160. ሰላማዊት ካሳ -SELAMAWIT KASSA 

 

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን፣ በቅርቡ መዝገበ-አዕምሮ / ኢንሳይክሎፒዲያ / በሚል ርእስ የሚድያ እና የኮሚኒኬሽን ባለሙያዎችን ታሪክ በጠንካራ ሽፋን መጽሀፍ አሳትሞ ያስመርቃል፡፡ ታሪካቸው በመጽሀፉ ውስጥ ከሚሰነድላቸው አሻራ ካኖሩ የሚድያ ሰዎች አንዷ የኮሙኒኬሽን ሚኒስትር ዲኤታ ሰላማዊት ካሳ አንዷ ናት፡፡

የእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህር በመሆን  አገልግላለች፡፡በኢትዮጵያ የቴሌቪዥን መስኮት ዘልቃ ከዜና እስከ ግዙፍ የሀገራችን መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ድረስ በምስልና በድምፅ አስቃኝታናለች። በኋላም በፋና ሬድዮና ቴሌቪዥንም የውጭ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ትንታኔ ስትሰጥ ቆይታለች፡፡  መምህርና ጋዜጠኛ በአሁኑ ወቅት ደግሞ የኢፌዲሪ መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዲኤታ ሰላማዊት ካሳ፡፡ እዝራ እጅጉና ባንቺአየሁ አሰፋ ታሪኳን እንደሚከተለው አቅርብውታል፡፡

 

          ልጅነትና አስተዳደግ

የበርካታ አህጉራዊ ድርጅቶች ዋና መቀመጫ በሆነችው በአፍሪካ መዲና አዲስ አበባ ልዩ ስሙ አሜሪካን ጊቢ አካባቢ ተወለደች።

 

ሰላማዊት ከልጅነቷ ጀምራ የአሜሪካን ግቢ አካባቢ ነዋሪዎችን የአኗኗር ሁናቴ ከቤቷ እስከ ጎረቤቷ ከጎረቤት እስከ አካባቢዋ በጥልቀት ስትመለከት አድጋለች "ማን ይናገር የነበረ ማን ያርዳ የቀበረ " ነውና  የአዱ ገነት ነዋሪዎች ኋላቸውን ለመሸፈን ሲሉ ምንም' ፊታቸውን በባዝሊን ቢያብረቀርቁት እና ሲኦሉን ቢክዱም ነገርግን ለሰላማዊት  ከባዝሊኑ ጀርባ ስላለው ጥልቅ ሚስጥር ስለጓዳ ጎድጓዳቸው የዘገኑት የጥሬ ቅንጣት የተጎነጩት የውኃ ብዛት አንጀታቸውን ያጠበቁበት የመቀነት ዙር ጥምጥም ሳይቀር የሚደበቅ አይደለም።  የረዥም ጊዜ ህልሟ እና ጥሪዋ ሆኖ የቆየውም የብዙሃን ልሳን የመሆን መረጃን ለህዝብ የማድረስና የተለያዩ አካባቢዎችን የማየት ነበር። በተለይም ደግሞ እንደ አሜሪካን ግቢ አይነቶችን።

 

 

 

 

       የጋዜጠኝነት ጉዞ 

 

ሰላማዊት በቋንቋና ሥነጽሑፍ ከተመረቀች በኋላ አንደ አብዛኞቹ ጋዜጠኞች  መሸጋገሪያ ሙያዋ መምህርነት ነበር።  ቅዱስ ዮሴፍ በተባለው የወንዶች ትምህርት ቤት የእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህርት ሆና ሰርታለች።

ከዚያም ወደ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በ2003 በመቀላቀል  በዜና ክፍል ውስጥ የሰራች ሲሆን በበርካታ  ቦታዎች ተዘዋውራም እንደ ህዳሴው ግድብ ያሉ ግዙፍ የመሰረተ-ልማት ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ ዶክመንተሪዎችን ሰርታ ለእይታ አቅርባለች አመታዊ የሃገር እቅድ ምልከታና እና ኦኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይም ተንትናለች። በክልሎች እና በበርካታ የሀገሪቱ ገጠራማ አካባቢዎች ተገኝታ የማህበረሰቡን የአኗኗር ዘይቤና መልካምድራዊ ገፅታ ግንባታ ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ ለመታዘብ ችላለች። ይህም ሀገሪቱን በደንብ እንድታውቅ ያለችበትን ሁናቴ እንድትረዳ እና ወደፊት ምን እንደሚያስፈልጋት እንድትለይ ያስቻላት ነበር፡፡









 

