161. ተገኘ ጃለታ ፈይሳ
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን፣ በቅርቡ
መዝገበ-አዕምሮ / ኢንሳይክሎፒዲያ / በሚል ርእስ የሚድያ እና የኮሚኒኬሽን ባለሙያዎችን ታሪክ በጠንካራ ሽፋን መጽሀፍ አሳትሞ
ያስመርቃል፡፡ ታሪካቸው በመጽሀፉ ውስጥ ከሚሰነድላቸው አሻራ ካኖሩ የሚድያ ሰዎች አንዱ ተገኘ ጃለታ ሲሆን ተገኘ በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ መስማት ለተሳናቸው የቲቪ ፕሮግራም ሲጀመር ቀዳሚው በመሆን
አንድ ያለው ተገኘ ነበር፡፡ በዚህም ትልቅ አሻራ በማኖሩ ያበረከታቸውን በአጭሩ እነሆ ብለናል፡፡
መርካቶ /አዳራሽ/ የከተማ አውቶብስ መናኸሪያ
ማለዳ ነው። ለስምሪት የመጡት የከተማ አውቶበሶች ስራቸውን ከመጀመራቸው በፊት መርካቶ መሀል /አዳራሽ/ በመሰባሰብ ሞተራቸውን ያሟሙቃሉ። በግምት 12 አመት ያልበለጠው ታዳጊ ህጻን ተገኘ ጃለታ አክስቶቹን ለመጎብኘት ወደ ሰበታ ለማቅናት በማሰብ 26 ቁጥር አውቶብስን ለመያዝ ሰልፉን ይዞ ይጠባበቃል። በዚህ መሀል ነው ታዲያ ከተለመደው የመርካቶ ጫጫታ ወጣ ያለ ጩኸት የሰማው። የተፈጠረውን ነገር ለመረዳት ጊዜም አልፈጀበትም።
ተገኘ ከቆመበት በግምት 30 ሜትር ላይ አንዱ የከተማ አውቶቡስ በኋላ ማርሽ ጉዞ ጀምሯል። ነገር ግን ሾፌሩ ከበስተኋላው የቆመውን ማየት የተሳነው የኔቢጤ አላስተዋለውም ነበረ። ይህንን የተመለከቱ ሰዎች ሰውየውን ለማዳን እየጮሁ ሾፌሩን መጣራት ጀመሩ። አውቶብሱም የኋልዮሸ ጉዞውን አላቆመም፤ ማየት የተሳነውም ከቆመበት አልተንቀሳቀሰም።
ይህ በሆነበት ቅጽበት ነው ታዳጊው ህጻን ተስፈንጠሮ ማየት ወደተሳነው ሰውዬ መሮጥ የጀመረው። ተንደርድሮ እንደደረሰም ሰውየውን ባለ በሌለ ኃይሉ መጎተት ጀመረ። ምን መአት እንደመጣበት ግራ የተጋባው ግለሰብ ከተገኘ ጉተታ ለማምለጥ ባደረገው ራሱን የመከላከል ርምጃ ቅጽበት ተገኘ በአውቶብሱ ጫፍ ተገፍቶ ቢወድቅም፣ ማየት የተሳነውን ዜጋ ከአደጋው ለመታደግ ችሏል፡፡ ይህንን አጋጣሚ ሲመለከቱ የነበሩ ሰዎችም ተሯሩጠው ተገኘን ከወደቀበት በማንሳት ደህና መሆኑን ካረጋገጡ በኋላ ማየት ለተሳነው ሰው ሁኔታውን አብራሩለት።
“ በዚያች ቀን “ ይላል ተገኘ ሲናገር “ በዚያች ቀን የተሰማኝ ደስታ እስከዛሬ አልረሳውም። ማየት የተሳነው ግለሰብን ሊፈጠር ከሚችለው አደጋ ለመታደግ ላደረግኩት ትንሽዬ ጥረት የተቸሩት የምስጋና አበረታች ቃላትና በውስጤ የተፈጠረው መንፈሳዊ እርካታ በቃላት ለመግለጽ ያዳግተኛል። እንዲሁም ወላጆቼ ለሰው ልጅ የሚጠቅም ተግባራት ማከናወን ምንኛ ጠቃሚ እንደሆነ ከሚናገረው አመለካከት ጋር ተዛማችነቱን አስረገጠልኝ ። በዚህ ለጋ እድሜ ይህንን ሰናይ ተግባር ማከናወን መቻሌ ለወደፊቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቴ መሰረት የጣለ እንደሆነ ነው የሚሰማኝ።
“
ተገኘ፣ ደራሲ ከበደ ሚካኤል
እና የእሁድ
ጠዋት የሬድዮ
ፕሮግራም
አዲስ አበባ /አራት ኪሎ/ ልዩ ስሙ እሪ በከንቱ ሰኔ
2/1962 ለተወለደው ተገኘ ጃለታ ከኪነ-ጥበብ ጋር ትውውቁ ገና በለጋነት ዕድሜ እንደሆነ ዛሬ ላይ ያስታውሳል።
