁ ። " ይላል ብርቱው ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ።
መዝጊያ ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ የኢንሳይክሎፒዲያ ቦርድ አቋም የሚንጸባረቅበት ነው ››
ጥበቡ በለጠ በጣም የሚናፈቅ ሰው ነው፡፡ ብዙዎች እውቀትን
ከእርጋታና ከትህትና ጋር ያደለው ሲሉ ይገልጹታል፡፡ በሚገባ ያነባል፡፡ ያነበበውንም ተንትኖ የማስረዳት ልዩ ክህሎት አለው፡፡ ጥበቡ
በልጅነቱ አንስቶ ወዶት የኖረውን የስነ-ጽሁፍና የጋዜጠኝነት ሙያ ዛሬም አስቀጥሎታል፡፡
ጥበቡ ለታሪክ የተፈጠረ ብቻ ሳይሆን የቆዩ ታሪኮችን
ቦታው ድረስ ሄዶ የተካፈለ በሚመስል መልኩ ሲያወራ የማሳመን ድንቅ
ክህሎት አለው፡፡ በአንድ በኩል ጥበቡ ተሰሚነት ያለው ተናጋሪ ነው፡፡ ጥበቡ በተለይ በቆዩ የሀገራችን ሰዎችና ታሪካዊ ስፍራዎች
ዙሪያ ጥልቅ ጥናት ያደረገ በመሆኑ ብዙዎች ከጥበቡ እውቀት ተጠቅመዋል፡፡
ጥበቡ በለጠ በሰራባቸው ቦታዎች ሁሉ መልካም ስም ይላበሳል፡፡ የኮሚኒኬሽን ክህሎቱ ደግሞ በብዙዎች የሚደነቅ ስለሆነ
በቀላሉ ሰዎችን ለመርዳት እና ልምዱን ለማካፈል አይቸግረውም፡፡ በኢትዮጵያ
የሚድያ ታሪክ በ1990ዎቹ መጀመሪያ ጎልተው ከወጡ ባለሙያዎች መካከል ጥበቡ አንዱና ቀዳሚው ነው፡፡ ጥበቡ ብዙ ሲያነብና አዳዲስ
እውቀቶችን ሲፈልግ ነው ዘመኑን ያሳለፈው፡፡ ተወዳጅ ሚድያ እንደ ጥበቡ አይነት የሰው መውደድ ያለው ፤ ሞገስን የተላበሰ
በሚሰራው ስራ የሚያኮራ አብረውት በሰሩት ሰዎች ዘንድ ሁሌም የሚመሰገን
ሰው ነው፡፡ እናም አዲሱ ትውልድ ልፋቱን እንዲያውቅለት የህይወቱን ገጽ መጥነንና አሳጥረን አቅርበናል፡፡
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