 ሙያዊ አስተዋጽኦ

ሰላማዊት ካሳ፣ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሳለች በ2006 ፤ 3 አመት ስንት ነው? በሚል ርእስ የህዳሴ ግድቡን አስመልክታ ዶክመንተሪ ሰርታለች፡፡ በተጨማሪም፣ አፋር ድረስ በማቅናት የተለያዩ ዘገባዎችን በመስራት የጋዜጠኝነት ሙያዊ አደራዋን ለመወጣት ሞክራለች፡፡ ከአባይ ጋር በተያያዘ ዘገባዎችን መስራት ትልቅ ርካታ የሚሰጣት ሰላማዊት ካሳ ከጉዳዩ ጋር በተገናኘ በቂ የሆነ እውቀት ማግኘት ችላለች፡፡  ሰላማዊት፣ በ2005 ግድም በኢትዮጵያ ቲቪ ትሰራ በነበረ ጊዜ ዲፕሎማሲያችን የተሰኘ ፕሮግራም አየር ላይ ታውል ነበር፡፡

ሰላማዊት፣ በጋዜጠኝነት ሙያዋ በውጭ ጉዳይ እና በመሰረተ ልማት ርእሶች ላይ ፕሮግራምና ዜናዎችን መስራት ያስደስታታል፡፡  የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ ላይ ከ2004 በኋላ  በርካታ ፕሮግራሞችን የሰራች ሲሆን በዚህም እውቀቷን በየጊዜው ከወቅቱ ጋር እንዲጓዝ በማድረግ ሙያዋን ከፍ ለማድረግ ሞክራለች፡፡

ይህች  እንስት ጋዜጠኛ  ከሀገሯ ኢትዮጵያ እስከ አህጉር አፍሪካ ወዲያም ተሻግራ በኢኮኖሚያዊ መሰረተ ልማት ዘርፉ እንዲሁም በሀገራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ እጅግ ድንቅ ሥራን  በመስራት ዓለምን ልዕለ ሀያሏ ሀገር እኔነኝ በማለት ዙፋኑን ለመንጠቅ እየተጋች እስካለችው ሀገረ ቻይና ድረስ ዘልቃ በርካታ ዘገባዎችን፣ የቀጥታ ስርጭት ፕሮግራምና ትንታኔዎችን በስፋት ሰርታለች።

 

ከሁለት ሽህ ሦስት (2003) .   ጀምራ በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ከዜና ክፍል ሪፖርተርነት እስከ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊነት ድረስ የዘለቀችው ሰላማዊት ካሳ ሥራዋን በአስደናቂ ሁኔታ ከውናለች።

 

Developmental Journalism ላይ ትኩረት አድርጋ ስራዋን የጀመረችው ሰላማዊት እግረ-መንገዷን ከፖለቲካዊ ጉዳዮች ጋር መነካካቷ ያልቀረ ቢሆንም በእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የተያዙ ትላልቅና ግዙፍ ሀገራዊና ማህበራዊ የልማት ፕሮጀክቶችን ትኩረት ሰጥታ በስፋት ዘግባለች። የአንድት ሀገር እድገቷ አሽቆለቆለ አልያም ደግሞ ጥሩ  የእድገት አቅጣጫ ላይ ትገኛለች ለማለት ከግምታዊ የኢኮኖሚ ብየና ወጥቶ በየጊዜው ወደ ሕብረተሰቡ የሚፈስ መረጃ መስጠት  ያስፈልጋል።

 

በመሆኑም በእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘርፍ ከመነሻ ጀምሮ ግብና የአፈፃፀም እቅድን ያካተተ መረጃ ለህዝብ በመስጠት የመሰረተልማትና የኢኮኖሚ ዕድገትን በመላው ሀገራችን ኢትዮጵያ ተዘዋውራ በመዘገብ መገናኛ ብዙሃኑ ላይ ለዓመታት ያህል ቆይታ አድርጋለች።  ጋዜጠኛ ሰላማዊት ካሳ በመገናኛ ብዙሃን ላይ በቆየችባቸው ወቅቶች በማክሮ ኢኮኖሚው ዘርፍ የሚፈለገው ኢኮኖሚውና መሰረተ ልማቱ ያሳዩትን የምጣኔ ሀብት እድገት ከዜጎች የነፍስ ወከፍ የገቢ መጠን ጋር በማነፃፀር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት  እንድሁም የመንግሥት የታክስ አሰባሰብ ሂደትን ብሎም የገቢ ወጪ ንግድ ምጣኔ ልውውጥ  መረጃን በአሃዛዊ ቁጥር በማስደገፍ ለህዝብ ይፋ አድርጋለች። በተለያዩ መሰናክሎች የተተበተበውን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በጥልቀት ተረድቶ እየተዘዋወሩ መዳሰስ ለሴቶች አዳጋች ቢመስልም ሰላማዊት ግን ከቁብ ሳትቆጥረው ቀርታለች።