እናቱ ወ/ሮ መስታወት እስጢፋኖስ የቤት እመቤት ሲሆኑ አባቱ አቶ ጃለታ ፈይሣ ደግሞ በኢትዮጵያ የሆቴሎች ታሪክ የመጀመሪያ በሆነው የጣይቱ ሆቴል ሰራተኛ ነበሩ። የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን ፒያሳ እሚገኘው ዓለም ብርሀን፣ አፍሪካ አንድነትና አራትኪሎ ፓርላማውን አለፍ ብሎ እሚገኘው በዓታ ገዳም ት/ቤቶች የተከታተለ ሲሆን፣ ከት/ቤት መልስ እዛው አባቱ መሳሪያቤት ያሳልፍ ነበር። በኮከበጽባሕና በምስራቅ አጠቃላይ ት/ቤቶች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በሚከታተልበትም ወቅት ጣይቱ ሆቴልን መጎብኘት አላቋረጠም። ሁለተኛ ቤቱም ነበር።
ደራሲና ባለቅኔ ከበደ ሚካኤል ለረጅም አመታት ጣይቱ ሆቴል ውስጥ ይኖሩ ነበር። የቡና ስኒ እና መጽሐፍ ከእጃቸው እንደማይለይ ተገኘ ያስታውሳል። በጊዜው ደራሲ ከበደ ሚካኤል ትልቅ መጽሐፍ የጻፉ የተከበሩ ሰው መሆናቸውን እንጂ የጻፉትን መጽሐፍ በውል ለይቶ አያውቅም ነበር። ኋላ ላይ ነበር አባቱ ወመዘከር /ቤተ መጽሐፍት/ ይዘውት በመሄድ የእርሳቸውን ሰራዎች እንዲያነብ ያደረጉት።
ወትሮም በውስጡ የማንበብ ፍቅር የነበረው ታዳጊ ይበልጥ እርሳቸውን እየተመለከተ የንባብ ፍቅሩ ጨመረ። እንደ እርሳቸው ደራሲ መሆንን መመኘት ጀመረ።
የእሁድ ጠዋት የሬድዮ ፕሮግራም እና የቅዳሜ ጠዋት የልጆች ክፍለ- ጊዜ ቋሚ አድማጭ ከመሆንም ባሻገር አንዳንድ ጽሁፎችን ለልጆች ክፍለ ጊዜ በመላክ መሳተፍን ቀጠለ።
1978 ዓ/ም ለተገኘ ጃለታ ልዩ አመት ነበር። የሽፋን ሰዕል ያለቀለት የአጫጭር ልበ-ወለድ ሥራዎቹን አሰባስቦ ለህትመት እንዲበቃለት ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ያስገባው በዚሁ ዓመት ሲሆን የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ተባባሪ አባል በመሆን በወቅቱ የማህበሩ ሊቀመንበር የሆኑትን ሌላውን ደራሲና ባለቅኔ ደበበ ሰይፉን ለመተዋወቅ እድል ያገኘበት አመት ነበር።
በአስራ ዘጠኝ ሰማንያዎቹ መጀመሪያ ላይ በሚኖርበት ቀበሌ የወጣቶች ማህበር አባል በመሆን በድራማና ሥነ-ጽሁፍ ኮሚቴ ተሳትፎ ማድረግ ጀመረ። በተለያዩ መድረኮች ላይ የሥነ-ጽሁፍ ሥራዎቹን ከማበርከቱም ባሻገር ተውኔቶችን በመጻፍና በመተወን የተሳትፎ አድማሱን አሰፋ። ሥራዎቹን በሚያቀርብበት አንድ መድረክ ላይ የተሳተፈ አንድ የወጣቶች ማህበር ተወካይ የኢሰፓ ካድሬ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ እስከ አሁን አይረሳውም። “ የወጣቶችን ቀልብ ያገኘኸው ስራዎችህ ቀልድና ቧልት ስለሚበዛው ነው። ስለአብዮቱ ምንም አለማለትህ ጥያቄ አስነስቶብሀል። ስለዚህ እርምጃህን አስተካክል''
በርካታ ደራስያንና ተዋናዮችን ባፈራውና በአዲስ አበባ ባህልና ስፖርት ቢሮ አዘጋጅነት በ1982 ዓ/ም ለመጀመሪያ ገዜ የተሰጠውን የሥነ ጽሁፍ ስልጠናም ተከታትሏል፡፡
አጋፔ ኪነጥበብ አገልግሎት 1986
ገና ከምስረታው ጀምሮ በሀገሪቱ ለመጀመሪያ ግዜ በተቋቋመው የአጋፔ መንፈሳዊ ኪነ ጥበብ አገልግሎት ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጻኦ ማድረግ የጀመረው በ1986 ዓ/ም ነበረ። አርቲስት አውላቸው ደጀኔ እና አርቲስት ኤልሳቤጥ መላኩን የመሳሰሉ ታላላቅ አርቲስቶች በአባልነት ባቀፈው በዚሁ የቲያትር ዘርፍ በሰብሳቢነት፣ በጸሃፊ ተውኔት፣ በአዘጋጅነትና በመሪ ተዋናይነት አገልግሏል።
እንዲሁም በወንጌላውያን አብያት ክርስቲያናት ዘንድ የመጀመሪያ የሆነውን ባለሙሉ ሰአት የመድረክ ተውኔት በከፊል በመጻፍ በማዘጋጀትና በመሪ ተዋናይነት በመሳተፍ በፕሮፌሽናል መድረክ ማለትም በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የትያትርና የባሕል አዳራሽ እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ድህረ ምረቃ አዳራሽ ለሕዝብ አቅርቦአል። እዚህጋ በከፊል በመጻፍ የሚለው አግባብ የሚከተለውን ሃሳብ ያንጸባርቃል። / አርቲስት ኤልሳቤጥ መላኩ ከአንድ የእንግሊዝኛ መጽሓፍ ላይ ያነበበችውን ተውኔት መሰረተ ሀሳብ መነሻ አድርጎ አዳብሮና አስፋፍቶ ነው ተገኘ የጻፈው/
በፈረንጆች አቆጣጥር በ1862 ቪክቶር ሁጎ ጽፎት ገናና የሆነውን /Les Miserables/ ታሪክ ቀንጥቦ አንድ የፈረንጅ ጸሃፊ ወደተውኔት የለወጠውንና የአርቲስት ስዩም ተፈራ የተረጎመውን '' የመቅረዙ ሻማ '' የተሰኘውን የሙሉ ሰአት ተውኔት በማዘጋጀትም በብሄራዊ ቲያትር ለሕዝብ አቅርቦአል።
መስማት
የተሳናቸው፣ ምልክት
ቋንቋና የአባቱ
ህልፈተ ሕይወት
የምልክት ቋንቋ እና ተገኘ የተዋወቁት 1983 መገባደጃ ላይ ነው። በአማኑኤል ባፕቲስት ቤተ ክርስቲያን የተሰጠውን የመሰረታዊ ምልክት ቋንቋ ስልጠና በወሰደ ጊዜ መስማት የተሳናቸውን ወገኖች በቤተ- ክርስቲያን ውስጥ ከማገልገል ያለፈ ሕልም አልነበረውም። ጥቅምት 1984 መገባደጃ ላይ
የተፈጠረው ክስተት ግን ይህንን ሃሳቡን በድንገት እንዲለውጥ አስገደደው።
አባቱ በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን ተከትሎ ተገኘን የማስተዛዘኑን ከፍተኛ ሚና የተጫወቱት በአጭር ግዜ ውስጥ የተዋወቃቸው መስማት የተሳናቸው ጓደኞቹ ነበሩ። በዚሁ የማስተዛዝን ሂደት በቀልድ እያዋዙ ባለመስማታቸው ምክንያት የሚደርስባቸውን የእለት ተዕለት ገጠመኞች ያካፍሉት ነበረ። በተለይ በ1983 የኢሕአዲግ ሃይሎች የደርግን መንግስት ለመጣል ወደ አዲስ አበባ ባደረጉት እንቅስቃሴ ባለመስማታቸው ምክንያት ለሞት የተዳረጉ መስማት የተሳናችው ወገኖች መኖራቸውን ሲሰማ እጅግ ማዘኑን አሁን ላይ ያስታውሳል። እየቀረባችው በሄደ ቁጥር ያሉባቸውን ዘርፈ- ብዙ ውስብስብ ችግሮች ተረዳ። በዚህም አላበቃም። መስማት የተሳናቸውን ወገኖቹን ለመርዳት የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት ከራሱ ጋር ቃል ገባ።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱን ሀ ብሎ የጀመረው በቤተክርስቲያን ውስጥ የማስተርጎም አገልግሎት በመስጠት ሲሆን በቀጣይነት በኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማህበር ውስጥም በትርጉምና በልዩልዩ ኮሚቴዎች መሳተፍ ጀመረ። የአገልግሎቱን አድማስ በማስፋት መንግስታዊ እና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም በግለሰብ ደረጃ መስማት ለተሳናቸው የትርጉምና የምክር አገልግሎት በነጻ ማከናወኑን ገፋበት። በማህበሩ ውስጥ የነበረው የመዋእለ ሕጻናት ት/ቤትም አገልግሎት ከሰጠባቸው ዘርፎች ይጠቀሳል። እንዲሁም ከአንደኛው አለም አቀፍ መስማት የተሳናችው ሳምንት ክብረ በአል አንስቶ በበዓል አዘጋጅ ኮሚቴ ውስጥ ለበርካታ አመታቶች አገልግሎአል።
በሀገሪቱ ለመጀመሪያ ግዜ የምልክት ቋንቋ ቴሌቪዥን ሥርጭት መጀመር