 

በሀገሪቷን የተለያዩ ክፍሎች የሰው ሀብት ልማት በዋነኛነት የትምህርትና ሥልጠና ዘርፉ በመላ ሀገሪቱ ባለው የመማር ማስተማር ሂደት ውስጥ የመምህራንና ተማሪዎች ጥምርታ እንዲሁም የአዳዲስ ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች  የቅድመ-ምረቃ መደበኛ ፕሮግራም  የተማሪዎች ተሳትፎ እና የአዳዲስ ትምህርት ተቋማት ግንባታ ላይ ዘገባዎቿ ያጠነጠኑ ሲሆን ለውጥን መፍጠር የሚችሉ ሲሆኑ ለሀገሪቷ ዕድገት ቁልፍ የሆነውን የቴክኖሎጂ አቅም ግንባታ በቀጥታ እና በሪፖርት ዘገባዎቿ አንስታለች።

 

 አንዱ መሰረተ ልማት መልካም አስተዳርን ማምጣትና ብልሹ አሰራሮችን ማስወገድ ሲሆን ሰላማዊት ከጊዜ ወደ ጊዜ በሀገሪቱ የሚታየውን የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እቅድና ግብ  የአፈፃፀም ደረጃውን ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እስከ  ፋና ዘጠና በዘገባዋ ትንታኔ ሰጥታበታለች። በተጨማሪም  በግብርና ዘርፉ ላይ ያለውን የሰብል ምርት አሰባሰብና ንግድ የንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት የእናቶችና ህፃናት ደህንነት እና የጤና ተቋማት ግንባታ በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎችና የመንግስት ትኩረት፣ የምንዛሪ መዋዠቅ የውጪ ምንዛሪ አቅርቦት እጥረትና የሀገሪቱን የእዳ ጫና አካትቶ የእድገትና ትራንስፎርሜሽኑን እቅድ አፈፃፀም በደረጃ ያሳየ ተዳግሮት የሆኑበትን ደግሞ ያስለየ ዘገባ በመስራት ከቀደሙ ዓመታት ጋር በንፅፅር በማስቀመጥ መግለጫዎችን በመከታተል ጥያቄዎችን በማንሳት እንዲሁም ሀሳቦችን በመሰንዘር ሰፊ መረጃ ተሰጥታለች 

 

 

የሀገር ኢኮኖሚ ዋልታ በመሆን ፈጣንና የተሳለጠ የንግድ  ልውውጥ ለመፍጠር የሚያስችለውን የትራንስፖርቴሽን ዘርፍየአስፋልት መንገድ ሲቪል አቬሽን ባቡር መንገድ ፕሮጀክት ( በተለይም በኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር ዝርጋታ ወቅት) የኢትዮጵያ የባህር ሀይል ትራንስፖርት የንግድ መርከብ እና በተለያዩ የኢንቨስትመንት ልማቶች ላይ የኢኮኖሚውን እድገት በማሳየት የማህበረሰቡን ጥያቄ ያማከለ ፕሮግራም በማዘጋጀትና መረጃዎችን በማቅረብ ለአድማጭ ተመልካቾች ተጨባጭ የሆነ በብዛትም በጥራትም እጅግ በርካታ ዘገባዎችን ሰርታለች።

 

 ጋዜጠኛ ሰላማዊት ካሳ እንደ ሜቴክ ባሉ ትልልቅ የንግድ ኩባንያዎች ላይ ያለውን የኢንቨስትመንት እና ልማት ተሳትፎ እንቅስቃሴ በመዳሰስ ትንታኔና ዘገባዎችን የሰራች ሲሆን በፕሮጀክት የሥራ ስምሪት ወቅት ከሀምሳ አራቱ የአፍሪካ ሀገራት አንዷ ወደሆነችው ምስራቅ አፍሪካዊቷ ኡጋንዳ ተጉዛ የኢትዮጵያ እና ኡጋንዳን የኢኮኖሚያዊ ዲፕሎማሲ ግንኙነት የሚያሳይ ሙሉ ዘጋቢ ፍልም ስትሰራ ወደጎረቤት ሀገር ጅቡቲም ጎራ ብላ የኢኮኖሚ ዘገባዎችን ሰርታለች።

 

 ቀጥላም በአህጉራችን አፍሪካ በከፍተኛ ደረጃ የመሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ላይ ተሳታፊ ወደሆነችው ሀገረ ቻይናም አቅንታለች።  ታዲያ በጉዞዋ ሙያዋን እንደ መሳሪያ በመጠቀም አስደናቂ እና ውስብስብ በሆኑት የቻይና አስፋልት መንገዶቿ ላይ በመራመድ የሥራ ፈጠራ አቅምና ቴክኖሎጂው የፈጠረውን ተጽእኖ እንዲሁም የሥራ ባህልን ቃኝታ ልምድ በመቅሰም ለሀገሯ ኢትዮጵያ አጋርታለች። ስራ በጀመረች በአጭር ጊዜ የህብረተሰቡን ችግሮች የሚያካትቱ ጥልቅ ፍተሻዎችን የሚጠይቁ  ውጤታማ የመሰረተ ልማት ሪፖርት ዘገባዎችን በመስራት ድል ስታደርግ በዲፕሎማሲው ዘርፍም ትልቅ ስራን ሰርታለች።

 

 በባልደረቦቿ ዓይን ጠንካራ፣ ሥራ ወደድና የእቅድ ሰው የሆነችው ጋዜጠኛ ሰላማዊት ካሳ በዓለም አቀፍ የዜና ዘገባዎች ላይ የሴቶች ተሳትፎ እምብዛም ሆኖ ሳለ ከተሰማሩት መካከል በቋንቋ ክህሎትም ሆነ በአሰራር ብስለትና ቅልጥፍና ተመራጭ እንዲሁም አካባቢዋን አህጉሯንና ዓለምን በጥሩ ብቃት የዳሰሰች ብርቱ ሴት ጋዜጠኛ ነች።

 

እንደ ኢጋድ እና የአፍሪካ ህብረት ባሉ የቀጠናው ሀገራት እድገትና አንድነትን በሚያጎለብቱ ኢኮኖሚያዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች ላይ በቀጥታ ስርጭት ዘገባዎቿ  ስራዎችን ሠርታለች።

 

  በአባይ ጉዳይ ወደኋላ ተጉዛ የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር በነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ አማካኝነት የተጣለውን የግድቡን መሰረተ ድንጋይ በማስታወስ ትላንትን ከዛሬ የሚያመሳክርና ለነገ ተስፋን የሚያስጭር ዘገባ አስደምጣለች

 

 

በዲፕሎማሲ ዘርፉ  በምስራቅ አፍሪካ በመካከለኛው ምስራቅ እና በአፍሪካዊ ጉዳዮች የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ግንኙነት ለአህጉሯ የእድገት በር ከፋች የሆነውን የአፍሪካን ጥቅም የማስከበርና የአፍሪካን ጉዳይ ለአፍሪካዊያን የመስጠት ጅማሮ አንድም በዲፕሎማሲያዊ አንድም ፖለቲካዊ፣ አንድም ኢኮኖሚያዊ በነበረው    የእንድምታ መንገድ ሁሉ ሰላማዊትና ማይኳ አብረው ቆይተዋል።  ብዙ መረጃዎችን በጠንካራ ማስረጃ እያደገፈች ከዜና ዘጋቢነት እስከ አቅራቢነት ከፕሮግራም አዘጋጅነት እስከ ኤዲተርነት ድረስ በብቃት ሰርታለች።

 

በመገናኛ ብዙሃን የቅርብ የሥራ ባልደረባዋ የነበረው ጋዜጠኛ ፍትሕአወቅ ወንድወሰን

ስለወጣቷ የበፊት መምህር የበኋላ ጋዜጠኛ የአሁኗ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ሀላፊ

ሰላማዊት ካሳ ለተወዳጅ ሚዲያ እንዲህ ይላል... " ሰላማዊት ሙያዋን አክብራ በፍቅር የምትሰራ ጎበዝ ጋዜጠኛ ነች። ሥራዋን በቅድሚያ በፍላጎት የምትጀምር ጥናት ላይ በማተኮር  በእያንዳንዱ ርዕሰ- ጉዳይ ላይ   በማንበብ ጊዜዋን የምታጠፋ  በቡድን ስራ የምታምን ሥራዎቿን ከኤዲተሯ ባለፈ ለሌሎች የሥራ ጓዶቿ በማሳየት ተጨማሪ የሆነ ሀሳብን በግብአትነት ለመውሰድ በቀናኢነት የምትሰራ ትልቅ የሚዲያ ባለሙያ ነች።"

 