የመስማት የተሳናችው ወገኖችን ዘርፈ ብዙ ችግር ለመቅረፍ የትርጉም አገልግሎት በመስጠት የመግባቢያ ድልድይ መሆን አንድ ነገር ሲሆን የመረጃ ጥማታችውን ምላሽ መስጠት ደግሞ ወሳኝ መሆኑን በማመን ቀጣይ አጀንዳው አድርጎ ተንቀሳቀስ። ለዚህም ብቸኛው አማራጭ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ማስጀመር እንደሆነ በማመን፣ ጥናቶችንና ቅድመ ዝግጅቶችን አደረገ። ከፍተኛ የሆነ የኪነጥበብ ተሰጣኦ ያላቸውን መስማት የተሳናቸው ወጣቶች በማሰባሰብና በማሰልጠን የዝግጅቱ አካል እንዲሆኑ አመቻቸ።
ብዙዎች ባለስልጣናትን ማነጋገርና ማሳመን፣ የብዙዎችን በር ማንኳኳት እንዲሁም ረጀም ውጣ ውረድን ማለፍ ጠይቆታል። ነገር ግን ተስፋ አልቆረጠም፡፡ ተሳካለትና በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነው የምልክት ቋንቋ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ጥቅምት
14/1987 ለ30 ደቂቃ ያህል በአየር ላይ ዋለ። የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የአየር ግዜውን ከመፍቀድ ውጭ የተገኘ ጃለታን ወጪ ለመጋራት ፈቃደኛ አልነበረም።
የናሙና ፕሮግራሙ መስማት ከተሳናቸው፣ ከቤተሰቦቻችው እና ከደጋፊዎቻቸው ከፍተኛ ተቀባይነት ቢያገኝም የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ፕሮግራሙን በቋሚነት ለመጀመርም ሆነ ወጪውን ለመሸፈን አልፈለገም። እንዲያም ሆኖ ተስፋ ያልቆረጠው ተገኘ፤ ከጥቅምት 14/1987 ጀምሮ ፕሮግራሙ በቋሚነት እስከተጀመረበት የካቲት 28/1990 ዓ/ም ግዜ ድረስ መስማት የተሳናቸው ወገኖችን የተመለከቱ የተለያዩ ፕሮግራሞችን ያለ ምንም ክፍያ ሰርቶ ለቴሌቪዥን አየር ሰአት አብቅቷል።
ቤተሰብ
መስማት የተሳናቸው
ኪነጥበባት ክለብ ምስረታ
በመጀመሪያው የምልክት ቋንቋ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ የተሳተፉትን መስማት የተሳናቸውን አርቲስቶች በማሰባሰብ በሃገሪቱ የመጀመሪያ የሆነውን የመስማት የተሳናቸውን ኪነጥበባት ክለብን የመሰረተውም በዚሁ በ1987 ዓ/ም ነበረ። 'ቤተሰብ' የሚለውን ስያሜ ያወጣው ይድነቃቸው ሽዋዘመድ የተባለ መስማት የተሳነው አርቲስት ሲሆን ትርጓሜውን ሲያስረዳ 'ሰሚውም ሆነ መስማት የተሳነን የአንድ ዓለም፣ የአንድ ቤተሰብ አካል ነን። አንዳችን ላንዳችን እናስፈልጋለን' ይላል።
ተገኘ ጃለታ ክለቡን በዳይሬክተርነት ለረጅም ዓመታት የመራ ሲሆን በሕይወት የሌለው አበራ ቱጁባን ጨምሮ አሚና ሳኒ፣ እጽገነት አሸብር፣ ዮሴፍ የማነ፣ ዳንኤል ፍቅሬ፣ ንጉሴ ሞገስና ነቢዩ ጌታቸው መሰራች አባላት ናቸው።
የመስማት የተሳናቸውን እምቅ የኪነጥበብ ችሎታ በቴሌቭዥንና በተለያዩ መድረኮች ከማስተዋውቅ በተጨማሪ በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን '' የመስማት የተሳናቸው ኪነጥበብ ፌስቲቫል '' አካሂዶአል። አርቲስት ኤልሳቤጥ መላኩና አርቲስት ሥዩም ተፈራ በአማካሪነት ክለቡን ያገዙ ሲሆን ሚስ ካሪን አስፕሉንድ፣ አርቲስት ፍቃዱ ተ/ማርያም እና አርቲስት አለሙ ገብረአብ አባላቶችን በማሰልጠን ከፍተኛ አስተዋጻኦ አድርገዋል።
መስማት ለተሳናችው ጸረ- ኤድስ ትምህርት
1988 ዓ/ም። ወቅቱ ኤች አይቪ ኤድስ ዓለምን የሚያምስበት ግዜ ነበረ። የመገናኛ ብዙሀን ባጠቃላይ ማለት ይቻላል ቅኝታችው አንድ ዓይነት ሆኖአል። ጸረ ኤች አይቪ ኤድስ ትምህርቱ ላይ አተኩረው ቅስቀሳውን ተያይዘውታል። ነገር ግን አንድ ትልቅ የህብረተሰበ አካልን ዘንግተዋል። መስማት የተሳናችውን።
ተገኘ የህንን ለማስተዋልግዜ አልፈጀበትም። '' መስማት የተሳናቸው የእኛው አካል ናቸው። በተመሳሳይ ዓለም የምንኖር የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ነን። እናም እነርሱን ያገለለ ጸረ ኤች አይቪ ኤድስ ትምህርት ውጤት አልባ ነው።'' የሚለውን መሰረተ ሃሳብ ይዞ መንቀሳቀስ ጀመረ። በወቅቱ 'ኦሳ' ወደሚባለው ድርጅት በማቅናት ምክክሮችን አካሄደ። በአሜሪካን የተራድኦ ድርጅት /ዩኤስ ኤይድ/ ፕሮጀክት አካል ወደሆነው እና /ኤድስ ካፕ/ ወደተባለው መስሪያ ቤት አቀና። እንዲሁም አባል በሆነበትና ቤዛ ለወገን በተሰኘ ሀገር በቀል ግብረ-ሰናይ ድርጅት ጋር
አብሮ ለመስራት ከስምምነት ላይ ደረሰ።
አሁንም በሃገሪቱ ለመጀመሪያ ግዜ ከተለያዩ መስማት የተሳናችው ከሚሰሩባቸው ተቋማትና ትምህርት ቤቶች ለተውጣጡ 20 ለሚሆኑ መስማት ለተሳናቸውና አስተርጓሚዎች ለሁለት ሳምንት የአሰልጣኞች ስልጠና በማካሄድ ፕሮጀክቱን ሀ በሎ ጀመረ። በዚሀም አላበቃም። ሰልጣኞቹ የኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማሕበርን ጨምሮ በመላው አዲስ አበባ መስማት የተሳናችው በሚገኙባቸው ተቋማት በመዘዋወር በሺዎች ለሚቆጠሩ ወገኖች የጸረ -ኤች አይቪ ኤድስ ዘመቻቸውን አከናወኑ።
ተገኘ አሁንም አላረፈም። በ1989 የዚህኑ ፕሮጀከት ክፍል ሁለት ለየት ባለ መልኩ በመቅረጽ መስማት የተሳናቸውን በጸረ ኤች አይቪ ኤድስ ትምህርት መድረሱን አጠናክሮ ቀጠለ። የመድረክ የሙሉ ሰአት ተውኔት በመጻፍ፣ በማዘጋጀትና በመተወን ለዕይታ አበቃ፡፡ በዚሁ በአይነቱ የመጀመሪያ በሆነው የሙሉ ገዜ የመድረክ ድራማ መስማት የተሳናቸው እና መስማት የሚችሉ ተዋንያን በጋራ የተሳተፉበት ከመሆኑም ባሻገር በድምጽና በምልክት ቋንቋ በማቀነባበር የቀረበ ነበር።
በሀገሪቱ
ለመጀመሪያ ግዜ የምልክት ቋንቋ ቴሌቪዥን ሥርጭት
በቋሚነት መጀመር
ከበርካታ አመታት እልህ አስጨራሽ ትግል በኋላ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የሥራ ኃላፊዎች ተገኘ ያቀረበውን እቅድ ሙሉ በሙሉ በመቀበል ፕሮግራሙን እንዲጀምር መንገድ ጠረጉለት። እናም ጥረቱ ፍሬ አፍርቶ ቅዳሜ የካቲት 28/ 1990 ዓ/ም በቋሚነት የምልክት ቋንቋ ሥርጭት ተጀመረ። እንደ 1987ቱ ሁሉ የቴሌቪዥን የምልክት ቋንቋ ስርጭቱ ሲጀመር የዜና እና የፕሮግራም አቅራቢውም ሆነ አዘጋጁ እራሱ ተገኘ ጃለታ ነበር።
የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን ከተቀላቀለ በኋላም አርፎ አልተቀመጠም። ሁሉም የቴሌቪዥን ፕሮግራም ፎርማቶችን በአግባቡ ከቃኘ በኋላ ሌላ አጀንዳ ይዞ ኃላፊዎችን መወትወት ጀመረ። አንዳችውም የማህበረሰቡ አንድ አካል የሆኑት አካል ጉዳተኛ ወገኖቻችንን ጉዳይ የሚዳስስ ይዘት ያለው የፕሮግራም ሽፋን ስላልነበራቸው ይህንን ክፍተት ለመሙላት ተነሳሳ። ቀላል ከማይባል ውጣ ውረድ በኋላ ተፈቀደለትና የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ በተለያየ ፕሮግራምች ውስጥ ሽፋን መስጠት ጀመረ። መደበኛ ዜና፣ ልዩ ዝግጅት፣