 በሀገራችን ኢትዮጵያ  የተለመደው ሚዲያውን በማያውቁ ግለሰቦች ማስመራት የነበረ ሲሆን አሁን ግን ሚዲያውን ከሪፖርተርነት ጀምራ እስከ ሀላፊነት ድረስ በእውቀት የዳበረ ልምድ ባካበተችው የሚዲያ ባለሙያ ሴት ጋዜጠኛ መመራቱ ለሚዲያውም ሆነ ለሀገሪቱ ጋዜጠኞች ትልቅ ዕድል ነው። ይህ ሲሆን ምናልባትም ሙያው እራሱን ችሎ በሁለት እግሩ እንዲቆም ለማገዝ የራሱ ሚና ይኖረዋል። በተጨማሪም በዘርፉ ብዙ ሰላማዊቶችን ለማፍራት ያግዛል።








 

   ሰላማዊት በፋና

በ ሁለት ሺህ ዘጠኝ (2009) ዓ.ም  ከኢትዮጵያ የሬዲዮና ቴሌቪዥን ወደፋና ብሮድካስት ያመራችሁ ጋዜጠኛ ሰላማዊት ካሳ በአጭር ጊዜ ውስጥ ስራውን በመላመድ የራሷን አሻራ ማስቀመጥ ችላለች። በኋላም ፋና ቴሌቪዥን ሲቋቋም ከመስራቾቹ ተርታ በመሰለፍ ቴሌቪዥኑ ሥሩ እንዲጠና ሥራው እንዲቃና ተግታለች።  በተለይም በኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች ላይ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ በመንቀሳቀስ በርካታ የትንታኔ ዘገባዎችን ፣ ፕሮግራሞችና የቀጥታ ስርጭት መረጃዎችን አጋርታለች።

በተለይም ሁለት ሺህ አሥር (2010) ዓ.ም ላይ በነበረው የሽግግር ለውጥ ወይንም የለውጥ መንግሥት ምስረታ ሂደትን እጅግ ጥንቃቄና ቅልጥፍናን ይጠይቅ በነበረውን ወቅታዊ ጉዳይ ከዘገቡት ድንቅ ጋዜጠኞች መካከል ሰላማዊት ካሳ ትጠቀሳለች። ለውጡ  አጠቃላይ በሀገሪቱና በህዝቡ ላይ የፈጠረውን ድባብ እና መንግሥት በተከታታይ ያሳያቸው የነበሩትን የለውጥ እጥፋቶች በንቃት ተከታትላ መረጃውን ለህዝብ ስታደርስ ቆይታለች።

 የአፍሪካ ቻይና ሪፎርምን እና በተለይም ደግሞ ለውጡን ተከትሎ የመጣው የዶክተር አብይ የኖቤል ሽልማት መንስኤ የነበረውን የኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት በአራቱም አቅጣጫ በየቀኑ በመንቀሳቀስ  በፍጥነት መላ አካላቷን ዓይንና ጆሮ በማድረግ ወቅታዊ ሂደቱን ከአዲስአበባ እስከ አሥመራ ተጉዛ አዲስና ትኩስ የሆኑ ዘገባዎችን በቀጥታ ስርጭት ጭምር ዘግባለች። በሀገራት መካከልም ሆነ የሀገራት መሪዎች በየግላቸው ስለሚያራምዱት ፖለቲካ እና በጥቅሉ ስለፖለቲካ ያላት ግንዛቤ በበርካታ አጣብቂኞች ውስጥ ያለውን ፍትጊያ በቀላሉ አልፋ እንድትወጣ አስችሏታል። ይህች እንስት ጋዜጠኛ በሰራችባቸው መገናኛ ብዙሃን ጣቢያዎችና ሥራዎቿ ለበርካቶች ምሳሌ መሆን የምትችል ናት፡፡

 

ጋዜጠኛ ሰላማዊት ካሳ እንደ ገፀ-ሰቧ ሁሉ ገፀ-ነፍሷም እጅግ ባማረ ሁኔታ የተገነባ በመልካም ስብእና የተሞላ ነው። ምንምኳ ሁሉም ሰው ሀገሬን እወዳለሁ ቢልም ሰላማዊት ግን ሀገር ወዳድነቷን የምታንፀባርቀው በምግባሯና በስራዋ ጭምር እንደሆነ  ጓደኞቿና የሥራ ባልደረቦቿ አፋቸውን ሞልተው ይመሰክሩላታል።

 