120 የመዝናኛ ዝግጅት፣ የልጆች ክፍለ ግዜ፣ ከየአቅጣጫው፣ ለወጣቶች፣ ሴቶች ወዘተ... ፕሮግራሞች ላይ የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ የሚዳስሱ ስራዎቹን አቅርቦአል።
ከብዙዎቹ መሀከል
1, የምልክት ቋንቋ ፣ የአካል ጉዳተኛ ሴቶች ተደራራቢ ችግርና የልዩ ፍላጎት ትምህርት /special needs education/ ትኩረት እንዲያገኝ
2, ኢትዮጰያ ሃገራችን አለም አቀፉን የአካል ጉዳተኞች መብት ኮንቬንሽን እንድትፈርም እንዲሁም የኦታዋ ትሪቲ በመባል የሚታወቀውና የጸረሰው ፈንጂን ማምረት፣መጠቀምና ማዘዋወር የሚያግደውን ስምምነት ፈራሚዋ ሀገራችን በፓርላማ እንድታጸድቅ
3, የጸረ ሰው ፈንጂን በሰው ልጆች ላይ የሚያደርሰውን ዘግናኝ የአካል ጉዳት ለማሳየት ከአለም የቀይ መስቀል ኮሚቴ ጋር በመተባበር ዘጋቢ ፊልም ማዘጋጀት። / የህንኑ ስራ ለማከናወን በ1992 ዓ/ም የጦርነት ቀጠና በሆኑት በባድመ፣ ዛላንበሳና ሸራሮ በአካል ተገኝቶአል/
4, ከአንደኛው ታላቁ ሩጫ ጀምሮ የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎ በቀጥታ ስርጭት ማካተት
5, የኤች አይቪ ኤድስና ሌሎች ጤና ነክ ጉዳዮችን ሰፊ ሽፋን መስጠት
6, የልዩ ልዩ ክህሎት ባለቤት የሆኑ አካል ጉዳተኞችን አኗኗር የተመለከቱ ሥራዎችን ለአየር ማብቃት
7, በሃገራችን የመጀመሪያ የሆነውን የልብ ሕሙማን ሆስፒታል ለመገንባት የአንድ ብር ለአንድ ልብ ዘመቻ ሲጀመር በሚዲያና ኮሚኒኬሽን ኮሚቴ ከማገልገል ባለፈ የዘመቻውን መጀመር የሚያበስረውን የግማሽ ሰአት ልዩ ዝግጅት በመስራት ለአየር ማብቃት ወዘተ .... ከብዙዎቹ ጥቂቶቹ ናቸው።
ምርጫ 1997
በ1997ቱ ምርጫ ሁለት አበይት ተግባራትን መፈጸሙን ይናገራል፡፡
ምርጫው እየተቃረበ ሲመጣ የፖለቲካ ተፎካካሪዎችም ሆኑ ገዢው ፓርቲ በሚያካሂዱት ክርክር አንዳቸውም አካል ጉዳትን የተመለከተ ሃሳብ ሲሰነዝሩ ባለመስማቱ አንድ ሃሳብ መጣለትና ይህንኑ ይዞ ወደ ቲቪ ሥራ አስኪያጅ ቢሮ ጎራ አለ። በወቅቱ አጠቃላይ የሕዝብ ቁጥር 12 በመቶ በላይ የሚሆኑ አካል ጉዳተኛ ኢትዮጵያውያን መኖራቸውን፣ይህም ሲሰላ የበርካታ ሚሊዮኖች ደምጽ ማለት እንደሆነ፣ እናም ይህንን ማሕበረሰብ በምርጫው ተሳታፊ እንዲሆን ትኩረት መሰጠት እንዳለበት ሞገተ። ብዙ ውጣ ውረዶችን ቢጠይቀውም በስተመጨረሻ በምሽት ልዩ ፕሮግራም የአየር ግዜ ተፈቀደለት።
በዕቅዱም መሰረት የአካል ጉዳተኛ ማህበራት ተወካዮችን ስቱዲዮ በመጋበዝ ከገዢው እና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ፊትለፊት በማፋጠጥ እጃችሁ ከምን ሲል ጠየቀ፣ አከራከረ። /ዝግጅቱ ከተላለፈ በኋላ በሥራ አስኪያጁ ተጠርቶ ወፈር ያለ ወቀሳና ማስጠንቀቂያ እነደተሰጠው ያስታውሳል።/
የምርጫውን ውጤት ይፋ መደረግ ተከትሎ በሃገሪቱ የተነሳው ረብሻና ብጥብጥ አሁንም ለተገኘ ሌላ ራስ ምታት ፈጠረበት። በእንደዚህ አይነት ሁኔታ መስማት የተሳናቸው ግንባር ቀደም ተጠቂ መሆናቸውን ጠንቅቆ ያውቃል። ለዚህም በ1983 ዓ/ም የኢህአዴግ አማጽያን አዲስ አበባን ሲቆጣጠሩ '' ቁም '' የሚለውን ድምጽ ያልሰሙ መስማት የተሳናቸው ላይ የደረሰባቸውን ያስታውሳል።
እርሱ የሚያዘጋጀው የምልክት ቋንቋ ፕሮግራም ዘወትር ቅዳሜ በሳምንት አንድ ግዜ ብቻ ይቀርብ ስለነበር በእንደዚህ አይነት አስቸኳይ ሁኔታዎች ዘግይቶ ደራሽ መሆኑን በመገንዘብ መላ ፈለገ። እናም ከቅርብ አለቃው ጀምሮ እስክ ሥራ አስኪያጁ ቢሮ ድረስ በመሔድ ሁኔታዎችን አስረዳ፡፡ '' ከመንግስት የሚተላለፉ መመሪያዎችና የአስቸኳይ ግዜ አዋጆች መስማት ለተሳናቸውም ወዲያውኑ ተተረጉመው መቅረብ አለበት'' በማለት ወተወተ።
ረበሻው እየተስፋፋ ሄደና ጉዳዩን አስመልክቶ የወቅቱ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ለሕዝብ ንግግር እንደሚያደርጉ ሰማ። ግዜም አላጠፋ። ወዲያውኑ ለአለቆቹ ሁኔታውን በማስረዳት የጠቅላይ ሚንስትሩን ንግግር በቀጥታ ሥርጭት መስማት ለተሳናቸው ወገኖቻችን ለመተርጎም ጥያቄ አቀረበ። ሰሚ ጠፋ። እርሱም ተስፋ ቆረጦ ወደቤቱ ሄደ።
ማምሻላይ ቤቱ ሆኖ ከቤተሰቡ ጋር ራት እየበላ ሳለ ስልክ ተደወለለት፡፡ አለቃው ነበረች የደወለችው። የጠቅላይ ሚንስትሩን ንግግር በቀጥታ እንድታስተረጉም ተፈቅዶአል፡፡ ''ያለችህ ከ40 ደቂቃ ያነሰ ነው። መምጣት ትችላለህ ወይ?''
አላመነታም። በታክሲ እየከነፈ ኢቲቪ ደረሰ፡፡ ስቱዲዮ ሲገባ ከነላቡ ነበረ። ከጥቂት የስቱዲዮ ዝግጅቶች በኋላ የጠቅላይ ሚንስትሩ ንግግር ተጀመረ፡፡ በሀገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ግዜ የአንድ የሀገር መሪ መልእክት በቀጥታ ስርጭት ሲተላለፍ መስማት የተሳናቸውን ባካተተ መልኩ በምልክት ቋንቋ ተተርጉሞ ቀረበ።
አዲስ የምልክት ቋንቋ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አቀራረብ
የምልክት ቋንቋ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ካስጀመረበት ግዜ አንስቶ በርካታ ከሆኑ የውጭ ሀገር ሚዲያዎች ጋር ጠንካራ ግነኙነት ፈጠረ፡፡ በተለይ ዴንማርክ ሀገር /TV Jounalism/ አጥንቶ እና በዛው በዴንማርክ ሀገር በሚገኘው የመስማት የተሳናቸው የቴሌቪዥን ጣቢያ የተግባር ልምምድ ካደረገ በኋላ በፕሮግራሙ ላይ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት ወሰነ። የምልክት ቋንቋ ከንግግር ቋንቋ የተለየ ስርአትና አግባብ ያለው እንደመሆኑ ቀድሞ በዘልማድ በድምጽና በምልክት ቋንቋ አንድ ሰው የሚያቅርብበትን ስርዓት በመለወጥ የሰለጠኑት ሀገራት የሚጠቀሙበትን የህንኑ ዘዴ ተግባራዊ አደረገ። አልተሳካለትም እንጂ የምልክት ቋንቋ ስርጭቱን ለማሻሻል በርካታ እቅዶችን አሰናድቶ ነበረ።
ተጨማሪ አገልግሎቶች
የተገኘ የበጎ ፈቃድ /volunteer service/ አገልግሎት ድንበር የለሽ ነበር። ከ17 በላይ በሚሆኑ በአካል ጉዳተኛ ማህበረስብ ዙሪያ በሚሰሩ ማህበራት፣ ት/ቤቶች፣ የስራ ቡድኖች፣ ክለባትና ማዕከላት በአማካሪነትና በተለያየ የስልጣን እርከን የነጻ አገልግሎት ሰጥቶአል።የአዲስ አበባ አካል ጉዳተኞች ስፖርት ፌዴሬሽንን በምክትል ፕሬዝዳንትነት አገልግሎአል።
በአዲስ ዘመን ጋዜጣና በግል የፕሬስ ውጤቶች ሰለአካልጉዳትና ጉዳተኝነት ብዙ ጽፎአል። ታላቁ ተልእኮ ከሚባል መንፈሳዊ ድርጅት ጋር በመተባብር 'እየሱስ' /Jesus/ ፊልም ያለ ምንም ክፍያ መስማት ለተሳናቸው በምልክት ቋንቋ ተርጉሞአል።
በእነዚህ ሁሉ አገልግሎቶች ባለፈበት ግዜ ብዙ የሚያሳዝኑ፣ ተስፋ የሚያስቆርጡ፣ ሕይወቱን ለአደጋ ያጋለጡ፣ የሚያስደስቱ፣ መንፈሳዊ ርካታን የሚሰጡ ወዘተ ገጠመኞች ባለቤት ነው።