 ሰላማዊት በየጊዜው እራሷን በአዳዲስ እውቀት የምታድስ ናት፡፡ ስራዋን የምታከብርና ቅድሚያ መስጠት ያለባትን ጉዳይ  ጠንቅቃ የምታውቅ ናት፡፡    ፕሮግራሞቿን በምታቀርብበት እና ወቅታዊ የሆኑ ጉዳዮችን ዜናና ትንታኔ በምትሰራበት ጊዜ የምትጠቀማቸው ቃላት የሰላምን ቅድመ ዝግጅት እና የቋንቋ ብስለት እንዲሁም ለጉዳዩ ያላትን እውቀት ያሳያል። ሰላማዊት ካሳ በቴሌቪዥን መስኮት ፊትለፊት ከሚታየው ማንነቷ  ጀርባ ደግሞ ተጫዋች ፣ ቀልድ ፣ አዋቂ ቁምነገረኛ ፣ የወደደችውን የምታጋራ ለቤተሰቧም በዙሪያዋ ላሉት ሁሉ አቅም የምትሆን በቅርበት ሲያዋዩዋት በጣም አድማጭና በጉዳዩ ልክ የተሰፋ ምክር የምታጎናጽፍ ጠንካራ ባለሙያና ጓደኛ ሴት ነች። ሰላማዊት ሙዚቃ አፍቃሪና አንጎራጓሪም ነች።

 












     ሚንስትር ዴኤታዋ ሰላማዊት  

 

ወጣቷ ጋዜጠኛ ሰላማዊት ካሳ በመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ በቆየችባቸው ጊዜያት ከአሥርት ዓመታት በላይ በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጭ በመንቀሳቀስ አገልግላለች። ይሁን እንጂ ሀገሬን በዚህ ብቻ ማገልገል አልችልም ከድሀ ማህበረሰብ እንደመውጣቴ መጠን በእኔ ዕድሜና በእኔ ትውልድ ያሉትን ዜጎች ድምፅ በምክርቤት ደረጃ ማሰማት እና ጥያቄያቸውን ማንሳት እፈልጋለሁ፤ አሜሪካን ግቢ የፈረሰ ቢሆንም  ኗሪዎቹ ቦታ ቀየሩ እንጂ የድህነትን ለምድ አላወለቁም፤ ጋዜጠኝነት የቱንም ያህል ህልሜ ቢሆን ዓላማዬን ለማሳካትና ለመወሰን እንዲሁም ጉዳዮችን በጥልቀት ለማወቅ አያስችለኝም በማለት በምርጫ ተወዳድራ ለአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ተመርጣለች። ቀጥሎም ዳግም ለተቋቋመው የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በሚኒስትር ዲኤታነት ተሹማለች።

   ሰላማዊት ካሳ ፣ ሚኒስትር ዴኤታ ሆና ከተሾመች በኋላ በወቅታዊ የሀገራችን ሁኔታ ላይ መግለጫ በመስጠት የተጣለባትን ትልቅ ሀገራዊ አደራ ለመወጣት ሞክራለች፡፡ ለአልጀዚራ፤ ለቢቢሲ፤ለስካይ ኒውስ መግለጫዎችን ሰጥታለች፡፡ ልምድና እውቀቷንም ለማካተት ጥራለች፡፡

 

የአዲስአበባ ተወላጆች የፖለቲካ ተሳትፎ እጅግ ውስን ነው ተብሎ በሚነገርበት ወቅት የ31 ዓመቷ ወጣት ሴት ፖለቲካውን ከባህሩ ገብታበታለች። ወጣት ሰላማዊት አሁንም ከመገናኛ ብዙሃን ብዙ አለመራቋ ምንም እንኳን አልሸሹም ዘወር አሉ ቢያስመስልባት ነገርግን በኮሙኒኬሽን ዘርፉ ተጽእኖ መፍጠር የሚያስችላት ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊነት ቦታ ላይ ትገኛለች።

በተለይ ወደ ሃላፊነት የመጣችበት ወቅት ኢትዮጵያ በጦርነትና እሱ ባስከተለው ውስብስብ ፈተና በምትንገላታበት ወቅት ነበርና ጊዜው በጣም ፈታኝም አስጨናቂም እንደነበር ትናገራለች።

 

ወጣቷ ሰላማዊት ካሳ ዓለም ኢትዮጵያን የሚመለከትበት የራሱ የሆነ እይታ ቢኖረውም ነገር ግን በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጪ ካሉ መገናኛ ብዙሃን ጋር በቅርበት የምትሰራ በመሆኑ በቆየችበት የሙያ ዘርፍ ዓለም ሀገራችን ኢትዮጵያን የሚያይበትን መነጽር እንዲቀይር አልያም አውልቆ እንዲጥል ማድረግ የተቋሙና የሁሉም ሃላፊነት መሆኑን ትናገራለች።

 

መረጃን ከጋዜጠኞች የመንፈግና ከመረጃ አቅርቦቱ በኋላ መኮነን ሳይሆን ወቅታዊና መንግሥታዊ መረጃዎችን በቀጥታ በመስጠት የመረጃ እጥረቱ የሚፈጥረውን ችግር መቅረፍ አስፈላጊ በመሆኑ ማህበራዊ ሚድያውንና መገናኛ ብዙሃኑን በማዋሃድ መረጃ እንዴት በፍጥነት ህዝብ ጋር መድረስ እንደሚቻል እንሰራለን ብላለች።