ትላንትን ሲያስታውስ ምን እንደሚሰማው ሲጠየቅ ተገኘ እንዲህ የላል '' በ1983 ከምልክት ቋንቋ እና መስማት ከተሳናችው ጋር በተዋወቅኩበት ወቅት ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ገብተው የትምህርት እድል ያገኙ መስማት የተሳናቸው በጣት የሚቆጠሩ ነበሩ። ዛሬ ላይ የምልክት ቋንቋ ትኩረት አግኝቶ፣ የልዩ ፍላጎት ትምህርት /Special Needs Education/ በበርካታ ዩንቨርስቲና ኮሌጆች እውቅና አግኝቶ ትምህርት የናፈቃችው በርካታ መስማት የተሳናቸው ምሁራንን ማፍራት መቻሉን ሳስብ ልቤ በደስታ የሞላል። እንዲሁም አካል ጉዳትና ጉዳተኝነት ላይ የነበረው ኋላቀር አመለካከትን ለመስበር በተደረጉ በርካታ ጥረቶች ዙሪያ ዘገምተኛም ቢሆን የሚታዩ ለውጦች በልቤ ተስፋን ያጭራሉ''
ሁለት ጓደኞቹ ተገኘን እንዲህ ሲሉ ገለጹት
....... የብዙ ነገር ጀማሪ መሆንህ በራሱ መታደል ነው
.... ወጣት ገና ለጋ ሆነህ፣ ሥራ እንኳን ሳትይዝ፣ መስማት በተሳናቸው ዙሪያ የሰራኸው ስራ አስደማሚ ነው። ገና በጠዋቱ የሰብአዊ መብት ጉዳይ ምንኛ የገባህ እንደሆነ ሳስበው ይገርመኛል። አንተ የሰዎች መብት ላይ መስራት የጀመርክበት እድሜ ማንም ወጣት በቅድሚያ ለራሱ ሥራ የሚፈልግበት ግዜ ነው።....
ተገኘ ጃለታ ከሁለት ልጆቹና ከባለቤቱ ጋር ኑሮውን በሀገረ አሜርካ በኒው ሃምሻየር ስቴት ካደረገ 12 አመታትን አስቆጥሮአል።
የመዝጊያ ሀሳብ ፤ ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የኢንሳይክሎፒዲያ ቦርድ
አባላት አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡
ተገኘ ጃለታ በአሁኑ ሰአት መኖሪያውን በባህርማዶ ያደረገ የምልክት ቋንቋ የቲቪ ፕሮግራም በኢትዮጵያ
እንዲጀመር ፈር የቀደደ የጥበብ እና የሚድያ ባለሙያ ነው፡፡ ተገኘ ታሪኩን እንዳነበብነው አካል ጉዳተኞችን መታደግ የጀመረው ገና
በብላቴና እድሜው ነበር፡፡ ተገኘ በምልክት ቋንቋ ዙሪያ የወሰደውን ስልጠና በመጠቀም በኢትዮጵያ ቲቪ የምልክት ቋንቋ ፕሮግራም እንዲጀመር
ታላቅ ጥረት አድርጓል፡፡ አዲስ ነገር መጀመር ብዙም በማይበረታታበት እንደ ኢትዮጵያ ባለ ሀገር ተገኘ ከዛሬ 24 አመት በፊት ያቀረበው
ሀሳብ አስፈላጊና ወሳኝ ቢሆንም በቀላሉ የሚፈቀድ ግን አልነበረም፡፡ ሰዎች ሲጥሩ አሻራ ማኖር ይጀምራሉ፡፡ አንድን ጉዳይ ከተከለከሉ
በዚያ ጉዳይ ላይ የራሳቸውን ጸጋ ወይም መክሊት ለማውጣት እድሉ ይመጣል፡፡ በተገኘም የስራ ህይወት የሆነው ይህ ነው፡፡ በኢትዮጵያ
ሚድያ ታሪክ ውስጥ መስማት ለተሳናቸው የቲቪ መሰናዶ ያስፈልጋቸዋል ብሎ ወገቡን ታጥቆ የታገለው ተገኘ ነበር፡፡ ለዚህ ደግሞ ታሪክ
ዛሬ ይከፍለዋል፡፡ ህልሙን ማሳካቱ አንድ ነገር ሆኖ የሚነገር ታሪክ ዛሬ ማስቀመጥ ቻለ፡፡ ተወዳጅ ሚድያ የሚነገር ታሪክ ላላቸው
ቅድሚያ ይሰጣቸዋል፡፡ ያሰበና ያወራ ሳይሆን እውን ያደረገ የተግባር ሰው ታሪኩ በነጭ ወረቀት ላይ በክብር ይሰፍራል፡፡ ልክ እንደተገኝ
አይነት፡፡ እንደ ተገኘ አይነት ሰዎች ታሪካቸውን ከትበው እንዲልኩ እናበረታለን፡፡ ሀገር ያለችው የሚሰሩ ሰዎች ውስጥ ነው፡፡ አሊያ
ተራራው ቢቆረስ ፤ ወንዙ ቢከፈል ….. ታሪክ አይኖርም፡፡
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