 

የመረጃ ባህልን መቀየር የግድ ሲሆን ጋዜጠኞችን እንደጦር ከመፍራት ይልቅ አስፈላጊና ተጨባጭ መረጃን በመስጠት እንደተቋም ነጥሮ መውጣት ያስፈልጋል ትላለች።

ተቋሙ በሚዲያዎችና በማህበረሰቡ ዘንድ ተአማኒነትን መገንባት እና ፈጣን የሆነ ትክክለኛ መረጃ ማቅረብ ከቻለ ለሚነሱ ጥያቅዎች በፍጥነት ምላሽ የሚሰጥበትን ዘዴ ከተጠቀመ መረጃን ለመፈለግ መሄዱ ቀርቶ መረጃዎች ወደ ተቋሙ እንዲመጡ ማድረግ ይቻላል። ይህም እንደተቋም የሚገጥሙንን ፈተናዎች ለማለፍ ያስችላል ። 

 

አሁን ባለው ወቅታዊ ጉዳይ እንደ ሀገር መረጃን ሚዛን ላይ አስቀምጦና አመዛዝኖ መጓዝ የግድ ይሆናል። የጋዜጠኝነት ሙያ እጅግ ፈታኝ ይሁን እንጂ ከነፈተናው የሚወደድ ስለሆነ አጋዥ ካገኘ ደግሞ ይበልጥ ትልቅ ሥራን ለመስራት ያስችላል። ኢትዮጵያ በጣም ብዙ ብቁና ታታሪ ጋዜጠኞች አሏት፣ እነሱን ማገዝ ደግሞ የኔ ሃላፊነት ነው ትላለች ሙያዊ ግዴታዋን ለመወጣት የቆረጠችው ወጣቷ የስራ ኃላፊ ሰላማዊት ካሳ።

 

ምናልባትም የመረጃ መዘግየት፣ መረጃውን ለሁሉም እኩል የማዳረስ፣ ተጽእኖ መፍጠር፣ ሁሉንም ጥያቄዎች የማስተናገድ አቅም ፣ ኃላፊነትን መወጣት መቻል ወደፊት ለሰላማዊትና ለምትመራው ተቋም ወሳኝ የቤት ሥራዎች ሲሆኑ አመርቂ ውጤት ለማስመዝገብ የሚስችሉም ናቸው። መረጃ አንድን ሀገር የማፍረስም ሆነ የመስራት ሀይል ያለው በመሆኑ ጥንቃቄ የተሞላ እና ወቅታዊ የሆነ የመረጃ ፍሰት መኖሩ አግባብ ነው ብላ ታምናለች።

 

ከአዲስ አበባ አሜሪካን ጊቢ የተገኘችው ሰላማዊት ካሳ ዛሬ የብዙዎች ድምፅ ለመሆንና ውሳኔዎችን ለማሳለፍ በሚያስችላት አቋም እና የመንግሥት ኃላፊነት ቦታ ላይ ትገኛለች።

 

ወጣቷ የመንግሥት የስራ ኃላፊ ሰላማዊት ካሳ ጋዜጠኛ የመሆን ፍላጎት በወላጅ እናቷ የተጠነሰሰ  ሲሆን በልጅቷ ስጋ ለብሶ ለመገለጥ ችሏል። የጥንካሬ ምንጬ እናቴ ናት የምትለው ሰላማዊት እናቷ በዛ አስቸጋሪ ሁኔታ ብቻቸውን ስላሳደጓትና ዛሬ ላለችበት ማንነት ስላበቋት በቃላት ሊገለጽ የማይችል ፍቅርና አክብሮት ከመስጠትና ከፈጣሪ ዘንድ እድሜና ጤናን ከመለመን ውጪ ለእናቴ እልፍ ውለታ ምንም ባደርግ፣ ምንም ብናገር፣ ምንም ያህል ባመሰግናት አይበቃኝም ትላለች።

 

እናቷ በልጃቸው ደስታ እሳቸው እየለመለሙ አድረው ወጣት እየሆኑ ህይወትን ይበልጥ እያጣጣሙ ለልጃቸው ስኬት በመፀለይና አቅማቸው በፈቀደ መጠን በማገዝ ለልጃቸው መበርታት የበኩላቸውን ይወጣሉ። ምንም እንኳ ኃላፊነት ያለባት ሴት ብትሆንም የቤተሰብ እገዛ ያልተለያት በመሆኑ በጣም እድለኛ መሆኗንና ከስራዋም ቅንጣት ዝንፍ እንደማትል ትናገራለች።

 

ወጣቷ የሥራ ኃላፊ ሰላማዊት ካሳ የአንድ ልጅ እናት ስትሆን ባለባት ኃላፊነት እና የሥራ ጫና ምክንያት ልጄ እንዳትረሳኝ ስል ብቻ እሰጋለሁ ትላለች።

ይሁን እንጂ እሷ ዛሬ ያገኘችውን እድል በቀላሉ እንደማታየውና ቢያንስ ለራሷም የማያሳፍራትን፣ ልጇንም የሚያኮራ ለሃገሯም የሚጠቅም ስራ ለመስራት የተሰጣትን ሃላፊነት በጥንቃቄ ለመወጣት ዝግጁ መሆኗን ተናግራለች።

 

በመጨረሻም ይህች ጠንካራ ወጣት ይኸም አልበቃትምና ወደፊት በሀገሯ ብዙ ሰዎችን ማገዝ የሚችል የግሏ የሆነ ተቋም የመመስረት ህልም እንደሰነቀች ጠቆም አድርጋለች

 

 

 

 

የመዝጊያ ሀሳብ ፤ ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የኢንሳይክሎፒዲያ ቦርድ አባላት አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡

ሰላማዊት ካሳ በውልደቷ ከአዲስአበባ  የተገኘች በሥራ ግብሯ ከመምህርነት ሙያ ጀምራ እስከ ጋዜጠኝነት አሥር አመት ገደማ አገልግላ አሁን ደግሞ በከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊነት ደረጃ ላይ ለመቀመጥ የቻለች ትጉህ ሥራ ወዳድ መሪ ጋዜጠኛ ነች ብንል በእርግጥም አላገነንነውም። ምክንያቱም ደግሞ የሀገራችን ፖለቲካ አይደለም ለሴት ቀርቶ ለወንድ ልጅ ያልተመቼ ብዙዎችን ለእስርና ለእንግልት የሚዳርግ ሆኖ ሳለ ነገርግን በሰላማዊት መዘወር በመቻሉ ነው።

ምንምኳን ኢትዮጵያ በቀደመ ታሪኳ ፖለቲካውን የሚዘውሩ ከወንዶች የላቀ ሚና የነበራች እና ሀገርን የሚመሩ በርካታ ሴቶችን አፍርታ እንደነበረ  ቢታወስም ጥርስ በሚያናክሰው የመገናኛ ብዙሃን ኮሙኒኬሽን ሚንስትር ደኤታነት ግን ሰላም አንዷ ነች። 

 

ይሁንእንጂ ታዲያ ሰላማዊትም ፆታና የሥራ ግብር ለየቅል መሆኑን በእንቅስቃሴዋ   ያስመሰከረች ሲሆን በተለይም ለወጣት ሴት የሚዲያ ባለሙያዎች ሙሉ የራስ መተማመን እንዲኖራቸው አይቻልምን ግንብ ደምስሰው በፈለጉበት ከፍታ ላይ መቆም እንደሚችሉ በድጋሚ አስታውሳለች። ሆናም አሳይታለች። ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን አቅም ያላቸው የሰሩ ሰዎች ታሪካቸው ይሰነድ ብሎ ይህን ራእይ እውን ሲያደርግ እንደሰላማዊት አይነት በወጣነታቸው ተምሳሌት የሆኑ ሰዎችን ብዙ ልምድ ሊያስቀስሙ እንደሚችሉ ስለሚያምን ነው፡፡ በተጨማሪም በሚድያውም ሆነ በሌላው ዘርፍ  አንድ አሻራ ያኖሩ ሰዎች  ጉልህ አስተዋጽኦዋቸው ሳይረሳ ለአዲሱ ትውልድ ታሪካቸው እንዲቀመጥ በማሰብ ነው፡፡ ሰላማዊትም ከ2000 በኋላ ሚድያው ካፈራቸው አንዷ ነችና ያለፈችበትን መንገድ ለማሳወቅ ከላይ የተቀመጠውን ታሪክ ሰንደን አስቀምጠናል፡፡ /ይህ ጽሁፍ በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉና በባንቺአየሁ አሰፋ ተሰናዳ፡፡ ይህን ጽሁፍ ስናሰናዳ በቂ መረጃ እና ምስክርነት በመስጠት ትብብር ላሳዩን ለጋዜጠኛ ፍትህአወቅ የወንድወሰን ፤ ጋዜጠኛ አላዛር ታደለ ፤ ለጋዜጠኛ ህሊና መስቀሉ የከበረ ምስጋናችንን ማቅረብ እንወዳለን፡፡ /

 






 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች